“ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ”
“ሁለተኛውም [ትእዛዝ] ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።”—ማቴ. 22:39
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ እንደተናገረው በሕጉ ውስጥ የሚገኘው ሁለተኛው ታላቅ ትእዛዝ የትኛው ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
አንድ ፈሪሳዊ ኢየሱስን ለመፈተን በማሰብ “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” በማለት ጠይቆት ነበር። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው” በማለት መልሶለታል። አክሎም “ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው።—ማቴ. 22:34-39
2 ኢየሱስ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ አዞናል። በመሆኑም ‘ባልንጀራችን ማን ነው? ባልንጀራችንን እንደምንወድ ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?’ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው።
ባልንጀራችን ማን ነው?
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ ምን ምሳሌ ተናገረ? (ለ) ደጉ ሳምራዊ፣ ተዘርፎ ከተደበደበ በኋላ በሞትና በሕይወት መካከል ለተጣለ ሰው ምን እርዳታ አበርክቷል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
3 ባልንጀራ ሲባል በአቅራቢያህ የሚኖር በጣም የምትቀርበውና በችግርህ ጊዜ የሚደርስልህ ሰው እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። (ምሳሌ 27:10) ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ላቀረበለት ራሱን ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥር አንድ ሰው የሰጠው መልስ ስለ ባልንጀራ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል። ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የደጉን ሳምራዊ ምሳሌ ተናገረ። (ሉቃስ 10:29-37ን አንብብ።) አንድ እስራኤላዊ ካህንና ሌዋዊ ወንበዴዎች ዘርፈው ከደበደቡት በኋላ በሞትና በሕይወት መካከል የጣሉትን አንድ ሰው ቢመለከቱ ጥሩ ባልንጀራ ይሆናሉ ብለን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ሁለቱም ለተጎዳው ሰው ምንም ሳያደርጉ ትተውት ሄዱ። ሰውየውን የረዳው አንድ ሳምራዊ ሰው ነው፤ ሳምራውያን ደግሞ የሙሴን ሕግ ይጠብቁ የነበረ ቢሆንም በአይሁዳውያን ዘንድ የተናቁ ነበሩ።—ዮሐ. 4:9
4 ደጉ ሳምራዊ፣ ሰውየው እንዲያገግም ለመርዳት ሲል በቁስሉ ላይ ዘይትና ወይን አፈሰሰበት። ከዚያም በእንግዳ ማረፊያ እንክብካቤ እንዲያገኝ ሁለት ዲናር ከፈለ፤ ይህ ደግሞ የአንድ ሰው የሁለት ቀን ደሞዝ ይሆናል። (ማቴ. 20:2) አደጋ ለደረሰበት ሰው እውነተኛ ባልንጀራ የሆነው ማን እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ለባልንጀራችን አሳቢነትና ፍቅር ማሳየት እንዳለብን ያስተምረናል።
5. በቅርቡ የተፈጥሮ አደጋ በደረሰበት ወቅት የይሖዋ አገልጋዮች ለባልንጀራቸው ፍቅር እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
5 እንደ ደጉ ሳምራዊ ያለ ርኅራኄ የሚያሳይ ሰው በአብዛኛው አይገኝም። በተለይም ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ጨካኞች እንዲሁም ጥሩ ነገር የማይወዱ ሰዎች በሞሉበት ‘በመጨረሻው ቀን’ እንዲህ ዓይነት ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-3) የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት የሚፈጠረው ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ለምሳሌ በጥቅምት 2012 በኒው ዮርክ ሲቲ ላይ ከባድ የአውሎ ነፋስ አደጋ ደርሶ ነበር። ከባድ ጉዳት በደረሰበት አንድ የከተማው ክፍል ሰዎች እንደ ኤሌክትሪክ ባሉ መሠረታዊ ነገሮች እጦት ተቸግረው ሳለ ሌቦች የነዋሪዎቹን ቤት ለመዝረፍ ይራወጡ ነበር። በሌላ በኩል ግን፣ በዚያው አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች የእምነት አጋሮቻቸውንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ዝግጅት አደረጉ። ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ የደግነት ተግባሮች የሚፈጽሙት ባልንጀራቸውን ስለሚወዱ ነው። ለመሆኑ ባልንጀራችንን እንደምንወድ የምናሳይባቸው ሌሎች መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
ባልንጀራችንን እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
6. የስብከቱ ሥራ ለባልንጀራ ፍቅር ከማሳየት ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
6 ሰዎችን በመንፈሳዊ በመርዳት። ይህን ማድረግ የምንችለው ሰዎች አበረታች በሆነው “ከቅዱሳን መጻሕፍት [በሚገኘው] መጽናኛ” ላይ እንዲያተኩሩ በመርዳት ነው። (ሮም 15:4) አገልግሎት በመውጣት ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስናካፍላቸው ለባልንጀራችን ፍቅር እያሳየን እንደሆነ ጥያቄ የለውም። (ማቴ. 24:14) “ተስፋ [ከሚሰጠው] አምላክ” የመጣውን የመንግሥት ምሥራች ማወጅ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ሮም 15:13
7. ወርቃማው ሕግ ምንድን ነው? ይህን ሕግ መጠበቅ ምን በረከት ያስገኝልናል?
7 ወርቃማውን ሕግ በመጠበቅ። ይህን ሕግ ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል፤ ሕግም ነቢያትም የሚሉት ይህንኑ ነው።” (ማቴ. 7:12) ሰዎችን የምንይዘው ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ከሆነ ‘ከሕግ’ (ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም) እና ‘ከነቢያት’ (በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ የትንቢት መጻሕፍት) በስተ ጀርባ ያለውን መንፈስ ተረድተናል ማለት ነው። እነዚህ መጻሕፍት፣ አምላክ ባልንጀሮቻቸውን የሚወዱ ሰዎችን እንደሚባርክ በግልጽ ያሳያሉ። ለምሳሌ ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል “ፍትሕን ጠብቁ፤ መልካሙን አድርጉ . . . እነዚህን የሚፈጽም ሰው የተባረከ ነው” በማለት ተናግሯል። (ኢሳ. 56:1, 2) በእርግጥም ባልንጀሮቻችንን በመውደዳችንና ለእነሱ መልካም በማድረጋችን ተባርከናል።
8. ጠላቶቻችንን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል?
8 ጠላቶቻችንን በመውደድ። ኢየሱስ “‘ባልንጀራህን ውደድ፣ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል” ብሏል። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ።” (ማቴ. 5:43-45) ሐዋርያው ጳውሎስም “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ የሚጠጣ ነገር ስጠው” በማለት ተመሳሳይ ሐሳብ ተናግሯል። (ሮም 12:20፤ ምሳሌ 25:21) በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ ሰው፣ የጠላቱ አህያ ሸክሙ ከብዶት ወድቆ ቢያይ መርዳት ነበረበት። (ዘፀ. 23:5) ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ ሰዎች ጥሩ ወዳጆች እንዲሆኑ ረድቷቸው መሆን አለበት። ክርስቲያኖች ለሌሎች ፍቅር በማሳየታቸው፣ ቀደም ሲል ይጠሏቸው የነበሩ ብዙ ሰዎች አመለካከታቸውን ቀይረዋል። ለጠላቶቻችን ሌላው ቀርቶ ዓመፀኛ ለሆኑ አሳዳጆች ጭምር ፍቅር የምናሳይ ከሆነ ከእነሱ መካከል የተወሰኑት እውነተኛውን የክርስትና ጎዳና ሊቀበሉ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ በጣም እንደሚያስደስተን ምንም ጥርጥር የለውም!
9. ከወንድማችን ጋር እርቅ ስለ መፍጠር ኢየሱስ ምን ብሏል?
9 ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት በማድረግ።’ (ዕብ. 12:14) “ከሰው ሁሉ ጋር” ሲባል ወንድሞቻችንንም እንደሚጨምር ምንም ጥያቄ የለውም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ፤ በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር እርቅ ፍጠር፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።” (ማቴ. 5:23, 24) ለወንድማችን ፍቅር የምናሳይና ከእሱ ጋር እርቅ ለመፍጠር አፋጣኝ እርምጃ የምንወስድ ከሆነ አምላክ ይባርከናል።
10. የሌሎችን ስህተት መለቃቀም የሌለብን ለምንድን ነው?
10 የሌሎችን ስህተት ከመለቃቀም በመቆጠብ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረዳችሁን ተዉ፤ በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል። ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ? ወይም በራስህ ዓይን ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን ‘ከዓይንህ ውስጥ ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ! በመጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።” (ማቴ. 7:1-5) እኛ ራሳችን ከባድ ስህተት የምንሠራ ሆነን ሳለን የሌሎችን ጥቃቅን ስህተቶች ከመለቃቀም እንድንቆጠብ የሚያሳስብ እንዴት ያለ ኃይለኛ ትምህርት ነው!
ለባልንጀራችን ፍቅር የምናሳይበት ከሁሉ የላቀው መንገድ
11, 12. ለባልንጀራችን ፍቅር የምናሳይበት ከሁሉ የላቀው መንገድ የትኛው ነው?
11 ለባልንጀራችን ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ከሁሉ የላቀ መንገድ አለ። ይኸውም እንደ ኢየሱስ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ነው። (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ‘ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ተከታዮቹን አዟል። (ማቴ. 28:19, 20) ይህንን ትእዛዝ ለመፈጸም የበኩላችንን የምናደርግ ከሆነ ባልንጀራችን ወደ ጥፋት የሚወስደውን ትልቅና ሰፊ ጎዳና ትቶ ወደ ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ እንዲጓዝ እንረዳዋለን። (ማቴ. 7:13, 14) ይሖዋ እንዲህ ያለውን ጥረት እንደሚባርክ ምንም ጥርጥር የለውም።
12 ልክ እንደ ኢየሱስ ሁሉ ሰዎች በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን እንዲያውቁ መርዳት እንፈልጋለን። (ማቴ. 5:3) ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ ደግሞ “የአምላክን ምሥራች” በመንገር መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዲችሉ እንረዳቸዋለን። (ሮም 1:1) የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር ይታረቃሉ። (2 ቆሮ. 5:18, 19) በመሆኑም ምሥራቹን መስበካችን ለባልንጀራችን ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ወሳኝ መንገድ ነው ሊባል ይችላል።
13. የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን ለሌሎች ያለህን ፍቅር በላቀ መንገድ በማሳየትህ ምን ይሰማሃል?
13 ውጤታማ በሆነ መንገድ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የምንመራ ከሆነ ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ መርዳት ስለምንችል እርካታ እናገኛለን። በዚህ ረገድ የምናደርገው ጥረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በአኗኗሩ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል። (1 ቆሮ. 6:9-11) በእርግጥም አምላክ “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ማስተካከያ እንዲያደርጉና ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ሲረዳቸው መመልከት በጣም የሚያስደስት ነው። (ሥራ 13:48) ብዙዎች ሐዘናቸው በደስታ፣ ጭንቀታቸው ደግሞ በሰማዩ አባት መታመን በሚሰጠው የደኅንነት ስሜት ተተክቷል። አዲሶች የሚያደርጉትን መንፈሳዊ እድገት መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ነው! የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን ለባልንጀራችን ያለንን ፍቅር ከሁሉ በላቀው መንገድ ማሳየታችን ትልቅ በረከት ነው ቢባል አትስማማም?
በመንፈስ መሪነት ስለ ፍቅር የተሰጠ መግለጫ
14. በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ ከሚገኙት የፍቅር ገጽታዎች መካከል የተወሰኑትን በራስህ አባባል ግለጽ።
14 ከባልንጀራችን ጋር ባለን ግንኙነት ጳውሎስ ፍቅርን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ከብዙ ችግሮች ይጠብቀናል፤ እንዲሁም ደስታና የአምላክን በረከት ያስገኝልናል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8ን አንብብ።) እስቲ ጳውሎስ ስለ ፍቅር የተናገረውን ሐሳብ በአጭሩ እንከልስ፤ እንዲሁም ከባልንጀራችን ጋር ባለን ግንኙነት ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ የምንችልበትን መንገድ እንመልከት።
15. (ሀ) ታጋሽና ደግ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ቅናትንና ጉራን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
15 “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው።” አምላክ ፍጽምና ለጎደላቸው የሰው ልጆች ትዕግሥትና ደግነት እንደሚያሳይ ሁሉ እኛም ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ እንዲሁም ግድ የለሽነት የሚንጸባረቅበት አልፎ ተርፎም ሥርዓት የጎደለው ድርጊት በሚፈጽሙበት ወቅት ትዕግሥትና ደግነት ማሳየት አለብን። “ፍቅር አይቀናም”፤ በመሆኑም እውነተኛ ፍቅር ካለን የሌሎችን ንብረት ወይም በጉባኤ ያገኙትን መብት አንመኝም። በተጨማሪም ፍቅር ካለን ጉራ አንነዛም ወይም አንታበይም። ደግሞም “ትዕቢተኛ ዐይን፣ እብሪተኛ ልብ፣ የክፉዎችም መብራት ኀጢአት ናቸው።”—ምሳሌ 21:4
16, 17. በ1 ቆሮንቶስ 13:5, 6 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
16 ፍቅር በባልንጀሮቻችን ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ ይረዳናል። አንዋሻቸውም፤ ከእነሱ አንሰርቅም፤ እንዲሁም የይሖዋን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንጥስ የሚያደርግ ምንም ነገር አናደርግም። በተጨማሪም ፍቅር የራሳችንን ፍላጎት ብቻ ከማስቀደም ይልቅ ለሌሎች እንድናስብ ያደርገናል።—ፊልጵ. 2:4
17 እውነተኛ ፍቅር በቀላሉ አይበሳጭም፤ እንዲሁም “የበደል መዝገብ የለውም።” ይኸውም ሌሎች በበደሉት ቁጥር ልክ ገቢና ወጪን እንደሚያሰፍር አንድ የሒሳብ ባለሙያ መዝግቦ አይዝም። (1 ተሰ. 5:15) በሌሎች ላይ ቂም የምንይዝ ከሆነ ይሖዋን እናሳዝነዋለን፤ እንዲሁም የተዳፈነ እሳት ሊቀጣጠል እንደሚችል ሁሉ ቂም የምንይዝ ከሆነ ስሜታችን የወጣ ዕለት በእኛም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ያስከትላል። (ዘሌ. 19:18) ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል”፤ በሌላ በኩል ደግሞ “በዓመፅ” ሌላው ቀርቶ የሚጠላን ሰው በደል ወይም ግፍ በሚፈጸምበት ጊዜም ጭምር ‘አንደሰትም።’—ምሳሌ 24:17, 18ን አንብብ።
18. 1 ቆሮንቶስ 13:7, 8 ስለ ፍቅር ምን ያስተምረናል?
18 ጳውሎስ ስለ ፍቅር የሰጠውን ተጨማሪ መግለጫ እስቲ እንመልከት። ፍቅር “ሁሉን ችሎ ያልፋል” ብሏል። አንድ ያስቀየመን ሰው ይቅርታ ቢጠይቀን ፍቅር ይቅር እንድንለው ያነሳሳናል። ፍቅር በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ነገር ‘ሁሉ ያምናል’፤ እንዲሁም ለምናገኘው መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት እንዲኖረን ይረዳናል። ፍቅር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ነገሮች ‘ሁሉ ተስፋ ያደርጋል’፤ ከዚህም ሌላ ስለ ተስፋችን ምክንያት እንድናቀርብ ለሚጠይቁን ሁሉ መልስ እንድንሰጥ ይገፋፋናል። (1 ጴጥ. 3:15) ከዚህም ባሻገር ፈታኝ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ወቅት የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ ተስፋ በማድረግ እንጸልያለን። ፍቅር “ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል”፤ ለምሳሌ በደል ሲፈጸምብን ብሎም ስደትና ሌሎች ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እንጸናለን። በተጨማሪም “ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም።” ምክንያቱም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ለዘላለም ፍቅርን እያንጸባረቁ ይኖራሉ።
ባልንጀራችሁን እንደ ራሳችሁ መውደዳችሁን ቀጥሉ
19, 20. ለባልንጀራችን ፍቅር ማሳየታችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ነው?
19 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ለባልንጀራችን ፍቅር ማሳየታችንን መቀጠል እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ፍቅር ካለን ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ዘር ያላቸውን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እንቀበላለን። ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” እንዳለም ማስታወስ ይገባናል። (ማቴ. 22:39) አምላክም ሆነ ክርስቶስ ባልንጀራችንን እንድንወድ ይጠብቁብናል። ከባልንጀራችን ጋር ባጋጠመን ሁኔታ የተነሳ ፍቅር ማሳየት ቢከብደን አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንዲመራን እንጸልይ። እንዲህ ማድረጋችን የይሖዋን በረከት የሚያስገኝልን ከመሆኑም ሌላ ችግሩን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ መፍታት እንድንችል ይረዳናል።—ሮም 8:26, 27
20 ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ የሚያዘው ሕግ “ንጉሣዊ ሕግ” ተብሎ ተጠርቷል። (ያዕ. 2:8) ጳውሎስ በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ትእዛዛትን ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎች ትእዛዛት በሙሉ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ በሚለው በዚህ ቃል ተጠቃለዋል። ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።” (ሮም 13:8-10) በመሆኑም ለባልንጀራችን ፍቅር ማሳየታችንን መቀጠል ያስፈልገናል።
21, 22. አምላክንና ባልንጀራችንን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?
21 ለባልንጀራችን ፍቅር ስለ ማሳየት በምናስብበት ጊዜ ኢየሱስ “በክፉና በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል፤ ጻድቅ በሆኑና ጻድቅ ባልሆኑ ሰዎች ላይም ዝናብ ያዘንባል” በማለት ስለ አባቱ የተናገረውን ሐሳብ ግምት ውስጥ ማስገባታችን ጥሩ ነው። (ማቴ. 5:43-45) ባልንጀራችን ጻድቅ ሆነም አልሆነ ለእሱ ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ይህን ማድረግ የሚቻልበት ቁልፍ መንገድ የመንግሥቱን ምሥራች ማካፈል ነው። ባልንጀራችን ምሥራቹን በአድናቆት ቢቀበል ግሩም የሆኑ በረከቶችን ያገኛል!
22 ምንም የምንቆጥበው ነገር ሳይኖር ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሱ ብዙ ምክንያቶች አሉን። በተጨማሪም ለባልንጀራችን ፍቅር እንዳለን የምናሳይባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። አምላክንና ባልንጀራችንን መውደዳችን ኢየሱስ እነዚህን አስፈላጊ ነገሮች አስመልክቶ የሰጠውን ትእዛዝ እንደምናከብር ያሳያል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይ ያለውን አፍቃሪ አባታችንን ማስደሰት እንችላለን።