“በማመዛዘን ችሎታችሁ ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት”
“ሰውነታችሁን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም በማመዛዘን ችሎታችሁ ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።”—ሮሜ 12:1 አዓት
1, 2. የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋልን መማር አንድን አዲስ ቋንቋ ከመማር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
አንድ አዲስ ቋንቋ ለመማር ሞክረህ ታውቃለህን? ሞክረህ የምታውቅ ከሆነ አዲስ ቋንቋ መማር ቀላል አይደለም ቢባል እንደምትስማማ አያጠራጥርም። አዳዲስ ቃላትን ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። አንድን ቋንቋ በደንብ መናገር የቋንቋውን ሰዋስው ጠንቅቆ ማወቅንም ይጠይቃል። ቃላት እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዛመዱና የተሟላ ሐሳብ ለመስጠት እንዴት እንደሚሰካኩ ማስተዋል አለብህ።
2 የአምላክን ቃል ጠንቅቆ ማወቅም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። የተመረጡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶችን ማወቅ ብቻ አይበቃም። በምሳሌያዊ አነጋገር የመጽሐፍ ቅዱስንም ሰዋስው መማር አለብን። ጥቅሶች እርስ በርስ እንዴት እንደሚዛመዱና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በዕለታዊ ሕይወታችን እንዴት እንደምንሠራባቸው ማስተዋል ያስፈልገናል። በዚህ መንገድ ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን’ ልንሆን እንችላለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:17
3. ለአምላክ በሚቀርበው አገልግሎት ረገድ በ33 እዘአ ምን ለውጥ ተደረገ?
3 ብዙ ትእዛዛት ያካተተው የሙሴ ሕግ ይሠራ በነበረበት ወቅት የአንድ ሰው ታማኝነት የሚታየው በግልጽ የሰፈሩ ሕጎችን አጥብቆ በተከተለበት መጠን ነበር። ሆኖም በ33 እዘአ ይሖዋ ልጁ በሞተበት ‘መስቀል [የመከራ እንጨት አዓት] ላይ ጠርቆ’ ሕጉን አስወገደው። (ቆላስይስ 2:13, 14) ከዚያ ጊዜ ወዲህ የአምላክ ሕዝቦች የሚያቀርቧቸውን መሥዋዕቶችና የሚከተሏቸውን ሕጎች በተመለከተ ብዛት ያላቸው ዝርዝሮች አልተሰጧቸውም። ከዚህ ይልቅ “ሰውነታችሁን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም በማመዛዘን ችሎታችሁ ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው” ተብሎ ተነግሯቸዋል። (ሮሜ 12:1 አዓት) አዎን፣ ክርስቲያኖች ሙሉ ልባቸውን፣ ነፍሳቸውን፣ አእምሯቸውንና ኃይላቸውን ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ለማዋል መጣር ነበረባቸው። (ማርቆስ 12:30፤ ከመዝሙር 110:3 አዓት ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ‘የማመዛዘን ችሎታን ተጠቅሞ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ’ ማለት ምን ማለት ነው?
4, 5. በማመዛዘን ችሎታችን ተጠቅመን ይሖዋን ማገልገል ምንን ይጨምራል?
4 “የማመዛዘን ችሎታ” የሚለው ሐረግ የተተረጎመው “ምክንያታዊ” ወይም “አስተዋይ” የሚል ትርጉም ካለው ሎጂኮስ ከተባለ ግሪክኛ ቃል ነው። የአምላክ አገልጋዮች በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን መጠቀም ይፈለግባቸዋል። ክርስቲያኖች ውሳኔ ሲያደርጉ ቀደም ሲል በወጡ አያሌ ሕጎች ከመመራት ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቃቄ ማመዛዘን አለባቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን “ሰዋስው” ወይም የተለያዩ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ እርስ በርስ እንዴት እንደሚዛመዱ ማስተዋል አለባቸው። በዚህ መንገድ በማመዛዘን ችሎታቸው ተጠቅመው ሚዛናዊ ውሳኔዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ።
5 እንደዚህ ሲባል ታዲያ ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ሕግ የላቸውም ማለት ነውን? በጭራሽ አይደለም። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የጣዖት አምልኮን፣ የጾታ ብልግናን፣ መግደልን፣ መዋሸትን፣ መናፍስትነትን፣ ደምን አላግባብ መጠቀምንና ሌሎች የተለያዩ ኃጢአቶችን በግልጽ ይከለክላሉ። (ሥራ 15:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:8) ሆኖም እስራኤላውያን ከሚፈለግባቸው ይበልጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለመማርና በሥራ ላይ ለማዋል የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል። አንድን አዲስ ቋንቋ በሚገባ ለማወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ይህም ጊዜንና ጥረትን ይጠይቃል። የማመዛዘን ችሎታችን ሊዳብር የሚችለው እንዴት ነው?
የማመዛዘን ችሎታችሁን ማዳበር
6. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ምንን ይጨምራል?
6 በመጀመሪያ ደረጃ ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆን አለብን። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አንድ ጥያቄ ሁልጊዜ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይመለሳል ብለን መጠበቅ የለብንም። ከዚህ ይልቅ አንድን አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም ጥያቄ ለመረዳት እንድንችል በርካታ ጥቅሶችን መመርመር ሊያስፈልገን ይችላል። አምላክ ጉዳዩን እንዴት እንደሚመለከተው ለማወቅ በትጋት መመርመር ያስፈልገናል። (ምሳሌ 2:3–5) ‘መልካም ምክርን ገንዘቡ የሚያደርገው አስተዋይ ሰው’ ስለሆነ ማስተዋል ጭምር ያስፈልገናል። (ምሳሌ 1:5) አስተዋይ ሰው ከአንድ ጉዳይ ጋር የሚያያዙትን የተለያዩ ነገሮች በተናጥል የመመልከትና እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት የማገናዘብ ችሎታ አለው። የተለያዩ ቁርጥራጮችን አንድ ላይ በማገጣጠም አንድ ነገር ለማስገኘት እንደሚደረገው ጨዋታ ሁሉ አንድ አስተዋይ ሰውም የተለያዩ ክፍሎችን አንድ ላይ በማገጣጠም የጉዳዩን ጠቅላላ ገጽታ ለማየት ይችላል።
7. ወላጆች ስለ ቅጣት የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሊሠሩባቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
7 ለምሳሌ ያህል፣ የወላጅነትን ኃላፊነት ተመልከት። ምሳሌ 13:24 ልጁን የሚወድ አባት “ተግቶ ይገሥጸዋል” ይላል። ይህ ጥቅስ ብቻውን ከተወሰደ ከባድና ምሕረት የሌለው ቅጣት መቅጣት ተገቢ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ አለቦታው በስሕተት ሊጠቀስ ይችላል። ሆኖም ቆላስይስ 3:21 “አባቶች ሆይ፣ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” በማለት ሚዛናዊ ምክር ይሰጣል። የማመዛዘን ችሎታቸውን የሚጠቀሙና ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው የሚሄዱ ወላጆች “ጭካኔ የተሞላበት” የሚባለውን ዓይነት ቅጣት አይቀጡም። ልጆቻቸውን በፍቅር፣ በማስተዋልና በክብር ይይዟቸዋል። (አፌሶን 6:4) ስለዚህ የወላጅነት ኃላፊነትንም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚያያዝ ማንኛውንም ሌላ ጉዳይ በተመለከተ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ የማመዛዘን ችሎታችንን ማዳበር እንችላለን። በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን “ሰዋስው” ማለትም የአምላክ ሐሳብ ምን እንደሆነና ይህን ነገር እንዴት እንደምንፈጽም ለመረዳት እንችላለን።
8. በመዝናኛ ረገድ ግትርና እኔ ያልኩት ይሁን የሚል አመለካከት ከመያዝ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
8 የማመዛዘን ችሎታችንን ለማዳበር የምንችልበት ሁለተኛው መንገድ ግትርና እኔ ያልኩት ይሁን የሚል አመለካከት ከመያዝ በመቆጠብ ነው። ድርቅ ያለ አመለካከት መያዝ የማመዛዘን ችሎታችን እንዳይዳብር እንቅፋት ይሆናል። የመዝናኛን ሁኔታ ተመልከቱ። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:19) ታዲያ ይህ ማለት እያንዳንዱ በዓለም የተዘጋጀ መጽሐፍ፣ ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም በሙሉ መጥፎና ሰይጣናዊ ነው ማለት ነውን? እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም። እርግጥ አንዳንዶች ከማናቸውም የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ ፊልም ወይም ዓለማዊ ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ ለመራቅ ይመርጡ ይሆናል። ይህ መብታቸው ነው፤ እንደዚህ በማድረጋቸውም ሊተቹ አይገባም። እነሱም ቢሆኑ ሌሎች የእነሱ ዓይነት አቋም እንዲይዙ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ አይገባም። ማኅበሩ መዝናኛን ወይም የጊዜ ማሳለፊያን በጥበብ እንድንመርጥ የሚያስችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያብራሩ የተለያዩ ርዕሶችን አውጥቷል። እነዚህን መመሪያዎች ችላ ማለትና በብዙዎቹ የዚህ ዓለም መዝናኛዎች ለሚቀርበው የብልግና አስተሳሰብ፣ ዓመፅ ወይም መናፍስትነት ራሳችንን ማጋለጥ ትልቅ ሞኝነት ነው። በእርግጥም በአምላክና በሰው ፊት ጥሩ ሕሊና ለመያዝ መዝናኛዎችን በጥበብ መምረጥ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ በማዋል ረገድ የማመዛዘን ችሎታን መጠቀምን ይጠይቃል።—1 ቆሮንቶስ 10:31–33
9. “የተሟላ ማስተዋል” ማለት ምን ማለት ነው?
9 በአሁኑ ወቅት ያለው አብዛኛው መዝናኛ ለክርስቲያኖች የሚስማማ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።a ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ነበሩት አንዳንድ ‘የሥነ ምግባር ስሜታቸው የጠፋባቸው’ ሰዎች እንዳንሆን ‘ክፉውን ለመጥላት’ ልባችንን ማሠልጠን አለብን። (መዝሙር 97:10፤ አፌሶን 4:17–19) እንደነዚህ ያሉ ጉዳዮችን ለማመዛዘን “ትክክለኛ እውቀትና የተሟላ ማስተዋል” ያስፈልገናል። (ፊልጵስዩስ 1:9 አዓት) እዚህ ላይ “ማስተዋል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የሥነ ምግባር ስሜት ያለው” ማለት ነው። ቃሉ እንደ ማየት ያሉትን ሰብዓዊ የስሜት ሕዋሳቶች ያመለክታል። መዝናኛን ወይም ሌላ የግል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ጉዳይን በተመለከተ የሥነ ምግባር ስሜታችን ጥሩና መጥፎ ተብለው በግልጽ የተቀመጡትን ነገሮች ብቻ ሳይሆን መሃል ላይ ያሉ ነገሮችንም ጭምር መለየት መቻል አለበት። ሆኖም ሁሉም ወንድሞቻችን እንደዚያው እንዲያደርጉ በመገፋፋት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ከመጠቀም መቆጠብ አለብን።—ፊልጵስዩስ 4:5 አዓት
10. በመዝሙር 15 ላይ የተገለጸውን የይሖዋን ሁለንተናዊ ባሕርይ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው?
10 የማመዛዘን ችሎታን ማዳበር የሚቻልበት ሦስተኛው መንገድ የይሖዋን አስተሳሰብ ማወቅና ይህን አስተሳሰብ በልባችን ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ ነው። ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ሁለንተናዊ ባሕሪውንና የአቋም ደረጃዎቹን ገልጾልናል። ለምሳሌ ያህል፣ በመዝሙር ምዕራፍ 15 ላይ ይሖዋ በድንኳኑ ውስጥ በእንግድነት የሚቀበለው ሰው እንዴት ያለ ሰው እንደሆነ እናነባለን። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ጽድቅን ያደርጋል፣ በልቡ እውነትን ይናገራል፣ የገባውን ቃል ይጠብቃል እንዲሁም የስስት ጥቅም አይፈልግም። ይህን መዝሙር ስታነብ ‘እነዚህ ባሕርያት የእኔን ጠባይ የሚገልጹ ናቸውን? ይሖዋ በድንኳኑ ውስጥ በእንግድነት ይቀበለኛልን?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ከይሖዋ መንገዶችና አስተሳሰብ ጋር እየተስማማን በሄድን መጠን የማስተዋል ችሎታችን ከፍ ይላል።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ዕብራውያን 5:14
11. ፈሪሳውያን ‘ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድን የተላለፉት’ እንዴት ነው?
11 ፈሪሳውያን በተለይ የጎደላቸው ይህ ነበር። ፈሪሳውያን የሕጉ ዝርዝር እውቀት የነበራቸው ቢሆንም የሕጉን “ሰዋስው” አላስተዋሉትም ነበር። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥቅሶችን በቃላቸው ቢያጠኑም ከሕጉ በስተጀርባ የነበረውን የይሖዋ ሁለንተናዊ ባሕርይ ማስተዋል ተሳናቸው። ኢየሱስ “ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ ወዮላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 11:42) ፈሪሳውያን ግትር አስተሳሰብና ደንዳና ልብ ስለነበራቸው የማመዛዘን ችሎታቸውን መጠቀም አልቻሉም ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሰንበት እሸት ቀጥፈው ሲበሉ ኢየሱስን በነቀፉበት ወቅት እርስ በርሱ የሚጋጭ አስተሳሰባቸው ገሃድ ወጣ፤ ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያኑ ቀን ኢየሱስን ለመግደል ሲያሤሩ ሕሊናቸው አልወቀሳቸውም!—ማቴዎስ 12:1, 2, 14
12. በግለሰብ ደረጃ ይሖዋን በይበልጥ መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
12 ፈሪሳውያንን መምሰል አንፈልግም። የአምላክ ቃል እውቀታችን በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ይበልጥ እንድንስማማ ሊረዳን ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ እንደሚከተሉት ባሉት ዓይነት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላቸው ጠቅሟቸዋል፦ ‘ይህ ትምህርት ስለ ይሖዋና ስለ ባሕሪዎቹ ምን ያስተምረኛል? ከሌሎች ሰዎች ጋር በማደርገው ግንኙነት የይሖዋን ባሕሪዎች ማንጸባረቅ የምችለው እንዴት ነው?’ እነዚህን በመሳሰሉ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን የማመዛዘን ችሎታችንን ለማዳበርና ‘እግዚአብሔርን ለመምሰል’ ያስችለናል።—ኤፌሶን 5:1 የ1980 ትርጉም
የአምላክና የክርስቶስ እንጂ የሰዎቸ ባሪያ አለመሆን
13. ፈሪሳውያን የሥነ ምግባር አምባገነኖች የሆኑት እንዴት ነበር?
13 ሽማግሌዎች በጥበቃቸው ሥር ያሉት በማመዛዘን ችሎታቸው እንዲጠቀሙ መፍቀድ አለባቸው። የጉባኤው አባሎች የሰዎች ባሪዎያች አይደሉም። ጳውሎስ “ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 1:10፤ ቆላስይስ 3:23, 24) ከዚህ በተቃራኒ ፈሪሳውያን በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ ሰዎች እንዲያምኑ ይፈልጉ ነበር። (ማቴዎስ 23:2–7፤ ዮሐንስ 12:42, 43) ፈሪሳውያን የራሳቸውን ሕጎች አውጥተው ሌሎች ከእነዚህ ብቃቶች ጋር ምን ያህል እንደተስማሙ የሚፈርዱ የሥነ ምግባር አምባገነኖች ለመሆን ራሳቸውን ሾመው ነበር። ፈሪሳውያንን የተከተሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናን በመጠቀም ረገድ ስለተዳከሙ የሰዎች ባሪያዎች ሆኑ።
14, 15. (ሀ) ሽማግሌዎች ከመንጋው ጋር አብረው የሚሠሩ እንደሆኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ሕሊናን የሚመለከቱ ጉዳዮችን መያዝ ያለባቸው እንዴት ነው?
14 በአሁኑ ዘመን የሚገኙ ሽማግሌዎች መንጋው በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠየቀው በእነሱ እንዳልሆነ ያውቃሉ። እያንዳንዱ ክርስቲያን የራሱን ወይም የራሷን ሸክም መሸከም አለበት። (ሮሜ 14:4፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24፤ ገላትያ 6:5) ይህም ተገቢ ነው። በእርግጥም የመንጋው አባሎች የሚቆጣጠራቸው ሲኖር ብቻ ታዛዥ የሚሆኑ የሰው ባሪያዎች ከሆኑ ሰዎች ሳይኖሩ ሲቀር ምን ያደርጋሉ? ጳውሎስ “እኔ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን አሁን ከእናንተ በራቅሁበት ወቅት ሁልጊዜ ታዛዦች እንደሆናችሁ ሁሉ የራሳችሁን መዳን ለመፈጸም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መሥራታችሁን ቀጥሉ” ብሎ ሲናገር የሚደሰትበት ምክንያት ነበረው። የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በእርግጥም የክርስቶስ ባሪያዎች ነበሩ እንጂ የጳውሎስ ባሪያዎች አልነበሩም።—ፊልጵስዩስ 2:12 አዓት
15 ስለዚህ ሽማግሌዎች በጥበቃቸው ሥር ላሉት ሰዎች ሕሊናን በሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ አያደርጉም። ከአንድ ጉዳይ ጋር የሚያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያብራራሉ፤ ከዚያም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለሰቦቹ በራሳቸው የማመዛዘን ችሎታ ተጠቅመው ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ይፈቅዳሉ። ይህ ከባድ ኃላፊነት ቢሆንም ግለሰቡ ራሱ ሊሸከመው ይገባል።
16. በእስራኤል ውስጥ ችግሮች የሚፈቱበት ሥርዓት ምን ነበር?
16 ይሖዋ እስራኤልን ለመምራት መሳፍንትን የተጠቀመበትን ጊዜ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር” በማለት ይነግረናል። (መሳፍንት 21:25) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቡ መመሪያ የሚያገኙበትን መንገድ አዘጋጅቶ ነበር። እያንዳንዱ ከተማ የሚነሱትን ጥያቄዎችና የሚያጋጥሙትን ችግሮች የሚፈቱ የበሰሉ ሽማግሌዎች ነበረው። ከዚህም በተጨማሪ ሌዋውያን ካህናት የአምላክን ሕጎች ለሕዝቡ በማስተማር ገንቢ ተጽዕኖ ያሳድሩ ነበር። በተለይ ከባድ ችግሮች ከተፈጠሩ ሊቀ ካህኑ በኡሪምና ቱሚም አማካኝነት አምላክን ሊጠይቅ ይችል ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎቸን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “በእነዚህ ዝግጅቶች የተጠቀመ፣ የአምላክ ሕግ እውቀት ያገኘና ይህን እውቀት በተግባር ላይ ያዋለ ሰው ሕሊናውን የሚመራበት ትክክለኛ መመሪያ ነበረው። በዚህ ረገድ ‘በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ማድረጉ’ አይጎዳውም ነበር። ይሖዋ ሕዝቡ ከፈቃደኝነት ወይም ከእንቢተኝነት መንፈስና አካሄድ መካከል አንዱን እንዲመርጡ ፈቅዶላቸው ነበር።”—ጥራዝ 2 ገጽ 162–3b
17. ሽማግሌዎች ከራሳቸው ብቃቶች ይልቅ በአምላክ ብቃቶች ተመርኩዘው ምክር እንደሚሰጡ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
17 እንደ እስራኤላውያን መሳፍንትና ካህናት ሁሉ የጉባኤ ሽማግሌዎችም በችግር ወቅት ብስለት የታከለበት እርዳታና ጠቃሚ ምክር ያበረክታሉ። ሌላው ቀርቶ አንዳንድ ጊዜ ‘ፈጽሞ እየታገሡና እያስተማሩ ወቀሳ፣ ተግሣጽና ምክር ይሰጣሉ።’ (2 ጢሞቴዎስ 4:2) እንደዚህ የሚያደርጉትም በአምላክ ብቃቶች እንጂ በራሳቸው ብቃቶች ተመርኩዘው አይደለም። ሽማግሌዎች ምሳሌ ሲሆኑና ልብን ለመንካት ሲጥሩ ይህ ምንኛ ውጤታማ ይሆናል!
18. በተለይ ሽማግሌዎች የሰውን ልብ ለመንካት መቻላቸው ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው ለምንድን ነው?
18 ልብ የክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችን “ሞተር” ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነው’ ይላል። (ምሳሌ 4:23) የሰውን ልብ የሚነኩ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ በአምላክ አገልግሎት የሚቻላቸውን ሁሉ ለመሥራት የሚገፋፉ ሰዎችን ያገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ሁልጊዜ የሌሎች ግፊት ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው አነሣሽነት የሚፈለግባቸውን ያደርጋሉ። ይሖዋ ሰዎች ተገደው እንዲታዘዙት አይፈልግም። እሱ የሚፈልገው በፍቅር ከተሞላ ልብ የሚመነጭ ታዛዥነትን ነው። ሽማግሌዎች መንጋው የማመዛዘን ችሎታውን እንዲያዳብር በመርዳት እንዲህ ዓይነቱን ከልብ ተነሳስቶ የሚደረግ አገልግሎት ሊያበረታቱ ይችላሉ።
‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማዳበር
19, 20. የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 ከዚህ በፊት እንደተገለጸው፣ የአምላክን ሕጎች ማወቅ ብቻ አይበቃም። መዝሙራዊው “እንዳስተውል አድርገኝ፣ ሕግህን እፈልጋለሁ፤ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ” በማለት አጥብቆ ለመነ። (መዝሙር 119:34) ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 2:16 አዓት) የማመዛዘን ችሎታውን ተጠቅሞ ይሖዋን በማገልገል ረገድ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። የአምላክን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሙሉ በሙሉ ከማስተዋሉም በላይ እንከን በሌለበት ሁኔታ በሥራ ላይ አውሏቸዋል። እሱ የተወውን ምሳሌ በማጥናት “ስፋቱና ርዝመቱ፣ ከፍታውም ጥልቀቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፣ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ” እንችላለን። (ኤፌሶን 3:17–19) አዎን፣ ስለ ኢየሱስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምንማረው ነገር ብዙ እውነታዎችን ከማወቅ በጣም የላቀ ነው፤ ይሖዋ ራሱ ምን እንደሚመስል በግልጽ እንድናውቅ ይረዳናል።—ዮሐንስ 14:9, 10
20 በዚህ መንገድ የአምላክን ቃል ባጠናን መጠን ይሖዋ ስለ ነገሮች ያለውን አስተሳሰብ ልናስተውልና ሚዛናዊ ውሳኔዎችን ልናደርግ እንችላለን። ይህም ጥረት ማድረግን ይጠይቃል። የይሖዋን ሁለንተናዊ ባሕርይና ብቃቶች የምናስተውል የአምላክ ቃል ትጉህ ተማሪዎች መሆን አለብን። በምሳሌያዊ አነጋገር አዲስ ሰዋስው እየተማርን ነው። ሆኖም እንዲህ የሚያደርጉ “ሰውነታችሁን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም በማመዛዘን ችሎታችሁ ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው” የሚለውን ምክር እየተከተሉ ናቸው።—ሮሜ 12:1 አዓት
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህ ክርስቲያኖች ሊቀበሏቸው የማይችሏቸውን ልክስክስ የጾታ ግንኙነት ወይም ልል የሆነ አመለካከት የሚያስፋፉትን የቤተሰብ መዝናኛ የሚባሉትን መዝናኛዎችንም ሆነ አጋንንታዊ የሆኑ መዝናኛዎችን፣ ሆን ተብሎ የጾታ ስሜት ለመቀስቀስ የሚዘጋጁ ጽሑፎችን ወይም የጭካኔ ድርጊቶች የተሞሉባቸውን መዝናኛዎች አይጨምርም።
b መጽሐፉ የታተመው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
ምን ተምረሃል?
◻ የአምላክን አገልግሎት በተመለከተ በ33 እዘአ ምን ለውጥ ተደረገ?
◻ የማመዛዘን ችሎታችንን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ሽማግሌዎች በመንጋው ውስጥ ያሉት የአምላክና የክርስቶስ ባሪያዎች እንዲሆኑ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌሎች በማመዛዘን ችሎታቸው እንዲጠቀሙ ሽማግሌዎች ይረዷቸዋል