አንድ ክርስቲያን ለባለ ሥልጣን ያለው አመለካከት
“ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና።”—ሮሜ 13:1
1. ይሖዋ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
ሥልጣን ከፈጣሪነት ጋር የተያያዘ ነው። ሕይወት ያላቸውንም ሆነ የሌላቸውን ፍጥረታት በሙሉ ወደ ሕልውና ያመጣቸው የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ይሖዋ አምላክ ነው። ያለምንም ጥርጥር እሱ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚከተለውን የሰማያዊ ፍጥረታት አባባል ይስማሙበታል፦ “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11
2. በጥንት የነበሩ ሰብአዊ ገዢዎች በባልንጀሮቻቸው ላይ ለመግዛት ትክክለኛ መብት የሌላቸው መሆኑን እንደተቀበሉ በተዘዋዋሪ ያሳዩት እንዴት ነው? ኢየሱስስ ለጴንጠናዊው ጲላጦስ ምን አለው?
2 ቀደም ሲል የነበሩት ብዙዎቹ ሰብአዊ መሪዎች ራሳቸው አምላክ ወይም የአምላክ ወኪሎች እንደሆኑ በመናገር ሥልጣናቸውን ሕጋዊ ለማድረግ መሞከራቸው ማንም ሰው በተፈጥሮ የወረሰው በሌሎች ሰዎች ላይ የመግዛት መብት እንደሌለው በተዘዋዋሪ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።a (ኤርምያስ 10:23) ብቸኛው የሕጋዊ ሥልጣን ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነው። ክርስቶስ ለሮማዊው የይሁዳ አገረ ገዥ ለጴንጠናዊው ጲላጦስ “ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም” ብሎት ነበር።—ዮሐንስ 19:11
“ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለም”
3. ሐዋርያው ጳውሎስ “የበላይ ባለ ሥልጣኖችን” አስመልክቶ ምን ተናገረ? የኢየሱስና የጳውሎስ አነጋገርስ ምን ጥያቄዎችን ያስነሣል?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም አገዛዝ ሥር ለነበሩት ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል ጽፎላቸዋል፦ “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።” (ሮሜ 13:1) ኢየሱስ የጲላጦስ ሥልጣን ከላይ የተሰጠ ነው ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስስ በእሱ ዘመን የነበሩት የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው ሲል ነገሩን በምን መንገድ ተመልክቶት ነው? እያንዳንዱ የዚህ ዓለም የፖለቲካ ገዢ እንዲሾም የሚያደረገው ይሖዋ ነው ማለታቸው ነውን?
4. ኢየሱስና ጳውሎስ ሰይጣንን ምን ብለው ጠሩት? ኢየሱስስ የትኛውን የሰይጣን አባባል አላስተባበለም?
4 ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ስለጠራውና ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ “የዚህ ዓለም አምላክ” ስላለው ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? (ዮሐንስ 12:31፤ 16:11፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን ኢየሱስን በፈተነበት ጊዜ ይህ ሥልጣን ሁሉ ለእሱ እንደተሰጠው በመናገር ‘በሁሉም የዓለም መንግሥታት ላይ’ “ሥልጣን” ሊሰጠው ግብዣ አቅርቦለት ነበር። ኢየሱስ ግብዣውን አልተቀበለም፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጣን ለመስጠት መብት የለህም ብሎ አላስተባበለም።—ሉቃስ 4:5–8
5. (ሀ) ኢየሱስና ጳውሎስ ሰብአዊ ባለ ሥልጣንን አስመልክተው የተናገሯቸውን ቃላት የምንረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) የበላይ ባለ ሥልጣኖች ‘አንፃራዊ ሥልጣናቸው ላይ የተቀመጡት በአምላክ ነው’ የሚባለው ከምን አንፃር ነው?
5 ሰይጣን ካመፀና አዳምንና ሔዋንንም ፈትኖ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ እንዲያምፁ ካደረጋቸው በኋላ በሕይወት እንዲኖር ይሖዋ በመፍቀዱ ሰይጣን በዚህ ዓለም ላይ ገዥ ሊሆን በቅቷል። (ዘፍጥረት 3:1–6፤ ከዘጸአት 9:15, 16 ጋር አወዳድር።) እንግዲያው የኢየሱስና የጳውሎስ አነጋገር በኤደን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች ቲኦክራሲን ወይም የአምላክን አገዛዝ አንቀበልም ካሉ በኋላ ከአምላክ ተለይተው መሄድ የጀመሩት ሰዎች ሥርዓታማ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ ለመኖር የሚያስችላቸው የራሳቸው የሥልጣን መዋቅር እንዲፈጥሩ ይሖዋ ፈቅዶላቸዋል ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል አንዳንድ ገዥዎች ወይም መንግሥታት እንዲወድቁ አድርጓል። (ዳንኤል 2:19–21) ሌሎቹን ደግሞ በሥልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ ፈቅዶላቸዋል። ይሖዋ እንዲገዙ ስለታገሣቸው ገዥዎች “በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” ሊባል ይችላል።
የጥንት ክርስቲያኖችና የሮም ባለ ሥልጣኖች
6. የጥንት ክርስቲያኖች ሮማዊ ባለ ሥልጣኖችን እንዴት ይመለከቷቸው ነበር? ለምንስ?
6 የጥንት ክርስቲያኖች እስራኤልን ይዘው በነበሩት ሮማውያን ላይ አድመው ከተዋጉት የአይሁድ ኃይሎች ጋር አልተባበሩም። በወቅቱ የነበሩት የሮም ባለ ሥልጣኖች በአንቀጽ ተከፋፍሎ በተዘጋጀው ሕጋቸው አማካኝነት በየብስም ሆነ በባሕር ሥርዓት እንዲከበር አድርገዋል። ብዙ ጠቃሚ የሆኑ የውኃ ቧንቧዎችን፣ መንገዶችንና ድልድዮችን ሠርተዋል፤ በአጠቃላይ ለሕዝቡ በጎ ነገር ሠርተዋል፤ ስለሆነም ክርስቲያኖች ‘ለመልካም ነገር ለእነሱ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆኑ’ አድርገው ተመልክተዋቸዋል። (ሮሜ 13:3, 4) ሕግና ሥርዓት መኖሩ ክርስቲያኖች ኢየሱስ እንዳዘዘው ምሥራቹን በርቀትና በስፋት እንዲሰብኩ የሚያስችላቸው ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ምንም እንኳን የተወሰነው ገንዘብ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለሌላቸው ዓላማዎች የሚውል ቢሆንም ክርስቲያኖች በሮማውያን የተጣለባቸውን ቀረጥ በንጹሕ ኅሊና ይከፍሉ ነበር።—ሮሜ 13:5–7
7, 8. (ሀ) ሮሜ 13:1–7ን በጥንቃቄ ማንበብ ምንን ለመረዳት ያስችላል? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብስ ምን ያሳያል? (ለ) ሮማውያን ባለ ሥልጣኖች እንደ ‘አምላክ አገልገይ’ ሆነው ያልሠሩባቸው ሁኔታዎች የትኞቹ ነበሩ? በዚህስ ጊዜ የጥንት ክርስቲያኖች ምን አቋም ነበራቸው?
7 የሮሜ ምዕራፍ 13ን የመጀመሪያ ሰባት ቁጥሮች በጥንቃቄ ብናነብ ፖለቲካዊ “የበላይ ባለ ሥልጣኖች” መልካም የሚያደርጉትን ለማመስገንና ክፉ የሚያደርጉትን ደግሞ ለመቅጣት የቆሙ ‘የአምላክ አገልጋዮች’ እንደነበሩ ለመረዳት እንችላለን። መልካም የሆነውንና ክፉ የሆነውን የሚወስነው አምላክ እንጂ የበላይ ባለ ሥልጣኖች እንዳልሆኑ በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ያስረዳል። እንግዲያው አንድ ሮማዊ ገዢ ወይም ማንኛውም ሌላ የፖለቲካ ባለ ሥልጣን አምላክ የሚከለክላቸውን ነገሮች እንዲያደርጉ ቢጠይቅ ወይም በተገላቢጦሽ አምላክ የሚጠይቃቸውን ነገሮች ደግሞ ቢከለክል እንደ አምላክ አገልጋይ ሆኖ አላገለገለም ማለት ነው። ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:21) የሮም መንግሥት የአምላክ የሆኑትን ነገሮች ማለትም እንደ አምልኮት ወይም የአንድን ሰው ሕይወት የመሳሰሉትን ቢጠይቅ እውነተኛ ክርስቲያኖች “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚለውን ሐዋርያዊ ምክር ይከተላሉ።—ሥራ 5:29
8 የጥንት ክርስቲያኖች ንጉሡን አናመልክም፣ የጣኦት አምልኮ አንፈጽምም፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባችንንም ሆነ ምሥራቹን መስበካችንን አናቆምም ማለታቸው ስደት አስከትሎባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በንጉሠ ነገሥት ኔሮ ትዕዛዝ እንደተገደለ ይታመናል። ሌሎች ንጉሠ ነገሥታትም በተለይም እንደ ዶሚሺያን፣ ማርከስ ኦሪሊየስ፣ ሴፕቲምየስ፣ ሴዋረስ፣ ዴሲየስና ዲኦክሺያን ያሉት ነገሥታት ጭምር የጥንት ክርስቲያኖችን አሳድደዋል። እነዚህ ነገሥታትና የበታች ባለ ሥልጣኖቻቸው ክርስቲያኖችን ባሳደዱበት ጊዜ ‘የአምላክ አገልጋዮች’ ሆነው እየሠሩ እንዳልነበሩ ግልፅ ነው።
9. (ሀ) የፖለቲካ የበላይ ባለ ሥልጣኖችን አቋም በተመለከተ የትኛው ነገር እውነት ነው? የፖለቲካ አውሬው ኃይሉንና ሥልጣኑን የተቀበለው ከማን ነው? (ለ) ለበላይ ባለ ሥልጣኖች ክርስቲያናዊ ተገዢነት ማሳየትን በተመለከተ ምን ቢባል ምክንያታዊ ነው?
9 ይህ ሁሉ የሚያስረዳው ነገር ቢኖር ፖለቲካዊ የበላይ ባለ ሥልጣኖች ሥርዓት ያለው ሰብአዊ ኅብረተሰብ እንዲኖር “የእግዚአብሔር አገልጋይ” ሆነው የሚያገለግሉም እንኳን ቢሆን ሰይጣን አምላኩ የሆነለት ዓለማዊ የነገሮች ሥርዓት ክፍል መሆናቸው ያልቀረ መሆኑን ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) በራእይ 13:1, 2 ላይ ባለው “አውሬ” የተመሰለው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ድርጅት ክፍል ናቸው። ይህ “አውሬ” ኃይሉንና ሥልጣኑን የተቀበለው ‘ከታላቁ ዘንዶ’ ከሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ራእይ 12:9) እንግዲያው ክርስቲያኖች ለእንዲህ ዓይነቱ ሥልጣን የሚያሳዩት ተገዢነት አንጻራዊ እንጂ ፍጹም አይደለም ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።—ከዳንኤል 3:16–18 ጋር አወዳድር።
ለሥልጣን ተገቢ አክብሮት ማሳየት
10, 11. (ሀ) በሥልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ማክበር እንዳለብን ጳውሎስ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ‘ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንቶች’ መጸለይ የሚቻለው እንዴትና ለምንድን ነው?
10 እንዲህ ሲባል ግን ክርስቲያኖች ለፖለቲካ የበላይ ባለ ሥልጣኖች የንቀትና የእምቢተኝነት ዝንባሌ ማሳየት አለባቸው ማለት አይደለም። እውነት ነው፣ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ በግልም ሆነ በሕዝብ ፊት ከሚያደርጉት ነገር አንፃር አክብሮት የማይገባቸው ናቸው። ይሁን እንጂ ሐዋርያት በተዉልን ምሳሌም ሆነ በሰጡት ምክር በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች መከበር እንዳለባቸው አሳይተዋል። ጳውሎስ ወራዳ ምግባር በሚፈጽመው በንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ሁለተኛ ፊት በቀረበ ጊዜ ተገቢ አክብሮት እያሳየ አነጋግሮታል።—ሥራ 26:2, 3, 25።
11 ጳውሎስ ሌላው ቀርቶ ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖችን በጸሎታችን ላይ መጥቀስ ተገቢ መሆኑን ገልጿል። በተለይ ይህን የምናደርገው ሕይወታችንና ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን የሚመለከት ውሳኔ እንዲያደርጉ በሚጠየቁበት ጊዜ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፣ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።” (1 ጢሞቴዎስ 2:1–4) ለእነዚህ ባለ ሥልጣኖች የሚኖረን አክብሮት የተሞላባት አቋም ‘ሰዎችን ሁሉ’ ለማዳን በምናደርገው ጥረት የምንሠራውን ሥራ በነፃነት እንድናከናውን እንዲፈቅዱልን ሊያደርጋቸው ይችላል።
12, 13. (ሀ) ጴጥሮስ ሥልጣንን በተመለከተ ምን ሚዛናዊ ምክር ሰጥቷል? (ለ) በይሖዋ ምሥክሮች ላይ መሠረተቢስ የሆነ ጥላቻ የሚዘሩትን “የማያውቁትን ሞኞች” ዝም ልናሰኝ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፣ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፣ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። በጎ እያደረጋችሁ፣ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፤ አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ። ሁሉን አክብሩ፣ ወንድሞችን ውደዱ፣ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ንጉሥን አክብሩ።” (1 ጴጥሮስ 2:13–17) እንዴት ያለ ሚዛናዊ ምክር ነው! ባሪያዎቹ እንደመሆናችን መጠን ለአምላክ ሙሉ በሙሉ የመገዛት ግዴታ አለብን፤ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት ለተላኩት የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች ደግሞ አንጻራዊና አክብሮት የሞላበት ተገዢነት እናሳያለን።
13 ብዙ ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ካለማወቅ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በጣም የተዛባ አመለካከት እንዳላቸው ታውቋል። ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች በክፋት ተነሳስተው ስለኛ የተሳሳተ ነገር ስለሚነግሯቸው ነው። ወይም ደግሞ ስለኛ ለማወቅ የቻሉት በመገናኛ ብዙኃን የተገለጸውን በመስማት ወይም በማንበብ ብቻ ሊሆን ይችላል። ጋዜጠኞች ደግሞ ሁልጊዜ ከአድልዎ ነፃ አይደሉም። የአክብሮት ጠባይ በማሳየት ወይም በሚቻልበት ቦታ ሁሉ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሥራና እምነት ትክክለኛ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ጽሑፍ በመስጠት የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች ከሩቁ ለእኛ ያላቸውን መሠረተቢስ የሆነ ጥላቻ ለማስወገድ እንችል ይሆናል። ሥራ ለሚበዛባቸው ባለ ሥልጣኖች የይሖዋ ምሥክሮች በሃያኛው መቶ ዘመን የተባለው ብሮሹር እጥር ምጥን ያለ ማብራሪያ ይሰጣል። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ ከተፈለገ ደግሞ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን መጽሐፍ ልንሰጣቸው እንችላለን። ይህ መጽሐፍ በተለያዩ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት መገኘት የሚገባው ነው።
በክርስቲያን ቤት ውስጥ ያለው ሥልጣን
14, 15. (ሀ) በአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ላለው ሥልጣን መሠረቱ ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያን ሚስቶች ለባሎቻቸው ሊኖራቸው የሚገባ ዝንባሌ ምንድን ነው? ለምንስ?
14 ክርስቲያኖች ለዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ተገቢውን አክብሮት እንዲያሳዩ አምላክ ከጠየቀባቸው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ አምላክ ያቋቋመውን የሥልጣን መዋቅርም በተመሳሳይ ማክበር እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለይሖዋ ሕዝብ የሚሠራውን የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት በአጭር አነጋገር አስቀምጦታል። “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ይህ የቲኦክራሲ ወይም የአምላክ አገዛዝ መሠረታዊ ሥርዓት ነው። ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል?
15 ለቲኦክራሲ አክብሮት ማሳየት የሚጀምረው ከቤት ነው። ባሏ የሚያምን ሆነም አልሆነም ለባሏ ሥልጣን ተገቢውን አክብሮት የማታሳይ ክርስቲያን ሚስት ቲኦክራሲያዊ አቋም የላትም። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል መክሯል፦ “ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ፣ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ።” (ኤፌሶን 5:21–24) ክርስቲያን ወንዶች ለክርስቶስ ራስነት መገዛት እንዳለባቸው ሁሉ ክርስቲያን ሴቶችም ባሎቻቸው ከአምላክ ላገኙት ሥልጣን መገዛት ጥበብ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ይህም ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ እርካታ ያመጣላቸዋል፤ ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ የይሖዋን በረከት ያስገኝላቸዋል።
16, 17. (ሀ) በክርስቲያን ቤቶች ውስጥ ያደጉ ልጆች ዛሬ ካሉት ሌሎች ልጆች የተለየ ጠባይ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህንንስ ጠባይ ለማሳየት ምን ነገር ሊገፋፋቸው ይችላል? (ለ) ኢየሱስ ዛሬ ላሉት ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? ምን እንዲያደርጉስ እናበረታታቸዋለን?
16 ቲኦክራሲያዊ አቋም ያላቸው ልጆች ለወላጆቻቸው ተገቢውን አክብሮት ለማሳየት ደስተኞች ናቸው። በመጨረሻው ዘመን የሚኖረውን ወጣት ትውልድ አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተነግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2) ይሁን እንጂ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ለክርስቲያን ወጣቶች እንደሚከተለው ይላል፦ “ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።” (ቆላስይስ 3:20) ለወላጅ ሥልጣን አክብሮት ማሳየት ይሖዋን ያስደስታል፤ እንዲሁም የእሱን በረከት ያስገኛል።
17 የኢየሱስ ምሳሌ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። ሉቃስ የመዘገበው ታሪክ እንደሚከተለው ይላል፦ “ከእነርሱም [ከወላጆቹ] ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፣ ይታዘዝላቸውም ነበር (ለእነሱ መታዘዙን ቀጠለ [አዓት])። . . . ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።” (ሉቃስ 2:51, 52) በዚያን ጊዜ ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ነበር። እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ግስ ለወላጆቹ ‘መታዘዝ መቀጠሉን ’ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ስለዚህ ወደ አሥራዎቹ ዕድሜው ሲገባም ታዛዥነቱ አላበቃም። እናንት ወጣቶች በመንፈሳዊ ለማደግ እንዲሁም በይሖዋና አምላካዊ በሆኑ ሰዎች ፊት በይበልጥ ሞገስ ለማግኘት የምትፈልጉ ከሆነ በቤታችሁ ውስጥም ሆነ ከቤታችሁ ውጭ ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ይኖርባችኋል።
በጉባኤ ውስጥ ያለው ሥልጣን
18. የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ማን ነው? እሱስ በውክልና ሥልጣን የሰጠው ለማን ነው?
18 ጳውሎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶ የሚከተለውን ጽፏል፦ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ . . . ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።” (1 ቆሮንቶስ 14:33, 40) ሁሉም ነገር በሥርዓት እንዲከናወን የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ክርስቶስ ለታማኝ ወንዶች በውክልና ሥልጣን ሰጥቷል። እንዲህ እናነባለን፦ “እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ . . . ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና . . . እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ።”—ኤፌሶን 4:11, 12, 15
19. (ሀ) ክርስቶስ በምድር ላይ ባለው ንብረቱ ሁሉ ላይ የሾመው ማንን ነው? ልዩ ሥልጣን የሰጠውስ ለማን ነው? (ለ) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን የሥልጣን ውክልና አለ? ይህስ በእኛ በኩል ምን ይጠይቅብናል?
19 በዚህ የመጨረሻ ዘመን ክርስቶስ ‘የታማኝና ልባም ባሪያን’ ቡድን “ባለው ሁሉ” ላይ ወይም በምድር ላይ በሚከናወኑት የመንግሥቱ ሥራዎች ላይ ሾሞታል። (ማቴዎስ 24:45–47) እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ ይህ ባሪያም ውሳኔዎችን እንዲያደርጉና ሌሎች የበላይ ተመልካቾችን እንዲሾሙ ክርስቶስ ሥልጣን በሰጣቸው የተቀቡ ክርስቲያን ወንዶች አባላት በሆኑበት የአስተዳደር አካል የሚወከል ነው። (ሥራ 6:2, 3፤ 15:2) የአስተዳደር አካል ደግሞ በተራው ለቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴዎች፣ ለወረዳና ለክልል የበላይ ተመልካቾች እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ከ73,000 በላይ በሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙት ለሽማግሌዎች በውክልና ሥልጣን ይሰጣል። እነዚህ በጣም የሚደክሙልን ክርስቲያን ወንዶች ሁሉ የእኛ ድጋፍና አክብሮት ይገባቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 5:17
20. በሥልጣን ላይ ላሉት መሰል ክርስቲያኖች አክብሮት በሚጎድላቸው ሰዎች ላይ ይሖዋ እንደሚቆጣ ምን ምሳሌ ያሳያል?
20 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሥልጣን ላይ ላሉት ማሳየት የሚገባንን አክብሮት በተመለከተ ለዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች ማሳየት ከሚገባ ተገዢነት ጋር ጥሩ አድርጎ ማነፃፀር ይቻላል። አንድ ሰው አምላክ የሚቀበለውን አንድ ሰብአዊ ሕግ ሲያፈርስ ‘በገዢዎች’ የሚወሰንበት ቅጣት በተዘዋዋሪ ‘ክፉ በሚያደርግ ላይ’ የመጣ የአምላክ ቁጣ መግለጫ ነው። (ሮሜ 13:3, 4) ይሖዋ አንድ ሰው ሰብአዊ ሕግ ሲያፈርስና ለዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች አክብሮት ሳያሳይ ሲቀር የሚቆጣ ከሆነ አንድ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሆነ ብሎ ሲጥስና በሥልጣን ላይ ላሉት መሰል ክርስቲያኖች ንቀት ሲያሳይ ይበልጥ አይከፋምን?
21. የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመከተል እንፈልጋለን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚመረመረውስ ጉዳይ ምንድን ነው?
21 የዓመፀኝነት ወይም በራሴ እመራለሁ የሚል ዝንባሌ በመያዝ በራሳችን ላይ የአምላክን ቁጣ ከማምጣት ይልቅ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈውን የሚከተለውን ምክር እንከተላለን፦ “ስለዚህ፣ ወዳጆቼ ሆይ፣ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፣ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፣ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጎራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ።” (ፊልጵስዩስ 2:12–15) በራሱ ላይ የሥልጣን ውዝግብ ካስከተለው ከዚህ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ በተለየ ሁኔታ የይሖዋ ሕዝቦች ለባለ ሥልጣን ለመገዛት ዝግጁ ናቸው። እንዲህ በማድረጋቸውም በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምናየው ብዙ ጥቅሞችን ያገኛሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከዚህ ከፊት ያለውን ርዕስ ተመልከት
ለክለሳ ያህል
◻ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ማን ነው? ሥልጣኑስ ሕጋዊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ የበላይ ባለ ሥልጣኖች “በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” የሚባለው ከምን አንፃር ነው?
◻ የበላይ ባለ ሥልጣኖች ‘የአምላክ አገልጋዮች’ መሆናቸውን የሚያቆሙት መቼ ነው?
◻ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ምን የሥልጣን መዋቅር አለ?
◻ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን የሥልጣን ውክልና አለ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ‘ የቄሣርን ለቄሣር አስረክቡ ’ ብሏል