በቀድሞ ዘመን የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ዘ ቾሰን ኢልቦ በተሰኘ አንድ የኮሪያ ጋዜጣ ላይ ትኩረት የሚስብ ርዕስ ወጥቶ ነበር። ርዕሱ “ስለ ኢየሱስ ምንም የማታውቀው ‘ተወዳጇ ሺም ቸንግ’ ገሃነም ገብታ ይሆን?” ይላል።
ይህ ርዕስ ብዙዎችን የሚያስቆጣ ነበር፤ ምክንያቱም በኮሪያ አፈ ታሪክ መሠረት ሺም ቸንግ፣ ዓይነ ስውር አባቷን ለመርዳት ስትል ሕይወቷን መሥዋዕት ያደረገች ተወዳጅ ወጣት ነበረች። ሺም ቸንግ ለብዙ ዓመታት ከፍተኛ አድናቆት ሲቸራት ቆይቷል። እንዲያውም በኮሪያ ሺም ቸንግ፣ ወላጆችን በመውደድ ረገድ እንደ አርዓያ ትታያለች።
እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያላት ሴት፣ የተጠመቀች ክርስቲያን ስላልነበረች ብቻ በገሃነመ እሳት ትቀጣለች የሚለው ሐሳብ ለብዙዎች ፍትሐዊነት የጎደለው አልፎ ተርፎም የሚያስቆጣ ነው። ደግሞም የሺም ቸንግ ታሪክ እንደተፈጸመ የሚነገረው ስለ ክርስቶስ የሚገልጸው መልእክት እሷ ወዳለችበት መንደር ከመድረሱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው።
ጋዜጣው ላይ የወጣው ርዕስ ከአንድ ቄስ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስንም አካትቶ ነበር። ቄሱ፣ ስለ ኢየሱስ ለማወቅ አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ሰዎች በሙሉ ወደ ገሃነመ እሳት ይገቡ እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። ታዲያ ምን ምላሽ ሰጡ? “የምናውቀው ነገር የለም። እንደዚህ ላሉት ሰዎች አምላክ ያሰበላቸው ነገር እንደሚኖር ግን መገመት እንችላለን” ብለዋል።
ለመዳን አስፈላጊ የሆነ ብቃት
ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “ጥምቀት ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነው። ክርስቶስ ራሱ እንደተናገረው አንድ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት አይገባም (ዮሐ 3.5)።” በዚህም ምክንያት አንዳንዶች፣ ሳይጠመቁ የሞቱ ሰዎች ወደ ገሃነመ እሳት እንደሚገቡ ወይም በሆነ መንገድ እንደሚሠቃዩ ያምናሉ።
ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ እምነት ትክክል እንዳልሆነ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ሳያውቁ ሞተዋል። ታዲያ ዘላለማዊ ሥቃይ ይገባቸዋል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ
አምላክ፣ እሱ ያወጣቸውን መመሪያዎች ለማያውቁ ሰዎች ግድ የሌለው እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። የሐዋርያት ሥራ 17:30 “አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ ቸል ብሎ አልፎታል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። ታዲያ ስለ አምላክ ለመማር አጋጣሚ ሳይኖራቸው ለሞቱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ተስፋ ይዟል?
የዚህ ጥያቄ መልስ ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅሎ ለሞተው ወንጀለኛ በነገረው ሐሳብ ውስጥ ይገኛል። ሰውየው ኢየሱስን “ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” ብሎት ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ምን መልስ ሰጠው? “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል።—ሉቃስ 23:39-43
ኢየሱስ፣ ይህ ሰው ወደ ሰማይ እንደሚሄድ ቃል መግባቱ ነበር? አልነበረም። ግለሰቡ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ አላሟላም፤ ይኸውም ከውኃና ከመንፈስ ‘ዳግመኛ አልተወለደም።’ (ዮሐንስ 3:3-6) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ፣ ይህ ወንጀለኛ ከሞት ተነስቶ በገነት የመኖር አጋጣሚ እንደሚያገኝ ቃል መግባቱ ነበር። ሰውየው አይሁዳዊ ስለነበረ ስለ ምድራዊ ገነት፣ ይኸውም በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ስለተገለጸው የኤደን የአትክልት ስፍራ ሳያውቅ አይቀርም። (ዘፍጥረት 2:8) ኢየሱስ የገባለት ቃል፣ በድጋሚ በምድር ላይ በሚቋቋመው ገነት ውስጥ ትንሣኤ የማግኘት አስተማማኝ ተስፋ እንዳለው አረጋግጦለታል።
እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” ተስፋ ይሰጣል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) “ዓመፀኞች” የተባሉት ከመሞታቸው በፊት የአምላክን ፈቃድ ባለማወቃቸው የተነሳ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ሳያሟሉ የቀሩ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ፣ ከእሱ ጋር የተሰቀለውን ዓመፀኛ እንዲሁም ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ ምንም ሳያውቁ የሞቱ በሚሊዮኖች ምናልባትም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችን ያስነሳቸዋል። ከዚያም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የአምላክን መሥፈርቶች የሚማሩ ሲሆን የአምላክን መመሪያዎች በመታዘዝ እሱን እንደሚወዱት ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ያገኛሉ።
ዓመፀኞች ከሞት ሲነሱ
ዓመፀኞች ከሞት በሚነሱበት ጊዜ የሚፈረድባቸው ከመሞታቸው በፊት ያደረጉትን ነገር መሠረት በማድረግ ነው? አይደለም። ሮም 6:7 “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” በማለት ይናገራል። ዓመፀኞች ሲሞቱ የኃጢአታቸውን ዋጋ ከፍለዋል። በመሆኑም የሚፈረድባቸው ትንሣኤ ካገኙ በኋላ በሚሠሩት ነገር እንጂ ከመሞታቸው በፊት ባለማወቅ በሠሩት ነገር መሠረት አይደለም። ይህ ዓመፀኞችን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
ከትንሣኤ በኋላ ዓመፀኞች፣ ምሳሌያዊ የመጽሐፍ ጥቅልሎች በሚከፈቱበት ጊዜ ይፋ የሚሆኑትን የአምላክ ሕጎች ለመማር አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ከዚያም “እንደየሥራቸው” ማለትም የአምላክን ሕግ በመታዘዛቸው ወይም ባለመታዘዛቸው ላይ የተመሠረተ ፍርድ ይሰጣቸዋል። (ራእይ 20:12, 13) ይህ ዝግጅት ለብዙዎቹ ዓመፀኞች ሁለተኛ አጋጣሚ የመስጠት ጉዳይ አይደለም፤ እንዲያውም የአምላክን ፈቃድ በመማርና በማድረግ በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ለመጀመሪያ ጊዜ አጋጣሚ እየተሰጣቸው ነው።
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ብዙዎች እንደገና በአምላክ ላይ እምነት እንዲጥሉ ረድቷቸዋል። እንደዚህ ካሉት ሰዎች አንዷ የንግ ሱግ ናት። የንግ ሱግ ያደገችው አጥባቂ ካቶሊክ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አንዳንድ የቤተሰቧ አባላት ቀሳውስት ነበሩ። እሷም መነኩሲት ለመሆን በማሰብ ገዳም ገብታ ነበር። በኋላ ግን በገዳሙ ውስጥ ሲፈጸም ባየችው ነገር ስላዘነች ገዳሙን ለቃ ወጣች። ከዚህም በላይ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ማሠቃየት ፍትሐዊነትና ፍቅር የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ስለተሰማት የገሃነመ እሳትን መሠረት ትምህርት መቀበል ከበዳት።
ከጊዜ በኋላ አንዲት የይሖዋ ምሥክር፣ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም” የሚለውን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለየንግ ሱግ አሳየቻት። (መክብብ 9:5) የይሖዋ ምሥክሯ፣ በቀድሞው ዘመን የሞቱት የየንግ ሱግ ዘመዶች በገሃነመ እሳት እየተሠቃዩ እንዳልሆኑ እንድትገነዘብ ረዳቻት። ከዚህ ይልቅ በሞት አንቀላፍተው ትንሣኤን እየጠበቁ እንደሚገኙ አስረዳቻት።
የንግ ሱግ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጨርሶ እንዳልሰሙ ስለምታውቅ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:14 ላይ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት የተናገረው ሐሳብ ልቧን ነካት። በአሁኑ ጊዜ ምሥራቹን በመስበኩና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አስደሳች ተስፋዋን ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ ትሳተፋለች።
‘አምላክ አያዳላም’
“አምላክ [አያዳላም] . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ደግሞም “ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል” የተባለለት አምላክ እንዲህ ያደርጋል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊ ነው።—መዝሙር 33:5