የምትኖረው ለአሁኑ ሕይወት ነው ወይስ ለዘላለም ሕይወት?
‘በዚህ ተስፋ ድነናል።’—ሮሜ 8:24 የ1980 ትርጉም
1. ኤፊቆሮሳውያን የሚያስተምሩት ምን ነበር? እንዲህ ያለው ፍልስፍናስ አንዳንዶቹን ክርስቲያኖች የነካቸው እንዴት ነበር?
ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች “ከእናንተ አንዳንዶቹ:- ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ?” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:12) የግሪኩ ጠቢብ የኤፊቆሮስ መርዘኛ ፍልስፍና ወደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሰርጎ ገብቶ እንደነበር ግልጽ ነው። በመሆኑም ጳውሎስ “ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” የሚለውን የኤፊቆሮሳውያንን ትምህርት በመጥቀስ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:32) የዚህ ፈላስፋ ተከታዮች ከሞት በኋላ ሕይወት አለ የሚለውን ተስፋ ሁሉ በማጣጣል ለአንድ ሰው ትልቁ ወይም ብቸኛው ቁምነገር ሥጋዊ ተድላ ነው ብለው ያምናሉ። (ሥራ 17:18, 32) የኤፊቆሮሳውያን ፍልስፍና በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ፣ ጥርጣሬ የሞላበትና የኋላ ኋላም የሥነ ምግባር ዝቀት የሚያስከትል ነበር።
2. (ሀ) ትንሣኤ የለም ብሎ መካድ አደገኛ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እምነት ያጠናከረው እንዴት ነው?
2 የትንሣኤን እምነት መካዳቸው ያስከተለው ውጤት ቀላል አልነበረም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ . . . በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።” (1 ቆሮንቶስ 15:13-19) አዎን፣ የዘላለማዊ ሕይወት ተስፋ ከሌለ ክርስትና “ከንቱ” ይሆናል። ዓላማ የለሽ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ አረማዊ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ሥር የወደቀው የቆሮንቶስ ጉባኤ በችግር ቢታመስ ምንም አያስደንቅም። (1 ቆሮንቶስ 1:11፤ 5:1፤ 6:1፤ 11:20-22) በመሆኑም የጳውሎስ ግብ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላቸውን እምነት ማጠናከር ነበር። አሳማኝ ምክንያቶችን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥቅሶችን እንዲሁም ምሳሌዎችን በማቅረብ የትንሣኤ ተስፋ ልብ ወለድ ሳይሆን፣ መፈጸሙ ምንም የማያጠራጥር እውነታ መሆኑን ምንም በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል። ከዚህ በመነሣት መሰል አማኞችን እንደሚከተለው በማለት አጥብቆ ማሳሰብ ችሏል:- “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።”—1 ቆሮንቶስ 15:20-58
“እንግዲህ ንቁ”
3, 4. (ሀ) ጴጥሮስ በመጨረሻ ዘመን የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ምን አደገኛ አመለካከት እንደሚያድርባቸው ገልጿል? (ለ) ስለ ምን ነገር ራሳችንን ከማሳሰብ መቦዘን የለብንም?
3 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ነገ የሚሆነውን አናውቅምና ዛሬ እንደሰት የሚል አፍራሽ አመለካከት አላቸው። (ኤፌሶን 2:2) ሐዋርያው ጴጥሮስ አስቀድሞ እንደተናገረው ነው። “ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ . . . እነርሱም:- የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና” እንደሚሉ ገልጿል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) እውነተኛ ክርስቲያኖች ለእንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ከተሸነፉ “ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች” ይሆናሉ። (2 ጴጥሮስ 1:8) ደስ የሚለው ግን ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች እንደዚህ ያለ አመለካከት የላቸውም።
4 በመምጣት ላይ ያለው የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ መቼ እንደሆነ ለማወቅ መጓጓት ስህተት አይደለም። የኢየሱስ ሐዋርያትም ለማወቅ ጓጉተው እንደነበር አስታውስ። “ጌታ ሆይ፣ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ሲሉ ጠይቀዋል። ኢየሱስ “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም” ሲል መለሰላቸው። (ሥራ 1:6, 7) እነዚህ ቃላት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁም . . . የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣል” በማለት ያስተላለፈውን መሠረታዊ መልእክት የሚያንጸባርቁ ናቸው። (ማቴዎስ 24:42, 44) ዘወትር ይህንን ምክር ማስታወስ ይኖርብናል! አንዳንዶች ‘ይህን ያህል እኮ መጣደፍና ስለ መጭው ጥፋት መጨነቅ አያስፈልገኝም’ የሚል አመለካከት ለመያዝ ይዳዳቸው ይሆናል። ይህ እንዴት ያለ ስህተት ይሆናል! “የነጐድጓድ ልጆች” የተባሉትን የያዕቆብንና የዮሐንስን ምሳሌ ተመልከት።—ማርቆስ 3:17
5, 6. ከያዕቆብና ከዮሐንስ ምሳሌ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
5 ያዕቆብ ከፍተኛ ቅንዓት የነበረው ሐዋርያ መሆኑን እናውቃለን። (ሉቃስ 9:51-55) ከክርስቲያን ጉባኤ መቋቋም ወዲህ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቶ መሆን አለበት። ይሁንና ሄሮድስ አግሪጳ ቀዳማዊ ገና ጎልማሳ የነበረውን ያዕቆብን አስገደለው። (ሥራ 12:1-3) ያዕቆብ ሕይወቱ በድንገት ሊቀጭ መሆኑን ሲመለከት ቀናተኛ ሆኖ በማገልገሉና ለአገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ራሱን በማቅረቡ የተቆጨ ይመስልሃል? በፍጹም! በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር ከነበረው የሕይወት ዘመኑ ውስጥ አብዛኛውን የጉልምስና ዕድሜውን በይሖዋ አገልግሎት በማሳለፉ ደስተኛ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬ ከእኛ መካከል ሕይወቱ በድንገተኛ ሁኔታ እንዲቀጭ የሚያደርግ ነገር ይገጥመው እንደሆነና እንዳልሆነ የሚያውቅ ሰው የለም። (መክብብ 9:11 NW፤ ከሉቃስ 12:20, 21 ጋር አወዳድር።) እንግዲያውስ ይሖዋን በከፍተኛ ቅንዓት ማገልገላችንን መቀጠላችን ጥበብ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። በዚህ መንገድ በአምላክ ዘንድ ያለንን መልካም ስም ከመጠበቃችንም ሌላ የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን እያሰብን መኖራችንን እንቀጥላለን።—መክብብ 7:1
6 ኢየሱስ “እንግዲህ ንቁ” እያለ አጥብቆ ሲያሳስብ በቦታው ከነበረው ከሐዋርያው ዮሐንስም ቢሆን የምናገኘው ትምህርት ይኖራል። (ማቴዎስ 25:13፤ ማርቆስ 13:37፤ ሉቃስ 21:34-36) ዮሐንስ ይህንን ምክር በማስተዋል ለብዙ አሥርተ ዓመታት በግለት አገልግሏል። እንዲያውም ከሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ ይበልጥ ረጅም ዘመን የኖረ ይመስላል። ዮሐንስ ዕድሜው በጣም ከገፋ በኋላ በታማኝነት በማገልገል ያሳለፋቸውን በርካታ አሥርተ ዓመታት መለስ ብሎ ሲመለከት ተሳስቶ እንደነበርና ሕይወቱን በአጉል አቅጣጫ እንደመራው ወይም ሚዛናዊነት ጎድሎት እንደነበር ተሰምቶታልን? በፍጹም እንደዚያ አልተሰማውም! በዕድሜ ገፍቶም ቢሆን የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ “በቶሎ እመጣለሁ” ባለ ጊዜ ዮሐንስ ወዲያው “አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ና” ሲል መልሷል። (ራእይ 22:20) ዮሐንስ ‘የተለመደውን ዓይነት’ ዘና ያለና የተረጋጋ ኑሮ በመፈለግ ለአሁኑ ሕይወቱ ብቻ የሚጨነቅ ሰው እንዳልነበር የተረጋገጠ ነው። ጌታ መቼም ይምጣ መቼ ሕይወቱና አቅሙ እስከፈቀደለት ድረስ ማገልገሉን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ያደረገ ሰው ነበር። እኛስ?
በዘላለም ሕይወት ለማመን የሚያስችሉ መሠረቶች
7. (ሀ)የዘላለም ሕይወት ተስፋ ቃል የተገባልን ‘ከዘመናት በፊት’ ነው ለማለት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ በዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው?
7 የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሰው አእምሮ የፈጠረው ሕልም ወይም ቅዠት እንዳልሆነ እርግጠኛ ሁን። ቲቶ 1:2 እንደሚለው ለአምላክ ያደርን መሆናችን የተመሠረተው ‘ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ከዘመናት በፊት ቃል በገባው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ’ ነው። የአምላክ የመጀመሪያው ዓላማ ሁሉም ታዛዥ የሰው ልጆች ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ይህንን ዓላማ ምንም ነገር፣ የአዳምና የሔዋንን ኃጢአት እንኳ ሊያጨናግፈው አይችልም። በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው አምላክ በሰው ዘር ላይ የደረሱትን ችግሮች ሁሉ የሚያስወግድ “ዘር” እንደሚመጣ ወዲያው ቃል ገብቷል። ይህ “ዘር” ወይም መሲሑ ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ ካስተማራቸው መሠረታዊ ትምህርቶች አንዱ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ነበር። (ዮሐንስ 3:16፤ 6:47, 51፤ 10:28፤ 17:3) ክርስቶስ ፍጹም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በማቅረብ ለሰው ልጅ የዘላለም ሕይወት የመስጠት ሕጋዊ መብት አግኝቷል። (ማቴዎስ 20:28) ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ጥቂቶቹ ማለትም 144,000 የሚያክል አጠቃላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሰማይ ለዘላለም ይኖራሉ። (ራእይ 14:1-4) በዚህ መንገድ በአንድ ወቅት ሟች የነበሩት የሰው ልጆች “የማይሞተውን” አካል ይላበሳሉ!—1 ቆሮንቶስ 15:53
8. (ሀ) ‘ያለመሞት’ ባሕርይ ምንድን ነው? ይሖዋ ለ144,000ዎቹ ያለመሞትን ባሕርይ የሰጣቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ‘ለሌሎች በጎች’ ምን ተስፋ ሰጥቷል?
8 ‘የማይሞት’ ማለት እንዲሁ ለዘላለም የሚኖር ማለት ብቻ አይደለም። “የማይጠፋ ሕይወት” ማግኘት ማለት ነው። (ዕብራውያን 7:16 NW፤ ከራእይ 20:6 ጋር አወዳድር።) ይሁንና አምላክ እንዲህ ያለውን አስገራሚ ስጦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? ሰይጣን የትኛውም የአምላክ ፍጥረት እምነት ሊጣልበት አይችልም በማለት ያስነሳውን ክርክር አስታውስ። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) አምላክ ለ144,000ዎቹ የማይሞት ሕይወት በመስጠት ለሰይጣን ግድድር ግሩም ምላሽ የሰጡትን እነዚህን ሰዎች ምን ያክል እንደሚተማመንባቸው ያሳያል። ይሁን እንጂ የቀረውስ የሰው ዘር? ኢየሱስ የመንግሥቱ ወራሽ ለሆነው “ታናሽ መንጋ” የመጀመሪያ አባላት ‘በዙፋኖች ተቀምጠው በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንደሚፈርዱ’ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 12:32፤ 22:30) ከዚህ እንደምንረዳው በምድር ላይ የመንግሥቱ ተገዥ ሆነው የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ ሌሎች ሰዎች ይኖራሉ። እነዚህ “ሌሎች በጎች” የማይሞት ሕይወት ባይሰጣቸውም “የዘላለም ሕይወት” ያገኛሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:46) እንግዲያውስ ሁሉም ክርስቲያኖች የዘላለም ሕይወት ተስፋ አላቸው። ይህ ቅዠት ሳይሆን ‘ሊዋሽ የማይችለው አምላክ’ የሰጠው ጠንካራና ውድ የሆነው የኢየሱስ ደምም የተከፈለበት ተስፋ ነው።—ቲቶ 1:2
የሚፈጸምበት ጊዜ ገና ሩቅ ነውን?
9, 10. ወደ ፍጻሜው እንደተቃረብን የሚጠቁሙት ግልጽ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚያስጨንቅ ዘመን” መምጣቱ ‘በመጨረሻው ዘመን’ የምንኖር መሆናችንን በማያሻማ መንገድ እንደሚያረጋግጥ አስቀድሞ ተናግሯል። በዙሪያችን ያለው የሰው ልጅ ኅብረተሰብ በፍቅር ማጣት፣ በስስት፣ በራስ ወዳድነት፣ ለአምላክ አክብሮት በጎደለው አድራጎት ተወጥሮ ሲፍረከረክ ስናይ ይሖዋ በዚህ ክፉ ዓለም ሥርዓት ላይ ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ እንዳለ አንገነዘብምን? ዓመፅና ጥላቻ በእጅጉ እየጨመረ ሲሄድ ጳውሎስ የተናገራቸው “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” የሚሉት ተጨማሪ ቃላት ፍጻሜያቸውን እያገኙ እንዳሉ አናስተውልምን? (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) አንዳንዶች አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ የ“ሰላምና ደህንነት” ጩኸት ያሰሙ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ይህ የሰላም ሕልም በንኖ ይጠፋል፤ ምክንያቱም “ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” የጊዜያችንን ትርጉም በሚመለከት በጭፍን እንድንመራ አልተተውንም። እንግዲያውስ “እንንቃ በመጠንም እንኑር።”—1 ተሰሎንቄ 5:1-6
10 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን “ጥቂት ዘመን” እንደሆነ ይጠቁማል። (ራእይ 12:12፤ ከ17:10 ጋር አወዳድር።) ከዚህ “ጥቂት ዘመን” መካከል አብዛኛው ክፍል ያለቀ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል የዳንኤል ትንቢት እስከዚህ መቶ ዘመን ድረስ የዘለቀውን ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ እና ‘በደቡቡ ንጉሥ’ መካከል ያለውን ቅራኔ በትክክል ይገልጻል። (ዳንኤል 11:5, 6) አሁን ፍጻሜውን የሚጠብቀው በዳንኤል 11:44, 45 ላይ የተገለጸው ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ የሚሰነዝረው የመጨረሻ ጥቃት ብቻ ነው።—ስለ ትንቢቱ ማብራሪያ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ 13-108ን እንዲሁም የኅዳር 1, 1993ን መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።
11. (ሀ) ማቴዎስ 24:14 እስከምን ድረስ ፍጻሜውን አግኝቷል? (ለ) በማቴዎስ 10:23 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ምን ይጠቁማሉ?
11 እንዲሁም ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል የተናገረው ትንቢት አለ። (ማቴዎስ 24:14) ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸውን በ233 አገሮች፣ ደሴቶችና ክልሎች ውስጥ እያከናወኑ ነው። አሁንም ገና ያልተነኩ ክልሎች መኖራቸው ባይካድም ይሖዋ ራሱ በወሰነው ጊዜ በሩን ይከፍተዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:9) ያም ሆኖ ግን ኢየሱስ በማቴዎስ 10:23 ላይ “የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም” በማለት የተናገራቸው ቃላት ሊጤኑ የሚገባቸው ናቸው። ምሥራቹ በምድር ዙሪያ እንደሚሰበክ የተረጋገጠ ነገር ቢሆንም ኢየሱስ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ ‘ከመምጣቱ’ በፊት የመንግሥቱን መልእክት በሁሉም የምድር ክፍሎች ተገኝተን እናዳርሳለን ማለት አይደለም።
12. (ሀ) በራእይ 7:3 ላይ የተገለጸው ‘መታተም’ ምንድን ነው? (ለ) በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ቁጥር እየቀነሰ መሄዱ ምን ትርጉም አለው?
12 ‘አራቱ ነፋሳት’ ጥፋት እንዳያስከትሉ የተያዙት “የአምላካችንን ባሪያዎች ግንባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ” ነው በማለት የሚገልጸውን የራእይ 7:1, 3 ጥቅስ ተመልከት። ይህ ጥቅስ የሚናገረው 144,000ዎቹ ሰማያዊ ጥሪ በሚያገኙበት ጊዜ የሚፈጸመውን የመጀመሪያ መታተም አይደለም። (ኤፌሶን 1:13) እዚህ ላይ የተጠቀሰው መታተም ተፈትነው የታመኑ ‘የአምላክ ባሪያዎች’ መሆናቸውን ባረጋገጡት ሰዎች ላይ በማይጠፋ መንገድ ስለሚደረገው የመጨረሻ ማኅተም ነው። በምድር ላይ በሕይወት የቀሩት እውነተኛዎቹ ቅቡዓን የአምላክ ልጆች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው የታላቁ መከራ የመክፈቻ ምዕራፍ ‘የሚያጥረው’ “ስለ ተመረጡት” ሲባል ነው። (ማቴዎስ 24:21, 22) ከቅቡዓን ክፍል ነን ከሚሉት መካከል አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው በጣም ገፍቷል። ይህስ ቢሆን መጨረሻው በጣም እንደቀረበ አይጠቁምምን?
የታመነ ጠባቂ
13, 14. የጠባቂው ክፍል ኃላፊነት ምንድን ነው?
13 እስከዚያው ድረስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ መከተላችን ተገቢ ይሆናል። (ማቴዎስ 24:45) በዚህ ዘመን ያለው “ባሪያ” ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት የታመነ “ጠባቂ” ሆኖ አገልግሏል። (ሕዝቅኤል 3:17-21) የጥር 1, 1984 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “ይህ ጠባቂ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት በምድር ላይ ምን ነገሮች እየተከናወኑ እንዳሉ ያስተውላል፤ ‘ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ ያልሆነ ታላቅ መከራ’ ሊመጣ እንደቀረበ ማስጠንቀቂያ ያሰማል እንዲሁም ‘የመልካምንም ወሬ የምሥራች’ ያውጃል።”—ማቴዎስ 24:21፤ ኢሳይያስ 52:7
14 የአንድ ጠባቂ ሥራ ‘የሚያየውን’ መናገር መሆኑን አትዘንጋ። (ኢሳይያስ 21:6-8) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ጠባቂ በቅጡ ተለይቶ ሊታይ በማይችልበት ርቀት ላይ ስለሚገኝ አስጊ ሁኔታ እንኳ ሳይቀር ያስጠነቅቅ ነበር። (2 ነገሥት 9:17, 18) በዚያን ዘመን የሐሰት ማስጠንቀቂያዎች የተሰሙበት ጊዜ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ አንድ ጥሩ ጠባቂ የተናገርኩት ሳይፈጸም ቀርቶ ኃፍረት ይደርስብኛል በሚል ፍርሃት ከማስጠንቀቅ ወደኋላ አይልም። ቤትህ በእሳት ቢያያዝና የእሳት አደጋ ሠራተኞች ጥሪው ሐሰት ሊሆን ይችላል ብለው በማሰብ ሳይመጡ ቢቀሩ ምን ይሰማሃል? እነዚህ ሰዎች ለማንኛውም የአደጋ ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንጂ እንደዚህ ማድረግ የለባቸውም! በተመሳሳይም የጠባቂው ክፍል ሁኔታዎቹ ማስጠንቀቂያ ማሰማትን የሚጠይቁ ሆነው ሲያገኛቸው ማስጠንቀቂያ ከማሰማት ወደኋላ ያለባቸው ጊዜያት የሉም።
15, 16. (ሀ) ስለ ትንቢቶች ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያዎች የተደረጉት ለምንድን ነው? (ለ) ስለ አንዳንድ ትንቢቶች የተሳሳተ ግንዛቤ ከነበራቸው የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ምን እንማራለን?
15 ይሁንና አንዳንድ ሁኔታዎች በመፈጸማቸው ስለ ትንቢቶች ያለን ግንዛቤ ይበልጥ እየጠራ መጥቷል። ታሪክ እንደሚያሳየው መለኮታዊ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ከማግኘታቸው በፊት ሙሉ በሙሉ የተስተዋሉበት ጊዜ እምብዛም ነው። የአብራም ልጆች ‘ለእነርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኛ’ ሆነው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ አምላክ የነገረው ሲሆን በዚያ የሚቆዩት ለ400 ዓመታት ነበር። (ዘፍጥረት 15:13) ይሁን እንጂ ሙሴ ይህ ጊዜ ሳይደርስ ራሱን ነፃ አውጭ አድርጎ አቅርቦ ነበር።—ሥራ 7:23-30
16 መሲሐዊ ትንቢቶችንም ተመልከት። መለስ ብለን ስናስበው የመሲሑ ሞትና ትንሣኤ አስቀድሞ በትንቢት መነገሩ ምንም የማያሻማ ነገር ሆኖ እናገኘዋለን። (ኢሳይያስ 53:8-10) አዎን፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንኳ የዚህን ትርጉም ሳያስተውሉ ቀርተዋል። (ማቴዎስ 16:21-23) ዳንኤል 7:13, 14 ፍጻሜውን የሚያገኘው ወደፊት በክርስቶስ ፓሩሲያ ወይም “መገኘት” ጊዜ እንደሆነ አላስተዋሉም። (ማቴዎስ 24:3 NW) በመሆኑም ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ሲጠይቁት ስሌታቸው ከትክክለኛው ጊዜ በ2,000 ዓመት ገደማ የራቀ ነበር። (ሥራ 1:6) የክርስቲያን ጉባኤ በሁለት እግሩ ከቆመም በኋላ እንኳ የተሳሳቱ ሐሳቦችና የሐሰት ተስፋዎች ብቅ ብቅ ማለታቸውን ቀጥለው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:1, 2) አንዳንዶች አልፎ አልፎ የተሳሳተ አመለካከት የነበራቸው ቢሆንም ይሖዋ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አማኞች ያከናወኑትን ሥራ መባረኩ የማይካድ ነው!
17. ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ባለን ግንዛቤ ላይ የሚደረጉትን ማስተካከያዎች በሚመለከት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
17 ዛሬም በተመሳሳይ የጠባቂው ክፍል ከጊዜ ወደ ጊዜ አመለካከቶቹን ማጥራት አስፈልጎታል። ይሁንና ይሖዋ ‘ታማኙን ባሪያ’ ስለመባረኩ ሊጠራጠር የሚችል ይኖራልን? ደግሞስ ሰፋ አድርገን ካየነው የተደረጉት አብዛኛዎቹ ማስተካከያዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት አይደሉምን? ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን መሠረታዊ ግንዛቤ አልተቀየረም። በመጨረሻው ዘመን ላይ እንደምንኖር ያለን እምነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጠንካራ ሆኗል!
ለዘላለማዊ ሕይወት መኖር
18. ለአሁኑ ሕይወት ብቻ ከመኖር መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?
18 ዓለም ‘እንብላና እንጠጣ፤ ነገ እንሞታለን’ ይል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እኛ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖረን አይገባም። ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት መጣር ስትችል ከአሁኑ ሕይወት ለሚገኘው ደስታ በከንቱ የምትደክምበት ምን ምክንያት ይኖራል? የወደፊት ተስፋህ በሰማይ የማይሞት ሕይወት ማግኘትም ይሁን በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይህ ሕልም ወይም ቅዠት አይደለም። ‘ሊዋሽ የማይችለው አምላክ’ ቃል የገባው እውነታ ነው። (ቲቶ 1:2) ተስፋችን እውን የሚሆንበት ጊዜ እጅግ እንደቀረበ የሚያሳዩት ማስረጃዎች በርካታ ናቸው! “የቀረው ዘመን አጭር ሆኖአል።”—1 ቆሮንቶስ 7:29 NW
19, 20. (ሀ) ይሖዋ ለመንግሥቱ ስንል የከፈልናቸውን መሥዋዕትነቶች እንዴት ያያቸዋል? (ለ) የዘላለም ሕይወትን እያሰብን መኖር ያለብን ለምንድን ነው?
19 በእርግጥም ይህ ሥርዓት ብዙዎች ካሰቡት ይበልጥ ረዝሟል። ዛሬ ጥቂቶች ይህን አስቀድሜ አውቄ ቢሆን ኖሮ አንዳንድ መሥዋዕቶችን አልከፍልም ነበር ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ በማድረጉ ሊጸጸት አይገባም። ደግሞም መሥዋዕትነት መክፈል የክርስትና ሕይወት ከሚጠይቃቸው መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ነው። ክርስቲያኖች ‘ራሳቸውን የካዱ’ ሰዎች ናቸው። (ማቴዎስ 16:24) አምላክን ለማስደሰት ያደረግነው ጥረት ከንቱ እንደሆነ ፈጽሞ ሊሰማን አይገባም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን . . . መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” (ማርቆስ 10:29, 30) ዛሬ ያላችሁ ሥራ፣ ቤት ወይም የባንክ ሒሳብ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ የሚጠቅማችሁ ምን ያህል ነው? ሆኖም ለይሖዋ ስትሉ የከፈላችሁት መሥዋዕትነት ከዛሬ አንድ ሚልዮን ብሎም ከአንድ ቢልዮን ዓመታትም በኋላ የሚኖረው ትርጉም ሕያው ነው! “እግዚአብሔር፣ . . . ያደረጋችሁትን ሥራ . . . ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።”—ዕብራውያን 6:10
20 እንግዲያውስ የዘላለም ሕይወትን እያሰብን እንኑር፤ ዓይናችን ‘የማይታየውን እንጂ የሚታየውን አይመልከት፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፣ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።’ (2 ቆሮንቶስ 4:18) ነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ ወደ ፍጻሜውም ይቸኩላል፣ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:3) መጨረሻውን ‘እየተጠባበቅን’ መኖራችን የግልና የቤተሰብ ኃላፊነቶቻችንን የምንወጣበትን መንገድ የሚነካው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች የሚዳስስ ይሆናል።
የክለሳ ነጥቦች
◻ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የዘገየ መስሎ መታየቱ ዛሬ ጥቂቶችን የነካው እንዴት ነው?
◻ የዘላለም ሕይወት ተስፋችን መሠረቱ ምንድን ነው?
◻ መንግሥቱን ለማስቀደም ስንል ለከፈልናቸው መሥዋዕቶች ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምድር አቀፉ የስብከት ሥራ መጠናቀቅ ይኖርበታል