“በተግባርና በእውነት” እንዋደድ
“በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።”—1 ዮሐ. 3:18
1. ከሁሉ የላቀው የፍቅር ዓይነት የትኛው ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
ትክክለኛ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተው ፍቅር ማለትም አጋፔ ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ ነው። የዚህ ፍቅር ምንጭ ይሖዋ ነው። (1 ዮሐ. 4:7) አጋፔ ከሁሉ የላቀው የፍቅር ዓይነት ነው። ይህ የፍቅር ዓይነት ለአንድ ሰው የሚኖረንን የመውደድ ስሜት የሚያካትት ቢሆንም በዋነኝነት የሚገለጸው ግን ለሌሎች ጥቅም ስንል በምናከናውነው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ተግባር ነው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ፣ አጋፔ የተባለውን የፍቅር ዓይነት “ለይቶ ማወቅ የሚቻለው በሚያከናውነው ተግባር ብቻ ነው” በማለት ገልጿል። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለሌሎች ስናሳይ ወይም ሌሎች እንዲህ ያለውን ፍቅር ሲያሳዩን ሕይወታችን አስደሳችና ትርጉም ያለው ይሆናል።
2, 3. ይሖዋ ለሰው ልጆች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
2 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከመፍጠሩ በፊትም እንኳ ለሰው ልጆች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። የሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ የሆነችውን ምድርን የፈጠራት በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉ ነገሮችን ብቻ እንድታሟላ አድርጎ ሳይሆን ሰዎች ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩባት በሚያስችል መንገድ ነው። ይሖዋ ይህን ያደረገው ሙሉ በሙሉ ለእኛ ጥቅም በማሰብ እንጂ ለእሱ የሚያስገኝለት ነገር ስላለ አይደለም። በተጨማሪም ይሖዋ በምድር ላይ ያሉ ልጆቹን በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ በመስጠት የባረካቸው ሲሆን በዚህ መንገድ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል።
3 አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላ ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ከሁሉ በላቀ መንገድ አሳይቷል። የሁለቱ ዓመፀኞች ዘር ከሆኑት የሰው ልጆች መካከል አንዳንዶቹ እሱ ላሳያቸው ፍቅር አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ በመተማመን ቤዛ አዘጋጅቷል። (ዘፍ. 3:15፤ 1 ዮሐ. 4:10) እንዲያውም ይሖዋ ቤዛውን እንደሚያዘጋጅ ቃል ከገባበት ጊዜ አንስቶ የቤዛው መሥዋዕት እንደተከፈለ አድርጎ ቆጥሮታል። ከዚያም ከ4,000 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሖዋ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍለው ቢሆንም አንድያ ልጁን ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ ላሳየን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ምንኛ አመስጋኞች ነን!
4. ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የማሳየት ችሎታ እንዳላቸው ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
4 አምላክ የፈጠረን በራሱ አምሳል ስለሆነ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የማሳየት ችሎታ አለን። በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ፍቅር ማሳየት ተፈታታኝ እንደሚሆንብን አይካድም፤ ሆኖም ይህን ችሎታችንን ሙሉ በሙሉ አላጣንም። አቤል፣ ካለው ነገር ምርጡን ለአምላክ በመስጠት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ዘፍ. 4:3, 4) ኖኅ የአምላክን መልእክት የሚሰብክላቸው ሰዎች ምንም ምላሽ ባይሰጡም ለአሥርተ ዓመታት በጽናት በመስበክ ለሰዎች ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (2 ጴጥ. 2:5) አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት እንዲያደርግ በተጠየቀ ጊዜ አምላክን ከምንም ነገር በላይ አስበልጦ እንደሚወድ አሳይቷል። (ያዕ. 2:21) እኛም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ልክ እንደ እነዚህ ታማኝ ሰዎች ፍቅር ማሳየት እንፈልጋለን።
እውነተኛ ፍቅርና የውሸት ፍቅር
5. እውነተኛ ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
5 መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ፍቅር የሚገለጸው “በቃልና በአንደበት” ሳይሆን “በተግባርና በእውነት” እንደሆነ ይናገራል። (1 ዮሐ. 3:18) እንዲህ ሲባል ታዲያ ፍቅራችንን በአንደበታችን መግለጽ አይኖርብንም ማለት ነው? በፍጹም! (1 ተሰ. 4:18) ይህ አባባል ፍቅራችንን በአንደበታችን በመግለጽ ብቻ መወሰን እንደሌለብን የሚያመለክት ነው፤ በተለይ ደግሞ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድን የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ፍቅራችንን በአንደበታችን ከመግለጽ ያለፈ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ለኑሮ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን አጥቶ ሲቸገር ብናየው እንዲሁ ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ነገር ልናደርግለት ይገባል። (ያዕ. 2:15, 16) በተጨማሪም ለይሖዋና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር፣ አምላክ “ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ” ከመለመን ባለፈ በስብከቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል።—ማቴ. 9:38
6, 7. (ሀ) “ግብዝነት የሌለበት” ፍቅር ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) የውሸት ፍቅር የታየባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ።
6 ሐዋርያው ዮሐንስ “በተግባርና በእውነት” መዋደድ እንዳለብን ጽፏል። በመሆኑም ፍቅራችን “ግብዝነት የሌለበት” ሊሆን ይገባል። (ሮም 12:9፤ 2 ቆሮ. 6:6) ጭንብል እንዳጠለቀ ሰው ያልሆንነውን ሆነን ለመታየት ጥረት የምናደርግ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር እያሳየን ነው ሊባል አይችልም። ለመሆኑ ግብዝነት ያለበት ፍቅር ሊኖር ይችላል? በፍጹም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግብዝነት ያለበት ፍቅር የሚያሳይ ሰው ፍቅር እያሳየ ሳይሆን እያስመሰለ ነው።
7 የውሸት ፍቅር የታየባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት። በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን ሔዋንን ያነጋገራት ለእሷ ደህንነት የተቆረቆረ በሚመስል መንገድ ነበር፤ ሆኖም ድርጊቱ ከራስ ወዳድነት የመነጨና ግብዝነት የሞላበት ነበር። (ዘፍ. 3:4, 5) የአኪጦፌልን ሁኔታም እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። አኪጦፌል የንጉሥ ዳዊት እውነተኛ ወዳጅ አልነበረም፤ ምክንያቱም ጥቅም የሚያስገኝለት ሁኔታ እንደተፈጠረ ሲሰማው ዳዊትን ከድቶታል። (2 ሳሙ. 15:31) ዛሬም በተመሳሳይ በጉባኤው ውስጥ ክፍፍል የሚፈጥሩ ከሃዲዎችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች አሳቢ መስለው ለመታየት ሲሉ ‘የለሰለሰ አንደበትና የሽንገላ ቃላት’ ይጠቀማሉ፤ እንደ እውነታው ከሆነ ግን እነዚህ ሰዎች የራስ ወዳድነት ፍላጎታቸውን ለማራመድ የሚጥሩ ናቸው።—ሮም 16:17, 18
8. ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
8 የውሸት ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች አምላካዊ ባሕርይ የሆነው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያላቸው መስለው ለመታየት ጥረት ማድረጋቸው በጣም አሳፋሪ ነው። እንዲህ ያለው ግብዝነት ሰዎችን ያታልል ይሆናል፤ ይሖዋን ግን በፍጹም ሊያታልለው አይችልም። እንዲያውም ኢየሱስ ግብዞች “ከባድ ቅጣት” እንደሚጠብቃቸው የሚጠቁም ሐሳብ ተናግሯል። (ማቴ. 24:51) እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን መቼም ቢሆን የውሸት ፍቅር ማሳየት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ይሁንና ‘ምንጊዜም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነና ማታለል የሌለበት እውነተኛ ፍቅር አሳያለሁ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው። “ግብዝነት የሌለበት” ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸውን ዘጠኝ አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት።
“በተግባርና በእውነት” እንደምንዋደድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9. እውነተኛ ፍቅር ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
9 የምትሠራውን ሥራ ሌሎች ባያዩትም እንኳ በደስታ ማገልገልህን ቀጥል። ለወንድሞቻችን ፍቅር እንዳለን የሚያሳዩ ተግባሮችን የሚቻል ከሆነ “በስውር” ማለትም ከሌሎች እይታ ውጭ ለማከናወን ፈቃደኞች መሆን አለብን። (ማቴዎስ 6:1-4ን አንብብ።) ሐናንያና ሰጲራ ያደረጉት ነገር ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ስላደረጉት መዋጮ ሌሎች እንዲያውቁላቸው ስለፈለጉ መዋጮዋቸውን ሆን ብለው አጋንነው ያቀረቡ ሲሆን ይህ የግብዝነት ድርጊታቸውም ለከፍተኛ ውድቀት ዳርጓቸዋል። (ሥራ 5:1-10) ለወንድሞቻችን እውነተኛ ፍቅር ካለን ለእነሱ ስንል ያከናወንነውን መልካም ተግባር ሌሎች እንዲያውቁልን ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ እነሱን በማገልገላችን ደስተኞች እንሆናለን። ለምሳሌ ያህል፣ መንፈሳዊ ምግብ በማዘጋጀት የበላይ አካሉን የሚረዱት ወንድሞች ወደ ራሳቸው ትኩረት በመሳብም ሆነ በየትኛው ሥራ ላይ እጃቸው እንዳለበት የሚጠቁም ሐሳብ በመናገር ስማቸው እንዲታወቅ ለማድረግ አይሞክሩም።
10. ሌሎችን ለማክበር ቀዳሚ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
10 ሌሎችን ለማክበር ቀዳሚ ሁን። (ሮም 12:10ን አንብብ።) ኢየሱስ በጣም ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በማከናወን ሌሎችን በማክበር ረገድ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐ. 13:3-5, 12-15) ለሌሎች አክብሮት ለማሳየት የሚያስፈልገውን ትሕትና ለማዳበር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ሐዋርያትም እንኳ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ነገሮች ትርጉም ሙሉ በሙሉ የተረዱት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ነው። (ዮሐ. 13:7) ለሌሎች አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ በትምህርት ደረጃችን፣ በቁሳዊ ሀብታችን ወይም በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ባሉን መብቶች ምክንያት ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን አድርገን ባለማሰብ ነው። (ሮም 12:3) በተጨማሪም ሌሎች ሲመሰገኑ አንቀናም፤ በጉዳዩ ውስጥ የእኛም አስተዋጽኦ እንዳለበት አሊያም ከእነሱ እኩል ልንመሰገን እንደሚገባ በሚሰማን ጊዜም እንኳ አብረናቸው እንደሰታለን።
11. ምስጋናችን ከልብ የመነጨ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
11 ወንድሞችህን ከልብ አመስግን። አንዳችን ሌላውን የምናመሰግንበትን አጋጣሚ በንቃት መከታተል ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን ‘ሌሎችን ያንጻል።’ (ኤፌ. 4:29) ይሁን እንጂ አንድን ሰው ስናመሰግን ከልባችን መሆን ይኖርበታል። ካልሆነ ግን ግለሰቡን እየሸነገልነው ወይም ለግለሰቡ የሚያስፈልገውን ምክር የመስጠት ኃላፊነታችንን ገሸሽ እያደረግን ነው ማለት ነው። (ምሳሌ 29:5) አንድን ሰው ካመሰገንነው በኋላ ከበስተጀርባው ስለ እሱ አሉታዊ ነገር መናገር ግብዝነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ረገድ ጠንቃቃ የነበረ ሲሆን ሌሎችን ያመሰገነበት መንገድ ለእነሱ እውነተኛ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያከናወኗቸውን አንዳንድ መልካም ነገሮች በመጥቀስ ከልብ አመስግኗቸዋል። (1 ቆሮ. 11:2) ይሁንና ምስጋና የማይገባውና መታረም ያለበት ተግባር በፈጸሙ ጊዜ ጉዳዩን በግልጽ ሆኖም ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አስረድቷቸዋል።—1 ቆሮ. 11:20-22
12. እንግዳ ተቀባይ ለመሆን ጥረት በምናደርግበት ጊዜ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
12 እንግዳ ተቀባይ ሁን። ይሖዋ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልግስና እንድናሳይ አዞናል። (1 ዮሐንስ 3:17ን አንብብ።) ይሁንና እንዲህ የምናደርገው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜትና በትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት ተነሳስተን መሆን ይኖርበታል። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በዋነኝነት በእንግድነት የምቀበለው የቅርብ ጓደኞቼን፣ የኃላፊነት ቦታ ያላቸውን ወይም በሆነ መንገድ ውለታ ሊመልሱልኝ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ሰዎች ነው? ወይስ በደንብ ለማላውቃቸው አሊያም ውለታ ሊመልሱልኝ ለማይችሉ ወንድሞችና እህቶች ልግስና ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ?’ (ሉቃስ 14:12-14) በሌላ በኩል ደግሞ የእምነት ባልንጀራችን ጥበብ የጎደለው እርምጃ በመውሰዱ ምክንያት ችግር ውስጥ ወደቀ ወይም ላሳየነው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አመስጋኝ ሳይሆን ቀረ እንበል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን “ሳታጉረመርሙ አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 4:9) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት ተነሳስቶ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም እንችላለን።—ሥራ 20:35
13. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ፣ ደካሞችን መርዳት ተፈታታኝ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ደካሞችን ለመርዳት ምን ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እንችላለን?
13 ደካሞችን ደግፍ። “ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ” ለሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ የምንሰጠው ምላሽ ፍቅራችን እውነተኛ መሆን አለመሆኑን ያሳያል። (1 ተሰ. 5:14) በአንድ ወቅት ደካማ የነበሩ በርካታ ሰዎች ከጊዜ በኋላ በእምነት ጠንካሮች ይሆናሉ፤ አንዳንዶች ግን በትዕግሥት ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ማግኘት ይፈልጋሉ። ይህም አበረታች የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማካፈልን፣ አብረውን አገልግሎት እንዲወጡ መጋበዝን ሌላው ቀርቶ ጊዜ ወስዶ ማዳመጥን ሊጨምር ይችላል። በተጨማሪም አንድን ወንድም ወይም አንዲትን እህት እንዲሁ በደፈናው “ጠንካራ” ወይም “ደካማ” ብሎ ከመፈረጅ ይልቅ ሁላችንም ጠንካራና ደካማ ጎን እንዳለን መገንዘብ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ ድክመት እንዳለበት አምኖ ተቀብሏል። (2 ቆሮ. 12:9, 10) በመሆኑም ሁላችንም የእምነት ባልንጀሮቻችን ድጋፍ ያስፈልገናል።
14. ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ይዘን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
14 ሰላም ፈጣሪ ሁን። ወንድሞቻችን በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱን ወይም እንደበደሉን በሚሰማን ጊዜም እንኳ ከእነሱ ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ይዘን ለመቀጠል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። (ሮም 12:17, 18ን አንብብ።) አንድን ሰው የሚጎዳ ነገር በምንፈጽምበት ጊዜ ይቅርታ መጠየቃችን የግለሰቡን ስሜት ሊጠግነው ይችላል፤ ሆኖም ይቅርታ ስንጠይቅ ከልባችን መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ “እንዲህ ስለተሰማህ አዝናለሁ” ከማለት ይልቅ “በተናገርኩት ነገር ስሜትህን ስለጎዳሁት በጣም ይቅርታ” ማለታችን ለተፈጠረው ችግር የእኛም ጥፋት እንዳለበት አምነን እንደተቀበልን ያሳያል። በተለይ ደግሞ በትዳር ውስጥ ሰላም በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ባልና ሚስት ሰው ፊት ሲሆኑ የሚዋደዱ እየመሰሉ ለብቻቸው በሚሆኑበት ጊዜ ግን የሚኮራረፉ፣ ኃይለ ቃል የሚነጋገሩ አሊያም አንዳቸው ሌላውን የሚማቱ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር አላቸው ሊባል አይችልም።
15. የበደሉንን ሰዎች ከልብ ይቅር እንዳልን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
15 በነፃ ይቅር በል። አንድ ሰው ሲበድለን በደሉን ይቅር ለማለትና እሱን በተመለከተ የሚሰማንን ቅሬታ ለማስወገድ ፈቃደኞች መሆን አለብን። አንዳንድ ጊዜ በደል የፈጸሙብን ሰዎች እንደበደሉን እንኳ ላያውቁ ይችላሉ፤ በዚህ ጊዜ “እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤ አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ እነዚህን ሰዎች በነፃ ይቅር ልንላቸው እንችላለን። (ኤፌ. 4:2, 3) ከልብ ይቅር ብለናል ሊባል የሚችለው በልባችን ውስጥ ምንም ዓይነት ‘የበደል መዝገብ ከሌለ’ ነው፤ ይህ ደግሞ አስተሳሰባችንን መቆጣጠርን ይጠይቃል። (1 ቆሮ. 13:4, 5) ቅሬታ እንዲያድርብን የምንፈቅድ ወይም ቂም የምንይዝ ከሆነ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድናም አደጋ ላይ ይወድቃል። (ማቴ. 6:14, 15) በሌላ በኩል ግን በደል ለፈጸሙብን ሰዎች መጸለያችን እነሱን ከልብ ይቅር እንዳልናቸው ያሳያል።—ሉቃስ 6:27, 28
16. በይሖዋ አገልግሎት ላገኘናቸው መብቶች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
16 የራስህን ጥቅም መሥዋዕት አድርግ። በይሖዋ አገልግሎት አንዳንድ መብቶችን ስናገኝ እነዚህን መብቶች ‘የራሳችንን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም በመፈለግ’ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን የምናሳይባቸው አጋጣሚዎች አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። (1 ቆሮ. 10:24) ለምሳሌ ያህል፣ አስተናጋጆች በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ የሚያከናውኑት ሥራ ስለሚኖር ሌሎች የሚገቡበት ሰዓት ከመድረሱ ቀደም ብለው ወደ ስብሰባ ቦታው ይገባሉ። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል አብዛኞቹ አጋጣሚውን ተጠቅመው ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ከሁሉ የተሻለውን ወንበር ከመያዝ ይልቅ በምድባቸው ሥር ባለ እምብዛም ምቹ ያልሆነ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ይመርጣሉ። በዚህ መልኩ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያሉ። አንተስ የእነሱን ምሳሌ መከተል የምትችልበት መንገድ ይኖር ይሆን?
17. እውነተኛ ፍቅር ከባድ ኃጢአት የሠራን አንድ ክርስቲያን ምን እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል?
17 በስውር የፈጸምከውን ኃጢአት ተናዘዝ፤ እንዲሁም እርግፍ አድርገህ ተወው። ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከኀፍረት ለመሸሽ አሊያም ሌሎችን ላለማሳዘን ሲሉ የፈጸሙትን ኃጢአት ለመደበቅ ይሞክራሉ። (ምሳሌ 28:13) ሆኖም እንዲህ ያለው አካሄድ ፍቅር የጎደለው ነው፤ ምክንያቱም ይህ ድርጊት ኃጢአት የፈጸመውን ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይጎዳል። የአምላክ መንፈስ በነፃነት እንዳይሠራ የሚያግድ ከመሆኑም ሌላ የመላውን ጉባኤ ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል። (ኤፌ. 4:30) ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ክርስቲያኖች እውነተኛ ፍቅር ካላቸው ሽማግሌዎችን በማነጋገር አስፈላጊውን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።—ያዕ. 5:14, 15
18. እውነተኛ ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
18 ፍቅር ከሁሉ የላቀ ባሕርይ ነው። (1 ቆሮ. 13:13) የኢየሱስ ተከታዮች መሆናችን የሚታወቀውና የፍቅር ምንጭ የሆነውን ይሖዋን እንደምንመስል የሚታየው ፍቅር ካለን ነው። (ኤፌ. 5:1, 2) ጳውሎስ “ፍቅር . . . ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 13:2) እንግዲያው ፍቅራችንን “በቃል” ብቻ ሳይሆን “በተግባርና በእውነት” ጭምር ለመግለጽ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።