የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ክርስቲያናዊ አንድነት ሲባል በሁሉም ነገር አንድ መሆን ማለት ነውን?
በዛሬው ጊዜ በሃይማኖቶች መካከል እርስ በርስ መከፋፈል በስፋት ይታያል። በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች እንኳ በመሠረተ ትምህርትና በሥነ ምግባር ረገድ እርስ በርስ የሚጋጩ አስተሳሰቦች ይኖሯቸዋል። አንዲት ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “አምላክን በሚመለከት ፍጹም ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ሁለት ሰዎች ማግኘት ይከብዳል። ዛሬ ዛሬ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ አለው።”
ከዚህ በተለየ መልኩ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን ‘ሁሉም አንድ ንግግር እንዲናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብ የተባበሩ እንዲሆኑ’ አሳስቧቸው ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:10) በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ይህ የጳውሎስ ማሳሰቢያ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል እንደሆነ ይሰማቸዋል። ‘ሰዎች በተፈጥሯቸው የተለያዩ ናቸው። ሁሉም ክርስቲያኖች በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት አንድ መሆን አለባቸው ማለት ምክንያታዊ አይደለም’ በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ፍጹም ተመሳሳይ ይሁኑ ማለቱ ነበርን? እያንዳንዱ ክርስቲያን የራሱን ምርጫ እንዲከተል መጽሐፍ ቅዱስ ነጻነት ይሰጣል?
አንድነት እንጂ በሁሉም ነገር አንድ መሆን አይደለም
ጳውሎስ በሌላ ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ‘በማመዛዘን ችሎታቸው’ ተጠቅመው አምላክን እንዲያገለግሉ አሳስቧቸዋል። (ሮሜ 12:1 NW ) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላትን አእምሮ እንደሌላቸው ሮቦቶች እንዲሆኑ መጠየቁ አልነበረም። ታዲያ ‘በአንድ ልብና በአንድ አሳብ የተባበሩ’ እንዲሆኑ የመከራቸው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ይህን ምክር የሰጠው በቆሮንቶስ የሚገኘው ጉባኤ ከባድ ችግር ላይ ወድቆ ስለነበረ ነው። አንዳንዶች አጵሎስን እንደ መሪያቸው አድርገው ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ጳውሎስን አሊያም ጴጥሮስን ከፍ አድርገው ይመለከቱ ወይም ኢየሱስን ብቻ ይቀበሉ ስለነበር በመካከላቸው መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ መለያየት የጉባኤውን ሰላም ያናጋ ስለነበር እንደ ቀላል የሚታይ አልነበረም።
ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን እንደመከረው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት” እንዲጠብቁ ፈልጎ ነበር። (ኤፌሶን 4:3) ወንድሞች ቡድን ለይተው እርስ በርስ ከመከፋፈል ይልቅ በአንድነት ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲከተሉ እያበረታታቸው ነበር። እንዲህ ካደረጉ ደስታ የሚያስገኝ የዓላማ አንድነት ይኖራቸዋል። (ዮሐንስ 17:22) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰጣቸው ምክር አስተሳሰባቸውን አስተካክለው አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ረድቷቸዋል። ይህ ሲባል ግን በሁሉም ነገር አንድ ሆነዋል ማለት አይደለም።—2 ቆሮንቶስ 13:9, 11
መሠረተ ትምህርትን በተመለከተም አንድነት አስፈላጊ ነው። የኢየሱስን ፈለግ የሚከተሉ ሰዎች ‘አንድ አምላክና አባት’ እንዳለ ሁሉ ‘አንድ እምነት’ ብቻ ሊኖር እንደሚገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 4:1-6) በመሆኑም ክርስቲያኖች እምነታቸው አምላክ ስለራሱና ስለ ዓላማው በቃሉ ውስጥ ካሰፈረው እውነት ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ስለ አምላክና እርሱ ከሰው ልጆች ምን እንደሚፈልግ ያላቸው እምነት አንድ አድርጓቸዋል። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከሰፈሩት የሥነ ምግባር መስፈርቶች ጋር ተስማምተው ይኖራሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ በሃይማኖታዊ እምነትም ሆነ በሥነ ምግባር አንድ ይሆናሉ።
የሐሳብ ልዩነቶችን መፍታት
እንዲህ ሲባል ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን በሁሉም የሕይወት ዘርፎች እንዴት ማሰብና ምን ማድረግ እንዳለበት ይነገረዋል ማለት አይደለም። አብዛኞቹ ጉዳዮች ለግል ምርጫ የተተዉ ናቸው። አንድ ምሳሌ ተመልከት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ይኖሩ ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ ከጣዖት አምልኮ ቤተ መቅደስ የመጣ ሊሆን የሚችል ሥጋን ስለ መብላት ጥርጣሬዎች ነበሯቸው። አንዳንዶች ይህን ሥጋ መብላት በሐሰት አምልኮ ከመካፈል ተለይቶ እንደማይታይ አጥብቀው የሚያምኑ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ሥጋው ስለመጣበት ቦታ መመራመር እንደማይገባ ይሰማቸው ነበር። ጳውሎስ ይህን ከባድ ጉዳይ በሚመለከት ክርስቲያኖች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልጽ ደምብ አላወጣም። ከዚህ ይልቅ የየራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ እንደሚችሉ ገልጾላቸዋል።a—1 ቆሮንቶስ 8:4-13
በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች ሥራን፣ ሕክምናን፣ መዝናኛንና ሌሎች የግል ምርጫ የሚጠይቁ ጉዳዮችን በሚመለከት አንዳቸው ከሌላው የተለየ ውሳኔ ያደርጉ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ የውሳኔ ልዩነት አንዳንዶችን ሊረብሻቸው ይችላል። እንዲሁም የአመለካከት ልዩነቶች በጉባኤው ውስጥ ክርክርና መከፋፈል ያመጣ ይሆናል የሚል ስጋት ሊያሳድርባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ የሙዚቃ ደራሲዎች ዜማ ለመፍጠር የሚጠቀሙባቸው ኖታዎች በቁጥር ውስን ቢሆኑም በእነዚህ ኖታዎች ተጠቅሞ ለቁጥር የሚያታክቱ ጣፋጭ ዜማዎችን ማቀናበር ይቻላል። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እስካልጣሱ ድረስ የተለያዩ የግል ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስችል የተወሰነ ነጻነት አላቸው።
የግለሰቦችን ምርጫ እያከበርንም ክርስቲያናዊ አንድነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ የሚረዳን ፍቅር ነው። ለአምላክ ያለን ፍቅር ለሕግጋቱ በፈቃደኝነት እንድንገዛ ይገፋፋናል። (1 ዮሐንስ 5:3) ለሰዎች ያለን ፍቅር ደግሞ የግል ጉዳዮችን በሚመለከት ሌሎች እንደ ሕሊናቸው ውሳኔ ለማድረግ ያላቸውን መብት እንድናከብር ያደርገናል። (ሮሜ 14:3, 4፤ ገላትያ 5:13) በዚህ ረገድ ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ከመሠረተ ትምህርት ጋር በተያያዘ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአስተዳደር አካል ለሚወስናቸው ውሳኔዎች ሁሉ ይገዛ ነበር። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ሥራ 15:1, 2) ለግል ውሳኔ የተተዉ ጉዳዮችን በሚመለከት ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን ሌሎች ሕሊናቸው ፈቅዶላቸው የሚያደርጉትን ውሳኔ እንዲያከብር አበረታቷል።—1 ቆሮንቶስ 10:25-33
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ማንም ሕሊናው ከፈቀደለት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጋጩ ውሳኔዎችን በማድረጉ ሊወገዝ አይገባም። (ያዕቆብ 4:12) በሌላ በኩል ግን ታማኝ ክርስቲያኖች መብቴ ነው በሚል የሌሎችን ሕሊና የሚረብሽ ወይም የጉባኤውን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ከማድረግ ይቆጠባሉ። እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ በግልጽ የተወገዘን ነገር የማድረግ ነጻነት እንዳላቸው ሆኖ ሊሰማቸው አይገባም። (ሮሜ 15:1፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 19) ለአምላክ ያለን ፍቅር ሕሊናችንን በእርሱ አስተሳሰብ እንድንቀርጸው ሊያነሳሳን ይገባል። ይህ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን አንድነት ጠብቀን ለመኖር ያስችለናል።—ዕብራውያን 5:14
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች ከመሆናቸው በፊት ጣዖትን ያመልኩ የነበሩት ሥጋውን መብላትና በአምልኮው መካፈል ምንም ልዩነት እንደሌለው ተሰምቷቸው ይሆናል። ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ደግሞ በመንፈሳዊ ደካማ የሆኑ ክርስቲያኖች ሁኔታውን በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ሊሰናከሉ ይችላሉ።