የጌታ እራት ለአንተ ትርጉም የሚኖረው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ የጌታን እራት በዓል የጀመረውና ያስተዋወቀው በሰብዓዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ ነው። ይህ የሆነው ሐሙስ ዕለት ማታ መጋቢት 31 ቀን ሲሆን ኢየሱስ የሞተው ዐርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ ሚያዝያ 1 ቀን ነው። በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት አንድ ቀን የሚቆየው ከምሽት እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ስለሆነ የጌታ እራት የተከበረውና ኢየሱስ የሞተው ኒሳን 14 ቀን 33 እዘአ ነው።
ኢየሱስ ይህንን እራት ያቋቋመው ለምን ነበር? እርሱ የተጠቀመባቸው ቂጣና ወይን ጠጁ ትርጉማቸው ምንድን ነው? ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚገባቸው እነማን ናቸው? ይህ እራት መቼ መቼ መከበር ይኖርበታል? ለአንተስ ትርጉም ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?
ለምን ተቋቋመ?
ኢየሱስ ስለጌታ እራት ሲናገር ለሐዋርያቱ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 11:24) እንዲያውም የጌታ እራት ብዙ ጊዜ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ተብሎ ይጠራል።
ኢየሱስ የሞተው ፍጹም አቋሙን ጠብቆ ሲሆን የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፎ በመቆም ሰይጣን የሰው ልጆች አምላክን የሚያገለግሉት ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ሲሉ ነው በማለት ያስነሳው ክስ ፍጹም ውሸት መሆኑን አስመስክሮአል። (ኢዮብ 2:1–5) የኢየሱስ ሞት የይሖዋን ልብ አስደስቶአል። — ምሳሌ 27:11
በተጨማሪም ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ በመሞቱ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ’ ችሎአል። (ማቴዎስ 20:28) የመጀመሪያው ሰው በአምላክ ላይ ኃጢአት በመሥራቱ ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱንና ይህም ሕይወት ሊያስገኝለት ይችል የነበረውን ተስፋ በሙሉ አጥቶአል። ይሁን እንጂ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላላም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:16) አዎ፣ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፣ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” — ሮሜ 6:23
“ከጌታ የተቀበልሁትን”
የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ስለ ክርስቶስ ሞት የመታሰቢያ በዓል ማብራሪያ ይሰጡናል። “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንስቶ አመሰገነ፣ ቆርሶም:- እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ [ማለት አዓት] ነው። ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንስቶ ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።” — 1 ቆሮንቶስ 11:23–26
ጳውሎስ ኒሳን 14 ቀን 33 እዘአ በተከበረው በዓል ላይ ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር በቦታው ስላልነበረ ይህን መረጃ የተቀበለው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት “ከጌታ” ተገልጦለት መሆን ይኖርበታል። ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ያቋቋመው የአስቆረቱ ይሁዳ በሮማውያን እጅ ተሰቅሎ እንዲገደል ላደረጉት ለአይሁዳውያን የሃይማኖት ጠላቶቹ አሳልፎ በሰጠበት ሌሊት ነው። ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ ሊካፈሉ የሚገባቸው ሁሉ ከቂጣው የሚበሉትና ከወይን ጠጁ የሚጠጡት ኢየሱስን ለማስታወስ ነው።
በዓሉ የሚከበረው በስንት በስንት ጊዜ ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” ሲል የተናገራቸው ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እስኪሞቱ ድረስ ከመታሰቢያው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን ጠጅ ደጋግመው ይካፈላሉ ማለት ነው። ከሞቱ በኋላ ግን ሰማያዊ ሕይወት አግኝተው ይነሳሉ። ከቂጣውና ከወይን ጠጁ በተካፈሉ ቁጥር ይሖዋ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ባዘጋጀው ቤዛ ላይ እምነት ያላቸው መሆኑን በአምላክና በዓለም ፊት ይናገራሉ ወይም ያውጃሉ። ይህን የሚያደርጉት እስከመቼ ድረስ ነው? ጳውሎስ “ጌታ እስኪመጣ ድረስ” በማለት ተናግሮአል። የዚህ በዓል አከባበር ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹን ከሙታን አስነስቶ በሰማይ እስከሚቀበልበት እስከ “መገኘቱ” ዘመን ድረስ ነው ማለቱ እንደነበረ ግልጽ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:14–17) ይህም ክርስቶስ ለአስራ አንዱ ታማኝ አገልጋዮቹ ከተናገረው ከሚከተለው ቃል ጋር ይስማማል። “እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” — ዮሐንስ 14:3
የክርስቶስ ሞት በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ መከበር ይኖርበታልን? ኢየሱስ የጌታን እራት አከባበር ያቋቋመውና የተገደለው እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት የወጡበት ቀን ይታሰብበት በነበረው የማለፍ ቀን ነው። እንዲያውም ኢየሱስ ለክርስቲያኖች የተሰዋ በግ ስለሆነ “ፋሲካችን ክርስቶስ” ተብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 5:7) የፋሲካ ወይም የማለፍ በዓል ይከበር የነበረው በየዓመቱ አንድ ጊዜ ኒሳን 14 ቀን ላይ ነበር። (ዘጸአት 12:6, 14፤ ዘሌዋውያን 23:5) ይህም የኢየሱስ ሞት በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ ሳይሆን እንደ ፋሲካ ወይም እንደ ማለፍ በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ መከበር እንደሚኖርበት ያመለክታል።
ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩ ሰዎች ለብዙ መቶ ዓመታት የኢየሱስን ሞት ያስቡ የነበረው በዓመት አንድ ጊዜ ነበር። ያከብሩ የነበረውም ኒሳን 14 ቀን ስለነበረ ኳርቶዴሲማንስ ወይም 14ተኛ ቀን አክባሪዎች ተብለው ይጠሩ ነበር። ታሪክ ፀሐፊው ጄ ኤል ፎን ሞስሃይም ስለእነዚህ ሰዎች ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል:- “የታናሽቱ እስያ ክርስቲያኖች ይህን የጌታ እራትና የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ የሆነውን ቅዱስ እራት የሚያከብሩት አይሁዳውያን የፋሲካ ወይም የማለፍ በጋቸውን በሚበሉት ጊዜ ማለትም በመጀመሪያው ወር [ኒሳን]፣ በወሩ አሥራ አራተኛ ቀን ምሽት ነበር። . . . ክርስቶስ የተወዉ ምሳሌ የሕግን ያህል የአስገዳጅነት ኃይል እንዳለው ያምኑ ነበር።”
የምሳሌዎቹ ትርጉም
ጳውሎስ ኢየሱስ “እንጀራን አንስቶ አመሰገነ፣ ቆርሶም እንካችሁ ብሉ” እንዳለ ተናግሮአል። ይህ እርሾ ያልገባበት ከውኃና ከዱቄት ብቻ የተዘጋጀ ስስ የሆነ ደረቅ ቂጣ ካልተቆረሰ ሊበላ አይችልም ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሾ የኃጢአት ወይም የምግባር መበላሸት ምሳሌ ነው። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጉባዔ ውስጥ የሚገኝን አንድ ዘማዊ ሰው እንዲያስወግዱ ሲያሳስብ “ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 5:6–8) ጥቂት ቦክቶ የኮመጠጠ ሊጥ ብዙውን ሊጥ ሊያቦካ እንደሚችል ሁሉ የዚህም ኃጢአተኛ ሰው መጥፎ ተጽዕኖ ካልተወገደ መላው ጉባዔ በአምላክ ዓይን የረከሰ ሆኖ ሊታይ ይችላል። እስራኤላውያን ከማለፍ በዓል በኋላ በሚያከብሩት የቂጣ በዓል ማንኛውንም እርሾ ከቤታቸው ማስወገድ እንደሚኖርባቸው ሁሉ እነርሱም እርሾውን ከመካከላቸው ማስወገድ ነበረባቸው።
ኢየሱስ የመታሰቢያውን ያልቦካ ቂጣ አስመልክቶ ሲናገር “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 11:24) ቂጣው ፍጹም የሆነውን የክርስቶስ ሥጋ ያመለክታል። ጳውሎስ ስለዚህ ሥጋ ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል። “ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም። ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ። በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም በዚያን ጊዜ እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደተጻፈ አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ይላል። በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል።” (ዕብራውያን 10:5–10) የኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ከማንኛውም ኃጢአት የነጻ በመሆኑ ለሰው ልጆች ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ ሊቀርብ ችሎአል። — ዕብራውያን 7:26
ኢየሱስ ባልተበረዘውና ባልተከለሰው ቀይ ወይን ላይ ከጸለየ በኋላ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” ብሎአል። (1 ቆሮንቶስ 11:25) ሌላ ትርጉም ደግሞ “ይህ ጽዋ በደሜ ዋጋ የሚጸድቀው አዲስ ቃልኪዳን ማለት ነው” ይላል። (ሞፋት ) በአምላክና በእስራኤል ብሔር መካከል የተቋቋመው የሕግ ቃል ኪዳን መሥዋዕት ሆነው በቀረቡ ኮርማዎችና ፍየሎች ደም እንደጸና ሁሉ ኢየሱስ ሲሞት በፈሰሰው ደሙ አዲሱን ቃል ኪዳን የጸና አድርጎታል። ይህ ቃል ኪዳን መጠቀሱ ከመታሰቢያው ምሳሌዎች መካፈል የሚገባቸው እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ይረዳናል።
መካፈል የሚገባቸው እነማን ናቸው?
ከመታሰቢያው ምሳሌያዊ ቂጣና የወይን ጠጅ መካፈል የሚችሉት በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የገቡት የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ናቸው። ይህ ቃል ኪዳን በአምላክና በመንፈሳዊ እስራኤል መካከል የተደረገ ነው። (ኤርምያስ 31:31–34፤ ገላትያ 6:16) ይሁን እንጂ አዲሱ ቃል ኪዳን ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ በረከት የሚያመጣ ነው። አንተም እነዚህን በረከቶች ልታገኝ ትችላለህ።
ከመታሰቢያው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን ጠጅ የሚካፈሉ ሁሉ ኢየሱስ በሰጠው የመንግሥት ቃልኪዳን ውስጥ የገቡ መሆን ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ ይህን እራት ባቋቋመበት ጊዜ ከጎኑ ለቆሙት ታማኝ ሐዋርያቱ “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃልኪዳን እንደገባ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ቃልኪዳን እገባለሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 22:29 አዓት) አምላክ ከንጉሥ ዳዊት ጋር የገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን በሰማያዊው መንግሥት ለዘላለም የሚገዛውን የኢየሱስን መምጣት ያመለክት ነበር። ከኢየሱስ ጋር በአገዛዝ የሚካፈሉት 144,000 መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊቱ ጽዮን እንደቆሙ ተገልጾአል። እነዚህ መንፈሳዊ እስራኤሎች ከሙታን ከተነሱ በኋላ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ይገዛሉ። (2 ሳሙኤል 7:11–16፤ ራእይ 7:4፤ 14:1–4፤ 20:6) በጌታ እራት ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና የወይን ጠጅ መካፈል የሚችሉት በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የገቡትና ከኢየሱስ ጋር በግል የመንግሥት ቃልኪዳን የተጋቡት ሰዎች ብቻ ናቸው።
ቅቡዓን የአምላክ ልጆች እንደሆኑና ከክርስቶስ ጋር ወራሾች እንዲሆኑ ከመንፈሣቸው ጋር ሆኖ የአምላክ መንፈስ ይመሰክርላቸዋል። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፎአል:- “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን። አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8:16, 17) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል በቅቡዓኑ ውስጥ ለሰማያዊ ሕይወት የተመደቡ ስለመሆናቸው እርግጠኛ የመሆን መንፈስ ይፈጥርባቸዋል። ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ሰማያዊ ሕይወት የሚናገሩት ሁሉ የተጻፉት ለእነርሱ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ። ምድራዊ ነገሮችን በሙሉ፣ ሰብዓዊ ሕይወታቸውን ጭምር መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። በምድራዊው ገነት ውስጥ መኖር የሚያስደስት ቢሆንም እነርሱ ያላቸው ተስፋ ይህ አይደለም። (ሉቃስ 23:43) ይህ ዓይነቱ የተረጋገጠ፣ የማይለዋወጥና በሐሰት ሃይማኖት አስተሳሰብ ላይ ያልተመሠረተ ተስፋ በመታሰቢያው ላይ ከሚቀርበው ቂጣና የወይን ጠጅ የመካፈል መብት ያሰጣቸዋል።
አንድ ሰው ሰማያዊ ጥሪ ሳይኖረው ሰማያዊ ንጉሥና ካህን ለመሆን እንደተጠራ አድርጎ ራሱን ቢያቀርብ ይሖዋ አይደሰትበትም። (ሮሜ 9:16፤ ራእይ 22:5) ቆሬ በትዕቢት ተነሳስቶ የክህነት ሹመት ስለፈለገ አምላክ ቀስፎታል። (ዘጸአት 28:1፤ ዘኁልቅ 16:4–11, 31–35) ስለዚህ አንድ ሰው በስሜት ግንፋሎት ወይም ቀድሞ በነበረው የተሳሳተ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ተነሳስቶ በስህተት ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን ተካፍሎ ከነበረ ምን ማድረግ ይኖርበታል? መካፈሉን አቁሞ አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግለት በትህትና መጸለይ ይኖርበታል። — መዝሙር 19:13
አንተንስ እንዴት ይነካል?
አንድ ሰው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ተጠቃሚ ለመሆንና በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን ጠጅ መካፈል አይፈለግበትም። ለምሳሌ ያህል እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ይሥሐቅ፣ ርብቃ፣ ቦዔዝ፣ ሩትና ዳዊት የመሰሉት ፈሪሐ አምላክ የነበራቸው ሰዎች ወደፊት ከቂጣውና ከወይኑ እንደሚካፈሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያመለክተው ነገር የለም። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎችም ሆኑ በዚህች ምድር ላይ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች በአምላክና በክርስቶስ እንዲሁም ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ባዘጋጀው ዝግጅት ማመን ይኖርባቸዋል። (ዮሐንስ 3:36፤ 14:1) የክርስቶስ ሞት ዓመታዊ በዓል ይህን ታላቅ መሥዋዕት የሚያስታውስ ይሆናል።
የኢየሱስ መሥዋዕት አስፈላጊነት በሚከተለው የሐዋርያው ዮሐንስ ቃል ተገልጾአል። “ልጆቼ ሆይ፣ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን። እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው። ለኃጢአታችን ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ኢየሱስ ‘የኃጢአታቸው ማስተስሪያ’ እንደሆነ ሊናገሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ኃጢአት ማስተሰሪያ መሥዋዕት ስለሆነ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ቅርብ በሆነችው ገነታዊ ምድር የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ይችላሉ።
በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ብትገኝ አእምሮን ከሚያመራምረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ጥቅም ለማግኘት ትችላለህ። ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያህል ታላላቅ ነገሮችን እንዳደረጉልን የሚያስገነዝብ ማሳሰቢያ ታገኛለህ። ለአምላክና ለክርስቶስ እንዲሁም ለኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የጠለቀ አክብሮት ካላቸው ሰዎች ጋር መሰብሰብ ብዙ መንፈሳዊ በረከቶችን ያስገኛል። አጋጣሚው ይገባናል በማንለው የአምላክ ደግነት ተቀባይ የመሆንና የዘላለም ሕይወት የማግኘት ፍላጎትህን ሊያጠናክርልህ ይችላል። የጌታ እራት ለአንተ ትልቅ ትርጉም ሊኖረው ስለሚችል ሚያዝያ 6 ቀን 1993 ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተሰብስበህ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት እንድታስብ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን።