ስለ መላእክት ያለው እውነታ
ከአንድ ሰው ጋር መተዋወቅ ብዙውን ጊዜ ስለዚያ ሰው ቤተሰብ ማወቅን ያካትታል። ይሖዋ አምላክን ማወቅም ልክ እንደዚሁ ነው። ስሙን ማወቅ ብቻ አይበቃም። በሰማይ ስለሚገኘው ‘ቤተሰቡም’ አንዳንድ ነገሮች ማወቅ አለብን። (ከኤፌሶን 3:14, 15 አዓት ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ መላእክትን የአምላክ “ልጆች” በማለት ይጠራቸዋል። (ኢዮብ 1:6) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የመላእክት ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት በአምላክ ዓላማ ውስጥ ምን ቦታ እንዳላቸው ይበልጥ ለማወቅ መፈለግ አለብን።
አዲስ ባህል እየተስፋፋ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች በመላእክት ማመናቸውን ብቻ ሳይሆን መላእክት በተወሰነ መጠን ተጽዕኖ እንዳሳደሩባቸው ይናገራሉ። “በሕይወታችሁ ውስጥ መላእክት እንደተከሰቱ ተሰምቷችሁ ያውቃል?” ተብለው ከተጠየቁ 500 አሜሪካውያን መካከል አንድ ሦስተኛው አዎን በማለት መልሰዋል። በጣም የሚያስገርመው በመላእክት እንደሚያምኑ የተናገሩት ወጣቶች ቁጥር ነው። በዩናይትድ ስትቴስ ውስጥ በተደረገ አንድ ጥናት 76 በመቶው በመላእክት እንደሚያምኑ ተናግረዋል! ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ሰዎች ለመላእክት ትኩረታቸውን ሰጥተዋል። ነገር ግን መላእክትን በተመለከተ አሁን ያለው አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሲለካ ምን ቦታ አለው?
የሰይጣን ስውር ደባ
ስለ መላእክት ስንናገር በአምላክ ላይ ያመፁ ሰማያዊ ፍጥረታት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርላቸው ክፉ መላእክትንም መርሳት የለብንም። ከእነዚህ ውስጥ ቀንደኛው ሰይጣን ነው። አስክ ዩር ኤንጅልስ የተባለ አንድ ታዋቂ መጽሐፍ ስለ ሰይጣን ሲናገር ሰዎች በማያቋርጥ ፈተና “መንፈሳዊ ጡንቻቸውን” እንዲያጠነክሩ የሚያደርግ “የአምላክ አንዱ ገጽታ” ነው ብሏል። የመጽሐፉ ደራሲዎች እንደተናገሩት ከሆነ ምንም እንኳ ሰይጣን “ፍቅራዊ አሳቢነት” ቢኖረውም ለብዙ መቶ ዘመናት ያለ ሥራው መጥፎ ስም ሲሰጠው ቆይቷል። በተጨማሪም ሰይጣንና ኢየሱስ “አንዱ የሌላኛው ማሟያ ባይሆንም እንኳ ቢያንስ ቢያንስ በአንድ ጎራ የተሰለፉ የአንድ አካል አስፈላጊ ክፍሎች ናቸው” ብለዋል። እነዚህ የሚያስገርሙ ሐሳቦች ናቸው፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን “የአምላክ አንዱ ገጽታ” ሳይሆን የአምላክ ጠላት እንደሆነ ይገልጻል። (ሉቃስ 10:18, 19፤ ሮሜ 16:20) ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት ከመገዳደሩም በላይ ፈጽሞ ለሰዎች “ፍቅራዊ” አሳቢነት የለውም። በአምላክ ምድራዊ አገልጋዮች ላይ ቁጣውን ያለርኅራኄ ይገልጣል። በአምላክ ፊት ቀንና ሌሊት ይከስሳቸዋል!a (ራእይ 12:10, 12, 15–17) የሰይጣን ዕቅድ በተቻለ መጠን አቋማቸውን ማበላሸት ነው። በጻድቁ ኢዮብ ላይ ያደረሰው ጭካኔ የተሞላበት መከራ ፈጽሞ ለሰው የማያዝን መሆኑን አጋልጧል።—ኢዮብ 1:13–19፤ 2:7, 8
ሰይጣንና ኢየሱስ እንኳን “በአንድ ጎራ ሊሰለፉ” ይቅርና ጭራሽ በጠላትነት የሚተያዩ ናቸው። ሄሮድስ ሕፃናት በጅምላ እንዲጨፈጨፉ ትእዛዝ እንዲያወጣ ያነሳሳው ሰይጣን ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ሁሉ ጥረት ትንሽ ልጅ የነበረውን ኢየሱስ ለመግደል ነበር! (ማቴዎስ 2:16–18) ሰይጣን በኢየሱስ ላይ ይሰነዝርበት የነበረው የማያቋርጥ ጥቃት እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል። (ሉቃስ 4:1–13፤ ዮሐንስ 13:27) ስለዚህ ኢየሱስና ሰይጣን “የአንድ አካል አስፈላጊ ክፍሎች” ከመሆን ይልቅ ፍጹም ተቃራኒዎች ናቸው። ጠላትነታቸው መቼም ቢሆን የማይቀር መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያሳያል። (ዘፍጥረት 3:15) አምላክ በወሰነው ጊዜ ሰይጣንን የሚያጠፋው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ መሆኑ ተስማሚ ነው።—ራእይ 1:18፤ 20:1, 10
ጸሎት የምናቀርበው ለማን ነው?
አንዳንድ የመላእክት እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ከመላእክት ጋር ግንኙነት ለማድረግ ማሰላሰልና ሌሎች ዘዴዎች ጥሩ እንደሆኑ ይናገራሉ። “ከማንኛውም ሰማያዊው ቤተሰብ አባል ጋር ግንኙነት ለማድረግ የሚቀርብ ልባዊ ልመና በፍጹም ሰሚ አጥቶ አይቀርም። ጠይቁ መልስ ታገኛላችሁ” በማለት አንድ መጽሐፍ ተናግሯል። መጽሐፉ እንድናማክራቸው ከጠቆመን መላእክት መካከል ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ኡራኤልና ሩፋኤል ይገኙበታል።b
ነገር ግን ኢየሱስ ተከታዮቹን ያስተማረው ወደ መላእክት እንዲጸልዩ ሳይሆን ወደ አምላክ እንዲጸልዩ ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) በተመሳሳይም ጳውሎስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ” በማለት ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:6 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ስለዚህ ክርስቲያኖች ጸሎታቸውን ከይሖዋ በቀር ለሌላ ለማንም አያቀርቡም። ጸሎታቸውን የሚያቀርቡትም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው።c—ዮሐንስ 14:6, 13, 14
መላእክት አንድ የተወሰነ ሃይማኖት የላቸውምን?
የኤንጅልዎች ኔትዎርክ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ኤሊን ኢሊስ ፍሪማን “መላእክት ከማንኛውም ሃይማኖት፣ ከማንኛውም ፍልስፍና፣ ከማንኛውም እምነት የላቁ ናቸው። እንዲያውም እኛ እስከምናውቀው ድረስ መላእክት ሃይማኖት የላቸውም” ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ታማኝ መላእክት ሃይማኖት እንዳላቸው ይገልጻል። ሌሎች አማልክት እንዲቀናቀኑት የማይፈቅደውን እውነተኛ አምላክ ይሖዋን ያመልካሉ። (ዘዳግም 5:6, 7፤ ራእይ 7:11) አንድ መልአክ ራሱን ለሐዋርያው ዮሐንስ ሲያስተዋውቅ የአምላክን ትእዛዝ ከሚጠብቁ ጋር “አብሬ ባሪያ ነኝ” ያለው ለዚህ ነው። (ራእይ 19:10) ታማኝ መላእክት ሌላ ማንኛውንም ዓይነት አምልኮ እንደሚደግፉ የሚያሳይ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትም ቦታ አናገኝም። የሚያቀርቡት አምልኮ ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ ነው።—ዘጸአት 20:4, 5
‘የሐሰት አባት’
አብዛኞቹ ከመላእክት ጋር ተደረጉ የሚባልላቸው ግንኙነቶች የሞቱ ሰዎችን ከማነጋገር ጋር የተያያዙ ናቸው። ኤሊስ የተባለች ሴት የሚሰማት ነገር የገድ ምልክት እንደሆነ ካመነች በኋላ “አጎቴ ወደ እኔ ለመምጣት የሚያስችለው መንገድ በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን ያሳወቀኝ ይመስለኛል” በማለት ተናግራለች። ቴሪ የተባለች ሴትም በተመሳሳይ በሞት የተለያትን ውድ ጓደኛዋን ታስታውሳለች። እንዲህ አለች፦ “ከተቀበረ ከሳምንት በኋላ ወደ እኔ ሲመጣ ሕልም መስሎኝ ነበር። በደስታና በሰላም ስለሚኖር በመለየቱ ማዘን እንደሌለብኝ ነገረኝ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሙታን “አንዳች አያውቁም” በማለት ይናገራል። (መክብብ 9:5) በተጨማሪም አንድ ሰው ሲሞት “ያን ጊዜ ምክሩ [“ሐሳቡ” አዓት] ሁሉ ይጠፋል” ይላል። (መዝሙር 146:4 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ቢሆንም ሰይጣን ‘የሐሰት አባት’ ነው። (ዮሐንስ 8:44) የሰው ነፍስ ከሞት በኋላ በሕይወት ትኖራለች የሚለውን ሐሰት የጠነሰሰው እርሱ ነው። (ከሕዝቅኤል 18:4 ጋር አወዳድር።) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ከሰይጣን ዓላማ ጋር በመስማማት ይህንን ያምናሉ። ይህም የክርስትና መሠረተ ትምህርት በሆነው በትንሣኤ ላይ ያለንን እምነት ዋጋ ቢስ ያደርገዋል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ስለዚህ ሙታንን ማማከር ወይም ለሰዎች እንደሚመስላቸው ከእነርሱ መልእክት መቀበል በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የመላእክት እንቅስቃሴ ሌላ ገጽታ ነው።
ወደ መላእክት ወይስ ወደ አጋንንት መቅረብ?
በሰፊው ተቀባይነት ካገኘው የመላእክት እንቅስቃሴ መካከል አብዛኛው ቀስ በቀስ ከተአምር ጋር እየተያያዘ ነው። የማርስያስን ተሞክሮ ተመልከት። እንዲህ አለች፦ “ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ 1986 ባለው ጊዜ ውስጥ ‘ከሰው በላይ ከሆነ ኃይል’ መልእክቶች ይደርሱኝ ጀመር። እንግዳ የሆኑ ምስሎችንና ‘ስላሳለፍኩት ሕይወት’ ለማመን የሚያስቸግሩ ሕልሞችን አልማለሁ። ከሞቱ ጓደኞቼ ጋር ከመገናኘቴም በተጨማሪ ቀረብ ብዬ ስለማላውቃቸው ሰዎች አንዳንድ ነገሮች ያወቅሁባቸው ሌሎች ምሥጢራዊ ገጠመኞችም ነበሩ። በተጨማሪም ከራሴ አእምሮ ውጪ በሆነ ግፊት የመጻፍንና ከመንፈሳዊ ዓለም የመጣ መልእክትን የማስተላለፍ ስጦታ በመቀበል ተባርኬአለሁ። በምድራዊ ሕይወታቸው አግኝቻቸው የማላውቃቸው ሰዎች በእኔ በኩል ለሌሎች መልእክት ይልካሉ።”
ከመላእክት ጋር “ለመገናኘት” በጥንቆላ መጠቀም የተለመደ ነው። አንድ ጽሑፍ አንባቢዎቹ በጥንቆላ ድንጋይ፣ ሥዕል ባለባቸው የካርታ መጫወቻዎች፣ በኢ ጂንግ ሳንቲም፣ የመዳፍ አሻራ በማንበብና በኮከብ ቆጠራ እንዲጠቀሙ በቀጥታ አበረታቷል። ደራሲው እንደዚህ በማለት ጽፏል፦ “ውስጣዊ ማንነታችሁ ከአማልክት ጋር መነጋገር ወደሚቻልበት ስፍራ እንዲመራችሁ ፍቀዱለት፤ እዚያም ከአንድ መልአክ ጋር እንደምትገናኙ እምነት ይኑራችሁ።”
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘እዚያ የምታገኘው’ ከአምላክ መላእክት አንዱን አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ጥንቆላ አምላክ ፈጽሞ የሚጠላው ነገር ስለሆነና በሰማይም ሆነ በምድር ከሚገኙ እውነተኛ አምላኪዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ነው። ጥንቆላ በእስራኤላውያን ዘንድ ከባድ ኃጢአት የነበረው ለዚህ ነው! ሕጉ “ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው” በማለት ይገልጻል።—ዘዳግም 13:1–5፤ 18:10–12
‘የብርሃን መልአክ’
ዲያብሎስ ጥንቆላን ጠቃሚ እንዲያውም የመላእክት እጅ ያለበት አስመስሎ ለማቅረብ መቻሉ ሊያስደንቀን አይገባም። ሰይጣን “የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ሌላው ቀርቶ ትንቢቶችን ፈጥሮ ካወራ በኋላ እንዲፈጸሙ በማድረግ ይህን የሚመለከቱ ሰዎች ትንቢቱ ከአምላክ እንደመጣ አድርገው እንዲያስቡ ሊያደርግ ይችላል። (ከማቴዎስ 7:21–23 ጋር አወዳድር፤ 2 ተሰሎንቄ 2:9–12) የሰይጣን ሥራዎች በጠቅላላ ምንም ያህል በጎ ወይም መጥፎ ሆነው ቢታዩም ከሚከተሉት ሁለት ዓላማዎች አንዱን ለማሳካት ያገለግላሉ። እነዚህም ሰዎችን ከይሖዋ መለየት ወይም “የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው” አእምሯቸውን ማሳወር ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) መጨረሻ የተጠቀሰው የማታለያ ዘዴ ብዙ ጊዜ የተሻለ ውጤት አስገኝቷል።
መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረች አንዲት አገልጋይ የሚናገረውን ታሪክ ተመልከት። ጥንቆላዋ ለጌቶችዋ ብዙ ትርፍ ያስገኝላቸው ነበር። “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው! እነርሱ የደኅንነትን መንገድ ያበሥሩአችኋል” እያለች ለብዙ ቀናት ደቀ መዛሙርቱን ተከታትላቸው ነበር። የምትናገረው እውነት ነበር። ቢሆንም ታሪኩ እንደሚነግረን ያደረባት መልአክ ሳይሆን “በጥንቆላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ” ነበር። በመጨረሻም ጳውሎስ “ዞር ብሎ ርኩሱን መንፈስ ‘በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርስዋ እንድትወጣ አዝዝሃለሁ!’ አለው። ርኩሱም መንፈስ ወዲያውኑ ወጣ።”—ሥራ 16:16–18 የ19 80 ትርጉም።
ጳውሎስ ይህንን መንፈስ ያስወጣው ለምንድን ነው? መቼም በአጋንንት ለተያዘችው ሴት ጌቶች ብዙ ገቢ አስገኝቶላቸዋል። ይህች አገልጋይ ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች በመታገዝ ገበሬዎች መቼ መዝራት እንደሚኖርባቸው፣ ቆነጃጅት መቼ ማግባት እንዳለባቸውና ማዕድን ፈላጊዎች የት ቦታ ወርቅ መፈለግ እንደሚኖርባቸው ተናግራ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ይህ መንፈስ ሴትየዋ ደቀ መዛሙርቱን በሰዎች ፊት በማወደስ ጥቂት የእውነት ቃላት እንድትናገር ገፋፍ ቷታል!
ያም ሆነ ይህ “ወደፊት የሚሆነውን ነገር በጥንቆላ የሚያናግር ርኩስ መንፈስ” ነበር። አጋንንት ደግሞ ስለ ይሖዋና ስላለው የመዳን ዝግጅት የማወጅ መብት የላቸውም። ምናልባት አገልጋዪቱ የምትናገራቸውን ትንቢቶች እውነት ለማስመሰል ታስበው የተነገሩት የሙገሳ ቃላት በዚያ የነበሩ ሰዎች እውነተኞቹን የክርስቶስ ተከታዮች እንዳይሰሙ ሐሳባቸውን ከፋፍሎባቸው ነበር። ጳውሎስ “ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም” በማለት የቆሮንቶስ ሰዎችን ያስጠነቀቀበት ጥሩ ምክንያት ነበረው። (1 ቆሮንቶስ 10:21) የመጀመሪያ መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከጥንቆላ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መጽሐፎቻቸውን በጠቅላላ ማጥፋታቸው አያስደንቅም።—ሥራ 19:19
‘በሰማይ መካከል እየበረረ ያለ መልአክ’
እስካሁን እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ ያለው አብዛኛው የመላእክት እንቅስቃሴ የአምላክ ጠላት ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጋር ቅርብ ትስስር እንዳለው ያሳያል። ይህ ማለት ቅዱሳን መላእክት በሰው ጉዳዮች ውስጥ አይገቡም ማለት ነውን? አይደለም፤ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ አስገራሚ ሥራ እየፈጸሙ ነው። ይህ ሥራ ምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የራእይ መጽሐፍ መመልከት አለብን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም መጽሐፍ ይልቅ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ መላእክት ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል።
በራእይ 14:6, 7 ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ በጽሑፍ ያሰፈረውን ትንቢታዊ ራእይ እናነባለን። የተቀበለው ራእይ ይህ ነበር፦ “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም፦ የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ።”
ይህ ጥቅስ በዛሬው ጊዜ መላእክት እየሠሩ ያሉትን አንገብጋቢ ሥራ ያጎላል። ከሁሉ የላቀ ስፍራ በሚሰጠው ይኸውም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጅ ሥራ እየተካፈሉ ነው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ቃል የገባላቸው ይህንን ሥራ በተመለከተ ነው። (ማቴዎስ 28:18–20) ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር የሚሆነው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ይህንን ሰፊ ሥራ ለማጠናቀቅ ለተከታዮቹ መላእክታዊ እርዳታ በመስጠት ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ በየዓመቱ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት ያሳልፋሉ። ይህንን ሥራ ሲያከናውኑ መላእክት እየመሯቸው እንዳለ የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች ይመለከታሉ። ከበር ወደ በር በሚያደርጉት አገልግሎት የአምላክን ዓላማዎች እንዲገነዘቡ የሚረዳቸው ሰው እንዲያገኙ እየጸለዩ ከነበሩ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ይገናኛሉ። በመላእክታዊ መሪነት ላይ ምሥክሮቹ በራሳቸው አነሳሽነት ለሥራ መዘጋጀታቸው ታክሎበት በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ አስችሏል!
በሰማይ መካከል የሚበርረውን መልአክ እያዳመጥክ ነውን? የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤትህ ሲመጡ ለምን ጊዜ ወስደህ ስለዚህ መላእክታዊ መልእክት ይበልጥ ከእነርሱ ጋር አትወያይም?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ሰይጣን” እና “ዲያብሎስ” የሚሉት ቃላት “ተቃዋሚ” እና “ስም አጥፊ” የሚል ፍቺ አላቸው።
b ሚካኤልና ገብርኤል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲጠቀሱ ሩፋኤልና ኡራኤል የሚሉት ስሞች ግን ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ባልሆኑት አዋልድ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
c ጸሎት የሚቀርበው በኢየሱስ በኩል እንጂ ለኢየሱስ እንዳልሆነ ልብ በል። ጸሎት በኢየሱስ ስም የሚቀርበው ያፈሰሰው ደሙ ወደ አምላክ የሚያቀርበውን መንገድ ስለከፈተ ነው።—ኤፌሶን 2:13–19፤ 3:12
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መላእክት እነማን ናቸው?
ብዙ ሰዎች እንደሚያምኑት መላእክት ከሞቱ ሰዎች ወጥተው የሄዱ ነፍሳት አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን “አንዳች አያውቁም” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ይናገራል። (መክብብ 9:5) ታዲያ መላእክት ከየት መጡ? ምድር ከመመሥረቷ በፊት አምላክ እንደፈጠራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 38:4–7) የአምላክ ሰማያዊ ቤተሰብ በመቶ ሚልዮን ምናልባትም በቢልዮን የሚቆጠሩ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ መላእክትን የያዘ ሊሆን ይችላል! አንዳንድ መላእክት በዚህ ዓመፅ ከሰይጣን ጋር ተባብረዋል።—ዳንኤል 7:10፤ ራእይ 5:11፤ 12:7–9
ይሖዋ የሥርዓት አምላክ ስለሆነ በጣም ሰፊ የሆነው መላእክታዊ ቤተሰቡ የተደራጀ መሆኑ አያስደንቅም።—1 ቆሮንቶስ 14:33
• በኃይልም ሆነ በሥልጣን ከሁሉ የሚበልጠው ሊቀ መልአክ ኢየሱስ ሲሆን ሚካኤል የሚልም ስም አለው። (1 ተሰሎንቄ 4:16፤ ይሁዳ 9) በእርሱ ሥልጣን ሥር ሱራፌሎች፣ ኪሩቤሎችና መላእክት አሉ።
• ሱራፌሎች ከአምላክ ዙፋን አካባቢ አይጠፉም። ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው የሥራ ምድባቸው የአምላክን ቅድስና ማወጅና የአምላክ ሕዝቦች ንጽሕናቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ማድረግ ነው።—ኢሳይያስ 6:1–3, 6, 7
• ኪሩቤሎች ልክ እንደ ሱራፌሎች በይሖዋ ፊት ታይተዋል። የአምላክ ዙፋን ተሸካሚዎች ወይም አጃቢዎች እንደመሆናቸው መጠን የይሖዋን ታላቅነት ያስከብራሉ።—መዝሙር 80:1፤ 99:1፤ ሕዝቅኤል 10:1, 2
• መላእክት (“መልእክተኞች” ማለት ነው) የይሖዋ ወኪሎችና እንደራሴዎች ናቸው። የአምላክን ሕዝቦች በመታደግም ሆነ ክፉዎችን በማጥፋት መለኮታዊውን ፈቃድ ይፈጽማሉ።—ዘፍጥረት 19:1–26
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰማይ መካከል የሚበርረውን መልአክ እያዳመጥክ ነውን?