ምዕራፍ 10
“የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋ ሄደ”
ጴጥሮስ ከእስር ነፃ ወጣ፤ ስደት ምሥራቹ እንዳይስፋፋ ማገድ አልቻለም
በሐዋርያት ሥራ 12:1-25 ላይ የተመሠረተ
1-4. ጴጥሮስ ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠመው? አንተ በእሱ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር?
ግዙፍ የሆኑት የብረት በሮች ከጴጥሮስ ኋላ ጓ ብለው ተዘጉ። ጴጥሮስ ከሁለት ወታደሮች ጋር በሰንሰለት እንደተቆራኘ ወደሚታሰርበት ክፍል ተወሰደ። መጨረሻው ምን ይሆን? ጴጥሮስ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፤ ፍርዱን የሚሰማው ከብዙ ሰዓታት ምናልባትም ከቀናት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ነው። ወዲያ ወዲህ ቢያማትር ዓይኑ የሚያርፍበት ነገር የለም፤ የታሰረበት ክፍል ግድግዳና በር ዙሪያውን ከብቦታል፤ ከእጁ ሰንሰለትና ከሚጠብቁት ወታደሮች በቀር ምንም የሚታይ ነገር የለም።
2 በመጨረሻም ጴጥሮስ ከባድ ቅጣት እንደተወሰነበት ሰማ። ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ቀዳማዊ፣ ጴጥሮስን ለማስገደል ቆርጦ ተነስቷል።a እንዲያውም ከፋሲካ በዓል በኋላ ይህን ለማድረግ አስቧል፤ በጴጥሮስ ላይ የሞት ብይን በማስተላለፍ ሕዝቡን ማስደሰት ፈልጓል። ይህ እንዲያው ተራ ዛቻ አልነበረም። ከጴጥሮስ ጋር ከሚያገለግሉት ሐዋርያት አንዱ የሆነው ያዕቆብ በቅርቡ በዚሁ ገዢ ተገድሏል።
3 ጴጥሮስ ብቻውን ጨለማ ክፍል ውስጥ እንደታሰረ ነው፤ በቀጣዩ ቀን ሞት ተደግሶለታል። በዚያች ምሽት ምን እያሰበ ይሆን? ከዓመታት በፊት ኢየሱስ ስለ እሱ የተናገረው ነገር ትዝ ብሎት ይሆን? አንድ ቀን እንደሚታሰርና ወደማይፈልግበት ቦታ ይኸውም ወደ ሞት እንደሚወሰድ ነግሮት ነበር። (ዮሐ. 21:18, 19) ምናልባት ጴጥሮስ ያ ጊዜ እንደደረሰ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል።
4 አንተ በጴጥሮስ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? ብዙዎች ሁኔታው ምንም ተስፋ እንደሌለው በማሰብ በጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ። ይሁንና ለአንድ እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ጨርሶ ተስፋ የሌለው ሁኔታ ሊኖር ይችላል? ጴጥሮስና ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ስደት ሲደርስባቸው ከወሰዱት እርምጃ ምን እንማራለን? እስቲ እንመልከት።
“ጉባኤው . . . አጥብቆ ይጸልይ ነበር” (የሐዋርያት ሥራ 12:1-5)
5, 6. (ሀ) ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ጥቃት የሰነዘረው ለምንና እንዴት ነበር? (ለ) የያዕቆብ መሞት ለጉባኤው ከባድ ፈተና የነበረው ለምንድን ነው?
5 ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ከአሕዛብ ወገን የሆነው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ክርስትናን መቀበላቸው ለክርስቲያን ጉባኤ ወሳኝ ምዕራፍ ነበር። ክርስትናን ያልተቀበሉ አይሁዳውያን ግን ይህ ሳያበሳጫቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከአሕዛብ ከመጡት ጋር በነፃነት ይሖዋን እያመለኩ ነው።
6 ሄሮድስ መሠሪ ፖለቲከኛ ነው፤ የአይሁዳውያንን ተወዳጅነት ለማትረፍ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ በማሰብ ክርስቲያኖችን ማንገላታት ጀመረ። ሐዋርያው ያዕቆብ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በጣም ይቀራረብ እንደነበር ሳያውቅ አይቀርም። በመሆኑም “የዮሐንስን ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው።” (ሥራ 12:2) ይህ ለጉባኤው ከባድ ፈተና ነው! ያዕቆብ የኢየሱስን ተአምራዊ መለወጥ ጨምሮ ሌሎቹ ሐዋርያት ያላዩአቸውን ተአምራት ከተመለከቱት ሦስት ሐዋርያት አንዱ ነበር። (ማቴ. 17:1, 2፤ ማር. 5:37-42) ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበራቸው ኢየሱስ “የነጎድጓድ ልጆች” ሲል ጠርቷቸዋል። (ማር. 3:17) ስለዚህ ጉባኤው ያጣው ደፋር፣ ታማኝ ምሥክርና ተወዳጅ የሆነ ሐዋርያ ነበር።
7, 8. ጴጥሮስ በታሰረበት ጊዜ ጉባኤው ምን አደረገ?
7 አግሪጳ እንዳሰበውም የያዕቆብ መገደል አይሁዳውያኑን አስደሰታቸው። ይህን ሲያይ የልብ ልብ ስለተሰማው ጴጥሮስንም ለመግደል ተነሳሳ። በመሆኑም በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ጴጥሮስን እስር ቤት አስገባው። ይሁንና በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ላይ እንደተጠቀሰው እስር ቤትም እንኳ ሐዋርያቱን ሊገታቸው የማይችልበት ጊዜ አለ፤ አግሪጳ ይህን ሳያስታውስ አይቀርም። ጴጥሮስ ምንም ዓይነት ማምለጫ ቀዳዳ እንዳያገኝ በማሰብ ከ2 ጠባቂዎች ጋር በሰንሰለት እንዲቆራኝ አደረገ፤ እንዲሁም 16 ጠባቂዎች ቀንና ሌሊት እየተፈራረቁ እንዲጠብቁት መደበ። ጴጥሮስ ካመለጠ ጠባቂዎቹ ለእሱ የታሰበውን ቅጣት ይቀበላሉ። እንዲህ ባለው አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮች ምን ያደርጉ ይሆን?
8 ጉባኤው ምን ማድረግ እንዳለበት በሚገባ አውቋል። የሐዋርያት ሥራ 12:5 “ጴጥሮስ እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ፤ ሆኖም ጉባኤው ስለ እሱ ወደ አምላክ አጥብቆ ይጸልይ ነበር” ይላል። አዎ፣ ወንድሞች በጣም ለሚወዱት ወንድማቸው አጥብቀው ይጸልዩ ነበር። የያዕቆብ መገደል ተስፋ አላስቆረጣቸውም፤ ጸሎት ምንም ዋጋ የለውም ብለው እንዲደመድሙም አላደረጋቸውም። ጸሎት በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው። ደግሞም ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል። (ዕብ. 13:18, 19፤ ያዕ. 5:16) ይህ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች ትልቅ ትምህርት ይዟል።
9. ጸሎትን በተመለከተ የጴጥሮስ የእምነት ባልንጀሮች ከተዉት ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?
9 መከራ እየደረሰባቸው ያሉ የምታውቃቸው ክርስቲያኖች አሉ? ለምሳሌ በስደት፣ መንግሥት በጣለው እገዳ ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከባድ ፈተናዎችን በጽናት የሚጋፈጡ አሉ። ታዲያ ስለ እነዚህ ወንድሞች አጥብቀህ ትጸልያለህ? በሌላ በኩል ደግሞ እምብዛም ጎልቶ የማይታይ መከራ ተቋቁመው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ታውቅ ይሆናል፤ ለምሳሌ ከቤተሰብ ችግር፣ ከተስፋ መቁረጥ ወይም እምነትን ከሚፈታተን ሌላ ችግር ጋር እየታገሉ ሊሆን ይችላል። እንግዲያው “ጸሎት ሰሚ” የሆነውን ይሖዋን በምታነጋግርበት ጊዜ በስም ልትጠቅሳቸው የምትፈልጋቸውን በርካታ ሰዎች ማስታወስ እንድትችል ከመጸለይህ በፊት ቆም ብለህ አስብ። (መዝ. 65:2) ደግሞስ አንተ ችግር ላይ ብትወድቅ ወንድሞችህና እህቶችህ እንዲሁ እንዲያደርጉልህ ትፈልግ የለ?
“ተከተለኝ” (የሐዋርያት ሥራ 12:6-11)
10, 11. የይሖዋ መልአክ ጴጥሮስን ከእስር ቤት ነፃ ያወጣው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
10 ጴጥሮስ ከፊቱ የተደቀነው አደጋ አስጨንቆት ነበር? ምን ተሰምቶት እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ ሆኖም በእስር ቤት ባሳለፈው በዚያ የመጨረሻ ሌሊት በንቃት እየጠበቁት ባሉት ሁለት ወታደሮች መካከል ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት ነበር። ይህ የእምነት ሰው ከፊቱ የሚጠብቀው ምንም ይሁን ምን ይሖዋ እንደማይተወው እርግጠኛ ነበር። (ሮም 14:7, 8) ያም ሆኖ ጴጥሮስ በዚያ ሌሊት የተፈጸሙት አስደናቂ ነገሮች ይከሰታሉ ብሎ ሊጠብቅ አይችልም። በታሰረበት ክፍል ውስጥ ድንገት ደማቅ ብርሃን በራ። አንድ መልአክ ጴጥሮስ አጠገብ ቆመና ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው፤ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ጠባቂዎቹ መልአኩን አላዩትም። ጴጥሮስ የታሰረበት የማይበጠስ የሚመስል ሰንሰለት ያለምንም ችግር ከእጆቹ ላይ ወደቀ!
11 መልአኩ ለጴጥሮስ አጠር አጠር ያሉ መመሪያዎች ሰጠው፤ “ቶሎ ብለህ ተነሳ! . . . ልብስህን ልበስ፤ ጫማህንም አድርግ፤ . . . መደረቢያህን ልበስ” አለው። ጴጥሮስ ወዲያው እንደታዘዘው አደረገ። በመጨረሻም መልአኩ “ተከተለኝ” አለው፤ ጴጥሮስም ተከተለው። ከዚያም ከእስር ቤቱ ክፍል ወጡ፤ ውጭ የቆሙትን ዘቦች አልፈው ኮሽታ ሳያሰሙ ወደ ግዙፉ የብረት በር አመሩ። ግን ይህን በር እንዴት ሊያልፉት ነው? ጴጥሮስ ይህ ጥያቄ ተፈጥሮበት ይሆን? ከነበረም አፍታ እንኳ ሳይቆይ መልሱን ሊያገኝ ነው። ወደ በሩ ሲቃረቡ “መዝጊያው . . . በራሱ ተከፈተላቸው።” ጴጥሮስ ምን እየተከናወነ እንዳለ እንኳ በቅጡ ሳይገባው በሩን አልፈው ወደ ጎዳናው ወጡ፤ ከዚያም መልአኩ ተሰወረ። ጴጥሮስ ብቻውን ቀረ፤ ምን እንደተከናወነ የገባው በዚህ ጊዜ ነበር። ራእይ እያየ አልነበረም። ከእስር ቤት ነፃ ወጥቷል!—ሥራ 12:7-11
12. ይሖዋ ጴጥሮስን እንዴት እንዳዳነው ማሰላሰላችን የሚያጽናናን እንዴት ነው?
12 ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይሉን ተጠቅሞ አገልጋዮቹን እንዴት እንደሚታደግ ስናሰላስል እጅግ አንጽናናም? ጴጥሮስን በቁጥጥር ሥር ያዋለው ንጉሥ የዋዛ አልነበረም፤ የዘመኑ እጅግ ኃያል መንግሥት የሾመው ንጉሥ ነው። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ሰተት ብሎ ከእስር ቤት ወጣ! ይህ ሲባል ግን ይሖዋ ሁሉንም አገልጋዮቹን በተአምር ይታደጋቸዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያዕቆብን በዚህ መንገድ አላዳነውም፤ ቆየት ብሎ ደግሞ ጴጥሮስ ራሱም እንዲህ አልተደረገለትም፤ ኢየሱስ እሱን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች ይሖዋ በተአምር ያድነናል ብለው አይጠብቁም። ይሁንና ይሖዋ ዛሬም አልተለወጠም። (ሚል. 3:6) በቅርቡ በልጁ አማካኝነት ሚሊዮኖችን ከማይደፈረው እስር ቤት ይኸውም ከሞት ነፃ ያወጣቸዋል። (ዮሐ. 5:28, 29) ዛሬ የተለያዩ መከራዎች ሲደርሱብን እነዚህ ተስፋዎች ድፍረት ይሰጡናል።
“ሲያዩት በጣም ተገረሙ” (የሐዋርያት ሥራ 12:12-17)
13-15. (ሀ) በማርያም ቤት የተሰበሰቡት ክርስቲያኖች የጴጥሮስን መምጣት ሲሰሙ ምን ተሰማቸው? (ለ) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከዚህ በኋላ በምን ላይ ያተኩራል? ሆኖም ጴጥሮስ በመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ላይ ምን ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሎ መሆን አለበት?
13 ጴጥሮስ ወዴት እንደሚሄድ እያሰበ በጨለማ በተዋጠው አውራ ጎዳና ላይ ቆሟል። ከዚያም ወዴት እንደሚሄድ ወሰነ። በዚያ አካባቢ የምትኖር ማርያም የተባለች አንዲት ክርስቲያን ነበረች። ማርያም ደህና ኑሮ ያላት መበለት ሳትሆን አትቀርም፤ ምክንያቱም ጉባኤው ሊሰበሰብበት የሚችል ሰፋ ያለ ቤት ነበራት። ማርያም የዮሐንስ ማርቆስ እናት ስትሆን እሱም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እዚህ ዘገባ ላይ ነው፤ ማርቆስ ከጊዜ በኋላ ለጴጥሮስ እንደ ልጁ ሆኖለት ነበር። (1 ጴጥ. 5:13) ምሽቱ ገፍቷል፤ ሆኖም ብዙዎቹ የጉባኤው አባላት በማርያም ቤት ተሰብስበው አጥብቀው እየጸለዩ ነበር። ጴጥሮስ ከእስር እንዲፈታ እየጸለዩ እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም ይሖዋ ወዲያው ምላሽ ይሰጠናል ብለው አልጠበቁም!
14 ጴጥሮስ የግቢውን በር አንኳኳ። አንዲት አገልጋይ በሩን ለመክፈት መጣች፤ የዚህች አገልጋይ ስም ሮዳ ሲሆን “ጽጌሬዳ” የሚል ትርጉም ያለው የተለመደ ግሪክኛ ስም ነው። ሮዳ የጴጥሮስን ድምፅ ስትሰማ ጆሮዋን ማመን አቃታት! ከደስታዋ የተነሳ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ ገባች፤ ጴጥሮስ በር ላይ እንደቆመም ለጉባኤው ተናገረች፤ እነሱ ግን አላመኗትም። እንዲያውም እንዳበደች ቆጠሯት፤ እሷ ግን ይህ የሚበግራት አልነበረችም። የተናገረችው ነገር እውነት መሆኑን አስረግጣ መናገሯን ቀጠለች። በመሆኑም አንዳንዶች ‘ምናልባት ጴጥሮስን የሚወክል መልአክ ሊሆን ይችላል’ ይሉ ጀመር። (ሥራ 12:12-15) ይህ ሁሉ ሲሆን ጴጥሮስ በሩን ማንኳኳቱን ቀጥሏል፤ በመጨረሻም ሄደው በሩን ከፈቱት።
15 በሩን ከፍተው ጴጥሮስን “ሲያዩት በጣም ተገረሙ”! (ሥራ 12:16) ጴጥሮስ በደስታ የሚያሰሙትን ጫጫታ በማስቆም ያጋጠመውን ነገር ተረከላቸው፤ ከዚያም ነገሩን ለያዕቆብና ለወንድሞች እንዲነግሯቸው አዘዛቸው፤ የሄሮድስ ወታደሮች መጥተው እንዳይዙትም አካባቢውን ለቆ ሄደ። ጴጥሮስ ለደህንነቱ ወደማያሰጋ ቦታ ሄዶ በታማኝነት ማገልገሉን ቀጠለ። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ የተጠቀሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ ብቻ ነው፤ ዘገባው ግርዘትን በተመለከተ የተነሳውን ክርክር ለመፍታት ጴጥሮስ ያደረገውን አስተዋጽኦ ይገልጻል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከዚህ ቀጥሎ ትኩረት የሚያደርገው ሐዋርያው ጳውሎስ ባከናወነው ሥራና ባደረጋቸው ጉዞዎች ላይ ነው። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ በሄደበት ስፍራ ሁሉ የወንድሞቹንና የእህቶቹን እምነት እንዳጠናከረ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በማርያም ቤት ተሰብስበው የነበሩት ክርስቲያኖች ጴጥሮስ ካገኛቸው በኋላ በጣም ተደስተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
16. ወደፊት ብዙ የደስታ ወቅቶች እንደሚጠብቁን በምን እናውቃለን?
16 አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ፣ ለአገልጋዮቹ ፈጽሞ ያልጠበቁትን ነገር ያደርግላቸዋል፤ በዚህ ጊዜ በደስታ ይፈነድቃሉ። በዚያን ሌሊት የጴጥሮስ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች የተሰማቸው እንደዚህ ነበር። እኛም ዛሬ የይሖዋን በረከት ስናገኝ እንዲሁ ይሰማናል። (ምሳሌ 10:22) ወደፊት ደግሞ ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ እንመለከታለን። የእነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜ ልንገምተው ከምንችለው የላቀ እንደሚሆን እርግጠኞች ነን። በመሆኑም በታማኝነት እስከጸናን ድረስ ወደፊት ብዙ የደስታ ወቅቶች እንደሚጠብቁን ልንተማመን እንችላለን።
“የይሖዋ መልአክ ቀሰፈው” (የሐዋርያት ሥራ 12:18-25)
17, 18. ሕዝቡ ሄሮድስን እንዲሸነግለው ያደረገው ምንድን ነው?
17 የጴጥሮስ ከእስር ቤት ማምለጥ ሄሮድስንም አስገርሞታል፤ ሆኖም ተገረመ እንጂ አልተደሰተም። ወዲያውኑ ጴጥሮስን ከየትም ፈልገው እንዲያመጡት አዘዘ፤ ጠባቂዎቹ ምርመራ እንዲካሄድባቸውም አደረገ። በኋላም “እርምጃ እንዲወሰድባቸው” አዘዘ፤ ይህ የሞት ቅጣት ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 12:19) ሄሮድስ አግሪጳ የሚታወቀው በጨካኝነቱ ነበር። ታዲያ ይህ ጨካኝ ሰው ከቅጣት ያመልጥ ይሆን?
18 ሄሮድስ አግሪጳ ጴጥሮስን ማስገደል አለመቻሉን እንደ ትልቅ ውርደት ሳይቆጥረው አልቀረም፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የቆሰለውን ስሜቱን የሚጠግንበት አጋጣሚ አገኘ። አንዳንድ ጠላቶቹ ከእሱ ጋር እርቅ መፍጠር ፈለጉ፤ ይህ ለእሱ ጥሩ አጋጣሚ ሆነለት፤ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ንግግር ለማቅረብ ጓጉቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ሉቃስ እንደዘገበው ሄሮድስ ይህን ልዩ ዝግጅት በማስመልከት “ልብሰ መንግሥቱን [ለበሰ]።” አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ የሄሮድስ ልብስ ከብር የተሠራ እንደነበረ ጽፏል፤ ብርሃን ልብሱ ላይ ሲያርፍ ስለሚያብረቀርቅ ግርማው የሚያስደምም ነበር። በትዕቢት የተወጠረው ይህ ፖለቲከኛ ንግግር ማቅረብ ጀመረ። በዚያ የተሰበሰበው አድርባይ ሕዝብ “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው አይደለም!” እያለ ይጮኽ ጀመር።—ሥራ 12:20-22
19, 20. (ሀ) ይሖዋ ሄሮድስን የቀጣው ለምንድን ነው? (ለ) ሄሮድስ አግሪጳ በድንገት ስለ መቀሰፉ ከሚገልጸው ዘገባ ምን ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን?
19 ይህ ዓይነቱ ክብር ሊሰጥ የሚገባው ለአምላክ ነው፤ አምላክ ደግሞ ሁኔታውን ይመለከት ነበር! ሄሮድስ ራሱን ከጥፋት ማዳን የሚችልበት አጋጣሚ ነበረው። ሕዝቡን መገሠጽ፣ ሌላው ቢቀር ትክክል አለመሆናቸውን መናገር ይችል ነበር። ሄሮድስ ግን “የትዕቢት መንፈስ . . . ውድቀትን ይቀድማል” ለሚለው አባባል ዓይነተኛ ምሳሌ ሆኗል። (ምሳሌ 16:18) “ወዲያውኑ የይሖዋ መልአክ ቀሰፈው”፤ በትዕቢት የተወጠረው ይህ ንጉሥ አሟሟቱ አላማረም። ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ “በትል ተበልቶ” ሞተ። (ሥራ 12:23) ጆሴፈስም ቢሆን ሄሮድስ በድንገት መቀሰፉን ገልጿል፤ አክሎ እንደጻፈውም ለሞት በሚዳርግ መቅሰፍት የተመታው የሕዝቡን ሽንገላ በመቀበሉ እንደሆነ ንጉሡ ራሱ ገብቶት ነበር። ሄሮድስ አምስት ቀን ሲሠቃይ ቆይቶ እንደሞተ ጆሴፈስ ጽፏል።b
20 አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት መጥፎ ድርጊት ቢፈጽሙም ከቅጣት የሚያመልጡ ሊመስል ይችላል። “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር” ስለሆነ ይህ ሊያስገርመን አይገባም። (1 ዮሐ. 5:19) ያም ሆኖ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች፣ ክፉ ሰዎች ከቅጣት እንዳመለጡ ሆኖ ሲሰማቸው አንዳንዴ ቅር ሊሰኙ ይችላሉ። እንዲህ ያሉትን ዘገባዎች ማንበባችን የሚያጽናናን በዚህ ጊዜ ነው። ይሖዋ ለክፉዎች የእጃቸውን እንደሚሰጣቸው ያስገነዝበናል፤ እሱ ፍትሕን የሚወድ አምላክ መሆኑንም ያስታውሰናል። (መዝ. 33:5) ይዋል ይደር እንጂ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረጉ አይቀርም።
21. በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 ላይ የሰፈረው ዘገባ ዋና መልእክት ምንድን ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ እኛን የሚያጽናናን ለምንድን ነው?
21 ይህ ዘገባ የሚደመደመው ከዚህም ይበልጥ በሚያበረታታ ሐሳብ ነው፤ “የይሖዋ ቃል . . . እየተስፋፋ ሄደ” ይላል። (ሥራ 12:24) የስብከቱ ሥራ እየተስፋፋ ስለ መሄዱ የሚገልጸው ይህ ዘገባ ይሖዋ በዘመናችን ይህንኑ ሥራ እንዴት እየባረከው እንዳለ ያስታውሰናል። የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 የአንድን ሐዋርያ መገደልና የሌላኛውን ከእስር ማምለጥ የሚተርክ ዘገባ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በሰይጣን ሴራ ላይ ያገኘውን ድል የሚያበስር ነው፤ ሰይጣን የክርስቲያን ጉባኤን ለማጥፋት ብሎም ጉባኤው በቅንዓት እያከናወነ ያለውን የስብከት ሥራ ለማዳፈን ያደረገው ሙከራ ከሽፎበታል። እንዲህ ያሉ ሙከራዎች ያኔም አልተሳኩም፤ ወደፊትም አይሳኩም። (ኢሳ. 54:17) በሌላ በኩል ግን ከይሖዋና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን የተሰለፉ ሰዎች መቼም ቢሆን የማይከሽፍ ሥራ እያከናወኑ ነው። ይህን ማወቅ የሚያበረታታ አይደለም? በዛሬው ጊዜ “የይሖዋ ቃል” እየተስፋፋ እንዲሄድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
a “ቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b ጸሐፊ የሆኑ አንድ ሐኪም እንደገለጹት ጆሴፈስም ሆነ ሉቃስ የገለጿቸው የበሽታ ምልክቶች በጥገኛ ትላትሎች ምክንያት የሚከሰቱ ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ትላትሎቹ የአንጀት ቱቦን በመዝጋት ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኛው ሲያስመልስ እነዚህ ትላትሎች ይወጣሉ፤ ወይም ሰውየው ሲሞት ከሰውነቱ እየተርመሰመሱ ይወጣሉ። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዳለው “የሕክምና ባለሙያ የሆነው ሉቃስ ሁኔታውን ቁልጭ አድርጎ የገለጸበት መንገድ [የሄሮድስ] አሟሟት ምን ያህል ዘግናኝ እንደነበር በግልጽ ያስረዳል።”