ክርስትና በትንሿ እስያ ተዳረሰ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በትንሿ እስያ (በዋነኝነት የዛሬዋ ቱርክ በምትገኝበት አካባቢ) በርካታ የክርስቲያን ጉባኤዎች ይገኙ ነበር። ብዙ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና አሕዛብ፣ ክርስቲያኖች ለሚያውጁት መልእክት ጥሩ ምላሽ ሰጥተው ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ሶርያንና ፍልስጥኤምን ሳይጨምር የክርስቲያኖች እንቅስቃሴ ቀዳሚና ታላቅ እድገት ያስመዘገበው በትንሿ እስያ ነበር” በማለት ገልጿል።
ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን በማጠናቀር ክርስትና በዚህ አካባቢ እንዴት እንደተሰራጨ የተሟላ ግንዛቤ ማግኘት እንችላለን። እነዚህን መረጃዎች በመመርመር ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
በትንሿ እስያ የነበሩ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች
በትንሿ እስያ ክርስትናን ለማሰራጨት ምክንያት የሆነው የመጀመሪያ ታላቅ ክንውን የተከሰተው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ነበር። በዚህ ዕለት፣ ከፍልስጥኤም ውጪ የሚኖሩትን አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡትን ጨምሮ የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ በርካታ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ነበር። የኢየሱስ ሐዋርያት ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡት ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ሰበኩላቸው። የታሪክ ዘገባው አብዛኞቹ ሰዎች የመጡት የትንሿ እስያን ሰፊ ክፍል ከሚሸፍኑት ከቀጰዶቅያ፣ ከጳንጦስ፣ ከእስያ አውራጃ፣a ከፍርግያና ከጵንፍልያ እንደነበር ይገልጻል። በዚህ ቀን 3,000 የሚሆኑ ሰዎች ክርስቲያኖች የሚሰብኩትን መልእክት በመቀበል ተጠመቁ። ከዚያም አዲሱን እምነታቸውን ይዘው ወደ አገራቸው ተመለሱ።—የሐዋርያት ሥራ 2:5-11, 41
ቀጣዩን መረጃ የምናገኘው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በትንሿ እስያ ስላደረጋቸው የሚስዮናዊ ጉዞዎች በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ነው። ጳውሎስ ከ47-48 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ባደረገው የመጀመሪያ ጉዞው ከቆጵሮስ ተነስቶ ወደ ትንሿ እስያ በመርከብ በመጓዝ ጵንፍልያ በምትገኘው ጰርጌን ደርሷል። ጳውሎስና ጓደኞቹ በጵስድያ ወዳለችው ወደ አንጾኪያ ከተማ በመሄድ ያደረጉት የስብከት እንቅስቃሴ ያስገኘላቸው ጥሩ ውጤት የአይሁዳውያንን ቅንዓትና ተቃውሞ አስነሳባቸው። ጳውሎስ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ተጉዞ ኢቆንዮን ሲደርስ ሌሎች አይሁዳውያን ሚስዮናውያኑን ለማንገላታት ሞከሩ። በልስጥራን አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ስሜታዊ ሆነው መጀመሪያ ላይ ጳውሎስ አምላክ እንደሆነ ተናገሩ። ይሁንና በአንጾኪያና በኢቆንዮን የነበሩት ተቃዋሚ አይሁዳውያን በቦታው ሲደርሱ በአካባቢው የነበረው ሕዝብ ጳውሎስን በድንጋይ ወገሩት፤ በኋላም የሞተ መስሏቸው ትተውት ሄዱ! ከዚህ በኋላ ጳውሎስና በርናባስ የሮም ግዛት ወደሆነችውና በገሊላ ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ደርቤን አቀኑ። በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች መግባቢያ ቋንቋ ሊቃኦንያ ነበር። በእነዚህ አካባቢዎች ጉባኤዎች የተቋቋሙ ሲሆን ሽማግሌዎችም ተሾሙ። የጰንጠቆስጤ በዓል በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረ ከ15 ዓመታት ገደማ በኋላ ክርስትና በትንሿ እስያ በጥሩ ሁኔታ መስፋፋቱን ከዚህ ማየት ትችላለህ።—የሐዋርያት ሥራ 13:13-14:26
ጳውሎስና የጉዞ ባልደረቦቹ ከ49 እስከ 52 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዟቸውን በየብስ ላይ ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያ የተጓዙትም ወደ ልስጥራን ነበር። በዚህ ጉዟቸው ላይ የጳውሎስ የትውልድ ከተማ የሆነችውን በኪልቅያ የምትገኘውን ጠርሴስን ሳያቋርጡ አልቀሩም። ጳውሎስ በልስጥራን የሚገኙትን ወንድሞች በድጋሚ ከጎበኘ በኋላ ወደ ሰሜን በማቅናት በቢታንያና በእስያ አውራጃዎች ‘ቃሉን ለመናገር’ ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ከለከለው። እነዚህ አካባቢዎች ከጊዜ በኋላ ወንጌል ይሰበክላቸዋል። ከዚህ ይልቅ አምላክ፣ ጳውሎስ በሰሜን ምዕራብ ወዳሉት የትንሿ እስያ ክፍሎች በመጓዝ የጠረፍ ከተማ ወደሆነችው ወደ ጢሮአዳ እንዲሄድ መራው። ከዚያም ጳውሎስ ምሥራቹን በአውሮፓ እንዲሰብክ በራእይ ተነገረው።—የሐዋርያት ሥራ 16:1-12፤ 22:3
ጳውሎስ ከ52 እስከ 56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ባደረገው ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው በድጋሚ ወደ ትንሿ እስያ የተጓዘ ሲሆን የእስያ የወደብ ከተማ እስከሆነችው እስከ ኤፌሶን ድረስ ዘልቋል። ለሁለተኛ ጊዜ ካደረገው የሚስዮናዊ ጉዞው ሲመለስ እዚህ ቦታ ቆይቶ ነበር። በዚህች ከተማ በንቃት የሚንቀሳቀስ አንድ የክርስቲያኖች ቡድን የነበረ ሲሆን ጳውሎስና ጓደኞቹ ለሦስት ዓመታት ያህል በዚያ ተቀምጠዋል። በወቅቱ አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታዎች ገጥመዋቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በኤፌሶን የሚገኙ የብር አንጥረኞች ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚያካሂዱትን ትርፋማ ንግድ ለማስጠበቅ ሲሉ ሁከት አስነስተው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 18:19-26፤ 19:1, 8-41፤ 20:31
በኤፌሶንና በዙሪያዋ ባሉት ከተሞች የተካሄደው ሚስዮናዊ ሥራ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ በግልጽ መረዳት ይቻላል። የሐዋርያት ሥራ 19:10 “በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ” በማለት ሁኔታውን ይገልጻል።
በትንሿ እስያ የተገኙ እድገቶች
ጳውሎስ በኤፌሶን ያደረገው ቆይታ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲቃረብ በቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች “በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት [“ጉባኤዎች፣” NW] ሰላምታ ያቀርቡላችኋል” በማለት ጽፎላቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 16:19) ጳውሎስ ይህን ሲል ስለ የትኞቹ ጉባኤዎች መናገሩ ነበር? ምናልባትም በቆላስይስ፣ በሎዶቅያና በኢያራ የሚገኙትን ጉባኤዎች አስቦ ሊሆን ይችላል። (ቈላስይስ 4:12-16) ፖል—ሂዝ ስቶሪ የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ብሏል:- “በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በሰርዴስና በፊላድልፍያ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ምክንያት የሆነው ኤፌሶንን መነሻ በማድረግ የተካሄደው ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ ነው ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። . . . ሁሉም አካባቢዎች የሚገኙት ከኤፌሶን 192 ኪሎ ሜትር ርቀት ክልል ውስጥ ሲሆን እርስ በርስ የሚያገናኟቸው ምቹ መንገዶችም ነበሯቸው።”
በመሆኑም የጰንጠቆስጤ በዓል በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተከበረ ከ20 ዓመታት በኋላ በትንሿ እስያ ደቡባዊና ምዕራባዊ ክፍሎች በርካታ የክርስቲያን ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። በሌሎቹ የትንሿ እስያ ክፍሎችስ ምን ዓይነት ሁኔታ ይታይ ነበር?
የጴጥሮስን ደብዳቤዎች የተቀበሉ ሰዎች
ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ይህ ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም ከ62 እስከ 64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ነበር። መልእክቱንም የጻፈው በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ነበር። ጴጥሮስ በደብዳቤው ላይ በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ ሽማግሌዎች ‘መንጋውን እንዲጠብቁ’ ምክር ስለሰጠ በአካባቢው የክርስቲያን ጉባኤዎች እንደነበሩ መገመት እንችላለን። እነዚህ ጉባኤዎች የተቋቋሙት መቼ ነበር?—1 ጴጥሮስ 1:1፤ 5:1-3
የጴጥሮስን ደብዳቤዎች ከተቀበሉት በእስያና በገላትያ በመሳሰሉ አካባቢዎች ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ምሥራቹን የሰሙት ከጳውሎስ ነበር። ይሁንና ጳውሎስ በቀጰዶቅያም ሆነ በቢታንያ አልሰበከም። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስትና ወደ እነዚህ ቦታዎች እንዴት እንደተዳረሰ የሚገልጸው ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጰንጠቆስጤ በዓል በተከበረበት ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በነበሩ አይሁዳውያን ወይም ወደ ይሁዲነት በተለወጡ ሰዎች አማካኝነት ተዳርሶ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ የጰንጠቆስጤ በዓል ከተከበረ ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ ጴጥሮስ ደብዳቤውን ሲጽፍ አንድ ምሑር እንደገለጹት ጉባኤዎች “በመላው ትንሿ እስያ ይገኙ” እንደነበር ግልጽ ነው።
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹት ሰባት ጉባኤዎች
አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ያስነሱት ዓመጽ በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኢየሩሳሌምን ጥፋት አስከትሏል። በዚህም ምክንያት ከጊዜ በኋላ አንዳንድ አይሁዳውያን የሆኑ ክርስቲያኖች ወደ ትንሿ እስያ ሄደው ይሆናል።b
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሐዋርያው ዮሐንስ አማካኝነት በትንሿ እስያ ለሚገኙ ሰባት ጉባኤዎች ደብዳቤዎችን ልኮ ነበር። በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊላድልፍያና በሎዶቅያ ለሚገኙ ጉባኤዎች የተላኩት ደብዳቤዎች፣ በእነዚህ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች እንደ ሥነ ምግባር ፈተና፣ መናፍቅነትና ክህደት ከመሳሰሉ የተለያዩ ፈተናዎች ጋር ይጋፈጡ እንደነበር የሚያሳዩ ናቸው።—ራእይ 1:9, 11፤ 2:14, 15, 20
በትሕትና እና በሙሉ ነፍስ የቀረበ አገልግሎት
ክርስትና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ያደረገው መስፋፋት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ከምናነበው የበለጠ ነገርን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ታዋቂዎቹ ሐዋርያት ማለትም ጴጥሮስና ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በተገለጹት ክንውኖች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሌሎች ክርስቲያኖች በተለያዩ ቦታዎች ይሰብኩ ነበር። በትንሿ እስያ የታየው እድገት የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስ “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ በቁም ነገር ተመልክተውት እንደነበር የሚያረጋግጡ ናቸው።—ማቴዎስ 28:19, 20
በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ከሚያከናውኗቸው የእምነት ሥራዎች አንጻር ሲታይ ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር የሚነገሩት ተሞክሮዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በትንሿ እስያ እንደነበሩት ታማኝ ወንጌላውያን ሁሉ በዘመናችን የሚገኙት አብዛኞቹ የምሥራቹ ሰባኪዎችም እምብዛም አይታወቁም። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በሥራ የተጠመዱ ከመሆናቸውም ባሻገር እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት እየመሩ ነው፤ በተጨማሪም ሌሎችን ለማዳን ራሳቸውን በታዛዥነት ማቅረባቸውን ስለሚያውቁ ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3-6
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትና በዚህ ርዕስ ውስጥ “እስያ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የእስያን አህጉር ሳይሆን የትንሿ እስያን ምዕራባዊ ክፍል ይሸፍን የነበረውን የሮም ግዛት ነው።
b ታሪክ ጸሐፊው ዩሲቢየስ (260-340 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) እንደገለጸው ከ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ትንሽ ቀደም ብሎ “ሐዋርያት በተሸረበባቸው የግድያ ሴራ ሕይወታቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ በመውደቁ ከይሁዳ ወጥተው ነበር። ያም ሆኖ መልእክታቸውን ለሌሎች ለማዳረስ ሲሉ በክርስቶስ ኃይል በየአገሩ ዞረዋል።”
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የጥንቱ ክርስትና በቢታንያና በጳንጦስ
ቢታንያንና ጳንጦስን ያቀፈው ጥምር ግዛት የሚገኘው በትንሿ እስያ ባለው የጥቁር ባሕር ዳርቻ ላይ ነው። ከባለ ሥልጣናቱ አንዱ የሆነው ወጣቱ ፕሊኒ የሮም ገዢ ለነበረው ለትራጃን የጻፈለትን ደብዳቤ በመመርመር በዚህ ግዛት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ብዙ ማወቅ ተችሏል።
ጴጥሮስ የጻፋቸው ደብዳቤዎች በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ ጉባኤዎች ከተዳረሱ ወደ 50 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ ፕሊኒ ክርስቲያኖችን ምን ቢያደርጋቸው እንደሚሻል ለማወቅ ትራጃንን ምክር ጠይቆት ነበር። ፕሊኒ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር:- “በክርስቲያኖች ላይ ምርመራ በሚካሄድበት ወቅት በቦታው ተገኝቼ አላውቅም። በመሆኑም በእነሱ ላይ የሚተላለፈው የቅጣት መጠን ምን ያህል መሆን እንዳለበት የማውቀው ነገር የለም። በሁሉም የዕድሜ ክልልና የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ችሎት ፊት የሚቀርቡ ሲሆን ይህ ሁኔታም የሚቀጥል ይመስለኛል። ከከተሞች በተጨማሪ አንዳንድ መንደሮችና ገጠራማ አካባቢዎች በዚህ የኑፋቄ ትምህርት ተመርዘዋል።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ጳውሎስ ያደረጋቸው ጉዞዎች
የመጀመሪያው ሚስዮናዊ ጉዞ
ቆጵሮስ
ጵንፍልያ
ጴርጌን
አንጾኪያ (በጲስድያ የምትገኘው)
ኢቆንዮን
ልስጥራን
ደርቤን
ሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞ
ኪልቅያ
ጠርሴስ
ደርቤን
ልስጥራን
ኢቆንዮን
አንጾኪያ (በጲስድያ የምትገኘው)
ፍርግያ
ገላትያ
ጢሮአዳ
ሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞ
ኪልቅያ
ጠርሴስ
ደርቤን
ልስጥራን
ኢቆንዮን
አንጾኪያ (በጲስድያ የምትገኘው)
ኤፌሶን
እስያ
ጢሮአዳ
[ሰባት ጉባኤዎች]
ጴርጋሞን
ትያጥሮን
ሰርዴስ
ሰምርኔስ
ኤፌሶን
ፊላድልፍያ
ሎዶቅያ
[ሌሎች ቦታዎች]
ኢያራ
ቆላስይስ
ሉቅያ
ቢታንያ
ጳንጦስ
ቀጰዶቅያ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንጾኪያ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጠርሴስ
[ምንጭ]
© 2003 BiblePlaces.com
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኤፌሶን የሚገኝ ቲያትር ማሳያ ሥፍራ።—የሐዋርያት ሥራ 19:29
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጴርጋሞን የሚገኘው የዚየስ መሠዊያ መሠረት። በዚህ ከተማ የነበሩ ክርስቲያኖች ይኖሩ የነበረው “የሰይጣን ዙፋን ባለበት” ነበር።—ራእይ 2:13
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.