ገማልያል የጠርሴሱን ሳውል አስተምሮታል
የተሰበሰበው ሕዝብ ረጭ ብሎ ቆሟል። ከትንሽ ጊዜ በፊት ጳውሎስን ሊገድሉት ሞክረው ከእጃቸው ያመለጠው ለጥቂት ነበር። የጠርሴሱ ሳውል በሚል ሌላ ስም የሚታወቀው ጳውሎስ የሮማ ወታደሮች ደርሰው ካዳኑት በኋላ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አቅራቢያ ከሚገኘው ደረጃ ላይ ከሕዝቡ ፊት ለፊት ቆሟል።
ጳውሎስ ሕዝቡ ፀጥ እንዲል በእጁ ምልክት ከሰጠ በኋላ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ በማለት ንግግሩን ጀመረ፦ “እናንተ ወንድሞች አባቶችም፣ አሁን ለእናንተ ነገሬን ስገልጥ ስሙኝ። . . . እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፣ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፣ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፣ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ።”—ሥራ 22:1-3
ጳውሎስ ሕይወቱ አደጋ ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት ከገማልያል የተማረ መሆኑን በመጥቀስ ክርክሩን የጀመረው ለምንድን ነበር? ገማልያል ማን ነበር? ከእርሱ መማሩስ ምን ትርጉም ነበረው? ሳውል ክርስቲያን ሐዋርያ ከሆነም በኋላ ይህ ሥልጠና በእርሱ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ነበርን?
ገማልያል ማን ነበር?
ገማልያል በሕዝብ ዘንድ የታወቀ ፈሪሳዊ ነበር። በፈሪሳውያን የአይሁድ እምነት ውስጥ ዋነኛ የሃይማኖታዊ ትምህርት ማዕከል ከነበሩት ሁለት ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱን ያቋቋመው የሽማግሌው የሂሌል የልጅ ልጅ ነው።a የሂሌል የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ከተፎካካሪው ከሸማይ ጋር ሲወዳደር ይበልጥ ለዘብ ያለ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። በ70 እዘአ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከተደመሰሰ በኋላ ቤት ሂሌል (የሂሌል ቤት) ከቤት ሸማያ (ከሸማይ ቤት) ይልቅ ተወዳጅ ሆኖ ነበር። ሌሎቹ የመናፍቃን ቡድኖች በሙሉ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጋር አብረው ስለጠፉ የሂሌል ቤት ተቀባይነት ያለው የአይሁድ እምነት መግለጫ ሆኖ ነበር። የቤት ሂሌል ውሳኔዎች ለታልሙድ መሠረት በጣለው በሚሽናህ ውስጥ ለሠፈሩት ለአብዛኞቹ የአይሁድ ሕጎች መነሻ የሆኑ ሲሆን በዚህ ረገድ የገማልያል ተጽዕኖ ትልቅ ሚና ሳይጫወት አልቀረም።
ገማልያል ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሰው ከመሆኑ የተነሣ ከረቢዎች በላይ ያለውን ራባን የሚለውን የማዕረግ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘ ሰው ነበር። እንዲያውም ሚሽና እንደሚከተለው ብሎ እስኪናገርለት ድረስ ገማልያል ትልቅ አክብሮት ያገኘ ሰው ነበር፦ “ሽማግሌው ራባን ገማልያል ሲሞት የቶራህ ክብር አበቃ፣ ንጽሕናና ቅድስና [ጥሬ ፍቺው “የተለዩ መሆን” ማለት ነው] አከተመለት።”—ሶታህ 9:15
ከገማልያል የተማረው እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለነበሩት ብዙ ሰዎች ‘በገማልያል እግር አጠገብ ቁጭ ብሎ የተማረ መሆኑን’ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? እንደ ገማልያል ያሉት አስተማሪዎች ደቀ መዝሙር መሆን ምን ትርጉም ነበረው?
ይህን ዓይነቱን ሥልጠና በተመለከተ የጁዊሽ ቲኦሎጂካል ሴሚናሪ ኦቭ አሜሪካ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶቭ ዝሎትኒክ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “የቃል ሕግ ትክክለኛነትና አስተማማኝነት ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል በመምህሩና በደቀ መዝሙሩ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ የተመካ ነው፤ ይህም መምህሩ ሕጉን ለማስተማር በሚያደርገው ጥንቃቄና ደቀ መዝሙሩም ለመማር በሚያደርገው ልባዊ ጥረት ላይ የተመካ ነው ማለት ነው። . . . በዚህም ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ በምሁራኑ እግር ሥር ተቀምጠው . . . የሚናገሩትን ቃል በሙሉ ‘ውኃ እንደተጠማ ሰው እንዲጠጡ’ ጠበቅ ተደርጎ ይነገራቸው ነበር።”—አቮት 1:4 ሚሽናህ
ኤሚል ሹረር ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ጁዊሽ ፒፕል ኢን ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ ክራይስት (በእንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ የመጀመሪያ መቶ ዘመን የረቢ አስተማሪዎች ስለሚጠቀሙበት ዘዴ አንዳንድ ነገሮችን ገልጸዋል። እንዲህ በማለት ጻፉ፦ “ብዙ ዓይነትና ስፋት ካለው ‘የቃል ሕግ’ ጋር በጥልቀት ለመተዋወቅ የሚያስችላቸውን ትምህርት ለማግኘት የሚጓጉ ብዙ ቁጥር ያላቸው ልጆች በጣም ታዋቂ ከሆኑት ረቢዎች ዙሪያ ይሰበሰባሉ። . . . ትምህርቱ የማያቋርጥ የማስታወስ ችሎታ ፈተናንም ያቀፈ ነበር። አስተማሪው ውሳኔ የሚጠይቁ በርካታ የሕግ ጥያቄዎችን ለተማሪዎቹ ያቀርብና እንዲመልሱ ያደርጋል ወይም ራሱ ይመልሳቸዋል። ተማሪዎቹም ለአስተማሪው ጥያቄ ማቅረብ ይችሉ ነበር።”
በረቢዎች አመለካከት ተማሪዎቹ የማለፊያ ነጥብ ከማምጣት የበለጠ ሊያስቡበት የሚገባ አንገብጋቢ ነገር ነበር። በእነዚህ አስተማሪዎች ሥር ሆነው የሚያጠኑ ተማሪዎች የሚከተለው ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው ነበር፦ “ከተማረው መካከል አንድ ነገር የሚረሳ ካለ በሕይወቱ እንደቆረጠ ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ።” (አቮት 3:8) “በደንብ እንደተመረገ ዕቃ አንዲት ጠብታ የማያመልጠው ተማሪ” ከፍተኛ ውዳሴ ያገኝ ነበር። (አቮት 2:8) በወቅቱ የጠርሴሱ ሳውል በሚል የዕብራይስጥ ስም ይታወቅ የነበረው ጳውሎስ ከገማልያል ያገኘው ሥልጠና ይህን ዓይነት ነበር።
የገማልያል ትምህርቶች ይዘት
ገማልያል የፈሪሳውያንን ትምህርት በመከተል በቃል ሕግ ላይ የነበረውን እምነት አስፋፍቷል። ይህም በመሆኑ ይበልጥ ያተኮረው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ሳይሆን በረቢዎች ወግ ላይ ነበር። (ማቴዎስ 15:3-9) ገማልያል እንደሚከተለው ሲል እንደተናገረ በሚሽና ላይ ሰፍሮ ይገኛል፦ “በራስህ መላምት ከልክ በላይ አሥራት እንዳትከፍል አንድ አስተማሪ [አንድ ረቢ] አብጅና ከጥርጣሬ ነፃ ሆነህ ኑር።” (አቮት 1:16) ይህም ማለት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ያስቀመጡት ነገር ከሌለ ግለሰቡ የራሱን የማመዛዘን ችሎታ ወይም ሕሊና አይጠቀምም ነበር ማለት ነው። ከዚያ ይልቅ በእርሱ ቦታ ሆኖ የሚወስንለት ብቃት ያለው ረቢ ይፈልግ ነበር። እንደ ገማልያል አባባል ከሆነ አንድ ሰው ኃጢአት ከመሥራት የሚቆጠበው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።—ከሮሜ 14:1-12 ጋር አወዳድር።
ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ገማልያል ሕግ ነክ በሆኑ ሃይማኖታዊ ደንቦቹ ረገድ ይበልጥ ለዘብተኛ እንደሆነ ተደርጎ የሚታይ ሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል “አንዲት ሴት [ባሏ እንደሞተ የሚመሠክር] አንድ ምሥክር ካገኘች ሌላ ባል እንድታገባ” የሚፈቅድ ደንብ በማውጣቱ ለሴቶች ያለውን አሳቢነት አሳይቷል። (የቫሞት 16:7፣ ሚሽና) በተጨማሪም ገማልያል ፍቺን ለመከላከል ሲል በፍቺ ጽሕፈት ጉዳይ ላይ ብዙ ገደቦችን አውጥቶ ነበር።
ገማልያል ለኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ተከታዮች ባደረገው ነገር ላይ ተመሳሳይ መንፈስ ተንጸባርቋል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚተርከው አይሁዳውያን ሲሰብኩ አግኝተው ያሠሯቸውን የኢየሱስ ሐዋርያት ሊገድሏቸው በፈለጉ ጊዜ “በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጓቸው አዘዘ፣ እንዲህም አላቸው፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። . . . ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።” ገማልያል የተናገረውን ቃል ሰሙት፤ ሐዋርያትም ተለቀቁ።—ሥራ 5:34-40
ከገማልያል ያገኘው ሥልጠና ለጳውሎስ ምን ትርጉም ነበረው?
ጳውሎስ ሥልጠናና ትምህርት ያገኘው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ የረቢ አስተማሪዎች መካከል ከአንዱ ነበር። ሐዋርያው ስለ ገማልያል መጥቀሱ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች ለንግግሩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት እንዳደረጋቸው ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ከገማልያል ስለሚልቅ አስተማሪ ይኸውም ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ ነግሯቸዋል። በዚህ ወቅት ጳውሎስ ለተሰበሰበው ሕዝብ ራሱን ያስተዋወቀው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደሆነ አድርጎ እንጂ የገማልያል ደቀ መዝሙር እንደሆነ አድርጎ አይደለም።—ሥራ 22:4-21
የገማልያል ሥልጠና ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ በሚያስተምረው ትምህርት ላይ ተጽዕኖ ነበረውን? በቅዱስ ጽሑፉና በአይሁዳውያን ሕግ ውስጥ የሚገኘው የማያወላውል መመሪያ ጳውሎስ ክርስቲያን አስተማሪ ከሆነ በኋላ እንደጠቀመው አይካድም። ይሁንና በመለኮታዊ መንፈስ መሪነት የተጻፉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ጳውሎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎች የገማልያልን መሠረታዊ የሆኑ ፈሪሳዊ እምነቶች አንቅሮ እንደተፋቸው ያሳያሉ። ጳውሎስ መሰል አይሁዳውያንም ሆኑ ሌሎች ሰዎች እንዲያተኩሩ ያደረገው በአይሁድ እምነት ረቢዎች ወይም ከሰዎች በመነጩ ወጎች ላይ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነበር።—ሮሜ 10:1-4
ጳውሎስ የገማልያል ደቀ መዝሙር ሆኖ ቢቀጥል ኖሮ ትልቅ ክብር ያለው ሰው ይሆን ነበር። ከገማልያል ጋር የነበሩት ሌሎች ሰዎች በአይሁድ እምነት የወደፊት ዕጣ ላይ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ለምሳሌ ያህል የገማልያል ልጅ የነበረው ስምዖን፣ ምናልባትም ከጳውሎስ ጋር አንድ ላይ የተማረ ሳይሆን አይቀርም አይሁዳውያን በሮማውያን ላይ ባካሄዱት አብዮት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መፍረስ በኋላ የገማልያል የልጅ ልጅ የሆነው ገማልያል ዳግማዊ የሳንሄድሪንን መቀመጫ ወደ ጃብኔ በማዛወር የሸንጎው ሥልጣን እንዲያንሠራራ አድርጓል። የገማልያል ዳግማዊ የልጅ ልጅ የሆነው ጁዳ ሃናሲ እስከ ዛሬ ድረስ ለዘለቀው የአይሁዳውያን አስተሳሰብ እንደ መሠረት ድንጋይ የሆነውን ሚሽናን ያጠናቀረ ሰው ነው።
የጠርሴሱ ሳውል የገማልያል ተማሪ እንደመሆኑ መጠን በአይሁድ እምነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ሰው ሊሆን ይችል ነበር። ይሁንና ጳውሎስ ይህን ዓይነቱን ሥራ በተመለከተ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጒዳት ቈጥሬዋለሁ። አዎን፣ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጒዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፣ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፣ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፣ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ።”—ፊልጵስዩስ 3:7, 8
ጳውሎስ የፈሪሳዊነት ሥራውን ወደኋላ በመተው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ የቀድሞው አስተማሪው “ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ እንዳትገኙ” ሲል የሰጠውን ምክር በአግባቡ ሠርቶበታል። ጳውሎስ የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ማሳደዱን በማቆም ከአምላክ ጋር መጣላቱን አቁሟል። በዚያ ፋንታ የክርስቶስ ተከታይ በመሆን ‘ከአምላክ ጋር አብሮ የሚሠራ’ ሆነ።—1 ቆሮንቶስ 3:9
የእውነተኛው ክርስትና መልእክት በዚህ ዘመን ባሉ የይሖዋ ቀናተኛ ምሥክሮችም መታወጁን ቀጥሏል። ከእነዚህም መካከል ብዙዎች ልክ እንደ ጳውሎስ በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አድርገዋል። አንዳንዶችም “ከእግዚአብሔር” በሆነው የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ይበልጥ ለመሳተፍ ሲሉ ብዙ ገንዘብ ሊያስገኙላቸው ይችሉ የነበሩትን ሥራዎች ትተዋል። (ሥራ 5:39) የጳውሎስን የቀድሞ አስተማሪ የገማልያልን ምሳሌ ሳይሆን የራሱን የጳውሎስን ምሳሌ በመከተላቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ ምንጮች ገማልያል የሂሌል ልጅ ነው ይላሉ። ታልሙድ በዚህ በኩል ግልጽ አድርጎ የሚናገረው ነገር የለም።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው የጠርሴሱ ሳውል ምሥራቹን ለሰው ሁሉ ሲያውጅ