ምዕራፍ 16
“ወደ መቄዶንያ ተሻገር”
የአገልግሎት ምድብ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆንና ስደትን በደስታ መቋቋም በረከት ያስገኛል
በሐዋርያት ሥራ 16:6-40 ላይ የተመሠረተ
1-3. (ሀ) መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስንና የጉዞ ጓደኞቹን የመራቸው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ነገሮች እንቃኛለን?
የተወሰኑ ሴቶች በመቄዶንያ ከምትገኘው የፊልጵስዩስ ከተማ እየወጡ ነው። ብዙም ሳይቆይ ጋንጂቲስ ወደተባለው ወንዝ ደረሱ። እንደ ልማዳቸውም ወንዙ ዳር ተቀምጠው ለእስራኤል አምላክ ይጸልዩ ጀመር። ይሖዋ እነዚህን ሴቶች ይመለከታቸው ነበር።—2 ዜና 16:9፤ መዝ. 65:2
2 ይህ በእንዲህ እንዳለ በስተ ምሥራቅ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተወሰኑ ወንዶች ጉዞ ጀምረዋል፤ በደቡባዊ ገላትያ ከምትገኘው የልስጥራ ከተማ እየወጡ ነው። ከቀናት ጉዞ በኋላ በስተ ምዕራብ ወደሚያቀና አንድ የሮማውያን አውራ ጎዳና ደረሱ፤ ይህ ጎዳና ብዙ ሕዝብ ወደሚኖርበት የእስያ አውራጃ ይወስዳል። መንገደኞቹ ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ ይህን መንገድ ይዘው መጓዝ ፈልገዋል፤ ስለ ክርስቶስ ያልሰሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚኖሩባቸው በኤፌሶንና በሌሎች ከተሞች ለመስበክ ጓጉተዋል። ይሁንና ገና ጉዟቸውን ከመጀመራቸው በፊት መንፈስ ቅዱስ ወደዚያ እንዳይሄዱ ከለከላቸው፤ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ያደረገው እንዴት እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ በእስያ እንዲሰብኩ አልተፈቀደላቸውም። ለምን? ኢየሱስ፣ ጳውሎስንና የጉዞ አጋሮቹን በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊመራቸው ስለፈለገ ነው፤ ትንሿን እስያ አቋርጠውና የኤጅያንን ባሕር ተሻግረው ጋንጂቲስ ወደሚባለው ትንሽ ወንዝ እንዲሄዱ ፈልጎ ነበር።
3 ኢየሱስ፣ ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ወደ መቄዶንያ ያደረጉትን ጉዞ ከመራበት መንገድ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። እስቲ በ49 ዓ.ም. ገደማ በጀመረው የጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞ ወቅት ከተከሰቱት ነገሮች መካከል የተወሰኑትን እንቃኝ።
“አምላክ . . . ጠርቶናል” (የሐዋርያት ሥራ 16:6-15)
4, 5. (ሀ) ጳውሎስና አብረውት የሚጓዙት ሰዎች ቢቲኒያ በደረሱ ጊዜ ምን አጋጠማቸው? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ምን ለማድረግ ወሰኑ? ውጤቱስ ምን ሆነ?
4 ጳውሎስና ባልደረቦቹ በእስያ እንዳይሰብኩ ስለተከለከሉ በቢቲኒያ ከተሞች ለመስበክ ወደ ሰሜን አቀኑ። ወደዚያ የሚወስደው መንገድ ለጉዞ አመቺ ተደርጎ የተሠራ አውራ ጎዳና አይደለም፤ ብዙ ሕዝብ ባልሰፈረባቸው በፍርግያና በገላትያ ክልሎች መካከል በጥርጊያ መንገድ ላይ ለብዙ ቀናት በእግራቸው ሳይጓዙ አልቀሩም። ይሁን እንጂ ወደ ቢቲኒያ ሲቃረቡ ኢየሱስ አሁንም በመንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞ ወደዚያ እንዳይገቡ አገዳቸው። (ሥራ 16:6, 7) በዚህ ጊዜ እነዚህ ወንድሞች ግራ ሳይጋቡ አልቀረም። ምን እንደሚሰብኩና እንዴት እንደሚሰብኩ ያውቃሉ፤ የት እንደሚሰብኩ ግን አያውቁም። ሁኔታውን በዚህ መልክ መግለጽ ይቻላል፦ ወደ እስያ የሚያስገባቸውን በር አንኳኩ፤ ሆኖም ሳይከፈትላቸው ቀረ። ወደ ቢቲኒያ የሚያስገባውን በር አንኳኩ፤ አሁንም አልተከፈተላቸውም። ጳውሎስ ግን የሚከፈትለት በር እስኪያገኝ ድረስ ማንኳኳቱን ለመቀጠል ቆርጦ ነበር። በዚህ ጊዜ ወንድሞች ምክንያታዊ የማይመስል ውሳኔ አደረጉ። ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ጉዞ ጀመሩ፤ በርካታ ከተሞችን እያለፉ 550 ኪሎ ሜትር ያህል በእግራቸው ከተጓዙ በኋላ ወደ ጥሮአስ ወደብ ደረሱ፤ ከዚህች ወደብ ወደ መቄዶንያ መሻገር ይቻላል። (ሥራ 16:8) በዚያም ጳውሎስ ለሦስተኛ ጊዜ በሩን አንኳኳ፤ በዚህ ጊዜ በሩ ወለል ብሎ ተከፈተ!
5 ከጳውሎስና ከጉዞ አጋሮቹ ጋር ጥሮአስ ላይ የተገናኘው ወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ቀጥሎ የሆነውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው በዚያ ቆሞ ‘ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን’ ብሎ ሲለምነው አየ። ጳውሎስ ይህን ራእይ እንዳየም ‘አምላክ ምሥራቹን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል’ የሚል መደምደሚያ ላይ ስለደረስን ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ሞከርን።”a (ሥራ 16:9, 10) በመጨረሻ ጳውሎስ የት እንደሚሰብክ አወቀ። ጉዞውን ከመሃል አቋርጦ ባለመመለሱ ምን ያህል ተደስቶ ይሆን! አራቱ ሰዎች ምንም ጊዜ ሳያባክኑ በመርከብ ወደ መቄዶንያ ተጓዙ።
6, 7. (ሀ) ጳውሎስ በጉዞው ላይ ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) የጳውሎስ ተሞክሮ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል?
6 ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? የአምላክ መንፈስ ጣልቃ የገባው ጳውሎስ ወደ እስያ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ በኋላ እንደሆነ ልብ በል፤ ኢየሱስም ለጳውሎስ መመሪያ የሰጠው ወደ ቢቲኒያ ከተቃረበ በኋላ ነው፤ በመጨረሻም ጳውሎስን ወደ መቄዶንያ የመራው ጥሮአስ ከደረሰ በኋላ ነው። ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል። (ቆላ. 1:18) ለምሳሌ፣ አቅኚ ለመሆን ወይም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደን ለማገልገል እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በአምላክ መንፈስ አማካኝነት የሚመራን፣ ግባችን ላይ ለመድረስ የሚያስችሉንን እርምጃዎች ከወሰድን በኋላ ሊሆን ይችላል። ለምን? የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ አንድ አሽከርካሪ መኪናውን ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ማዞር የሚችለው መኪናው እየተንቀሳቀሰ ከሆነ ብቻ ነው። በተመሳሳይም ኢየሱስ አገልግሎታችንን ልናሰፋ የምንችልበትን መንገድ የሚመራን እንቅስቃሴ ላይ ከሆንን ይኸውም ግባችን ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረግን ከሆነ ብቻ ነው።
7 ሆኖም ጥረታችን ወዲያው ፍሬ ባያፈራስ? የአምላክ መንፈስ እየመራን እንዳልሆነ በማሰብ ተስፋ ልንቆርጥ ይገባል? በፍጹም! ጳውሎስም እንቅፋቶች ገጥመውት እንደነበር አስታውስ። ይሁን እንጂ የሚከፈትለት በር እስኪያገኝ ድረስ መፈለጉን አላቆመም። እኛም በተመሳሳይ “ትልቅ የሥራ በር” እስክናገኝ ድረስ መፈለጋችንን ከቀጠልን በረከት እንደምናጭድ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮ. 16:9
8. (ሀ) የፊልጵስዩስ ከተማ ምን ትመስል እንደነበር ግለጽ። (ለ) ጳውሎስ በአንድ “የጸሎት ስፍራ” መስበኩ ምን አስደሳች ውጤት አስገኘ?
8 ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ መቄዶንያ አውራጃ ከደረሱ በኋላ ወደ ፊልጵስዩስ ተጓዙ፤ የዚህች ከተማ ነዋሪዎች በሮም ዜግነታቸው ይኮሩ ነበር። ፊልጵስዩስ ስፋቷ እንጂ ከሮም ጋር የሚያመሳስሏት ብዙ ነገሮች ነበሩ፤ በዚያ ለሚኖሩት ጡረታ የወጡ የሮም ወታደሮች ፊልጵስዩስ ትንሿ ሮም ነበረች። ከከተማዋ በር ውጭ አንድ ትንሽ ወንዝ አለ፤ ሚስዮናውያኑ በዚህ ወንዝ ዳር “የጸሎት ስፍራ” እንደሚኖር ጠብቀው ነበር።b በሰንበት ቀን ወደዚያ በወረዱ ጊዜ አምላክን ለማምለክ የተሰበሰቡ በርከት ያሉ ሴቶችን አገኙ። ደቀ መዛሙርቱም ተቀምጠው ያነጋግሯቸው ጀመር። ሊዲያ የተባለች አንዲት ሴት የሚናገሩትን “እያዳመጠች ነበር፤ ይሖዋም . . . ልቧን በደንብ ከፈተላት።” ሊዲያ ሚስዮናውያኑ በነገሯት ነገር ልቧ ስለተነካ እሷና በቤቷ የሚኖሩ ሰዎች ተጠመቁ። ከዚያም ቤቷ ገብተው በእንግድነት እንዲያርፉ ሚስዮናውያኑን ግድ አለቻቸው።c—ሥራ 16:13-15
9. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የጳውሎስን ምሳሌ የተከተሉት እንዴት ነው? ምን በረከትስ አግኝተዋል?
9 በእርግጥም የሊዲያ መጠመቅ ሚስዮናውያኑን ምን ያህል አስደስቷቸው እንደሚሆን መገመት ይቻላል! ጳውሎስ ‘ወደ መቄዶንያ እንዲሻገር’ የቀረበለትን ግብዣ በመቀበሉ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው እነዚያ ሴቶች ላቀረቡት ጸሎት ምላሽ ለመስጠት እሱንና የጉዞ ጓደኞቹን በመጠቀሙም ጳውሎስ እንደተደሰተ ጥያቄ የለውም። በዛሬው ጊዜ ወጣት፣ ሽማግሌ እንዲሁም ነጠላ፣ ባለትዳር ሳይል በርካታ ወንድሞችና እህቶች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው እያገለገሉ ነው። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው፤ ይሁንና ልክ እንደ ሊዲያ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚቀበሉ ሰዎችን ሲያገኙ የሚሰማቸው እርካታ ችግሩን የሚያስረሳ ነው። አንተስ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ‘ተሻግረህ’ ለማገልገል አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችል ይሆን? ይህን ማድረግህ በረከት ያስገኝልሃል። የአሮንን ምሳሌ እንመልከት፤ በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው አሮን አገልግሎቱን ለማስፋት በመካከለኛው አሜሪካ ወደሚገኝ አንድ አገር ሄዷል። ይህ ወንድም የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ የብዙዎችን ስሜት የሚገልጽ ነው፦ “ወደ ሌላ አገር ሄጄ ማገልገሌ መንፈሳዊነቴ እንዲጠናከርና ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድቀርብ ረድቶኛል። አገልግሎቱም ቢሆን አስደሳች ነው፤ ስምንት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናለሁ!”
“ሕዝቡም . . . በእነሱ ላይ ተነሳ” (የሐዋርያት ሥራ 16:16-24)
10. አጋንንት በጳውሎስና በጉዞ ጓደኞቹ ላይ ችግር እንዲፈጠር ያደረጉት እንዴት ነው?
10 ሰይጣን እሱም ሆነ አጋንንቱ እንደ ልብ ይፈነጩበት በነበረው አካባቢ ምሥራቹ ሥር መስደዱ እጅግ እንዳስቆጣው ጥርጥር የለውም። ስለሆነም አጋንንት በጳውሎስና በጉዞ ጓደኞቹ ላይ ችግር እንዲፈጠር ማድረጋቸው ምንም አያስገርምም! አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ እየሄዱ ሳለ በጥንቆላ ሥራዋ ለጌቶቿ ከፍተኛ ገቢ ታስገኝ ከነበረች አንዲት አገልጋይ ጋር ተገናኙ፤ የጥንቆላ ጋኔን ያደረባት ይህች ሴት እነጳውሎስን እየተከተለች “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚያውጁላችሁ የልዑሉ አምላክ ባሪያዎች ናቸው” በማለት ትጮኽ ጀመር። ጋኔኑ ይህች ሴት እንደዚያ እያለች እንድትጮኽ ያደረገው፣ የእሷ የጥንቆላ ሥራም ሆነ የጳውሎስ መልእክት ምንጩ አንድ እንደሆነ ለማስመሰል ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ሰዎች ለእውነተኞቹ የክርስቶስ ተከታዮች ትኩረት እንዳይሰጡ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ጳውሎስ ጋኔኑን ከሴትየዋ በማስወጣት ዝም አሰኛት።—ሥራ 16:16-18
11. ጋኔኑ ከሴትየዋ ከወጣ በኋላ ጳውሎስና ሲላስ ምን አጋጠማቸው?
11 ጌቶቿ የገቢ ምንጫቸው መድረቁን ባዩ ጊዜ እጅግ ተቆጡ። ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጎተቱ ወደ ገበያ ስፍራው ወሰዷቸው፤ ሮማውያን የሾሟቸው የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ለፍርድ የሚሰየሙት እዚህ ነው። ጌቶቿ፣ ባለሥልጣናቱ አይሁዳውያንን እንደሚጠሉና በሮማዊነታቸው እንደሚኮሩ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ‘እነዚህ አይሁዳውያን እኛ ሮማውያን ልንቀበለው የማይገባንን ልማድ በማስተማር ሽብር እየፈጠሩ ነው’ ብለው ከሰሷቸው። ያቀረቡት ክስ ወዲያውኑ ተደማጭነት አገኘ። በገበያ ስፍራው የነበረው ሕዝብ “በአንድነት በእነሱ [በጳውሎስና በሲላስ] ላይ ተነሳ”፤ የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎችም “በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ።” ከዚያም ጳውሎስንና ሲላስን ጎትተው እስር ቤት አስገቧቸው። የእስር ቤቱ ጠባቂ የተደበደቡትን ሰዎች ወደ እስር ቤቱ ውስጠኛ ክፍል ካስገባቸው በኋላ እግራቸውን በእግር ግንድ አሰረው። (ሥራ 16:19-24) በሩን ሲዘጋው ጳውሎስና ሲላስ እርስ በርሳቸው መተያየት እስከማይችሉ ድረስ ክፍሉ በጨለማ ተዋጠ። ይሖዋ ግን ያያቸው ነበር።—መዝ. 139:12
12. (ሀ) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለሚደርስባቸው ስደት ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው? ለምንስ? (ለ) ሰይጣንና ወኪሎቹ ተቃውሞ ለማስነሳት ምን ዘዴዎችን ይጠቀማሉ?
12 ከዓመታት በፊት ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ስደት ያደርሱባችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 15:20) በመሆኑም ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ወደ መቄዶንያ ሲሻገሩ ተቃውሞ እንደሚገጥማቸው መጠበቃቸው አይቀርም። ስለዚህ ስደት ሲደርስባቸው የይሖዋን ሞገስ እንዳጡ አልተሰማቸውም፤ ከዚህ ይልቅ የሰይጣን ቁጣ መግለጫ እንደሆነ ያውቃሉ። ዛሬም ቢሆን የሰይጣን ወኪሎች፣ ተቃዋሚዎች በፊልጵስዩስ የተጠቀሙበትን ዓይነት ዘዴ ይጠቀማሉ። አንዳንድ አታላይ የሆኑ ተቃዋሚዎች በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ቦታ የተዛባ ወሬ በማናፈስ ስደት ለመቆስቆስ ይጥራሉ። በአንዳንድ አገሮች የሃይማኖት መሪዎች፣ የማኅበረሰቡን “ወግ ልማድ” የሚሽር ትምህርት በማስተማር ሁከት እያስነሳን እንደሆነ በመግለጽ ፍርድ ቤት ፊት ይወነጅሉናል። የእምነት ባልንጀሮቻችን የተደበደቡባቸውና እስር ቤት የተጣሉባቸው ቦታዎችም አሉ። ይሖዋ ግን ይህን ሁሉ ያያል።—1 ጴጥ. 3:12
“ወዲያውኑ ተጠመቁ” (የሐዋርያት ሥራ 16:25-34)
13. የእስር ቤቱ ጠባቂ “ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” ብሎ እንዲጠይቅ ያደረገው ምንድን ነው?
13 ጳውሎስና ሲላስ በዚያ ቀን ከደረሰባቸው እንግልት በኋላ ራሳቸውን ለማረጋጋት የተወሰነ ጊዜ አስፈልጓቸው መሆን አለበት። ይሁንና እኩለ ሌሊት አካባቢ፣ ሁሉን ነገር ረስተው “እየጸለዩና አምላክን በመዝሙር እያወደሱ ነበር።” በዚህ መሃል ድንገት የምድር ነውጥ ተከስቶ እስር ቤቱን አናጋው! የእስር ቤቱ ጠባቂ ከእንቅልፉ ሲነቃ በሮቹ መከፈታቸውን አየ፤ በዚህ ጊዜ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ደነገጠ። ይህ የሚያስከትልበትን ቅጣት ስላወቀ “ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ።” ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ “በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ! ሁላችንም እዚህ አለን” ሲል ተናገረ። የእስር ቤቱ ጠባቂም በፍርሃት እየተርበተበተ “ጌቶቼ፣ ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” በማለት ጠየቀ። ጳውሎስና ሲላስ ሊያድኑት አይችሉም፤ ሊያድነው የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው። በመሆኑም “በጌታ ኢየሱስ እመን፤ [ትድናለህ]” አሉት።—ሥራ 16:25-31
14. (ሀ) ጳውሎስና ሲላስ ለእስር ቤቱ ጠባቂ ምን አደረጉለት? (ለ) የደረሰባቸውን ስደት በደስታ መቋቋማቸው ምን በረከት አስገኝቶላቸዋል?
14 እውነት የእስር ቤቱ ጠባቂ ጥያቄ ከቅንነት የመነጨ ነው? ጳውሎስ የሰውየውን ቅንነት አልተጠራጠረም። ጠባቂው አይሁዳዊ አይደለም፤ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ምንም እውቀት የለውም። ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት መሠረታዊ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን መማርና አምኖ መቀበል ያስፈልገው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስና ሲላስ ጊዜ ወስደው ‘የይሖዋን ቃል ነገሩት።’ እነዚህ ወንድሞች ትኩረታቸው ሁሉ ያረፈው ቅዱሳን መጻሕፍትን በማስተማር ላይ ስለነበር ድብደባው ያስከተለባቸውን ሕመም ረስተውት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ የእስር ቤቱ ጠባቂ ጀርባቸው መቁሰሉን ስላስተዋለ ቁስሉን አጠበላቸው። ከዚያም እሱም ሆነ መላው ቤተሰቡ “ወዲያውኑ ተጠመቁ።” በእርግጥም ጳውሎስና ሲላስ የደረሰባቸውን ስደት በደስታ መቋቋማቸው በረከት አስገኝቶላቸዋል!—ሥራ 16:32-34
15. (ሀ) ዛሬ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የጳውሎስንና የሲላስን ምሳሌ የተከተሉት እንዴት ነው? (ለ) በክልላችን ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በተደጋጋሚ ቤታቸው እየሄድን ማነጋገር ያለብን ለምንድን ነው?
15 እንደ ጳውሎስና ሲላስ ሁሉ ዛሬ ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች፣ በእምነታቸው ምክንያት ታስረውም ምሥራቹን ይሰብካሉ፤ ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። የስብከት ሥራችን በታገደበት አንድ አገር ውስጥ የሆነውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ በአንድ ወቅት በአገሪቱ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት እውነትን የተማሩት እስር ቤት ሳሉ ነበር! (ኢሳ. 54:17) ልብ ልንለው የሚገባ ሌላም ነገር አለ፦ የእስር ቤቱ ጠባቂ እርዳታ ለማግኘት ጥያቄ ያቀረበው የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ በኋላ ነው። በተመሳሳይም ዛሬ፣ የመንግሥቱን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበሩ ሰዎች እንደ ነውጥ ያለ ድንገተኛ መከራ ከገጠማቸው በኋላ ጆሮ ይሰጡ ይሆናል። በክልላችን ወዳሉት ሰዎች ደጋግመን መሄዳችን ምሥራቹን ለመስማት ዝግጁ በሚሆኑበት ወቅት እነሱን ለመርዳት ያስችለናል።
“ታዲያ አሁን በድብቅ አስወጥተው ሊጥሉን ይፈልጋሉ?” (የሐዋርያት ሥራ 16:35-40)
16. ጳውሎስና ሲላስ በተገረፉ ማግስት ነገሩ የተገላቢጦሽ የሆነው እንዴት ነው?
16 ጳውሎስና ሲላስ በተገረፉ ማግስት የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ሁለቱ ሰዎች እንዲፈቱ ትእዛዝ አስተላለፉ። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “እኛ የሮም ዜጎች ሆነን ሳለ ያለፍርድ በሕዝብ ፊት ገርፈው እስር ቤት ወረወሩን። ታዲያ አሁን በድብቅ አስወጥተው ሊጥሉን ይፈልጋሉ? እንዲህማ አይሆንም! እነሱ ራሳቸው መጥተው ይዘውን ይውጡ።” የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች፣ ሁለቱ ሰዎች ሮማውያን መሆናቸውን ሲሰሙ “ፍርሃት አደረባቸው”፤ ምክንያቱም የሰዎቹን መብት ጥሰዋል።d አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱ የተደበደቡት በሕዝብ ፊት ነበር፤ በመሆኑም ሕግ አስከባሪዎቹ በሕዝብ ፊት ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱም ጳውሎስንና ሲላስን ለመኗቸው። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ይህን ለማድረግ ተስማሙ፤ ከከተማዋ ከመውጣታቸው በፊት ግን ጊዜ ወስደው አዳዲሶቹን ደቀ መዛሙርት አበረታቷቸው። ከተማዋን ለቀው የሄዱት ይህን ካደረጉ በኋላ ነው።
17. አዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ጳውሎስና ሲላስ ካሳዩት ጽናት ምን ጠቃሚ ትምህርት ያገኛሉ?
17 ጳውሎስና ሲላስ ገና ከመነሻው የሮም ዜግነት መብታቸው እንዲከበርላቸው አድርገው ቢሆን ኖሮ ከመገረፍ ይድኑ ነበር። (ሥራ 22:25, 26) ይህ ግን በፊልጵስዩስ በነበሩት ደቀ መዛሙርት ላይ የሚፈጥረውን ስሜት አስበው፤ ጳውሎስና ሲላስ መብታቸውን በመጠቀም፣ ለክርስቶስ ሲሉ ከሚደርስባቸው ሥቃይ ራሳቸውን ለማዳን እንደሞከሩ ሊሰማቸው ይችል ነበር። የሮም ዜግነት የሌላቸው ደቀ መዛሙርትስ ምን ይሰማቸዋል? ሕጉ ከመገረፍ ሊያድናቸው እንደማይችል የታወቀ ነው። ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ቅጣቱን አሜን ብለው የተቀበሉት ለዚህ ነው፤ የክርስቶስ ተከታዮች የሚደርስባቸውን ስደት በጽናት መቋቋም እንደሚችሉ ለአዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ምሳሌ ሆነው አሳይተዋል። በተጨማሪም ጳውሎስና ሲላስ በኋላ ላይ የዜግነት መብታቸው እንዲከበርላቸው ስለጠየቁ የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ሕገ ወጥ ድርጊት እንደፈጸሙ በይፋ ለማመን ተገድደዋል። ይህ ደግሞ ወደፊት የጳውሎስን የእምነት ባልንጀሮች ከማንገላታታቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ ምናልባትም ወደፊት ተመሳሳይ የሆነ ጥቃት እንዳይፈጸም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሕግ ከለላ ያስገኛል።
18. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው? (ለ) በዘመናችን ‘ለምሥራቹ መሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ’ የምንችለው በምን መንገድ ነው?
18 በዛሬው ጊዜም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ የበላይ ተመልካቾች ሌሎችን የሚመሩት ምሳሌ በመሆን ነው። የእምነት ባልንጀሮቻቸው እንዲፈጽሙ የሚፈልጉትን ማንኛውንም ነገር እነሱ ራሳቸው ለመፈጸም ፈቃደኞች ናቸው። በተጨማሪም እኛም እንደ ጳውሎስ ከለላ ለማግኘት ሕጋዊ መብታችንን እንዴትና መቼ መጠቀም እንዳለብን በጥንቃቄ መመዘን ይኖርብናል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ፣ አምልኳችንን ለማከናወን የሚያስችለን ሕጋዊ ከለላ ለማግኘት በአካባቢያችንና በአገራችን ላሉ አልፎ ተርፎም ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ‘አቤት’ እንላለን። ዓላማችን ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣት አይደለም፤ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ከታሰረ ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ በዚያ ለነበረው ጉባኤ ሲጽፍ እንደተናገረው ዓላማችን ‘ለምሥራቹ መሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ’ ነው። (ፊልጵ. 1:7) እነዚህ ፍርድ ቤቶች የሚያስተላልፉት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን፣ የጳውሎስንና የጉዞ ጓደኞቹን ምሳሌ እንከተላለን፤ የአምላክ መንፈስ በሚመራን ቦታ ሁሉ ‘ምሥራቹን መስበካችንን’ እንቀጥላለን።—ሥራ 16:10
a “ሉቃስ—የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b የፊልጵስዩስ ከተማ የወታደሮች መኖሪያ ስለነበረች በዚያ የሚኖሩ አይሁዳውያን በከተማዋ ውስጥ ምኩራብ እንዳይሠሩ ተከልክለው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በከተማዋ ውስጥ አሥር አይሁዳውያን ወንዶች አልነበሩም ይሆናል፤ በአንድ ከተማ ውስጥ ምኩራብ እንዲኖር ቢያንስ አሥር ወንዶች መኖር ነበረባቸው።
c “ሊዲያ—የሐምራዊ ጨርቅ ነጋዴ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
d በሮማውያን ሕግ መሠረት ዜጎች ምንጊዜም ጉዳያቸው በተገቢው መንገድ ችሎት ፊት ሊታይ ይገባል፤ እንዲሁም አንድ ሰው ጥፋተኛ እንደሆነ ሳይፈረድበት በሕዝብ ፊት አይቀጣም።