የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የክርስቲያን ጉባኤ ስለ መቋቋሙና እየተስፋፋ ስለመሄዱ የሚገልጽ ሰፋ ያለ ዘገባ ይዟል። የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሐኪሙ ሉቃስ ሲሆን ከ33 እስከ 61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባሉት 28 ዓመታት ውስጥ ክርስቲያኖች ያደረጉትን እንቅስቃሴ ሕያው በሆነ መንገድ ይተርካል።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጀመሪያው ክፍል በዋነኝነት የሚያተኩረው ሐዋርያው ጴጥሮስ ባከናወናቸው ነገሮች ላይ ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ስለ ሐዋርያው ጳውሎስ እንቅስቃሴዎች ይዘግባል። ሉቃስ “እኛ” የሚለውን ተውላጠ ስም መጠቀሙ አንዳንዶቹ ክንውኖች በተፈጸሙበት ወቅት በቦታው እንደነበር የሚጠቁም ነው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ለሚገኘው መልእክት ትኩረት መስጠታችን የአምላክ ቃልና መንፈስ ቅዱስ ያላቸውን ኃይል እንድናደንቅ ይረዳናል። (ዕብ. 4:12) በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈረው መልእክት የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንድናዳብር የሚረዳን ከመሆኑም በላይ በአምላክ መንግሥት ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።
ጴጥሮስ “የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች” ተጠቀመ
ሐዋርያት፣ መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው በኋላ በድፍረት ምሥክርነት መስጠት ጀመሩ። ጴጥሮስ ‘ከመንግሥተ ሰማይ መክፈቻዎች’ የመጀመሪያውን በመጠቀም ለአይሁዳውያንና ‘ቃሉን ለተቀበሉ’ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች የእውቀትን በር እንዲሁም ወደ አምላክ መንግሥት መግባት የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ማቴ. 16:19፤ ሥራ 2:5, 41) የስደት ማዕበል በመነሳቱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ተለያየ ቦታ ቢበታተኑም ይህ ሁኔታ የስብከቱ ሥራ እንዲስፋፋ አድርጓል።
በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የአምላክን ቃል መቀበላቸውን ሲሰሙ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ እነሱ ላኳቸው። ጴጥሮስ በሁለተኛው መክፈቻ በመጠቀም ለሰማርያ ሰዎች ወደ አምላክ መንግሥት የመግባት አጋጣሚ ከፈተላቸው። (ሥራ 8:14-17) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የጠርሴሱ ሳውል አስገራሚ ለውጥ በማድረግ ክርስቲያን ሆነ። በ36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጴጥሮስ በሦስተኛው መክፈቻ የተጠቀመ ሲሆን ያልተገረዙ አሕዛብም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀበሉ።—ሥራ 10:45
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
2:44-47፤ 4:34, 35—ያመኑት ሰዎች ንብረታቸውን በመሸጥ ያገኙትን ገንዘብ የሰጡት ለምን ነበር? አማኝ ከሆኑት ሰዎች አብዛኞቹ የመጡት ራቅ ካሉ አካባቢዎች ሲሆን በኢየሩሳሌም ረዘም ላለ ጊዜ ለመቆየት የሚያስፈልጓቸው ነገሮች አልነበሯቸውም። ያም ቢሆን ስለ አዲሱ እምነታቸው ይበልጥ ለመማርና ለሌሎች ለመመሥከር ሲሉ በኢየሩሳሌም መቆየት ፈልገው ነበር። እነዚህን ሰዎች ለመርዳት አንዳንድ ክርስቲያኖች ንብረታቸውን የሸጡ ሲሆን ገንዘቡም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተከፋፍሏል።
4:13—ጴጥሮስ እና ዮሐንስ መሃይሞች ወይም ያልተማሩ ሰዎች ነበሩ? አልነበሩም። “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” የተባሉት በረቢዎች ትምህርት ቤት ገብተው ሃይማኖታዊ ትምህርት ስላልተከታተሉ ነው።
5:34-39—ሉቃስ፣ በሳንሄድሪን ዝግ ችሎት ላይ ገማልያል የተናገረውን ነገር ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነበር? ይህን ማድረግ የሚችልባቸው ቢያንስ ሦስት መንገዶች አሉ:- (1) ቀደም ሲል የገማልያል ተማሪ የነበረው ጳውሎስ ስለ ስብሰባው ለሉቃስ ነግሮት ሊሆን ይችላል፤ (2) ሉቃስ እንደ ኒቆዲሞስ ያለ ተባባሪ የሆነ የሳንሄድሪን አባል አማክሮ ይሆናል አሊያም (3) የአምላክ መንፈስ ገልጦለት ይሆናል።
7:59—እስጢፋኖስ የጸለየው ለኢየሱስ ነበር? አልነበረም። አንድ ሰው ማምለክ ያለበት ይሖዋ አምላክን ብቻ ስለሆነ መጸለይ የሚገባውም ለእሱ ብቻ ነው። (ሉቃስ 4:8፤ 6:12) በሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ እስጢፋኖስ የሚጸልየው ወደ ይሖዋ ሲሆን ይህንንም የሚያደርገው በኢየሱስ ስም ነበር። (ዮሐ. 15:16) በዚህ ወቅት ግን እስጢፋኖስ ‘የሰው ልጅ በአምላክ ቀኝ ቆሞ’ በራእይ ተመለከተ። (ሥራ 7:56) እስጢፋኖስ፣ ኢየሱስ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንደተሰጠው በሚገባ ያውቅ ስለነበር መንፈሱን እንዲቀበል በቀጥታ ጠይቆታል እንጂ ወደ ኢየሱስ አልጸለየም።—ዮሐ. 5:27-29
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:8:- የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚያካሂዱት የስብከት ሥራ ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሊከናወን አይችልም።
4:36 እስከ 5:11:- በቆጵሮስ የሚኖረው ዮሴፍ፣ “የመጽናናት ልጅ” የሚል ትርጉም ያለው በርናባስ የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። ሐዋርያት ለዚህ ሰው ይህን ስም የሰጡት አፍቃሪ፣ ደግና ሌሎችን የሚረዳ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። እኛም አስመሳይ፣ ግብዝና ተንኮለኛ ከነበሩት ከሐናንያና ከሰጲራ በተለየ መልኩ በርናባስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
9:23-25:- የስብከቱን ሥራ ለመቀጠል ስንል ከጠላቶቻችን በዘዴ ማምለጥ የፍርሃት ምልክት አይደለም።
9:28-30:- በአንዳንድ አካባቢዎች ወይም ለአንዳንድ ግለሰቦች ስንሰብክ፣ አካላዊና ሥነ ምግባራዊ ብሎም መንፈሳዊ አደጋ ሊያጋጥመን የሚችልበት ሁኔታ ከተፈጠረ የምንሰብክበትን ቦታና ጊዜ በተመለከተ ጠንቃቆችና መራጮች መሆን ይኖርብናል።
9:31:- በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም ባለበት ወቅት በማጥናትና በማሰላሰል መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ እያዋልን ይሖዋን በመፍራት እንድንመላለስ እንዲሁም በአገልግሎት ቀናተኛ እንድንሆን ይረዳናል።
ጳውሎስ በቅንዓት ያከናወነው አገልግሎት
በ44 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አጋቦስ የተባለው ነቢይ ወደ አንጾኪያ መጣ፤ በርናባስና ሳውል በዚያ “አንድ ዓመት ሙሉ” ሲያስተምሩ ነበር። አጋቦስ “ታላቅ ራብ እንደሚሆን” ትንቢት የተናገረ ሲሆን ይህም ከሁለት ዓመት በኋላ ተፈጸመ። (ሥራ 11:26-28) በርናባስና ሳውል ለወንድሞች እርዳታ ከማድረግ ጋር በተያያዘ “ተልእኮአቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም” ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። (ሥራ 11:29, 30፤ 12:25) በ47 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ማለትም ሳውል ወደ ክርስትና ከተለወጠ ከ12 ዓመታት በኋላ፣ በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የሚስዮናዊነትን አገልግሎት ጀመሩ። (ሥራ 13:1-4) በ48 ከክርስቶስ ልደት በኋላ “ለእግዚአብሔር ጸጋ በዐደራ ወደ ተሰጡባት ወደ አንጾኪያ” ተመለሱ።—ሥራ 14:26
ይህ ከሆነ ከዘጠኝ ወራት ገደማ በኋላ ጳውሎስ (ሳውል በመባልም ይጠራል) የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን ሲላስን በመምረጥ ሁለተኛ ጉዞውን አደረገ። (ሥራ 15:40) ጳውሎስ በአገልግሎቱ ላይ እያለ ጢሞቴዎስና ሉቃስም አብረውት መጓዝ ጀመሩ። ሐዋርያው ወደ አቴና ከዚያም ወደ ቆሮንቶስ ሲሄድ ሉቃስ በፊልጵስዩስ ቀረ፤ ጳውሎስ በቆሮንቶስ አቂላንና ጵርስቅላን ያገኛቸው ሲሆን በዚያም አንድ ዓመት ተኩል ተቀመጠ። (ሥራ 18:11) በ52 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጀመሪያ አካባቢ ሐዋርያው፣ ጢሞቴዎስንና ሲላስን በቆሮንቶስ ትቶ ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ወደ ሶርያ በመርከብ ሄደ። (ሥራ 18:18) አቂላና ጵርስቅላ እስከ ኤፌሶን ድረስ አብረውት ከሄዱ በኋላ በዚያ ቀሩ።
ጳውሎስ በሶርያ በምትገኘው አንጾኪያ ለጥቂት ጊዜ የቆየ ሲሆን በ52 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሦስተኛ ጉዞውን ጀመረ። (ሥራ 18:23) በኤፌሶን “የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።” (ሥራ 19:20) ሐዋርያው በዚያ ሦስት ዓመት ገደማ ቆይቷል። (ሥራ 20:31) በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ነበር። በዚያም ታስሮ በነበረበት ወቅት ለባለ ሥልጣናቱ ያለ አንዳች ፍርሃት መሠከረ። ሐዋርያው ሮም ውስጥ ለሁለት ዓመት (ከ59 እስከ 61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ) የቁም እስረኛ የነበረ ሲሆን በዚያ ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብክና “ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ” ያስተምር ነበር።—ሥራ 28:30, 31
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
14:8-13—የልስጥራ ሰዎች በርናባስን “ድያ” ሲሉት ጳውሎስን “ሄርሜን” ያሉት ለምን ነበር? በግሪካውያን አፈ ታሪክ መሠረት ድያ የአማልክት ገዥ ሲሆን ልጁ ሄርሜን ደግሞ አንደበተ ርቱዕ በመሆኑ የታወቀ ነበር። ዋና ተናጋሪ የነበረው ጳውሎስ በመሆኑ የልስጥራ ሰዎች ሄርሜን ብለው የጠሩት ሲሆን በርናባስን ደግሞ ድያ ብለውታል።
16:6, 7—መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስንና ባልደረቦቹን በእስያና በቢታንያ እንዳይሰብኩ የከለከላቸው ለምን ነበር? ሠራተኞቹ ጥቂት ስለነበሩ መንፈስ ቅዱስ ይበልጥ ፍሬያማ ወደሆኑ አካባቢዎች እንዲሄዱ መመሪያ ሰጥቷቸዋል።
18:12-17—ሕዝቡ ሶስቴንስን ሲደበድበው ገዥው ጋልዮስ ጣልቃ ያልገባው ለምን ነበር? በጳውሎስ ላይ የተነሳውን ዓመጽ ያስተባበረው ሶስቴንስ ሳይሆን አይቀርም፤ በመሆኑም ጋልዮስ ይህ ሰው የእጁን እንዳገኘ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ይህ አጋጣሚ ሶስቴንስ ወደ ክርስትና እንዲለወጥ ምክንያት ስለሆነ ጥሩ ውጤት ያስገኘ ይመስላል። ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ ሶስቴንስን ‘ወንድማችን’ በማለት ጠርቶታል።—1 ቆሮ. 1:1
18:18—ጳውሎስ የተሳለው ስእለት ምን ነበር? አንዳንድ ምሑራን ጳውሎስ፣ ናዝራዊ ለመሆን ተስሎ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። (ዘኍ. 6:1-21) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ተሳለው ስእለት ምንም ፍንጭ አይሰጥም። ከዚህም በላይ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ጳውሎስ ስእለቱን የተሳለው ወደ ክርስትና ከመለወጡ በፊት ይሁን ወይም ከዚያ በኋላ እንዲሁም ስእለቱን ገና መሳሉ ይሁን ወይም መፈጸሙ ምንም አይናገሩም። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን እንዲህ ዓይነቱን ስእለት መሳል ኃጢአት አልነበረም።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
12:5-11:- ለወንድሞቻችን መጸለይ የምንችል ከመሆኑም በላይ እንዲህ ማድረግ ይገባናል።
12:21-23፤ 14:14-18:- ሄሮድስ ለአምላክ ብቻ የሚገባው ክብር ሲሰጠው ተቀብሏል። የዚህ ሰው ሁኔታ፣ ተገቢ ያልሆነ ውዳሴና ክብር ሲሰጣቸው ወዲያውኑ በኃይል ከተቃወሙት ከጳውሎስና ከበርናባስ ምንኛ የተለየ ነው! እኛም በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ለምናከናውነው ለማንኛውም ነገር ክብር ከመፈለግ መቆጠብ ይኖርብናል።
14:5-7:- ጠንቃቆች መሆናችን አገልግሎታችንን መቀጠል እንድንችል ይረዳናል።—ማቴ. 10:23
14:22:- ክርስቲያኖች መከራ እንደሚደርስባቸው ያውቃሉ። በመሆኑም እምነታቸውን በማላላት ከእነዚህ መከራዎች ለማምለጥ አይሞክሩም።—2 ጢሞ. 3:12
16:1, 2:- ወጣት ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ ለአምላክ የሚያቀርቡትን አገልግሎት በትጋት ማከናወን አለባቸው፤ እንዲሁም ጥሩ ስም ለማትረፍ የይሖዋን እርዳታ መፈለግ ይኖርባቸዋል።
16:3:- ምሥራቹ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ስንል ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጩ ነገሮችን ለማድረግ የተቻለንን ያህል መጣር ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 9:19-23
20:20, 21:- ከቤት ወደ ቤት መመሥከር የአገልግሎታችን አስፈላጊ ክፍል ነው።
20:24፤ 21:13:- ለአምላክ ታማኝ መሆን ሕይወታችንን ከማትረፍ የበለጠ አስፈላጊ ነው።
21:21-26:- ጥሩ ምክር ሲሰጠን ለመቀበል ዝግጁና ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል።
25:8-12:- በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ‘ለምሥራቹ ለመሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ በሕጋዊ መንገዶች መጠቀም ይችላሉ፤ ደግሞም እንደዚህ ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ፊልጵ. 1:7 NW
26:24, 25:- ምንም እንኳ ‘መንፈሳዊ ላልሆነ ሰው’ “እውነተኛና ትክክለኛ ነገር” መናገር ሞኝነት ቢመስለውም እኛ ግን ይህን ማድረግ ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 2:14
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ “የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች” የተጠቀመው መቼ ነበር?
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለም ዙሪያ የሚካሄደው የስብከት ሥራ ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ሊከናወን አይችልም