ክርስቲያኖች ሰንበትን ማክበር ይኖርባቸዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ክርስቲያኖች ሳምንታዊውን ሰንበት ማክበር አይጠበቅባቸውም። ክርስቲያኖች ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ናቸው፤ ይህ ሕግ ደግሞ ሰንበት ማክበርን አይጨምርም። (ገላትያ 6:2፤ ቆላስይስ 2:16, 17) ይህን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? እስቲ በመጀመሪያ ሰንበትን ማክበር የተጀመረው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ሰንበት ምንድን ነው?
“ሰንበት” የሚለው ቃል “ማረፍ፤ ማቆም” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው ለጥንት እስራኤላውያን በተሰጠው ትእዛዝ ላይ ነው። (ዘፀአት 16:23) ለምሳሌ ያህል፣ የአሥርቱ ትእዛዛት አራተኛ ሕግ እንዲህ ይላል፦ “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ። ሥራህንና የምታከናውናቸውን ነገሮች በሙሉ በስድስት ቀን ሠርተህ አጠናቅ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለይሖዋ ሰንበት ነው። በዚህ ቀን . . . ምንም ሥራ አትሥሩ።” (ዘፀአት 20:8-10) የሰንበት ቀን የሚባለው ዓርብ ፀሐይ ከጠለቀችበት አንስቶ ቅዳሜ ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ድረስ ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ እስራኤላውያን ከሰፈራቸው ርቀው አይሄዱም፣ እሳት አያቀጣጥሉም፣ እንጨት አይሰበስቡም ወይም ምንም ዓይነት ሸክም አይሸከሙም። (ዘፀአት 16:29፤ 35:3፤ ዘኁልቁ 15:32-36፤ ኤርምያስ 17:21) የሰንበትን ሕግ መጣስ በሞት ያስቀጣል።—ዘፀአት 31:15
በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ሰባተኛውና ሃምሳኛው ዓመት እንዲሁም አንዳንድ ቀናት ሰንበት ተብለው ይጠሩ ነበር። በሰንበት ዓመት መሬቱ ሳይታረስ ይተው የነበረ ሲሆን ዕዳ ያለባቸው እስራኤላውያንም ዕዳቸው ይሰረዝላቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 16:29-31፤ 23:6, 7, 32፤ 25:4, 11-14፤ ዘዳግም 15:1-3
የሰንበት ሕግ በክርስቲያኖች ላይ የማይሠራው ለምንድን ነው?
የሰንበት ሕግ ይሠራ የነበረው በሙሴ በኩል የእረፍት ሕግ በተሰጣቸው ሕዝቦች ላይ ብቻ ነው። (ዘዳግም 5:2, 3፤ ሕዝቅኤል 20:10-12) አምላክ ሌሎች ሕዝቦች የሰንበትን ሕግ እንዲያከብሩ አይጠብቅባቸውም ነበር። ከዚህም በላይ አይሁዳውያንም ቢሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አሥሩን ትእዛዛት ጨምሮ በሙሴ በኩል ከተሰጣቸው ‘ሕግ ነፃ ወጥተዋል።’ (ሮም 7:6, 7፤ 10:4፤ ገላትያ 3:24, 25፤ ኤፌሶን 2:15) ክርስቲያኖች የሚመሩት በሙሴ ሕግ ሳይሆን ከዚያ በሚልቀው የፍቅር ሕግ ነው።—ሮም 13:9, 10፤ ዕብራውያን 8:13
ሰዎች ስለ ሰንበት ያሏቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች
የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ ሰንበትን ያቋቋመው በሰባተኛው ቀን ከሥራው ባረፈበት ጊዜ ነው።
እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና።” (ዘፍጥረት 2:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይህ ጥቅስ የሚናገረው ለሰው ሕግ እንደተሰጠው ሳይሆን አምላክ በሰባተኛው የፍጥረት ቀን ምን እንዳደረገ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከሙሴ ዘመን በፊት ሰዎች ሰንበትን ያከብሩ እንደነበረ አይናገርም።
የተሳሳተ አመለካከት፦ እስራኤላውያን የሙሴ ሕግ ከመሰጠቱ በፊትም በሰንበት ሕግ ሥር ነበሩ።
እውነታው፦ ሙሴ “ይሖዋ በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል” በማለት ለእስራኤላውያን ተናግሮ ነበር፤ ኮሬብ ሲና ተራራ አካባቢ የሚገኝ ቦታ ነው። ይህ ቃል ኪዳን የሰንበትን ሕግ ይጨምራል። (ዘዳግም 5:2, 12) ከእስራኤላውያን ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው የሰንበት ሕግ ለእነሱ አዲስ ነበር። እስራኤላውያን በግብፅ ሳሉ በሰንበት ሕግ ሥር ቢሆኑ ኖሮ ‘የሰንበትን ቀን የምታከብሩት ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣታችሁን እንዲያስታውሳችሁ ነው’ ብሎ አምላክ ይነግራቸው ነበር? (ዘዳግም 5:15) በተጨማሪም በሰባተኛው ቀን መና እንዳይሰበስቡ ይነገራቸው ነበር? (ዘፀአት 16:25-30) የሰንበትን ሕግ በጣሰው በመጀመሪያው ሰው ላይ ምን እርምጃ እንደሚወሰድበት ማወቅ ይቸግራቸው ነበር?—ዘኁልቁ 15:32-36
የተሳሳተ አመለካከት፦ የሰንበት ሕግ የዘላለም ቃል ኪዳን ስለሆነ አሁንም ይሠራል።
እውነታው፦ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሰንበትን “የዘላለም ኪዳን” በማለት ገልጸውታል። (ዘፀአት 31:16 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይሁን እንጂ፣ “የዘላለም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ላልተወሰነ ጊዜ” የሚል ትርጉምም ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ከ2,000 ዓመት በፊት እንዲቋረጥ ስላደረገው በእስራኤል የነበረ የክህነት ሥርዓት ለመግለጽ ተመሳሳይ ቃል ይጠቀማል።—ዘፀአት 40:15፤ ዕብራውያን 7:11, 12
የተሳሳተ አመለካከት፦ ኢየሱስ ሰንበትን ስለጠበቀ ክርስቲያኖችም መጠበቅ አለባቸው።
እውነታው፦ ኢየሱስ ሰንበትን የጠበቀው አይሁዳዊ በመሆኑ የሙሴን ሕግ የመጠበቅ ግዴታ ስለነበረበት ነው። (ገላትያ 4:4) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሰንበትን ጨምሮ የሕጉ ቃል ኪዳን ተወግዷል ወይም ተሽሯል።—ቆላስይስ 2:13, 14
የተሳሳተ አመለካከት፦ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላም እንኳ ሰንበትን ጠብቋል።
እውነታው፦ ጳውሎስ በሰንበት ወደ ምኩራብ ገብቷል፤ ይህን ያደረገው ግን ከአይሁዳውያን ጋር ሥርዓቱን ለማክበር አልነበረም። (የሐዋርያት ሥራ 13:14፤ 17:1-3፤ 18:4) ከዚህ ይልቅ በዘመኑ በነበረው ልማድ መሠረት ለአምልኮ የተሰበሰቡ ሰዎችን እንዲያስተምር የቀረበለትን ግብዣ ተቀብሎ ምሥራቹን በምኩራብ ለመስበክ ሊሆን ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 13:15, 32) ጳውሎስ በሰንበት ቀን ብቻ ሳይሆን “በየዕለቱ” ይሰብክ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 17:17
የተሳሳተ አመለካከት፦ እሁድ የክርስቲያኖች ሰንበት ነው።
እውነታው፦ ክርስቲያኖች እሁድን ማለትም የሳምንቱን የመጀመሪያ ቀን ለእረፍትና ለአምልኮ እንዲጠቀሙበት የሚገልጽ ትእዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ለጥንት ክርስቲያኖች እሁድ እንደ ሌሎቹ ቀናት ሁሉ የሥራ ቀን ነበር። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “እሁድ እንደ ሰንበት ተቆጥሮ መከበር የጀመረው ቆስጠንጢኖስ በ4ኛው መቶ ዘመን አንዳንድ የሥራ ዓይነቶች እሁድ ዕለት መሠራት እንደሌለባቸው ከደነገገበት ጊዜ አንስቶ ነው።”a
እሁድ የተለየ ቀን እንደሆነ የሚጠቁሙ ጥቅሶችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን” ማለትም እሁድ ዕለት ከእምነት አጋሮቹ ጋር ምግብ እንደበላ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ይሁንና ጳውሎስ በማግሥቱ ከእነሱ ተለይቶ ወደ ሌላ አካባቢ ይሄድ ስለነበር እንዲህ ማድረጉ የሚጠበቅ ነገር ነው። (የሐዋርያት ሥራ 20:7) በተመሳሳይም አንዳንድ ጉባኤዎች “በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን” ማለትም እሁድ ዕለት ለእርዳታ የሚሆን ገንዘብ እንዲያስቀምጡ ተነግሯቸው ነበር፤ ሆኖም ይህ ገንዘብ አያያዝን በሚመለከት ለክርስቲያኖች የተሰጠ ምክር ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች መዋጮውን የሚያስቀምጡት በመሰብሰቢያ ቦታቸው ሳይሆን በቤታቸው ነው።—1 ቆሮንቶስ 16:1, 2
የተሳሳተ አመለካከት፦ በየሳምንቱ ለእረፍት ወይም ለአምልኮ የሚሆን አንድ ቀን መመደብ ስህተት ነው።
እውነታው፦ ይህ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የተተወ ውሳኔ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሮም 14:5
a በተጨማሪም የሚከተለውን ተመልከት፦ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ ሁለተኛ እትም፣ ጥራዝ 13፣ ገጽ 608