የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ኅዳር 2018
ከኅዳር 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዮሐንስ 20-21
“ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?”
(ዮሐንስ 21:1-3) ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደገና ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠ። የተገለጠውም በዚህ መንገድ ነበር፤ 2 ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ፣ የገሊላ ቃና ሰው የሆነው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ሌሎች ሁለት ደቀ መዛሙርቱ አብረው ነበሩ። 3 ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው። እነሱም “እኛም አብረንህ እንሄዳለን” አሉት። ወጥተው ሄዱና ጀልባ ላይ ተሳፈሩ፤ በዚያ ሌሊት ግን አንድም ዓሣ አልያዙም።
(ዮሐንስ 21:4-14) ይሁን እንጂ ጎህ ሲቀድ ኢየሱስ መጥቶ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። 5 ከዚያም ኢየሱስ “ልጆቼ፣ የሚበላ ነገር አላችሁ?” አላቸው። እነሱም “የለንም!” ብለው መለሱለት። 6 እሱም “መረቡን ከጀልባዋ በስተ ቀኝ ጣሉት፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነሱም መረቡን ጣሉ፤ ከዓሣውም ብዛት የተነሳ መረቡን መጎተት አቃታቸው። 7 በዚህ ጊዜ፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን ሲሰማ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ስለነበር መደረቢያውን ለበሰና ዘሎ ባሕሩ ውስጥ ገባ። 8 ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ ብዙም ሳይርቁ 90 ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ስለነበሩ በዓሣዎች የተሞላውን መረብ እየጎተቱ በትንሿ ጀልባ መጡ። 9 ወደ ባሕሩ ዳርቻ በደረሱ ጊዜ በከሰል ፍም ላይ የተቀመጠ ዓሣ እንዲሁም ዳቦ አዩ። 10 ኢየሱስ “አሁን ከያዛችሁት ዓሣ የተወሰነ አምጡ” አላቸው። 11 ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጀልባዋ ላይ ወጥቶ በትላልቅ ዓሣዎች የተሞላውን መረብ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ጎተተው፤ የዓሣዎቹም ብዛት 153 ነበር። መረቡ ይህን ያህል ብዙ ዓሣ ቢይዝም አልተቀደደም። 12 ኢየሱስ “ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ” አላቸው። ጌታ መሆኑን አውቀው ስለነበር ከደቀ መዛሙርቱ መካከል “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። 13 ኢየሱስም መጥቶ ዳቦውን አነሳና ሰጣቸው፤ ዓሣውንም አንስቶ እንዲሁ አደረገ። 14 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር።
(ዮሐንስ 21:15-19) ቁርስ በልተው ከጨረሱም በኋላ ኢየሱስ፣ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” አለው። እሱም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። 16 ደግሞም ለሁለተኛ ጊዜ “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ትወደኛለህ?” አለው። እሱም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ግልገሎቼን ጠብቅ” አለው። 17 ለሦስተኛ ጊዜም “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ በጣም ትወደኛለህ?” አለው። ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ “በጣም ትወደኛለህ?” ብሎ ስለጠየቀው አዘነ። በመሆኑም “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ግልገሎቼን መግብ። 18 እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ወጣት ሳለህ ራስህ ለብሰህ ወደፈለግክበት ቦታ ትሄድ ነበር። ስታረጅ ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያለብስሃል፤ ወደማትፈልግበትም ቦታ ይወስድሃል።” 19 ይህን የተናገረው፣ ጴጥሮስ በምን ዓይነት አሟሟት አምላክን እንደሚያከብር ለማመልከት ነበር። ይህን ካለ በኋላ “እኔን መከተልህን ቀጥል” አለው።
nwtsty ለጥናት የሚረዱ መረጃዎች—ዮሐ 21:15, 17
ኢየሱስ፣ ስምዖን ጴጥሮስን . . . አለው፦ በኢየሱስና በጴጥሮስ መካከል ይህ ውይይት የተካሄደው ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ከካደው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ለእሱ ያለውን ስሜት ለማወቅ ሦስት ጥያቄዎችን አቀረበለት፤ ኢየሱስ ይህን ጥያቄ ለሦስተኛ ጊዜ ማንሳቱ ጴጥሮስን ‘አሳዝኖት ነበር።’ (ዮሐ 21:17) በዮሐ 21:15-17 ላይ በሚገኘው ዘገባ ላይ ዮሐንስ አጋፓኦ እና ፊሌኦ የሚሉትን ሁለት የግሪክኛ ግሶች ተጠቅሟል። በአማርኛ ሁለቱም ግሶች ‘መውደድ’ ተብለው ተተርጉመዋል። ኢየሱስ ጴጥሮስን “ትወደኛለህ?” በማለት ሦስት ጊዜ ጠይቆታል። በሦስቱም ጊዜያት ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደሚወደው ተናገረ፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ለእሱ ያለው ፍቅር ጠቦቶች ወይም ‘ግልገሎች’ ተብለው የተገለጹትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመንፈሳዊ እንዲመግብ እና ‘እንዲጠብቅ’ ሊያነሳሳው እንደሚገባ ነግሮታል። (ዮሐ 21:16, 17፤ 1ጴጥ 5:1-3) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ለእሱ ያለውን ፍቅር ሦስት ጊዜ እንዲገልጽ ካደረገ በኋላ በጎቹን የመንከባከብ ኃላፊነት ሰጥቶታል። ኢየሱስ ይህን ማድረጉ፣ ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ ቢክድም ሙሉ በሙሉ ይቅር እንዳለው እርግጠኛ እንዲሆን አድርጎት መሆን አለበት።
ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?፦ “ከእነዚህ አስበልጠህ” የሚለው ሐረግ ከሰዋስው አንጻር በተለያየ መንገድ ሊተረጎም ይችላል። አንዳንድ ምሁራን “እነዚህን ደቀ መዛሙርት ከምትወዳቸው ይበልጥ ትወደኛለህ?” ወይም “እነዚህ ደቀ መዛሙርት ከሚወዱኝ ይበልጥ ትወደኛለህ?” የሚለውን አተረጓጎም ይመርጣሉ። ይሁን እንጂ ይበልጥ ትርጉም የሚሰጠው “ከእነዚህ ነገሮች ይበልጥ ትወደኛለህ?” የሚለው ፍቺ ይመስላል፤ ኢየሱስ ይህን ሲል ደቀ መዛሙርቱ ከያዟቸው ዓሦች ወይም ደግሞ ዓሣ ከማጥመድ ሥራው ይበልጥ ይወደው እንደሆነ መጠየቁ ነበር። በመሆኑም የጥቅሱ አጠቃላይ መልእክት ‘ከቁሳዊ ነገሮች ወይም ከሰብዓዊ ሥራ ይበልጥ ትወደኛለህ? ከሆነ በጎቼን መግብ’ የሚል ሳይሆን አይቀርም። ጴጥሮስ ቀደም ሲል ካደረገው ነገር አንጻር ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይመስላል። ጴጥሮስ ከኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቢሆንም (ዮሐ 1:35-42) ሥራውን ትቶ ኢየሱስን መከተል የጀመረው ወዲያውኑ አይደለም። በመሃሉ ዓሣ ወደ ማጥመድ ሥራው ተመልሶ ነበር። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ሰፋ ያለ ጊዜ የሚወስድበትን ሥራውን ትቶ ‘ሰው አጥማጅ’ እንዲሆን ጠራው። (ማቴ 4:18-20፤ ሉቃስ 5:1-11) ሆኖም ኢየሱስ ከሞተም በኋላ ጴጥሮስ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” ብሎ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሌሎቹም ሐዋርያት አብረውት ሄደዋል። (ዮሐ 21:2, 3) በመሆኑም ኢየሱስ፣ ቁርጥ ውሳኔ የማድረግን አስፈላጊነት ለጴጥሮስ ጠበቅ አድርጎ እየነገረው የነበረ ይመስላል፦ ጴጥሮስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ከፊታቸው የተከመሩት ዓሦች ለሚወክሉት ነገር ይኸውም ዓሣ ለማጥመድ ሥራው ነው? ወይስ የኢየሱስን ጠቦቶች ወይም ተከታዮች በመንፈሳዊ ለመመገቡ ሥራ?—ዮሐ 21:4-8
ለሦስተኛ ጊዜ፦ ጴጥሮስ ጌታውን ሦስት ጊዜ ክዶት ነበር፤ ኢየሱስም ለእሱ ያለውን ፍቅር ሦስት ጊዜ እንዲገልጽ አጋጣሚ ሰጥቶታል። ጴጥሮስ ለኢየሱስ ያለውን ፍቅር ደጋግሞ የገለጸ ሲሆን በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ለቅዱስ አገልግሎት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ በመስጠት ይህን ፍቅሩን እንዲያሳይ አሳስቦታል። ጴጥሮስ ኃላፊነት ካላቸው ሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን ታማኝ የኢየሱስ ተከታዮችን ያቀፈውን የክርስቶስ መንጋ ይመግባል፤ ያጠናክራል እንዲሁም ይጠብቃል። እነዚህ የክርስቶስ ተከታዮች ቅቡዓን ቢሆኑም በመንፈሳዊ መመገብ ያስፈልጋቸዋል።—ሉቃስ 22:32
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዮሐንስ 20:17) ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግኩምና። ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው’ ብለሽ ንገሪያቸው።”
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 20:17
ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ፦ አፕቶሜ የሚለው የግሪክኛ ግስ “መንካት” አሊያም ደግሞ “ጥብቅ አድርጎ መያዝ፤ የሙጥኝ ማለት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “አትንኪኝ” ብለው ተርጉመውታል። ይሁንና ኢየሱስ መግደላዊቷ ማርያም እንዳትነካው እየተከላከለ አልነበረም፤ ምክንያቱም ከሞት ከተነሳ በኋላ ያገኙት ሌሎች ሴቶች ‘እግሩን ሲይዙት’ አልተቃወማቸውም። (ማቴ 28:9) መግደላዊቷ ማርያም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ነው የሚል ስጋት አድሮባት የነበረ ይመስላል። ከጌታዋ ላለመለየት ካላት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ኢየሱስን አጥብቃ ያዘችው። ኢየሱስም የሚሄድበት ጊዜ ገና እንደሆነ ሊያረጋግጥላት ስለፈለገ እሱን ጥብቅ አድርጋ ከመያዝ ይልቅ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄዳ ከሞት መነሳቱን እንድታበስር ነገራት።
(ዮሐንስ 20:28) ቶማስም መልሶ “ጌታዬ፣ አምላኬ!” አለው።
nwtsty ለጥናት የሚረዳ መረጃ—ዮሐ 20:28
ጌታዬ፣ አምላኬ!፦ ቃል በቃል “የእኔ ጌታ እና የእኔ አምላክ [ሆ ቴኦስ]!” አንዳንድ ምሁራን ቶማስ በአድናቆት ተውጦ ይህን ያለው ለኢየሱስ ቢሆንም “ጌታዬ፣ አምላኬ!” ብሎ የጠራው ግን የኢየሱስ አባት የሆነውን ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ይገልጻሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ ጥቅስ መጀመሪያ በተጻፈበት የግሪክኛ ሰዋስው መሠረት፣ ቶማስ እንዲህ ብሎ የጠራው ኢየሱስን መሆን እንዳለበት ይናገራሉ። ያም ቢሆን እንኳ “ጌታዬ፣ አምላኬ!” የሚለውን ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚገኙ ሌሎች ጥቅሶች አንጻር መመልከቱ የተሻለ ነው። ኢየሱስ ቀደም ሲል ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው” የሚል መልእክት ልኮ እንደነበር ዘገባው ስለሚገልጽ ቶማስ ኢየሱስን ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ አድርጎ እንዲያስብ የሚያደርገው ምንም ምክንያት የለም። (ዮሐ 20:17) ቶማስ፣ ኢየሱስ ወደ ‘አባቱ’ ሲጸልይ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” ብሎ እንደጠራው ሰምቷል። (ዮሐ 17:1-3) በመሆኑም ቶማስ ኢየሱስን “አምላኬ” ብሎ የጠራው በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል፦ ኢየሱስን ሁሉን ቻይ አምላክ አድርጎ ባይመለከተውም እንደ “አምላክ” አድርጎ ተመልክቶት ሊሆን ይችላል። (ለዮሐ 1:1 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።*) አሊያም ደግሞ ቶማስ ኢየሱስን የጠራው አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ከይሖዋ የተላኩ መላእክትን በጠሩበት መንገድ ሊሆን ይችላል፤ መላእክት በዚህ መንገድ እንደተጠሩ የሚያሳዩ ዘገባዎችን በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እናገኛለን። ቶማስ፣ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንድን መልአክ፣ ይሖዋ አምላክ እንደሆነ አድርገው የተናገሩባቸው ጊዜያት እንዳሉ የሚገልጹ ዘገባዎችን ሳያነብ አልቀረም። (ከዘፍ 16:7-11, 13፤ 18:1-5, 22-33፤ 32:24-30፤ መሳ 6:11-15 እና 13:20-22 ጋር አወዳድር።) ከዚህ አንጻር ቶማስ ኢየሱስን “አምላኬ” ብሎ የጠራው ኢየሱስ የእውነተኛው አምላክ ተወካይና ቃል አቀባይ መሆኑን አምኖ እንደተቀበለ ለማሳየት ሊሆን ይችላል።
* ለዮሐ 1:1 የተዘጋጀ ለጥናት የሚረዳ መረጃ፦ ቃልም አምላክ ነበር፦ ወይም “ቃልም መለኮት [ወይም “እንደ አምላክ ያለ”] ነበር።” ዮሐንስ እዚህ ላይ የተናገረው ሐሳብ ‘የቃልን’ (ግሪክኛው፣ ሆ ሎጎስ፤ በዚህ ጥቅስ ሥር የሚገኘውን ቃል የሚለውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት) ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስን ባሕርይ የሚገልጽ ነው። ቃል “አምላክ፤ እንደ አምላክ ያለ፤ መለኮት፤ መለኮታዊ አካል” ተብሎ የተጠራው አምላክ ሁሉንም ነገሮች ለመፍጠር የተጠቀመበት የበኩር ልጁ እንደመሆኑ መጠን ከሁሉ የላቀ ቦታ ስላለው ነው። በርካታ ተርጓሚዎች “ቃልም አምላክ [God] ነበር” ብለው በመተርጎም ኢየሱስን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል አድርገውታል። ሆኖም ዮሐንስ “ቃል” ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል ነው ማለቱ እንዳልነበር የሚያሳዩ አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፣ “ቃልም አምላክ ነበር” ከሚለው ዓረፍተ ነገር በፊትም ሆነ በኋላ ያሉት ዓረፍተ ነገሮች ቃል “ከአምላክ ጋር” እንደነበር ይገልጻሉ። በተጨማሪም ቴኦስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በቁጥር 1 እና 2 ላይ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። በመጀመሪያውና በሦስተኛው ላይ ቴኦስ ከሚለው ቃል በፊት የግሪክኛው ጽሑፍ ጠቃሽ አመልካች የሚጨምር ሲሆን በሁለተኛው ላይ ግን ጠቃሽ አመልካች አይጨምርም። በርካታ ምሁራን ከሁለተኛው ቴኦስ በፊት ጠቃሽ አመልካች አለመኖሩ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር እንደሆነ ይስማማሉ። በዚህ አገባብ፣ ጠቃሽ አመልካች ሲጨመር ቴኦስ የሚለው ቃል ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ያመለክታል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ሰዋስዋዊ አወቃቀር፣ ጠቃሽ አመልካች ካልተጨመረ ቴኦስ ባሕርይን ማለትም ‘የቃልን’ ባሕርይ የሚያመለክት ቃል ይሆናል። በመሆኑም በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛና በፈረንሳይኛ የሚገኙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ከአዲስ ዓለም ትርጉም ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ይኸውም ቃል “አምላክ [a god]፤ መለኮት፤ መለኮታዊ አካል፤ መለኮታዊ፤ እንደ አምላክ ያለ” እንደሆነ በሚገልጽ መንገድ ተርጉመውታል። የኮፕቲክ ቋንቋ ቀበሌኛዎች በሆኑት የሳሂዲክና የቦሄሪክ ቋንቋዎች የተዘጋጁት የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ትርጉሞችም (በሦስተኛውና በአራተኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. የተዘጋጁ እንደሆኑ ይገመታል) በዮሐ 1:1 ላይ፣ የመጀመሪያውን ቴኦስ የተረጎሙት ከሁለተኛው ቴኦስ በተለየ መንገድ ሲሆን ይህም በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ያለውን አተረጓጎም የሚደግፍ ነው። እነዚህ አተረጓጎሞች “ቃል” ከአምላክ ጋር ተመሳሳይ ባሕርይ እንዳለው ጎላ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው እንጂ ከአባቱ ማለትም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል እንደሆነ የሚያሳዩ አይደሉም። ከዚህ ጥቅስ ጋር በሚስማማ መልኩ ቆላ 2:9 “መለኮታዊው ባሕርይ በተሟላ ሁኔታ” በክርስቶስ ውስጥ እንደሚኖር ይናገራል። በተጨማሪም 2ጴጥ 1:4 እንደሚለው ከክርስቶስ ጋር አብረው የሚገዙት ተባባሪ ወራሾችም ጭምር “ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች” ይሆናሉ። ከዚህም ሌላ በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ፣ ቴኦስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “አምላክ” ተብለው የሚተረጎሙትና “ኃያል የሆነው፤ ብርቱ የሆነው” የሚል መሠረታዊ ትርጉም እንደሚያስተላልፉ የሚታመኑት ኤል እና ኤሎሂም የሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት አቻ ሆኖ ተሠርቶበታል። እነዚህ የዕብራይስጥ ቃላት ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ፣ ከሌሎች አማልክትና ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ተሠርቶባቸዋል። ቃል “አምላክ (a god)” ወይም “ኃያል የሆነው” መባሉ መሲሑ “ኃያል አምላክ” (“ሁሉን ቻይ አምላክ” አይደለም) ተብሎ እንደሚጠራና ተገዢዎቹ የመሆን መብት ላገኙ ሁሉ “የዘላለም አባት” እንደሚሆን ከሚናገረው ከኢሳ 9:6 ትንቢት ጋር ይስማማል። ደግሞም ይህ ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርገው የአባቱ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቅንዓት” ነው።—ኢሳ 9:7
አንዳንዶች ‘ጌታ’ እና ‘አምላክ’ ከሚሉት ቃላት በፊት የግሪክኛ ጠቃሽ አመልካች መግባቱ፣ እነዚህ ቃላት ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ እንደሚያመለክቱ ያሳያል ብለው ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ እዚህ ጥቅስ ላይ ጠቃሽ አመልካች የገባው በግሪክኛ ሰዋስው ምክንያት ብቻ ሊሆን ይችላል። በግሪክኛ ከስም በፊት ጠቃሽ አመልካች የገባባቸው አንዳንድ ቦታዎች አሉ፤ ለምሳሌ ሉቃስ 12:32 (ቃል በቃል “ትንሹ መንጋ”) እና ቆላ 3:18–4:1 (ቃል በቃል “ሚስቶቹ”፤ “ባሎቹ”፤ “ልጆቹ”፤ “አባቶቹ”፤ “ባሪያዎቹ”፤ “ጌቶቹ”)። በተመሳሳይም 1ጴጥ 3:7 ቃል በቃል ቢተረጎም “ባሎቹ” ተብሎ ይቀመጣል ማለት ነው። በመሆኑም “ጌታዬ፣ አምላኬ!” በሚለው ሐረግ ላይ ጠቃሽ አመልካች መግባቱ ቶማስ በተናገረው ሐሳብ ትርጉም ላይ ለውጥ ላያመጣ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዮሐንስ 20:1-18) በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን መግደላዊቷ ማርያም በማለዳ፣ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብሩ መጣች፤ መቃብሩ የተዘጋበትም ድንጋይ ተንከባሎ አየች። 2 ስለዚህ ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች መጥታ “ጌታን ከመቃብሩ ውስጥ ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው። 3 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ መቃብሩ አመሩ። 4 ሁለቱም አብረው ይሮጡ ጀመር፤ ሆኖም ሌላው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ቀድሞ በመሮጥ መቃብሩ ጋ ደረሰ። 5 ጎንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት የበፍታ ጨርቆቹ እዚያ ተቀምጠው አየ፤ ወደ ውስጥ ግን አልገባም። 6 ከዚያም ስምዖን ጴጥሮስ ተከትሎት መጥቶ መቃብሩ ውስጥ ገባ። የበፍታ ጨርቆቹም በዚያ ተቀምጠው አየ። 7 በራሱ ላይ የነበረው ጨርቅ፣ ከመግነዝ ጨርቆቹ ጋር ሳይሆን ለብቻው ተጠቅልሎ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ አየ። 8 ከዚያም ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደርሶ የነበረው ሌላው ደቀ መዝሙርም ወደ ውስጥ ገባ፤ እሱም አይቶ አመነ። 9 ከሞት መነሳት እንዳለበት የሚናገረውን የቅዱስ መጽሐፉን ቃል ገና አልተረዱም ነበር። 10 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ። 11 ይሁን እንጂ ማርያም እዚያው መቃብሩ አጠገብ ቆማ ታለቅስ ነበር። እያለቀሰችም ወደ መቃብሩ ውስጥ ለማየት ጎንበስ አለች፤ 12 ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክትም የኢየሱስ አስከሬን አርፎበት በነበረው ቦታ አንዱ በራስጌው ሌላው በግርጌው ተቀምጠው አየች። 13 እነሱም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ?” አሏት። እሷም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” አለቻቸው። 14 ይህን ካለች በኋላ ዞር ስትል ኢየሱስን በዚያ ቆሞ አየችው፤ ነገር ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቀችም። 15 ኢየሱስም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ? የምትፈልጊው ማንን ነው?” አላት። እሷም አትክልተኛው ስለመሰላት “ጌታዬ፣ አንተ ከዚህ ወስደኸው ከሆነ የት እንዳደረግከው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው። 16 ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እሷም ዞር ብላ በዕብራይስጥ “ራቦኒ!” አለችው (ትርጉሙም “መምህር!” ማለት ነው)። 17 ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግኩምና። ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው’ ብለሽ ንገሪያቸው።” 18 መግደላዊቷ ማርያም መጥታ “ጌታን አየሁት!” ብላ ለደቀ መዛሙርቱ አበሰረቻቸው፤ እሱ ያላትንም ነገረቻቸው።
ከኅዳር 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | የሐዋርያት ሥራ 1-3
“በክርስቲያን ጉባኤ ላይ መንፈስ ቅዱስ ፈሰሰ”
(የሐዋርያት ሥራ 2:1-8) በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር። 2 ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው። 3 የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ አረፉ፤ 4 ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ ባስቻላቸው መሠረት በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር። 5 በዚያን ጊዜ በምድር ዙሪያ ካለ አገር ሁሉ የመጡ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ነበሩ። 6 ስለዚህ ይህ ድምፅ በተሰማ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እያንዳንዱም ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ። 7 ደግሞም ሕዝቡ እጅግ ተደንቀው እንዲህ አሉ፦ “እንዴ፣ እነዚህ እየተናገሩ ያሉት የገሊላ ሰዎች አይደሉም? 8 ታዲያ እያንዳንዳችን በአገራችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማው እንዴት ነው?
(የሐዋርያት ሥራ 2:14) ጴጥሮስ ግን ከአሥራ አንዱ ጋር ተነስቶ በመቆም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፣ አንድ ማወቅ ያለባችሁ ነገር ስላለ ንግግሬን በጥሞና አዳምጡ።
(የሐዋርያት ሥራ 2:37, 38) ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነክቶ ጴጥሮስንና የቀሩትን ሐዋርያት “ወንድሞች፣ ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሏቸው። 38 ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ነፃ ስጦታ ትቀበላላችሁ።
(የሐዋርያት ሥራ 2:41) ስለዚህ ቃሉን በደስታ የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጨመሩ።
(የሐዋርያት ሥራ 2:42-47) የሐዋርያቱንም ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን ቀጠሉ፤ አንድ ላይ ይሰበሰቡ፣ ምግባቸውንም አብረው ይበሉ እንዲሁም በጸሎት ይተጉ ነበር። ሰው ሁሉ ፍርሃት አደረበት፤ ሐዋርያቱም ብዙ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ያደርጉ ጀመር። 44 ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ ያላቸውም ነገር ሁሉ የጋራ ነበር፤ 45 በተጨማሪም ያላቸውን ሀብትና ንብረት በመሸጥ ገንዘቡን ለሁሉም አከፋፈሉ። ለእያንዳንዱም ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ሰጡ። 46 በየዕለቱም በአንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደሱ አዘውትረው ይገኙ ነበር፤ ምግባቸውንም በተለያዩ ቤቶች ይበሉ የነበረ ሲሆን የሚመገቡትም በታላቅ ደስታና በንጹሕ ልብ ነበር፤ 47 አምላክንም ያወድሱ የነበረ ከመሆኑም በላይ በሰው ሁሉ ፊት ሞገስ አግኝተው ነበር። ይሖዋም የሚድኑ ሰዎችን በየዕለቱ በእነሱ ላይ ይጨምር ነበር።
w86-E 12/1 29 አን. 4-5, 7
ልብን ደስ የሚያሰኙ መዋጮዎች
በ33 ዓ.ም. የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመበት ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ተጠመቁ፤ እነዚህ አዲስ ክርስቲያኖች “ያላቸውን ነገር አብረው ይካፈሉ፣ ምግባቸውንም አብረው ይበሉ እንዲሁም በጸሎት ይተጉ ነበር።” ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? ከተጠመቁ ብዙም ያልቆዩት እነዚህ ክርስቲያኖች ‘የሐዋርያቱን ትምህርት በትኩረት መከታተላቸውን በመቀጠል’ እምነታቸውን ማጠናከር ፈልገው ነበር።—ሥራ 2:41, 42 ግርጌ
የጴንጤቆስጤን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት አይሁዳውያንም ሆኑ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች በዚያ ሊቆዩ ያሰቡት በበዓሉ ወቅት ብቻ ነበር። ሆኖም ከእነዚህ ሰዎች መካከል ወደ ክርስትና የተቀየሩት በኢየሩሳሌም ቆይተው ተጨማሪ ትምህርት በመቅሰም እምነታቸውን ማጠናከር ፈለጉ። በዚህም ምክንያት ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምግብና ማረፊያ በአስቸኳይ ማዘጋጀት አስፈለገ። ከእንግዶቹ መካከል አንዳንዶቹ በቂ ገንዘብ አልያዙም ነበር፤ ሌሎቹ ደግሞ ትርፍ ገንዘብ ይዘው ነበር። በመሆኑም ያላቸውን ነገር አንድ ላይ አሰባስበው እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በመስጠት ለዚያ ወቅት የሚሆን መፍትሔ አበጁ።—ሥራ 2:43-47
እነዚያ ክርስቲያኖች ንብረታቸውን የሸጡትና ያላቸውን ከሌሎች ጋር የተካፈሉት በገዛ ፈቃዳቸው ነበር። ማንም ሰው ንብረቱን እንዲሸጥ ወይም መዋጮ እንዲያደርግ አልተገደደም፤ በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች ድህነትን እያበረታቱም አልነበረም። ጥቅሱ፣ ሀብታም የሆኑት ክርስቲያኖች ንብረታቸውን ሁሉ ሸጠው ድሃ እንደሆኑ አይገልጽም። ከዚህ ይልቅ በወቅቱ ተቸግረው ለነበሩት የእምነት ባልንጀሮቻቸው ስላዘኑ የተወሰነ ንብረት ሸጠው ከሽያጩ ያገኙትን በሙሉ የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ እንዳዋሉት ይጠቁማል።—ከ2 ቆሮንቶስ 8:12-15 ጋር አወዳድር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 3:15) በአንጻሩ ግን የሕይወትን “ዋና ወኪል” ገደላችሁት። አምላክ ግን ከሞት አስነሳው፤ እኛም ለዚህ ነገር ምሥክሮች ነን።
it-2-E 61 አን. 1
ኢየሱስ ክርስቶስ
‘የሕይወት ዋና ወኪል።’ ክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም ሰብአዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፤ በዚህ መንገድ የአባቱ ጸጋ ተገልጿል። ኢየሱስ ሕይወቱን መስጠቱ፣ የተመረጡ የክርስቶስ ተከታዮች በሰማይ ከእሱ ጋር መግዛት እንዲችሉ እንዲሁም በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ሰዎች በምድር ላይ መኖር እንዲችሉ በር ከፍቷል። (ማቴ 6:10፤ ዮሐ 3:16፤ ኤፌ 1:7፤ ዕብ 2:5፤ RANSOM የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) በዚህ መንገድ ለመላው የሰው ዘር ‘የሕይወት ዋና ወኪል [“ገዢ፣” KJ; JB]’ ሆኗል። (ሥራ 3:15) እዚህ ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ስያሜ መሠረታዊ ትርጉሙ “ዋና መሪ” የሚል ነው፤ ቃሉ ሙሴ በእስራኤል “ገዢ” (ሥራ 7:27, 35) እንደሆነ ለመግለጽ ከተሠራበት ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው።
(የሐዋርያት ሥራ 3:19) “ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል
“ይቅር ባይ” አምላክ
14 የይሖዋ ይቅር ባይነት በሐዋርያት ሥራ 3:19 ላይም ተገልጿል:- ‘ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።’ “ይደመሰስ ዘንድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ “ሙልጭ አድርጎ መጥረግን፣ . . . መሰረዝን ወይም ማጥፋትን” ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ ምሑራን እንደሚሉት እዚህ ላይ ያለው አገላለጽ አንድን የእጅ ጽሑፍ ማጥፋትን የሚጠቁም ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጻፍ ይጠቀሙበት የነበረው ቀለም ከካርቦን፣ ከሙጫና ከውኃ የተሠራ ነበር። አንድ ሰው በዚህ ቀለም ሲጽፍ ከቆየ በኋላ ጽሑፉን በእርጥብ ስፖንጅ ሊያጠፋው ይችል ነበር። ይህ የይሖዋን ምሕረት የሚያሳይ ግሩም መግለጫ ነው። ኃጢአታችንን ይቅር በሚልበት ጊዜ በስፖንጅ የማጥፋት ያህል ሙሉ በሙሉ ይደመስሰዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 2:1-21) በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር። 2 ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውንም ቤት ሞላው። 3 የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ አረፉ፤ 4 ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ ባስቻላቸው መሠረት በተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር። 5 በዚያን ጊዜ በምድር ዙሪያ ካለ አገር ሁሉ የመጡ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ነበሩ። 6 ስለዚህ ይህ ድምፅ በተሰማ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እያንዳንዱም ሰው ደቀ መዛሙርቱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ። 7 ደግሞም ሕዝቡ እጅግ ተደንቀው እንዲህ አሉ፦ “እንዴ፣ እነዚህ እየተናገሩ ያሉት የገሊላ ሰዎች አይደሉም? 8 ታዲያ እያንዳንዳችን በአገራችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማው እንዴት ነው? 9 እኛ ከጳርቴና፣ ከሜዶን፣ ከኤላም፣ ከሜሶጶጣሚያ፣ ከይሁዳ፣ ከቀጰዶቅያ፣ ከጳንጦስ፣ ከእስያ አውራጃ፣ 10 ከፍርግያ፣ ከጵንፍልያ፣ ከግብፅ፣ በቀሬና አቅራቢያ ካሉት የሊቢያ አውራጃዎችና ከሮም የመጣን አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጥን ሰዎች፣ 11 የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች ሁላችን ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እየሰማናቸው ነው።” 12 ስለዚህ ሁሉም ተገርመውና ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ይባባሉ ነበር። 13 ይሁን እንጂ ሌሎች “ያልፈላ የወይን ጠጅ ተግተው ነው” በማለት አፌዙባቸው። 14 ጴጥሮስ ግን ከአሥራ አንዱ ጋር ተነስቶ በመቆም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፣ አንድ ማወቅ ያለባችሁ ነገር ስላለ ንግግሬን በጥሞና አዳምጡ። 15 ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለሆነ እነዚህ ሰዎች እናንተ እንዳሰባችሁት አልሰከሩም። 16 ከዚህ ይልቅ ይህ የሆነው በነቢዩ ኢዩኤል በኩል እንዲህ ተብሎ በተነገረው መሠረት ነው፦ 17 ‘አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻው ቀን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ወጣቶቻችሁ ራእዮችን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ 18 በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ እነሱም ትንቢት ይናገራሉ። 19 በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮች፣ በታች በምድር ደግሞ ተአምራዊ ምልክቶች አሳያለሁ፤ ደም፣ እሳትና የጭስ ደመናም ይታያል። 20 ታላቁና ክብራማው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። 21 የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”’
በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ተጣጣር
it-1-E 129 አን. 2-3
ሐዋርያ
የአስቆሮቱ ይሁዳን በመተካት አሥራ ሁለተኛ ሐዋርያ የሆነው ማን ነው? የአስቆሮቱ ይሁዳ በሞተበት ወቅት ታማኝ አልነበረም፤ በዚህም ምክንያት ሐዋርያቱ 11 ብቻ ሆነው ነበር፤ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳበት ወደ ሰማይ እስካረገበት ጊዜ በነበሩት 40 ቀናት ውስጥ በይሁዳ ምትክ ማንንም አልሾመም። ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ሌላ ሰው መምረጥ አስፈላጊ ነው ብለው ያሰቡት ኢየሱስ ካረገበት ዕለት እስከ ጴንጤቆስጤ በዓል ባሉት አሥር ቀናት ውስጥ ነበር፤ ጴጥሮስ የጠቀሰው ጥቅስ እንደሚያመለክተው፣ ይሁዳን መተካት ያስፈለገው ስለሞተ ሳይሆን የክህደት ሥራ በመፈጸሙ ምክንያት ነው። (ሥራ 1:15-22፤ መዝ 69:25፤ 109:8፤ ከራእይ 3:11 ጋር አወዳድር።) ታማኙ ሐዋርያ ያዕቆብ በተገደለ ጊዜ ግን ሐዋርያት እሱን የሚተካ ሐዋርያ ለመሾም እንዳሰቡ የሚገልጽ ዘገባ የለም።—ሥራ 12:2
ጴጥሮስ ከተናገረው ሐሳብ መገንዘብ እንደሚቻለው የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሚሆነው ሰው፣ ክርስቶስን በሚገባ ማወቅ እንዲሁም ላከናወናቸው ሥራዎችና ተአምራት በተለይ ደግሞ ለትንሣኤው የዓይን ምሥክር መሆን እንዳለበት ሐዋርያት ተሰምቷቸው ነበር። ከእነዚህ ብቃቶች አንጻር፣ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሐዋርያት በሌሎች መተካታቸው ይቀጥላል ብሎ መጠበቅ የማይሆን ነገር ነው፤ ከዚህ የተለየ ሁኔታ ሊኖር የሚችለው አምላክ ራሱ ለሐዋርያት ምትክ የሚሆን ሰው ከመረጠ ብቻ ነው። በዚያ ወቅት ግን አስፈላጊውን ብቃት የሚያሟሉ ወንዶች ነበሩ፤ በመሆኑም ከሃዲ የሆነውን የአስቆሮቱ ይሁዳን ሊተኩ የሚችሉ ሁለት ሰዎች ቀረቡ። ሐዋርያት ምሳሌ 16:33ን መሠረት በማድረግ ሳይሆን አይቀርም ዕጣ ጣሉ፤ በዚህ መንገድ ማትያስ የተመረጠ ሲሆን “ከአሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ።” (ሥራ 1:23-26) በመሆኑም ግሪክኛ ተናጋሪ ከሆኑት ደቀ መዛሙርት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ችግር ከፈቱት “አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት” አንዱ መሆን ችሏል (ሥራ 6:1, 2)፤ ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:4-8 ላይ ኢየሱስን ከሞት ከተነሳ በኋላ ስላዩት ሰዎች ሲናገር ከጠቀሳቸው “አሥራ ሁለቱ” ሐዋርያት መካከል ማትያስም ተካትቶ መሆን አለበት። ስለዚህ የጴንጤቆስጤ በዓል በደረሰ ጊዜ በዚያ ቀን ለተቋቋመው መንፈሳዊ እስራኤል መሠረት የሚሆኑ 12 ሐዋርያት ነበሩ።
ከኅዳር 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | የሐዋርያት ሥራ 4-5
“የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራቸውን ቀጠሉ”
(የሐዋርያት ሥራ 4:5-13) በማግስቱም የሕዝቡ ገዢዎች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ 6 የካህናት አለቃው ሐና፣ ቀያፋ፣ ዮሐንስ፣ እስክንድርና የካህናት አለቃው ዘመዶችም ሁሉ ከእነሱ ጋር ነበሩ። 7 ጴጥሮስንና ዮሐንስን በመካከላቸው አቁመው “ይህን ያደረጋችሁት በምን ሥልጣን ወይም በማን ስም ነው?” ብለው ጠየቋቸው። 8 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የሕዝቡ ገዢዎችና ሽማግሌዎች፣ 9 ዛሬ በእኛ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ያለው ለአንድ ሽባ ሰው በተደረገ መልካም ሥራ የተነሳ ከሆነና ይህን ሰው ያዳነው ማን እንደሆነ ማወቅ የምትፈልጉ ከሆነ፣ 10 ይህ ሰው ጤናማ ሆኖ እዚህ ፊታችሁ የቆመው፣ እናንተ በእንጨት ላይ በሰቀላችሁት ሆኖም አምላክ ከሞት ባስነሳው በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ ይኸውም በኢየሱስ አማካኝነት እንደሆነ እናንተም ሆናችሁ መላው የእስራኤል ሕዝብ ይወቅ። 11 ‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ እሱ ነው። 12 ደግሞም መዳን በሌላ በማንም አይገኝም፤ ምክንያቱም ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።” 13 ሰዎቹ ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ ያልተማሩና ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ። ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩም ተገነዘቡ።
w08 9/1 15 ሣጥን
በቃል ከሚተላለፉ መልእክቶች ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት—ጽሕፈትና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች
ሐዋርያት ማንበብና መጻፍ አይችሉም ነበር?
ገዥዎችና የኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች፣ ‘ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፣ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ።’ (የሐዋርያት ሥራ 4:13) በእርግጥ ሐዋርያቱ ያልተማሩ ወይም ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ነበሩ? ይህንን አስመልክቶ ዘ ኒው ኢንተርፕሪተርስ ባይብል የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል:- “ጴጥሮስ [እና ዮሐንስ] መደበኛ ትምህርት ያልተከታተሉ እንዲሁም ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ስለሚያስመስል ይህ አነጋገር ቃል በቃል መወሰድ የለበትም። ሰዎቹ እንዲህ ያሉት ሐዋርያቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ቦታ በእነሱ ላይ ለመፍረድ ከተቀመጡት ሰዎች እጅግ የተለየ መሆኑን ለመግለጽ ነው።”
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
4:13—ጴጥሮስ እና ዮሐንስ መሃይሞች ወይም ያልተማሩ ሰዎች ነበሩ? አልነበሩም። “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” የተባሉት በረቢዎች ትምህርት ቤት ገብተው ሃይማኖታዊ ትምህርት ስላልተከታተሉ ነው።
(የሐዋርያት ሥራ 4:18-20) ከዚያም ጠርተዋቸው በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩ ወይም እንዳያስተምሩ አዘዟቸው። 19 ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ። 20 እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።”
(የሐዋርያት ሥራ 4:23-31) ከተለቀቁ በኋላ ወደ ወንድሞቻቸው ሄደው የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው። 24 እነሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ ሲሉ ወደ አምላክ ጸለዩ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ሆይ፣ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠርክ አንተ ነህ፤ 25 በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለሃል፦ ‘ብሔራት ለምን ታወኩ? ሕዝቦችስ ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ? 26 የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ ገዢዎችም በአንድነት ተሰብስበው በይሖዋና እሱ በቀባው ላይ ተነሱ።’ 27 በእርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ ተሰብስበው አንተ በቀባኸው በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ ተነሱ፤ 28 ይህም የሆነው እጅህና ፈቃድህ አስቀድመው የወሰኑት እንዲፈጸም ነው። 29 አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው፤ 30 ለመፈወስም የዘረጋኸውን እጅህን አትጠፍ፤ በቅዱስ አገልጋይህ በኢየሱስ ስም ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ማድረግህንም ቀጥል።” 31 ምልጃ ካቀረቡም በኋላ ተሰብስበውበት የነበረው ቦታ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር ጀመሩ።
it-1-E 128 አን. 3
ሐዋርያ
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያደረጉት እንቅስቃሴ። በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ መፍሰሱ በእጅጉ አበርትቷቸዋል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጀመሪያ አምስት ምዕራፎች እንደሚገልጹት የሕዝቡ ገዢዎች ሐዋርያትን ቢያስሯቸው፣ ቢገርፏቸውና እንደሚገድሏቸው ቢዝቱባቸውም ሐዋርያቱ ፍርሃት አላደረባቸውም፤ እንዲያውም ምሥራቹንና የኢየሱስን ትንሣኤ በድፍረት ይሰብኩ ነበር። ከጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ በነበሩት የመጀመሪያ ቀናት፣ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሰጡት ግሩም አመራር የክርስቲያን ጉባኤ አስደናቂ እድገት እንዲያደርግ አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ሥራ 2:41፤ 4:4) መጀመሪያ ላይ አገልግሎታቸው በአብዛኛው በኢየሩሳሌም ላይ ያተኮረ ቢሆንም ውሎ አድሮ ግን በሰማርያ ከዚያም በወቅቱ ይታወቅ በነበረው ዓለም በሙሉ ተስፋፍቷል።—ሥራ 5:42፤ 6:7፤ 8:5-17, 25፤ 1:8
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 4:11) “እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማዕዘን ራስ የሆነው ድንጋይ እሱ ነው።”
it-1-E 514 አን. 4
የማዕዘን ራስ ድንጋይ
መዝሙር 118:22 ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” (ዕብራይስጥ፣ ሮሽ ፒና) እንደሚሆን ይናገራል። ኢየሱስ ይህን ትንቢት ከጠቀሰ በኋላ ትንቢቱ “የማዕዘን ራስ ድንጋይ” (ግሪክኛ፣ ኬፋሊ ጎኒያስ፣ የማዕዘኑ ራስ ማለት ነው) በሆነው በእሱ ላይ እንደሚፈጸም ተናግሯል። (ማቴ 21:42፤ ማር 12:10, 11፤ ሉቃስ 20:17) ኢየሱስ ክርስቶስ የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ የመደምደሚያ ድንጋይ (ወይም ከላይ የሚቀመጠው ድንጋይ) በመሆኑ በአንድ ሕንፃ ማዕዘን አናት ላይ ከሚገኝ ድንጋይ ጋር ተነጻጽሯል፤ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈውን ጉባኤ ይወክላል። ጴጥሮስም መዝሙር 118:22 በክርስቶስ ላይ እንደተፈጸመ ተናግሯል፤ ሰዎች የናቁት “ድንጋይ” ክርስቶስ መሆኑን ከተናገረ በኋላ አምላክ “የማዕዘኑ ራስ” እንዲሆን እንደመረጠው ገልጿል።—ሥራ 4:8-12፤ 1ጴጥ 2:4-7ንም ተመልከት።
(የሐዋርያት ሥራ 5:1) ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ከሚስቱ ከሰጲራ ጋር መሬት ሸጠ።
ጴጥሮስና ሐናንያ ዋሹ—ከዚህ ምን እንማራለን?
ሐናንያና ሚስቱ አዲስ የተጠመቁትን ደቀ መዛሙርት ለመርዳት ሲሉ መሬታቸውን ሸጡ። ሐናንያ ገንዘቡን ወደ ሐዋርያት በወሰደ ጊዜ ከሽያጩ ያገኘውን ገንዘብ በሙሉ እንዳመጣ ተናገረ። ይህ ግን እውነት አይደለም! የተወሰነውን ገንዘብ ለራሱ አስቀርቷል! አምላክ ይህን ጉዳይ ለጴጥሮስ ስላሳወቀው ሐናንያን “ያታለልከው ሰውን ሳይሆን አምላክን ነው” አለው። ወዲያውኑ ሐናንያ ወድቆ ሞተ! ከሦስት ሰዓት በኋላ ሚስቱ መጣች። ሰጲራም በባሏ ላይ የደረሰውን ነገር ስላላወቀች ዋሸች፤ በዚህ ጊዜ እሷም ወድቃ ሞተች።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 5:27-42) አምጥተውም በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት አቆሟቸው። ከዚያም ሊቀ ካህናቱ ይጠይቃቸው ጀመር፤ 28 እንዲህም አለ፦ “በዚህ ስም ማስተማራችሁን እንድታቆሙ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል፤ የዚህንም ሰው ደም በእኛ ላይ ለማምጣት ቆርጣችሁ ተነስታችኋል።” 29 ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያትም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል። 30 እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሳው። 31 እስራኤል ንስሐ እንዲገባና የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኝ አምላክ እሱን “ዋና ወኪል” እና “አዳኝ” አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። 32 ለዚህም ጉዳይ እኛ ምሥክሮች ነን፤ እንዲሁም አምላክ እሱን እንደ ገዢያቸው አድርገው ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምሥክር ነው።” 33 እነሱም ይህን ሲሰሙ እጅግ ተቆጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ። 34 ሆኖም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ፣ የሕግ አስተማሪ የሆነ ገማልያል የሚባል አንድ ፈሪሳዊ በሳንሄድሪኑ ሸንጎ መካከል ተነስቶ ሰዎቹን ለጊዜው ወደ ውጭ እንዲያስወጧቸው አዘዘ። 35 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ያሰባችሁትን ነገር በተመለከተ ልትጠነቀቁ ይገባል። 36 ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ ቀደም ቴዎዳስ ራሱን እንደ ታላቅ ሰው በመቁጠር ተነስቶ ነበር፤ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎችም ከእሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታትነው እንዳልነበሩ ሆኑ። 37 ከእሱ በኋላ ደግሞ የሕዝብ ቆጠራ በተካሄደበት ወቅት የገሊላው ይሁዳ ተነስቶ ተከታዮች አፍርቶ ነበር። ይሁንና እሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ። 38 ስለዚህ አሁን የምላችሁ፣ እነዚህን ሰዎች አትንኳቸው፤ ተዉአቸው። ይህ ውጥን ወይም ይህ ሥራ ከሰው ከሆነ ይጠፋል፤ 39 ከአምላክ ከሆነ ግን ልታጠፏቸው አትችሉም። እንዲያውም ከአምላክ ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።” 40 እነሱም ምክሩን ተቀበሉ፤ ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፏቸው፤ ከዚያም በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ አዘው ለቀቋቸው። 41 እነሱም ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ እያላቸው ከሳንሄድሪን ሸንጎ ወጡ። 42 ከዚያም በየቀኑ በቤተ መቅደስም ሆነ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ስለ ክርስቶስ ይኸውም ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን ቀጠሉ።
ከኅዳር 26–ታኅሣሥ 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | የሐዋርያት ሥራ 6-8
“አዲስ የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ተፈተነ”
(የሐዋርያት ሥራ 6:1) በዚያን ወቅት የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ መበለቶቻቸው ቸል ስለተባሉባቸው ዕብራይስጥ ተናጋሪ በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ።
“አምላክን እንደ ገዥያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል”
17 ገና አዲስ በሆነው ጉባኤ ውስጥ የጉባኤውን ሕልውና ስጋት ላይ የሚጥል አንድ ስውር አደጋ ተፈጥሯል። ለመሆኑ ይህ ስውር አደጋ ምንድን ነው? በወቅቱ የተጠመቁት አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት ከኢየሩሳሌም ውጭ የመጡ ሲሆኑ ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት በዚያ ቆይተው ተጨማሪ እውቀት መቅሰም ፈልገው ነበር። በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ደቀ መዛሙርት እነዚህ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብና ቁሳቁስ ለማሟላት በፈቃደኝነት የገንዘብ መዋጮ አድርገው ነበር። (ሥራ 2:44-46፤ 4:34-37) በዚህ ጊዜ ልዩ ትኩረት የሚያሻው አንድ ጉዳይ ተነሳ። “በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ” ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑት መበለቶች ‘ቸል ተባሉ።’ (ሥራ 6:1) ዕብራይስጥ ተናጋሪ የሆኑት መበለቶች ግን ቸል አልተባሉም። የተፈጠረው ችግር በጉባኤ ውስጥ መድሎ እንደተፈጸመ የሚጠቁም ነበር። ይህ ደግሞ መከፋፈል እንዲፈጠር የሚያደርግ ከባድ ችግር ነው።
(የሐዋርያት ሥራ 6:2-7) ስለዚህ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ደቀ መዛሙርቱን በሙሉ ጠርተው እንዲህ አሏቸው፦ “በማዕድ ምግብ ለማከፋፈል ስንል የአምላክን ቃል የማስተማር ሥራችንን ብንተው ተገቢ አይሆንም። 3 ስለዚህ ወንድሞች፣ ለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ እንድንሾማቸው ከእናንተ መካከል መልካም ስም ያተረፉ፣ በመንፈስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ወንዶች ምረጡ፤ 4 እኛ ግን በጸሎትና ቃሉን በማስተማሩ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ እናተኩራለን።” 5 የተናገሩት ነገር ሁሉንም ደስ አሰኛቸው፤ ስለሆነም ጠንካራ እምነት የነበረውንና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን እንዲሁም ፊልጶስን፣ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞንን፣ ፓርሜናስንና ወደ ይሁዲነት ተለውጦ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ። 6 ሐዋርያትም ፊት አቀረቧቸው፤ እነሱም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። 7 ከዚህም የተነሳ የአምላክ ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤ በጣም ብዙ ካህናትም ይህን እምነት ተቀበሉ።
“አምላክን እንደ ገዥያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል”
18 በወቅቱ እየሰፋ በመሄድ ላይ ያለው ጉባኤ የበላይ አካል ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ሐዋርያት ‘ምግብ ለማከፋፈል ሲሉ የአምላክን ቃል የማስተማር ሥራቸውን መተዋቸው’ ተገቢ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ነበር። (ሥራ 6:2) ስለዚህ ሐዋርያቱ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ይህን “አስፈላጊ ሥራ” የሚያከናውኑ “በመንፈስና በጥበብ የተሞሉ” ሰባት ወንዶችን እንዲመርጡ ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጧቸው። (ሥራ 6:3) ሥራው ምግብ ማከፋፈልን ብቻ ሳይሆን ገንዘቡን በተገቢው መንገድ መያዝን፣ ቁሳቁሶችን መግዛትንና መረጃዎቹን በጥንቃቄ መመዝገብን ይጨምር ስለነበር ብቃት ያላቸው ወንዶች ያስፈልጉ ነበር። የተመረጡት ወንዶች በሙሉ የግሪክኛ ስም የነበራቸው ሲሆኑ ምናልባት ይህ ቅር ተሰኝተው በነበሩት መበለቶች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ሳያደርጋቸው አይቀርም። ሐዋርያቱ የተመረጡትን ሰዎች ሁኔታ በጸሎት ከመረመሩ በኋላ ይህን “አስፈላጊ ሥራ” እንዲያከናውኑ ሰባቱን ሰዎች ሾሙ።
(የሐዋርያት ሥራ 7:58–8:1) ይዘውት ከከተማው ውጭ ካስወጡት በኋላ በድንጋይ ይወግሩት ጀመር። ምሥክሮቹም መደረቢያቸውን ሳኦል በተባለ ወጣት እግር አጠገብ አስቀመጡ። 59 እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ መንፈሴን ተቀበል” ብሎ ተማጸነ። 60 ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ “ይሖዋ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ ጮኸ። ይህን ከተናገረም በኋላ በሞት አንቀላፋ።
8 ሳኦልም በእሱ መገደል ተስማምቶ ነበር። በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከባድ ስደት ተነሳ፤ ከሐዋርያት በስተቀር ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(የሐዋርያት ሥራ 6:15) በሳንሄድሪን ሸንጎ ተቀምጠው የነበሩትም ሁሉ ትኩር ብለው ሲያዩት ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ታያቸው።
‘ጸጋና ኃይል የተሞላው’ እስጢፋኖስ
2 በዚህ ወቅት በእስጢፋኖስ ፊት ላይ አንድ አስደናቂ ነገር ይታይ ነበር። ዳኞቹ ትኩር ብለው ሲያዩት ፊቱ “እንደ መልአክ ፊት” ሆኖ ታያቸው። (ሥራ 6:15) መላእክት የይሖዋ አምላክን መልእክት የሚያደርሱ እንደመሆናቸው መጠን ደፋሮችና የመረጋጋት ስሜት የሚታይባቸው መሆናቸው አያስገርምም። በእስጢፋኖስም ላይ የሚታየው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፤ ሌላው ቀርቶ በጥላቻ የተሞሉት ዳኞች እንኳ ይህን ማስተዋል ችለዋል። እስጢፋኖስ እንዲህ ሊረጋጋ የቻለው ለምንድን ነው?
(የሐዋርያት ሥራ 8:26-30) ይሁንና የይሖዋ መልአክ ፊልጶስን “ተነስተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ሂድ” አለው። (ይህ መንገድ የበረሃ መንገድ ነው።) 27 እሱም ተነስቶ ሄደ፤ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሥልጣንና የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባም አገኘ። ይህ ሰው ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር፤ 28 እየተመለሰም ሳለ በሠረገላው ውስጥ ተቀምጦ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያነብ ነበር። 29 መንፈስም ፊልጶስን “ሂድና ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው። 30 ፊልጶስ ከሠረገላው ጎን እየሮጠ ጃንደረባው የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ጮክ ብሎ ሲያነብ ሰማና “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” አለው።
“ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች” ማወጅ
16 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ፊልጶስ ይሠራው በነበረው ዓይነት ሥራ የመካፈል መብት አላቸው። ብዙውን ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይሰብካሉ፤ ለምሳሌ በጉዞ ላይ ሳሉ አብረዋቸው ለሚጓዙ ሰዎች ለመመሥከር ጥረት ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር የሚገናኙት እንዲሁ ባጋጣሚ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የመንግሥቱ ምሥራች “ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ” ይዳረስ ዘንድ መላእክት የስብከቱን ሥራ እንደሚመሩ ስለሚናገር ይህ መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ነው። (ራእይ 14:6) የስብከቱ ሥራ የመላእክት አመራር እንደሚኖረው ኢየሱስ ከረጅም ጊዜ በፊት በግልጽ ተናግሯል። ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ላይ በመከር ወቅት ይኸውም በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ‘አጫጆቹ መላእክት’ እንደሚሆኑ ገልጿል። አክሎም እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት “እንቅፋት የሚፈጥሩትን ነገሮች ሁሉና ዓመፅ የሚፈጽሙትን ሰዎች ከመንግሥቱ ይለቅማሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 13:37-41) በዚህ ጊዜም መላእክቱ ይሖዋ ወደ ድርጅቱ ሊስባቸው የሚፈልጋቸውን ሰዎች ይኸውም ወደፊት በሰማይ የመንግሥቱ ወራሽ የመሆን ተስፋ ያላቸውን ሰዎች፣ በመቀጠል ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆነውን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ይሰበስባሉ።—ራእይ 7:9፤ ዮሐ. 6:44, 65፤ 10:16
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(የሐዋርያት ሥራ 6:1-15) በዚያን ወቅት የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማከፋፈል ሥራ መበለቶቻቸው ቸል ስለተባሉባቸው ዕብራይስጥ ተናጋሪ በሆኑት አይሁዳውያን ላይ ቅሬታ ማሰማት ጀመሩ። 2 ስለዚህ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ደቀ መዛሙርቱን በሙሉ ጠርተው እንዲህ አሏቸው፦ “በማዕድ ምግብ ለማከፋፈል ስንል የአምላክን ቃል የማስተማር ሥራችንን ብንተው ተገቢ አይሆንም። 3 ስለዚህ ወንድሞች፣ ለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ እንድንሾማቸው ከእናንተ መካከል መልካም ስም ያተረፉ፣ በመንፈስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ወንዶች ምረጡ፤ 4 እኛ ግን በጸሎትና ቃሉን በማስተማሩ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ እናተኩራለን።” 5 የተናገሩት ነገር ሁሉንም ደስ አሰኛቸው፤ ስለሆነም ጠንካራ እምነት የነበረውንና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን እንዲሁም ፊልጶስን፣ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞንን፣ ፓርሜናስንና ወደ ይሁዲነት ተለውጦ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ። 6 ሐዋርያትም ፊት አቀረቧቸው፤ እነሱም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። 7 ከዚህም የተነሳ የአምላክ ቃል መስፋፋቱን ቀጠለ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄደ፤ በጣም ብዙ ካህናትም ይህን እምነት ተቀበሉ። 8 እስጢፋኖስም ጸጋና ኃይል ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ታላላቅ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ይፈጽም ነበር። 9 ይሁን እንጂ ‘ነፃ የወጡ ሰዎች ምኩራብ’ ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከተወሰኑ የቀሬና፣ የእስክንድርያ፣ የኪልቅያና የእስያ ሰዎች ጋር መጥተው እስጢፋኖስን ተከራከሩት። 10 ይሁንና ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም። 11 ስለዚህ “ይህ ሰው በሙሴና በአምላክ ላይ የስድብ ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” ብለው እንዲናገሩ አንዳንድ ሰዎችን በድብቅ አግባቡ። 12 በተጨማሪም ሕዝቡንና ሽማግሌዎችን እንዲሁም ጸሐፍትን ቀሰቀሱ፤ ከዚያም ድንገት መጡና በኃይል ይዘው ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ ወሰዱት። 13 የሐሰት ምሥክሮችም አቀረቡ፤ እነሱም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው ይህን ቅዱስ ስፍራና ሕጉን የሚቃወም ነገር ከመናገር ሊቆጠብ አልቻለም። 14 ለምሳሌ ያህል፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ እንደሚያፈርሰውና ሙሴ ያስተላለፈልንን ወግ እንደሚለውጥ ሲናገር ሰምተነዋል።” 15 በሳንሄድሪን ሸንጎ ተቀምጠው የነበሩትም ሁሉ ትኩር ብለው ሲያዩት ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ታያቸው።