የጥናት ርዕስ 42
“ለመታዘዝ ዝግጁ” ነህ?
“ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ለመታዘዝ ዝግጁ . . . ነው።”—ያዕ. 3:17
መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት
ማስተዋወቂያa
1. መታዘዝ ከባድ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?
አንዳንድ ጊዜ መታዘዝ ያታግልሃል? ንጉሥ ዳዊት እንደዚህ ተሰምቶት ያውቃል። በመሆኑም “አንተን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጤ እንዲቀሰቀስ አድርግ” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (መዝ. 51:12) ዳዊት ይሖዋን ይወደው ነበር። ያም ቢሆን ዳዊት መታዘዝ የከበደው ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ እኛም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። ለምን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ያለመታዘዝ ዝንባሌ ወርሰናል። ሁለተኛ፣ ሰይጣን ልክ እንደ እሱ እንድናምፅ ሁልጊዜ ሊገፋፋን ይሞክራል። (2 ቆሮ. 11:3) ሦስተኛ፣ የምንኖረው የዓመፀኝነት ዝንባሌ በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ነው፤ ይህ ዝንባሌ “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ መንፈስ” ተብሎ ተጠርቷል። (ኤፌ. 2:2) ያለብንን የኃጢአት ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን ዲያብሎስና ይህ ዓለም እንዳንታዘዝ የሚያደርጉብንን ጫናም መዋጋት ይኖርብናል። ለይሖዋና እሱ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች ለመታዘዝ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
2. “ለመታዘዝ ዝግጁ” መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? (ያዕቆብ 3:17)
2 ያዕቆብ 3:17ን አንብብ። ያዕቆብ ጥበበኛ ሰዎች “ለመታዘዝ ዝግጁ” እንደሆኑ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ የተወሰነ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች ለመታዘዝ ፈቃደኞች ልንሆን ብሎም ልንጓጓ ይገባል። እርግጥ ነው ይሖዋ፣ እሱ የሰጠንን ትእዛዝ እንድንጥስ የሚጠይቀንን ሰው እንድንታዘዝ አይጠብቅብንም።—ሥራ 4:18-20
3. ይሖዋ እሱ ሥልጣን የሰጣቸውን ሰዎች እንድንታዘዝ የሚጠብቅብን ለምንድን ነው?
3 ሰዎችን ከመታዘዝ ይልቅ ይሖዋን መታዘዝ ሊቀለን ይችላል። ምክንያቱም ይሖዋ የሚሰጠን መመሪያ ሁልጊዜም ፍጹም ነው። (መዝ. 19:7) ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ግን ፍጹማን አይደሉም። ያም ቢሆን የሰማዩ አባታችን ለወላጆች፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ለሽማግሌዎች የተወሰነ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (ምሳሌ 6:20፤ 1 ተሰ. 5:12፤ 1 ጴጥ. 2:13, 14) እነሱን ስንታዘዝ ይሖዋን እየታዘዝን ነው ሊባል ይችላል። ይሖዋ ሥልጣን የሰጣቸው ሰዎች የሚሰጡንን መመሪያ መቀበልና መከተል አንዳንድ ጊዜ ከባድ ቢሆንብንም እነሱን መታዘዝ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ወላጆችህን ታዘዝ
4. ብዙ ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙት ለምንድን ነው?
4 ወጣት ክርስቲያኖች፣ አብዛኞቹ እኩዮቻቸው “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) ይሁንና ብዙዎቹ ወጣቶች ታዛዥ ያልሆኑት ለምንድን ነው? አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን የሚያዙትን ነገር እነሱ ራሳቸው አያደርጉትም። በመሆኑም ልጆቻቸው እነሱን መታዘዝ ይከብዳቸዋል። ሌሎች ደግሞ የወላጆቻቸው ምክር ጊዜ ያለፈበት፣ ምክንያታዊነት የጎደለው ወይም ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ወጣቶች፣ እናንተስ እንደዚህ ተሰምቷችሁ ያውቃል? ብዙዎች “ከጌታ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ የጽድቅ ተግባር ነውና” የሚለውን የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ ከባድ ይሆንባቸዋል። (ኤፌ. 6:1) ታዲያ ይህን ለማድረግ ምን ሊረዳህ ይችላል?
5. ኢየሱስ ለወላጆች በመታዘዝ ረገድ ከሁሉ የተሻለ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ሉቃስ 2:46-52)
5 ኢየሱስ በታዛዥነት ረገድ ወደር የሌለው ምሳሌ ነው፤ አንተም ከእሱ መማር ትችላለህ። (1 ጴጥ. 2:21-24) ኢየሱስ ፍጹም ሰው ነበር፤ ወላጆቹ ግን ፍጹማን አልነበሩም። የኢየሱስ ወላጆች ስህተት ቢሠሩም፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ቢረዱትም ኢየሱስ እነሱን ማክበሩን ቀጥሏል። (ዘፀ. 20:12) ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ምን እንደተከናወነ እስቲ እንመልከት። (ሉቃስ 2:46-52ን አንብብ።) ወላጆቹ ኢየሩሳሌም ትተውት ሄዱ። ከበዓሉ ሲመለሱ ሁሉም ልጆቻቸው አብረዋቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ የዮሴፍና የማርያም ኃላፊነት ነበር። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ሲያገኙት ማርያም እንዳስጨነቃቸው በመግለጽ ኢየሱስን ወቀሰችው። ኢየሱስ ይህን ማድረጓ ተገቢ እንዳልሆነ መግለጽ ይችል ነበር። እሱ ግን ለወላጆቹ አጭርና አክብሮት የሚንጸባረቅበት መልስ ሰጣቸው። ዮሴፍና ማርያም ግን “ምን እያላቸው እንዳለ አልገባቸውም።” ያም ቢሆን ኢየሱስ ‘እንደ ወትሮው ይገዛላቸው ነበር።’
6-7. ወጣቶች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
6 ወጣቶች፣ ወላጆቻችሁ ስህተት ሲሠሩ ወይም በተሳሳተ መንገድ ሲረዷችሁ እነሱን መታዘዝ ከባድ ይሆንባችኋል? በዚህ ጊዜ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? በመጀመሪያ ይሖዋ ምን እንደሚሰማው አስቡ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወላጆቻችሁን መታዘዛችሁ ‘ጌታን እንደሚያስደስተው’ ይናገራል። (ቆላ. 3:20) ይሖዋ፣ ወላጆቻችሁ ሙሉ በሙሉ ላይረዷችሁ እንደሚችሉ እንዲሁም የሚያወጡት ሕግ አንዳንድ ጊዜ ምክንያታዊ ላይሆን እንደሚችል ይገባዋል። እንደዚያም ሆኖ እነሱን ለመታዘዝ ስትመርጡ ይደሰትባችኋል።
7 ሁለተኛ፣ ወላጆቻችሁ ምን እንደሚሰማቸው አስቡ። ወላጆቻችሁን ስትታዘዙ ታስደስቷቸዋላችሁ፤ እንዲሁም አመኔታቸውን ታተርፋላችሁ። (ምሳሌ 23:22-25) ከእነሱ ጋር ይበልጥ መቀራረባችሁም አይቀርም። በቤልጂየም የሚኖር አሌክሳንደር የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ ወላጆቼ የሚጠይቁኝን ነገር ይበልጥ መታዘዝ ስጀምር ግንኙነታችን ተሻሻለ። ይበልጥ ተቀራረብን፤ ደስታችንም ጨመረ።”b ሦስተኛ፣ በአሁኑ ጊዜ ታዛዥ መሆናችሁ ለወደፊቱ የሚጠቅማችሁ እንዴት እንደሆነ አስቡ። በብራዚል የሚኖረው ፓውሎ “ወላጆቼን መታዘዝ መማሬ ይሖዋንና ሥልጣን ያላቸውን ሌሎች ሰዎች ለመታዘዝ ረድቶኛል” ብሏል። የአምላክ ቃል ወላጆቻችሁን ለመታዘዝ የሚያነሳሳችሁን ወሳኝ ምክንያት ሲገልጽ “ይህም መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህ በምድር ላይ እንዲረዝም ነው” ይላል።—ኤፌ. 6:2, 3
8. ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ለመታዘዝ የመረጡት ለምንድን ነው?
8 ብዙ ወጣቶች፣ ወላጆቻቸውን ሲታዘዙ ነገሮች እንደሚሰምሩላቸው አስተውለዋል። በብራዚል የምትኖረው ሉዊዛ ወላጆቿ እስከተወሰነ ዕድሜ ድረስ ስልክ እንዳይኖራት ያደረጉት ለምን እንደሆነ መረዳት ከብዷት ነበር። ምክንያቱም ብዙዎቹ እኩዮቿ ስልክ አላቸው። ውሎ አድሮ ግን ወላጆቿ ጥበቃ እያደረጉላት እንደሆነ ተገነዘበች። አሁን፣ ወላጆቿ የሚያወጧቸውን ሕጎች መፈናፈኛ እንደሚያሳጣ ገደብ ሳይሆን ሕይወቷን እንደሚያድንላት መመሪያ አድርጋ መመልከት ጀምራለች። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ኤሊዛቤት የተባለች ወጣት እህት አሁንም አንዳንድ ጊዜ ወላጆቿን መታዘዝ ያታግላታል። እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ አንድን ሕግ ያወጡበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ መረዳት ሲከብደኝ ከዚህ ቀደም ያወጧቸው ሕጎች እንዴት እንደጠቀሙኝ አስታውሳለሁ።” በአርሜኒያ የምትኖረው ሞኒካ ደግሞ ወላጆቿን ካልታዘዘችባቸው ጊዜያት ይልቅ እነሱን ስትታዘዛቸው ሁሌም የተሻለ ውጤት እንደምታገኝ ተናግራለች።
‘የበላይ ባለሥልጣናትን’ ታዘዝ
9. ብዙ ሰዎች ሕግ ስለማክበር ምን ይሰማቸዋል?
9 ብዙ ሰዎች፣ መንግሥታት መኖራቸው ጠቃሚ እንደሆነና ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ ከሚያወጧቸው ሕጎች መካከል ቢያንስ የተወሰኑትን መታዘዝ እንዳለብን ያምናሉ። (ሮም 13:1) ሆኖም እነዚያው ሰዎች፣ አንድ ሕግ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ወይም ብዙ መሥዋዕት እንደሚያስከፍላቸው ከተሰማቸው ያንን ሕግ ለመታዘዝ ፈቃደኞች ላይሆኑ ይችላሉ። ግብር መክፈልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በአንድ የአውሮፓ አገር በተካሄደ ጥናት ላይ በጥናቱ ከተካፈሉት ሰዎች አንድ አራተኛ የሚሆኑት፣ የተጣለባቸው ግብር ፍትሐዊ እንዳልሆነ ከተሰማቸው ባይከፍሉ ችግር እንደሌለው ያምናሉ። በዚህም የተነሳ በዚህ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የሚከፍሉት ከሚጠበቅባቸው ግብር ሁለት ሦስተኛውን ብቻ ነው።
10. የማንወዳቸውን ሕጎች እንኳ መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰብዓዊ መንግሥታት መከራ እንደሚያመጡ፣ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንደሆኑና በቅርቡ እንደሚጠፉ ይናገራል። (መዝ. 110:5, 6፤ መክ. 8:9፤ ሉቃስ 4:5, 6) በሌላ በኩል ደግሞ “ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል” ይላል። ይሖዋ ሥርዓት እንዲሰፍን ሲል የበላይ ባለሥልጣናት ለተወሰነ ጊዜ እንዲገዙ ፈቅዶላቸዋል፤ ስለዚህ እንድንታዘዛቸው ይጠብቅብናል። በመሆኑም ግብርን፣ አክብሮትንና ታዛዥነትን ጨምሮ ‘ለሁሉም የሚገባውን ማስረከብ’ ይጠበቅብናል። (ሮም 13:1-7) አንድ ሕግ የማይመች፣ ፍትሐዊ ያልሆነ ወይም ብዙ ወጪ የሚያስወጣን እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ይሖዋን መታዘዝ እንፈልጋለን፤ እሱ ደግሞ ያወጣውን ሕግ እንድንጥስ እስካልጠየቁን ድረስ ለበላይ ባለሥልጣናት እንድንታዘዝ ነግሮናል።—ሥራ 5:29
11-12. በሉቃስ 2:1-6 መሠረት ዮሴፍና ማርያም እንግልት የሚያስከትልባቸውን ሕግ የታዘዙት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
11 አመቺ ባልሆነ ጊዜ ጭምር ለበላይ ባለሥልጣናት በመታዘዝ ረገድ ከዮሴፍና ከማርያም ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 2:1-6ን አንብብ።) ማርያም የዘጠኝ ወር እርጉዝ ሳለች እሷና ዮሴፍ የታዛዥነት ፈተና አጋጠማቸው። የሮም ገዢ የሆነው አውግስጦስ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዘዘ። ማርያምና ዮሴፍ ዳገት ቁልቁለት አቋርጠው 150 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ቤተልሔም መሄድ ነበረባቸው። ይህ ጉዞ በተለይ ለማርያም የሚያንገላታ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የማርያምና የፅንሱ ደህንነት አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል። መንገድ ላይ ሳለች ምጧ ቢመጣስ? በማህፀኗ የተሸከመችው ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ ነው። እነዚህ ነገሮች መንግሥትን ላለመታዘዝ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ?
12 ዮሴፍና ማርያም እነዚህ ምክንያቶች የመንግሥትን ሕግ ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲሉ እንዲያደርጓቸው አልፈቀዱም። ይሖዋም ለታዛዥነታቸው ባርኳቸዋል። ማርያም ወደ ቤተልሔም በሰላም ደረሰች። በዚያም ጤናማ ልጅ ተገላገለች። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጋለች።—ሚክ. 5:2
13. ታዛዥነታችን ወንድሞቻችንን የሚነካው እንዴት ነው?
13 የበላይ ባለሥልጣናትን ስንታዘዝ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን። እንዴት? አንደኛ፣ ሕጉን የሚተላለፉ ሰዎች ከሚደርስባቸው ቅጣት እንድናለን። (ሮም 13:4) በግለሰብ ደረጃ ታዛዥነት ማሳየታችን ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን በቡድን ደረጃ በሚያዩበት መንገድ ላይ ለውጥ ያመጣል። ለምሳሌ ያህል፣ ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት ናይጄርያ ውስጥ ወታደሮች ስብሰባ እየተካሄደ ሳለ ወደ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ገቡ። ወታደሮቹ ግብር መክፈልን የሚቃወሙ ዓመፀኞችን እየፈለጉ ነበር። ሆኖም ኃላፊያቸው “የይሖዋ ምሥክሮች ግብር መክፈልን አይቃወሙም” በማለት ወታደሮቹን እንዲወጡ አዘዛቸው። አንድን ሕግ በታዘዝክ ቁጥር የይሖዋ ምሥክሮች በሰዎች ዘንድ ላላቸው መልካም ስም አስተዋጽኦ ልታበረክት ትችላለህ፤ ይህ መልካም ስም ደግሞ አንድ ቀን የእምነት አጋሮችህን ሊያድናቸው ይችላል።—ማቴ. 5:16
14. አንዲት እህት የበላይ ባለሥልጣናትን ለመታዘዝ ዝግጁ እንድትሆን የረዳት ምንድን ነው?
14 ያም ቢሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ለበላይ ባለሥልጣናት ለመታዘዝ ተነሳሽነት ላይኖረን ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ጆአና የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ታዛዥ መሆን በጣም ከብዶኝ ነበር። ምክንያቱም አንዳንድ የቤተሰቤ አባላት በባለሥልጣናት ግፍ ተፈጽሞባቸዋል።” ነገር ግን ጆአና አስተሳሰቧን ለመቀየር የታሰበበት ጥረት አደረገች። በመጀመሪያ፣ ለባለሥልጣናት አሉታዊ ስሜት እንዲያድርባት የሚያደርጉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚወጡ ሐሳቦችን ማንበቧን አቆመች። (ምሳሌ 20:3) ሁለተኛ፣ በመንግሥት ለውጥ ላይ ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእሱ ለመታመን እንዲረዳት ይሖዋን በጸሎት ጠየቀችው። (መዝ. 9:9, 10) ሦስተኛ፣ በጽሑፎቻችን ላይ ስለ ገለልተኝነት የወጡ ሐሳቦችን አነበበች። (ዮሐ. 17:16) ጆአና ባለሥልጣናትን ማክበሯና መታዘዟ “በቃላት ሊገለጽ የማይችል ውስጣዊ ሰላም” እንደሰጣት ተናግራለች።
ከይሖዋ ድርጅት የሚመጡ መመሪያዎችን ታዘዝ
15. ከይሖዋ ድርጅት የሚመጡ መመሪያዎችን መታዘዝ ሊያታግለን የሚችለው ለምንድን ነው?
15 ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ‘አመራር ለሚሰጡን እንድንታዘዝ’ ይጠብቅብናል። (ዕብ. 13:17) መሪያችን ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም ምድር ላይ አመራር እንዲሰጡን የሚጠቀምባቸው ወንድሞች ፍጹማን አይደሉም። በተለይ ማድረግ የማንፈልገውን ነገር እንድናደርግ በሚጠይቁን ጊዜ እነሱን መታዘዝ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ለመታዘዝ አመንትቶ ነበር። አንድ መልአክ በሙሴ ሕግ መሠረት ርኩስ የሆኑ እንስሳትን እንዲበላ ባዘዘው ጊዜ ጴጥሮስ ከአንዴም ሦስት ጊዜ አልበላም ብሏል። (ሥራ 10:9-16) ለምን? አዲሱ መመሪያ ምክንያታዊ እንደሆነ አልተሰማውም። ዕድሜ ልኩን ከሚያውቀው የተለየ ነበር። ጴጥሮስ አንድ ፍጹም መልአክ የሰጠውን መመሪያ መታዘዝ ከከበደው እኛ ደግሞ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የሚሰጡንን መመሪያ መታዘዝ ይበልጥ ሊከብደን ይችላል።
16. ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰጠው መመሪያ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ሊሰማው ቢችልም ምን አደረገ? (የሐዋርያት ሥራ 21:23, 24, 26)
16 ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት የተሰጠው መመሪያ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ሊሰማው ቢችልም “ለመታዘዝ ዝግጁ” ነበር። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ ጳውሎስ ‘የሙሴን ሕግ እንዲተዉ ሲያስተምር እንደቆየ’ የሚገልጽ ወሬ ሰምተው ነበር። (ሥራ 21:21) በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ጳውሎስ ሕጉን እንደሚከተል ለማሳየት አራት ሰዎችን ይዞ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲሄድና የመንጻት ሥርዓት እንዲፈጽም አዘዙት። ሆኖም ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በሕጉ ሥር እንዳልሆኑ ያውቃል። እንዲሁም ምንም ያጠፋው ጥፋት የለም። ያም ቢሆን ጳውሎስ ሳያመነታ ታዟል። “በማግስቱ ሰዎቹን ይዞ በመሄድ አብሯቸው የመንጻት ሥርዓቱን ፈጸመ።” (የሐዋርያት ሥራ 21:23, 24, 26ን አንብብ።) የጳውሎስ ታዛዥነት አንድነት እንዲሰፍን አድርጓል።—ሮም 14:19, 21
17. ከስቴፋኒ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
17 ስቴፋኒ የተባለች እህት በአገሯ የሚኖሩ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ያደረጉትን አንድ ውሳኔ መቀበል ከብዷት ነበር። እሷና ባለቤቷ በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ቡድን ውስጥ በደስታ እያገለገሉ ነበር። ከዚያም ቅርንጫፍ ቢሮው ቡድኑን አፈረሰው፤ እነሱም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወደሚመራ ጉባኤ ተዛወሩ። ስቴፋኒ እንዲህ ስትል በሐቀኝነት ተናግራለች፦ “በጣም አዝኜ ነበር። በአፍ መፍቻ ቋንቋችን የሚመራው ጉባኤ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሆኖ አልተሰማኝም።” ያም ቢሆን አዲሱን መመሪያ ለመደገፍ ወሰነች። እንዲህ ብላለች፦ “ውሎ አድሮ ውሳኔው ጥበብ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ማስተዋል ቻልኩ። እውነት ውስጥ ቤተሰብ ለሌላቸው ብዙ ወንድሞች መንፈሳዊ ወላጆች መሆን ችለናል። በቅርቡ ተነቃቅታ አገልግሎት ለጀመረች እህት ጥናት እየመራሁ ነው። በተጨማሪም አሁን ለግል ጥናት የሚሆን ሰፊ ጊዜ አለኝ።” አክላም “ታዛዥ ለመሆን አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ እንዳደረግኩ ስለማውቅ ንጹሕ ሕሊና አለኝ” ብላለች።
18. መታዘዝ ምን ጥቅም ያስገኛል?
18 ታዛዥነትን ልንማር እንችላለን። ኢየሱስ ‘መታዘዝን የተማረው’ ሁሉ ነገር ተመቻችቶለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “ከደረሰበት መከራ” ነው። (ዕብ. 5:8) እኛም እንደ ኢየሱስ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን መታዘዝን እንማራለን። ለምሳሌ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት በስብሰባ አዳራሾች መሰብሰባችንንና ከቤት ወደ ቤት ማገልገላችንን እንድናቆም መመሪያ በተሰጠን ወቅት መታዘዝ አታግሎህ ነበር? ያም ቢሆን መታዘዝህ ጥበቃ አድርጎልሃል፤ ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር አንድነት እንዲኖርህ አድርጓል፤ እንዲሁም ይሖዋን አስደስቶታል። አሁን ሁላችንም፣ በታላቁ መከራ ወቅት የሚሰጠንን ማንኛውንም መመሪያ ለመታዘዝ ይበልጥ ዝግጁ ነን። እንዲህ ማድረጋችን የሕይወትና የሞት ጉዳይ ሊሆን ይችላል።—ኢዮብ 36:11
19. ታዛዥ መሆን የምትፈልገው ለምንድን ነው?
19 ታዛዥነት ስፍር ቁጥር የሌላቸው በረከቶች እንደሚያስገኝ ተምረናል። ሆኖም ይሖዋን ለመታዘዝ እንድንመርጥ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ስለምንወደውና እሱን ማስደሰት ስለምንፈልግ ነው። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋ ላደረገልን መልካም ነገሮች ሁሉ ውለታውን ፈጽሞ ልንከፍለው አንችልም። (መዝ. 116:12) ይሁንና እሱንም ሆነ በእኛ ላይ ሥልጣን የሰጣቸውን ሰዎች ልንታዘዝ እንችላለን። ስንታዘዝ ጥበበኞች መሆናችንን እናሳያለን። ጥበበኛ ሰዎች ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛሉ።—ምሳሌ 27:11
መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ
a ፍጹማን ስላልሆንን ሁላችንም አንዳንድ ጊዜ መታዘዝ ሊያታግለን ይችላል። መመሪያ የሰጠን ሰው እኛን ለማዘዝ ሥልጣን ቢኖረውም እንኳ መታዘዝ ሊከብደን ይችላል። ይህ ርዕስ ወላጆቻቸውን፣ ‘የበላይ ባለሥልጣናትን’ እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች የሚታዘዙ ሁሉ የሚያገኟቸውን በረከቶች ያብራራል።
b ለመታዘዝ ከሚከብዱህ ሕጎች ጋር በተያያዘ ከወላጆችህ ጋር ለመነጋገር እንዲረዳህ jw.org ላይ የሚገኘውን “ወላጆቼ ስላወጧቸው ሕጎች ከእነሱ ጋር መነጋገር የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ዮሴፍና ማርያም የቄሳርን አዋጅ በመታዘዝ ለምዝገባ ወደ ቤተልሔም ሄደዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ ያወጧቸውን የትራፊክ ሕጎች፣ የግብር ደንቦች እንዲሁም የጤና መመሪያዎች ይታዘዛሉ።