ምዕራፍ 19
“መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል”
ጳውሎስ መተዳደሪያ ለማግኘት ቢሠራም ቅድሚያ የሚሰጠው ለአገልግሎቱ ነው
በሐዋርያት ሥራ 18:1-22 ላይ የተመሠረተ
1-3. ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የመጣው ለምንድን ነው? ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎችስ ገጥመውታል?
ጊዜው በ50 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አሁን ያለው ቆሮንቶስ ውስጥ ነው፤ ይህች ከተማ በርካታ ግሪካውያን፣ ሮማውያንና አይሁዳውያን የሚኖሩባት የበለጸገች የንግድ ማዕከል ነች።a ጳውሎስ ወደዚህች ከተማ የመጣው ለመገበያየት ወይም ሥራ ለመፈለግ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን ሥራ ለማከናወን ይኸውም ስለ አምላክ መንግሥት ለመመሥከር ነው። ያም ሆኖ ጳውሎስ የሚያርፍበት ቦታ ያስፈልገዋል፤ ደግሞም በቁሳዊ ነገሮች ረገድ በሌሎች ላይ ሸክም ላለመሆን ቆርጧል። አገልግሎቱን ቁሳዊ ጥቅም ማግኛ አድርጎ እንደሚጠቀምበት የሚያስመስል ነገር ማድረግ አልፈለገም። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን?
2 ጳውሎስ ድንኳን የመስፋት ሙያ ነበረው። ድንኳን መስፋት አድካሚ ሥራ ቢሆንም መተዳደሪያ ለማግኘት ሲል ይህን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነው። ታዲያ ሰዎች በሚተራመሱባት በዚህች ከተማ ውስጥ ሥራ ያገኝ ይሆን? የሚያርፍበት አመቺ ቦታስ? እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ዋነኛ ሥራውን ይኸውም አገልግሎቱን አልዘነጋም።
3 ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለተወሰነ ጊዜ መሰንበቱ አልቀረም፤ በዚያ ያከናወነው አገልግሎትም ብዙ ፍሬ አፍርቷል። እንግዲያው በቆሮንቶስ ያከናወናቸውን ነገሮች በመመርመር በክልላችን ውስጥ ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ ስለ መመሥከር የምናገኘውን ትምህርት እንመልከት።
“ሙያቸው . . . ድንኳን መሥራት ነበር” (የሐዋርያት ሥራ 18:1-4)
4, 5. (ሀ) ጳውሎስ ቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ያረፈው የት ነው? መተዳደሪያ ለማግኘት ምን ይሠራ ነበር? (ለ) ጳውሎስ ድንኳን የመሥራት ሙያ የተማረው እንዴት ሊሆን ይችላል?
4 ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ከሄደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቂላ ከተባለ አይሁዳዊና ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር ተገናኘ፤ እነዚህ ሰዎች በእንግዳ ተቀባይነታቸው የሚታወቁ ነበሩ። ባልና ሚስቱ ወደ ቆሮንቶስ የሄዱት ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ “አይሁዳውያን ሁሉ ከሮም እንዲወጡ” ስላዘዘ ነው። (ሥራ 18:1, 2) አቂላና ጵርስቅላ፣ ጳውሎስ አብሯቸው እንዲኖር ብቻ ሳይሆን ከእነሱ ጋር እንዲሠራም አድርገዋል። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ሙያቸው አንድ ዓይነት በመሆኑ እነሱ ቤት ተቀምጦ አብሯቸው ይሠራ ነበር፤ ሙያቸውም ድንኳን መሥራት ነበር።” (ሥራ 18:3) ጳውሎስ በቆሮንቶስ ባገለገለበት ወቅት ያረፈው፣ ደግና እንግዳ ተቀባይ በሆኑት በእነዚህ ባልና ሚስት ቤት ነው። ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን አንዳንዶቹን ደብዳቤዎች የጻፈው ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ይኖር በነበረበት ጊዜ ሊሆን ይችላል።b
5 “በገማልያል እግር ሥር” ተቀምጦ የተማረው ጳውሎስ የድንኳን ሥራ ሙያም ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? (ሥራ 22:3) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ለልጆቻቸው የእጅ ሙያ ማስተማር የሚያሳፍራቸው አይመስልም፤ በእርግጥ ልጆቹ ተጨማሪ ትምህርት እንዲከታተሉም ያደርጉ ነበር። ጳውሎስ በኪልቅያ የምትገኘው የጠርሴስ ሰው ነው፤ ለድንኳን ሥራ የሚያገለግለው ሰለሲየም የተባለው ጨርቅ በብዛት የሚመረተው እዚህ አካባቢ ነው፤ በመሆኑም የድንኳን ሥራን በልጅነቱ ተምሮ ሊሆን ይችላል። ድንኳን መሥራት ምን ነገሮችን ይጨምራል? የድንኳኑን ጨርቅ መሸመንን ወይም ሸካራና ጠንካራ የሆነውን ይህን ጨርቅ መቁረጥና መስፋትን ሊጨምር ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሥራው በጣም አድካሚ ነው።
6, 7. (ሀ) ጳውሎስ ድንኳን የመሥራት ሙያውን እንዴት ይመለከተው ነበር? አቂላና ጵርስቅላም ተመሳሳይ አመለካከት እንደነበራቸው የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች የጳውሎስን፣ የአቂላንና የጵርስቅላን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?
6 ጳውሎስ ይህን ሙያውን እንደ ዋነኛ ሥራው አድርጎ አልተመለከተውም። ይህን ሥራ የሚሠራው፣ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማሟላትና ምሥራቹን “ያለዋጋ” ለመስበክ ነው። (2 ቆሮ. 11:7) አቂላና ጵርስቅላስ ለዚህ ሙያቸው ምን አመለካከት ነበራቸው? ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ለሰብዓዊ ሥራቸው የጳውሎስ ዓይነት አመለካከት እንደነበራቸው ግልጽ ነው። እንዲያውም ጳውሎስ በ52 ዓ.ም. ቆሮንቶስን ለቅቆ ወደ ኤፌሶን ሲሄድ አቂላና ጵርስቅላ ንግዳቸውን ትተው ተከትለውታል፤ ኤፌሶን ከሄዱ በኋላም ቤታቸው ለጉባኤው መሰብሰቢያ ሆኖ አገልግሏል። (1 ቆሮ. 16:19) ከጊዜ በኋላ ወደ ሮም የተመለሱ ሲሆን ከዚያም እንደገና ወደ ኤፌሶን ሄደዋል። እነዚህ ቀናተኛ ባልና ሚስት መንግሥቱን ያስቀደሙ ከመሆኑም ሌላ ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ሌሎችን አገልግለዋል፤ በዚህም ምክንያት “በአሕዛብ መካከል የሚገኙ ጉባኤዎች” ሁሉ አመስግነዋቸዋል።—ሮም 16:3-5፤ 2 ጢሞ. 4:19
7 በዘመናችን የሚገኙ ክርስቲያኖችም የጳውሎስን፣ የአቂላንና የጵርስቅላን ምሳሌ ይከተላሉ። እነዚህ ቀናተኛ አገልጋዮች ሌሎችን “ብዙ ወጪ በማስወጣት ሸክም [ላለመሆን]” ሲሉ ተግተው ይሠራሉ። (1 ተሰ. 2:9) በርካታ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ሲሉ በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት ወይም በዓመት ለተወሰኑ ወራት ይሠራሉ፤ ሆኖም ቅድሚያውን የሚሰጡት ለክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው በመሆኑ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። እንደ አቂላና ጵርስቅላ እንግዳ ተቀባይ የሆኑ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችም አሉ፤ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን ቤታቸው ተቀብለው ያስተናግዳሉ። በዚህ መንገድ “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” ያዳበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረግ ምን ያህል እንደሚያበረታታና እንደሚያንጽ ያውቃሉ።—ሮም 12:13
“በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር” (የሐዋርያት ሥራ 18:5-8)
8, 9. ጳውሎስ ለአይሁዳውያን በትጋት መስበኩ የመረረ ተቃውሞ ሲያስከትልበት ምን አደረገ? ከዚያ በኋላስ ለመስበክ ወዴት ሄደ?
8 ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ የተለያዩ ስጦታዎችን ይዘው መጡ፤ ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ያደረገው ነገር በግልጽ እንደሚያሳየው ሰብዓዊ ሥራ ይሠራ የነበረው አገልግሎቱን ሲያከናውን ኑሮውን ለመደጎም እንዲያግዘው ብቻ ነው። (2 ቆሮ. 11:9) ዘገባው እንደሚገልጸው ጳውሎስ ወዲያውኑ “ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠመደ [“በማስተማር ጊዜውን ሁሉ ያሳልፍ ነበር፣” የ1980 ትርጉም]።” (ሥራ 18:5) ይሁን እንጂ ይህ የስብከት እንቅስቃሴ ከአይሁዳውያን ዘንድ የመረረ ተቃውሞ ገጠመው። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ሕይወት አድን መልእክት ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ከዚያ በኋላ በኃላፊነት እንደማይጠየቅ ለማሳየት ልብሱን አራገፈ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን። እኔ ንጹሕ ነኝ። ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ።”—ሥራ 18:6፤ ሕዝ. 3:18, 19
9 ታዲያ ጳውሎስ ከዚህ በኋላ የት ይሰብክ ይሆን? ቲቶስ ኢዮስጦስ የተባለ አንድ ሰው ቤቱን ከፈተለት፤ ይህ ሰው ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሳይሆን አይቀርም፤ በምኩራቡ አጠገብ የሚገኘውን ቤቱን እንዲጠቀምበት ለጳውሎስ ፈቀደለት። ስለዚህ ጳውሎስ ምኩራቡን ለቅቆ ወደ ኢዮስጦስ ቤት ገባ። (ሥራ 18:7) ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሳለ የሚኖረው በአቂላና በጵርስቅላ ቤት ነው፤ የስብከት ሥራውን የሚያከናውነው ግን በኢዮስጦስ ቤት ነበር።
10. ጳውሎስ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ሰዎች ብቻ ለመስበክ ወስኖ እንዳልነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
10 ጳውሎስ “ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” ማለቱ አይሁዳውያንንም ሆነ ወደ ይሁዲነት የተለወጡትን ሰዎች ጨርሶ እንደተዋቸው የሚያሳይ ነው? መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ለሚሆኑት እንኳ ትኩረት አይሰጥም ማለት ነው? ይህ ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ ያህል፣ “የምኩራብ አለቃው ቀርስጶስ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ” የሚል ዘገባ እናነባለን። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በምኩራቡ ይሰበሰቡ ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎች ቀርስጶስ የወሰደው ዓይነት እርምጃ ወስደዋል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ይጠመቁ ጀመር” ይላል። (ሥራ 18:8) በመሆኑም በቆሮንቶስ የተቋቋመው አዲስ ጉባኤ በቲቶስ ኢዮስጦስ ቤት መሰብሰብ ጀመረ። ሉቃስ ይህን ዘገባ የጻፈው እንደተለመደው በጊዜ ቅደም ተከተል ከሆነ እነዚህ አይሁዳውያንም ሆኑ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ክርስትናን የተቀበሉት ጳውሎስ ልብሱን ካራገፈ በኋላ ነው። ይህም ስለ ሐዋርያው የሚነግረን ቁም ነገር አለ፤ ጳውሎስ ምሥራቹን ሲሰብክ እንደ ሁኔታው ማስተካከያ የሚያደርግ ሰው ነበር።
11. ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ላሉ ሰዎች በሚሰብኩበት ጊዜ የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?
11 በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በብዙ አገሮች ውስጥ ረጅም ዘመን አስቆጥረዋል፤ በአባሎቻቸው ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በአንዳንድ አገሮችና ደሴቶች ላይ የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ብዙዎችን ወደ ሃይማኖታቸው ማምጣት ችለዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ እንደነበሩት አይሁዳውያን ሁሉ ዛሬም ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች በወግ የተተበተቡ ናቸው። ያም ቢሆን እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ልክ እንደ ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች በቅንዓት እንሰብካለን፤ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ካላቸው መጠነኛ እውቀት ተነስተን ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንሞክራለን። ቢቃወሙን ወይም የሃይማኖት መሪዎቻቸው ስደት ቢያደርሱብንም ተስፋ አንቆርጥም። እነዚህ ሰዎች “ለአምላክ ቅንዓት [ቢኖራቸውም] ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም”፤ ከእነሱ መካከል ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ የሚፈልጉ ብዙ ቅኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ እነሱን ፈልገን ማግኘት ይኖርብናል።—ሮም 10:2
“በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝ” (የሐዋርያት ሥራ 18:9-17)
12. ጳውሎስ በራእይ ምን ማረጋገጫ ተሰጠው?
12 ጳውሎስ በቆሮንቶስ አገልግሎቱን መቀጠል ይኖርበት እንደሆነና እንዳልሆነ ጥያቄ ተፈጥሮበት ይሆን? ከሆነም ጌታ ኢየሱስ ሌሊት በራእይ ሲገለጥለት መልሱን ሊያገኝ ነው፤ እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፤ መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ ማንም አንተን ሊያጠቃና ሊጎዳህ አይችልም፤ በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝና።” (ሥራ 18:9, 10) እንዴት የሚያበረታታ ራእይ ነው! ጳውሎስ ምንም ጉዳት እንደማይደርስበት እንዲሁም ምሥራቹን መስማት የሚገባቸው ብዙ ሰዎች በከተማዋ ውስጥ እንዳሉ ጌታ ራሱ ማረጋገጫ ሰጠው። ታዲያ ጳውሎስ ለዚህ ራእይ ምን ምላሽ ሰጥቶ ይሆን? ዘገባው “በመካከላቸው የአምላክን ቃል እያስተማረ ለአንድ ዓመት ተኩል እዚያ ቆየ” ይላል።—ሥራ 18:11
13. ጳውሎስ ወደ ፍርድ ወንበሩ ሲቃረብ ምን ትዝ ብሎት ሊሆን ይችላል? ሆኖም እሱ ይህ ሁኔታ እንደማይገጥመው እርግጠኛ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
13 ጳውሎስ በቆሮንቶስ አንድ ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ፣ የጌታ ድጋፍ እንደማይለየው ተጨማሪ ማረጋገጫ አግኝቷል። ዘገባው እንደሚነግረን “አይሁዳውያን ግንባር ፈጥረው በጳውሎስ ላይ ተነሱበት”፤ ከዚያም ቪማ ተብሎ በሚጠራው ‘የፍርድ ወንበር ፊት አቀረቡት።’ (ሥራ 18:12) አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ቪማ በሰማያዊና በነጭ እብነ በረድ የተሠራና በተለያዩ ቅርጾች ያጌጠ ከፍ ያለ መድረክ ነው፤ ቪማ የሚገኘው በቆሮንቶስ የገበያ ስፍራ መሃል አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ከፊት ለፊቱ ያለው ክፍት ቦታ ሰፊ በመሆኑ ብዙ ሕዝብ ሊሰበሰብበት ይችል ነበር። የአርኪኦሎጂ ግኝቶች እንደሚጠቁሙት የፍርድ ወንበሩ የሚገኘው ከምኩራቡ ብዙም ሳይርቅ ይመስላል፤ የኢዮስጦስ ቤት ደግሞ ከምኩራቡ አጠገብ ነበር። ጳውሎስ ወደ ቪማው ሲቃረብ፣ የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት እንደሆነ የሚነገርለት እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ የተገደለበት ሁኔታ ትዝ ብሎት ይሆን? በዚያን ጊዜ ሳኦል ተብሎ ይጠራ የነበረው ጳውሎስ “በእሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።” (ሥራ 8:1) ታዲያ እሱም ተመሳሳይ ነገር ይገጥመው ይሆን? በፍጹም፤ ምክንያቱም “ማንም . . . ሊጎዳህ አይችልም” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶታል።—ሥራ 18:10
14, 15. (ሀ) አይሁዳውያን በጳውሎስ ላይ ምን ክስ ሰነዘሩ? ጋልዮስ ክሱን ውድቅ ያደረገውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሶስቴንስ ምን ደረሰበት? የደረሰበት ሁኔታስ ምን ውጤት አስገኝቶ ሊሆን ይችላል?
14 ጳውሎስ በፍርድ ወንበሩ ፊት ሲቀርብ ምን ተከሰተ? የሮማዊው ፈላስፋ የሴኔካ ታላቅ ወንድምና የአካይያ አገረ ገዢ የሆነው ጋልዮስ በፍርድ ወንበሩ ላይ ተሰይሟል። አይሁዳውያኑ “ይህ ሰው ሕጉን በሚጻረር መንገድ ሰዎች አምላክን እንዲያመልኩ እያሳመነ ነው” ሲሉ ጳውሎስን ከሰሱት። (ሥራ 18:13) አይሁዳውያኑ፣ ሃይማኖት በማስቀየር ሕግ እየጣሰ ነው ብለው ጳውሎስን እየወነጀሉት ነው። ይሁንና ጋልዮስ፣ ጳውሎስ ምንም “በደል” እንዳልፈጸመና በየትኛውም “ከባድ ወንጀል” ተጠያቂ እንዳልሆነ አውቆ ነበር። (ሥራ 18:14) ጋልዮስ በአይሁዳውያን ውዝግብ ውስጥ እጁን ማስገባት አልፈለገም። ጳውሎስ አንድ የመከላከያ ቃል እንኳ ከአፉ ሳይወጣ ጋልዮስ ክሱን ውድቅ አደረገው! በዚህ ጊዜ ከሳሾቹ በጣም ተበሳጩ። ከዚያም በሶስቴንስ ላይ ንዴታቸውን ተወጡ፤ ሶስቴንስ የምኩራብ አለቃ የሆነው ቀርስጶስን ተክቶ ሳይሆን አይቀርም። አይሁዳውያኑ “ሶስቴንስን ይዘው በፍርድ ወንበሩ ፊት ይደበድቡት ጀመር።”—ሥራ 18:17
15 ጋልዮስ ሕዝቡ ሶስቴንስን እንዳይደበድበው ያልተከላከለው ለምንድን ነው? በጳውሎስ ላይ የተነሳው ዓመፅ መሪ ሶስቴንስ እንደሆነ አስቦ ዋጋውን እንዳገኘ ተሰምቶት ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ይህ ገጠመኝ በመጨረሻ ጥሩ ውጤት ሳያስገኝ አይቀርም። ጳውሎስ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ሶስቴንስ ስለተባለ ወንድም ጠቅሷል። (1 ቆሮ. 1:1, 2) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሶስቴንስ በቆሮንቶስ ተደብድቦ የነበረው ይሆን? ከሆነ ሶስቴንስ የደረሰበት መከራ ክርስትናን እንዲቀበል አድርጎት ሊሆን ይችላል።
16. ጌታ “መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር [ነኝ]” በማለት የተናገረው ሐሳብ በአገልግሎታችን እንድንቀጥል የሚያበረታታን እንዴት ነው?
16 ጌታ ኢየሱስ ለጳውሎስ “አትፍራ፤ መናገርህን ቀጥል እንጂ ዝም አትበል፤ እኔ ከአንተ ጋር [ነኝ]” የሚል ማረጋገጫ የሰጠው አይሁዳውያን መልእክቱን አንቀበልም ካሉ በኋላ እንደነበር አስታውስ። (ሥራ 18:9, 10) እኛም በተለይ ሰዎች መልእክታችንን አልቀበል ሲሉን ይህን ሐሳብ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ይሖዋ ልብን እንደሚያነብና ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ራሱ እንደሚስብ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። (1 ሳሙ. 16:7፤ ዮሐ. 6:44) ይህ አገልግሎታችንን በትጋት ማከናወናችንን እንድንቀጥል የሚያበረታታ አይደለም? በየዓመቱ መቶ ሺዎች ይጠመቃሉ፤ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይጠመቃሉ ማለት ነው። “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚለውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ላሉ ሁሉ ኢየሱስ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” የሚል ዋስትና ሰጥቷል።—ማቴ. 28:19, 20
“ይሖዋ ከፈቀደ” (የሐዋርያት ሥራ 18:18-22)
17, 18. ጳውሎስ በመርከብ ወደ ኤፌሶን ሲጓዝ ስለ ምን ነገር አስቦ ሊሆን ይችላል?
17 በቆሮንቶስ የሚገኘው ጨቅላ የክርስቲያን ጉባኤ ሰላም እንዲያገኝ ያደረገው ጋልዮስ ከጳውሎስ ከሳሾች ጋር በተያያዘ የወሰደው እርምጃ ይሆን? ይህን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሆኖም ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኙትን ወንድሞቹን ተሰናብቶ ከመሄዱ በፊት “በዚያ ለተወሰኑ ቀናት” ቆይቷል። አሁን ጊዜው 52 ዓ.ም. የጸደይ ወቅት ነው፤ ጳውሎስ ከቆሮንቶስ በስተ ምሥራቅ 11 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘው ከክንክራኦስ ወደብ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ሶርያ ለመሄድ አቀደ። ከክንክራኦስ ከመነሳቱ በፊት ግን “ስእለት ስለነበረበት . . . ፀጉሩን በአጭሩ ተቆረጠ።”c (ሥራ 18:18) ከዚያም ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር የኤጅያንን ባሕር አቋርጦ በትንሿ እስያ ወደምትገኘው ወደ ኤፌሶን ሄደ።
18 ጳውሎስ ከክንክራኦስ ተነስቶ በመርከብ ሲጓዝ በቆሮንቶስ ስላሳለፈው ጊዜ መለስ ብሎ አስቦ ይሆን? ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ብዙ ጥሩ ትዝታዎችና ልቡን በደስታ የሚሞሉ ነገሮች አሉት። ለአንድ ዓመት ተኩል በዚያ ያከናወነው አገልግሎት ፍሬ አፍርቷል። በቆሮንቶስ የመጀመሪያው ጉባኤ ተቋቁሞ በኢዮስጦስ ቤት መሰብሰብ ጀምሯል። አማኞች ከሆኑት መካከል ኢዮስጦስ፣ ቀርስጶስና ቤተሰቡ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ አዳዲስ አማኞች ለጳውሎስ ውድ ናቸው፤ ምክንያቱም ክርስቲያኖች እንዲሆኑ የረዳቸው እሱ ነው። ከጊዜ በኋላ ደብዳቤ የጻፈላቸው ሲሆን ለእሱ በልቡ ላይ የተጻፈ የምሥክር ወረቀት እንደሆኑ ነግሯቸዋል። እኛም እውነተኛውን አምልኮ እንዲቀበሉ ለረዳናቸው ሰዎች ልዩ የሆነ ፍቅር አለን። እነሱን ስናይ ጥልቅ የእርካታ ስሜት ይሰማናል፤ አዎ፣ ለእኛ ሕያው “የምሥክር ወረቀት” ናቸው!—2 ቆሮ. 3:1-3
19, 20. ጳውሎስ ኤፌሶን እንደደረሰ ምን አደረገ? መንፈሳዊ ግቦች ላይ ከመድረስ ጋር በተያያዘ ከእሱ ምን እንማራለን?
19 ጳውሎስ ኤፌሶን እንደደረሰ ወደ ሥራ ገባ። ዘገባው “ወደ ምኩራብ ገብቶ ከአይሁዳውያን ጋር ይወያይ ነበር” ይላል። (ሥራ 18:19) በዚህ ወቅት ጳውሎስ በኤፌሶን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነው። ወንድሞች ረዘም ላለ ጊዜ እንዲሰነብት ቢጠይቁትም “ፈቃደኛ አልሆነም።” የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ተሰናብቷቸው ሲሄድ “ይሖዋ ከፈቀደ ተመልሼ እመጣለሁ” ብሏቸዋል። (ሥራ 18:20, 21) ጳውሎስ በኤፌሶን ገና ብዙ መሰበክ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። ሐዋርያው ተመልሶ ለመምጣት አቅዷል፤ ሆኖም ጉዳዩን በይሖዋ እጅ መተው መርጧል። ይህ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ አይደለም? መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ የእኛ የራሳችን ተነሳሽነት እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ምንጊዜም ይሖዋ በሚሰጠን አመራር መታመንና ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።—ያዕ. 4:15
20 ጳውሎስ አቂላንና ጵርስቅላን በኤፌሶን ተዋቸው፤ መርከብ ተሳፍሮም ወደ ቂሳርያ ወረደ። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም “ወጥቶ” በዚያ ለሚገኘው ጉባኤ ሰላምታ አቀረበ። (ሥራ 18:22 ግርጌ) በመጨረሻም ጳውሎስ ወደ ማረፊያው ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ ሄደ። ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው በዚህ መንገድ በተሳካ ሁኔታ ተደመደመ። በመጨረሻው ሚስዮናዊ ጉዞው ደግሞ ምን ይጠብቀው ይሆን?
a “ቆሮንቶስ—የሁለት ባሕሮች እመቤት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b “በመንፈስ መሪነት የተጻፉ የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
c “የጳውሎስ ስእለት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።