ምንጊዜም በይሖዋ ታመኑ!
“ሰዎች ሆይ፣ ሁልጊዜ በእሱ ታመኑ።”—መዝ. 62:8
1-3. ጳውሎስ ይሖዋ እንደሚረዳው እንዲተማመን ያደረገው ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
በሮም የክርስትና እምነት ተከታይ መሆን አደገኛ የነበረበት ወቅት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች በ64 ዓ.ም. ከተማዋን በእሳት እንዳቃጠሉ እንዲሁም የሰውን ዘር እንደሚጠሉ የሚገልጽ ወሬ ስለተነዛ ሕዝቡ ለእነሱ ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው። በዚያ ጊዜ ብትኖር ኖሮ ክርስቲያን በመሆንህ በማንኛውም ቀን ልትታሰር ብሎም ከፍተኛ ሥቃይ ሊደርስብህ ይችላል። ምናልባትም ከመንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ አንዳንዶቹን አራዊት ቦጫጭቀዋቸዋል፤ አሊያም ማታ ላይ እንደ መብራት እንዲያገለግሉ እንጨት ላይ ተቸንክረው በእሳት ተቃጥለዋል።
2 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረው እንዲህ ያለ ያልተረጋጋ ሁኔታ በሰፈነበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ታዲያ ሌሎች ክርስቲያኖች ሊረዱት ይመጡ ይሆን? ጳውሎስ መጀመሪያ ላይ ይህ ጉዳይ ሳያሳስበው አልቀረም፤ ምክንያቱም ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “የመጀመሪያ መከላከያዬን ባቀረብኩበት ወቅት ሁሉም ትተውኝ ሄዱ እንጂ ከእኔ ጎን የቆመ ማንም አልነበረም፤ አምላክ ይህን አይቁጠርባቸው” ብሏል። ያም ሆኖ ጳውሎስ ምንም እርዳታ አላገኘም ማለት አይደለም። “ጌታ አጠገቤ ቆሞ ኃይል ሰጠኝ” በማለት ጽፏል። በእርግጥም፣ ጌታ ኢየሱስ ለጳውሎስ የሚያስፈልገውን ኃይል ሰጥቶታል። ለመሆኑ ይህ መለኮታዊ እርዳታ ምን ያህል ጠቅሞታል? ጳውሎስ ‘ከአንበሳ አፍ ዳንኩ’ በማለት ውጤቱን ነግሮናል።—2 ጢሞ. 4:16, 17a
3 ጳውሎስ ይህን ሁኔታ ማስታወሱ፣ በዚያ ወቅት ያጋጠሙትንም ሆነ ወደፊት የሚደርሱበትን ፈተናዎች በጽናት እንዲወጣ ይሖዋ ሊያጠናክረው የሚችል መሆኑን እንዲተማመን በማድረግ አበረታትቶት መሆን አለበት። እንዲያውም “ጌታ ከክፉ ሥራ ሁሉ ይታደገኛል” በማለት አክሎ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 4:18) በእርግጥም ጳውሎስ፣ ከሰዎች የሚገኘው እርዳታ ውስን በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይሖዋና ልጁ በሚሰጡን እርዳታ መተማመን እንደሚቻል ተምሯል።
‘በይሖዋ መታመናችንን’ ለማሳየት የሚያስችሉን አጋጣሚዎች
4, 5. (ሀ) የሚያስፈልግህን እርዳታ ምንጊዜም ቢሆን ከማን ማግኘት ትችላለህ? (ለ) ከይሖዋ ጋር ያለህን ግንኙነት ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?
4 አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባጋጠሙህ ጊዜ ማንም የሚረዳህ እንደሌለ ተሰምቶህ ያውቃል? ሥራ አጥተህ ወይም በትምህርት ቤት ተጽዕኖ ደርሶብህ አሊያም የጤና እክል ወይም ሌላ የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። ምናልባትም እርዳታ ጠይቀህ ሌሎች የሚያስፈልግህን ድጋፍ ሊሰጡህ ባለመቻላቸው አዝነህ ይሆናል። ለነገሩ አንዳንድ ችግሮች ከሰው ልጆች አቅም በላይ ናቸው። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? መጽሐፍ ቅዱስ “በይሖዋ ታመን” የሚል ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 3:5, 6) ሆኖም ይሖዋ እንደሚረዳህ መተማመን ትችላለህ? እንዴታ! መለኮታዊ እርዳታ እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንደምንችል የሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አሉ።
5 እንግዲያው ሰዎች ብዙም ስላልረዱህ ቅር ከመሰኘት ይልቅ ሐዋርያው እንዳደረገው ሁሉ አንተም እነዚህን ሁኔታዎች በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመታመን እና የእሱን ፍቅራዊ እንክብካቤ ለማየት እንደሚያስችሉህ አጋጣሚዎች አድርገህ ተመልከታቸው። እንዲህ ማድረግህ በእሱ ይበልጥ እንድትተማመንና ከእሱ ጋር ያለህ ዝምድና እንዲጠናከር ያደርጋል።
በአምላክ መታመን ከእሱ ጋር ላለን ግንኙነት ወሳኝ ነው
6. በተለይ አስጨናቂ ሁኔታ ሲያጋጥመን በይሖዋ መታመን ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው?
6 አንድ አስጨናቂ ችግር ሲያጋጥምህ ጉዳዩን ለይሖዋ በጸሎት ከነገርከው በኋላ የምትችለውን እንዳደረግህና የቀረውን እሱ እንደሚፈታው በመተማመን ውስጣዊ ሰላም ማግኘት ትችላለህ? እንዴታ! (መዝሙር 62:8ን እና 1 ጴጥሮስ 5:7ን አንብብ።) በይሖዋ መታመንን መማር ከእሱ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከር አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው። ይሁንና የሚያስፈልግህን ነገር ይሖዋ እንደሚሰጥህ መተማመን ከባድ ሊሆን ይችላል። ለምን? ይሖዋ ለጸሎታችን ወዲያውኑ ምላሽ የማይሰጥባቸው ጊዜያት ስላሉ ነው።—መዝ. 13:1, 2፤ 74:10፤ 89:46፤ 90:13፤ ዕን. 1:2
7. ይሖዋ ለምንጠይቀው ነገር አንዳንድ ጊዜ አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጠን ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ለምንጠይቀው ነገር አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጠን ለምንድን ነው? ይሖዋ ከእሱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና በአባትና በልጅ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር እንዳመሳሰለው አስታውስ። (መዝ. 103:13) አንድ ልጅ፣ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ወላጆቹ እንዲያደርጉለት ወይም ፍላጎቱን በሙሉ ወዲያውኑ እንዲያሟሉለት መጠበቁ ተገቢ አይሆንም። ልጁ አንዳንድ ነገሮችን የሚጠይቀው በስሜታዊነት በመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ይረሳዋል። የሚጠይቃቸውን ሌሎች ነገሮች ለማድረግ ደግሞ ተገቢው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ያስፈልግ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ልጁ የሚፈልገው ነገር እሱንም ሆነ ከእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሌሎች ሰዎች የሚጎዳ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ወላጆች ልጁ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ካደረጉለት ግንኙነታቸው የጌታና የባሪያ ዓይነት ይሆንና ልጁ አዛዥ ሆኖ ቁጭ ይላል። በተመሳሳይም ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ከመስጠቱ በፊት የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ የሚያደርገው ለእኛ ጥቅም ሲል ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ጥበበኛ ፈጣሪያችን፣ አፍቃሪ ጌታችንና ሰማያዊ አባታችን እንደ መሆኑ መጠን ይህን የማድረግ መብት አለው። የጠየቅነውን ሁሉ ወዲያውኑ የሚያደርግልን ከሆነ በመካከላችን ያለው ግንኙነት ትክክለኛውን አካሄድ የጠበቀ አይሆንም።—ከኢሳይያስ 29:16 እና 45:9 ጋር አወዳድር።
8. ይሖዋ፣ ከአቅማችን ጋር በተያያዘ ምን ቃል ገብቶልናል?
8 ሌላው ምክንያት ደግሞ ይሖዋ አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ በደንብ የሚያውቅ መሆኑ ነው። (መዝ. 103:14) ስለዚህ የሚያጋጥመንን ፈተና በራሳችን ኃይል እንድንወጣው አይጠብቅብንም፤ ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ አባት እርዳታ ይሰጠናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ፈተናውን መቋቋም የማንችልበት ደረጃ ላይ እንደደረስን ይሰማን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከሚችሉት በላይ እንዲፈተኑ ፈጽሞ እንደማይፈቅድ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። እንዲያውም “መውጫ መንገዱን” ያዘጋጅልናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ።) እንግዲያው ይሖዋ መሸከም የምንችለው ምን ያህል እንደሆነ በትክክል እንደሚያውቅ ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን።
9. እርዳታ ለማግኘት ከጸለይን በኋላ ወዲያውኑ ምላሽ እንዳላገኘን ሲሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
9 እርዳታ ለማግኘት ከጸለይን በኋላ ወዲያውኑ ምላሽ እንዳላገኘን ከተሰማን፣ እኛን ለመርዳት መቼ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የሚያውቀውን አምላካችንን በትዕግሥት እንጠብቅ። ይሖዋ እኛን ለመርዳት በጣም ስለሚጓጓ እሱም ቢሆን መታገሥ እንደሚያስፈልገው እናስታውስ። “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና። እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።”—ኢሳ. 30:18
“ከአንበሳ አፍ”
10-12. (ሀ) በጠና የታመመ የቤተሰቡን አባል የሚንከባከብ አንድ ክርስቲያን ሁኔታዎች በጣም ተፈታታኝ ሊሆኑበት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመው በይሖዋ መታመኑ ከእሱ ጋር ያለውን ዝምድና የሚነካው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
10 ከባድ ፈተና ሲያጋጥምህ አንተም ልክ እንደ ጳውሎስ “አንበሳ አፍ” ውስጥ እንደገባህ ወይም ልትገባ እንደተቃረብክ ያህል ሊሰማህ ይችላል። በይሖዋ መታመን በጣም አስቸጋሪ ሆኖም በጣም አስፈላጊ የሚሆነው በዚህ ጊዜ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በጠና የታመመ የቤተሰብህን አባል እየተንከባከብክ ይሆናል። ምናልባትም ይሖዋ ጥበብና ብርታት እንዲሰጥህ ጸልየህ ሊሆን ይችላል።b ታዲያ በዚህ ረገድ የምትችለውን ሁሉ ካደረግህ በኋላ፣ የይሖዋ ዓይን በአንተ ላይ እንደሆነና በታማኝነት ለመጽናት የሚያስፈልግህን ነገር እሱ እንደሚሰጥህ በማወቅህ ውስጥህ አይረጋጋም?—መዝ. 32:8
11 ይሁንና በተለያዩ ሁኔታዎች የተነሳ እንዲህ ማድረግ እንደማትችል ይሰማህ ይሆናል። ሐኪሞች የተለያየ አስተያየት ሊሰጡህ አሊያም ደግሞ ያጽናኑኛል ብለህ ያሰብካቸው ዘመዶችህ ሁኔታው ይበልጥ ከባድ እንዲሆንብህ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህ ወቅት እርዳታ ለማግኘት ምንጊዜም በይሖዋ ታመን። ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ጥረት አድርግ። (1 ሳሙኤል 30:3, 6ን አንብብ።) ውሎ አድሮ፣ ይሖዋ ችግሮችህን እንዴት እንዳቃለለልህ ስትገነዘብ ከእሱ ጋር ያለህ ዝምድና ይበልጥ ይጠናከራል።
12 ሊንዳc ይህ እውነት መሆኑን የተገነዘበችው በዕድሜ የገፉ ወላጆቿን ከመሞታቸው በፊት ለተወሰኑ ዓመታት ስታስታምማቸው ከቆየች በኋላ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ ሁኔታ ውስጥ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ እንዲሁም ወንድሜ ምን እንደምናደርግ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባን ነበር። ነገሮች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ የሚሰማን ወቅት ነበር። መለስ ብለን ስናስበው ግን ይሖዋ ያደረገልንን ነገር አሁን ይበልጥ ማስተዋል ችለናል። ይሖዋ አበረታቶናል፤ እንዲሁም አማራጭ የሌለን በሚመስልበት ጊዜም እንኳ የሚያስፈልገንን ነገር አድርጎልናል።”
13. አንዲት እህት በይሖዋ መታመኗ አስጨናቂ ሁኔታዎች በተደራረቡባት ወቅት የጠቀማት እንዴት ነው?
13 በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን ከባድ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜም ይጠቅመናል። ራንዳ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟታል። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባሏ የፍቺ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት ወንድሟ ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ እንዳለበት ታወቀ። ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ የወንድሟ ባለቤት ሞተች። ራንዳ እነዚህ አስጨናቂ ሁኔታዎች ካሳደሩባት ጫና እንዳገገመች ሲሰማት በዘወትር አቅኚነት ማገልገል ጀመረች። ሆኖም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እናቷ አረፉ። ራንዳ እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንድትቋቋም የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ጥቃቅን ከሆኑ ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ እንኳ ይሖዋን በየዕለቱ በጸሎት አነጋግረው ነበር። እንዲህ ማድረጌ ይሖዋ እውን እንዲሆንልኝ ረድቶኛል። በራሴ ወይም በሌሎች ሰዎች ከመታመን ይልቅ በይሖዋ መታመንን አስተምሮኛል። እሱ ያደረገልኝን ድጋፍ በሕይወቴ መመልከት ችያለሁ፤ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች በሙሉ አሟልቶልኛል። በዚህም የተነሳ ከይሖዋ ጋር ተቀራርቤ የመሥራት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።”
14. የቤተሰቡ አባል የተወገደበት አንድ ክርስቲያን ይሖዋ ምን እንደሚያደርግለት መተማመን ይችላል?
14 ሌላ ሁኔታ ደግሞ እንመልከት። አንድ የቤተሰብህ አባል ተወገደ እንበል። ከተወገዱ ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ምን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ተምረሃል። (1 ቆሮ. 5:11፤ 2 ዮሐ. 10) ይሁንና ግለሰቡ እንዲወገድ የተደረገውን ውሳኔ መደገፍ በጣም ከባድ አልፎ ተርፎም የማይቻል የሚመስልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል።d ታዲያ ውገዳን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ በማክበር ረገድ ጽኑ አቋም ለመያዝ የሚያስፈልግህን ጥንካሬ በሰማይ ያለው አባትህ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ? ይህ ሁኔታ ወደ ይሖዋ በመቅረብ ከእሱ ጋር ያለህን ዝምድና ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማሃል?
15. አዳም በኤደን የይሖዋን ትእዛዝ የጣሰው ለምንድን ነው?
15 ከዚህ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ለማስታወስ ሞክር። አዳም ይሖዋን ሳይታዘዝ በሕይወት መኖር እንደሚችል አስቦ ነበር? አልነበረም፤ ምክንያቱም ቅዱሳን መጻሕፍት “አዳም አልተታለለም” ይላሉ። (1 ጢሞ. 2:14) ታዲያ የይሖዋን መመሪያ ያልታዘዘው ለምንድን ነው? አዳም፣ ሔዋን የሰጠችውን ፍሬ የበላው ከሚስቱ ላለመለየት ስለፈለገ መሆን አለበት። አምላኩን ይሖዋን ከመስማት ይልቅ የሚስቱን ቃል ሰማ።—ዘፍ. 3:6, 17
16. ከማንም በላይ ልንወደው የሚገባው ማንን ነው? ለምንስ?
16 ይህ ሲባል ታዲያ የቤተሰባችንን አባላት ከልብ ልንወዳቸው አይገባም ማለት ነው? በፍጹም! ሆኖም ከማንም በላይ ልንወደው የሚገባው ይሖዋን ነው። (ማቴዎስ 22:37, 38ን አንብብ።) የቤተሰባችን አባላት በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን እያገለገሉ ሆኑም አልሆኑ የሚጠቅማቸው ይህን ማድረጋችን ነው። እንግዲያው ለይሖዋ ያለህን ፍቅር አጠናክር፤ እንዲሁም በእሱ ይበልጥ ታመን። የተወገደው የቤተሰብህ አባል በተከተለው ጎዳና የተነሳ ስለ እሱ በጣም የምትጨነቅ ከሆነ የውስጥህን አውጥተህ ለይሖዋ በጸሎት ንገረው።e (ሮም 12:12፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ከይሖዋ ጋር ያለህን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገህ ተመልከተው። እንዲህ ማድረግህ ከሁሉ የተሻለውን መፍትሔ ከይሖዋ እንድትጠብቅ ይረዳሃል።
ስንጠባበቅ
17. በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ስንጠመድ በይሖዋ እንደምንታመን የምናሳየው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ፣ ጳውሎስን “ከአንበሳ አፍ” ያዳነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ “የስብከቱ ሥራ በእኔ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸምና ብሔራት ሁሉ እንዲሰሙት [ነው]” በማለት መልሱን ሰጥቶናል። (2 ጢሞ. 4:17) እኛም እንደ ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ከተጠመድን ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ሌሎች ነገሮች በሙሉ ‘እንደሚሰጠን’ መተማመን እንችላለን። (ማቴ. 6:33) የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንደመሆናችን መጠን “ምሥራቹን በአደራ” ተቀብለናል፤ እንዲሁም ይሖዋ ከእሱ ጋር “አብረን የምንሠራ” እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል። (1 ተሰ. 2:4፤ 1 ቆሮ. 3:9) በአምላክ ሥራ በተቻለን መጠን ንቁ ተሳትፎ ማድረጋችን ችግሮቻችን እስኪቃለሉ ድረስ መጠበቅ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል።
18. በይሖዋ መታመንና ከእሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር የምንችለው ምን በማድረግ ነው?
18 እንግዲያው የቀረውን ጊዜ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር እንጠቀምበት። የሚያስጨንቀን ሁኔታ ሲያጋጥመን ይህን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርገን እንመልከተው። በእርግጥም፣ የአምላክን ቃል በጥልቀት የምናጠና፣ አዘውትረን የምንጸልይ እንዲሁም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምንጠመድ ከሆነ ይሖዋ አሁን ያሉብንንም ሆነ ወደፊት ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድንወጣ ሊረዳን እንደሚችልና ይህንንም እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን።
a ጳውሎስ ‘ከአንበሳ አፍ ዳንኩ’ ሲል ቃል በቃል አሊያም በምሳሌያዊ መንገድ እየተናገረ ሊሆን ይችላል።
b የታመሙ ክርስቲያኖችም ሆኑ የሚንከባከቧቸው ሰዎች ሁኔታውን መቋቋም እንዲችሉ የሚረዱ ርዕሶች በጽሑፎቻችን ላይ ወጥተዋል። የየካቲት 8, 1994 (እንግሊዝኛ)፤ የየካቲት 8, 1997 (እንግሊዝኛ)፤ የመስከረም 2000 እና የየካቲት 2001 የንቁ! እትሞችን ተመልከት።
c ስሞቹ ተቀይረዋል።
d በዚህ እትም ላይ ያለውን “ውገዳ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
e ታማኝ ክርስቲያኖች አንድ የቤተሰባቸው አባል ይሖዋን ማገልገሉን ሲተው ሁኔታውን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ የሚገልጹ ትምህርቶች በጽሑፎቻችን ላይ ወጥተዋል። የመስከረም 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 17-21ን እና የጥር 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 17-20ን ተመልከት።