ፍቅር (አጋፔ ) ምን አያደርግም? ምንስ ያደርጋል?
“በጠበቀ ወንድማዊ መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።” — 2 ጴጥሮስ 1:5, 7 አዓት
1. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ለየትኛው የላቀ ባሕርይ ነው?(ለ) ብዙውን ጊዜ “ፍቅር” ተብለው የተተረጎሙት የትኞቹ አራት የግሪክኛ ቃላት ናቸው? በ1 ዮሐንስ 4:8 ላይ የተጠቀሰው የትኛው ፍቅር ነው?
የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው አንድ ባሕርይ ቢኖር ፍቅር ነው። የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች በተጻፉበት በመጀመሪያው የግሪክኛ ቋንቋ ብዙ ጊዜ “ፍቅር” ተብለው የተተረጎሙ አራት ቃሎች አሉ። አሁን የምንመለከተው ፍቅር በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የማይገኘውና በጾታ መሳሳብ ላይ የተመሠረተ ፍቅር ስለሆነው ኤሮስ አይደለም፤ ወይም ደግሞ በሥጋ ዝምድና ላይ የተመሠረተ ፍቅር ስለሆነው ስቶርጂ አይደለም፤ ወይም በመጀመሪያው ርዕስ ላይ ውይይት በተደረገበት በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተው የሞቀ የወዳጅነት መዋደድ ስለሆነው ፊሊያ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ራስ ወዳድ ካለመሆን ጋር አንድ ነው ሊባልለት ስለሚችለው ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት የጠቀሰው በመሠረተ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ፍቅር ስለሆነው አጋፔ ነው። — 1 ዮሐንስ 4:8
2. ስለ ፍቅር (አጋፔ ) የተገለጸ ምን ጥሩ አባባል አለ?
2 ይህን ፍቅር (አጋፔ ) በተመለከተ ፕሮፌሰር ዊልያም ባርክሌይ የአዲስ ኪዳን ቃላት በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “አጋፔ ከአእምሮ ጋር ግንኙነት ያለው ነው:- ሳናስበው በልባችን ውስጥ እንደሚቀሰቀሰው ስሜት [በፊሊያ ረገድ እንደሚያጋጥመው ዓይነት] አይደለም፤ ሆነ ብለን የምንመራበት መሠረታዊ ሥርዓት ነው። አጋፔ ከፈቃድ ጋር ከፍተኛ ግንኙነት አለው። አጋፔ ድልና በጥረት የሚገኝ የሥራ ክንውን ነው። በተፈጥሮው ጠላቱን ወዶ የሚያውቅ ሰው የለም። ጠላትን መውደድ በሁሉም የተፈጥሮ ዝንባሌዎቻችንና ስሜቶቻችን ላይ ድል ማድረግ ማለት ነው። እንዲያውም አጋፔ . . . ሊፈቀር የማይችለውን እንድናፈቅር፣ ደስ የማይሉንን ሰዎች እንድንወድ የሚያደርግ ኃይል ነው።”
3. ኢየሱስ ክርስቶስና ጳውሎስ ስለ ፍቅር አጥብቀው የገለጹት ምንድን ነው?
3 አዎን፣ የይሖዋ አምላክን ንጹሕ አምልኮ ከሌሎች የአምልኮ ዓይነቶች ሁሉ ከሚለዩበት ብዙ ነገሮች ውስጥ አንዱ ይህ ዓይነቱን ፍቅር የሚያጎላ መሆኑ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለቱ ታላላቅ ትዕዛዛት “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፣ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም:- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነበር። (ማርቆስ 12:29–31) ሐዋርያው ጳውሎስም በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 ላይ ይህንኑ ፍቅር አጥብቆ ገልጿል። ፍቅር ያለ እርሱ ምንም ማድረግ አይቻልም ሊባልለት የሚችል ዋነኛ ባሕርይ መሆኑን ከገለጸ በኋላ “እንዲህም ከሆነ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” በማለት ንግግሩን ደምድሟል። (1 ቆሮንቶስ 13:13) ኢየሱስ የተከታዮቹ መለያ ምልክት ፍቅር ነው ማለቱ ተገቢ ነው። — ዮሐንስ 13:35
ፍቅር ምን አያደርግም?
4. ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 13:4–8 ላይ ስለፍቅር ምን ያህል አዎንታዊ ገጽታዎችንና ምን ያህልስ አሉታዊ ገጽታዎችን ጠቅሷል?
4 ፍቅር ምን እንደሚያደርግ ከመናገር ይልቅ ፍቅር ምን እንደማያደርግ መናገር ይቀላል የሚባል አነጋገር አለ። ይህ አነጋገር ጥቂት እውነትነት አለው፣ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ፍቅር በጻፈበት ምዕራፍ በ1 ቆሮንቶስ 13 ቁጥር ከ4 እስከ 8 ላይ ፍቅር የማያደርጋቸው ዘጠኝ ነገሮችንና የሚያደርጋቸውን ሰባት ነገሮችን ዘርዝሯል።
5. “ቅንዓት” ምን ፍቺ ተሰጥቶታል? በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መልካም ትርጉም ተሰጥቶት የተሠራበት እንዴት ነው?
5 ጳውሎስ ፍቅር ምን እንደማያደርግ በመጀመሪያ የተናገረው “አይቀናም” በማለት ነው። ቅንዓት ገንቢና አፍራሽ ገጽታዎች ስላሉት ይህ አባባል ምን ማለት እንደሆነ ጥቂት ማብራሪያ ይጠይቃል። አንድ መዝገበ ቃላት ቅንዓትን “ፉክክርን መታገስ የማይችል” እና “ለእርሱ ብቻ የተወሰኑ መሆንን የሚጠይቅ” በማለት ይፈታዋል። በመሆኑም ሙሴ በዘጸአት 34:14 ላይ “ስሙ ቀናተኛ የሆነ ይሖዋ ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ” ይላል። በዘጸአት 20:5 ላይ ይሖዋ “እኔ ይሖዋ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና” ይላል። በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና” በማለት ጽፏል። — 2 ቆሮንቶስ 11:2
6. ፍቅር ቀናተኛ እንዳልሆነ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ያሳያሉ?
6 ይሁን እንጂ “ቅንዓት” በአብዛኛው መጥፎ ገጽታ ስላለው በገላትያ 5:20 ላይ ከሥጋ ሥራዎች አንዱ እንደሆነ ተመዝግቧል። አዎን፣ እንደዚህ ዓይነቱ ቅንዓት ራስ ወዳድ ስለሆነ ጥላቻን ይወልዳል፣ ጥላቻ ደግሞ የፍቅር ተቃራኒ ነው። ቃየል አቤልን እስከመግደል ድረስ እንዲጠላው ያደረገውና ዮሴፍን አሥሩ ወንድሞቹ ሊገድሉት እስከመፈለግ ድረስ እንዲጠሉት ያደረጋቸው ቅንዓት ነበር። ንጉሥ አክአብ የናቡቴን የወይን አትክልት ለራሱ ለማድረግ እንደተመኘው ፍቅር የሌሎችን ንብረት ወይም ጥቅም በቅናት ዓይን እንድንመለከት አያደርግም። — 1 ነገሥት 21:1–19
7. (ሀ) ይሖዋ በትምክህተኝነት እንደማይደሰት የሚያሳየው አንድ አጋጣሚ ምንድን ነው? (ለ) ፍቅር ሳያስበውም እንኳን በትምክህት የማይናገረው ለምንድን ነው?
7 ጳውሎስ ቀጥሎም ፍቅር “አይመካም ” በማለት ይነግረናል። ትምክህት ትምክህተኛውን ግለሰብ ከሌሎች ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ አድርጎ እንዲመለከት ስለሚያደርገው ፍቅር እንደጎደለው ያሳያል። ንጉሥ ናቡከደነፆር በትምክህት በተናገረ ጊዜ ይሖዋ እንዴት እንዳዋረደው ስናይ እርሱ በትምክህተኞች እንደማይደሰት ግልጽ ይሆንልናል። (ዳንኤል 4:30–35) ብዙውን ጊዜ ሰው ባከናወነው ሥራ ወይም በንብረቱ ምክንያት በትምክህት የሚናገረው ሳይታወቀው ነው። አንዳንዶች በክርስቲያናዊ አግልግሎታቸው በሚያገኙት ስኬት በትምክህት መናገር ይቀናቸው ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ 50,000 ዶላር ያህል የፈጀ አውቶሞቢል መግዛቱን ለጓደኞቹ ለመንገር ስልክ እንደደወለው አንድ ሽማግሌ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ትምክህተኛው ግለሰብ በአድማጮቹ ዘንድ ከሌሎች በላይ የሆነ ስለሚያስመስለው ፍቅር የጎደለው ነው።
8. (ሀ) ይሖዋ በትዕቢት ስለተነፉ ሰዎች ያለው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) ፍቅር እንደዚህ የማያደርገው ለምንድን ነው?
8 ከዚህም ሌላ ፍቅር “አይታበይም ” ተብለናል። በትዕቢት የተወጠረ ወይም ኩሩ የሆነ ሰው ፍቅር በጎደለው መንገድ ራሱን ከሌሎች በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነቱ የአእምሮ ዝንባሌ በጣም ጥበብ የጎደለው ነው፤ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ፀጋን ይሰጣል።” (ያዕቆብ 4:6) የፍቅር ተግባር ግን የዚህ ቀጥተኛ ተቃራኒ ነው፤ ፍቅር ሌሎች ከእርሱ በላይ እንደሆኑ ይቆጥራል። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2:2, 3 ላይ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር” በማለት ጽፎአል። እንዲህ ዓይነቱ የአእምሮ ዝንባሌ ሌሎች የተዝናና መንፈስ እንዲኖራቸው ሲያደርግ ትዕቢተኛ ሰው ግን በኩራቱ ሌሎች እንዲሸማቀቁ ያደርጋል።
9. ፍቅር የማይገባውን የማያደርገው ለምንድን ነው?
9 በተጨማሪም ጳውሎስ ፍቅር “የማይገባውን አያደርግም ” ይለናል። እዚህ ላይ “የማይገባ” ተብሎ የተተረጎመው “ኢንዲሰንት” ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል መዝገበ ቃላት የሚሰጡት ፍቺ “ለጥሩ ሥነ ሥርዓት ወይም ለጥሩ ሥነ ምግባር በጣም ተገቢ ያልሆነ ወይም ቀፋፊ የሆነ” የሚል ነው። የማይገባ ጠባይ የሚያሳይ ሰው ስለሌሎች ስሜት ደንታ የለውም። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የግሪክኛውን ቃል “ባለጌ” በማለት ይተረጉሙታል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተገቢ የሆነውንና ለዛ ያለውን ነገር ያንቋሽሸዋል። ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየት ማለት ሌሎችን የሚያስቀይሙ ወይም የሚዘገንኑ የብልግና ወይም ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ሁሉ ማራቅ ማለት ነው።
ፍቅር የማያደርጋቸው ሌሎች ነገሮች
10. ፍቅር የራሱን ጥቅም ብቻ የማይፈልግ የሆነው በምን መንገድ ነው?
10 ቀጥሎም ፍቅር “የራሱን ጥቅም ብቻ ፈላጊ አይደለም (የ1980 ትርጉም)” ተብለናል። ይህም ጉዳዩ የግል ጥቅማችንንና የሌሎች ሰዎችን ጥቅም የሚመለከት በሚሆንበት ጊዜ ነው። ሐዋርያው በሌላ ሥፍራ ላይ “ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን . . . ይመግበዋል ይከባከበውማል” ብሏል። (ኤፌሶን 5:29) ይሁንና የራሳችን ጥቅም የሌሎችን የሚሻማ በሚሆንበት ጊዜና ጉዳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓትን የማያስጥስ ከሆነ የሌላውን ሰው ምርጫ በመጠበቅ አብርሃም በወንድሙ ልጅ በሎጥ ረገድ እንዳደረገው ማድረግ ይኖርብናል። — ዘፍጥረት 13:8–11
11. ፍቅር አይበሳጭም ማለት ምን ማለት ነው?
11 በተጨማሪም ፍቅር ቶሎ አይቀየምም። ስለዚህ ጳውሎስ ፍቅር “አይበሳጭም” ይለናል። ፍቅር ቆዳው ስስ አይደለም። ፍቅር ራሱን ይገዛል። በተለይም የተጋቡ ባልና ሚስት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የትዕግሥት ማለቅንና ቁጣን በሚያመለክት ድምፅ ወይም አንዱ በሌላው ላይ በመጮህ እንዳይናገሩ በመጠንቀቅ ይህን ምክር ልብ ሊሉት ይገባል። በቀላሉ ለመበሳጨት የምንችልባቸው ሁኔታዎች ስላሉ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። . . . የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ [ያስተምር አዓት]” በማለት መክሮታል። — 2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25
12. (ሀ) ፍቅር በደልን የማይቆጥረው በምን መንገድ ነው? (ለ) በደልን መቁጠር ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
12 ጳውሎስ ፍቅር የማያደርጋቸውን ነገሮች መዘርዘሩን በመቀጠል “ፍቅር . . . በደልን አይቆጥርም” ብሏል። ይህ ማለት በደል ምን ማለት እንደሆነ አይገባውም ማለት አይደለም። ከባድ በደል ሲደርስብን እንዴት ልንይዘው እንደሚገባ ኢየሱስ ገልጾአል። (ማቴዎስ 18:15–17) ይሁን እንጂ ፍቅር አኩርፈንና ቂም እንደያዝን እንድንቀጥል አይፈቅድልንም። በደልን አለመቁጠር ማለት ይቅር ባይ መሆንና ጉዳዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ መንገድ ከተፈታ በኋላ ጨርሶ መርሳት ማለት ነው። አዎን፣ ራሳችሁን አታሰቃዩ ወይም ስለበደሉ መላልሳችሁ በማሰብ ወይም የበደል መዝገብ በመያዝ ራሳችሁን አትበድሉ!
13. በዓመፃ መደሰት ማለት ምን ማለት ነው? ፍቅር እንዲህ ሊያደርግ የማይችለውስ ለምንድን ነው?
13 ከዚህም በላይ ፍቅር “በዓመፃ ደስ አይለውም።” ዓመፅ ከሞላባቸውና የጾታ ስሜትን ለመቀስቀስ ተብለው ከሚዘጋጁ ሥዕሎችና ጽሑፎች፣ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ለመረዳት እንደምንችለው ዓለም በዓመፃ ደስ ይለዋል። እንዲህ ዓይነቱ ደስታ የአምላክን የጽድቅ ሥርዓቶችም ሆነ የሌሎችን ደህንነት ከምንም የማይቆጥር ራስ ወዳድ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ራስ ወዳድ ደስታ በሥጋ መዝራት ስለሆነ ጊዜው ሲደርስም ከሥጋ መበስበስን ያሳጭዳል። — ገላትያ 6:8
14. ፍቅር አይወድቅም ብሎ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚቻለው ለምንድን ነው?
14 አሁን ደግሞ ፍቅር የማያደርገው የመጨረሻው ነገር ይኸውና:- “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።” ፍቅር ፈጽሞ የማይወድቅበት ወይም የማያከትምበት አንደኛው ምክንያት አምላክ ፍቅር ስለሆነና እርሱ “የዘላለም ንጉሥ” ስለሆነ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) ሮሜ 8:38, 39 ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር እንደማይወድቅ ያረጋግጥልናል:- “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቻለሁ።” በተጨማሪም ፍቅር ምንም የሚያቅተው ነገር ስለሌለ አይወድቅም። ፍቅር ማንኛውንም ወቅትና ማንኛውንም ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም ይችላል።
ፍቅር የሚያደርጋቸው ነገሮች
15. ጳውሎስ ስለ ፍቅር አዎንታዊ ገጽታዎች በሚዘረዝርበት ጊዜ ትዕግሥትን በመጀመሪያ የጠቀሰው ለምንድን ነው?
15 አሁን ደግሞ ፍቅር ስለሚያደርጋቸው ነገሮች ሲዘረዝር ጳውሎስ “ፍቅር ይታገሣል” በማለት ይጀምራል። ታጋሽነት ማለትም እርስ በርስ መቻቻል ከሌለ ክርስቲያናዊ ህብረት ሊኖር አይችልም ተብሏል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችንና አለፍጽምናችንና ድክመቶቻችን ለሌሎች ሰዎች ፈተና ስለሚሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅር ምን እንደሚያደርግ ሲዘረዝር ይህን የፍቅር ገጽታ አስቀድሞ መጥቀሱ አያስደንቅም!
16. የቤተሰብ አባሎች እርስ በርሳቸው ደግነት ሊያሳዩ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?
16 ጳውሎስ ፍቅር “ደግ ነው” በማለት ይናገራል። (የ1980 ትርጉም) ይህም ማለት ፍቅር ለመርዳት ዝግጁ የሆነ፣ ደግ አሳቢ፣ ለሰው አሳቢ ነው ማለት ነው። ደግነት በትናንሽና በትላልቅ ነገሮች ይገለጻል። መልካም ጎረቤት የነበረው ሳምራዊ ሰው ወንበዴዎች አድፍጠው ለዘረፉት ሰው ደግነት እንዳሳየ ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 10:30–37) ፍቅር “እባክህ” ማለት ያስደስተዋል። “እንጀራ አምጪ” ብሎ መናገር ትዕዛዝ ነው። “እባክሽ” የሚል ቃል ማስቀደም ግን ጥያቄ ያደርገዋል። ባሎች በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም:- “እናንተም ባሎች ሆይ፣ ጸሎታችሁ እንዳይታገድ ከእነርሱ ጋር በእውቀት መኖራችሁን ቀጥሉ፤ ለደካማ ዕቃ እንደምታደርጉት ሴትን በክብር ያዙ፤ ይገባናል የማንለውን የሕይወት ስጦታ አብራችሁ ወራሽ ናችሁና” በማለት የተሰጠውን ምክር ሲሠሩበት ለሚስቶቻቸው ደግ ይሆናሉ። ሚስቶች ደግሞ “ጥልቅ አክብሮት” የሚያሳዩ ከሆነ ለባሎቻቸው ደግ ይሆናሉ። (ኤፌሶን 5:33 አዓት) አባቶች በኤፌሶን 6:4 ላይ “እናንተ አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” የሚለውን ምክር ሲከተሉ ለልጆቻቸው ደግ ይሆናሉ።
17. ፍቅር ከእውነት ጋር ደስ የሚለው በምን ሁለት መንገዶች ነው?
17 ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል” እንጂ በዓመፃ አይደሰትም። ፍቅርና እውነት ጎን ለጎን የሚሄዱ ነገሮች ናቸው። አምላክ ፍቅር ነው፤ የዚያኑ ያህልም “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝሙር 31:5) ፍቅር እውነት በሐሰት ላይ ድል ሲያደርግና ሐሰት ሲጋለጥ ማየት ደስ ይለዋል፤ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ አምላኪዎች በቁጥር እያገኙት ላለው ጭማሪ ምክንያቱ በከፊል ይኸው ነው። ይሁን እንጂ እውነት ከዓመፃ ጋር ስለተነፃፀረ ፍቅር ከጽድቅ ጋር ደስ ይለዋል የሚለው አስተሳሰብም ያስኬዳል። የይሖዋ አምላኪዎች ታላቂቱ ባቢሎን በምትወድቅበት ጊዜ ደስ እንዲላቸው እንደታዘዙት ሁሉ ጽድቅ ድል ሲያደርግ ፍቅር ደስ ይለዋል። — ራእይ 18:20
18. ፍቅር ሁሉን ችሎ የሚታገሠው በምን መልኩ ነው?
18 ጳውሎስ በተጨማሪም ፍቅር “ሁሉን ይታገሣል” በማለት ይነግረናል። ኪንግደም ኢንተርሊኒየር እንደሚገልጸው ሐሳቡ ፍቅር ሁሉን ነገር እንደሚሸፍን ለመግለጽ ነው። ክፉ ሰዎች እንደሚያደርጉት ፍቅር የወንድሙን “ገመና አያወጣም።” (መዝሙር 50:20፤ ምሳሌ 10:12፤ 17:9) አዎን፣ እዚህ ላይ ለማስተላለፍ የተፈለገው ሐሳብ በ1 ጴጥሮስ 4:8 ላይ ከተጠቀሰው ጋር አንድ ነው:- “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” እርግጥ አንድ ሰው በይሖዋና በክርስቲያን ጉባኤ ላይ የተሠራ ከባድ ኃጢአትን እንዳይሸፍን ታማኝነት ሊጠብቀው ይገባል።
19. ፍቅር ሁሉን ነገር የሚያምነው በምን መንገድ ነው?
19 ከዚህም በላይ ፍቅር “ሁሉን ያምናል።” ፍቅር ገንቢና አዎንታዊ ነው እንጂ አፍራሽና አሉታዊ አይደለም። ይህ ማለት ግን ፍቅር በቀላሉ የሚታለል ነው ማለት አይደለም። ፍቅር ስሜት የሚቀሰቅሱ አነጋገሮችን ለማመን ፈጣን አይደለም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በአምላክ እምነት እንዲኖረው ከፈለገ ለማመን ፍላጎት ያለው መሆን አለበት። ስለዚህ ፍቅር ተጠራጣሪና ስህተት ፈላላጊ አይደለም። በድርቅና አምላክ የለም እንደሚለው አምላክ የለም ባይ፣ ወይም ከየት እንደመጣን፣ ለምን እንደተፈጠርንና መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል እርግጡን ማወቅ አይቻልም ብሎ እንደሚደርቀውና ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም ብሎ እንደሚያምነው ሰው አይደለም። የአምላክ ቃል እነዚህን ሁሉ ነገሮች በተመለከተ አስተማማኝ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ፍቅር የማያስፈልግ ጥርጣሬ የሚያሳድር ሳይሆን እምነት የሚያሳድር በመሆኑ ሌላውን ለማመን ዝግጁ ነው።
20. ፍቅር ከተስፋ ጋር የሚገናኘው እንዴት ነው?
20 ሐዋርያው ጳውሎስ ጨምሮም ፍቅር “ሁሉን ተስፋ ያደርጋል” በማለት ያረጋግጥልናል። ፍቅር አዎንታዊ እንጂ አፍራሽ ስላልሆነ በአምላክ ቃል ውስጥ ባሉት የተስፋ ቃሎች ሁሉ ላይ ጠንካራ እምነት አለው። “የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም እንዲካፈል በተስፋ ሊያበራይ ስለሚገባው” ተብሎ ተነግሮናል። (1 ቆሮንቶስ 9:10) ፍቅር ሁሉን አማኝ ስለሆነ ተስፋ አድራጊና ሁልጊዜም ጥሩ ነገርን ተስፋ የሚያደርግ ነው።
21. ፍቅር በሁሉ እንደሚጸና ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማረጋገጫ አለ?
21 በመጨረሻም ፍቅር “በሁሉ ይጸናል” የሚል ዋስትና ተሰጥቶናል። ፍቅር በሁሉ ሊጸና የሚችለው ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ እንደሚከተለው ብሎ በነገረን ምክንያት ነው:- “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” ፍቅር በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በፈተና የጸኑ የአምላክ አገልጋዮችን ምሳሌነት፣ በዕብራውያን 12:2, 3 ላይ ማሳሰቢያ እንደተሰጠንም ከእነርሱም ዋነኛ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንመለከት ያደርገናል።
22. የአምላክ ልጆች እንደመሆናችን መጠን ሁልጊዜ ሊያሳስበን የሚገባው ምን የላቀ ባሕርይን የማሳየት ጉዳይ ነው?
22 በእርግጥም ፍቅር (አጋፔ ) ስለማያደርጋቸውና ስለሚያደርጋቸው ነገሮች በተገለጸልን መሠረት እኛ ክርስቲያን የይሖዋ ምስክሮች ልንኮተኩተው የሚያስፈልገን የላቀ ባሕሪ ነው። እኛም የአምላክ ልጆች በመሆን ይህን የአምላክ መንፈስ ፍሬ ማሳየት ምንጊዜም የሚያሳስበን ይሁን። እንዲህ ማድረግ አምላክን መምሰል ነው፣ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” መባሉን አስታውሱ።
ታስታውሳለህን?
◻ ኢየሱስ ክርስቶስና ጳውሎስ ፍቅር የላቀ ባሕርይ መሆኑን የገለጹት እንዴት ነው?
◻ ፍቅር የማይቀናው በምን መንገድ ነው?
◻ ፍቅር ‘ሁሉን ችሎ የሚታገሠው’ እንዴት ነው?
◻ ፍቅር ለሁልጊዜ አይወድቅም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ ፍቅር ከእውነት ጋር የሚደሰትባቸው ሁለት መንገዶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፍቅር (አጋፔ )
ምን አያደርግም? ምንስ ያደርጋል?
1. አይቀናም 1. ይታገሣል
2. በትምክህት አይናገርም 2. ደግ ነው
3. አይታበይም 3. ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል
4. የማይገባውን አያደርግም 4. ሁሉን ችሎ ያሳልፋል
5. የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግም 5. ሁሉን ያምናል
6. አይበሳጭም 6. ሁሉን ተስፋ ያደርጋል
7. በደልን አይቆጥርም 7. በሁሉ ይጸናል
8. በዓመፃ ደስ አይለውም
9. ለሁልጊዜ አይወድቅም
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናቡከደነፆር በትምክህት በመናገሩ ይሖዋ አዋርዶታል