-
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
7. የአምላክ መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የላቁ ሕጎች አሉት
መንግሥታት ለዜጎቻቸው ጥቅምና ጥበቃ ያስገኛሉ ብለው የሚያስቧቸውን ሕጎች ያወጣሉ። የአምላክ መንግሥትም ተገዢዎቹ ሊያከብሯቸው የሚገቡ ሕጎች አሉት። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ሁሉም ሰው አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች ቢከተል ዓለማችን ምን መልክ የሚኖራት ይመስልሃል?a
ይሖዋ የመንግሥቱ ተገዢዎች እነዚህን ሕጎች እንዲያከብሩ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
እነዚህን ሕጎች የማይታዘዙ ሰዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?—ቁጥር 11ን ተመልከት።
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 41
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ምን ይላል?
ብዙ ሰዎች ስለ ፆታ ግንኙነት ማውራት ይከብዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ሆኖም ጨዋነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ይናገራል። የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ እኛን የሚጠቅም መረጃ ይዟል። ይህ መሆኑ አያስገርምም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን ይሖዋ ያጻፈው መጽሐፍ ነው። ይሖዋ ደግሞ ለእኛ የተሻለውን ነገር ያውቃል። እሱን ለማስደሰትና ለዘላለም በደስታ ለመኖር ምን ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል።
1. ይሖዋ ለፆታ ግንኙነት ምን አመለካከት አለው?
የፆታ ግንኙነት ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው። ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የፆታ ግንኙነት በመፈጸም ደስታ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ይህ ስጦታ ባለትዳሮች ልጆች እንዲወልዱ ብቻ ሳይሆን አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ተፈጥሯዊ በሆነና እርካታ በሚያስገኝ መንገድ እንዲገልጹ ያስችላቸዋል። የአምላክ ቃል “ከወጣትነት ሚስትህ . . . ጋር ደስ ይበልህ” የሚለው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 5:18, 19) ይሖዋ ትዳር የመሠረቱ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ እንዲሆኑ ይፈልጋል፤ በመሆኑም ባለትዳሮች ምንዝር ከመፈጸም ሊርቁ ይገባል።—ዕብራውያን 13:4ን አንብብ።
2. የፆታ ብልግና ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሴሰኞች [የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች] የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የፆታ ብልግናን ለመግለጽ ፖርኒያ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ተጠቅመዋል። ይህ ቃል (1) ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነትa (2) ግብረ ሰዶምን እና (3) ከእንስሳት ጋር የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት ያካትታል። ‘ከፆታ ብልግና መራቃችን’ ይሖዋን የሚያስደስት ከመሆኑም ሌላ እኛንም ይጠቅመናል።—1 ተሰሎንቄ 4:3
ጠለቅ ያለ ጥናት
ከፆታ ብልግና መራቅ የምትችለው እንዴት እንደሆነና የሥነ ምግባር ንጽሕናህን መጠበቅህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ እንመለከታለን።
3. ከፆታ ብልግና ሽሽ
ዮሴፍ የተባለ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሥነ ምግባር ንጽሕናውን ለመጠበቅ ብዙ ትግል አድርጓል። ዘፍጥረት 39:1-12ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ዮሴፍ የሸሸው ለምንድን ነው?—ቁጥር 9ን ተመልከት።
ዮሴፍ ያደረገው ነገር ትክክል ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የዮሴፍን ምሳሌ በመከተል ከፆታ ብልግና መሸሽ የሚችሉት እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ይሖዋ ሁላችንም ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ይፈልጋል። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:18ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የፆታ ብልግና ወደመፈጸም ሊመሩ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
ከፆታ ብልግና መሸሽ የምትችለው እንዴት ነው?
4. ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ትችላለህ
የፆታ ብልግና እንድንፈጽም የሚደረግብንን ጫና መቋቋም ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ የታየው ወንድም፣ የሚያስባቸውና የሚያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች ለባለቤቱ ያለውን ታማኝነት እንዲያጓድል ሊያደርጉት እንደሚችሉ ሲገነዘብ ምን አደረገ?
ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ አስተሳሰባቸው ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ለማድረግ መታገል ሊያስፈልጋቸው ይችላል። የብልግና ሐሳቦችን እንዳታውጠነጥን ምን ይረዳሃል? ፊልጵስዩስ 4:8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ስለ ምን ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል?
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈላችን ኃጢአት ለመፈጸም ስንፈተን የሚረዳን እንዴት ነው?
5. ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተላችን ይጠቅመናል
ይሖዋ ለእኛ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነና እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን ገልጾልናል። ምሳሌ 7:7-27ን አንብቡ ወይም ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ወጣት ራሱን ፈተና ውስጥ ያስገባው እንዴት ነው?—ምሳሌ 7:8, 9ን ተመልከት።
ምሳሌ 7:23, 26 ላይ እንደተገለጸው የፆታ ብልግና መፈጸም አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ከየትኞቹ ችግሮች ያድነናል?
የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቃችን ለዘላለም በደስታ ለመኖር የሚያስችለን እንዴት ነው?
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን አስመልክቶ የሚናገረው ሐሳብ ፍቅር የጎደለው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሆኖም አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ሁሉም ሰው ለዘላለም በደስታ እንዲኖር ይፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር አለብን። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በዚህ ጥቅስ መሠረት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ግብረ ሰዶም ብቻ ነው?
አምላክን ለማስደሰት ሁላችንም የተለያዩ ለውጦች ማድረግ ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ ነው? መዝሙር 19:8, 11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ያወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምክንያታዊ ወይም ተገቢ ይመስሉሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ማንም ሰው ከፈለገው ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይችላል። ዋናው ነገር መዋደዳቸው ነው።”
አንተ ምን ትላለህ?
ማጠቃለያ
የፆታ ግንኙነት ትዳር በመሠረቱ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ሊፈጸም የሚገባ የይሖዋ ስጦታ ነው።
ክለሳ
የፆታ ብልግና ምን ነገሮችን ያካትታል?
ከፆታ ብልግና እንድንርቅ ምን ይረዳናል?
ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መከተላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
ምርምር አድርግ
አምላክ አብረው መኖር የሚፈልጉ ወንድና ሴት ትዳር እንዲመሠርቱ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
“መጽሐፍ ቅዱስ ሳይጋቡ አብሮ መኖርን በተመለከተ ምን ይላል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም የሚያስተምረው ትምህርት ጥላቻን የሚያስፋፋ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
አምላክ ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ጋር በተያያዘ ያወጣው ሕግ ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው?
“የያዙኝ በአክብሮት ነበር” የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ግብረ ሰዶማዊ የነበረ አንድ ሰው አምላክን ለማስደሰት ሲል አኗኗሩን እንዲቀይር ያነሳሳው ምን እንደሆነ ተመልከት።
a በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የፆታ ግንኙነት በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ግንኙነትን፣ የሌላን ግለሰብ የፆታ ብልት ማሻሸትንና እንዲህ የመሳሰሉ ሌሎች ድርጊቶችን ያካትታል።
-
-
ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 43
ክርስቲያኖች ለአልኮል መጠጥ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ለአልኮል መጠጥ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች አልፎ አልፎ ከጓደኞቻቸው ጋር መጠጣት ደስ ይላቸዋል። ሌሎች ደግሞ የአልኮል መጠጥ ጨርሶ አይጠጡም። እስኪሰክሩ ድረስ የሚጠጡ ሰዎችም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን ይላል?
1. የአልኮል መጠጦችን መጠጣት ስህተት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን አይከለክልም። እንዲያውም አምላክ ከሰጠን በርካታ ስጦታዎች መካከል “የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ” እንደሚገኝበት ይገልጻል። (መዝሙር 104:14, 15) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች የአልኮል መጠጥ ይጠጡ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 5:23
2. መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ምን ምክር ይሰጣል?
ይሖዋ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። (ገላትያ 5:21) ቃሉ “ብዙ የወይን ጠጅ እንደሚጠጡ . . . ሰዎች አትሁን” ይላል። (ምሳሌ 23:20) በመሆኑም ለብቻችን በምንጠጣበት ጊዜም እንኳ አስተሳሰባችን እስኪዛባ፣ ንግግራችንንና ድርጊታችንን መቆጣጠር እስኪያቅተን ወይም ጤናችን እስከሚጎዳ ድረስ መጠጣት አይኖርብንም። የምንጠጣውን መጠን መቆጣጠር የሚከብደን ከሆነ ከናካቴው መጠጥ ለማቆም መወሰን ሊያስፈልገን ይችላል።
3. ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ የሌሎችን ምርጫ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት ወይም ካለመጠጣት ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ሊያደርግ ይገባል። አንድ ሰው በልክ ለመጠጣት ከወሰነ ልንተቸው አይገባም፤ መጠጣት የማይፈልግንም ሰው እንዲጠጣ መጫን አይኖርብንም። (ሮም 14:10) የእኛ መጠጣት ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ከሆነ አለመጠጣትን እንመርጣለን። (ሮም 14:21ን አንብብ።) ‘የራሳችንን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም እንፈልጋለን።’—1 ቆሮንቶስ 10:23, 24ን አንብብ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ወይም ላለመጠጣት እንድትወስን አሊያም በምትጠጣው መጠን ላይ ገደብ እንድታበጅ የሚረዱህ እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ከመጠጥ ጋር የተያያዘ ችግር ካለብህ ምን ማድረግ እንደምትችል እንመረምራለን።
4. የአልኮል መጠጥ መጠጣት ይኖርብህ እንደሆነና እንዳልሆነ ወስን
ኢየሱስ የአልኮል መጠጥ ስለመጠጣት ምን አመለካከት ነበረው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ኢየሱስ የፈጸመውን የመጀመሪያ ተአምር እንመልከት። ዮሐንስ 2:1-11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይህ ተአምር ኢየሱስ ለአልኮል መጠጥም ሆነ የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ስላለው አመለካከት ምን ይጠቁመናል?
ኢየሱስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ስላላወገዘ ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ ለሚጠጡ ሰዎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ መጠጣት ቢችሉም እንዲህ ማድረጋቸው ጥሩ የማይሆንበት ጊዜ አለ። ምሳሌ 22:3ን አንብቡ፤ ከዚያም የሚከተሉት ሁኔታዎች ሰዎች ላለመጠጣት እንዲወስኑ ሊያደርጓቸው የሚችሉት ለምን እንደሆነ ተወያዩ፦
የሚያሽከረክሩ ወይም ማሽን ላይ የሚሠሩ ከሆነ
ነፍሰ ጡር ከሆኑ
ሐኪም የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ ከነገራቸው
የሚጠጡትን መጠን መቆጣጠር የሚከብዳቸው ከሆነ
የአገሪቱ ሕግ የአልኮል መጠጥ እንዲጠጡ የማይፈቅድላቸው ከሆነ
የሚጠጣውን መጠን መቆጣጠር ስለሚከብደው ጨርሶ ላለመጠጣት ከወሰነ ሰው ጋር አብረው ሲሆኑ
በሠርግ ድግስ ላይ ወይም በሌሎች ግብዣዎች ላይ የአልኮል መጠጥ ማቅረብ ይኖርብህ ይሆን? ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦችን ለማግኘት ቪዲዮውን ተመልከቱ።
ሮም 13:13ን እና 1 ቆሮንቶስ 10:31, 32ን አንብቡ። እያንዳንዱን ጥቅስ ካነበባችሁ በኋላ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባር ላይ ማዋልህ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳህ እንዴት ነው?
5. ምን ያህል እንደምትጠጣ ወስን
የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ከወሰንክ ይህን ማስታወስ ይኖርብሃል፦ ይሖዋ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ባያወግዝም ከልክ በላይ መጠጣትን ያወግዛል። ለምን? ሆሴዕ 4:11, 18ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ከልክ በላይ መጠጣት ምን ጉዳት ያስከትላል?
ከልክ በላይ እንዳንጠጣ ምን ይረዳናል? ልካችንን ወይም ገደባችንን ማወቅ ይኖርብናል። ምሳሌ 11:2ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በምትጠጣው መጠን ላይ ገደብ ማስቀመጥህ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?
6. ከልክ በላይ የመጠጣት ልማድን ማሸነፍ
ከልክ በላይ ይጠጣ የነበረ አንድ ሰው ይህን ልማድ እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ ዲሚትሪ የአልኮል መጠጥ ሲጠጣ ምን ዓይነት ጠባይ ያሳይ ነበር?
የመጠጥ ሱሱን ወዲያው ማሸነፍ ችሏል?
በመጨረሻም ከአልኮል መጠጥ ሱስ መላቀቅ የቻለው እንዴት ነው?
አንደኛ ቆሮንቶስ 6:10, 11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ስካር እንደ ቀላል የሚታይ ጉዳይ ነው?
ከልክ በላይ የአልኮል መጠጥ ይጠጣ የነበረ ሰው ሊለወጥ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?
ማቴዎስ 5:30ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
‘እጅን መቁረጥ’ የሚለው አገላለጽ ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ መሥዋዕትነት መክፈልን ያመለክታል። የመጠጥ ሱስን ለማሸነፍ እየታገልክ ከሆነ ምን ማድረግህ ይረዳሃል?a
አንደኛ ቆሮንቶስ 15:33ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ብዙ ከሚጠጡ ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆንህ ምን ጉዳት ይኖረዋል?
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
የአልኮል መጠጥ ይሖዋ ደስታ እንድናገኝ ሲል ከሰጠን ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው፤ ሆኖም ይሖዋ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል።
ክለሳ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን ይላል?
ከልክ በላይ መጠጣት ምን ጉዳት ያስከትላል?
ሌሎች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ምርጫ እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
ምርምር አድርግ
ወጣቶች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
ከልክ በላይ የመጠጣት ችግርን ለማስወገድ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?
ክርስቲያኖች መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ ጽዋቸውን ሊያነሱ ይገባል?
‘ቀዳዳ በርሜል ነበርኩ’ የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ከልክ በላይ የመጠጣት ችግር የነበረበት አንድ ሰው ይህን ልማዱን ያሸነፈው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።
a የአልኮል መጠጥ ሱስ ያለባቸው ሰዎች ከሱሳቸው ለመላቀቅ የባለሙያ እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ብዙ ሐኪሞች የመጠጥ ችግር የነበረባቸው ሰዎች ጨርሶ ባይጠጡ የተሻለ እንደሆነ ይመክራሉ።
-
-
ከባድ ኃጢአት ብትፈጽም ምን ማድረግ ይኖርብሃል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ይሖዋን ከልብ የምትወድና እሱን ላለማሳዘን የቻልከውን ያህል ጥረት የምታደርግ ቢሆንም አልፎ አልፎ ስህተት መሥራትህ አይቀርም። ይሁንና አንዳንድ ስህተቶች ከሌሎቹ የበለጠ ክብደት አላቸው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ከባድ ኃጢአት ከፈጸምክ ይሖዋ ለአንተ ያለው ፍቅር እንደማይለወጥ እንዲሁም ይቅር ሊልህና ሊረዳህ ፈቃደኛ እንደሆነ አስታውስ።
1. ይሖዋ ይቅር እንዲለን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ከባድ ኃጢአት እንደፈጸሙ ሲገነዘቡ ከልብ እንደሚያዝኑ የታወቀ ነው። ይሁንና ይሖዋ ለሕዝቡ የገባውን ቃል ማስታወሳቸው ያጽናናቸዋል። ይሖዋ “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል” ብሏል። (ኢሳይያስ 1:18) ከልባችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር ይለናል። ንስሐ እንደገባን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በፈጸምነው ኃጢአት ከልብ ማዘን፣ መጥፎ ድርጊታችንን ማቆምና ይሖዋ ይቅር እንዲለን መለመን ይኖርብናል። ከዚያም ኃጢአት ወደመፈጸም የመራንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ወይም ልማድ ለማስወገድ እንዲሁም ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው።—ኢሳይያስ 55:6, 7ን አንብብ።
2. ኃጢአት ስንሠራ ይሖዋ በሽማግሌዎች አማካኝነት የሚረዳን እንዴት ነው?
ይሖዋ ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንድንጠራ’ ነግሮናል። (ያዕቆብ 5:14, 15ን አንብብ።) እነዚህ የተሾሙ ወንዶች ይሖዋንና ሕዝቦቹን ይወዳሉ። በተጨማሪም ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማደስ እንዲችሉ ለመርዳት በቂ ሥልጠና አግኝተዋል።—ገላትያ 6:1
ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ሽማግሌዎች የሚረዱን እንዴት ነው? ሁለት ወይም ሦስት ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው እርማት ይሰጡናል። በተጨማሪም ዳግመኛ ኃጢአት ከመፈጸም እንድንርቅ የሚረዳ ጠቃሚ ሐሳብ ወይም ማበረታቻ ያካፍሉናል። ሽማግሌዎች ጉባኤውን ከጎጂ ተጽዕኖ ለመጠበቅ ሲሉ፣ ከባድ ኃጢአት ፈጽመው ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ከጉባኤው እንዲወገዱ ያደርጋሉ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ይሖዋ ስለሚሰጠን እርዳታ ያለህን ግንዛቤና አድናቆት እንድታሳድግ የሚረዳ ሐሳብ እንመለከታለን።
3. ኃጢአታችንን መናዘዛችን ፈውስ እንድናገኝ ይረዳናል
ማንኛውንም ኃጢአት ስንፈጽም ይሖዋን ስለምናሳዝን ኃጢአታችንን ለእሱ መናዘዛችን ተገቢ ነው። መዝሙር 32:1-5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የፈጸምነውን ኃጢአት ከመሸፋፈን ይልቅ ለይሖዋ መናዘዛችን የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?
ኃጢአታችንን ለይሖዋ ከመናዘዝ በተጨማሪ የሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቃችን እረፍት ያስገኝልናል። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ ሽማግሌዎች ካነንን ወደ ይሖዋ እንዲመለስ የረዱት እንዴት ነው?
የፈጸምነውን ኃጢአት ለሽማግሌዎች በግልጽና በሐቀኝነት መናገራችን አስፈላጊ ነው፤ ዋነኛ ዓላማቸው እኛን መርዳት ነው። ያዕቆብ 5:16ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ሐቀኛ መሆናችን ሽማግሌዎች እኛን መርዳት ቀላል እንዲሆንላቸው የሚያደርገው እንዴት ነው?
4. ይሖዋ ለኃጢአተኞች ምሕረት ያደርጋል
ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ፈቃደኛ ካልሆነ ከጉባኤው ይወገዳል። እንዲህ ካለው ሰው ጋር ጊዜ አናሳልፍም። አንደኛ ቆሮንቶስ 5:6, 11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው ሁሉ ንስሐ ከማይገባ ኃጢአተኛ ጋር ጊዜ ማሳለፍም በጉባኤ ውስጥ ባሉት ላይ ምን ጉዳት ይኖረዋል?
ይሖዋ ፍጹም ላልሆኑ ኃጢአተኞች ምሕረት ያሳያል፤ ሽማግሌዎችም ከጉባኤ የተወገዱትን ለመርዳት ጥረት በማድረግ የእሱን ምሳሌ ይከተላሉ። ብዙዎች የተሰጣቸው ተግሣጽ ቢያሳዝናቸውም ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ ስለረዳቸው ወደ ጉባኤው ተመልሰዋል።—መዝሙር 141:5
• ይሖዋ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችን የሚይዝበት መንገድ ፍትሐዊ፣ መሐሪና አፍቃሪ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
5. ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር ይለናል
ኢየሱስ፣ ይሖዋ ንስሐ ለገባ ኃጢአተኛ ያለውን አመለካከት የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። ሉቃስ 15:1-7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይህ ጥቅስ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምርሃል?
ሕዝቅኤል 33:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ንስሐ መግባት የትኛውን አስፈላጊ እርምጃ መውሰድን ይጨምራል?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የፈጸምኩትን ኃጢአት ለሽማግሌዎች ብናገር ከጉባኤ እወገዳለሁ ብዬ እፈራለሁ።”
እንዲህ ለሚሰማው ሰው ምን ልትለው ትችላለህ?
ማጠቃለያ
ከባድ ኃጢአት ስንፈጽም ከልባችን ካዘንን እና መጥፎ ድርጊታችንን ለመተው ቁርጥ ውሳኔ ካደረግን ይሖዋ ይቅር ይለናል።
ክለሳ
ኃጢአታችንን ለይሖዋ መናዘዛችን ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲል ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን የሽማግሌዎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
ምርምር አድርግ
አንድ ሰው በኢሳይያስ 1:18 ላይ የተገለጸውን የይሖዋን ምሕረት በሕይወቱ ማየት የቻለው እንዴት ነው?
ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸሙትን የሚረዱት እንዴት ነው?
ሽማግሌዎች ንስሐ ላልገቡ ኃጢአተኞች ፍቅርና ምሕረት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
“ወደ ይሖዋ መመለስ ነበረብኝ” የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ ከእውነት ርቆ የነበረ አንድ ሰው ይሖዋ ወደ ራሱ መልሶ እንደሳበው የተሰማው ለምን እንደሆነ ተመልከት።
-