ውዳሴ ነው ወይስ ሽንገላ?
አንድ ሰው “ይህ አበጣጠር በጣም ያምርብሃል!” ይላችኋል። ውዳሴ ነው ወይስ ሽንገላ? “ይኸኛው ልብስ እላይህ ላይ የተሰፋ እኮ ነው የሚመስለው!” ውዳሴ ወይስ ሽንገላ? “በሕይወቴ እንደዚህ የሚጣፍጥ ምግብ በልቼ አላውቅም!” ውዳሴ ነው ወይስ ሽንገላ? እንደነዚህ ዓይነት የአድናቆት መግለጫዎችን ስንሰማ በእርግጥ ከልብ የመነጩና እውነተኛ ናቸው ወይስ ተናጋሪው ሳያምንባቸው እንዲሁ እኛን ለማስደሰት ብቻ የተናገራቸው ብለን እናስብ ይሆናል።
አንድ ሰው የሚነግረን ነገር ውዳሴ ይሁን ወይም ሽንገላ እንዴት ማወቅ እንችላለን? የፈለገውን ቢናገር ምን ለውጥ ያመጣል? እኛ ምን አመራመረን፤ የተናገረውን እንዲሁ ተቀብለን አንደሰትም? እኛስ ሌሎችን ስናወድስ እንዴት ነው? ሌሎችን ስናወድስ ውስጣዊ ዝንባሌያችንን መርምረን እናውቃለን? በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን አስተዋዮች እንድንሆን የሚረዳን ከመሆኑም በላይ አንደበታችንን ለይሖዋ አምላክ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ እንድንጠቀምበት ያስችለናል።
የውዳሴና የሽንገላ ትርጉም
የዌብስተር መዝገበ ቃላት ውዳሴ ተብሎ የተተረጎመውን ፕሬይዝ የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የድጋፍ መግለጫ ወይም ምስጋና በማለት የሚፈታው ሲሆን ቃሉ አምልኮን ወይም ክብር መስጠትን ሊያመለክትም ይችላል። የኋለኞቹ ሁለት ፍችዎች ለይሖዋ አምላክ ብቻ የሚቀርበውን ውዳሴ እንደሚያመለክቱ ግልጽ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው መዝሙራዊ “መልካም ነውና። . . . ምስጋና ያማረ ነው”፤ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን” በማለት አበክሮ እንደገለጸው ለይሖዋ ምስጋና ማቅረብ የእውነተኛው አምልኮ ቋሚ ክፍል ነው።—መዝሙር 147:1፤ 150:6
እንዲህ ሲባል ግን ሰዎችን ማወደስ አይቻልም ማለት አይደለም። ድጋፍን በመግለጽ በማመስገን ወይም ጥሩ ግምት እንዳለን በመግለጽ ሰዎችን ማወደስ ይቻላል። ኢየሱስ በሰጠው ምሳሌ ውስጥ ጌታው አገልጋዩን “መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ” ብሎታል!—ማቴዎስ 25:21
በሌላ በኩል ደግሞ ሽንገላ ተብሎ የተተረጎመው ፍላተሪ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ውሸት፣ ልባዊ ያልሆነ ወይም የተጋነነ ውዳሴ የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። የሽንገላ ቃላት የሚናገረው ሰው ብዙውን ጊዜ ስውር የሆነ የራስ ወዳድነት ዝንባሌ አለው። ከሌላ ሰው ሙገሳ ወይም ቁሳዊ ጥቅሞችን ለማግኘት ወይም ሸንጋዩ ሌሎችን የእርሱ ተገዥ ለማድረግ ሲፈልግ በዘዴ ያሞካሻቸዋል ወይም ከልክ ያለፈ አድናቆት ይቸራቸዋል። ስለዚህ የሽንገላ ቃላት የሚናገሩ ሰዎች ውስጣዊ ግፊታቸው ራስ ወዳድነት ነው። በይሁዳ 16 መሠረት እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች “የሆነ ጥቅም ሲያዩ ሰዎችን በቃላት ይሸነግላሉ።”—ዘ ጀሩሳሌም ባይብል
ቅዱስ ጽሑፋዊው አመለካከት
ሰዎችን ስለማወደስ ቅዱስ ጽሑፉ ምን ይላል? ይሖዋ በዚህ ረገድ ልንከተለው የምንችለውን ምሳሌ ይነግረናል። የይሖዋን ፈቃድ ካደረግን እንደምንወደስ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ከአምላክ ዘንድ ውዳሴ ይቀበላል” በማለት ተናግሯል። ጴጥሮስ የተፈተነ እምነታችን ‘ውዳሴ ሊያስገኝልን እንደሚችል’ ተናግሯል። ይሖዋ ሰዎችን እንደሚያመሰግን የሚገልጸው ሐቅ እውነተኛ ምስጋና መስጠት ደግነት ያለበት፣ ፍቅራዊና ጠቃሚ የሆነ ድርጊት ስለሆነ ችላ ሊባል የማይገባ ነገር እንደሆነ ያሳያል።—1 ቆሮንቶስ 4:5 NW፤ 1 ጴጥሮስ 1:7 NW
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው መልካም ባሕርያችንን አስተውለው በሐቀኝነት ከሚያመሰግኑን የመንግሥት ባለሥልጣኖችም ውዳሴ ልንቀበል እንችላለን። “መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል” ተብሎ ተነግሮናል። (ሮሜ 13:3) ከዚህም በተጨማሪ የሚናገሩትን ነገር ከልብ ከሚያምኑበትና እኛን በማመስገን ከበስተኋላ ምንም የተለየ ዓላማ ከሌላቸው ሰዎች ምስጋና ልናገኝ እንችላለን። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች በምሳሌ 27:2 NW ላይ “ሌላ ያወድስህ እንጂ የገዛ አንደበትህ አይደለም” በማለት ይገልጻሉ። ይህ ከሰዎች ውዳሴ መቀበል ተገቢ መሆኑን ያሳያል።
ሆኖም ሌሎችን መሸንገልም ሆነ በሌሎች መሸንገል ከዚህ የተለየ ነው። የሽንገላ ንግግር ይሖዋን የማያስደስተው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ሽንገላ ከልብ የመነጨ አይደለም፤ ይሖዋ ደግሞ ከልብ ያልመነጨ ነገር አይወድም። (ከምሳሌ 23:6, 7 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ ደግሞ ሰውን መሸንገል ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ነው። መዝሙራዊው በአምላክ ዘንድ ጨርሶ ተቀባይነት ስለሌላቸው ሰዎች ሲናገር “እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ። የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል” ብሏል።—መዝሙር 12:2, 3
ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ሰውን መሸንገል ፍቅር የጎደለው ተግባር ነው። በራስ ወዳድነት ግፊት የሚነገር ነው። መዝሙራዊው ሸንጋይ ስለሆኑ ሰዎች ከተናገረ በኋላ እንዲህ ሲል የሚናገሩትን ጠቅሷል:- “በመናገራችን የፈለግነውን እናገኛለን፤ እንደ ፈቀድን እንናገራለን፤ ከእኛ በላይ ሆኖ ሊከለክለን የሚችል ማን ነው?” ይሖዋ እንደዚህ የመሰሉትን ራስ ወዳድ ሰዎች ‘ችግረኞችን የሚያራቁቱ’ በማለት ጠርቷቸዋል። ሸንጋይ ምላሳቸው የሚያገለግለው ሌሎችን ለማነጽ ሳይሆን ሌሎችን ለማራቆትና ለማጥቃት ነው።—መዝሙር 12:4, 5 የ1980 ትርጉም
ሽንገላ ወጥመድ ነው
“ወዳጆችህን የምታቆላምጥ [“የምትሸነግል፣” NW] ከሆነ ለራስህ ወጥመድ ትዘረጋለህ” በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን የተናገራቸው ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! (ምሳሌ 29:5) ፈሪሳውያን ኢየሱስን በመሸንገል ወጥመድ ሊዘረጉበት ሞክረው ነበር። “መምህር ሆይ፣ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፣ ለማንምም አታደላም፣ የሰውን ፊት አትመለከትምና” አሉት። እንዴት ያለ ልብ የሚሰርቅ አባባል ነው! ሆኖም ኢየሱስ በለዘበ አነጋገራቸው አልተታለለም። የእርሱን የእውነት ትምህርት እንዳላመኑ ያውቅ ነበር። እነርሱ ጥረት ያደረጉት ለቄሣር ግብር ስለ መክፈል በተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ላይ በሚናገረው ነገር ለመወንጀል ነበር።—ማቴዎስ 22:15-22
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ንጉሥ የነበረው ሄሮድስ ከኢየሱስ ፈጽሞ የተለየ አቋም ወስዷል። በቂሣርያ ከተማ ለሕዝቡ ንግግር ባደረገበት ጊዜ ተሰብስቦ የነበረው ሕዝብ “የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም” ብለው ምላሽ ሰጡ። ሄሮድስ ድፍረት ለተሞላበት ለእንዲህ ዓይነቱ የሐሰት ውዳሴ ሰዎቹን ከመገሠጽ ይልቅ ሽንገላቸውን ተቀበለ። የይሖዋ መልአክ ሄሮድስ በትል ተበልቶ እንዲሞት በማድረግ ቅጽበታዊ የሆነ የበቀል እርምጃ ወስዷል።—ሥራ 12:21-23
አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ሽንገላው ለምን ዓላማ እንደተነገረ ለማስተዋል ንቁ ነው። በተለይ ጉዳዩ በፍርድ ኮሚቴ እየታየ ያለ አንድ ሰው የአድናቆት ቃላትን የሚያዥጎደጉድ ከሆነ የጉባኤ ሽማግሌዎች ነገሩን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ይኖርባቸዋል። ይህ ግለሰብ ከእገሌ ይልቅ አንተ እኮ ደግና የሰው ችግር የሚገባህ ነህ እያለ ለአንዱ ሽማግሌ በመንገር አንዱን ሽማግሌ ከሌላው ሽማግሌ እስከማወዳደር ሊደርስ ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወጣት በአንዲት አሳች ሴት አነጋገር ተስቦ እንዴት ወደ ብልግና ሊያመራ እንደሚችል በመግለጽ ሽንገላ ሊያስከትል የሚችለውን ሌላ አደጋ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጧል። (ምሳሌ 7:5, 21) ይህ ማስጠንቀቂያ ዛሬ ላለው ሁኔታም በሚገባ ይሠራል። በየዓመቱ ከክርስቲያን ጉባኤ ከሚወገዱት ውስጥ አብዛኛዎቹ በብልግና ድርጊት ምክንያት የሚወገዱ ናቸው። ይህን የመሰለው ከባድ ኃጢአት በሽንገላ ጀምሮ ይሆን? ሰዎች ሲወደሱና ሲደነቁ መስማት በጣም ስለሚያስደስታቸው ሸንጋይ ከሆኑ ከንፈሮች የሚወጣው የለዘበ ቃል አንድ ክርስቲያን ተገቢ ያልሆነን ድርጊት ለመቋቋም ያለውን ኃይል ሊያዳክምበት ይችላል። እንዲህ ካሉት ከለዘቡ የሽንገላ ቃላት ራሳችንን ካልጠበቅን አስከፊ ውጤት ወደሚያስከትል ሁኔታ ሊመራን ይችላል።
ሽንገላን መከላከል
ሽንገላ፣ የተሸነገለው ሰው ለራሱ ያለውን ግምት ወይም ራሱን ከፍ አድርጎ እንዲመለከት ያደርገዋል። ሽንገላ አንድ ሰው ስለራሱ ዋጋማነት የተጋነነ አመለካከት እንዲኖረውና በሆነ መንገድ ከሌሎች የሚልቅ እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። ፍራንስዋ ደ ላ ሮሽፎኮል የተባሉት ፈላስፋ ሽንገላን ከሐሰት የብር ኖት ጋር በማመሳሰል “ሁለቱም ከንቱ ስሜት ከማሳደር አልፈው የሚፈይዱት ነገር የለም” በማለት ተናግረዋል። በመሆኑም ራስን ከሽንገላ መከላከል የሚቻለው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ራስን ዝቅ ማድረግን አስመልክቶ እንዲህ በማለት የሰጠውን ምክር በመከተል ነው:- “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፣ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ።”—ሮሜ 12:3
ምንም እንኳ ተፈጥሮአዊ ዝንባሌያችን ለጆሮአችን የሚጥም ነገር መስማት ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ በጣም የሚያስፈልገን ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክርና ተግሳጽ ነው። (ምሳሌ 16:25) ንጉሥ አክዓብ መስማት የፈለገው የሚያስደስተውን ነገር ብቻ ነበር። እንዲያውም የእርሱ አገልጋዮች ነቢዩ ሚክያስ የሚናገረው ቃል “እንደ ቃላቸው እንዲሆን [ሸንጋይ እንደሆኑት የአክዓብ ነቢያት] መልካም እንድትናገር” በማለት አስጠንቅቀውታል። (1 ነገሥት 22:13) አክዓብ በግልጽ የተነገረውን ነገር ለመስማት ፈቃደኛ ቢሆንና የዓመፀኝነት መንገዱን ቢተው ኖሮ በእስራኤል ላይ የደረሱትን አስከፊ የጦርነት ሽንፈቶች ማስቀረትና ሕይወቱንም ከሞት ማትረፍ በቻለ ነበር። በሽንገላ ንግግር ጆሯችንን በመኮርኮር በጣም ጥሩ ሰዎች መሆናችንን የሚነግሩንን ሰዎች ከመፈለግ ይልቅ የተሾሙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ቀና በሆነው የእውነት መንገድ መሄዳችንን እንድንቀጥል ለመርዳት በማሰብ ጥብቅ፣ ሆኖም ፍቅራዊ ምክር ሲሰጡን ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን ስንል ምላሽ ለመስጠት ፈጣኖች መሆን አለብን!—ከ2 ጢሞቴዎስ 4:3 ጋር አወዳድር።
ክርስቲያኖች በምንም ዓይነት ወደ ሽንገላ ዘወር ለማለት በጭራሽ አይፈልጉም። ታማኝ እንደነበረው ኤሊሁ እነርሱም በቁርጠኝነት እንዲህ በማለት ይጸልያሉ:- “ለሰው ፊት ግን አላደላም፤ ሰውንም አላቆላምጥም [“አልሸነግልም፣” NW]። በማቆላመጥ [“በሽንገላ፣” NW] እናገር ዘንድ አላውቅምና፤ ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ከሕይወቴ ይለየኝ ነበር።” እንዲህ ካደረጉ ልክ እንደ ጳውሎስ “እያቈላመጥን [“በሽንገላ ቃላት፣” NW] ከቶ አልተናገርንም፣ . . . እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም” ብለው ለመናገር ይችላሉ።—ኢዮብ 32:21, 22፤ 1 ተሰሎንቄ 2:5, 6
ተገቢ ሆኖ ሲገኝ አመስግኑ
በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ምሳሌ ውዳሴ እንደ መመዘኛ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ብር በከውር ወርቅም በማቅለጫ ይፈተናል፤ ሰውም በሚያመሰግኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል።” (ምሳሌ 27:21) አዎን፣ ውዳሴ የበላይነትን ወይም የኩራትን ስሜት ሊያሳድር ይችላል፤ ይህ ደግሞ የአንድን ሰው ውድቀት ያስከትላል። በሌላ በኩል ደግሞ የተወደሰው ግለሰብ እንዲወደስ ላደረገው ማንኛውም የሥራ ክንውን ተመስጋኙ ይሖዋ መሆኑን ከገለጸ ቦታውን የሚያውቅና ትሑት መሆኑን ሊያሳይ ይችላል።
ጥሩ ለሆነ ጠባይ ወይም የሥራ ክንውን የሚነገር ትክክለኛ ውዳሴ የሚያወድሰውንም ሆነ የሚወደሰውን ግለሰብ ያንጻል። አንዱ ለሌላው ሞቅ ያለና ንጹሕ የሆነ አድናቆት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደርጋል። የሚያስመሰግኑ ግቦችን ለመከታተል ሊያበረታታ ይችላል። ምስጋና ለሚገባቸው ወጣቶች ምስጋና መስጠት ጠንክሮ የመሥራት ፍላጎት ሊቀሰቅስባቸው ይችላል። ከሚጠበቅባቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው ለመኖር ግብ በሚያደርጉበት ጊዜ ባሕርያቸውን ለመቅረጽ ሊረዳ ይችላል።
ስለዚህ ሰጪም ሆንን ተቀባይ ሽንገላን እናስወግድ። ሰዎች ሲያወድሱን ኩራት አይሰማን። በአምልኮታችን ይሖዋን በደስታና በሙሉ ነፍስ ዘወትር እናወድስ። በተጨማሪም ‘በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል መልካም’ እንደሆነ በማስታወስ በትክክለኛ የአመስጋኝነትና የአድናቆት መንፈስ ሌሎችን ከልብ የምናወድስ እንሁን!—ምሳሌ 15:23