ሩጫውን በጽናት መሮጥ
“በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።”—ዕብራውያን 12:1
1. (ሀ) ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን በፊታችን የሚጠብቀን ምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ሊዘጋጅ የሚገባው ለምን ዓይነት ሩጫ ነው?
ራሳችንን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለይሖዋ ስንወስን አምላክ በምሳሌያዊ ሁኔታ አንድ ዓይነት ሩጫ በፊታችን አስቀምጦልናል። ሩጫው በሚፈጸምበት ጊዜ ሩጫውን በተሳካ ሁኔታ ለጨረሱ ሯጮች ሽልማት ይሰጣል። ሽልማቱ ምንድን ነው? የዘላለም ሕይወት ነው። ይህን አስደናቂ ሽልማት ለማግኘት ክርስቲያኑ ሩዋጭ ለአጭርና ቶሎ ለሚያልቅ ሳይሆን ለረዥም ርቀት ሩጫ መዘጋጀት አለበት። የረዥሙን ርቀት ድካምና በሩጫው ወቅት የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች በመጽናትና በትዕግሥት መወጣት ይኖርበታል።
2, 3. (ሀ) ክርስቲያኖች ሩጫችንን እስከ መጨረሻው ለመሮጥ የሚረዳን ምንድን ነው? (ለ) ደስታ ኢየሱስን በትዕግሥት እንዲሮጥ የረዳው እንዴት ነው?
2 እንዲህ ዓይነቱን ሩጫ እስከመጨረሻው እንድንሮጥ የሚረዳን ምንድን ነው? ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለመጽናት የረዳው ምን ነበር? ከደስተኛነት ባሕርዩ ውስጣዊ ጥንካሬ አግኝቷል። ዕብራውያን 12:1-3 እንዲህ ይነበባል፦ “እንግዲህ እነዚህን የሚያክሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን የእምነታችንን ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል [በመከራ እንጨት (አዓት)] ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና።”
3 ኢየሱስ በሕዝባዊ አገልግሎቱ ሁሉ በይሖዋ ይደሰት ስለነበር ሩጫውን በተሳካ ሁኔታ ሊሮጥ ችሎ ነበር። (ከነህምያ 8:10 ጋር አወዳድር) ደስታው በመከራ እንጨት ላይ በአሳፋሪ ሁኔታ እስከ መሞት ድረስ እንዲታገሥ ረድቶታል። ከዚያ በኋላ ከሙታን የመነሣትንና የአምላክን ሥራ ወደ ፍጻሜው ሊያደርስ ወደሚችልበት ወደ አባቱ ቀኝ ጎን የማረግን በቃላት ሊነገር የማይችል ደስታ ቀምሷል። ሰው ሆኖ በኖረበት ጊዜ በጽናት ከአምላክ ጎን በመቆሙ የዘላለም ሕይወትን መብት ጨብጧል። አዎን፣ ሉቃስ 21:19 እንደሚለው “በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።”
4. ኢየሱስ ለመሰል ሯጮች ምን ምሳሌ ትቷል? አእምሮአችን ማተኮር ያለበትስ በምን ላይ ነው?
4 ኢየሱስ ክርስቶስ ለሩጫ ባልንጀሮቹ ግሩም ምሳሌ ትቷል። የሱ ምሳሌነት እኛም አሸናፊዎች ልንሆን እንደምንችል ያረጋግጥልናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ እንድናደርግ የሚጠይቀንን ሁሉ ማድረግ እንችላለን። እሱ እንደጸና እኛም መጽናት እንችላለን። ሳናወላውል በቁርጠኝነት እሱን በመምሰል በቀጠልን መጠን ደስተኞች ለመሆን በሚያስችሉን ምክንያቶች ላይ አእምሮአችን እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርብናል። (ዮሐንስ 15:11, 20, 21) ደስተኛነት ታላቁን የዘላለም ሕይወት ሽልማት እስክናገኝ ድረስ በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገውን ሩጫ እንዳናቋርጥ ያበረታታናል።—ቆላስይስ 1:10, 11
5. በፊታችን ባለው ሩጫ ደስተኞች ልንሆን የምንችለውና ልንበረታታ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ በሩጫው ጸንተን እንድንቀጥል እኛን ለመርዳት ከተለመደው የበለጠ ኃይል ይሰጠናል። ስደት ሲደርስብን ይህ ኃይል እንዳለንና ስደት የመቀበል መብት ለምን እንደተሰጠን ማወቃችን ያበረታታናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7-9) ለአምላክ ስም ክብርና የሱን የበላይ ገዥነት በመደገፋችን ምክንያት የሚደርስብን ማንኛውም፣ ነገር ማንም ሰው ሊወስድብን የማይችል ደስታ ያስገኝልናል። (ዮሐንስ 16:22) ይህም ሐዋርያት ይሖዋ አምላክ በኢየሱስ ከክርስቶስ በኩል ስለፈጸማቸው ድንቅ ነገሮች ምስክርነት በመስጠታቸው ምክንያት በአይሁድ ሸንጎ ትእዛዝ ከተገረፉ በኋላ “ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለተቆጠሩ” የተደሰቱበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። (ሥራ 5:41, 42) ደስታ ያገኙት ከስደቱ ከራሱ ሳይሆን ይሖዋና ኢየሱስን እያስደሰቱ እንደነበሩ ከማወቃቸው ባገኙት ውስጣዊ ጥልቅ እርካታ ነበር።
6, 7. ክርስቲያኑ ሯጭ መከራ እያለበት ሊደሰት የሚችለው ለምንድን ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?
6 በሕይወታችን ውስጥ ሌላው ኃይል ሰጪ ነገር አምላክ በፊታችን ያስቀመጠልን ተስፋ ነው። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት እንደተናገረው ነው፦ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል። በእግዚአብሔር ክብርም (ላይ በተመሠረተ) ተስፋ እንመካለን። ይህም ብቻ አይደለም። ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ ትዕግሥትም [ተቀባይነት ያለው አካሄድን፣ ተቀባይነት ያለው አካሄድም (አዓት)]፣ ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን። ተስፋውም አያሳፍርም።”—ሮሜ 5:1-5
7 መከራ መቀበል በራሱ የሚያስደስት ነገር አይደለም። መከራ የሚያስገኛቸው ሰላማዊ ፍሬዎች ግን አስደሳች ናቸው። እነዚህም ፍሬዎች ትዕግሥት (ጽናት)፣ ተቀባይነት ያለው አካሄድ፣ ተስፋና የዚያ ተስፋ ፍጻሜ ናቸው። መጽናታችን መለኮታዊ ተቀባይነት ያስገኝልናል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ሲኖረን ደግሞ ቃል የገባልንን ተስፋ ፍጻሜ በትምክህት ልንጠብቅ እንችላለን። ተስፋው በመንገዳችን ላይ እንድንጸናና ተስፋው እስኪፈጸም ድረስ መከራ ሲያጋጥመን የደስተኛነት መንፈስ እንዲኖረን ያደርጋል።—2 ቆሮንቶስ 4:16-18
የሚጸኑ ደስተኞች ናቸው!
8. ይህ በመጠባበቅ የምናሳልፈው ጊዜ፣ ጊዜ ማባከን የማይሆንብን ለምንድን ነው?
8 አምላክ ሽልማቱን ለሯጮቹ የሚያከፋፍልበትን ጊዜ በምንጠባበቅበት ጊዜ የሚያጋጥሙን ለውጦች አሉ። እነዚህም ለውጦች ፈተናን በተሳካ ሁኔታ በመወጣትና ይህንንም በማድረጋችን ከአምላክ ከምናገኘው ታላቅ ሞገስ የሚመጡ መንፈሳዊ ዕድገቶች ናቸው። ፈተናዎቹ ማን ወይም ምን ዓይነቶች ሰዎች መሆናችንን የሚመሰክሩ ከመሆናቸውም በላይ የቀድሞ ዘመን ታማኝ ሰዎችና በተለይም ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየውን ዓይነት መልካም ባሕርያት በሥራ እንድንገልጽ አጋጣሚ ይሰጡናል። ደቀመዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “ወንድሞቼ ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስት ቁጠሩት። ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉአን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።” (ያዕቆብ 1:2-4) አዎን ልዩ ልዩ ፈተናዎች እንደሚደርስብን እንጠብቅ ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ፈተናዎች ተገቢ ባሕርያትን በመኮትኮት እንድንቀጥል ያገለግላሉ። በዚህም ሽልማቱ እስኪገኝ ድረስ ምንም ዓይነት መሰናክሎች ቢገጥሙን በሩጫው እንደምንቀጥል እናሳያለን።
9, 10. (ሀ) በመከራ የሚጸኑ ሰዎች ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው? መከራን መቻል የሚገባን እንዴት ነው? (ለ) በቀድሞ ዘመን ደስተኞች የነበሩ ሰዎች እነማን ናቸው? ከእነዚህስ መሃል ልንቆጠር የምንችለው እንዴት ነው?
9 እንግዲያውስ ያዕቆብ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው። ከፈተና በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና!” (ያዕቆብ 1:12) ፈተናዎችን ከማሸነፍ በሚገኙትና በሚያበረቱን አምላካዊ ባሕርያት ታጥቀን ያለማቋረጥ ፈተናዎችን እንታገሥ።—2 ጴጥሮስ 1:5-8
10 አምላክ በእኛ ረገድ የሚያደርገው የአሠራር መንገድ አዲስ እንዳልሆነ አስብ። በቀድሞ ዘመን የነበሩት “እንደ ደመና ያሉ ምስክሮች” ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት ባረጋገጡበት ጊዜ የነበረው የአምላክ አሠራር አሁንም አልተለወጠም። (ዕብራውያን 12:1) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ መሆናቸው በቃሉ ውስጥ ተመዝግቧል። ሁሉም በፈተና ስለጸኑ ደስተኞች እንላቸዋለን። ያዕቆብ “ወንድሞች ሆይ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን [በይሖዋ (አዓት)] ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን [ደስተኞች(አዓት)] እንላቸዋለን። ኢዮብ እንደታገሠ ሰምታችኋል። [ይሖዋም (አዓት)] እንደፈጸመለት [የሰጠውን ውጤት (አዓት)] አይታችኋል። [ይሖዋም (አዓት)] እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና” ብሏል። (ያዕቆብ 5:10, 11) በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት በጥንት ዘመን እንደነበሩት ነቢያት ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሰዎች በዓለም መድረክ ላይ ብቅ እንደሚሉ በትንቢት ተነግሯል። ከእነዚህ መካከል በመሆናችን ደስተኞች አይደለንምን?—ዳንኤል 12:3፤ ራእይ 7:9
አበረታች ከሆነው የይሖዋ ቃል ተገቢ ጥቅም ማግኘት
11. የአምላክ ቃል ለመጽናት የሚረዳን እንዴት ነው? በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው “ጭንጫ መሬት” መሆን የሌለብን ለምንድን ነው?
11 ጳውሎስ “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ብሎ በተናገረ ጊዜ ለመጽናት የሚያግዝ አንድ ነገር አመልክቷል። (ሮሜ 15:4) በማንኛውም ጊዜ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት እንድንችል እውነት የሆነው የአምላክ ቃል በውስጣችን ጠልቆ ሥር መስደድ አለበት። ኢየሱስ በተናገረው የዘሪ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው ጭንጫ መሬት በመሆኑ ፈጽሞ ጥቅም አናገኝም፦ “በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል። ለጊዜው ነው እንጂ በእነርሱ ስር የላቸውም። በኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ።” (ማርቆስ 4:16, 17) ከአምላክ ቃል የሚገኘው እውነት በእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ውስጥ ጠልቆ ስር አይሰድም። ስለዚህ በመከራ ጊዜ እንደ እውነተኛ የብርታትና የተስፋ ምንጭ አድርገው ሊጠቀሙበት አይችሉም።
12. የምሥራቹን ስንቀበል ራሳችንን ማሞኘት የሌለብን ስለምን ነገር ነው?
12 የመንግሥቱን የምሥራች የሚቀበል ማንኛውም ሰው ወደፊት ስለሚያጋጥመው ሁኔታ ራሱን ማሞኘት የለበትም፤ መከራ ወይም ስደት የሚያመጣ የሕይወት መንገድ መያዙ ወይም መጀመሩ እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል አጥብቆ በመያዙና ስለሱም ለሌሎች በመናገሩ ምክንያት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ቢደርሱበት መብት ማግኘቱ ስለሆነ እንደ “ሙሉ ደስታ” ሊቆጥረው ይገባል።—ያዕቆብ 1:2, 3
13. ጳውሎስ በተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የተደሰተው እንዴትና ለምን ነበር?
13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተሰሎንቄ የነበሩ ተቃዋሚዎች በጳውሎስ ስብከት ምክንያት ብጥብጥ አስነሥተው ነበር። ጳውሎስ ወደ ቤሪያ ሲሄድ እነዚህ አሳዳጆች እዚያም ብጥብጥ ለማነሣሣት ተከትለውት ሄዱ። ስደት የደረሰበት ይህ ሐዋርያ በተሰሎንቄ ለቀሩት ታማኞች እንዲህ ሲል ጻፈላቸው፦ “ወንድሞች ሆይ እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን። ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን። ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቆጠሩ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው።” (2 ተሰሎንቄ 1:3-5) የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጠላቶቻቸው እጅ ቢሰቃዩም ክርስቶስን በመምሰልና በቁጥር አድገው ነበር። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ከይሖዋ አበረታች ቃል ኃይል ስላገኙ ነበር። የጌታን ትእዛዞች በመፈጸም ሩጫውን በትዕግሥት ይሮጡ ነበር።—2 ተሰሎንቄ 2:13-17
ለሌሎች ደህንነት ማሰብ
14. (ሀ) ችግር ቢያጋጥመንም በአገልግሎቱ በደስታ መጽናት ያለብን በምን ምክንያቶች ነው? (ለ) ስለምን እንጸልያለን? ለምንስ?
14 በመጀመሪያ ደረጃ መከራንና ስደትን በታማኝነትና ያለማጉረምረም የምንታገሠው የአምላክን ስም ለመቀደስ ስንል ነው። ይሁን እንጂ ለእነዚህ ነገሮች ራሳችንን የምናስገዛበት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ሌላ ምክንያት አለ፦ እሱም ሌሎች ሰዎች የመንግሥቱ አስፋፊዎች በመሆን “ለመዳን በአፋቸው ለመመስከር” ይነሣሱ ዘንድ የመንግሥቱን ዜና ማስተላለፍ ነው። (ሮሜ 10:10) በአምላክ አገልግሎት ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች የመከሩ ጌታ ተጨማሪ የመንግሥት አስፋፊዎችን በመስጠት ሥራቸውን እንዲባርክላቸው መጸለይ ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 9:38) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ አብረኸኝ መከራ ተቀበል።”—2 ጢሞቴዎስ 2:2, 3
15. ራሳችንን እንደ ወታደሮችና “በጨዋታ” እንደሚታገል አድርገን መምራት ያለብን ለምንድን ነው?
15 አንድ ወታደር እንደልብ ይኖርበት ከነበረው ወታደራዊ ያልሆነ የሲቪል አኗኗር ራሱን ይለያል። እኛም በተመሳሳይ በጌታ ሠራዊት ውስጥ ባልሆኑና እንዲያውም በተቃራኒው ወገን ባሉ ሰዎች ጉዳይ ራሳችንን ማጠላለፍ የለብንም። ስለዚህ ጉዳይ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱ አያጠላልፍም። ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል የድሉን አክሊል አያገኝም።” (2 ጢሞቴዎስ 2:4, 5) ሯጮች “የሕይወት አክሊል” ለማግኘት በሚደረገው ሩጫ ለድል ሲታገሉ ራስ መግዛትን ልማድ ማድረግና አስፈላጊ ያልሆኑ ሸክሞችንና መጠላለፎችን ማስወገድ አለባቸው። በዚህ መንገድም ለሌሎች የመዳንን የምሥራች በማምጣት ሥራ ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ።—ያዕቆብ 1:12፤ ከ1 ቆሮንቶስ 9:24, 25
16. ሊታሠር የማይችለው ምንድን ነው? የምንጸናው ለእነማን ጥቅም ስንል ነው?
16 አምላክን ለማግኘት የሚፈልጉትን በግ መሰል ሰዎች ስለምንወድ ለሌሎች የመዳንን ወንጌል ለማዳረስ ስንል በብዙ ነገሮች በደስታ እንታገሣለን። የአምላክን ቃል በመስበካችን ጠላቶች ያስሩን ይሆናል። የአምላክ ቃል ግን ሊታሠር አይችልም። ለሌሎች ተነግሮ ደህንነት እንዳያስገኝ በሰንሰለት ሊያዝ አይችልም። ጳውሎስ ለምን መከራ ለመጋፈጥ ፈቃደኛ እንደሆነ ለጢሞቴዎስ እንዲህ በማለት ገልጾለታል፦ “በወንጌል እንደምሰብከው ከሙታን የተነሣውን ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ። ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ። የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሠርም። ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ።” (2 ጢሞቴዎስ 2:8-10) ዛሬ የምናስባቸው ሰማያዊ መንግሥት ለማግኘት የተዘጋጁት አነስተኛ ቀሪዎች ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ መንግሥት ሥር ምድራዊ ገነት የሚያገኙት የመልካሙ እረኛ የሌሎች በጎች እጅግ ብዙ ሰዎች ጭምር ነው።—ራእይ 7:9-17
17. ሩጫውን መተው የሌለብን ለምንድን ነው? በሩጫው እስከ መጨረሻ ከቀጠልን ምን ውጤት ይገኛል?
17 ወደኋላችን ብንመለስ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መዳንን ለማግኘት ልንረዳ አንችልም። በክርስቲያናዊ ሩጫ ከጸናን ምንም ዓይነት መሰናክሎች ቢያጋጥሙንም ራሳችንን ባለማቋረጥ ለሽልማቱ እናዘጋጃለን። ራሳችንም ጥሩ የብርታት ምሳሌዎች እየሆንን ሌሎች ሰዎች ለመዳን እንዲችሉ ልንረዳቸው እንችላለን። ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ጳውሎስ የነበረው “ሽልማቱን ለማግኘት ወደ ግቡ የመሮጥ” ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል።—ፊልጵስዩስ 3:14, 15
ሩጫውን ባለማቋረጥ መቀጠል
18. ሽልማቱን ማግኘት የሚመካው በምን ላይ ነው? እስከመጨረሻ ለመቀጠል ግን መወገድ ያለበት ነገር ምንድን ነው?
18 ከይሖዋ ጎን በመቆም ክርስቲያናዊ ሩጫችንን በድል አድራጊነት መጨረሳችንና ያስቀመጠልንን ሽልማት ማግኘታችን የተመካው ሩጫው እስኪያልቅ ያለማቋረጥ በመሮጣችን ላይ ነው። ስለዚህ ለጽድቅ ጉዳይ የማይጠቅሙንን ነገሮች በራሳችን ላይ በመጫን ሸክማችንን ካበዛን እስከ ፍጻሜው መቀጠል አንችልም። ከእነዚህ አስፈላጊ ያልሆኑ ሸክሞች ከተላቀቅን በኋላ እንኳ ብቃቶቹ ብዙ ጥረትን የሚጠይቁ በመሆናቸው ትኩረታችንን በእነሱ ላይ ለማሳረፍ ከፍተኛ ጥንካሬ ይጠይቅብናል። ስለዚህ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይመክረናል፦ “እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን . . . በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ። ” (ዕብራውያን 12:1) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ልንቋቋመው የሚገባንን ሥቃይ ከልክ በላይ አክብደን ሳንመለከት አስደሳቹን ሽልማት ለማግኘት እንደሚካፈሉ አነስተኛ ዋጋዎች ብቻ መቁጠር ይገባናል።—ከሮሜ 8:18 ጋር አወዳድር።
19. (ሀ) ጳውሎስ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ምን ትምክህት እንዳለው ገለጸ? (ለ) የጽናትን ሩጫ ወደ መጨረሱ ስንቀርብ ተስፋ ስለተገባው ሽልማት ምን ትምክህት ሊኖረን ይገባል?
19 ጳውሎስ ወደ ሕይወቱ መጨረሻ ገደማ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ። ሩጫውን ጨርሻለሁ። ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ። ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” ሊል ችሏል። (2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) በዚህ የጽናት ሩጫ ውስጥ የገባነው የዘላለም ሕይወትን ሽልማት ለማግኘት ነው። ሩጫው በጀመርንበት ጊዜ ካሰብነው በላይ ረዥም በመሆኑ ምክንያት ያለማቋረጥ መሮጣችንን ትተን ብናዘግም ተስፋ የተገባውን ሽልማት ልናገኝ ከተቃረብን በኋላ ለሽልማቱ ብቁ ሳንሆን እንቀራለን። አትሳሳቱ። ሽልማቱ ስለመኖሩ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር የለም።
20. ሩጫው እስኪያልቅ ድረስ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
20 ስለዚህ ታላቁ መከራ ጀምሮ መጀመሪያ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ከዚያም በቀሪው የዲያብሎስ ድርጅት ላይ ጥፋት የሚመጣበትን ጊዜ ስንጠባበቅ ዓይኖቻችን አይድከሙ። (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) በዙሪያችን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች የሞሉ መሆናቸውን እየተመለከትን የወደፊቱን ጊዜ በእምነት ዓይናችን እንጠባበቅ። የጽናት ኃይላችንን እንደ ወገብ መታጠቂያ እንታጠቅና ፍጻሜው ደርሶን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የይሖዋ እውነተኛነትና ጻድቅነት ተረጋግጦ አስደሳቹን ሽልማት እስክናገኝ ድረስ ይሖዋ በፊታችን ባስቀመጠልን ሩጫ በብርታት እንቀጥል።
እንዴት ትመልሳለህ?
◻ አንድ ክርስቲያን ሊዘጋጅ የሚገባው ለምን ዓይነት ሩጫ ነው?
◻ በሩጫው ለመጽናት ደስታ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ መከራ ቢያጋጥመንም በአገልግሎቱ መጽናት ያለብን በምን ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሣ ነው?
◻ አምላክ በፊታችን ያስቀመጠውን ሩጫ መተው የሌለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች እንደ ረዥም ርቀት ሯጮች ጽናትና ትዕግሥት ማሳየት ይኖርባቸዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሯጮች “የሕይወትን አክሊል” ሽልማት ለማግኘት በሚሮጡበት ጊዜ ራሳቸውን መቆጣጠርና መግዛት ይገባቸዋል