የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መጋቢት 2019
ከመጋቢት 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሮም 12-14
“ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየት ሲባል ምን ማለት ነው?”
(ሮም 12:10) በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።
it-1-E 55
መውደድ
ሁሉም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የወንድማማች ፍቅር (ግሪ. ፊላደልፊያ፣ ቃል በቃል፣ “ወንድምን መውደድ”) ሊኖራቸው ይገባል። (ሮም 12:10፤ ዕብ 13:1፤ በተጨማሪም 1ጴጥ 3:8ን ተመልከት።) በመሆኑም የጉባኤው አባላት፣ ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ እርስ በርስ ሊቀራረቡ እንዲሁም ጠንካራና ልባዊ የሆነ ወዳጅነት ሊኖራቸው ይገባል። የጉባኤው አባላት አንዳቸው ለሌላው የወንድማማች ፍቅር የሚያሳዩ ቢሆንም ይህን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንዲያደርጉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—1ተሰ 4:9, 10
ፊሎስቶርጎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ከልብ መውደድ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ለሌላ ሰው ጥልቅ ፍቅር ያለው ግለሰብ የሚኖረውን ስሜት ለመግለጽ ይሠራበታል። ፊሎስቶርጎስ የሚለው ቃል ሁለት ቃላትን አጣምሮ የያዘ ነው፤ ከእነዚህ ቃላት አንዱ የሆነው ስቴርጎ የተባለው ሥርወ ቃል ብዙ ጊዜ የሚሠራበት፣ በቤተሰብ አባላት መካከል የሚታየውን ዓይነት ተፈጥሯዊ ፍቅር ለማመልከት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዲያዳብሩ ክርስቲያኖችን አበረታቷል። (ሮም 12:10) በተጨማሪም ጳውሎስ በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” (ግሪ. አስቶርዪ) እንደሚሆኑና እነዚህ ሰዎች ሞት እንደሚገባቸው ተናግሯል።—2ጢሞ 3:3፤ ሮም 1:31, 32
(ሮም 12:17-19) ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት አድርጉ። 18 ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። 19 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ “‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ” ተብሎ ስለተጻፈ ለቁጣው ዕድል ስጡ።
‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ’
3 ሮም 12:17ን አንብብ። ጳውሎስ ሰዎች በሚጠሉን ጊዜ አጸፋውን መመለስ እንደሌለብን ገልጿል። በተለይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። አንድ ክርስቲያን የማታምን የትዳር ጓደኛው ደግነት የጎደለው ነገር ስትናገረው ወይም ስታደርግበት እሱም በዚያው መንገድ ምላሽ መስጠት አይኖርበትም። ‘በክፉ ፋንታ ክፉ መመለስ’ ምንም ጥቅም አያስገኝም። እንዲህ ማድረግ ሁኔታውን ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር የለም።
“ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ”
12 ቀጥሎም ጳውሎስ ከአማኞችና ከማያምኑ ሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነት በተመለከተ “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ይህ ጥቅስ ጳውሎስ ቀደም ብሎ ከተናገረው “ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ” ከሚለው ሐሳብ ጋር የሚዛመድ ነው። ደግሞስ አንድ ሰው ክፉን በክፉ የሚመልስ ከሆነ፣ ክፉ የሆነውን ከልቡ እንደሚጸየፍ ቢናገር ውሸት አይሆንበትም? ክፉን በክፉ መመለስ “ያለ ግብዝነት” ፍቅር ከማሳየት ጋር ይቃረናል። ቀጥሎም ጳውሎስ “በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ” ብሏል። (ሮሜ 12:9, 17) ይህንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
13 ጳውሎስ ቀደም ሲል ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሐዋርያት ስላጋጠማቸው ስደት ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ለዓለም ሁሉ፣ ለመላእክትም ለሰዎችም ትርኢት ሆነናል . . . ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን።” (1 ቆሮንቶስ 4:9-13) በተመሳሳይም በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚገኙትን እውነተኛ ክርስቲያኖች ይመለከቷቸዋል። ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እየተፈጸመብንም እንኳ የምናደርጋቸውን መልካም ነገሮች የሚመለከቱ ሰዎች የምንሰብከውን መልእክት ሊቀበሉ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 2:12
(ሮም 12:20, 21) ነገር ግን “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።” 21 በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።
እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ
13 አንዳንድ ጊዜ የበደለህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት እንዲገነዘብ ማድረግ ትችል ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “‘ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው፤ ይህን በማድረግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ።’ በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።” (ሮም 12:20, 21) የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥምህ ጉዳዩን ረጋ ብለህ ለመፍታት ጥረት በማድረግ ልበ ደንዳና የሆነ ሰው እንኳ ልቡ እንዲለሰልስና መልካም ባሕርይው ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ ትችላለህ። አስተዋይ በመሆን፣ የሰዎችን ችግር እንደራስ አድርጎ በመመልከት አልፎ ተርፎም ርኅራኄ በማሳየት የበደለህ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቅ ልትረዳው ትችላለህ። ግለሰቡ የሚሰጠው ምላሽ ምንም ይሁን ምን ገርና ደግ መሆንህ ያሳየኸውን መልካም ምግባር ቆም ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል።—1 ጴጥ. 2:12፤ 3:16
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሮም 12:1) እንግዲህ ወንድሞች፣ ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በአምላክ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።
ጥሩ መዝናኛ መምረጥ የምንችለው እንዴት ነው?
5 በሕይወታችን ውስጥ የምናደርገው እያንዳንዱ ነገር ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር ግንኙነት አለው። ጳውሎስ “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]” በማለት ይህን ነጥብ አጉልቷል። (ሮም 12:1) ኢየሱስ ደግሞ “አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:30) ምንጊዜም ቢሆን ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት እንፈልጋለን። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት ሲያቀርቡ ጤናማ የሆነ እንስሳ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር። መሥዋዕቱ ጉድለት ካለው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። (ዘሌዋውያን 22:18-20) እኛም ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ተቀባይነት እንዲያጣ ሊያደርግ የሚችል ነገር አለ። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?
6 ይሖዋ “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብሎናል። (1 ጴጥሮስ 1:14-16፤ 2 ጴጥሮስ 3:11) ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበውን አምልኮ የሚቀበለው አምልኳችን ቅዱስ ወይም ንጹሕ ከሆነ ብቻ ነው። (ዘዳግም 15:21) እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ዓመፅ ወይም አጋንንታዊ ድርጊቶች ያሉ ይሖዋ የሚጠላቸው ነገሮችን የምንፈጽም ከሆነ አምልኳችን ንጹሕ እንደማይሆን የታወቀ ነው። (ሮም 6:12-14፤ 8:13) እንዲህ ያሉ ነገሮች በሚንጸባረቁበት መዝናኛ የምንካፈል ከሆነም ይሖዋ ያዝንብናል። እንደዚህ ባለው መዝናኛ መካፈል አምልኳችን ንጹሕ እንዳይሆንና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደርጋል፤ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድናም ያበላሽብናል።
(ሮም 13:1) ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።
የሮሜ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
13:1—“ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው? ሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት “በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” የሚባለው እንዲገዙ የፈቀደላቸው አምላክ በመሆኑ ነው፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አምላክ ስለ አገዛዛቸው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በርካታ ገዥዎች አስቀድሞ የተናገረው ትንቢት ይህንን ያረጋግጥልናል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሮም 13:1-14) ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው። 2 ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል፤ ይህን ዝግጅት የሚቃወሙ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ። 3 ገዢዎች የሚያስፈሩት ክፉ ለሚያደርጉ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ አይደለምና። እንግዲያው ባለሥልጣንን መፍራት የማትፈልግ ከሆነ መልካም ማድረግህን ቀጥል፤ ከእሱም ምስጋና ታገኛለህ፤ 4 ለአንተ ጥቅም ሲባል የተሾመ የአምላክ አገልጋይ ነውና። ክፉ የምታደርግ ከሆነ ግን ልትፈራ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ሰይፍ የሚታጠቀው እንዲያው በከንቱ አይደለም። ክፉ የሚሠራን በመቅጣት የሚበቀል የአምላክ አገልጋይ ነው። 5 ስለዚህ ቁጣውን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ስለ ሕሊናችሁ ስትሉም መገዛታችሁ አስፈላጊ ነው። 6 ቀረጥ የምትከፍሉትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፤ የዘወትር ተግባራቸውም ይኸው ነው። 7 ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ፣ ግብር ለሚጠይቅ ግብር ስጡ፤ መፈራት የሚፈልገውን ፍሩ፤ መከበር የሚፈልገውን አክብሩ። 8 እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሰውን የሚወድ ሁሉ ሕጉን ፈጽሟልና። 9 ምክንያቱም “አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ አትጎምጅ” የሚሉት ሕጎችና ሌሎች ትእዛዛት በሙሉ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በሚለው በዚህ ቃል ተጠቃለዋል። 10 ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው። 11 ምን ዓይነት ዘመን ላይ እንደምንገኝ ስለምታውቁም ይህን አድርጉ፤ አማኞች ከሆንበት ጊዜ ይልቅ አሁን መዳናችን ይበልጥ ስለቀረበ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን ነው። 12 ሌሊቱ እየተገባደደ ነው፤ ቀኑም ቀርቧል። ስለዚህ ከጨለማ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አውልቀን የብርሃንን የጦር ዕቃዎች እንልበስ። 13 መረን በለቀቀ ፈንጠዝያና በስካር፣ ልቅ በሆነ የፆታ ግንኙነትና ዓይን ባወጣ ምግባር እንዲሁም በጠብና በቅናት ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደምንመላለስ በጨዋነት እንመላለስ። 14 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ።
ከመጋቢት 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ሮም 15-16
“ጽናትንና መጽናኛን እንዲሰጣችሁ ወደ ይሖዋ ዞር በሉ”
(ሮም 15:4) በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና።
“ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”
11 አልዓዛር በሞተበት ወቅት ኢየሱስ በጥልቅ ሐዘን እንደተዋጠ የሚገልጸው ዘገባ፣ አጽናኝ በሆነው የአምላክ ቃል ውስጥ ከምናገኛቸው በርካታ የሚያጽናኑ ሐሳቦች መካከል አንዱ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና” ይላል፤ በመሆኑም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚያጽናኑ ሐሳቦች በብዛት መገኘታቸው የሚያስገርም አይደለም። (ሮም 15:4) አንተም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ቀጥሎ እንደቀረቡት ያሉት ጥቅሶች ሊያጽናኑህ ይችላሉ፦
▪ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።”—መዝ. 34:18, 19
▪ “በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”—መዝ. 94:19
▪ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲሁም የወደደን፣ በጸጋም አማካኝነት ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ የሰጠን አባታችን የሆነው አምላክ ልባችሁን ያጽናኑ፤ እንዲሁም ምንጊዜም . . . ያጽኗችሁ።”—2 ተሰ. 2:16, 17
(ሮም 15:5) ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው አምላክ፣ ሁላችሁም ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ያድርግ፤
“ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም”
5 ይሖዋ ብርታት እንዲሰጥህ ጠይቀው። ይሖዋ “ጽናትንና መጽናኛን [የሚሰጥ] አምላክ” ነው። (ሮም 15:5) የሚያጋጥሙንን ችግሮች ብቻ ሳይሆን ያለንበት ሁኔታ፣ ስሜታችን እንዲሁም ተፈጥሯችን የሚያስከትሉብንን ጫና ሙሉ በሙሉ ሊረዳልን የሚችለው እሱ ብቻ ነው። በመሆኑም እንድንጸና ከማንም በተሻለ ሊረዳን የሚችለው ይሖዋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “የሚፈሩትን ሰዎች ፍላጎት ያረካል፤ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል” ይላል። (መዝ. 145:19) ታዲያ አምላክ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን ስንጸልይ መልስ የሚሰጠን እንዴት ነው?
(ሮም 15:13) በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።
‘አምላክህን ይሖዋን ውደድ’
11 ይሖዋ ‘ውስጣችን በደስታና በሰላም እንዲሞላ የሚያደርግ ተስፋ ሰጥቶናል።’ (ሮም 15:13) አምላክ የሰጠን ተስፋ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም ያስችለናል። ‘እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን የሚያስመሠክሩ’ ቅቡዓን በሰማይ “የሕይወትን አክሊል” ይቀበላሉ። (ራእይ 2:10) በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ደግሞ ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ከሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ዘላለማዊ በረከት ያገኛሉ። (ሉቃስ 23:43) ታዲያ እንዲህ ያለው ተስፋ ምን እንዲሰማን ያደርጋል? ውስጣችን በደስታና በሰላም እንዲሞላ አያደርግም? ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት’ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ከልብ እንድንወደውስ አያነሳሳንም?—ያዕ. 1:17
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ሮም 15:27) አዎ፣ ይህን ያደረጉት በፈቃደኝነት ነው፤ ደግሞም የእነሱ ዕዳ ነበረባቸው፤ ምክንያቱም አሕዛብ የእነሱን መንፈሳዊ ነገር ከተካፈሉ እነሱ ደግሞ ለሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች የማዋጣት ዕዳ አለባቸው።
w89-E 12/1 24 አን. 3
“የፍቅራችሁ እውነተኝነት የሚፈተንበት”
በእርግጥም ከአሕዛብ ወገን የሆኑት ወንድሞቻቸው፣ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የደረሰባቸውን ችግር በመመልከት እነሱን ለመርዳት ሊነሳሱ ይገባል። ደግሞም ከአሕዛብ ወገን የሆኑት ክርስቲያኖች የእነሱ “ዕዳ” ነበረባቸው። ምሥራቹ ለአሕዛብ የደረሰው በኢየሩሳሌም ካሉት ክርስቲያኖች ነው። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አይሁዳውያን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሀብታቸውን ለአሕዛብ ካካፈሉ፣ አሕዛብ ደግሞ ለእነሱ ቁሳዊ እርዳታ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ግልጽ ነው።”—ሮም 15:27 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል
(ሮም 16:25) አምላክ ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ ከቆየው ቅዱስ ሚስጥር መገለጥ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እኔ በማውጀው ምሥራችና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሰበከው መልእክት መሠረት ሊያጸናችሁ ይችላል።
it-1-E 858 አን. 5
አስቀድሞ ማወቅ፣ አስቀድሞ መወሰን
መሲሑ ወይም ክርስቶስ፣ ከምድር ቤተሰቦች ሁሉ የተገኙ ጻድቃን ሰዎች የሚባረኩበት የተስፋው ዘር ነው። (ገላ 3:8, 14) ይህ “ዘር” ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በኤደን ዓመፅ ከተቀሰቀሰ በኋላ ሆኖም አቤል ከመወለዱ በፊት ነበር። (ዘፍ 3:15) ይህ የሆነው ደግሞ የመሲሐዊ “ዘር” ማንነት በግልጽ በመታወቁ የተነሳ “ቅዱሱ ሚስጥር” ከመገለጡ 4,000 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት ነው። በመሆኑም ይህ ሚስጥር “ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ [ቆይቷል]” ሊባል ይችላል።—ሮም 16:25-27፤ ኤፌ 1:8-10፤ 3:4-11
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ሮም 15:1-16) እኛ በእምነት ጠንካሮች የሆን ጠንካሮች ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት ልንሸከም ይገባል እንጂ ራሳችንን የምናስደስት መሆን የለብንም። 2 እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ እናስደስተው። 3 ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተምና፤ ይህም “ሰዎች አንተን ይነቅፉበት የነበረው ነቀፋ በእኔ ላይ ደረሰ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 4 በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና። 5 ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው አምላክ፣ ሁላችሁም ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ያድርግ፤ 6 ይኸውም በኅብረትና በአንድ ድምፅ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት እንድታከብሩ ነው። 7 ስለዚህ ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን ሁሉ አምላክ እንዲከበር እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ። 8 ክርስቶስ፣ አምላክ እውነተኛ መሆኑን ለማሳየት ሲል ለተገረዙት አገልጋይ እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ፤ በተጨማሪም አገልጋይ የሆነው፣ አምላክ ለአባቶቻቸው የገባውን ቃል ለማረጋገጥ 9 እንዲሁም ብሔራት አምላክን ስለ ምሕረቱ ያከብሩት ዘንድ ነው። ይህም “ስለዚህ በብሔራት መካከል በይፋ አወድስሃለሁ፤ ለስምህም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። 10 ደግሞም “እናንተ ብሔራት፣ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል። 11 እንደገናም “ብሔራት ሁሉ፣ ይሖዋን አወድሱት፤ ሕዝቦችም ሁሉ ያወድሱት” ይላል። 12 እንዲሁም ኢሳይያስ “የእሴይ ሥር ይገለጣል፤ ብሔራትንም የሚገዛው ይነሳል፤ ብሔራትም ተስፋቸውን በእሱ ላይ ይጥላሉ” ይላል። 13 በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ። 14 ወንድሞቼ ሆይ፣ እናንተ ራሳችሁ በጥሩነት የተሞላችሁ እንደሆናችሁ፣ የተሟላ እውቀት እንዳላችሁና አንዳችሁ ሌላውን መምከር እንደምትችሉ እኔ ራሴ ስለ እናንተ እርግጠኛ መሆን ችያለሁ። 15 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጉዳዮችን ግልጥልጥ አድርጌ የጻፍኩላችሁ ተጨማሪ ማሳሰቢያ ልሰጣችሁ ስለፈለግኩ ነው። ይህን የማደርገው ከአምላክ በተሰጠኝ ጸጋ የተነሳ ነው። 16 ይህ ጸጋ የተሰጠኝም ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው። የአምላክን ምሥራች በማወጁ ቅዱስ ሥራ የምካፈለው እነዚህ አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰ፣ ተቀባይነት ያለው መባ ሆነው ለአምላክ እንዲቀርቡ ነው።
ከመጋቢት 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ቆሮንቶስ 1-3
“ዓለማዊ ሰው ነህ ወይስ መንፈሳዊ ሰው?”
(1 ቆሮንቶስ 2:14) ዓለማዊ ሰው ግን ከአምላክ መንፈስ የሆኑትን ነገሮች አይቀበልም፤ እንዲህ ያሉት ነገሮች ለእሱ ሞኝነት ናቸውና፤ በመንፈስ የሚመረመሩ ስለሆኑም ሊረዳቸው አይችልም።
መንፈሳዊ ሰው መሆን—ምን ማለት ነው?
4 እስቲ በመጀመሪያ ዓለማዊ ሰው ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳለው እንመልከት። በዓለም ላይ ባሉ በብዙዎች ዘንድ የሚንጸባረቀው አስተሳሰብ ሥጋዊ ፍላጎትን በማርካት ላይ ያተኮረ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ መንፈስ” በማለት ገልጾታል። (ኤፌ. 2:2) ይህ መንፈስ አብዛኞቹ ሰዎች፣ የብዙኃኑን አካሄድ እንዲከተሉ ያደርጋቸዋል። እንዲህ ያሉት ሰዎች ትኩረታቸው በሙሉ ያረፈው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ነው። በመሆኑም የሚያደርጉት ለራሳቸው ትክክል መስሎ የታያቸውን ነገር ሲሆን አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ፈጽሞ ጥረት አያደርጉም። ዓለማዊ የሆነ ወይም ሥጋዊ አመለካከት ያለው ሰው ለራሱ ክብር ማግኘትና ቁሳዊ ነገሮችን ማካበት በሕይወቱ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ያሳስበዋል፤ በተጨማሪም መብቴ ነው ብሎ ለሚያስበው ነገር ትልቅ ቦታ ይሰጣል።
5 ዓለማዊ ሰው ተለይቶ የሚታወቅበት ሌላስ ምን ነገር አለ? ዓለማዊ የሆኑ ሰዎች “የሥጋ ሥራዎች” ተብለው የተገለጹትን ነገሮች ይፈጽማሉ። (ገላ. 5:19-21) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ተለይተው የሚታወቁባቸውን ሌሎች ነገሮችም ገልጿል። ከእነዚህም መካከል ክፍፍልና አለመግባባት መፍጠር፣ ወገንተኝነት፣ እርስ በርስ በፍርድ ቤት መካሰስ፣ ለራስነት ሥልጣን አክብሮት አለማሳየት እንዲሁም ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት ይገኙበታል። ሥጋዊ አመለካከት ያለው ሰው፣ ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ ሲፈተን በቀላሉ ይሸነፋል። (ምሳሌ 7:21, 22) አንዳንድ ሰዎች ዓለማዊ አስተሳሰብ ስለተቆጣጠራቸው ጨርሶ ‘መንፈሳዊ እንዳልሆኑ’ ወይም የአምላክ መንፈስ እንደሌላቸው ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ተናግሯል።—ይሁዳ 18, 19
(1 ቆሮንቶስ 2:15, 16) ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ሰው ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤ እሱ ራሱ ግን በማንም ሰው አይመረመርም። 16 “ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” ተብሏልና፤ እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።
መንፈሳዊ ሰው መሆን—ምን ማለት ነው?
6 “መንፈሳዊ ሰው” መሆን ሲባልስ ምን ማለት ነው? ከዓለማዊ ሰው በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ሰው ከአምላክ ጋር ላለው ዝምድና ትልቅ ቦታ ይሰጣል። መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ‘አምላክን ለመምሰል’ ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌ. 5:1) ይህም ሲባል የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ብሎም ነገሮችን እሱ በሚመለከትበት መንገድ ለመመልከት ይጥራሉ ማለት ነው። ለእነዚህ ሰዎች አምላክ እውን ሆኖ ይታያቸዋል። ሥጋዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች በተቃራኒ መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች፣ መላ ሕይወታቸውን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመምራት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። (መዝ. 119:33፤ 143:10) መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው በሥጋ ሥራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ “የመንፈስ ፍሬ” ለማፍራት ጥረት ያደርጋል። (ገላ. 5:22, 23) ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ፦ ነገሮችን ሁልጊዜ በአዎንታዊ መንገድ የሚመለከት ሰው አዎንታዊ አስተሳሰብ አለው ይባላል፤ በተመሳሳይም ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሰው መንፈሳዊ አስተሳሰብ አለው ሊባል ይችላል።
መንፈሳዊ ሰው መሆን—ምን ማለት ነው?
15 እያንዳንዳችን ክርስቶስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 2:16 ላይ ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ስለመያዝ ይናገራል። ሮም 15:5 ደግሞ “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ” ስለማዳበር ይገልጻል። በመሆኑም ክርስቶስን ለመምሰል፣ እሱ የሚያስብበትን መንገድ ማወቅና ማንነቱን በደንብ መረዳት ያስፈልገናል። ከዚያም የእሱን ፈለግ መከተል ይኖርብናል። ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከአምላክ ጋር ላለው ዝምድና ነው። ስለዚህ ኢየሱስን መምሰላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ያስችለናል። የኢየሱስን አስተሳሰብ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ቆሮንቶስ 1:20) የዚህ ሥርዓት ጥበበኞች የት አሉ? ጸሐፍትስ የት አሉ? ተሟጋቾችስ የት አሉ? አምላክ የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገም?
it-2-E 1193 አን. 1
ጥበብ
የዚህ ዓለም ጥበበኞች፣ አምላክ በክርስቶስ በኩል ያደረገውን ዝግጅት እንደ ሞኝነት ስለቆጠሩት አልተቀበሉትም፤ ገዢዎቹ ብቃት ያላቸውና አስተዋይ አስተዳዳሪዎች ቢሆኑም እንኳ “ታላቅ ክብር ያለውን ጌታ [ሰቅለውታል]።” (1ቆሮ 1:18፤ 2:7, 8) ሆኖም አምላክ የዓለምን ጥበበኞች ጥበብ፣ ሞኝነት አድርጎታል፤ አምላክ፣ መፈጸሙ የማይቀረውን ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል የዓለም ጥበበኞች “የአምላክ ሞኝነት” እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩትን ነገር እንዲሁም ‘ሞኝ፣ ደካማና የተናቁ’ እንደሆኑ አድርገው የሚመለከቷቸውን ሰዎች በመጠቀም የዓለምን ጠቢባን አሳፍሯቸዋል። (1ቆሮ 1:19-28) ጳውሎስ ‘የዚህ ሥርዓት ጥበብ እና የዚህ ሥርዓት ገዢዎች ጥበብ’ እንደሚጠፋ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ነግሯቸዋል፤ በመሆኑም ሐዋርያው የላከው መንፈሳዊ መልእክት ይህን ጥበብ የያዘ አይደለም። (1ቆሮ 2:6, 13) በቆላስይስ ያሉትን ክርስቲያኖችም “በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና [ፊሎሶፊያስ፣ ቃል በቃል፣ የጥበብ ፍቅር] ከንቱ ማታለያ” እንዳይማረኩ አስጠንቅቋቸዋል።—ቆላ 2:8፤ ከቁ. 20-23 ጋር አወዳድር።
(1 ቆሮንቶስ 2:3-5) ወደ እናንተም የመጣሁት ደካማ ሆኜ እንዲሁም በፍርሃትና እጅግ በመንቀጥቀጥ ነበር፤ 4 ንግግሬም ሆነ የሰበክሁላችሁ መልእክት የሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንፈስና ኃይል የሚያሳይ ነበር፤ 5 ይኸውም እምነታችሁ በአምላክ ኃይል ላይ እንጂ በሰው ጥበብ ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን ነው።
ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:3-5፦ ጳውሎስ፣ የግሪክ ፍልስፍናና ትምህርት ማዕከል በሆነችው በቆሮንቶስ በሚሰብክበት ጊዜ አድማጮቹን በሚያሳምን መንገድ መናገር መቻሉ አሳስቦት ይሆናል። ሆኖም ድካምም ሆነ ፍርሃት አምላክ የሰጠውን አገልግሎት እንዳያከናውን እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም። እኛም በተመሳሳይ አስቸጋሪ ወይም እንግዳ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከማወጅ ወደኋላ ልንል አይገባም። ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ይሖዋ እንደሚረዳን በመተማመን ወደ እሱ ዘወር ማለት እንችላለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ቆሮንቶስ 1:1-17) በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከሶስቴንስ፣ 2 በቆሮንቶስ ለሚገኘው የአምላክ ጉባኤ ይኸውም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባላችሁ አንድነት ለተቀደሳችሁ፣ እንዲሁም የእነሱም ሆነ የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ሆነው ከሚጠሩ ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ፦ 3 ከአባታችን ከአምላክና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4 በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ በሰጠው ጸጋ የተነሳ አምላኬን ሁልጊዜ ስለ እናንተ አመሰግናለሁ፤ 5 ምክንያቱም በሁሉም ነገር ይኸውም በመናገር ችሎታ ሁሉና በእውቀት ሁሉ በክርስቶስ በልጽጋችኋል፤ 6 ደግሞም ስለ ክርስቶስ የተሰጠው ምሥክርነት በእናንተ መካከል በሚገባ ሥር ሰዷል፤ 7 ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጉጉት ስትጠባበቁ ማንኛውም ስጦታ ፈጽሞ አይጎድልባችሁም። 8 በተጨማሪም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ከማንኛውም ክስ ነፃ መሆን እንድትችሉ እስከ መጨረሻው ያጸናችኋል። 9 ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ የጠራችሁ አምላክ ታማኝ ነው። 10 እንግዲህ ወንድሞች፣ ሁላችሁም ንግግራችሁ አንድ እንዲሆንና በመካከላችሁ መከፋፈል እንዳይኖር፣ ከዚህ ይልቅ በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት እንዲኖራችሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጥብቄ አሳስባችኋለሁ። 11 ወንድሞቼ ሆይ፣ የቀሎኤ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አንዳንዶች በመካከላችሁ አለመግባባት እንዳለ ነግረውኛል። 12 ይኸውም እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” “እኔ ግን የአጵሎስ ነኝ፣” “እኔ ደግሞ የኬፋ ነኝ፣” “እኔ የክርስቶስ ነኝ” ትላላችሁ። 13 ታዲያ የክርስቶስ ጉባኤ ተከፋፍሏል ማለት ነው? ጳውሎስ ለእናንተ ሲል በእንጨት ላይ ተሰቅሏል እንዴ? ወይስ የተጠመቃችሁት በጳውሎስ ስም ነው? 14 ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በስተቀር ከእናንተ አንዳችሁንም ባለማጥመቄ አምላክን አመሰግናለሁ፤ 15 በመሆኑም ከእናንተ መካከል በእኔ ስም እንደተጠመቀ ሊናገር የሚችል ማንም የለም። 16 እርግጥ የእስጢፋናስን ቤተሰብም አጥምቄአለሁ። ከእነዚህ ሌላ ግን ያጠመቅኩት ሰው መኖሩን አላስታውስም። 17 ክርስቶስ የላከኝ እንዳጠምቅ ሳይሆን ምሥራቹን እንዳውጅ ነው፤ ደግሞም የክርስቶስ የመከራ እንጨት ከንቱ እንዳይሆን ምሥራቹን የማውጀው በንግግር ጥበብ አይደለም።
ከመጋቢት 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ቆሮንቶስ 4-6
“ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካዋል”
(1 ቆሮንቶስ 5:1, 2) በመካከላችሁ የፆታ ብልግና እንደተፈጸመ ይወራል፤ እንዲህ ዓይነቱ ብልግና ደግሞ በአሕዛብ መካከል እንኳ ታይቶ አይታወቅም፤ ከአባቱ ሚስት ጋር የሚኖር ሰው አለ ተብሏል። 2 ታዲያ በዚህ ትኩራራላችሁ? ይልቁንም በዚህ ማዘንና ድርጊቱን የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ ማስወጣት አይገባችሁም?
(1 ቆሮንቶስ 5:5-8) እንዲህ ያለውን ሰው ለሰይጣን አሳልፋችሁ ልትሰጡት ይገባል፤ ይህም እሱ በጉባኤው ላይ ያሳደረው መጥፎ ተጽዕኖ እንዲወገድና የጉባኤው መንፈስ በጌታ ቀን ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ነው። 6 መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁም? 7 አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም የፋሲካችን በግ የሆነው ክርስቶስ ስለተሠዋ ከእርሾ ነፃ ናችሁ። 8 ስለዚህ በዓሉን በአሮጌ እርሾ እንዲሁም በክፋትና በኃጢአት እርሾ ሳይሆን እርሾ በሌለበት በቅንነትና በእውነት ቂጣ እናክብር።
(1 ቆሮንቶስ 5:13) በውጭ ባሉት ላይ አምላክ ይፈርዳል። “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት።”
it-2-E 230
እርሾ
ሐዋርያው ጳውሎስም በቆሮንቶስ የሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ የሥነ ምግባር ብልግና የፈጸመን ሰው እንዲያስወግድ መመሪያ በሰጠበት ወቅት እርሾን እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁም? አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም የፋሲካችን በግ የሆነው ክርስቶስ ስለተሠዋ ከእርሾ ነፃ ናችሁ” በማለት ተናግሯል። ከዚያም “እርሾ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ በግልጽ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ስለዚህ በዓሉን በአሮጌ እርሾ እንዲሁም በክፋትና በኃጢአት እርሾ ሳይሆን እርሾ በሌለበት በቅንነትና በእውነት ቂጣ እናክብር።” (1ቆሮ 5:6-8) እዚህ ላይ ጳውሎስ፣ ከፋሲካ ቀጥሎ የሚከበረውን የአይሁዳውያን የቂጣ በዓል እንደ ምሳሌ መጥቀሱ ነበር። ትንሽ እርሾ ብዙ ሊጥ ሊያቦካ እንደሚችል ሁሉ፣ የፆታ ብልግና የፈጸመው ሰው የሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ ካልተወገደም መላው ጉባኤ በአምላክ ዓይን የረከሰ ሊሆን ይችላል። እስራኤላውያን በበዓሉ ወቅት ማንኛውንም እርሾ ከቤታቸው ማስወገድ እንደሚኖርባቸው ሁሉ የቆሮንቶስ ጉባኤም ‘እርሾውን’ ማስወገድ ነበረበት።
it-2-E 869-870
ሰይጣን
‘ሥጋው እንዲጠፋ አንድን ሰው ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት’ ሲባል ምን ማለት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ የሚገኘው ጉባኤ፣ ከአባቱ ሚስት ጋር የፆታ ብልግና በሚፈጽመው የጉባኤ አባል ላይ እርምጃ እንዲወስድ ባሳሰበበት ወቅት “እንዲህ ያለውን ሰው ለሰይጣን አሳልፋችሁ ልትሰጡት ይገባል፤ ይህም . . . ሥጋው እንዲጠፋ [ነው]” ብሎ ነበር። (1ቆሮ 5:5 ግርጌ) ጳውሎስ ይህን ሲል ግለሰቡን ከጉባኤ እንዲያስወግዱትና ከእሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው መመሪያ መስጠቱ ነበር። በመሆኑም ግለሰቡን ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት ሲባል ከክርስቲያን ጉባኤ እንዲወጣና ሰይጣን አምላክና ገዢ የሆነለት ዓለም ክፍል እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው” ሁሉ ይህ ግለሰብም በጉባኤው መካከል እንደ “ሥጋ” ሆኖ መጥፎ ተጽዕኖ እያሳደረ ነበር፤ መንፈሳዊ አመለካከት ያለው ይህ ጉባኤ የፆታ ብልግና የፈጸመውን ግለሰብ በማስወገድ ‘ሥጋውን’ ከመካከሉ ያጠፋል። (1ቆሮ 5:6, 7) ጳውሎስ በተመሳሳይም ሄሜኔዎስንና እስክንድርን ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፤ ይህን ያደረገው እምነታቸውን እንዲሁም ጥሩ ሕሊናቸውን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጋቸው ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ስለጠፋ ነው።—1ጢሞ 1:20
(1 ቆሮንቶስ 5:9-11) ከሴሰኞች ጋር መግጠማችሁን እንድትተዉ በደብዳቤዬ ላይ ጽፌላችሁ ነበር፤ 10 እንዲህ ስል ግን በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም ሴሰኞች፣ ስግብግብ ሰዎች፣ ቀማኞች ወይም ጣዖት አምላኪዎች ጋር አትገናኙ ማለቴ አይደለም። እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ ጨርሶ ከዓለም መውጣት ያስፈልጋችሁ ነበር። 11 አሁን ግን የጻፍኩላችሁ፣ ወንድም ተብሎ እየተጠራ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖት አምላኪ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ቀማኛ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጋር መግጠማችሁን እንድትተዉ አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ እንዳትበሉ ነው።
lvs 241 ተጨማሪ ሐሳብ
ውገዳ
ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው፣ ንስሐ ለመግባትና የይሖዋን መሥፈርቶች ለመከተል እንቢተኛ ከሆነ የጉባኤው አባል ሆኖ መቀጠል አይችልም። ግለሰቡ ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። ከተወገደ ሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረንም፤ እንዲሁም ግለሰቡን አናነጋግረውም። (1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 2 ዮሐንስ 9-11) የውገዳ ዝግጅት የይሖዋ ስም እንዳይነቀፍና ጉባኤው እንዳይበከል ያደርጋል። (1 ቆሮንቶስ 5:6) በተጨማሪም ውገዳ፣ ግለሰቡን የሚጠቅም ተግሣጽ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ዝግጅት ግለሰቡ ወደ ይሖዋ ለመመለስ ሲል ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው ይችላል።—ሉቃስ 15:17
▸ ምዕራፍ 3 አንቀጽ 19
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(1 ቆሮንቶስ 4:9) አምላክ እኛን ሐዋርያቱን ሞት እንደተፈረደባቸው ሰዎች መጨረሻ ላይ ወደ መድረክ እንድንወጣ ያደረገን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ለዓለም፣ ለመላእክትና ለሰዎች ትርዒት ሆነናል።
መላእክት—“የሕዝብ አገልጋዮች የሆኑ መናፍስት”
16 ፈተና እየደረሰባቸው ያሉ ክርስቲያኖች ‘በመላእክት ፊት እንደ ትርዒት ይታያሉ።’ (1 ቆሮ. 4:9) መላእክት በታማኝነት የምናከናውናቸውን ነገሮች ሲመለከቱ በጣም የሚደሰቱ ከመሆኑም በላይ አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባበት ጊዜም ሐሴት ያደርጋሉ። (ሉቃስ 15:10) ክርስቲያን ሴቶች የሚያሳዩትን አምላካዊ ባሕርይ መላእክት በትኩረት ይከታተላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በመላእክት ምክንያት ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ” ይላል። (1 ቆሮ. 11:3, 10) አዎን፣ ክርስቲያን ሴቶችም ሆኑ በምድር ላይ ያሉ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ቲኦክራሲያዊ ሥርዓትንና የራስነትን ሥልጣን ሲያከብሩ መላእክት ይደሰታሉ። እንዲህ ያለው ታዛዥነት በሰማይ ለሚገኙት ለእነዚህ የአምላክ ልጆች ጥሩ ማሳሰቢያ ሆኖ ያገለግላቸዋል።
(1 ቆሮንቶስ 6:3) በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁም? ታዲያ በአሁኑ ሕይወት በሚያጋጥሙ ጉዳዮች ላይ ለምን አትፈርዱም?
it-2-E 211
ሕግ
ለመላእክት የተሰጠ ሕግ። ከሰው ልጆች በላይ የሆኑት መላእክት ለአምላክ ትእዛዛትና ሕግጋት ይገዛሉ። (ዕብ 1:7, 14፤ መዝ 104:4) ይሖዋ፣ ጠላቱ ለሆነው ለሰይጣን እንኳ መመሪያ ሰጥቶታል፤ እንዲሁም ገደብ አስቀምጦለታል። (ኢዮብ 1:12፤ 2:6) የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ “ይሖዋ ይገሥጽህ” ማለቱ የሁሉ የበላይ የሆነው ዳኛ ይሖዋ መሆኑን አምኖ እንደተቀበለና የእሱን ሥልጣን እንደሚያከብር ያሳያል። (ይሁዳ 9፤ ከዘካ 3:2 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ አምላክ ሁሉም መላእክት፣ ክብር ለተጎናጸፈው ለኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን እንዲገዙ አድርጓል። (ዕብ 1:6፤ 1ጴጥ 3:22፤ ማቴ 13:41፤ 25:31፤ ፊልጵ 2:9-11) በመሆኑም ኢየሱስ ለአንድ መልአክ ትእዛዝ በመስጠት ወደ ዮሐንስ ልኮታል። (ራእይ 1:1) ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 6:3 ላይ የክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች በመላእክት ላይ ለመፍረድ እንደተሾሙ ተናግሯል፤ ይህን ሲል በክፉ መናፍስት ላይ በመፍረድ ረገድ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው መግለጹ መሆን አለበት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(1 ቆሮንቶስ 6:1-14) ከእናንተ መካከል አንዱ ከሌላው ጋር የሚከራከርበት ጉዳይ ቢኖረው፣ ጉዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፋንታ በዓመፀኛ ሰዎች ፊት ለማቅረብ ፍርድ ቤት ለመሄድ እንዴት ይደፍራል? 2 ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁም? ታዲያ እናንተ በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ በጣም ተራ የሆኑ ጉዳዮችን ለመዳኘት አትበቁም? 3 በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁም? ታዲያ በአሁኑ ሕይወት በሚያጋጥሙ ጉዳዮች ላይ ለምን አትፈርዱም? 4 ደግሞስ በአሁኑ ሕይወት የሚያጋጥሙ ዳኝነት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ ጉባኤው የሚንቃቸው ሰዎች እንዲዳኙት ታደርጋላችሁ? 5 ይህን የምለው ኀፍረት እንዲሰማችሁ ብዬ ነው። ወንድሞቹን መዳኘት የሚችል አንድ እንኳ ጥበበኛ ሰው በመካከላችሁ የለም? 6 አንድ ወንድም ሌላውን ወንድም ፍርድ ቤት ይወስዳል፤ ያውም የማያምኑ ሰዎች ፊት! 7 እንግዲህ እርስ በርስ ተካስሳችሁ ፍርድ ቤት መሄዳችሁ ለእናንተ ትልቅ ሽንፈት ነው። ከዚህ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም? ደግሞስ እናንተ ራሳችሁ ብትታለሉ አይሻልም? 8 እናንተ ግን ትበድላላችሁ እንዲሁም ታታልላላችሁ፤ ያውም የገዛ ወንድሞቻችሁን! 9 ወይስ ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም? አትታለሉ፤ ሴሰኞችም ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶማውያን 10 ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም። 11 አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችኋል። 12 ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም። ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ለምንም ነገር ተገዢ መሆን አልሻም። 13 ምግብ ለሆድ፣ ሆድም ለምግብ ነው፤ አምላክ ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። አካል ለጌታ ነው እንጂ ለፆታ ብልግና አይደለም፤ ጌታ ደግሞ ለአካል ነው። 14 ይሁን እንጂ አምላክ በኃይሉ አማካኝነት ጌታን እንዳስነሳው እኛንም ከሞት ያስነሳናል።