“ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ”
“ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ።”—ሮሜ 12:17
1. ብዙዎች ምን የማድረግ ልማድ አላቸው?
አንድ ልጅ ወንድሙ ቢገፋው መጀመሪያ የሚታየው ነገር እርሱም መልሶ መግፋት ነው። የሚያሳዝነው ግን እንዲህ የሚያደርጉት ልጆች ብቻ አይደሉም። በርካታ አዋቂዎችም አንድ ነገር ሲደረግባቸው አጸፋ ይመልሳሉ። አንድ ሰው ቅር ካሰኛቸው ብድር መመለስ ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ አዋቂዎች ግለሰቡን ቃል በቃል መልሰው አይገፈትሩት ይሆናል፤ ሆኖም ብዙዎች ስውር በሆኑ መንገዶች አጸፋውን ይመልሳሉ። ምናልባትም ያስቀየማቸውን ሰው በተመለከተ ጎጂ ሐሜት ያናፍሱ ወይም ስኬታማ እንዳይሆን ጥረት ያደርጉ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የሚጠቀሙበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን፣ ዓላማቸው አጸፋ መመለስ ወይም መበቀል ነው።
2. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች አጸፋ ከመመለስ የሚቆጠቡት ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎችና የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንመረምራለን?
2 የሰው ልጆች አጸፋ የመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ” በማለት የሰጠውን ምክር ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። (ሮሜ 12:17) ከዚህ ላቅ ያለ መሥፈርት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ክፉን በክፉ መመለስ የሌለብን ለእነማን ነው? አጸፋ ከመመለስ ከተቆጠብን ምን ጥቅሞች እናገኛለን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጳውሎስ በሰጣቸው ማሳሰቢያዎች ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች እንመልከት፤ እንዲሁም ሮሜ ምዕራፍ 12 አጸፋ ከመመለስ መቆጠብ ትክክለኛ ብሎም ፍቅርና ትሕትና የሚንጸባረቅበት እርምጃ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመርምር። እነዚህን ሦስት ነጥቦች አንድ በአንድ እንመለከታለን።
‘እንግዲህ ወንድሞች ሆይ እለምናችኋለሁ’
3, 4. (ሀ) ጳውሎስ ከሮሜ ምዕራፍ 12 ጀምሮ የትኞቹን ጉዳዮች አብራርቷል? “እንግዲህ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? (ለ) የአምላክ ርኅራኄ በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖችን ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባ ነበር?
3 ጳውሎስ ከምዕራፍ 12 ጀምሮ ባሉት ምዕራፎች ላይ የክርስቲያኖችን ሕይወት የሚነኩ አራት ተዛማጅነት ያላቸው ርዕሶችን ያብራራል። ከይሖዋ፣ ከእምነት ባልንጀሮቻችን፣ ከማያምኑ ሰዎችና ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነት ይገልጻል። ጳውሎስ አጸፋ የመመለስ ፍላጎትን ጨምሮ መጥፎ ዝንባሌዎችን እንድንዋጋ የሚገፋፋን መሠረታዊ ምክንያት እንዳለ ሲገልጽ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ . . . በእግዚአብሔር ርኀራኄ እለምናችኋለሁ” ብሏል። (ሮሜ 12:1) እዚህ ላይ “እንግዲህ” የሚለውን ቃል ልብ እንበል፤ ይህ ቃል “ቀደም ሲል ከተመለከትነው አንጻር” የሚል ትርጉም አለው። በሌላ አባባል ጳውሎስ ‘ከዚህ ቀደም ካብራራሁላችሁ ነገሮች አንጻር ቀጥሎ የምነግራችሁን እንድታደርጉ እለምናችኋለሁ’ ማለቱ ነበር። ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ቀደም ሲል ያብራራላቸው ምን ነበር?
4 ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ የመጀመሪያዎቹ 11 ምዕራፎች ላይ አይሁዳውያንም ሆኑ አሕዛብ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አብረው የመግዛት ግሩም መብት እንዳገኙ አብራርቷል፤ እስራኤላውያን ግን ይህንን መብት ሳይቀበሉት ቀርተዋል። (ሮሜ 11:13-36) ይህ ውድ መብት ሊገኝ የቻለው “በእግዚአብሔር ርኀራኄ” ብቻ ነው። ክርስቲያኖች ለዚህ ይገባናል የማንለው የአምላክ ደግነት ምን ምላሽ መስጠት አለባቸው? ልባቸው በጥልቅ አድናቆት ሊሞላና ጳውሎስ ቀጥሎ የተናገረውን ለማድረግ ሊነሳሱ ይገባል፤ ሐዋርያው “ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]፤ . . . ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኮአችሁ ነው” ብሏቸዋል። (ሮሜ 12:1) ይሁን እንጂ እነዚያ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለአምላክ “መሥዋዕት” አድርገው ማቅረብ የሚችሉት እንዴት ነበር?
5. (ሀ) አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ “መሥዋዕት” አድርጎ ማቅረብ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በአንድ ክርስቲያን አኗኗር ላይ ተጽዕኖ ሊያደርግ የሚገባው የትኛው መሠረታዊ ሥርዓት ነው?
5 ጳውሎስ ቀጥሎ እንዲህ ብሏል:- “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) ክርስቲያኖች የዓለም መንፈስ አስተሳሰባቸውን እንዲቀርጸው ከመፍቀድ ይልቅ አእምሯቸው ታድሶ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ ነበረባቸው። (1 ቆሮንቶስ 2:16፤ ፊልጵስዩስ 2:5) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ የምንገኘውን ጨምሮ በሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች የዕለት ተዕለት አኗኗር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል።
6. ጳውሎስ በሮሜ 12:1, 2 ላይ በሰጠው ማብራሪያ መሠረት አጸፋ ከመመለስ እንድንቆጠብ የሚያደርገን ምንድን ነው?
6 ጳውሎስ በሮሜ 12:1, 2 ላይ የሰጠው ማብራሪያ ለእኛ የሚጠቅመን እንዴት ነው? በሮም እንደነበሩት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም አምላክ በተለያዩ መንገዶች ላሳየንና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ዘወትር ለሚያሳየን ርኅራኄ ከልብ የመነጨ አድናቆት አለን። እንግዲህ ልባችን በአድናቆት መሞላቱ አምላክን በሙሉ ኃይላችን፣ ጥሪታችንና ችሎታችን እንድናገለግለው ያነሳሳናል። እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት እንደ ዓለም ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ለማሰብ የተቻለንን ያህል እንድንጥርም ይገፋፋናል። የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ መያዛችን ደግሞ ከእምነት ባልንጀሮቻችንም ሆነ ከማያምኑ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ገላትያ 5:25) ለምሳሌ፣ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ካለን አጸፋ ለመመለስ የሚታገለንን ስሜት ለማሸነፍ እንገፋፋለን።—1 ጴጥሮስ 2:21-23
“ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን”
7. በሮሜ ምዕራፍ 12 ላይ የተገለጸው ምን ዓይነት ፍቅር ነው?
7 ክፉን በክፉ ከመመለስ የምንቆጠበው፣ ትክክለኛ እርምጃ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ፍቅር የሚንጸባረቅበት አካሄድ በመሆኑም ጭምር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅር ምን እንድናደርግ እንደሚያነሳሳን ሲገልጽ ምን እንዳለ እንመልከት። ሐዋርያው፣ በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ የአምላክንና የክርስቶስን ፍቅር ለመግለጽ አጋፔ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ብዙ ጊዜ ተጠቅሞበታል። (ሮሜ 5:5, 8፤ 8:35, 39) በምዕራፍ 12 ላይ ግን ጳውሎስ አጋፔ የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ለየት ባለ መንገድ ይኸውም ለሌሎች ሰዎች የምናሳየውን ፍቅር ለመግለጽ ነው። ጳውሎስ መንፈሳዊ ስጦታዎች የተለያዩ እንደሆኑና አንዳንድ አማኞች ደግሞ እነዚህ ስጦታዎች እንዳሏቸው ከተናገረ በኋላ ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያዳብሩት የሚገባውን ባሕርይ ሲጠቅስ “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን” ብሏል። (ሮሜ 12:4-9) ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ማሳየት የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዋና መለያ ነው። (ማርቆስ 12:28-31) ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የምናሳየው ፍቅር ከልብ የመነጨ መሆን እንዳለበት አሳስቦናል።
8. ከግብዝነት የራቀ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ በመቀጠልም ከግብዝነት የራቀ ፍቅር እንዴት ማሳየት እንደሚቻል ሲገልጽ “ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ፤ በጎ ከሆነው ነገር ጋር ተቈራኙ” ብሏል። (ሮሜ 12:9) “ተጸየፉ” እና “ተቈራኙ” የሚሉት ቃላት ጠንከር ያለ አንድምታ አላቸው። “ተጸየፉ” የሚለው ቃል “አጥብቆ መጥላት” ተብሎ ሊተረጎምም ይችላል። ክፉ ነገር የሚያስከትላቸውን መዘዞች ብቻ ሳይሆን ክፉ የሆነውን ነገር ጭምር መጥላት ይገባናል። (መዝሙር 97:10) “ተቈራኙ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “መጣበቅ” ማለት ነው። እውነተኛ ፍቅር ያለው ክርስቲያን በጎ ከሆነው ነገር ጋር በጥብቅ ስለሚቆራኝ በጎነት የባሕርይው ክፍል ይሆናል።
9. ጳውሎስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል?
9 ጳውሎስ ፍቅር የሚገለጽበትን አንዱን መንገድ በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅሶታል። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ።” “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ።” “ወዳጆቼ ሆይ፤ . . . አትበቀሉ።” “ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።” (ሮሜ 12:14, 17-19, 21) የጳውሎስ አነጋገር ከማያምኑ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ከሚቃወሙንም ጋር እንኳ ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ በግልጽ ያሳያል።
“የሚያሳድዷችሁን መርቁ”
10. አሳዳጆቻችንን መመረቅ የምንችለው በምን መንገድ ነው?
10 “የሚያሳድዷችሁን መርቁ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ የምናደርገው እንዴት ነው? (ሮሜ 12:14) ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 5:44፤ ሉቃስ 6:27, 28) የሚያሳድዱንን የምንመርቅበት አንዱ መንገድ ስለ እነርሱ በመጸለይ ይኸውም የሚያሳድዱን ባለማወቅ ከሆነ ይሖዋ እውነትን ማስተዋል እንዲችሉ ዓይናቸውን እንዲገልጥላቸው በመለመን ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እርግጥ ነው፣ የሚያሳድደንን ሰው አምላክ እንዲመርቀው መጠየቅ ያልተለመደ ነገር ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ አስተሳሰባችን ከክርስቶስ አስተሳሰብ ጋር እየተመሳሰለ በሄደ መጠን ለጠላቶቻችን ይበልጥ ፍቅር ማሳየት እንችላለን። (ሉቃስ 23:34) እንዲህ ያለ ፍቅር ማሳየት ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
11. (ሀ) እስጢፋኖስ ከተወው ምሳሌ ምን መማር እንችላለን? (ለ) ከጳውሎስ ተሞክሮ እንደታየው አንዳንድ አሳዳጆች ምን ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ?
11 ለአሳዳጆቻቸው ከጸለዩት ሰዎች አንዱ እስጢፋኖስ ሲሆን ጸሎቱም መና ሆኖ አልቀረም። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ብዙም ሳይቆይ፣ የክርስቲያን ጉባኤን የሚቃወሙ ሰዎች እስጢፋኖስን ይዘው ከኢየሩሳሌም ውጭ ካወጡት በኋላ በድንጋይ ወገሩት። እስጢፋኖስ ከመሞቱ በፊት “ጌታ ሆይ! ይህን ኀጢአት አትቊጠርባቸው” በማለት ጮክ ብሎ ጸለየ። (የሐዋርያት ሥራ 7:58 እስከ 8:1) በዚያን ዕለት እስጢፋኖስ ከጸለየላቸው ሰዎች አንዱ፣ ሲገደል የተመለከተውና በግድያው የተስማማው ሳውል ነበር። ቆየት ብሎም፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለሳውል ተገለጠለት። በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል አሳዳጅ የነበረው ይህ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ሆነ፤ ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራ ሲሆን ለሮም ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈውም እሱ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 26:12-18) እስጢፋኖስ ባቀረበው ጸሎት መሠረት ይሖዋ፣ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን በማሳደድ የፈጸመውን ኃጢአት ይቅር እንዳለው በግልጽ መመልከት ይቻላል። (1 ጢሞቴዎስ 1:12-16) በመሆኑም ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “የሚያሳድዷችሁን መርቁ” ብሎ መምከሩ ምንም አያስደንቅም! አሳዳጆች የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ከጊዜ በኋላ የአምላክ አገልጋዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ከራሱ ተሞክሮ ያውቅ ነበር። በዘመናችንም አሳዳጆች የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች በሚያሳዩት ሰላማዊ ባሕርይ የተነሳ አማኞች ሆነዋል።
“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ”
12. በሮሜ ምዕራፍ 12 ቁጥር 9 እና 17 ላይ የሚገኙት ሐሳቦች የሚዛመዱት እንዴት ነው?
12 ቀጥሎም ጳውሎስ ከአማኞችና ከማያምኑ ሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነት በተመለከተ “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ይህ ጥቅስ ጳውሎስ ቀደም ብሎ ከተናገረው “ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ” ከሚለው ሐሳብ ጋር የሚዛመድ ነው። ደግሞስ አንድ ሰው ክፉን በክፉ የሚመልስ ከሆነ፣ ክፉ የሆነውን ከልቡ እንደሚጸየፍ ቢናገር ውሸት አይሆንበትም? ክፉን በክፉ መመለስ “ያለ ግብዝነት” ፍቅር ከማሳየት ጋር ይቃረናል። ቀጥሎም ጳውሎስ “በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ” ብሏል። (ሮሜ 12:9, 17) ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
13. “በሰው ሁሉ ፊት” ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት አለብን?
13 ጳውሎስ ቀደም ሲል ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሐዋርያት ስላጋጠማቸው ስደት ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ለዓለም ሁሉ፣ ለመላእክትም ለሰዎችም ትርኢት ሆነናል . . . ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን።” (1 ቆሮንቶስ 4:9-13) በተመሳሳይም በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚገኙትን እውነተኛ ክርስቲያኖች ይመለከቷቸዋል። ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እየተፈጸመብንም እንኳ የምናደርጋቸውን መልካም ነገሮች የሚመለከቱ ሰዎች የምንሰብከውን መልእክት ሊቀበሉ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 2:12
14. ሰላማዊ ለመሆን የምንጥረው እስከምን ድረስ ነው?
14 ይሁን እንጂ ሰላማዊ ለመሆን የምንጥረው እስከምን ድረስ ነው? የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ወንድሞቹን “ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ብሏቸዋል። (ሮሜ 12:18) “ቢቻላችሁስ” እና “በበኩላችሁ” የሚሉት አገላለጾች ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር ሁልጊዜ እንደማይቻል ያሳያሉ። ለምሳሌ፣ ከሰዎች ጋር በሰላም ለመኖር ብለን የአምላክን ትእዛዝ አንጥስም። (ማቴዎስ 10:34-36፤ ዕብራውያን 12:14) ያም ሆኖ ግን የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች ሳንጥስ “ከሰው ሁሉ ጋር” በሰላም ለመኖር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።
“አትበቀሉ”
15. በሮሜ 12:19 ላይ ከመበቀል እንድንርቅ የሚያነሳሳን ምን ምክንያት ተገልጿል?
15 ጳውሎስ መበቀል የሌለብን ለምን እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ አሳማኝ ማስረጃ ሰጥቶናል፤ ብድራት አለመመለስ ትሑቶች እንደሆንን ያሳያል። “ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቊጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና” ብሏል። (ሮሜ 12:19) ለመበቀል የሚሞክር ክርስቲያን ትዕቢተኛ ነው። እንዲህ ማድረግ አምላክ ሊወስደው የሚገባውን እርምጃ እርሱ መውሰድ ይሆንበታል። (ማቴዎስ 7:1) ከዚህም በላይ ለደረሰበት ነገር የአጸፋ እርምጃ መውሰዱ ይሖዋ “እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት በሰጠው ማረጋገጫ ላይ እምነት እንደሌለው ያሳያል። ከዚህ በተቃራኒ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሖዋ ‘ለምርጦቹ እንደሚፈርድላቸው’ ይተማመናሉ። (ሉቃስ 18:7, 8፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-8) አምላክ እንዲበቀልላቸው ጉዳዩን ለእርሱ በመተው ትሑቶች መሆናቸውን ያሳያሉ።—ኤርምያስ 30:23, 24፤ ሮሜ 1:18
16, 17. (ሀ) “የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ” የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው? (ለ) በተደረገለት ደግነት ተነክቶ ልቡ የለሰለሰ የማያምን ሰው ታውቃለህ? ምሳሌ ስጥ።
16 ጠላትን መበቀል የግለሰቡን ልብ ሊያደነድነው ይችላል፤ ደግነት ማሳየት ግን ልቡን ያለሰልሰው ይሆናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለሮም ክርስቲያኖች የተናገረውን ልብ እንበል:- “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው። ይህን በማድረግህም የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ።” (ሮሜ 12:20፤ ምሳሌ 25:21, 22) ይህ ምን ማለት ነው?
17 “የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ” የሚለው አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረው ብረት የማቅለጥ ዘዴ የተወሰደ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። ያልተጣራ ብረት፣ ምድጃ ውስጥ ይከተትና ከታች ብቻ ሳይሆን ከላይም ፍም ይደረግበታል። ከላይ የተከመረበት ፍም የሙቀቱን መጠን ስለሚጨምረው ብረቱ ቀልጦ ከቆሻሻው እንዲለይ ያደርገዋል። በተመሳሳይም ለተቃዋሚ ሰው ደግነት በማሳየት የልቡ ደንዳናነት “ቀልጦ” መልካም ባሕርያቱ እንዲወጡ ልናደርግ እንችላለን። (2 ነገሥት 6:14-23) እንዲያውም በርካታ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት መጀመሪያ ወደ እውነተኛው አምልኮ የሳባቸው የይሖዋ አገልጋዮች ያሳዩአቸው ደግነት ነው።
አጸፋ የማንመልስበት ምክንያት
18. አጸፋ ከመመለስ መቆጠብ ትክክለኛ እንዲሁም ፍቅርና ትሕትና የሚንጸባረቅበት እርምጃ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
18 በሮሜ ምዕራፍ 12 ላይ ባደረግነው አጠር ያለ ምርምር ‘ለማንም ክፉን በክፉ ከመመለስ’ እንድንቆጠብ የሚያደርጉንን በርካታ ምክንያቶች ተመልክተናል። በመጀመሪያ፣ አጸፋ ከመመለስ መቆጠብ ልንከተለው የሚገባ ትክክለኛ አካሄድ ነው። አምላክ ካሳየን ርኅራኄ አንጻር ራሳችንን ለአምላክ መሥዋዕት አድርገን ማቅረባችንና ጠላቶቻችንን እንድንወድ የተሰጠንን ትእዛዝ ጨምሮ ሌሎች መመሪያዎቹን በፈቃደኝነት መታዘዛችን ትክክልና ምክንያታዊ ነው። ሁለተኛ፣ ክፉን በክፉ ከመመለስ መራቃችን ፍቅር የሚንጸባረቅበት አካሄድ ነው። አጸፋ ከመመለስ በመቆጠብና ሰላም በማስፈን አንዳንዶችን ሌላው ቀርቶ ኃይለኛ ተቃዋሚዎች የነበሩ ሰዎችንም እንኳ የይሖዋ አምላኪ እንደሚሆኑ ተስፋ በማድረግ በፍቅር ልንረዳቸው እንችላለን። ሦስተኛ፣ ክፉን በክፉ አለመመለሳችን ትሑቶች እንደሆንን ያሳያል። ይሖዋ “በቀል የእኔ ነው” ስላለ ራሳችን ለመበቀል መሞከር መታበይ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል “ትዕቢት ስትመጣ ውርደትም ትከተላለች፤ በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 11:2) በደል ሲደርስብን አምላክ እንዲበቀልልን ጉዳዩን በጥበብ ለእርሱ በመተው ትሑቶች እንደሆንን እናሳያለን።
19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
19 ጳውሎስ ከሌሎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ያሰፈረውን ሐሳብ ሲደመድም “ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” በማለት ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚሆን ምክር ሰጥቷል። (ሮሜ 12:21) በዛሬው ጊዜ ምን ክፉ ኃይሎች ያጋጥሙናል? እንዴትስ ልናሸንፋቸው እንችላለን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህና ተዛማጅነት ላላቸው ሌሎች ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።
ልታብራራ ትችላለህ?
• በሮሜ ምዕራፍ 12 ላይ ተደጋግሞ የተገለጸው ምክር ምንድን ነው?
• አጸፋ ከመመለስ እንድንቆጠብ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
• ‘ክፉን በክፉ ካልመለስን’ እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች ምን ጥቅሞች እናገኛለን?
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንድ ክርስቲያን ጋር ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙነት በሮሜ ምዕራፍ 12 ላይ ተብራርቷል
• ከይሖዋ
• ከእምነት ባልንጀሮቹና
• ከማያምኑ ሰዎች
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት የአምላክ አገልጋዮች የጻፈው ደብዳቤ ክርስቲያኖች ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ምክሮችን ይዟል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?