ማርቆስ—‘ለአገልግሎት የሚጠቅም ሰው’
በአንጾኪያ ጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ተከስተው ነበር፤ በሐዋርያው ጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ግን ከዚህ ጋር የተያያዘ አይደለም። ጳውሎስና በርናባስ የሚስዮናዊ ጉዞ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበሩ፤ ሆኖም ማንን ይዘው እንደሚሄዱ ሲነጋገሩ ‘በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ተፈጠረ።’ (ሥራ 15:39) በዚህም ምክንያት በተለያየ አቅጣጫ ሄዱ። በመካከላቸው ለተነሳው ጠብ መነሾው ሦስተኛው ሚስዮናዊ ማርቆስ ነበር።
ለመሆኑ ማርቆስ ማን ነበር? ሁለቱ ሐዋርያት በእሱ ምክንያት የተጣሉት ለምንድን ነው? ሁለቱም ሐሳባቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑት ለምንድን ነው? ከዚያ በኋላ አመለካከታቸው ተለውጦ ይሆን? ከማርቆስ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?
በኢየሩሳሌም በሚገኝ ቤት ውስጥ
ከአንድ ሀብታም አይሁዳዊ ቤተሰብ እንደመጣ የሚገመተው ማርቆስ ያደገው ኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር። ስለ እሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ተጠቅሶ የምናገኘው ጥንት ከነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ታሪክ ጋር በተያያዘ ነው። በ44 ዓ.ም. ገደማ አንድ የይሖዋ መልአክ ሐዋርያው ጴጥሮስን ከቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ እስር ቤት በተአምራዊ መንገድ ካስፈታው በኋላ ጴጥሮስ በቀጥታ “ማርቆስ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ በዚያም በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው ይጸልዩ ነበር።”—ሥራ 12:1-12a
የኢየሩሳሌም ጉባኤ የማርቆስን እናት ቤት ለመሰብሰቢያነት ይጠቀምበት የነበረ ይመስላል። “በርከት ያሉ ሰዎች” መሰብሰባቸው ቤቱ ትልቅ እንደነበር ያሳያል። ማርያም፣ ሮዳ የተባለች አንዲት አገልጋይ ነበረቻት፤ ጴጥሮስ ‘በሩን ሲያንኳኳ ሄዳ የከፈተችለት’ እሷ ነበረች። ይህ ሁኔታ ማርያም ደህና ኑሮ እንደነበራት ይጠቁማል። ቤቱ በባሏ ሳይሆን በእሷ ስም መጠራቱ ማርያም ባሏ የሞተባት ሴት ልትሆን እንደምትችልና ማርቆስ በወቅቱ ትንሽ ልጅ እንደነበረ ያሳያል።—ሥራ 12:13
ማርቆስ ለጸሎት ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል የነበረ ይመስላል። ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና ስለ ኢየሱስ አገልግሎት የዓይን ምሥክር ከነበሩ ሌሎች ሰዎች ጋር በደንብ ሳይተዋወቅ አልቀረም። እንዲያውም ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት እሱን ለመከተል የሞከረውና ሊይዙት ሲሞክሩ በፍታውን ትቶ ራቁቱን ያመለጠው ወጣት ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም።—ማር. 14:51, 52
በጉባኤ ውስጥ የነበረው ኃላፊነት
ማርቆስ ጎልማሳ ከነበሩ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረቡ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ምንም ጥርጥር የለውም። ጥሩ መንፈሳዊ እድገት በማድረጉ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ወንድሞችን ዓይን መሳብ ችሏል። በ46 ዓ.ም. ገደማ ጳውሎስና በርናባስ በረሃብ ለተጎዱት “የእርዳታ አገልግሎት ለመስጠት” ከአንጾኪያ ወደ ኢየሩሳሌም በሄዱበት ጊዜ ማርቆስ ትኩረታቸውን ሳይስብ አልቀረም። በመሆኑም ጳውሎስና በርናባስ ወደ አንጾኪያ ሲመለሱ ማርቆስን ይዘውት ሄዱ።—ሥራ 11:27-30፤ 12:25
አንድ ሰው ታሪኩን ልብ ብሎ ካላነበበው እነዚህ ሦስት ሰዎች መንፈሳዊ ወንድማማች ከመሆናቸው ሌላ ምንም ዓይነት ሥጋዊ ዝምድና የሌላቸው ይመስለው እንዲሁም ጳውሎስና በርናባስ ማርቆስን የመረጡት ችሎታውን አይተው ብቻ እንደሆነ ይሰማው ይሆናል። ይሁንና ጳውሎስ ከጻፋቸው ደብዳቤዎች መካከል በአንዱ ላይ ማርቆስ የበርናባስ የአጎቱ ልጅ እንደሆነ ተገልጿል። (ቆላ. 4:10) ይህን ማወቃችን ማርቆስን በተመለከተ የተከሰተውን ሁኔታ ለመረዳት ያስችለናል።
አንድ ዓመት አካባቢ ካለፈ በኋላ ጳውሎስና በርናባስ በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ሚስዮናዊ ጉዟቸውን ጀመሩ። በመጀመሪያ ከአንጾኪያ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ማርቆስ “እንደ አገልጋይ ሆኖ” አብሯቸው ሄዶ ነበር። (ሥራ 13:2-5) በጉዟቸው ወቅት ጳውሎስና በርናባስ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማርቆስ አንዳንድ አስፈላጊ ሥራዎችን በማከናወን ሳይረዳቸው አልቀረም።
ጳውሎስ፣ በርናባስና ማርቆስ እግረ መንገዳቸውን እየሰበኩ ቆጵሮስን አቋርጠው ወደ ትንሿ እስያ አቀኑ። ትንሿ እስያ ሲደርሱ ዮሐንስ ማርቆስ ጳውሎስን ያበሳጨ ውሳኔ አደረገ። ታሪኩ እንደሚናገረው ሦስቱም ሰዎች ጴርጌ ሲደርሱ ‘ዮሐንስ ከእነሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።’ (ሥራ 13:13) ማርቆስ እንዲህ ያደረገው ለምን እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጳውሎስ፣ በርናባስና ማርቆስ ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። ጳውሎስና በርናባስ በመጀመሪያ ጉዟቸው ወቅት የጎበኟቸውን ሰዎች ለማበረታታት ሁለተኛ የሚስዮናዊ ጉዞ ለማድረግ እየተወያዩ ነበር። በርናባስ የአጎቱ ልጅ ማርቆስ አብሯቸው እንዲሄድ ፈለገ፤ ጳውሎስ ግን ማርቆስ ከዚያ ቀደም ጥሏቸው ተመልሶ ስለነበር የእሱ ስም እንዲነሳበት እንኳ አልፈለገም። በመግቢያ ላይ የተጠቀሰው ጭቅጭቅ እንዲፈጠር ያደረገው ይህ ሁኔታ ነበር። በርናባስ ማርቆስን ይዞ ወደ ትውልድ ቦታው ወደ ቆጵሮስ ሲሄድ ጳውሎስ ደግሞ ወደ ሶርያ አመራ። (ሥራ 15:36-41) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስና በርናባስ ማርቆስ ከዚህ ቀደም ያደረገውን ውሳኔ የተመለከቱት በተለያየ ዓይን ነበር።
እርቅ ወረደ
ማርቆስ በሁኔታው አዝኖ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል። ይህ ሁኔታ ከተፈጸመ ከ11 ወይም ከ12 ዓመት ገደማ በኋላ ማርቆስ በጥንት ክርስትና ታሪክ ውስጥ እንደገና ብቅ አለ። ከማን ጋር እንደተጠቀሰ ልትገምት ትችላለህ? ከጳውሎስ ጋር ነበር።
ከ60-61 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ጳውሎስ ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት በአሁኑ ጊዜ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑ በርከት ያሉ ደብዳቤዎችን ጽፎ ነበር። በቆላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አብሮኝ የታሰረው አርስጥሮኮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ የበርናባስ የአጎቱ ልጅ ማርቆስም ሰላም ብሏችኋል፤ (እሱን በተመለከተም ወደ እናንተ ከመጣ እንድትቀበሉት መመሪያ ደርሷችኋል፤) . . . ለአምላክ መንግሥት አብረውኝ የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነሱም የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።”—ቆላ. 4:10, 11
እንዴት ያለ ለውጥ ነው! ጳውሎስን በጣም አሳዝኖት የነበረው ማርቆስ አሁን ግን ጳውሎስ የሚፈልገው የሥራ ባልደረባ ሆኗል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ማርቆስ ሄዶ ሊጎበኛቸው እንደሚችል ገልጾላቸው ነበር። ማርቆስ ሄዶ ጎብኝቷቸው ከነበረ ወደ ቆላስይስ የሄደው የጳውሎስ ወኪል ሆኖ ነው።
በጳውሎስና በማርቆስ መካከል የነበረው ግንኙነት የተሻሻለው ጳውሎስ ከዓመታት በፊት በማርቆስ ላይ የተቆጣው አላግባብ መሆኑን አምኖ ስለተቀበለ ይሆን? ወይስ ማርቆስ የተሰጠውን ተግሣጽ ተቀብሎ ማሻሻያ ስላደረገ? አሊያም በሁለቱም ምክንያቶች የተነሳ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በመካከላቸው እርቅ መውረዱ ጳውሎስም ሆነ ማርቆስ መጎልመሳቸውን ያሳያል። ሁለቱም ያለፈውን ነገር ረስተው እንደገና አብረው ማገልገል ጀምረዋል። ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር የአመለካከት ልዩነት ተፈጥሮ ለተቃቃሩ ክርስቲያኖች ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
ተጓዥ የነበረው ማርቆስ
ማርቆስ ስላደረጋቸው የተለያዩ ጉዞዎች ስታነብ ብዙ እንደተጓዘ ትገነዘባለህ። በመጀመሪያ ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ተጓዘ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስና ወደ ጴርጌ አቀና። በኋላ ላይ ደግሞ ወደ ሮም ሄደ። በሮም እያለም ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ ሊልከው ፈለገ። ይሁንና ጉዞው በዚህ ብቻ አላበቃም።
ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያውን ደብዳቤ የጻፈው ከ62 እስከ 64 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ነበር። በዚህ ደብዳቤው ላይ “በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥ. 5:13) በመሆኑም ማርቆስ ከዓመታት በፊት በእናቱ ቤት በሚደረጉ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ከነበረው ሐዋርያ ጋር ለማገልገል ወደ ባቢሎን ተጉዟል።
ጳውሎስ በ65 ዓ.ም. ገደማ ለሁለተኛ ጊዜ ሮም ውስጥ በታሰረበት ወቅት ጢሞቴዎስ ከኤፌሶን ወደ ሮም እንዲመጣ ደብዳቤ ጽፎለት ነበር፤ በዚያ ደብዳቤ ላይ ‘ማርቆስን ከአንተ ጋር ይዘኸው ና’ ብሎት ነበር። (2 ጢሞ. 4:11) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ማርቆስ በዚያ ጊዜ ኤፌሶን ነበር። የጳውሎስን ጥሪ ተቀብሎ ከጢሞቴዎስ ጋር ወደ ሮም ተመልሶ እንደሄደ ጥርጥር የለውም። በዚያን ወቅት ጉዞ ማድረግ ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም ማርቆስ በፈቃደኝነት ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዟል።
ሌላ ታላቅ መብት
ማርቆስ ካገኛቸው ታላላቅ መብቶች መካከል አንዱ በይሖዋ መንፈስ መሪነት አንደኛውን ወንጌል መጻፉ ነው። ሁለተኛውን ማለትም የማርቆስን ወንጌል ማን እንደጻፈው ባይጠቀስም አንዳንድ ጥንታዊ መረጃዎች ጸሐፊው ማርቆስ እንደሆነና መረጃውን ያገኘው ከጴጥሮስ እንደሆነ ይጠቁማሉ። እንዲያውም ማርቆስ ለዘገባቸው ነገሮች በሙሉ ጴጥሮስ የዓይን ምሥክር ነበር።
በማርቆስ ወንጌል ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎች ማርቆስ የጻፈው ለአሕዛብ አንባቢዎች መሆኑን ይናገራሉ፤ በወንጌሉ ላይ የአይሁድ ልማዶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል። (ማር. 7:3፤ 14:12፤ 15:42) ማርቆስ አይሁዳውያን ያልሆኑ አንባቢዎቹ በሚገባ እንዲረዱት ሲል በአረማይክ ቋንቋ የተገለጹ አነጋገሮችን ተርጉሞ ያስቀምጥ ነበር። (ማር. 3:17፤ 5:41፤ 7:11, 34፤ 15:22, 34) በርካታ የላቲን ቃላትን የተጠቀመ ከመሆኑም ሌላ የላቲን ቃላትን ተጠቅሞ የተለመዱ ግሪክኛ ቃላትን ያብራራ ነበር። እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው በሮም ነው የሚለውን ጥንታዊ ታሪክ ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ።
‘ለአገልግሎት ይጠቅመኛል’
ማርቆስ ሮም ሳለ ወንጌል በመጻፍ ብቻ አልተወሰነም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ‘ማርቆስን ከአንተ ጋር ይዘኸው ና’ ያለውን አስታውስ። ጳውሎስ ይህን ያለው ለምን ነበር? ‘ለአገልግሎት ስለሚጠቅመው’ ነበር።—2 ጢሞ. 4:11
ወደ መጨረሻ ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል በሆነው በዚህ ደብዳቤ ላይ ማርቆስ መጠቀሱ ስለ እሱ ብዙ ነገሮችን እንድናውቅ ያስችለናል። ማርቆስ ባሳለፈው ቲኦክራሲያዊ ታሪክ ላይ በየትኛውም ቦታ ላይ እንደ ሐዋርያ፣ መሪ ወይም ነቢይ ተደርጎ አልተጠቀሰም። ማርቆስ የሌሎችን ትእዛዝ ተቀብሎ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆነ አገልጋይ ነበር። ጳውሎስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ማርቆስ ከእሱ ጋር የነበረ መሆኑ ይህን ሐዋርያ ጠቅሞት ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።
ማርቆስን በተመለከተ ያገኘናቸውን የተለያዩ መረጃዎች አንድ ላይ ስናሰባስብ ማርቆስ ምሥራቹን ወደ ተለያዩ የምድር ክፍሎች በቅንዓት የሚያሰራጭ እንዲሁም ሌሎችን በደስታ የሚያገለግል ሰው እንደነበር ይገልጹልናል። በእርግጥም ማርቆስ ተስፋ ቆርጦ ወደኋላ ባለማለቱ የተለያዩ የአገልግሎት መብቶችን በማግኘት ተባርኳል!
እኛም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ልክ እንደ ማርቆስ የመንግሥቱን ምሥራች በቆራጥነት እንሰብካለን። አንዳንዶቻችን ምሥራቹን ለማስፋፋት ልክ እንደ ማርቆስ ወደ ሌሎች ቦታዎች አልፎ ተርፎም ወደ ሌላ አገር መሄድ እንችላለን። እርግጥ ብዙዎቻችን እንዲህ ማድረግ አንችል ይሆናል፤ ሆኖም ሁላችንም ማርቆስን መምሰል የምንችልበት ሌላ መንገድ አለ። ማርቆስ ክርስቲያን ወንድሞቹን ለማገልገል የተለየ ጥረት እንዳደረገ ሁሉ እኛም የእምነት ባልንጀሮቻችን ለአምላክ የሚያቀርቡትን አገልግሎት መፈጸም እንዲችሉ እነሱን ለመርዳት የተቻለንን ያህል ጥረት ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ ምንጊዜም ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች እንሁን።—ምሳሌ 3:27፤ 10:22፤ ገላ. 6:2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ማርቆስ በኖረበት ዘመን ሰዎች በዕብራይስጥ ወይም በሌላ ቋንቋ ሁለተኛ ስም ይኖራቸው ነበር። የማርቆስ የአይሁድ ስም ዮሐናን ወይም በአማርኛ ዮሐንስ ነበር። በላቲን ቋንቋ የሚጠራበት ሁለተኛ ስሙ ደግሞ ማርከስ ወይም ማርቆስ ነበር።—ሥራ 12:25
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ማርቆስ ከጎበኛቸው ከተሞች መካከል አንዳንዶቹ
ሮም
ኤፌሶን
ቆላስይስ
ጴርጌ
አንጾኪያ (በሶርያ የምትገኘው)
ቆጵሮስ
ሜድትራንያን ባሕር
ኢየሩሳሌም
ባቢሎን