አምላክ ድርጅት አለው?
የአምላክ ፍጥረት በሙሉ በሥርዓት የተደራጀ መሆኑን በግልጽ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ “ያልተወሳሰበ” የሚባለው አንድ የፈንገስ ሴል በአስደናቂ ሁኔታ የተደራጀ ነው። ይህ ሴል የተገነባባቸው የተለያዩ ክፍሎች ብዛት አንድ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ከተገነባባቸው የተለያዩ ክፍሎች ብዛት ጋር እኩል ነው። ሆኖም በሚያስፈልጉበት ቦታ ላይ የሚገኙት ሁሉም የሴሉ ክፍሎች አምስት ማይክሮንa ስፋት ባለው ክብ ነገር ውስጥ ተቀምጠዋል። በተጨማሪም የፈንገስን ሴሎች ከአውሮፕላን ልዩ የሚያደርጋቸው መባዛት መቻላቸው ነው። እንዴት ያለ አስደናቂ ሥርዓትና አደረጃጀት ነው!—1 ቆሮንቶስ 14:33
እንዲህ ያለ የተደራጀ ሁኔታ በግልጽ የሚታየው በምድር ባሉ ፍጥረታት ላይ ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊው ዓለምም ከፈጣሪ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ መሆኑን ያመለክታል። ነቢዩ ዳንኤል በሰማይ በአምላክ የፍርድ ጉባኤ ፊት በራእይ ስለተመለከታቸው እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት ሲናገር “ሺህ ጊዜ ሺሆች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል” ብሏል። (ዳንኤል 7:9, 10) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ይኸውም ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ የሆኑት እነዚህ መላእክት አምላክ እዚህ ምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን ለመርዳት ሲል የሚነግራቸውን ነገር ለመስማትና ለመታዘዝ ምን ያህል የተደራጁ መሆን እንደሚኖርባቸው ለማሰብ ሞክር!—መዝሙር 91:11
ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ታላቅ አደራጅ ቢሆንም ምንም ዓይነት ስሜት የሌለው ወይም ድርቅ ያለ ሕግ የሚያወጣ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ፍጥረታቱ ደኅንነት የሚያስብና አፍቃሪ የሆነ ደስተኛ አምላክ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ 1 ጴጥሮስ 5:7) የጥንቱን የእስራኤል ብሔርና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ከያዘበት መንገድ ይህን ሁኔታ በግልጽ ማየት ይቻላል።
በሚገባ የተደራጀው የጥንቱ የእስራኤል ብሔር
ይሖዋ አምላክ ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ እስራኤላውያንን ለማደራጀት በሙሴ ተጠቅሟል። እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ በቆዩበት ወቅት እንዲሰፍሩ የተደረገበትን መንገድ ብቻ እንኳ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ድንኳኑን በፈለገበት ቦታ እንዲተክል ቢፈቀድለት ኖሮ ምን ያህል ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይሖዋ እያንዳንዱ ነገድ የት መስፈር እንዳለበት የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ ለብሔሩ ሰጥቷል። (ዘኍልቍ 2:1-34) በተጨማሪም የሙሴ ሕግ ስለ ጤናና ስለ ንጽሕና አጠባበቅ የሚገልጹ ዝርዝር ደንቦችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሰውን ዓይነ ምድር ከማስወገድ ጋር በተያያዘ የተሰጠው ሕግ ይገኝበታል።—ዘዳግም 23:12, 13
እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በገቡ ጊዜ በብዙ መንገዶች በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ ብሔር ነበሩ። ብሔሩ በ12 ነገዶች ተከፋፍሎ የነበረ ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱ ነገድ የራሱ የሆነ የመሬት ውርስ ነበረው። ይሖዋ በሙሴ በኩል ለብሔሩ የሰጠው ሕግ እያንዳንዱን የሕይወታቸውን ዘርፍ ማለትም አምልኮን፣ ጋብቻን፣ ቤተሰብን፣ ትምህርትን፣ ንግድን፣ አመጋገብን፣ ግብርናን፣ የእንስሳ አያያዝንና እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚዳስስ ነበር።b ምንም እንኳ አንዳንዶቹ ሕጎች አንድን ጉዳይ ለይተው የሚጠቅሱና ዝርዝር መመሪያዎችን የያዙ ቢሆኑም ሁሉም ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን አሳቢነት የሚያሳዩ እንዲሁም ለደስታቸው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ነበሩ። እስራኤላውያን የፍቅር መግለጫ የሆኑትን እነዚህን መመሪያዎች ጠብቀው በመኖር የይሖዋን ልዩ ሞገስ ማግኘት ችለው ነበር።—መዝሙር 147:19, 20
ሙሴ ልዩ ችሎታ ያለው መሪ መሆኑ ባይካድም ይህን ኃላፊነቱን በተሳካ ሁኔታ መወጣት አለመወጣቱ የተመካው በነበረው አመራር የመስጠት ችሎታ ላይ ሳይሆን ለአምላክ ድርጅት ታማኝ በመሆኑ ላይ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ በምድረ በዳው ውስጥ የትኛውን መንገድ መከተል እንዳለባቸው የወሰነው እንዴት ነበር? ይሖዋ ቀን ቀን በደመና ዓምድ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ አማካኝነት የሚሄዱበትን አቅጣጫ ይመራቸው ነበር። (ዘፀአት 13:21, 22) ምንም እንኳ አምላክ በሰዎች የተጠቀመ ቢሆንም ሕዝቡን ያደራጅና ይመራ የነበረው ይሖዋ ራሱ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር።
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በሚገባ የተደራጁ ነበሩ
ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት በቅንዓት በመስበካቸው የተነሳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በእስያና በአውሮፓ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የክርስቲያን ጉባኤዎች ተቋቁመው ነበር። ምንም እንኳ እነዚህ ጉባኤዎች በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚገኙ ቢሆኑም ከሌሎቹ ጉባኤዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ይኸውም የማንም መመሪያ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ በሚገባ የተደራጁ ነበሩ፤ እንዲሁም ሐዋርያት ከሚሰጧቸው ፍቅራዊ አመራር ይጠቀሙ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉን ነገር ‘እንዲያደራጅ’ ቲቶን በቀርጤስ መድቦት ነበር። (ቲቶ 1:5 የ1954 ትርጉም) እንዲሁም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ ሲጽፍ አንዳንድ ወንድሞች ‘የማደራጀት ችሎታ’ እንዳላቸው ወይም ‘አደራጆች’ እንደነበሩ ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 12:28 ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ስፒች፣ ዘ ባይብል ኢን ኮንቴምፖራሪ ላንጉጅ) ይሁን እንጂ እንዲህ ካለው አደረጃጀት በስተጀርባ ያለው ማን ነበር? ጳውሎስ ጉባኤውን ‘ያዋሃደው’ ወይም ‘ያደራጀው’ አምላክ እንደሆነ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 12:24 ዘ ሪቨርሳይድ ኒው ቴስታመንት
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሹመት ያላቸው የበላይ ተመልካቾች በእምነት አጋሮቻቸው ላይ ጌቶች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንፈስ አመራር በመከተል ከሌሎቹ ጋር ‘አብረው የሚሠሩ’ ሰዎች ነበሩ፤ እንዲሁም “ለመንጋው ምሳሌ” መሆን ይጠበቅባቸው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 1:24፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) “የጉባኤው ራስ” ሆኖ የሚያገለግለው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ማንኛውም ሰው ወይም ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት አንድ ቡድን አይደለም።—ኤፌሶን 5:23
በቆሮንቶስ የነበረው ጉባኤ አንዳንድ ነገሮችን ከሌሎች ጉባኤዎች ፈጽሞ በተለየ መንገድ ማከናወን በጀመረ ጊዜ ጳውሎስ “ለመሆኑ የአምላክ ቃል የመጣው ከእናንተ ነው? ወይስ የአምላክ ቃል የደረሰው ወደ እናንተ ብቻ ነው?” በማለት ጽፎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:36) ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ያነሳው አስተሳሰባቸውን ለማስተካከልና የማንም መመሪያ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው እንዲገነዘቡ ለመርዳት ነበር። ጉባኤዎች የሐዋርያትን አመራር በተከተሉ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረና እየተስፋፉ ሄዱ።—የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5
የአምላክ ፍቅር መግለጫ
በዛሬው ጊዜ ስላለው ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል? አንዳንዶች የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል ከመሆን ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም ምንጊዜም በራሱ ድርጅት እንደሚጠቀም በግልጽ ይናገራል። ይሖዋ በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አገልጋዮቹን አደራጅቷቸው ነበር፤ የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም በተደራጀ መንገድ እንዲያመልኩት አድርጎ ነበር።
ታዲያ ይሖዋ አምላክ በጥንት ጊዜ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ሕዝቡን ይመራል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ አይሆንም? አዎ፣ አገልጋዮቹ የተደራጁና አንድነት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረጉ ለእነሱ ፍቅራዊ አሳቢነት እንዳለው የሚያሳይ ነው። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ለመፈጸም በድርጅቱ ይጠቀማል። ታዲያ የይሖዋ ድርጅት ተለይቶ የሚታወቀው እንዴት ነው? እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን መመዘኛዎች ተመልከት።
▪ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድን ሥራ ለማከናወን የተደራጁ ናቸው። (ማቴዎስ 24:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ኢየሱስ የመንግሥቱን ምሥራች ለሁሉም ሰው እንዲሰብኩ ተከታዮቹን አዝዞ ነበር፤ ሆኖም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው አንድ ድርጅት ከሌለ ይህን ሥራ መሥራት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድን ሰው ያለ ማንም እርዳታ ብቻህን ልትመግበው ትችላለህ፤ ነገር ግን በብዙ ሺህ አልፎ ተርፎም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ በቅንጅት የሚሠሩ አባላት ያሉት በሚገባ የተደራጀ ቡድን ያስፈልግሃል። እውነተኛ ክርስቲያኖችም ተልእኳቸውን ለመፈጸም “ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው” (NW) ወይም ‘አንድ ሆነው አምላክን እያገለገሉ ነው።’ (ሶፎንያስ 3:9 የ1954 ትርጉም) አንድነት ያለውና ስምም ሆኖ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ሳይኖር ከብዙ አገሮች፣ ከብዙ ቋንቋዎች እንዲሁም የተለያየ ዘር ካላቸው ሰዎች ጋር የሚያገናኝን ሥራ ማከናወን ይቻላል? መልሱ ግልጽ ነው።
▪ እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ለመደጋገፍና ለመበረታታት በሚያስችል መንገድ የተደራጁ ናቸው። ብቻውን ሆኖ ተራራ የሚወጣ ሰው የትኛውን ተራራ መውጣት እንደሚፈልግ በራሱ ሊወስን ይችላል፤ እንዲሁም ተራራ በመውጣት ረገድ እምብዛም ልምድ የሌላቸውን ሰዎች መርዳት አይጠበቅበትም። ይሁን እንጂ አንድ አደጋ ቢደርስበት ወይም የሆነ ነገር ቢያጋጥመው የሚረዳው ሰው ስለማይኖር ከባድ ችግር ውስጥ መውደቁ አይቀርም። በእርግጥም ራስን ከሌሎች ማግለል ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው። (ምሳሌ 18:1) ክርስቲያኖችም ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም እርስ በርስ መረዳዳትና መደጋገፍ አለባቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20) የክርስቲያን ጉባኤ ሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን ተልእኮ መወጣታቸውን እንዲቀጥሉና ተስፋ እንዳይቆርጡ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ፣ ሥልጠናና ማበረታቻ ይሰጣል። መመሪያ ማግኘትና ፈጣሪን ማምለክ የሚቻልባቸው በተደራጀ መንገድ የሚካሄዱ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከሌሉ አንድ ሰው የይሖዋን መንገዶች ለመማር ወዴት መሄድ ይችላል?—ዕብራውያን 10:24, 25
▪ እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን በአንድነት ለማገልገል በሚያስችል መንገድ የተደራጁ ናቸው። የኢየሱስ በጎች ድምፁን ሲሰሙ በእሱ አመራር ሥር ያሉ “አንድ መንጋ” ይሆናሉ። (ዮሐንስ 10:16) የኢየሱስ በጎች የማንም መመሪያ ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው መንቀሳቀስ በሚችሉ አብያተ ክርስቲያናትና ቡድኖች ውስጥ ተበታትነው አይገኙም፤ ወይም ደግሞ በሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች የተከፋፈሉ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም ‘ንግግራቸው አንድ’ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:10) በአንድነት ለመኖር መመሪያ የሚሆን ደንብ ያስፈልጋል፤ እንዲህ ዓይነት ደንብ እንዲኖር ደግሞ የግድ ድርጅት ያስፈልጋል። የአምላክን በረከት ማግኘት የሚችለው አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር ብቻ ነው።—መዝሙር 133:1, 3
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያላቸው ልባዊ ፍቅር ከላይ የተገለጹትንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መመዘኛዎችን ወደሚያሟላ አንድ ድርጅት እንዲሳቡ እያደረጋቸው ነው። በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የተደራጀና አንድነት ያለው ሕዝብ በመሆን የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም እየጣሩ ነው። አምላክም “በመካከላቸው እኖራለሁ፤ ከእነሱም ጋር እሄዳለሁ፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፣ እነሱ ደግሞ ሕዝቤ ይሆናሉ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:16) አንተም ይሖዋ አምላክን ከድርጅቱ ጋር በመተባበር ካመለክኸው ይህን አስደናቂ በረከት ታገኛለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንድ ማይክሮን ወይም ማይክሮሜትር የአንድ ሜትር አንድ ሚሊዮንኛ ነው።
b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ከገጽ 214-220 ተመልከት።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን የሰፈሩት በሚገባ በተደራጀ መንገድ ነበር
[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ለመፈጸም የግድ ድርጅት ያስፈልጋል
ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት
በአደጋ ለተጎዱ የሚደረግ እርዳታ
ትልልቅ ስብሰባዎች
የአምልኮ ቦታዎች ግንባታ