የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 45—ሮሜ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ቆሮንቶስ
ተጽፎ ያለቀው:- 56 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ቀደም ሲል አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን በጭካኔ ያሳድድ የነበረው ጳውሎስ፣ አይሁድ ላልሆኑ አሕዛብ በመስበኩ ሥራ ቀናተኛ የክርስቶስ ሐዋርያ እንደሆነ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተመልክተናል። ቀድሞ ፈሪሳዊ የነበረውና አሁን ግን ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሆነው ይህ ሰው በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከጻፋቸው 14 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት መካከል በመጀመሪያ የሮሜን መጽሐፍ እንመለከታለን። ጳውሎስ የሮሜን መጽሐፍ በጻፈበት ጊዜ ሁለት ረዥም የስብከት ጉዞዎችን አካሂዶ የነበረ ሲሆን ሦስተኛውን ደግሞ ወደ ማገባደዱ ተቃርቦ ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ ከዚህ በፊት ሌሎች አምስት ደብዳቤዎችን በመንፈስ አነሳሽነት ጽፏል። እነዚህም አንደኛና ሁለተኛ ተሰሎንቄ፣ ገላትያ እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ቆሮንቶስ ናቸው። የሮሜ መጽሐፍ ጳውሎስ የሰበከላቸው ሁለት ቡድኖች ማለትም አይሁድና አይሁድ ያልሆኑት አሕዛብ እኩል ስለመሆናቸው የሚገልጽ አዲስ ሐሳብ በዝርዝር ስለያዘ በጊዜያችን ባሉት መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ከሌሎቹ መጻሕፍት ቀድሞ መቀመጡ ተገቢ ነው። መጽሐፉ አምላክ ከሕዝቡ ጋር የነበረው ግንኙነት አዲስ መልክ እንደያዘና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው እንደተነበዩት ምሥራቹ አይሁድ ላልሆኑ አሕዛብም እንደሚታወጅ ያሳያል።
2 ጳውሎስ ጤርጥዮስን ጸሐፊው አድርጎ በመጠቀም፣ ጠንካራ መልእክት ከያዙት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል አንዱ በሆነው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ኃይለኛ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ እጅግ ብዙ ጥቅሶችን አስፍሯል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤዎች የአይሁድና የግሪክ ሰዎችን ያቅፉ በነበረበት ጊዜ የተነሱትን ችግሮች እጅግ ግሩም በሆኑ ቃላት አብራርቷል። አይሁዳውያን የአብርሃም ዝርያ በመሆናቸው ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቷቸው ነበር? የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከሙሴ ሕግ ነፃ መውጣታቸው ያስገኘላቸውን መብት በመጠቀም ገና ከጥንታዊ ልማዶች ያልተላቀቁትን ደካማ ሕሊና ያላቸው አይሁዳውያን ወንድሞቻቸውን ማደናቀፍ ይገባቸው ነበር? ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ላይ አይሁድና አይሁድ ያልሆኑ ሰዎች በአምላክ ፊት እኩል መሆናቸውንና ሰዎች የሚጸድቁት በሙሴ ሕግ አማካኝነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና በአምላክ ጸጋ መሆኑን በአጽንኦት ተናግሯል። እንዲሁም ክርስቲያኖች ከበላያቸው ላሉ የተለያዩ ባለ ሥልጣናት በተገቢው መንገድ እንዲገዙ አምላክ ይጠብቅባቸዋል።
3 የሮሜ ጉባኤ የተቋቋመው እንዴት ነበር? ፖምፒ በ63 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአይሁድ ማኅበረሰብ በሮም ይኖር ነበር። የሐዋርያት ሥራ 2:10, 11 ከእነዚህ አይሁዳውያን መካከል ጥቂቶቹ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም እንደነበሩ በግልጽ ያሳያል። አይሁዳውያኑ በዚያ ወቅት ምሥራቹ ሲሰበክ ሰምተዋል። ለጊዜው ብቻ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የነበሩትና ያመኑት አዳዲስ ሰዎች ከሐዋርያት ለመማር በዚያው ቆይተዋል። ከዚያም ከሮም የመጡት ተመልሰው ወደ አገራቸው እንደሄዱ ጥርጥር የለውም፤ ምናልባትም አንዳንዶቹ ወደ ሮም የተመለሱት በኢየሩሳሌም ስደት በተነሳበት ወቅት ሊሆን ይችላል። (ሥራ 2:41-47፤ 8:1, 4) በተጨማሪም በዚያን ዘመን ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመሄድ ልማድ ነበራቸው። ይህም በሮም ጉባኤ የሚገኙት ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ከጳውሎስ ጋር የቅርብ ወዳጅነት የነበራቸው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ እውነትን የተቀበሉት በግሪክ ወይም በእስያ ሳሉ የጳውሎስን ስብከት በመስማታቸው ሳይሆን አይቀርም።
4 ይህን ጉባኤ በተመለከተ የመጀመሪያው አስተማማኝ መረጃ የሚገኘው በጳውሎስ ደብዳቤ ውስጥ ነው። ጉባኤው የተገነባው በአይሁድና አይሁድ ባልሆኑ ክርስቲያኖች እንደሆነና ወንድሞች የሚያስመሰግን ቅንዓት እንደነበራቸው ከደብዳቤው በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች ‘እምነታችሁ በዓለም ሁሉ ተሰምቷል’ እንዲሁም “የእናንተን ታዛዥነት ሁሉም ሰምተዋል” ብሏቸው ነበር። (ሮሜ 1:8፤ 16:19) ስዊቶኒየስ በሁለተኛው መቶ ዘመን ሲጽፍ አይሁዳውያን በቀላውዴዎስ የግዛት ዘመን (ከ41-54 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ከሮም እንደተባረሩ ገልጿል። ይሁን እንጂ አቂላና ጵርስቅላ በሮም እንደነበሩ መጠቀሱ አይሁዳውያን ከጊዜ በኋላ ወደ ሮም ተመልሰው ሄደው እንደነበር ያሳያል። ጳውሎስ ቀደም ሲል በቆሮንቶስ አግኝቷቸው የነበሩት እነዚህ ክርስቲያኖች የቀላውዴዎስ ትእዛዝ በወጣበት ጊዜ ሮምን ለቀው የወጡና ጳውሎስ እዚያ ለነበረው ጉባኤ ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ደግሞ ከሄዱበት ተመልሰው በዚያው በሮም ይኖሩ የነበሩ አይሁዳውያን ናቸው።—ሥራ 18:2፤ ሮሜ 16:3
5 የደብዳቤው ትክክለኛነት በጠንካራ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ነው። በመግቢያው ላይ እንደምናገኘው ደብዳቤውን የጻፈው ‘የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያና ሐዋርያ ሊሆን የተጠራው ጳውሎስ’ ሲሆን መልእክቱን የጻፈውም ‘በአምላክ ለተወደዱትና ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት በሮም ላሉት ሁሉ’ ነው። (ሮሜ 1:1, 7) የመጽሐፉን ትክክለኛነት የሚያረጋግጠው ውጫዊ ማስረጃ፣ ለክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ከተገኙት የመጀመሪያዎቹ ማስረጃዎች መካከል የሚመደብ ነው። ጴጥሮስ ከስድስት ወይም ከስምንት ዓመታት አካባቢ በኋላ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ብዛት ያላቸው ተመሳሳይ አገላለጾችን የተጠቀመ ሲሆን ብዙ ምሑራንም ጴጥሮስ የሮሜን መጽሐፍ ግልባጭ ሳያነብ እንዳልቀረ ይሰማቸዋል። የሮሜ መጽሐፍ ጳውሎስ ከጻፋቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ መሆኑ ግልጽ ነው። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይና በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ይኖሩ እንደነበሩት እንደ ሮማዊው ክሌመንት፣ የሰምርኔሱ ፖሊካርፕ እና የአንጾኪያው ኢግናቲየስ የመሳሰሉ ሰዎች ጳውሎስ የሮሜ መጽሐፍ ጸሐፊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
6 የሮሜ መጽሐፍ ከሌሎች ስምንት የጳውሎስ ደብዳቤዎች ጋር ቼስተር ቢቲ ፓፒረስ ቁ. 2 (P46) ተብሎ በሚታወቀው ጥንታዊ የኮዴክስ ጽሑፍ ውስጥ ይገኛል። ሰር ፍሬደሪክ ኬንየን ይህን ጥንታዊ የኮዴክስ ጽሑፍ በማስመልከት እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “አሁን በሦስተኛው መቶ ዘመን መግቢያ አካባቢ የተጻፉ የጳውሎስ ደብዳቤ ጥንታዊ ቅጂዎች ከሞላ ጎደል አሉን።”a የቼስተር ቢቲ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ፓፒረሶች በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከተጻፉትና በሰፊው ከሚታወቁት ከሳይናይቲክና ከቫቲካን በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎች [ቁ. 1209] የበለጠ ዕድሜ አላቸው። እነዚህ ቅጂዎችም የሮሜን መጽሐፍ በውስጣቸው ይዘዋል።
7 የሮሜ መጽሐፍ የተጻፈው መቼና የት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው በሦስተኛ የሚስዮናዊ ጉዞው ማብቂያ ላይ ግሪክን ለጥቂት ወራት በጎበኘበት ወቅት ምናልባትም በቆሮንቶስ ሆኖ ነው በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ማስረጃ በቆሮንቶስ መጻፉን ያመለክታል። ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው የቆሮንቶስ ጉባኤ አባል ከሆነው ከጋይዮስ ቤት ሆኖ ነው። በተጨማሪም በቆሮንቶስ የባሕር ወደብ ላይ የሚገኘው የክንክራኦስ ጉባኤ አባል የሆነችውን ፌቤንን እንዲቀበሏት አደራ ብሏቸዋል። እንዲያውም ይህን ደብዳቤ ወደ ሮም የወሰደችው ፌቤን ራሷ ሳትሆን አትቀርም። (ሮሜ 16:1, 23፤ 1 ቆሮ. 1:14) ጳውሎስ በሮሜ 15:23 [የ1980 ትርጉም] ላይ ‘በዚያ አካባቢ ባሉት አገሮች የነበረውን ሥራ መጨረሱን’ ከገለጸ በኋላ በሚቀጥለው ቁጥር ላይ ደግሞ የሚስዮናዊ ሥራውን በምዕራብ በኩል ወደ ስፔን ለማስፋት ማቀዱን ገልጿል። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሊጽፍ የሚችለው በሦስተኛ ጉዞው መገባደጃ ላይ ማለትም በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ላይ ነው።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
20 የሮሜ መጽሐፍ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል” በማለት በአምላክ ለማመን የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ ያቀርባል። ይሁንና ከዚህ በበለጠ የአምላክን ጽድቅ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ እንዲሁም ስለ አምላክ ታላቅ ምሕረትና ስለ ጸጋው ይገልጻል። ይህ የአምላክ ባሕርይ፣ የተፈጥሮ የሆኑት ቅርንጫፎች ተቆርጠው ስለመጣላቸውና በቦታቸው የበረሐ ቅርንጫፎች ስለመተካታቸው በሚናገረው የወይራ ዛፍ ምሳሌ ላይ ማራኪ በሆነ መንገድ ተገልጾልናል። ጳውሎስ ስለ አምላክ ኃያልነት እንዲሁም ስለ ደግነቱ ካሰላሰለ በኋላ እንዲህ ሲል በመደነቅ ተናግሯል:- “[የአምላክ] የጥበቡና የዕውቀቱ ባለ ጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!”—1:20፤ 11:33
21 የሮሜ መጽሐፍ ከዚህ ጋር በማያያዝ ስለ አምላክ ቅዱስ ምሥጢር ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል። ከአሁን በኋላ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለና ከዚህ ይልቅ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ካገኘነው የይሖዋ ጸጋ ሊካፈሉ እንደሚችሉ ይገልጻል። “እግዚአብሔር ለማንም አያዳላም።” “አንድ ሰው ይሁዲ የሚሆነው በውስጣዊ ማንነቱ ይሁዲ ሆኖ ሲገኝ ነው። ግዝረትም ግዝረት የሚሆነው በተጻፈው ሕግ ሳይሆን፣ በመንፈስ የልብ ግዝረት ሲኖር ነው።” “በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል።” ለእነዚህ ሁሉ ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረላቸው የሠሩት ሥራ ሳይሆን እምነታቸው ነው።—2:11, 29፤ 10:12፤ 3:28
22 በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች የተጻፈው ደብዳቤ የያዘው ጠቃሚ ምክር በዓለም ውስጥ እንደ መጻተኛ ለሚኖሩትና ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች ለሚያጋጥሟቸው በጊዜያችን ላሉ ክርስቲያኖችም ይጠቅማል። ክርስቲያኖች ከጉባኤ ውጪ ያሉትን ሰዎች ጨምሮ ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንዲኖሩ’ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ማንኛውም ሰው የአምላክ ዝግጅት ክፍል ለሆኑት “በሥልጣን ላሉት ሹማም[ን]ት መገዛት” አለበት። እነዚህ የበላይ ባለ ሥልጣናት የሚያስፈሩት ሕግ አክባሪ ለሆኑ ሰዎች ሳይሆን ለክፉ አድራጊዎች ነው። ክርስቲያኖች ሕግ የሚያከብሩት የሚደርስባቸውን ቅጣት በመፍራት ብቻ ሳይሆን ስለ ክርስቲያናዊ ሕሊናቸው ሲሉም ነው። በመሆኑም ቀረጥ ይከፍላሉ፣ ለእያንዳንዱ የሚገባውን ያስረክባሉ፤ እንዲሁም ግዴታቸውን ይወጣሉ። በተጨማሪም ‘እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር’ የማንም ዕዳ እንዳይኖርባቸው ይጠነቀቃሉ። ምክንያቱም ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።—12:17-21፤ 13:1-10
23 ጳውሎስ ለሕዝብ የመመሥከርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። አንድ ሰው በልቡ ማመኑ የሚያጸድቀው ሲሆን ለመዳን የሚያበቃው ግን ለሕዝብ የሚሰጠው ምሥክርነት ነው። “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” ይሁን እንጂ ይህ እንዲሆን ሰባኪዎች ወደ ሰዎች መሄድና ‘ምሥራቹን ማወጅ’ ይኖርባቸዋል። ድምፃቸው “እስከ ዓለም ዳርቻ” ድረስ ከሚሰማው ከእነዚህ ሰባኪዎች መካከል ከሆንን ደስተኞች ነን! (10:13, 15, 18) ለዚህ የስብከት ሥራ ስንዘጋጅ ልክ እንደ ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ሙሉ በሙሉ እንተዋወቅ። ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ የተወሰነ ክፍል ውስጥ ብቻ እንኳ (10:11-21) ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ በተደጋጋሚ ጠቅሷል። (ኢሳ. 28:16፤ ኢዩ. 2:32 NW፤ ኢሳ. 52:7፤ 53:1፤ መዝ. 19:4፤ ዘዳ. 32:21፤ ኢሳ. 65:1, 2) በመሆኑም “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ለማለት ችሏል።—ሮሜ 15:4
24 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ግሩም የሆነ ምክር ተሰጥቷል። የመጡበት ብሔር፣ ዘር ወይም ማኅበራዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁሉም ክርስቲያኖች “መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም” እንደሆነው የአምላክ ፈቃድ፣ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ በአእምሯቸው መታደስ መለወጥ አለባቸው። (11:17-22፤ 12:1, 2) ጳውሎስ በሮሜ 12:3-16 ላይ ያሰፈረው ሐሳብ ምክንያታዊነት የሚንጸባረቅበት ግሩም ምክር ይዟል! እዚህ ላይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ ቅንዓትን ስለ መገንባት፣ ስለ ትሕትናና ስለ ወንድማማች መዋደድ በጣም ጥሩ የሆኑ ምክሮች ተሰጥተዋል። ጳውሎስ በመጽሐፉ መደምደሚያ ምዕራፎች ላይ መከፋፈል የሚፈጥሩ ሰዎችን ስለ መከታተልና ከእነሱ ስለ መራቅ ጥብቅ የሆነ ማሳሰቢያ ከመስጠቱም በተጨማሪ በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ወንድሞች ጋር ንጹሕ የሆነ ወዳጅነት መመሥረት ደስታና የመንፈስ እርካታ እንደሚያስገኝ ገልጿል።—16:17-19፤ 15:7, 32
25 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ምንጊዜም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ምክንያቱም “[የአምላክ] መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ጽድቅ፣ ሰላምና ሐሤት ነው እንጂ፣ የመብልና የመጠጥ ጉዳይ አይደለም።” (14:17) ይህ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ በተለይ በሰማያዊው መንግሥት ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ በመሆን ከእሱ ጋር “የክብሩ ተካፋዮች” የሚሆኑት የሚያገኙት ነው። የሮሜ መጽሐፍ በኤደን የተሰጠውን የመንግሥት ተስፋ ተፈጻሚነት አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ ሲሰጥ “የሰላም አምላክ፣ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል” ይላል። (ሮሜ 8:17፤ 16:20፤ ዘፍ. 3:15) በእነዚህ አስደናቂ እውነቶች በማመን በደስታ፣ በሰላምና በተስፋ መሞላታችንን እንቀጥል። በላይ በሰማይም ይሁን በታች በምድር ያለ ማንኛውም ነገር “ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን” እንደማይችል ስለተረዳን ከመንግሥቱ ዘር ጋር በድል አድራጊነት ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ሮሜ 8:39፤ 15:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አወር ባይብል ኤንድ ዚ ኤንሸንት ማኒዩስክሪፕትስ፣ 1958 ገጽ 188