መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መንፈሳዊ ፍላጎትህን ማርካት ትችላለህ
ሰዎች ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ መንፈሳዊ ነገሮችን የማግኘት መሠረታዊ ፍላጎትም አላቸው። በሕይወት ለመኖር የሚያስችሉን ብዙ ዓይነት ጥሩ ምግቦች ስላሉ የምንፈልገውን መምረጥ እንችላለን። በመንፈሳዊ ፍላጎታችን ረገድስ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው? መንፈሳዊ ፍላጎታችንን እንደሚያሟሉ የሚነገርላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ባሕሎችና ሃይማኖታዊ ልማዶች አሉ።
ብዙዎች፣ አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ተግባር እስከፈጸምክ ድረስ በምንም ብታምን ወይም በየትኛውም ዓይነት አምልኮ ብትካፈል ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ይሰማቸዋል። አንተ ምን ይመስልሃል? መንፈሳዊ ፍላጎትህን የምታሟላበት መንገድ ልዩነት ያመጣል? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
እውነተኛ መንፈሳዊነት እንዲኖረን ምን ያስፈልገናል?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ መንፈሳዊ ፍላጎት ሊኖረን የቻለበትን ምክንያት ሲገልጽ በዘፍጥረት 1:27 ላይ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” ይሖዋ አምላክ መንፈስ ስለሆነ በእሱ መልክ መፈጠር የሚያመለክተው አካላዊ መመሳሰልን ሳይሆን የባሕርይ መመሳሰልን ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም፣ እንደ ፈጣሪው ሁሉ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርን፣ ደግነትን፣ ርኅራኄን፣ ፍትሕን፣ ራስን መግዛትንና የመሳሰሉትን ባሕርያት ከፍ አድርጎ መመልከት እንዲሁም ማንጸባረቅ ይችል ነበር። በተጨማሪም ነፃ ምርጫውን ከአምላክ ሕጎች ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲጠቀምበት የሚመራው ሕሊና ማለትም በውስጡ ያለ የሥነ ምግባር ሕግ ተሰጥቶት ነበር። እነዚህ ነገሮች አዳምን ከእንስሳት የሚለዩት ከመሆኑም ሌላ የፈጣሪውን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችል ልዩ ብቃት እንዲኖረው አድርገውታል።—ዘፍጥረት 1:28፤ ሮም 2:14
መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለይቶ ይገልጻል። በ1 ቆሮንቶስ 2:12-15 ላይ መንፈሳዊ የሆነ ሰው ከአምላክ የሆነውን መንፈስ የተቀበለ እንደሆነ ተገልጿል። ይህ መንፈስ በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል ሲሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ለማወቅ የግድ ያስፈልገናል። ይህ መንፈስ ካለን መንፈሳዊ አመለካከት በመያዝ ነገሮችን ከዚያ አንጻር መመርመርና መረዳት እንችላለን። በተቃራኒው ደግሞ የአምላክ መንፈስ የሌለው ሰው ሥጋዊ ሰው ተብሎ ተጠርቷል፤ እንዲህ ዓይነቱ ሰው መንፈሳዊ ነገሮችን እንደ ሞኝነት ይቆጥራቸዋል። በዚህም የተነሳ ይህ ዓይነቱ ሰው የሚደርስበት መደምደሚያ የሰው ጥበብ ሊገልጽለት በሚችለው ነገር ላይ ብቻ የተወሰነ ነው።
በአምላክ መልክ በመፈጠራችን መንፈሳዊ ፍላጎት ሊኖረን ቢችልም እውነተኛ መንፈሳዊነት ማንነትን በማወቅ፣ በሰብዓዊ ጥበብ ወይም በራስ ጥረት የሚገኝ ነገር አይደለም። እውነተኛ መንፈሳዊነት እንዲኖረን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መመራት ያስፈልገናል። እንዲያውም የራሳቸውን ምኞትና መጥፎ ነገሮችን መከተልን በመምረጥ በአምላክ መንፈስ ለመመራት አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች መንፈሳዊ እንዳልሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች በሥጋዊ ፍላጎቶችና ዝንባሌዎች የሚመሩ ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 2:14፤ ይሁዳ 18, 19
መንፈሳዊ ፍላጎትን ማሟላት
መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በትክክል ለማሟላት በመጀመሪያ ይሖዋ ፈጣሪያችን መሆኑን አምነን መቀበልና ሕይወታችንን ያገኘነው ከእሱ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል። (ራእይ 4:11) በዚህ መንገድ ሕይወታችን ትርጉም የሚኖረው የእሱን ፈቃድ ከፈጸምን ብቻ መሆኑን እንደምንገነዘብ እናሳያለን። (መዝሙር 115:1) የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ሕይወታችን ዓላማ ያለው እንዲሆን ያደርጋል፤ ለመኖር ምግብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ነው። መንፈሳዊ ሰው በመሆኑ የሚታወቀው ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሎ ሊናገር የቻለው ለዚህ ነው። (ዮሐንስ 4:34) ኢየሱስ፣ የአምላክን ፈቃድ መፈጸሙ መንፈሱ እንዲታደስና እርካታ እንዲያገኝ ስለሚያደርገው ብርታት ይሰጠው ነበር።
የተፈጠርነው በአምላክ መልክ በመሆኑ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በትክክል ለማሟላት የፈጣሪያችንን ባሕርያት የሚያንጸባርቅ ስብዕናም ሊኖረን ይገባል። (ቆላስይስ 3:10) እንዲህ በማድረግ ክብራችንን ዝቅ የሚያደርግ ወይም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያበላሽብን ድርጊት ከመፈጸም እንቆጠባለን። (ኤፌሶን 4:24-32) ይሖዋ ባወጣቸው መሥፈርቶች መሠረት ለመኖር መምረጣችን የተሻለ ሕይወት እንዲኖረን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ከሕሊና ወቀሳ ስለሚያድነን እውነተኛ የአእምሮ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል።—ሮም 2:15
ኢየሱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” ብሎ በተናገረ ጊዜ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ከማሟላት ጋር የተያያዘውን ሌላ መሠረታዊ እውነት ገልጿል። (ማቴዎስ 4:4) መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማሟላት ያላሰለሰ ትኩረት ይጠይቃል። ይሖዋ ሕይወትን በተመለከተ ሁሉም ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መልስ ይሰጣል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
የእውነተኛ ደስታ ምንጭ
አንድ ሰው ከመጣፈጥ ያለፈ ለሰውነት እምብዛም የማይጠቅሙ ምግቦችን በመብላት ረሃቡን ያስታግስ ይሆናል። በተመሳሳይ እኛም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን የሚያሟሉ በሚመስሉ ተግባሮች ወይም ፍልስፍናዎች “ሆዳችንን ልንሞላ” እንችላለን። ይሁን እንጂ ጥሩ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በሽታ ወይም ከዚያ የከፋ ነገር እንደሚያስከትል ሁሉ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በተገቢው መንገድ አለማሟላትም የኋላ ኋላ ጉዳት ያስከትላል።
ይሁን እንጂ ከይሖዋ አምላክ ጋር ዝምድና የምንመሠርት፣ ፈቃዱን ለማድረግ የምንጥርና አመራሩን የምንከተል ከሆነ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነተኝነት በሕይወታችን ውስጥ እንመለከተዋለን።—ማቴዎስ 5:3
ይህን አስተውለኸዋል?
◼ መንፈሳዊ ፍላጎት ሊኖርህ የቻለው ለምንድን ነው?—ዘፍጥረት 1:27
◼ በራሳችን ጥረት መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማሟላት እንችላለን?—1 ቆሮንቶስ 2:12-15
◼ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ምን ማድረግ አለብን?—ማቴዎስ 4:4፤ ዮሐንስ 4:34፤ ቆላስይስ 3:10
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በተገቢው መንገድ አለማሟላት የኋላ ኋላ ጉዳት ያስከትላል