የክርስቲያን ቤተሰብ አረጋውያንን ይረዳል
“በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፣ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ።” — መዝሙር 71:9
1. በብዙ ባሕሎች አረጋውያን ምን እያጋጠማቸው ነው?
“በደል ከሚፈጸምባቸው ሰባት አረጋውያን መካከል ስድስቱ (86 በመቶ የሚያክሉት) አግባብ ያልሆነ ድርጊት የሚፈጸምባቸው በራሳቸው ቤተሰቦች እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ” በማለት ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ገልጿል። ሞደርን ማቹሪቲ የተባለው መጽሔት “አረጋውያንን ማንገላታት በቅርቡ ከተደበቀበት ጓዳ ወደ አሜሪካ ጋዜጦች መውጣት የጀመረ [የቤተሰብ ዓመፅ] ነው” ሲል ገልጿል። አዎ፣ በብዙ ባሕሎች ውስጥ የሚኖሩ አረጋውያን በጣም እየተንገላቱና ቸል እየተባሉ ነው። በእርግጥም ጊዜያችን ብዙ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ . . . የማያመሰግኑ (ውለታ ቢሶች 1980 ትርጉም ) ሐሰተኞች፣ የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” የሆኑበት ጊዜ ነው። — 2 ጢሞቴዎስ 3:1–3 አዓት
2. በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ይሖዋ አረጋውያንን የሚመለከተው እንዴት ነው?
2 ይሁን እንጂ በጥንት እስራኤል አረጋውያን በዚህ መንገድ መያዝ አልነበረባቸውም። ሕጉ እንዲህ ይላል:- “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር፣ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ የጥበብ ምሳሌዎች የሚገኙበት መጽሐፍም እንዲህ ሲል ይመክረናል:- “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።” እንዲህም ሲል ያዝዛል:- “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው።” የሙሴ ሕግ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች አረጋውያን አክብሮትና አሳቢነት ማሳየት እንደሚገባ ያስተምራል። ይሖዋ አረጋውያን እንዲከበሩ እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። — ዘሌዋውያን 19:32፤ ምሳሌ 1:8፤ 23:22
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አረጋውያንን መንከባከብ
3. ዮሴፍ ላረጀው አባቱ ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነበር?
3 አክብሮት ማሳየት የነበረባቸው በቃል ብቻ ሳይሆን አሳቢነት በተሞላባቸው ሥራዎች ጭምር ነበር። ዮሴፍ ላረጀው አባቱ ትልቅ የርኅራኄ ስሜት አሳይቷል። ያዕቆብ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ተጉዞ ከከነዓን ወደ ግብጽ እንዲመጣ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ ዮሴፍ ለያዕቆብ “የግብፅን በረከት የተሸከሙ አሥር አህዮችን፣ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ ስንዴና እንጀራ የተሸከሙ አሥር ሴቶች አህዮችን” ላከ። ያዕቆብም ጌሤም ሲደርስ ዮሴፍ ሊቀበለው ወጣ፣ “ባየውም ጊዜ በአንገቱ ላይ ወደቀ፣ አቅፎትም ረጅም ጊዜ አለቀሰ።” ዮሴፍ ለአባቱ ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል። ለአረጋውያን አሳቢ እንድንሆን የሚያነሳሳን እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ ነው! — ዘፍጥረት 45:23፤ 46:5, 29
4. ሩት ልንከተላት የሚገባን ጥሩ ምሳሌ የሆነችው ለምንድን ነው?
4 ለአረጋውያን ደግ በመሆን ረገድ ልንከተላት የሚገባን ሌላዋ ግሩም ምሳሌ ሩት ነች። ምንም እንኳን ከአሕዛብ ወገን ብትሆንም አይሁዳዊ ከሆነችው አሮጊት መበለት አማትዋ ከኑኃሚን ጋር የሙጥኝ ብላለች። ሌላ ባል የማግኘት ዕድሏን የሚያሳጣት ቢሆንም የራሷን ሕዝብ ትታ ሄዳለች። ሩት ወደ ራሷ ሕዝብ እንድትመለስ ኑኃሚን ብትወተውታትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፉት ሁሉ እጅግ ውብ በሆኑት በሚከተሉት ቃላት መለሰችላት:- “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፣ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፣ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ አለች።” (ሩት 1:16, 17) በተጨማሪም ሩት ዋርሳ ማግባት በሚያዘው ዝግጅት መሠረት በእድሜ የገፋውን ቦዔዝን ለማግባት ፈቃደኛ በመሆን ግሩም ባሕርያትን አሳይታለች። — ሩት ምዕራፍ 2 እስከ ምዕራፍ 4
5. ኢየሱስ ለአረጋውያን ባደረጋቸው ነገሮች ምን ባሕሪዎችን አሳይቶ ነበር?
5 ኢየሱስም ለሰዎች ባደረጋቸው ነገሮች ተመሳሳይ ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ ትዕግስተኛ፣ አዛኝ፣ ደግና ሰዎችን የሚያሳርፍ ነበር። ለ38 ዓመት መራመድ ለማይችል አካለ ስንኩል ለነበረ አንድ ሰው አዘነለትና ፈወሰው። ለመበለቶችም አሳቢነት አሳይቷል። (ሉቃስ 7:11–15፤ ዮሐንስ 5:1–9) በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ይሠቃይ በነበረበት ጊዜ እንኳን ምናልባት በ50ዎቹ እድሜዋ ውስጥ የምትገኘው እናቱ የሚያስፈልጋትን እንክብካቤ እንድታገኝ አድርጓል። ከግብዞቹ ጠላቶቹ በስተቀር ሌሎች ሰዎችን በሙሉ ያዝናና ያሳርፍ ነበር። በዚህ ምክንያት እንዲህ ለማለት ችሏል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።” — ማቴዎስ 9:36፤ 11:28, 29፤ ዮሐንስ 19:25–27
አሳቢነት የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው?
6. (ሀ) ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው? (ለ) ራሳችንን ምን ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን?
6 እንክብካቤ በማድረግ ረገድ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የመሰለ ግሩም ምሳሌ ስለተዉልን ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖችም የእነሱን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ ነው። ለብዙ ዓመት ሲደክሙና ከባድ ኃላፊነቶችን ተሸክመው የቆዩ በሽምግልና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አረጋውያን ወንድሞችና እኅቶች በመካከላችን አሉ። አንዳንዶቹ ወላጆቻችን ወይም አያቶቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ እነዚህን በግዴለሽነት እንመለከታቸዋለንን? እያቃለልናቸውና ዝቅ እያደረግናቸው ነውን? ወይስ ያላቸውን ሰፊ ተሞክሮና ጥበብ ከልብ እናደንቃለን? እውነት ነው፣ አንዳንዶች አብዛኛውን ጊዜ በእርጅና ወቅት የሚያዩአቸው የተለዩ ፀባዮች ትዕግሥታችንን ሊፈትኑት ይችላሉ። ይሁን እንጂ “እኔ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ብሆን ኖሮ ከእነሱ የተለየሁ እሆን ነበርን?” ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።
7. ራሳችንን በአረጋውያን ቦታ አድርገን መመልከት እንደሚያስፈልገን የትኛው ምሳሌ ያስረዳል?
7 ለአንዲት አሮጊት ርኅራኄ ስላሳየች አንዲት ወጣት ልጃገረድ የሚናገር ከመካከለኛው ምሥራቅ የተገኘ ልብን የሚነካ አንድ ታሪክ አለ። አንዲት አያት ወጥቤት ውስጥ ልጃቸውን እያገዙ ሳሉ አንድ የሸክላ ሳህን በድንገት ይወድቅና ይሰበርባቸዋል። በራሳቸው ቅልጥፍና ማጣት ተናደዱ። ልጃቸውም ከእሳቸው የበለጠ በጣም ተቆጣች። ከዚያም ልጅቱ የራሷን ሴት ልጅ ትጠራና በአካባቢው ከሚገኘው ሱቅ ለአያቷ የማይሰበር የእንጨት ሳህን እንድትገዛ ትልካታለች። ልጅቷም ሁለት የእንጨት ሳህኖች ይዛ መጣች። እናትየዋም “ለምን ሁለት ሳህኖች ገዛሽ?” ስትል ጠየቀቻት። ልጅቷም ፈራ ተባ እያለች “አንዱ ለአያቴ አንዱ ደግሞ ስታረጂ ለአንቺ ይሆናል” ስትል መለሰች። አዎ፣ በዚህ ዓለም እስከኖርን ድረስ ሁላችንም ከእርጅና አናመልጥም። ታዲያ በምናረጅበት ጊዜ በትዕግሥትና በደግነት ብንያዝ ደስ አይለንምን? — መዝሙር 71:9
8, 9. (ሀ) በመካከላችን ያሉትን አረጋውያን እንዴት አድርገን መያዝ ይኖርብናል? (ለ) በቅርቡ ክርስቲያን የሆኑ አንዳንዶች ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው?
8 ብዙዎች በዕድሜ ያረጁ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን የረጅም ጊዜ ክርስቲያናዊ የታማኝነት ተግባር እንዳስመዘገቡ በፍጹም አትዘንጉ። በእርግጥም የእኛ አክብሮት፣ አሳቢነት፣ የደግነት እርዳታና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ጠቢቡ ሰው “የሸበተ ጠጉር የክብር ዘውድ ነው፣ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል” ሲል የተናገረው ትክክል ነው። ይህ የሸበተ ሰው፣ ወንድ ይሁን ሴት መከበር ይኖርበታል። ከእነዚህ አረጋውያን ወንዶችና ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ አሁንም ታማኝ አቅኚዎች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። ብዙ ወንዶችም በጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌዎች ሆነው በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል፤ አንዳንዶቹም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በመሆን በምሳሌነት የሚጠቀስ ሥራ ይሠራሉ። — ምሳሌ 16:31
9 ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል መክሮታል:- “ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፣ እርሱን ግን እንደ አባት፣ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፣ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፣ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው።” (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ባለጌ ከሆነው ዓለም ወጥተው በቅርቡ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ የመጡ ሰዎች በፍቅር ላይ የተመሠረቱትን የጳዎሎስን ቃላት ልብ ሊሏቸው ይገባል። ወጣቶች በትምህርት ቤት የምታዩአቸውን መጥፎ ዝንባሌዎች አትቅሰሙ። በእድሜ ያረጁ የይሖዋ ምስክሮች የሚሰጧችሁን የደግነት ምክር አትጥሉ። (1 ቆሮንቶስ 13:4–8፤ ዕብራውያን 12:5, 6, 11) ሆኖም አረጋውያን በጤና ወይም በገንዘብ ችግር ምክንያት እርዳታ ሲያስፈልጋቸው እነሱን ለመርዳት በቅድሚያ ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?
አረጋውያንን በመንከባከብ ረገድ የቤተሰብ ሚና
10, 11. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት አረጋውያንን በመንከባከብ ረገድ ቀዳሚ መሆን የሚኖርበት ማን ነው? (ለ) አረጋውያንን መንከባከብ ሁልጊዜ ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው?
10 በጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መበለቶችን በመንከባከብ ረገድ ችግር ተነስቶ ነበር። መበለቶች ስለሚረዱበት መንገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ያመለከተው እንዴት ነበር? “በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን ከካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” — 1 ጢሞቴዎስ 5:3, 4, 8
11 አረጋውያንን መርዳት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የመጀመሪያዎቹ ረዳቶች የቅርብ ቤተሰብ አባሎች መሆን ይኖርባቸዋል።a ራሳቸውን የቻሉ ልጆች ወላጆቻቸው እነሱን በመንከባከብ ላሳለፉአቸው የፍቅርና የድካም ዓመታት ያላቸውን አድናቆት በዚህ መንገድ ሊያሳዩ ይችላሉ። ይህም ቀላል ላይሆን ይችላል። ሰዎች እያረጁ ሲሄዱ ጉትት ይላሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም አካለ ስንኩል ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ ባይመስላቸውም እንኳን ራስ ወዳዶችና ምናልባትም ብዙ ነገር እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ እኛስ ሕፃናት በነበርንበት ጊዜ ራስ ወዳዶችና ብዙ ነገር እንዲደረግልን የምንጠይቅ አልነበርንምን? ወላጆቻችንስ እኛን ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አልነበራቸውምን? አሁን ግን በእርጅና ዕድሜያቸው ሁኔታው ተለውጦአል። ታዲያ ምን ያስፈልጋል? ርኅራኄና ትዕግሥት አያስፈልግምን? — ከ1 ተሰሎንቄ 2:7, 8 ጋር አወዳድር።
12. ለአረጋውያን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ላሉት ለሌሎች ሁሉ እንክብካቤ ለማድረግ ምን ባሕሪያት ያስፈልጋሉ?
12 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ በመጻፍ በሥራ ላይ ሊውል የሚችል ምክር ሰጥቷል:- “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።” እንዲህ ዓይነቱን ርኅራኄና ፍቅር በጉባኤ ውስጥ ማሳየት የሚኖርብን ከሆነ ታዲያ በቤተሰብ ውስጥ ይበልጥ ማሳየት አይኖርብንምን? — ቆላስይስ 3:12–14
13. ከአረጋውያን ወላጆቻችን ወይም አያቶቻችን ሌላ እነማን እርዳታ ሊፈልጉ ይችላሉ?
13 አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ እርዳታ የሚያስፈልገው ለወላጆቻችንና ለአያቶቻችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አረጋውያን ዘመዶቻችን ጭምር ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ልጆች የሌሉአቸው አረጋውያን በሚሲዮናዊነት አገልግሎት፣ በተጓዥነት አገልግሎትና በሌላ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለብዙ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው። በሕይወታቸው ሁሉ መንግሥቱን ከልብ ሲያስቀድሙ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 6:33) ታዲያ ለእነዚህ አረጋውያን የአሳቢነት መንፈስ ማሳየት ተገቢ አይሆንምን? የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለአረጋውያን የቤቴል አባሎች የሚያደርገው እንክብካቤ ግሩም ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። በብሩክሊን በሚገኘው ዋናው ቤቴልና በብዙ የማኅበሩ ቅርንጫፎች በርካታ ያረጁ ወንድሞችና እኅቶች በዚህ ሥራ በተመደቡ የሰለጠኑ የቤተሰቡ አባላት በየቀኑ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። እነዚህን አረጋውያን እንደ ወላጆቻቸውና እንደ አያቶቻቸው አድርገው በመመልከት በደስታ ይንከባከቧቸዋል። በዚያውም ከእነዚህ አረጋውያን የሕይወት ተሞክሮ ብዙ ይማራሉ። — ምሳሌ 22:17
አረጋውያንን በመንከባከብ ረገድ ጉባኤው ያለው ሚና
14. በጥንት ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለነበሩት አረጋውያን ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር?
14 ዛሬ በብዙ አገሮች ላረጁ ሰዎች የሚሰጥ የመንግሥት ጡረታና የሕክምና አገልግሎት አለ። ክርስቲያኖች ከዚህ ዝግጅት የመጠቀም መብት ካላቸው ሙሉ በሙሉ መጠቀም ይችላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ግን እንዲህ ዓይነት ዝግጅት አልነበረም። ስለዚህ የክርስቲያን ጉባኤ ችግር ላይ የወደቁትን መበለቶች ለመርዳት አፋጣኝ እርምጃ ወስዷል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጥቷል:- “ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዲያንስ፣ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤ ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፣ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፣ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፣ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።” እንግዲያው አረጋውያንን በመርዳት ረገድ ጉባኤውም ጭምር የራሱ ድርሻ እንዳለው ጳውሎስ አሳይቷል። የሚያምኑ ልጆች የሌላትና መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላት ሴት ለዚህ ዓይነቱ እርዳታ ብቁ ትሆናለች። — 1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10
15. መንግሥት ለአረጋውያን የሚያደርገውን እርዳታ ለማግኘት እርዳታ ሊያስፈልግ የሚችለው ለምንድን ነው?
15 መንግሥት አረጋውያንን በሚጦርባቸው አገሮችም ቢሆን ከጡረታው ተጠቃሚ ለመሆን ማመልከቻ መጻፍንና ማስገባትን የመሳሰለ አድካሚ ሥራ ማከናወን አስፈላጊ ይሆናል። እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ አረጋውያኑ እርዳታውን እንዲያገኙ ወይም ያገኙ የነበረውን እርዳታ ለማስጨመር ወይም ለማሳደስ በጉባኤ ውስጥ ያሉ የበላይ ተመልካቾች እርዳታ እንዲደረግ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ይሆናል። የጡረታውን ገንዘብ እንዲጨመር የሚያስችሉ ሁኔታዎች የሚፈጠሩበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። አረጋውያኑ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የበላይ ተመልካቾች ዝግጅት ሊያደርጉ የሚችሉባቸው ብዙ ሌሎች ተግባራዊ የሆኑ ነገሮችም አሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
16, 17. በጉባኤ ውስጥ ላሉት አረጋውያን በምን የተለያዩ መንገዶች እንግዳ ተቀባይነትን ልናሳይ እንችላለን?
16 እንግዳ ተቀባይነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጀምሮ የነበረ ባሕል ነው። እስከ ዛሬም ድረስ በብዙ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ቢያንስ ቢያንስ ቡና ወይም ሻይ በማቅረብ እንግዶችን ተቀብሎ ማስተናገድ የተለመደ ነው። እንግዲያው ጳውሎስ “ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ” ብሎ መጻፉ አያስገርምም። (ሮሜ 12:13) እንግዳ መቀበል (ሆስፒታሊቲ) ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ፊሎክሴኒያ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “እንግዶችን ማፍቀር (መውደድ ወይም ለእንግዶች ደግነት ማሳየት)” ማለት ነው። አንድ ክርስቲያን እንግዶችን ተቀብሎ የማስተናገድ ግዴታ ካለበት በእምነት ለሚዛመዱት የበለጠ ማድረግ አይኖርበትምን? ምግብ መጋበዝ ብዙውን ጊዜ ያረጀውን ሰው አሰልቺ ከሆነው ዕለታዊ ሥራ ያሳርፈዋል። በማኅበራዊ ግብዣዎቻችሁ ላይ የጥበብ ቃልና ተሞክሮ ለመስማት ከፈለጋችሁ አረጋውያን እንዲገኙ አድርጉ። — ከሉቃስ 14:12–14 ጋር አወዳድር።
17 ያረጁ ሰዎች ሊበረታቱ የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ወደ መንግሥት አዳራሽ ወይም ወደ ትልልቅ ስብሰባዎች በምንጓዝበት ጊዜ በዛ ብለን በአንድ መኪና የምንጓዝ ከሆነ ይዘናቸው ብንሄድ ደስ የሚላቸው አረጋውያን አሉን? እነሱ እስኪጠይቋችሁ ድረስ አትጠብቁ። ይዛችኋቸው ለመሄድ እንደምትፈልጉ ንገሯቸው። እነሱን የምንረዳበት ሌላው ተግባራዊ የሆነ መንገድ ገበያቸውን መገብየት ነው። ወይም የሚችሉ ከሆነ እኛ ወደ ገበያ በምንሄድበት ጊዜ ይዘናቸው ልንሄድ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይዘናቸው በምንሄድበት ጊዜ ምናልባት አስፈላጊ ከሆነ ለማረፍ የሚችሉበት ቦታ መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ትዕግሥትና ደግነት እንደሚጠይቅ ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ የአረጋውያኑ ልባዊ ምስጋና ድካማችንን ያካክስልናል። — 2 ቆሮንቶስ 1:11
የጉባኤው ውብ ንብረቶች
18. አረጋውያን ለጉባኤው በረከት የሆኑት ለምንድን ነው?
18 በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ የሸበቱ ሰዎችን (አርጅተው ራሰ በራ የሆኑትን ጭምር) ማየት እንዴት ያለ በረከት ነው! ይህ ማለት በወጣቶች ብርታትና ጥንካሬ መካከል የጥበብና የሕይወት ተሞክሮ ነጠብጣብ ይኖራል ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ለማንኛውም ጉባኤ ትልቅ ንብረት ነው። እውቀታቸው ከጉድጓድ እንደሚቀዳ የሚያረካ ውኃ ነው። ምሳሌ 18:4 “የሰው አፍ ቃል የጠለቀ ውኃ ነው፣ የጥበብም ምንጭ ፈሳሽ ወንዝ ነው” እንደሚለው ነው። ያረጁ ሰዎች የሚፈለጉና የሚወደዱ መሆናቸውን ማወቃቸው በጣም ያበረታታቸዋል። — ከመዝሙር 92:14 ጋር አወዳድር።
19. አንዳንዶች ለአረጋውያን ወላጆቻቸው ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉት እንዴት ነው?
19 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ አንዳንድ ወንድሞችና እኅቶች የደከሙ ወላጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ ያሏቸውን መብቶች መተውና ወደ አገራቸው መመለስ ግዴታቸው እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ቀደም ሲል ለእነሱ ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ለከፈሉላቸው ወላጆቻቸው መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ከዚህ በፊት ሚሲዮናውያን የነበሩና አሁንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ አንድ ባልና ሚስት አረጋውያን ወላጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ወላጆቻቸውን ሲጦሩ ቆይተዋል። ከአራት ዓመት በፊት የወንድዬው እናት ለአረጋውያን እንክብካቤ ወደሚደረግላቸው ድርጅት መግባት ተገደዋል። አሁን በ60ዎቹ ዓመታት እድሜ ውስጥ የሚገኘው ባል የ93 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን እናቱን በየቀኑ ይጠይቃል። “እናቴ ነች እኮ! እንዴት ልተዋት እችላለሁ?” ሲል ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ ልጆቻቸው በተመደቡበት ሥራ እንዲቀጥሉ ለማስቻል ጉባኤዎችና ግለሰቦች አረጋውያኑን ለመንከባከብ ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲህ ዓይነቱ ከራስ ወዳድነት የራቀ ፍቅር በጣም ሊመሰገን የሚገባው ነው። አረጋውያን ቸል መባል ስለሌለባቸው እያንዳንዱ ሁኔታ በማስተዋል መያዝ አለበት። አረጋውያን ወላጆቻችሁን ከልብ እንደምትወዱ አሳዩ። — ዘጸአት 20:12፤ ኤፌሶን 6:2, 3
20. አረጋውያንን በመንከባከብ ረገድ ይሖዋ ምን ምሳሌ ሰጥቶናል?
20 በእርግጥም አረጋውያን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ለሚኖሩበት ቤተሰብም ሆነ ጉባኤ ውብ የሆኑ የክብር ዘውድ ናቸው። ይሖዋ እንዲህ ብሏል:- “እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፣ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ።” እኛም በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ለሚገኙት ያረጁ ወንድሞችና እህቶች ተመሳሳይ ትዕግሥትና እንክብካቤ እናሳይ። — ኢሳይያስ 46:4፤ ምሳሌ 16:31
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አረጋውያንን ለመርዳት የቤተሰብ አባሎች ምን ማድረግ እንደሚችሉ ዝርዝር ሐሳቦችን ለማግኘት ሰኔ 1, 1987 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13–18 ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ አረጋውያንን በመንከባከብ ረገድ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች አሉልን?
◻ አረጋውያንን እንዴት መያዝ ይኖርብናል?
◻ የቤተሰብ አባሎች ለሚያፈቅሯቸው አረጋውያን እንክብካቤ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ አረጋውያንን ለመርዳት ጉባኤው ምን ሊያደርግ ይችላል?
◻ አረጋውያን ለሁላችንም በረከት የሆኑት ለምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት አሮጊት ለነበረችው ለኑኃሚን ደግነትና አክብሮት አሳይታለች
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አረጋውያን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የጉባኤው አባላት ናቸው