“ጎልማሳ” ክርስቲያን ነህን?
“ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፣ እንደ ልጅም አስብ ነበር፣ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር።” ይህን ያለው ሐዋርያው ጳውሎስ ነበር። በእርግጥም፣ ሁላችንም በአንድ ወቅት ክፉና ደጉን የማንለይ ሕፃናት ነበርን። ይሁን እንጂ እንደዚያ ሆነን አልቀረንም። ጳውሎስ “ጒልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ” ሲል ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 13:11
በተመሳሳይ ክርስቲያኖች በሙሉ በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ሕፃናት ነበሩ። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ሁሉም “በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት በኩል አንድ ወደ መሆን፣ ጎልማሳ ወደ መሆን፣ የክርስቶስ ሙሉነት ወደ ሆነው የዕድገት ደረጃ” ሊደርሱ ይችላሉ። (ኤፌሶን 4:13 NW ) በ1 ቆሮንቶስ 14:20 ላይ “ወንድሞች ሆይ፣ በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ . . . በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ” የሚል ምክር ተሰጥቶናል።
በተለይ ዛሬ እጅግ ብዙ አዳዲስ ሰዎች ወደ እውነት ስለመጡ የጎለመሱ ክርስቲያኖች መኖራቸው ለአምላክ ሕዝቦች በረከት ነው። በአንድ ጉባኤ ውስጥ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ካሉ ጉባኤው በመንፈሳዊ ጠንካራ ይሆናል። በየትኛውም ጉባኤ ቢኖሩ በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።
አነሰም በዛ አካላዊ እድገት በራሱ የሚመጣ ነገር ሲሆን መንፈሳዊ እድገት ግን ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ነው። በጳውሎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች አምላክን ለብዙ ዓመታት ቢያገለግሉም ‘ወደ ጉልምስና ማደግ’ አለመቻላቸው ምንም አያስደንቅም። (ዕብራውያን 5:12፤ 6:1 NW ) አንተስ? አምላክን ለብዙ ወይም በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለጥቂት ዓመታት ያገለገልክ ብትሆንም ራስህን በሐቀኝነት መመርመሩ ተገቢ ነው። (2 ቆሮንቶስ 13:5) በእርግጥ ጎልምሰዋል ከሚባልላቸው ክርስቲያኖች መካከል ነህ? ካልሆነ ወደ ጉልምስና ማደግ የምትችለው እንዴት ነው?
“በማስተዋል ችሎታ መብሰል”
በመንፈሳዊ ሕፃን የሆነ ሰው በቀላሉ ‘እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኰል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ ይፍገመገማል፤ ወዲያና ወዲህም ይንሳፈፋል።’ ስለዚህ ጳውሎስ “እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ” በማለት አሳስቧል። (ኤፌሶን 4:14, 15) አንድ ክርስቲያን ማደግ የሚችለው እንዴት ነው? ዕብራውያን 5:14 NW “ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ለሚያሰለጥኑ ለጎለመሱ ሰዎች ነው” ይላል።
የጎለመሱ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ለማድረግ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ወይም በልምድ እንዳሰለጠኑት ልብ በል። ስለዚህ አንድ ሰው በአንድ ጀንበር ሊጎለምስ እንደማይችል የታወቀ ነው፤ መንፈሳዊ እድገት ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ነው። ቢሆንም በግል ጥናት አማካኝነት የአምላክን ቃል ጥልቅ ነገሮች በመመርመር መንፈሳዊ እድገትህን ለማፋጠን ብርቱ ጥረት ማድረግ ትችላለህ። በቅርብ ዓመታት መጠበቂያ ግንብ ለብዙ ጥልቅ ርዕሶች ማብራሪያ ሰጥቷል። የጎለመሱ ክርስቲያኖች እነዚህ ርዕሶች “ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር” ስለያዙ ብቻ ከማንበብ ወደኋላ አይሉም። (2 ጴጥሮስ 3:16) ከዚህ ይልቅ እንደዚህ ያለውን ጠንካራ ምግብ በጉጉት ይመገባሉ!
ቀናተኛ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዟቸው ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) በተጨማሪም በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል መንፈሳዊ እድገትህን ሊያፋጥንልህ ይችላል። ሁኔታህ በፈቀደ መጠን ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ለምን ጥረት አታደርግም?—ማቴዎስ 13:23
አንዳንድ ጊዜ ኑሮ የሚፈጥረው ጫና ለስብከት ጊዜ ሊያሳጣህ ይችላል። ሆኖም ለመስበክ ‘ብርቱ ትግል በማድረግ’ ‘ለምሥራቹ’ ምን ያህል ትልቅ ግምት እንደምትሰጠው ታሳያለህ። (ሉቃስ 13:24፤ ሮሜ 1:16) በዚህም ‘በሚያምኑት ዘንድ እንደ ምሳሌ’ ልትታይ ትችላለህ።—1 ጢሞቴዎስ 4:12
የአቋም ጽናት የሚያሳዩ ሰዎች
ወደ ጉልምስና ማደግ የአቋም ጽናትህን ለማሳየት ጥረት ማድረግንም ይጨምራል። በመዝሙር 26:1 ላይ እንደተመዘገበው ዳዊት “አቤቱ፣ እኔ በየውሃቴ [“በአቋም ጽናቴ፣” NW ] ሄጃለሁና ፍረድልኝ” በማለት ተናግሯል። የአቋም ጽናት ማለት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን መጠበቅ ማለት ነው። ይህ ሲባል ግን ፍጹም መሆን ማለት አይደለም። ዳዊት ራሱ የተለያዩ ከባድ ኃጢአቶችን ሠርቷል። ሆኖም የተሰጠውን ወቀሳ ተቀብሎ መንገዱን በማስተካከሉ ይሖዋ አምላክን ከልብ እንደሚያፈቅር አሳይቷል። (መዝሙር 26:2, 3, 6, 8, 11) የአቋም ጽናት በሙሉ ልብ ወይም በፍጹም ልብ አምላክን መውደድን ይጨምራል። ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን “የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው” በማለት መክሮታል።—1 ዜና መዋዕል 28:9
የአቋም ጽናት ብሔራት ከሚያራምዱት ፖለቲካና ከሚያደርጉት ጦርነት በመራቅ ‘የዓለም ክፍል አለመሆንን’ ይጨምራል። (ዮሐንስ 17:16) እንዲሁም ከዝሙት፣ ከምንዝርና አደገኛ ዕፆችን መውሰድን ከመሳሰሉ ብልሹ ምግባሮች መቆጠብ ይገባል። (ገላትያ 5:19-21) የአቋም ጽናትን ማሳየት ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መቆጠብ ማለት ብቻ አይደለም። ሰሎሞን “የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤ እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል” በማለት አስጠንቅቋል። (መክብብ 10:1) አዎን፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተገቢ ባልሆነ መንገድ መቀለድን ወይም መሽኮርመምን የመሰለ “ትንሽ ስንፍና” እንኳ የአንድን ሰው “ጥበብ” ሊያጎድፍበት ይችላል። (ኢዮብ 31:1) ስለዚህ “ከክፉ ነገር” በመራቅ በአኗኗርህ ሁሉ ምሳሌ ለመሆን በመጣር መጎልመስህን አሳይ።—1 ተሰሎንቄ 5:22
ታማኞች
በተጨማሪም ጎልማሳ ክርስቲያን ታማኝ ነው። በኤፌሶን 4:24 ላይ እንደምናነበው ሐዋርያው ጳውሎስ:- “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና [“ታማኝነት፣” NW ] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” በማለት አሳስቧል። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ታማኝነትን” ለማመልከት የገባው መሠረታዊው ቃል ቅድስና፣ ጽድቅ፣ ላቅ ያለ ክብር የሚል ሐሳብም ያስተላልፋል። ታማኝ ሰው ለአምላክ ያደረና ጻድቅ ነው፤ በአምላክ ዘንድ ያለበትን ግዴታ ሁሉ በጥንቃቄ ይወጣል።
እንደዚህ ያለ ታማኝነት ማሳየት የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? አንደኛው መንገድ ከጉባኤህ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ነው። (ዕብራውያን 13:17) ክርስቶስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ሆኖ መሾሙን ስለሚቀበሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ‘የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቁ’ ለተሾሙት ታማኝነትን ያሳያሉ። (ሥራ 20:28) የተሾሙ ሽማግሌዎችን ስልጣን መጠራጠር ወይም ማናናቅ ከባድ ስህተት ነው! ሌላው ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲሁም የባሪያው ክፍል መንፈሳዊ ‘ምግብን በጊዜው’ ለማሰራጨት ለሚጠቀምባቸው ወኪሎቹ ታማኝነት ማሳየት እንዳለብህ ሊሰማህ ይገባል። (ማቴዎስ 24:45) በመጠበቂያ ግንብ እንዲሁም በሌሎች የማኅበሩ ጽሑፎች ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ለማንበብና ያነበብከውን ተግባራዊ ለማድረግ ፈጣን ሁን።
ፍቅርን በተግባር መግለጽ
ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ [ይብዛ]” በማለት ጽፎላቸው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 1:3) በፍቅር ማደግ መንፈሳዊ ጉልምስና የሚታይበት ዓይነተኛው መንገድ ነው። በዮሐንስ 13:35 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። እንዲህ ያለው የወንድማማች ፍቅር እንዲሁ በስሜት ብቻ የተወሰነ አይደለም። በቫይንስ የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ እንዳስቀመጠው “ፍቅር የሚገለጸው በድርጊት ነው።” አዎን፣ ፍቅርን በተግባር በመግለጽ ወደ ጉልምስና እደግ!
ለምሳሌ ያህል በሮሜ 15:7 ላይ “እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” የሚል እናነባለን። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ወንድሞችንም ሆነ እንግዶችን ሞቅ ባለ ስሜት ከልብ ሰላም ማለት ፍቅራችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው! እያንዳንዳቸውን ቀርበህ እወቃቸው። ሌሎችን ‘የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ከልብ’ ጣር። (ፊልጵስዩስ 2:4) ምናልባትም የተለያዩ ወንድሞችን ቤትህ በመጋበዝ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ልታሳይ ትችላለህ። (ሥራ 16:14, 15) አንዳንድ ጊዜ የሌሎች አለፍጽምና የፍቅርህን ጥልቀት ሊፈትን ይችላል። ይሁን እንጂ ሌሎችን ‘በፍቅር መታገስ’ ስትማር እየጎለመስህ መሆንህን ታሳያለህ።—ኤፌሶን 4:2
ሃብታችንን ንጹሕ አምልኮን ለማስፋፋት መጠቀም
በጥንት ዘመን አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ በማለት ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ቀርተዋል። ስለዚህ አምላክ እንደ ሐጌ እና ሚልክያስ የመሳሰሉ ነቢያትን በመላክ ሕዝቦቹ በዚህ ረገድ ለተግባር እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል። (ሐጌ 1:2-6፤ ሚልክያስ 3:10) ዛሬ ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች የይሖዋን አምልኮ ለመደገፍ ሃብታቸውን በደስታ ይለግሳሉ። በ1 ቆሮንቶስ 16:1, 2 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በመከተል፣ ለጉባኤውና የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ለሚያከናውኑት ሥራ ለማዋጣት በየጊዜው ‘እንደ ቀናህ መጠን በማስቀመጥ’ ምሳሌያቸውን ኮርጅ። የአምላክ ቃል “በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል” የሚል ተስፋ ሰጥቷል።—2 ቆሮንቶስ 9:6
እንደ ጊዜና ጉልበት የመሳሰሉ ነገሮች ትልቅ ሃብት መሆናቸውን አትዘንጋ። ብዙም አስፈላጊ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ በመቀነስ ‘ጊዜ ለመዋጀት’ ጥረት አድርግ። (ኤፌሶን 5:15, 16፤ ፊልጵስዩስ 1:10) በጊዜ አጠቃቀምህ ረገድ ይበልጥ የተዋጣልህ ለመሆን ራስህን አሰልጥን። እንዲህ ማድረግህ የይሖዋ አምልኮ እንዲስፋፋ በሚያደርጉ የመንግሥት አዳራሽ እደሳና ሌሎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ላይ መካፈል ትችላለህ። ያለህን ሃብት በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋልህ የጎለመስህ ክርስቲያን መሆንህን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።
ወደ ጉልምስና እደግ!
የሚያነቡና እውቀት የሚያካብቱ፣ በቅንዓት የሚሰብኩ፣ ፍጹም አቋማቸውን ከመጠበቅ ዝንፍ የማይሉ፣ ታማኝና አፍቃሪ የሆኑ እንዲሁም ለመንግሥቱ ሥራ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን በልግስና የሚሰጡ ወንዶችና ሴቶች በእርግጥም ታላቅ በረከት ናቸው። እንግዲያው ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ [“ጉልምስና፣” NW ] እንሂድ” የሚል ማሳሰቢያ መስጠቱ ምንም አያስደንቅም!—ዕብራውያን 6:1
አንተስ ጎልማሳ ክርስቲያን ነህ? ወይስ በአንዳንድ መንገዶች አሁንም በመንፈሳዊ ሕፃንነት ይታይብሃል? (ዕብራውያን 5:13) ያም ሆነ ይህ የግል ጥናት ለማድረግ፣ ለመስበክና ወንድሞችህን እንደምታፈቅር ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጡህን ማንኛውንም ዓይነት ምክርና እርማት በደስታ ተቀበል። (ምሳሌ 8:33) ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶችህን በሙሉ ተወጣ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድና በምታደርገው ጥረት አንተም “የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ” መድረስ ትችላለህ።—ኤፌሶን 4:13
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአንድ ጉባኤ ውስጥ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ካሉ ጉባኤው በመንፈሳዊ ጠንካራ ይሆናል። በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጎለመሱ ክርስቲያኖች ለሌሎች በግል አሳቢነትን በማሳየት ጉባኤው ጥሩ መንፈስ እንዲኖረው የበኩላቸውን ያደርጋሉ