ሁሉም ሰው ነፃ ይሆናል
“ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፣ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና።”—ሮሜ 8:18-22
በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሚገኘው ይህ ሐሳብ ሐዋርያው ጳውሎስ የብዙ ሰዎች ሕይወት እውነተኛ ነፃነት ያጣውና አብዛኛውን ጊዜ ባዶነትና ሥቃይ ዕጣ ፈንታቸው የሆነው ለምን እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። በተጨማሪም እውነተኛ ነፃነት እንዴት ማግኘት እንደምንችል አብራርቷል።
“የአሁኑ ዘመን ሥቃይ”
ጳውሎስ ‘ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ሲመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም አይደለም’ ብሎ ሲናገር የዚህን ዘመን ሥቃይ አቅልሎ መመልከቱ አልነበረም። በጳውሎስ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ክርስቲያኖች ለሰብዓዊ መብቶች ግዴለሽ በሆኑት የሮማ ባለ ሥልጣናት አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር በእጅጉ ማቅቀዋል። የሮማ መንግሥት ክርስቲያኖች የመንግሥት ጠላት ናቸው ብሎ አንዴ ስላመነ በኃይል ይጨቁናቸው ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ እንዲህ ብለዋል:- “በዋና ከተማው [ሮማ] የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች በትግል መወዳደሪያዎች ውስጥ ወይም ከነሕይወታቸው በእሳት ተቃጥለው በአሰቃቂ ሁኔታ ሞተዋል።” (ሾርተር ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ) አንድ ሌላ ዘገባ ስለነዚህ የኔሮ የጭካኔ ድርጊት ሰለባዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “አንዳንዶች ተሰቅለዋል፤ አንዳንዶች በአውሬዎች ቆዳ ከተሸፈኑ በኋላ ውሾች እንዲቦጫጭቋቸው ተደርገዋል፤ እንዲሁም አንዳንዶች ሲመሽ እንደ ችቦ ብርሃን እንዲሰጡ ሲባል በላያቸው ላይ ቃጥራሜ ፈሶባቸው በእሳት ተለኩሰዋል።”—ኒው ቴስታመንት ሂስትሪ በኤፍ ኤፍ ብሩስ
እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች እንዲህ ካለው ጭቆና ነፃ ለመውጣት እንደሚፈልጉ የተረጋገጠ ነው፤ ሆኖም ይህን ነፃነት ለማግኘት ሲሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች ለመጣስ ፈቃደኞች አልነበሩም። ለምሳሌ ያህል በገዥው የሮማ ባለ ሥልጣናትና ዜለትስ በመባል በሚታወቁት ቀናኢ አይሁዳውያን የነፃነት ተዋጊዎች መካከል ይደረግ ከነበረው ትግል ፍጹም ገለልተኞች ነበሩ። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) በዜለትስ አስተሳሰብ “በወቅቱ ለተከሰተው ችግር ብቸኛው መፍትሔ አምላክ የወሰነውን መልካም ጊዜ መጠባበቅ አልነበረም።” አሁን የሚፈለገው ነገር “በጠላት [በሮም] ላይ የኃይል እርምጃ መውሰድ” ነው የሚል ነበር። (ኒው ቴስታመንት ሂስትሪ) የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ግን ከዚህ የተለየ አስተሳሰብ ነበራቸው። ለእነሱ “አምላክ የወሰነውን መልካም ጊዜ መጠባበቅ” ብቸኛው ትክክለኛ አማራጭ ነበር። “የአሁኑ ዘመን ሥቃይ” ለዘላለም ተወግዶ እውነተኛና ዘላቂ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው አምላክ ጣልቃ ሲገባ መሆኑን ያምኑ ነበር። (ሚክያስ 7:7፤ ዕንባቆም 2:3) ይሁንና ይህ እንዴት እንደሚሆን ከመመልከታችን በፊት መጀመሪያውኑ ‘ፍጥረት ለከንቱነት የተገዛው’ ለምን እንደሆነ እንመርምር።
“ለከንቱነት ተገዝቶአል”
ዚ ኤምፋቲክ ዳያግሎት በተባለው መጽሐፍ ላይ ቤንጃሚን ዊልሰን “ፍጥረት” የሚለው ቃል አንዳንዶች እንደሚያስቡት “እንስሳትንና ግዑዙን ፍጥረት” ሳይሆን “መላውን የሰው ዘር” የሚያመለክት ነው ብለዋል። (ከቆላስይስ 1:23 ጋር አወዳድር።) መላውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ማለትም ነፃነት ለማግኘት የምንናፍቀውን ሁላችንንም የሚያመለክት ነው። ‘ለከንቱነት የተገዛነው’ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በወሰዱት እርምጃ ምክንያት ነው። ወደን ‘በፈቃዳችን’ ያደረግነው ወይም በግለሰብ ደረጃ በግል የመረጥነው ነገር አይደለም። ያለንበት ሁኔታ በውርስ ያገኘነው ነው። ከቅዱስ ጽሑፋዊው አመለካከት አንፃር ሲታይ ሩሶ “ሰው ነፃ ሆኖ ተወልዷል” ብሎ ሲናገር ተሳስቷል። እያንዳንዳችን በኃጢአትና በአለፍጽምና ቀንበር ሥር የተወለድን ሲሆን በተስፋ መቁረጥና በከንቱነት ለተሞላ ሥርዓት ባሮች ሆነናል ለማለት ይቻላል።—ሮሜ 3:23
ይህ የሆነው ለምን ነበር? የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን “እንደ አምላክ” ለመሆን በመፈለጋቸው ነበር። ጥሩና መጥፎ የሆነውን ለራሳቸው በመወሰን ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን በራሳቸው መምራት በመፈለጋቸው ነበር። (ዘፍጥረት 3:5) ነፃነትን የሚመለከት አንድ ወሳኝ ሐቅ ችላ ብለው ነበር። ፍጹም የሆነ ነፃነት ሊኖረው የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው። የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እሱ ነው። (ኢሳይያስ 33:22፤ ራእይ 4:11) ሰብዓዊ ነፃነት ገደብ ያለው ነፃነት ነው። ለዚህም ነው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች ‘ነጻ በሚያወጣው ፍጹሙ ሕግ’ እንዲመሩ ያበረታታው።—ያዕቆብ 1:25
ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከጽንፈ ዓለሙ ቤተሰብ አስወጣቸው፤ በዚህም ምክንያት ሞቱ። (ዘፍጥረት 3:19) ይሁን እንጂ ዘሮቻቸውስ? አዳምና ሔዋን ለልጆቻቸው ማስተላለፍ የሚችሉት አለፍጽምናን፣ ኃጢአትንና ሞትን ብቻ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በምሕረቱ ልጆችን እንዲወልዱ ፈቀደላቸው። ስለዚህ “ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ 5:12) በዚህ መንገድ አምላክ ‘ፍጥረትን ለከንቱነት አስገዝቶታል።’
‘የእግዚአብሔር ልጆች መገለጥ’
ይሖዋ፣ ፍጥረት ለከንቱነት እንዲገዛ ያደረገው ወደፊት አንድ ቀን ሰብዓዊው ቤተሰብ የእግዚአብሔር ልጆች በሚፈጽሙት ተግባር አማካኝነት ነፃነት እንደሚጎናጸፍ ‘ተስፋ’ በመስጠት ነው። እነዚህ ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ እነማን ናቸው? እንደተቀረው “[ሰብዓዊ] ፍጥረት” በኃጢአትና በአለፍጽምና ባርነት ሥር የተወለዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ናቸው። በውልደት ንጹሕና ፍጹም በሆነው የአምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ውስጥ ለእነሱ የሚገባ ቦታ የለም። ሆኖም ይሖዋ አንድ ልዩ ነገር ያደርግላቸዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከወረሱት የኃጢአት ቀንበር ነፃ ያወጣቸዋል፤ እንዲሁም ‘ጻድቃን’ ወይም መንፈሳዊ ንጽሕና ያላቸው ሰዎች አድርጎ ይቆጥራቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:11) ከዚያም “የእግዚአብሔር ልጆች” አድርጎ በመቁጠር ወደ ጽንፈ ዓለማዊው ቤተሰብ መልሶ ያመጣቸዋል።—ሮሜ 8:14-17
ይሖዋ ልጆቹ አድርጎ የተቀበላቸው እንደመሆናቸው መጠን ክብራማ መብት ይኖራቸዋል። የአምላክ ሰማያዊ ግዛት ወይም መንግሥት አባላት በመሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ‘የአምላካችን ካህናት ሆነው በምድር ላይ ይነግሣሉ።’ (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-4) ይህ መንግሥት በጭቆናና በአምባገነንነት ላይ ሳይሆን በነፃነትና በፍትሕ መመሪያዎች ላይ በጥብቅ የተመሠረተ ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 61:1-4) ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ የአምላክ ልጆች ከረዥም ጊዜ በፊት ተስፋ የተሰጠበት ‘የአብርሃም ዘር’ የሆነው የኢየሱስ ወዳጆች መሆናቸውን ገልጿል። (ገላትያ 3:16, 26, 29) ስለዚህም አምላክ ለወዳጁ ለአብርሃም የገባውን ቃል በመፈጸም ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። የዚህ ተስፋ አንዱ ክፍል በአብርሃም ዘር (ወይም ዝርያ) አማካኝነት ‘የምድር አሕዛብ ሁሉ በእርግጥ ራሳቸውን የሚባርኩ’ መሆናቸው ነው።—ዘፍጥረት 22:18 NW
ለሰው ልጆች ምን በረከቶች ያመጡላቸዋል? የአምላክ ልጆች መላውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ከአዳማዊ ኃጢአት መጥፎ መዘዞች ነፃ በማውጣቱና የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና በመመለሱ ተግባር ይካፈላሉ። ‘ከሕዝብ፣ ከነገድና ከወገን’ የተውጣጡ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመንና በደግነት ለሚያስተዳድረው የክርስቶስ መንግሥት ተገዥ በመሆን ራሳቸውን ሊባርኩ ይችላሉ። (ራእይ 7:9, 14-17፤ 21:1-4፤ 22:1, 2፤ ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) በዚህ መንገድ “ፍጥረት ሁሉ” ‘የእግዚአብሔርን ልጆች ክብራማ ነፃነት’ መልሶ ያገኛል። ይህ ነፃነት ውሱንና ጊዜያዊ የሆነ ፖለቲካዊ ነፃነት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አዳምና ሔዋን የአምላክን ሉዓላዊነት አንቀበልም ካሉበት ጊዜ አንስቶ በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ሥቃይና ጭንቀት ካስከተሉ ነገሮች በሙሉ ነፃ መውጣት ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የታመኑ ሰዎች ከሚፈጽሙት ክብራማ አገልግሎት ጋር ሲወዳደር ‘የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም አይደለም’ ብሎ መናገሩ ምንም አያስደንቅም!
‘የእግዚአብሔር ልጆች መገለጥ’ የሚጀምረው መቼ ነው? ይሖዋ የእግዚአብሔር ልጆች እነማን መሆናቸውን ግልጽ በሚያደርግበት ጊዜ በቅርቡ ይሆናል። ይህ የሚሆነው ከሞት ተነሥተው ወደ መንፈሳዊው ዓለም የገቡት እነዚህ “ልጆች” ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በአምላክ የአርማጌዶን ጦርነት ይህችን ምድር ከክፋትና ከጭቆና ነፃ በማውጣቱ ተግባር በሚካፈሉበት ጊዜ ነው። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14, 27፤ ራእይ 2:26, 27፤ 16:16፤ 17:14፤ 19:11-21) ወደ ‘መጨረሻዎቹ ቀናት’ ዘልቀን መግባታችንን ማለትም አምላክ ለረዥም ጊዜ ታግሦ የቆየው ዓመፅና የእሱ ውጤት የሆነው ክፋት የሚያበቃበት ጊዜ መቅረቡን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች በዙሪያችን እንመለከታለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:3-31
አዎን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩ” እውነት ነው። ሆኖም ሁኔታው በዚህ መልኩ አይቀጥልም። በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ ሰላምን፣ ነፃነትንና ፍትሕን ማጎናጸፍን ጨምሮ ‘እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው ነገር ሁሉ ሲፈጸም’ ይመለከታሉ።—ሥራ 3:21
በመጨረሻ እውነተኛ ነፃነት ይጨበጣል
‘የእግዚአብሔርን ልጆች ክብራማ ነፃነት’ አግኝተህ ለመደሰት ምን ማድረግ አለብህ? ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል።” (ዮሐንስ 8:31, 32) ነፃነት የሚያስገኘው ቁልፍ የክርስቶስን ሕግጋትና ትምህርቶች መማርና መታዘዝ ነው። ይህን ማድረጉ አሁን እንኳ የተወሰነ ነፃነት ያስገኛል። በቅርቡ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አገዛዝ ሥር ፍጹም ነፃነት ያስገኛል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት የኢየሱስን ‘ቃል’ ማወቅ ጥበብ ያለበት አካሄድ ነው። (ዮሐንስ 17:3) እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት በሚገኙበት ጉባኤ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ይኑርህ። እንዲህ በማድረግ በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት ከሚያቀርባቸው ነፃ የሚያወጡ የእውነት ትምህርቶች ልትጠቀም ትችላለህ።—ዕብራውያን 10:24, 25
‘የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ እየተጠባበቅህ’ እየደረሰብህ ያለው መከራና የፍትሕ መጓደል ከአቅምህ በላይ የሆነ በሚመስልህ ጊዜ እንኳ ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ ጥበቃና ድጋፍ ላይ የነበረውን ዓይነት ትምክህት አዳብር። ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር ልጆች መገለጥ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን?” (ሮሜ 8:35) እርግጥ እንደ ሩሶ አባባል በጳውሎስ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በአንድ መልኩም ይሁን በሌላ በጨቋኝ ኃይሎች “የባርነት ቀንበር” ሥር ይገኙ ነበር። “እንደሚታረዱ በጎች” ‘ቀኑን ሙሉ እንደሚገደሉ’ ሆነው ነበር። (ሮሜ 8:36) ታዲያ በዚህ ሁኔታ እጃቸውን ሰጡን?
ጳውሎስ “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 8:37) የጥንት ክርስቲያኖች ያንን ሁሉ መከራ በጽናት ተቋቁመው አሸናፊ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነበር? ጳውሎስ መልስ ሲሰጥ “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ” ብሏል። (ሮሜ 8:38, 39) አንተም ብትሆን በአሁኑ ጊዜ በጽናት ልትቋቋመው የሚገባህ ‘መከራ፣ ጭንቀት ወይም ስደት’ ቢኖርብህም ‘በአሸናፊነት’ ልትወጣው ትችላለህ። በቅርቡ ‘ከማንኛውም ዓይነት ባርነት ነፃ ወጥተን የእግዚአብሔርን ልጆች ክብራማ ነፃነት እንደምንጎናጸፍ’ የአምላክ ፍቅር አስተማማኝ ማረጋገጫ ይሰጣል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ [ይኖራል]”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ፍጥረት ከጥፋት ባርነት ሁሉ ነፃ ወጥቶ የእግዚአብሔርን ልጆች ክብራማ ነፃነት ይጎናጸፋል’