-
ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ?መጠበቂያ ግንብ—2010 | ጥቅምት 15
-
-
‘ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት’ የተዘጋጁ ስብስባዎች
13. (ሀ) ስብሰባዎቻችን በተሰብሳቢዎቹ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባል? (ለ) ሽማግሌዎች በተለይ የትኛውን ጥያቄ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል?
13 ጳውሎስ የጉባኤ ስብሰባዎች ዋነኛ ዓላማ ተሰብሳቢዎቹን ‘ማነጽ፣ ማበረታታትና ማጽናናት’ እንደሆነ ገልጿል።c (1 ቆሮ. 14:3) በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች በስብሰባዎች ላይ የሚያቀርቧቸው ክፍሎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የሚያንጹና የሚያጽናኑ እንዲሆኑ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን ለመመለስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ከተከታዮቹ ጋር ያደረገውን ስብሰባ እንመልከት።
14. (ሀ) ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ስብሰባ ከማድረጉ በፊት ምን ተከስቶ ነበር? (ለ) ሐዋርያቱ ‘ኢየሱስ ቀርቦ’ ሲያነጋግራቸው እፎይታ የተሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
14 በመጀመሪያ ከዚህ ስብሰባ በፊት የነበሩትን ሁኔታዎች እንመልከት። ኢየሱስ ከመገደሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ሐዋርያቱ ‘ጥለውት የሸሹ’ ሲሆን አስቀድሞ እንደተነገረው ‘ሁሉም ወደየቤታቸው ተበታተኑ።’ (ማር. 14:50፤ ዮሐ. 16:32) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ግን በሐዘን የተዋጡትን ሐዋርያቱን በአንድ ለየት ያለ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋበዛቸው።d ከዚያም “አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወደሚገኘው፣ ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ።” እዚያ ሲደርሱም ‘ኢየሱስ ቀርቦ’ አነጋገራቸው። (ማቴ. 28:10, 16, 18) ሐዋርያቱ ኢየሱስ ቅድሚያውን ወስዶ ስላነጋገራቸው ትልቅ እፎይታ ተሰምቷቸው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ኢየሱስ በስብሰባው ላይ ምን ነጥቦችን አንስቶ ይሆን?
15. (ሀ) ኢየሱስ በስብሰባው ወቅት ምን ነጥቦችን አነሳ? ምንስ አላደረገም? (ለ) ስብሰባው በሐዋርያቱ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?
15 ኢየሱስ ንግግሩን የጀመረው “ሥልጣን ሁሉ . . . ተሰጥቶኛል” በማለት ነበር። ከዚያም ለተከታዮቹ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ተልዕኮ ሰጣቸው። በመጨረሻም “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ፍቅር የሚንጸባረቅበት ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:18-20) ሆኖም ኢየሱስ በዚህ ወቅት ምን እንዳላደረገ አስተዋልክ? በዚህ ስብሰባ ላይ ለሐዋርያቱ እርማት አልሰጣቸውም፤ አሊያም ደግሞ ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን እንደሚጠራጠር የሚያሳይ ወይም እምነታቸው ደክሞ የነበረበትን ወቅት በማስታወስ ይበልጥ በጥፋተኝነት ስሜት እንዲዋጡ የሚያደርግ ነገር አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከባድ ኃላፊነት በመስጠት እሱም ሆነ አባቱ እንደሚወዷቸው በድጋሚ አረጋግጦላቸዋል። ኢየሱስ ያደረገው ነገር በሐዋርያቱ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረባቸው? በእጅጉ በመታነጻቸው፣ በመበረታታታቸውና በመጽናናታቸው ይህ ስብሰባ ከተካሄደ ብዙም ሳይቆይ ‘ምሥራቹን ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን መቀጠል’ ችለዋል።—ሥራ 5:42
16. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ስብሰባዎች መንፈስን የሚያድሱ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?
16 እንደ ኢየሱስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ሽማግሌዎችም ስብሰባዎችን የሚመለከቷቸው ይሖዋ ለሕዝቡ የማይነጥፍ ፍቅር እንዳለው ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ለማረጋገጥ እንደሚያስችሏቸው አጋጣሚዎች አድርገው ነው። (ሮም 8:38, 39) በመሆኑም ሽማግሌዎች በስብሰባዎች ላይ ክፍል ሲያቀርቡ ትኩረት የሚያደርጉት በወንድሞቻቸው ጠንካራ ጎኖች እንጂ በድክመቶቻቸው ላይ አይደለም። የወንድሞቻቸውን ውስጣዊ ዝንባሌ አይጠራጠሩም። ከዚህ ይልቅ ሽማግሌዎች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ይሖዋን እንደሚወዱና ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እንደሚጥሩ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነገር ይናገራሉ። (1 ተሰ. 4:1, 9-12) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ለጉባኤው በአጠቃላይ እርማት መስጠት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ መስተካከል የሚያስፈልጋቸው ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ከሆኑ ግን ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ምክር ለሚመለከታቸው ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ቢሰጥ የተሻለ ነው። (ገላ. 6:1፤ 2 ጢሞ. 2:24-26) ሽማግሌዎች ለጉባኤው በአጠቃላይ ንግግር ሲያቀርቡ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ምስጋናቸውን ለመግለጽ ይጥራሉ። (ኢሳ. 32:2) ስብሰባው ሲያበቃ ሁሉም ተሰብሳቢዎች መንፈሳቸው እንደታደሰና እንደተነቃቁ እንዲሰማቸው በሚያደርግ መንገድ ለመናገር ጥረት ያደርጋሉ።—ማቴ. 11:28፤ ሥራ 15:32
-
-
ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ?መጠበቂያ ግንብ—2010 | ጥቅምት 15
-
-
c በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ “ማበረታታት” እና “ማጽናናት” በሚሉት ቃላት መካከል ስላለው ልዩነት ሲያብራራ “ማጽናናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “[ከማበረታታት] ይበልጥ ልባዊ አሳቢነት” እንደሚንጸባረቅበት ገልጿል።—ከዮሐንስ 11:19 ጋር አወዳድር።
-