ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ላገባ ስል ወላጆቼ ቢቃወሙኝስ?
ላኬሻና የወንድ ጓደኛዋ ለመጋባት ቢያስቡም እናቷ በውሳኔዋ አልተስማማችም። “በዚህ ዓመት 19 ዓመት ይሆነኛል” ትላለች ላኬሻ “እማዬ ግን 21 ዓመት እስኪሞላሽ ድረስ መቆየት አለብሽ አለችኝ።”
ለማግባት ካቀዳችሁ ወላጆቻችሁ በሐሳባችሁ እንዲደሰቱ መፈለጋችሁ የማይቀር ነው። ወላጆቻችሁ በምርጫችሁ አለመስማማታቸው ሊያሳዝናችሁ ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ አለባችሁ? ፍላጎታቸውን ከቁብ ሳትቆጥሩ እቅዳችሁን ለማሳካት ጥረት ማድረጋችሁን ትገፉበታላችሁ?a
ይህ በተለይ ለአካለ መጠን ከደረሳችሁና ወላጆቻችሁ ባይስማሙም እንኳ ሕጉ ለማግባት የሚፈቅድላችሁ ከሆነ ፈታኝ ሊሆንባችሁ ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ወላጆቹን ማክበር የሚኖርበት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ የሚጠቁም የዕድሜ ገደብ አይጠቅስም። (ምሳሌ 1:8) ደግሞም የወላጆቻችሁን ስሜት ችላ ካላችሁ ከእነሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ለዘለቄታው ሊበላሽ ይችላል። ከዚህም በላይ ወላጆቻችሁ የማግባት እቅዳችሁን የተቃወሙባቸው ተገቢ ምክንያቶች ሊኖሯቸው ይችል ይሆናል።
አንድ ሰው ለትዳር አልደረሰም የሚባለው ዕድሜው ምን ያህል ሲሆን ነው?
ለምሳሌ ያህል ወላጆቻችሁ ለትዳር ገና አልደረሳችሁም እያሉ ነውን? እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ማግባት የሚችለው ከዚህ ዕድሜ በላይ ሲሆን ነው አይልም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከማግባቱ በፊት “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” ማለትም የጾታ ፍላጎቶች የሚያይሉባቸው የጉርምስና ዓመታት ማለፍ እንዳለባቸው ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW) ለምን? ምክንያቱም በዚህ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የተሳካ የትዳር ሕይወት ለመምራት የግድ አስፈላጊ የሆኑትን የስሜት ብስለት፣ ራስን የመግዛትና ሌሎች መንፈሳዊ ባሕርያት ገና አላጎለበቱም።—ከ1 ቆሮንቶስ 13:11 እና ከገላትያ 5:22, 23 ጋር አወዳድር።
የሃያ ዓመቱ ዳል ሊያገባ መሆኑን ሲነግራቸው ወላጆቹ በመቃወማቸው በጣም አዘነ። “ገና ልጅ እንደሆንኩና ተሞክሮ እንደሌለኝ ነገሩኝ” ሲል ይገልጻል። “እኔና እጮኛዬ ዝግጁ እንደሆንና ከተጋባን በኋላ ሌሎች ነገሮችን ልንማር እንደምንችል ተሰማኝ። ወላጆቼ ግን በስሜት ብቻ እየተመራሁ እንዳልሆንኩ ማረጋገጥ ፈለጉ። ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቁኝ። በየቀኑ የሚያጋጥሙኝን ውሳኔዎች ለማድረግ፣ ገንዘብ በተገቢው መንገድ ለመያዝና ቤተሰቤ የሚያስፈልጉትን ሥጋዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ነገሮች ለማቅረብ እችላለሁን? ወላጅ ለመሆን ዝግጁ ነኝን? ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ተምሬአለሁን? የትዳር ጓደኛዬን ፍላጎቶች በትክክል ተረድቻለሁን? ለሌላ ዐዋቂ ሰው እንክብካቤ ማድረግ ከመጀመሬ በፊት ራሴን በተሻለ መንገድ ማወቅ እንዳለብኝ ተሰምቷቸው ነበር።
“የመቆየት ፍላጎት ያልነበረን ቢሆንም ብስለት ለማግኘት ጊዜ እንዲኖረን ስንል የመጋባት እቅዳችንን ለሌላ ጊዜ አስተላለፍነው። በመጨረሻ ስንጋባ የተሻለ መሠረትና ለትዳራችን ስኬታማነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የተሻሉ ባሕሪያትና ችሎታዎች ነበሩን።”
ጉዳዩ ሃይማኖታዊ ልዩነቶችን የሚመለከት በሚሆንበት ጊዜ
ቴሪ ሃይማኖታዊ እምነቷን ከማይጋራ ሰው ጋር ፍቅር ስለያዛት እየተቀጣጠረች በድብቅ አብራው ጊዜ ታሳልፍ ነበር። ቴሪ ለማግባት ያላትን እቅድ ስትገልጽ እናቷ ስለ ተቃወመቻት ምን እንደምታደርግ ግራ ገባት። “እናቴ ስለ እኔ እንዲህ እንዲሰማት አልፈልግም። አሁንም ቢሆን በመካከላችን የእናትና የልጅ ግንኙነት እንዲኖር እፈልጋለሁ” ስትል በምሬት ተናግራለች።
ይሁን እንጂ ለግንኙነታቸው እንቅፋት የሆነው ማን ነው? የቴሪ እናት ለልጅዋ ክፉ አስባ ወይም ምክንያታዊ ሳትሆን ቀርታ ይሆን? አይደለም፣ “በጌታ ይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለማክበር ፈልጋ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:39) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ሲል ያዛል። (2 ቆሮንቶስ 6:14, 15) ለምን?
በመጀመሪያ ደረጃ የተሳካና ደስታ የሞላበት ትዳር ለመመሥረት ተጋቢዎቹ አንድ ዓይነት እምነት የሚከተሉ መሆናቸው በጣም ወሳኝ ነው። የተለያየ ሃይማኖት ባላቸው ባለ ትዳሮች መካከል በብዛት የሚከሰተው ጭንቀትና ውጥረት ብዙውን ጊዜ ለፍቺ እንደሚያደርስ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ሆኖም ከዚህ ይበልጥ የሚያሳስበው ሃይማኖታዊ አቋማችሁን እንድታላሉ ወይም ከነአካቴው ሃይማኖታችሁን እንድትተዉ ግፊት ሊደረግባችሁ መቻሉ ነው። አንድ የማያምን የትዳር ጓደኛ በአምልኮ ጣልቃ ባይገባም እንኳ ከእሱ ወይም ከእሷ ጋር ጠንካራ እምነቶችሽን(ህን) መጋራት ባለመቻልሽ(ህ) የሚሰማሽን(ህን) ጥልቅ ሐዘን ተሸክመሽ(ህ) ለመኖር ትገደጃለሽ(ዳለህ)። ታዲያ ይህ በትዳር ውስጥ ደስታ ለማግኘት የሚያስችል ሁኔታ ይመስላችኋል?
ከዚህ የተነሣ በቴሪ ፊት አስቸጋሪ ውሳኔ ተጋርጦ ነበር። “ይሖዋ አምላክን እወደዋለሁ። ሆኖም የወንድ ጓደኛዬን ላጣ አልፈልግም” ትላለች ቴሪ። በአጭር አነጋገር ከሁለት አንዱን መምረጥ የግድ ነው። የአምላክን የአቋም ደረጃዎች አቃሎ እንደገና ደግሞ የእሱን ሞገስና በረከት ማግኘት አይቻልም።
ሆኖም ወላጆቻችሁ የእምነት ጓደኛችሁ የሆነን አንድ ክርስቲያን እንዳታገቡ ይፈልጉ ይሆናል። የእናንተው ዓይነት እምነት ካለው ሰው ጋርም በማይመች አካሄድ የምትጠመዱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላልን? አዎን፣ አለ። ግለሰቡ እንደ እናንተ ዓይነት መንፈሳዊ ግቦች ወይም አምልኮታዊ ፍቅር ከሌለው ከዚህ ሰው ጋር መጋባታችሁ በማይመች አካሄድ ተጠምዳችኋል ሊያስብል ይችላል። ወላጆቻችሁ የተቃወሙት በዚህ ምክንያት ከሆነ ወይም ያ(ያቺ) ግለሰብ ባለበት(ችበት) ጉባኤ ወንድሞች ዘንድ ‘ጥሩ ስም’ ከሌለው(ላት) ወላጆቻችሁ ያንን ሰው ማግባታችሁ ቢያሳስባቸው ተገቢ ነው።—ሥራ 16:2 የ1980 ትርጉም
የዘር ወይም የባህል ልዩነትን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል?
የሊን ወላጆች የማግባት ሐሳቧን የተቃወሙበት ምክንያት ደግሞ ሌላ ነበር። ሊን ልታገባ ያሰበችው የእሷ ዘር ያልሆነን ሰው ነበር። ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘አምላክ እንደማያዳላ’ እና ‘የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ እንደ ፈጠረ’ ይነግረናል። (ሥራ 10:34, 35፤ 17:26) ሰዎች ሁሉ የመጡት ከአንድ ዘር ነው። በአምላክ ፊትም እኩል ናቸው።
በማንኛውም ትዳር ውስጥ ‘በሥጋ ላይ መከራ’ የሚያመጡ ነገሮች ቢኖሩም እንኳ የተለያየ ዘር ያላቸው ባልና ሚስቶች በሚጋቡበት ጊዜ ተጨማሪ ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ለምን? ምክንያቱም ዛሬ ባለው በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ዘርን በተመለከተ የአምላክ ዓይነት አመለካከት የላቸውም። በአንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች መጋባታቸው በጣም እየተለመደ የመጣ ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች ግን ይህ ዓይነቱ ጋብቻ በጣም ይጠላል። ስለሆነም ወላጆቻችሁ እነዚህን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም ዝግጁ እንዳልሆናችሁ ሊሰማቸው ይችላል።
“ወላጆቼ ሁኔታው በጣም ከባድ እንደሚሆንብኝ ተሰማቸው” ትላለች ሊን። ሊን ጉዳዩን በጥበብ በመያዝና የወላጆቿን ስሜት በማክበር ለማግባት ከመጣደፍ ተቆጠበች። ወላጆቿ የሊንን ብስለት ሲያስተውሉና ያፈቀረችውን ግለሰብ ይበልጥ እያወቁት ሲሄዱ ቀስ በቀስ ይህ ትዳር የሚያስከትላቸውን ተጽዕኖዎች መቋቋም እንደምትችል ማመን ጀመሩ። ሊን “አብረን በደስታ መኖር እንደምንችል ስለ ተሰማቸው በሐሳባችን ተስማሙ” ብላለች።
አንዳንድ ጊዜ ግን ችግር የሚፈጥረው የዘር ልዩነት ሳይሆን የባህል ልዩነት ነው። ወላጆቻችሁ ከእናንተ ፈጽሞ የተለየ ዓይነት አኗኗር፣ የሕይወት ግቦች እንዲሁም የምግብ፣ የሙዚቃና የመዝናኛ ምርጫ ካለው ሰው ጋር መኖር እያደር ያስቸግራችኋል ብለው ያስቡ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የተለየ ዘር ወይም ባህል ያለውን ሰው ማግባት ከባድ ፈተናዎች ሊያስከትል ይችላል። ታዲያ እነዚህን ፈተናዎች ለመወጣት ዝግጁ ናችሁን?
የወላጆች ተቃውሞ አግባብነት የሌለው በሚመስልበት ጊዜ
ይሁን እንጂ ወላጆቻችሁ መቃወማቸው ፈጽሞ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ቢሰማችሁስ? ፌዝ የተባለች አንዲት ወጣት ስለ እናቷ እንዲህ ትላለች:- “እማማ ብዙ ጊዜ አግብታ ፈታለች። የምታገቢውን ሰው ማንነት በደንብ ልታውቂው የምትችዪው ብዙ ነገር ውስጥ ከገባሽ በኋላ ነው ትላለች። በትዳር ፈጽሞ ልደሰት እንደማልችል ይሰማታል።” ትዳራቸው ያልተሳካላቸው ወላጆች ብዙውን ጊዜ የልጆቻቸውንም ትዳር በዚያው መልኩ ይመለከቱታል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወላጆች የልጆቻቸውን የማግባት ሐሳብ የሚቃወሙት ልጆቻቸው ከቁጥጥራቸው እንዳይወጡ ስለሚፈልጉና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ዝንባሌዎች ስላላቸው ሊሆን ይችላል። ወላጆቻችሁ የምታቀርቧቸውን አሳማኝ ምክንያቶች ለማዳመጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የይሖዋ ምሥክሮች የሚያጋጥሟቸውን የቤተሰብ ችግሮች ለመፍታት የጉባኤ ሽማግሌዎችን ማማከር ይችላሉ። እነዚህ ሽማግሌዎች ለማንም አድልዎ ሳያደርጉ የቤተሰቡ አባላት ጉዳዩን በተረጋጋ፣ ሰላማዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወያዩበት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ያዕቆብ 3:18
ሰላምን መሻት
እርግጥ የወላጆቻችሁን ተቃውሞ ሊያስነሡ የሚችሉ ሌሎች በርካታ ሁኔታዎችም ይኖራሉ። ለምሳሌ የገንዘብ ጉዳይ ወይም ልታገቡ ያሰባችሁት ሰው ባሕርይ ሊያሳስባቸው ይችላል። በተጨማሪም ልታገቡት ያሰባችሁት ሰው ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ልቅ የሆነ ሕይወት ሲመራ የቆየ ከነበረ በዚህ ኤድስና ሌሎች የአባለ ዘር በሽታዎች በተስፋፉበት ዘመን ወላጆቻችሁ ስለ ጤንነታችሁ ማሰባቸው ተገቢ ነው።b
በወላጆቻችሁ ሥር እስከ ኖራችሁ ድረስ በእናንተ ላይ ያላቸውን ሥልጣን የመቀበል ግዴታ አለባችሁ። (ቆላስይስ 3:20) ይሁን እንጂ ራሳችሁን ችላችሁ የምትኖሩና የራሳችሁን ውሳኔ ለማድረግ በምትችሉበት ዕድሜ ላይ የምትገኙ ብትሆኑም እንኳ የወላጆቻችሁን ሐሳብ አቅልላችሁ ለመመልከት አትቻኮሉ። ወላጆቻችሁ የሚነግሯችሁን ለማዳመጥ ፈቃደኞች ሁኑ። (ምሳሌ 23:22) ማግባት የሚያስከትላቸውን ውጤቶች በጥንቃቄ አመዛዝኑ።—ከሉቃስ 14:28 ጋር አወዳድር።
ይህን ካደረጋችሁ በኋላ ማግባት አለብኝ ብላችሁ ትወስኑ ይሆናል። ይህ ውሳኔ የሚያስከትልባችሁን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የምትሸከሙት እናንተው ራሳችሁ እንደሆናችሁ ግልጽ ነው። (ገላትያ 6:5) የተቻላችሁን ያህል የወላጆቻችሁን አመለካከት ግምት ውስጥ ለማስገባት ከጣራችሁ ምርጫቸው ባይሆንም እንኳ የእናንተን ውሳኔ ለመደገፍ ይገፋፉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ተቃውሟቸውን ከገፉበት በእነሱ ላለመማረር ወይም ላለመናደድ ሞክሩ። ወላጆቻችሁ እንደሚወዷችሁና የወደፊቱ ሕይወታችሁ አስደሳች እንዲሆን እንደሚፈልጉ መዘንጋት የለባችሁም። ከእነሱ ጋር ቅያሜ ላለመፍጠር ጥረት ማድረጋችሁን ቀጥሉ። ትዳራችሁ ሰምሮ ሲያዩ አመለካከታቸው ይለወጥ ይሆናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆቻችሁ የሚሉትን ሁሉ በቁም ነገር ካሰባችሁበት እንዲሁም ራሳችሁንም ሆነ ልታገቡት በጣም የጓጓችሁለትን ሰው በሐቀኝነት ከመረመራችሁ በኋላ ወላጆቼ ትክክል ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ብትደርሱ አይግረማችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ላይ የቀረበው ሐሳብ የራስን የትዳር ጓደኛ መምረጥ በተለመደባቸው አገሮች ለሚኖሩ ወጣቶች ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
b ሚያዝያ—ሰኔ 1995 ንቁ! ላይ “ኤድስ የያዛቸውን ሰዎች መርዳት” በሚል ርዕስ የወጣውን ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆቻችሁ ለትዳር እንዳልደረሳችሁ ይሰማቸው ይሆናል