ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ፖሊስ ንብረታችንን የሚሰርቁ ወይም በቤተሰባችን ላይ አደጋ የሚፈጥሩ ወንጀለኞችን የማሰር ሥልጣን ያለው በመሆኑ አመስጋኝ የማይሆን ማን አለ? እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ኅብረተሰቡን ከአደጋ ለመጠበቅ ወንጀለኞችን የመቅጣት ሥልጣን ያላቸው መሆኑን አናደንቅምን?
በአብዛኛው መንግሥት ከሚጥላቸው ቀረጦች በሚሰበሰብ ገቢ የሚከናወኑት እንደ መንገድ ጥገና፣ የአካባቢ ንጽሕናና ትምህርት ስለመሳሰሉ ሌሎች ጠቃሚ ሕዝባዊ አገልግሎቶችም ማሰብ ይቻላል። እውነተኛ ክርስቲያኖች በተገቢ መንገድ ለተቋቋመ ሥልጣን አክብሮት ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን በመቀበል ረገድ ግንባር ቀደም ናቸው። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱን አክብሮት ማሳየት ያለብን እስከምን ድረስ ነው? እንዲሁም ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት የሚያስፈልገው በየትኞቹ የሕይወት መስኮች ነው?
በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ ሥልጣን
አማኞች ሆኑም አልሆኑ ለኅብረተሰቡ ጥቅም ሲል ለሚያገለግል የሕዝብ ባለሥልጣን ሁሉም ሰዎች አክብሮት እንዲያሳዩ መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በሮም ለነበሩ የእምነት ጓደኞቹ የጻፈላቸው ሲሆን ሮሜ 13:1-7 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው መሠረት የተናገረውን መመርመሩ ጠቃሚ ነው።
ጳውሎስ ሮማዊ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ሮም የዓለም ኃያል ነበረች። ጳውሎስ በ56 እዘአ ገደማ የጻፈው ደብዳቤ ክርስቲያኖች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ዜጎች እንዲሆኑ የሚያሳስብ ምክር ይዞ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።”
ጳውሎስ አምላክ ባይፈቅድ ኖሮ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ሥልጣን ሊኖር እንደማይችል ገልጿል። በዚህ አባባል መሠረት የበላይ ባለ ሥልጣኖች በአጠቃላዩ የአምላክ ዓላማ ውስጥ አንጻራዊ የሆነ ቦታ አላቸው። ከዚህ የተነሳ “ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል” ሊባል ይቻላል።
እነዚህ የበላይ ባለሥልጣኖች መልካም የሚያደርጉ ዜጎችን ለማመስገን ብቻ ሳይሆን ክፉ አድራጊዎችንም ለመቅጣት ሥልጣን አላቸው። መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ባለ ሥልጣኖች ‘የበቀል’ እርምጃ ለመውሰድ ያላቸውን መብት የሚፈሩበት በቂ ምክንያት አላቸው። መንግሥታት ይህንን የሚያደርጉት “የእግዚአብሔር አገልጋይ” በመሆን ነው።
ጳውሎስ የመከራከሪያ ሐሳቡን ሲደመድም እንዲህ ብሏል:- “ስለዚህ ስለ ቊጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና።”
የተሰበሰበው ቀረጥ ለምን እንደሚውል የመመደቡ ኃላፊነት የወደቀው በቀረጥ ከፋዩ እጅ ሳይሆን በበላይ ባለሥልጣኖች ላይ ነበር። አንድ ክርስቲያን ሐቀኛ ዜጋ እንደመሆኑ መጠን በጎ ሕሊና ይይዛል። ለበላይ ባለ ሥልጣኖች በመገዛትና ተገቢውን ቀረጥ በመክፈል እሱ የሚኖርበትን የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ መደገፍ ብቻ ሳይሆን ከመለኮታዊ መሥፈርቶችም ጋር ተስማምቶ እየኖረ መሆኑን ይገነዘባል።
ቤተሰብና ሥልጣን
በቤተሰብ ውስጥ ስላለ ሥልጣንስ ምን ለማለት ይቻላል? አንድ ሕፃን ትኩረት እንዲሰጠው ሲፈልግ አብዛኛውን ጊዜ ያለቅሳል ወይም ይነጫነጫል። ሆኖም አንድ አስተዋይ ወላጅ የሕፃኑ ትክክለኛ ፍላጎት ምን እንደሆነ ከመረዳቱም በላይ ሕፃኑ እንዲሁ ስላለቀሰ ብቻ የጠየቀውን ሁሉ ያደርግለታል ማለት አይደለም። አንዳንድ ልጆች እያደጉ ሲሄዱ መረን ከመለቀቃቸውም በላይ የራሳቸውን የአቋም ደረጃዎች እንዲያወጡ ተፈቅዶላቸዋል። እንዲህ ያሉት ልጆች ተሞክሮ ስለሌላቸው በተለያዩ ወንጀሎች ወይም ሌሎች መጥፎ ድርጊቶች ውስጥ በመግባት ቤተሰባቸውንም ሆነ በአጠቃላይ ኅብረተሰቡን ሊያውኩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በአካባቢው ያሉ ብዙዎቹ ባለ ሥልጣኖች በሚገባ የሚያውቁት ጉዳይ ነው።
ሮዝሊንድ ማይልስ ችልድረን ዊ ዲዘርቭ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ወላጆች ልጆቻቸውን ማሰልጠን የሚጀምሩት በጣም ዘግይተው ነው” ብለዋል። “ስልጠናው መጀመር ያለበት ልጁ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ነው።” ከመጀመሪያው አንስቶ ወላጆች ደግነትና አሳቢነት በተሞላበት ሁኔታ ሥልጣናቸውን ከገለጹና በሚወስዷቸው እርምጃዎችም የማይወላውሉ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ልጆች ይህን ሥልጣንና ከዚያ የሚመነጨውን ፍቅራዊ ተግሳጽ መቀበልን ይማራሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ ሥልጣንን በተመለከተ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ ጠቢቡ ሰሎሞን “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው” በማለት አምላክን የሚፈሩ ወላጆች በልጆቻቸው ፊት በሚይዙት ተመሳሳይ አቋም ላይ ትኩረት አድርጓል። (ምሳሌ 1:8) ወላጆች በልጆቻቸው ፊት እንዲህ ዓይነት ምክንያታዊ የሆነ ተመሳሳይ አቋም ሲይዙ ልጆች ገደባቸውን ያውቃሉ። ልጆች ማምለጫ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ወላጆችን እርስ በርስ ለማጋጨት ቢሞክሩም እንኳ አንድነት ያለው የወላጆች ሥልጣን ለልጆች ጥበቃ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ባል ለልጆቹ ብቻ ሳይሆን ለሚስቱም መንፈሳዊ ደኅንነት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ይናገራል። ይህ የራስነት ሥልጣን ተብሎ ተገልጿል። ይህ የራስነት ሥልጣን እንዴት ሊሠራበት ይገባል? ጳውሎስ፣ ክርስቶስ የጉባኤ ራስ እንደሆነ ሁሉ ባል የሚስት ራስ መሆኑን ጠቅሷል። ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን [መንፈሳዊ ሙሽራውን] እንደ ወደዳትና ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” (ኤፌሶን 5:25) አንድ ባል የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የራስነት ሥልጣኑን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሲሠራበት የሚስቱን “ጥልቅ አክብሮት” ያገኛል። (ኤፌሶን 5:33 NW ) በእንዲህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ልጆችም ከአምላክ የተገኘ ሥልጣን ያለውን ጥቅም የሚረዱ ሲሆን ይህን ሥልጣን ለመቀበልም ይበረታታሉ።—ኤፌሶን 6:1-3
የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡትን ጨምሮ ነጠላ ወላጆች ይህን ኃላፊነት መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው? አባትም ሆኑ እናት ይሖዋ አምላክ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ካላቸው ሥልጣን በቀጥታ እርዳታ መጠየቅ ይችላሉ። ኢየሱስ ሲያስተምር አባቱና በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ያላቸውን ሥልጣን ምንጊዜም ይጠቅስ ነበር።—ማቴዎስ 4:1-10፤ 7:29፤ ዮሐንስ 5:19, 30፤ 8:28
መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ በርካታ ጠቃሚ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። አንድ ወላጅ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በማወቅና ሥራ ላይ በማዋል ለልጆቹ ፍቅራዊና ገንቢ የሆነ ምክር መስጠት ይችላል። (ዘፍጥረት 6:22፤ ምሳሌ 13:20፤ ማቴዎስ 6:33፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ፊልጵስዩስ 4:8, 9) በተጨማሪም ወላጆች የቅዱሳን ጽሑፎችን ሥልጣን ማክበር የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እንዲያደንቁ ልጆቻቸውን ለማሰልጠን ይረዳቸው ዘንድ የተዘጋጀ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍም ማንበብ ይችላሉ።a
የክርስቲያን ጉባኤና ሥልጣን
“በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት።” (ማቴዎስ 17:5) ይሖዋ አምላክ ራሱ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ኢየሱስ በመለኮታዊ ሥልጣን እንዲናገር ድጋፍ ሆነውታል። እሱ የተናገራቸው ነገሮች በአራቱ የወንጌል ዘገባዎች ላይ ስለሰፈሩ በቀላሉ ልናገኛቸው እንችላለን።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ሲል ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 28:18) ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን በምድር የእሱን ፈለግ በመከተል ላይ ያሉትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከፈሰሰላቸው ጊዜ አንስቶ የእውነት መግለጫ መስመር ማለትም “ታማኝና ልባም ባሪያ” አድርጎም ተጠቅሞባቸዋል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ሥራ 2:1-36) ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን ለማጠናከር ሲል ይህን ሁሉ ለማከናወን ምን አድርጓል? ‘ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ወንዶችን ስጦታ አድርጎ ሰጥቷል።’ (ኤፌሶን 4:8) እነዚህ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙና የእምነት አጋሮቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎቶች እንዲያሟሉ ሥልጣን የተሰጣቸው ክርስቲያን ሽማግሌዎች ናቸው።—ሥራ 20:28
ከዚህ የተነሳ ጳውሎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል:- “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።” እነዚህ የታመኑ ወንዶች የኢየሱስን አኗኗር በቅርብ ስለሚከተሉ እምነታቸውን መኮረጅ በእርግጥ የጥበብ ጎዳና ነው። ከዚያም ጳውሎስ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ [“በእናንተ ላይ ያላቸውን ሥልጣን ምንጊዜም አስታውሱ፣” ዚ አምፕሊፋይድ ባይብል] እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።”—ዕብራውያን 13:7, 17
እንዲህ ዓይነት መመሪያ ሲጣስ ምን ይከተላል? የመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ አንዳንድ አባላት ይህን መመሪያ በመጣስ ከሃዲዎች ሆነው ነበር። ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ የአንዳንዶችን እምነት እንደገለበጡና ከንቱ ልፍለፋቸው ‘ለዓለም የሚመች’ እንደሆነ ተገልጿል። ከተናገሯቸው ነገሮች አንዱ መንፈሳዊ ወይም ምሳሌያዊ ትንሣኤን በማስመልከት ሊሆን ይችላል፣ አስቀድሞ ስለተከናወነ ወደፊት በአምላክ መንግሥት ሥር ተጨማሪ ትንሣኤ አይኖርም የሚል ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 2:16-18
በዚህ ጊዜ ሥልጣን የነበረው አካል ሁኔታውን ለማስተካከል ጣልቃ ገባ። ክርስቲያን ሽማግሌዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ወኪሎች እንደመሆናቸው መጠን ቅዱሳን ጽሑፎችን ባለ ሥልጣን አድርገው በመጠቀም እንዲህ ዓይነቶቹን የመከራከሪያ ሐሳቦች ማፍረስ ችለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ዛሬም ቢሆን “የእውነት ዓምድና መሠረት” ተብሎ በተገለጸው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው አሠራር ተመሳሳይ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) የሐሰት ትምህርቶች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ መልካም አደራ ተጠብቆ የቆየልንን ‘የጤናማ ቃል ምሳሌ’ እንዲያበላሹ አይፈቀድላቸውም።—2 ጢሞቴዎስ 1:13, 14
በዓለም ላይ ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት በከፍተኛ ፍጥነት እየጠፋ በመሄድ ላይ ቢሆንም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በኅብረተሰብ፣ በቤተሰብና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ተገቢ ሥልጣን ለጥቅማቸው የተቋቋመ መሆኑን ይገነዘባሉ። ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ለአካላዊ፣ ለስሜታዊና ለመንፈሳዊ ጤንነታችን በጣም ጠቃሚ ነው። ለእንዲህ ዓይነቱ ከአምላክ የተገኘ ሥልጣን እውቅና እንዲሁም አክብሮት በመስጠት የመጨረሻዎቹ ባለ ሥልጣኖች ከሆኑት ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለማዊ ደህንነታችን ጥበቃ እናገኛለን።—መዝሙር 119:165፤ ዕብራውያን 12:9
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች እና ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባሉትን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙትን መጻሕፍት ተመልከቱ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ ሥልጣንን በተመለከተ ብዙ የሚናገረው ነገር አለ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነጠላ ወላጆች ይሖዋ አምላክ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ካላቸው ሥልጣን በቀጥታ እርዳታ መለመን ይችላሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በቤተሰብ፣ በክርስቲያን ጉባኤ እና በኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኝ ተገቢ የሆነ ሥልጣን ለጥቅማቸው የተቋቋመ መሆኑን ይገነዘባሉ
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Photo by Josh Mathes, Collection of the Supreme Court of the United States