በጎነትን እየተከታተላችሁ ነውን?
“በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8
1. ብልግና ምንድን ነው? የይሖዋን አምልኮ ያልበከለውስ ለምንድን ነው?
ብልግና፣ ወራዳ ወይም ብልሹ የሆነ ምግባር ሲሆን የምንኖርበትን ዓለም በሰፊው አጥለቅልቆት ይገኛል። (ኤፌሶን 2:1-3) ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ንጹሕ አምልኮው እንዲበከል አይፈቅድም። ክርስቲያናዊ ጽሑፎች፣ የጉባኤ ስብሰባዎች፣ የልዩና የወረዳ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎች ከዓመፅ ድርጊቶች እንድንርቅ ወቅታዊ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጡናል። በአምላክ ፊት ‘በጎ ከሆነው ነገር ጋር ለመጣበቅ’ የሚረዱን ጠቃሚ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች ይሰጡናል። (ሮሜ 12:9) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በድርጅት ደረጃ ንጹሕና በጎዎች ለመሆን እየጣሩ ነው። ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃስ እንዴት ነን? በእርግጥ አንተ በግልህ በጎነትን እየተከታተልክ ነውን?
2. በጎነት ምንድን ነው? በጎ ሆኖ መመላለስ ጥረት የሚጠይቀው ለምንድን ነው?
2 በጎነት ጥሩ ሥነ ምግባር፣ መልካም ጠባይ፣ ትክክለኛ ድርጊትና አስተሳሰብ ነው። በጎነት ድርጊት አልባ ባሕርይ ሳይሆን የሚያንቀሳቅስና ገንቢ ባሕርይ ነው። በጎነት ከኃጢት በመቆጠብ ብቻ አይወሰንም፤ መልካም የሆነውን ነገር መከታተልን ይጨምራል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11) ሐዋርያው ጴጥሮስ መሰል ክርስቲያኖችን “በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ” በማለት አጥብቆ መክሯል። እንዴት? ‘ስለዚህም ምክንያት [አምላክ ውድ ተስፋ ስለ ሰጣችሁ] ትጋትን ሁሉ በማሳየት’ ነው ብሏል። (2 ጴጥሮስ 1:5) ኃጢአተኞች በመሆናችን በጎ ሆኖ መኖር ብርቱ ጥረት ይጠይቃል። ይሁንና ጥንት የነበሩ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ከባድ መሠናክሎች ቢገጥሟቸውም በጎ ሆነው ኖረዋል።
በጎነትን ተከታትሏል
3. ንጉሥ አካዝ ምን ክፉ ድርጊቶችን ፈጽሟል?
3 ቅዱሳን ጽሑፎች በጎነትን ስለተከታተሉ ሰዎች የሚገልጹ ብዙ ዘገባዎችን ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል በጎ ሰው የነበረውን ሕዝቅያስን እንውሰድ። ማስረጃዎቹ እንደሚያረጋግጡት የይሁዳ ንጉሥ የነበረው አባቱ አካዝ ሞሎክን የሚያመልክ ሰው ነበር። “አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጎልማሳ ነበር፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም። ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብ ርኩሰት ልጁን በእሳት አሳለፈው። በመስገጃዎችና በኮረብቶቹ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር።” (2 ነገሥት 16:2-4) አንዳንዶች ‘በእሳት አሳለፈው’ የሚለው አነጋገር ስለ ሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓት የሚገልጽ እንጂ የሰው መሥዋዕት ስለማቅረቡ የሚናገር ነገር አይደለም ብለው ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ በጆን ዴይ የተዘጋጀው ሞሌክ—ኤ ጎድ ኦቭ ሂውማን ሳክሪፋይስ ኢን ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “በከነዓናውያኑ ዓለም የሰዎች መሥዋዕት ይቀርብ እንደነበር የሚያረጋግጡ ጥንታዊ የታሪክ መዛግብትና የፑኒክ [ካርቴጂያን] ምንጮች እንዲሁም ስሩጥንታዊ (አርኪኦሎጂያዊ) ማስረጃዎች ስላሉ . . . ብሉይ ኪዳን [የሰው መሥዋዕት ይቀርብ እንደነበር] የሚናገረውን ነገር የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም።” ከዚህም በተጨማሪ 2 ዜና መዋዕል 28:3 አካዝ “ልጆቹን በእሳት አቃጠለ” በማለት በቀጥታ ይገልጻል። (ከዘዳግም 12:31፤ ከመዝሙር 106:37, 38 ጋር አወዳድር።) እንዴት ያለ የክፋት ድርጊት ነው!
4. ሕዝቅያስ ዙሪያውን በብልግና ተከቦ እያለ እንዴት ተመላልሷል?
4 ሕዝቅያስ ይህን በብልግና የተሞላ ሁኔታ የተወጣው እንዴት ነው? አንዳንዶች 119ኛውን መዝሙር ያቀነባበረው ሕዝቅያስ ነው ብለው ስለሚያስቡ ይህንን መዝሙር መመርመር ትኩረት የሚስብ ነው፤ ሕዝቅያስ ይህን መዝሙር ያቀነባበረው መስፍን ሆኖ እያለ ነበር። (መዝሙር 119:46, 99, 100) በመሆኑም “አለቆች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ ባሪያህ ግን ሕግህን ያሰላስል ነበር። ከኀዘኔ የተነሣ ነፍሴ አንቀላፋች [“እንቅልፍ አጣች፣” NW]” የሚሉት ቃላት የነበረበትን ሁኔታ ሊጠቁሙ ይችሉ ይሆናል። (መዝሙር 119:23, 28) ሕዝቅያስ ዙሪያውን በሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ተከቦ የነበረ እንደመሆኑ መጠን እንቅልፍ እስኪያጣ ድረስ በንጉሣዊው ቤተሰብ መካከል ማፌዣ አድርገውት ሊሆን ይችላል። ይሁንና በጎነትን ከመከታተል ወደኋላ አላለም፤ ውሎ አድሮም ንጉሥ በሆነ ጊዜ ‘በይሖዋ ፊት ቅን ነገርን ማድረጉን ከመቀጠሉም ሌላ በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ታምኗል።’—2 ነገሥት 18:1-5
በጎዎች ሆነው ኖረዋል
5. ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ምን ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል?
5 በበጎነት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑን ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዳንኤል እንዲሁም ሃናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ የተባሉት ሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ ናቸው። ከትውልድ አገራቸው በኃይል ተወስደው በባቢሎን በግዞት እንዲቀመጡ ተደርገው ነበር። እነዚህ አራት ወጣቶች ብልጣሶር፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብደናጎ የሚል የባቢሎናውያን ስም ተሰጥቷቸው ነበር። በአምላክ ሕግ የተከለከሉ ምግቦችን ጨምሮ “ከንጉሡ መብል” እንዲቀርብላቸው ተደረገ። ከዚህም በላይ ‘ከከለዳውያን ትምህርትና ቋንቋ ጋር’ የተያያዘ የሦስት ዓመት ሥልጠና እንዲወስዱ ተገደው ነበር። እዚህ ቦታ ላይ የገባው ‘ከለዳውያን’ የሚለው ቃል የተማረውን ክፍል የሚያመለክት በመሆኑ ይህ ሌላ ቋንቋ የመማር ጉዳይ ብቻ አልነበረም። በዚህ መንገድ ዕብራውያኑ ወጣቶች ብልሹ ለሆነው የባቢሎናውያን ትምህርት ተጋልጠው ነበር።—ዳንኤል 1:1-7
6. ዳንኤል በጎነትን ተከታትሏል ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
6 ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ በዙሪያቸው ካለው ሁኔታ ጋር ተመሳስለው እንዲኖሩ የሚያስገድድ ብዙ ተጽእኖ የነበረባቸው ቢሆንም ከብልግና ይልቅ በጎነትን መርጠዋል። ዳንኤል 1:21 እንደ 1980 ትርጉም “በዚህ ዓይነት ዳንኤል የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እስከነገሠበት መጀመሪያ ዓመት ድረስ በቤተ መንግሥት ውስጥ ማገልገሉን ቀጠለ” ይላል። አዎን፣ ዳንኤል የተለያዩ ኃያላን ነገሥታት ሲፈራረቁ 80 ለሚያክሉ ዓመታት በጎ የይሖዋ አገልጋይ ሆኖ ማገልገሉን ‘ቀጥሏል።’ ዳንኤል ብልሹ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ተመሳጥረው በሚፈጽሙት ሤራና በጾታ ብልግና የተሞላ የባቢሎናውያን ሃይማኖት መሀል ለአምላክ የታመነ ሆኖ ቀጥሏል። ዳንኤል በጎነትን ከመከታተል ወደኋላ አላለም።
7. ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ከተከተሉት ጎዳና ምን ነገር መማር እንችላለን?
7 ፈሪሃ አምላክ ከነበረው ከዳንኤልና ከጓደኞቹ ብዙ ነገር መማር እንችላለን። የባቢሎናውያንን ባሕል ተጽእኖ ተቋቁመው በጎነትን ተከታትለዋል። የባቢሎናውያን ስም ቢሰጣቸውም የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸው በጉልህ ይታይ ነበር። እንዲያውም የባቢሎኑ ንጉሥ ከ70 ዓመታት በኋላ እንኳ ዳንኤልን በዕብራዊ ስሙ ጠርቶታል! (ዳንኤል 5:13) ዳንኤል በረጅም የሕይወት ዘመኑ በሙሉ በጥቃቅን ነገሮች እንኳ ሳይቀር አቋሙን ለማላላት አሻፈረኝ ብሏል። ገና በወጣትነቱ “ደስ የሚያሰኘውን የንጉሡን ምግብ በመመገብ . . . ራሱን ላለማርከስ ቁርጥ ውሳኔ” አድርጎ ነበር። (ዳንኤል 1:8 የ1980 ትርጉም) ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ የወሰዱት ይህ የማያወላውል አቋም በኋላ የገጠሟቸውን የሕይወትና የሞት ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንደሰጣቸው ምንም አያጠራጥርም።—ዳንኤል ምዕራፍ 3 እና 6
ዛሬ በጎነትን መከታተል
8. ክርስቲያን ወጣቶች በሰይጣን ዓለም እንዳይዋጡ መከላከል የሚችሉት እንዴት ነው?
8 ዛሬ ያሉት የአምላክ ሕዝቦችም ልክ እንደ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ በሰይጣን ክፉ ዓለም ላለመዋጥ ትግል ያደርጋሉ። (1 ዮሐንስ 5:19) ክርስቲያን ወጣት ከሆንክ እኩዮችህ በአለባበስ፣ በፀጉር አያያዝና በሙዚቃ ረገድ የእነርሱን ቅጥ ያጣ ምርጫ እንድትከተል ጠንካራ ግፊት ያሳድሩብህ ይሆናል። የመጣውን ፋሽን ሁሉ ከመከተል ይልቅ ጸንተህ ቁም፤ ‘ይህን ዓለም አትምሰል።’ (ሮሜ 12:2) ‘ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደህ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ በጽድቅ ለአምላክ ያደርክ ሆነህ ተመላለስ።’ (ቲቶ 2:11, 12 NW) ትልቁ ነገር በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትህ እንጂ በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትህ አይደለም።—ምሳሌ 12:2
9. በንግዱ ዓለም የተሠማሩ ክርስቲያኖች ምን ግፊቶች ሊገጥሟቸው ይችላሉ? እንዴት መመላለስስ ይገባቸዋል?
9 በዕድሜ የጎለመሱ ክርስቲያኖችም ግፊት ስለሚገጥማቸው በጎዎች መሆን ይኖርባቸዋል። በንግድ ሥራ የተሠማሩ ክርስቲያኖች አጠያያቂ ዘዴዎችን ለመጠቀም ወይም መንግሥት ያወጣቸውን መተዳደሪያ ደንቦች ወይም የቀረጥ ሕጎች ለመጣስ ሊፈተኑ ይችላሉ። የንግድ ተፎካካሪዎቻችን ወይም አብረውን ያሉት የሥራ ባልደረቦቻችን የሚያደርጉት ነገር ምንም ይሁን ምን ‘በነገር ሁሉ በሐቀኝነት ልንኖር’ ይገባናል። (ዕብራውያን 13:18 NW) ቅዱሳን ጽሑፎች ከአሠሪዎቻችን፣ ከሠራተኞቻችን፣ ከደንበኞቻችንና ከባለ ሥልጣኖች ጋር በሐቀኝነትና በአግባቡ እንድንመላለስ ያዝዙናል። (ዘዳግም 25:13-16፤ ማቴዎስ 5:37፤ ሮሜ 13:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:18፤ ቲቶ 2:9, 10) በተጨማሪም በንግድ ነክ ጉዳዮቻችንም ሥርዓታማ ለመሆን እንጣር። ትክክለኛ መዝገብ በመያዝና ስምምነቶችን በጽሑፍ በማስፈር ብዙውን ጊዜ ያለመግባባቶችን ማስቀረት እንችላለን።
ራሳችሁን ጠብቁ!
10. የሙዚቃ ምርጫችንን በሚመለከት ‘ራሳችንን መጠበቅ’ የሚገባን ለምንድን ነው?
10 መዝሙር 119:9 በአምላክ ዓይን በጎ ሆኖ መኖር የሚቻልበትን ሌላ ዘርፍ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። መዝሙራዊው “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው” ሲል ዘምሯል። በጣም ውጤታማ ከሆኑት የሰይጣን መሣሪያዎች አንዱ ሙዚቃ ሲሆን ስሜትን የመቀስቀስ ኃይል አለው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖች ሙዚቃን በሚመለከት ‘ራሳቸውን መጠበቅ’ ተስኗቸው እንደ ራፕና ሄቪ ሜታል ባሉት መጥፎ የሙዚቃ ዓይነቶች ተወስደዋል። አንዳንዶች እንዲህ ዓይነት ሙዚቃ እኔን ምንም አይጎዳኝም ወይም ደግሞ እኔ እኮ ግጥሙን አልሰማም ይሉ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የሚያስደስታቸው ሙዚቃው ሲደልቅ ወይም ጠንካራው የጊታር ድምፅ ሲነዝር መስማት ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ለክርስቲያኖች ጉዳዩ አንድን ነገር የመውደድና ያለመውደድ ብቻ አይደለም። እነርሱ የሚያሳስባቸው ‘ለጌታ ደስ የሚያሰኝ’ መሆን አለመሆኑ ነው። (ኤፌሶን 5:10) በጥቅሉ ሲታይ የሄቪ ሜታልና የራፕ ሙዚቃዎች ጸያፍ ንግግሮችን፣ ዝሙትን አልፎ ተርፎም ሰይጣናዊ አምልኮና እነዚህን የመሳሰሉትን ብልግናዎች የሚያስተጋቡ ሲሆኑ እነዚህ ነገሮች ደግሞ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ቦታ የላቸውም።a (ኤፌሶን 5:3) ወጣቶችም ሆንን አዋቂዎች በሙዚቃ ምርጫዬ ረገድ እየተከታተልኩ ያለሁት በጎነትን ነው ወይስ ብልግናን? በሚለው ጥያቄ ላይ ማሰባችን የተገባ ይሆናል።
11. አንድ ክርስቲያን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ የቪዲዮ ፊልሞችን እና ሲኒማዎችን በተመለከተ ራሱን መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው?
11 ብዙዎቹ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የቪዲዮ ፊልሞችና ሲኒማዎች ብልግናን የሚያስፋፉ ናቸው። አንድ ታዋቂ የሥነ አእምሮ ባለሙያ እንዳሉት ዛሬ በሚወጡት በአብዛኞቹ ሲኒማዎች ‘በሕይወት ውስጥ ዋነኛው ነገር መደሰት ነው የሚለው አስተሳሰብ፣ የጾታ ድርጊቶች፣ ዓመፅ፣ ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት’ ገንነው ይታያሉ። እንግዲያው በዛሬው ጊዜ ራስን መጠበቅ ለማየት በምንፈልገው ነገር ረገድ መራጮች መሆንን ይጨምራል። መዝሙራዊው “ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 119:37) ጆሴፍ የተባለ አንድ ክርስቲያን ወጣት ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ አውሏል። ሲያየው የነበረ አንድ ፊልም ግልጽ የጾታ ብልግናና ዓመፅ ማሳየት ሲጀምር አዳራሹን ለቅቆ ወጣ። ይህን ለማድረግ እፍረት ተሰምቶት ነበርን? “በፍጹም” ይላል ጆሴፍ። “በመጀመሪያ ያሰብኩት ስለ ይሖዋና እርሱን ማስደሰት ስለ መቻሌ ነበር።”
ጥናትና ማሰላሰል የሚጫወቱት ሚና
12. በጎነትን ለመከታተል እንድንችል የግል ጥናትና ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?
12 ከክፉ ነገሮች መራቅ ብቻ አይበቃም። በጎነትን መከታተል በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ ልንሠራባቸው እንድንችል እነዚህን ጥሩ ነገሮች ማጥናትንና በእነርሱ ላይ ማሰላሰልን ይጨምራል። መዝሙራዊው “ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 119:97) መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን በግል ማጥናት የሳምንቱ ፕሮግራምህ ክፍል ነውን? የአምላክን ቃል በትጋት ለማጥናትና ባጠናነው ነገር ላይ ጸሎት የታከለበት ማሰላሰል ለማድረግ ጊዜ መዋጀት ፈታኝ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ነገሮች ላይ ጊዜ መዋጀት ይቻላል። (ኤፌሶን 5:15, 16) ምናልባትም የማለዳውን ሰዓት ለጸሎት፣ ለጥናትና ለማሰላሰል በሚገባ ልትጠቀምበት ትችላለህ።—ከመዝሙር 119:147 ጋር አወዳድር።
13, 14. (ሀ) ማሰላሰል ይህ ነው የማይባል ጠቀሜታ አለው ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) የጾታ ብልግናን እንድንጸየፍ ሊረዳን የሚችለው በየትኞቹ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰል ነው?
13 ማሰላሰል የተማርነውን ነገር እንዳንረሳ ስለሚረዳን ያለው ጠቀሜታ ይህ ነው አይባልም። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላካዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አምላክ ዝሙትን እንደሚከለክል ማወቅ አንድ ነገር ሲሆን ‘ክፉውን ነገር በመጸየፍ ከበጎ ነገር ጋር መጣበቅ’ ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። (ሮሜ 12:9) “እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጐምጀት ነው” በማለት አጥብቆ እንደሚመክረው እንደ ቆላስይስ 3:5 በመሳሰሉ ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰላችን ይሖዋ ስለ ጾታ ብልግና ያለውን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ልገድለው የሚገባኝ የጾታ ፍትወት ምን ዓይነት ነው? ርኩስ ምኞቶችን እንዳይቀሰቅስብኝ ላስወግደው የሚገባኝ ነገር ምን አለ? ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ ላደርጋቸው የሚገቡኝ ለውጦች አሉን?’—ከ1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2 ጋር አወዳድር።
14 ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከዝሙት እንዲርቁና ራሳቸውን እንዲገዙ አጥብቆ አሳስቧል፤ ይህም ‘የሌላውን ወንድማቸውን መብት እንዳይጋፉና እንዳይጎዱት’ ይጠብቃቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 4:3-7 NW) ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ዝሙት መፈጸም ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ኃጢአት ብሠራ በራሴና በሌሎች ላይ የማስከትለው ጉዳት ምንድን ነው? በመንፈሳዊ፣ በስሜታዊና በአካላዊ ሁኔታዬ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ምንድን ነው? የአምላክን ሕግ የጣሱና ንስሐ ያልገቡ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችስ? ምን ደርሶባቸዋል?’ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ እንዲህ ዓይነቱ አድራጎት በሚናገሩት ነገር ላይ በጥሞና ማሰብ በአምላክ ዓይን ክፉ ለሆነው ነገር ያለንን ጥላቻ ያጠናክርልናል። (ዘጸአት 20:14፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 6:9, 10፤ ገላትያ 5:19-21፤ ራእይ 21:8) ጳውሎስ ዝሙትን የሚያደርግ “ሰውን የሚያቃልል አይደለም፣ . . . አምላክን ነው እንጂ” ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 4:8 NW) ሰማያዊ አባቱን ሊያቃልል የሚፈልግ እውነተኛ ክርስቲያን ማን ነው?
በጎነትና ባልንጀርነት
15. በጎነትን ለመከታተል በምናደርገው ጥረት ባልንጀርነት ምን ሚና ይጫወታል?
15 በጎዎች ሆነን ለመኖር የሚረዳን ሌላው ነገር መልካም ባልንጀርነት ነው። መዝሙራዊው “እኔ ለሚፈሩህ [ይሖዋን ለሚፈሩ] ሁሉ፣ ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 119:63) በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ የሚገኘው ጤናማ ባልንጀርነት ያስፈልገናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ራሳችንን የምናገልል ከሆነ ስለራሳችን ጥቅም ብቻ የምናስብ እንሆንና በቀላሉ በብልግና ልንዋጥ እንችላለን። (ምሳሌ 18:1) ይሁን እንጂ ሞቅ ያለው ክርስቲያናዊ ወዳጅነት በጎዎች ሆነን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠናክርልን ይችላል። እርግጥ ነው ከክፉ ባልንጀርነትም ልንርቅ ይገባናል። ጎረቤቶቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንንና አብረውን የሚማሩትን በወዳጅነት ልንመለከታቸው እንችላለን። ሆኖም በጥበብ የምንመላለስ ከሆነ ክርስቲያናዊ በጎነትን ከማይከታተሉ ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ከመፍጠር እንቆጠባለን።—ከቆላስይስ 4:5 ጋር አወዳድር።
16. አንደኛ ቆሮንቶስ 15:33ን ሥራ ላይ ማዋል በዛሬው ጊዜ በጎነትን ለመከታተል የሚረዳን እንዴት ነው?
16 ጳውሎስ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል ጽፏል። ጳውሎስ ይህን ሲናገር አማኞች ቅዱስ ጽሑፋዊውን የትንሣኤ ትምህርት ከማይቀበሉት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ጋር በመወዳጀት እምነታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ማስጠንቀቁ ነበር። ከጳውሎስ ማስጠንቀቂያ በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ የሚኖረንን ባልንጀርነት ይነካል። (1 ቆሮንቶስ 15:12, 33) ከእኛ የግል አመለካከት ጋር ስላልተስማሙ ብቻ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ልንርቃቸው እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 7:4, 5፤ ሮሜ 14:1-12) ያም ሆኖ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች አጠያያቂ የሆነ አካሄድ ከጀመሩ ወይም የማማረርና የማጉረምረም መንፈስ ካመጡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። (2 ጢሞቴዎስ 2:20-22) ‘እርስ በርስ ልንተናነጽ ከምንችላቸው’ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረባችን ጥበብ ይሆናል። (ሮሜ 1:11, 12) ይህም የበጎነትን ጎዳና እንድንከታተልና ‘በሕይወት መንገድ’ መመላለሳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።—መዝሙር 16:11
በጎነትን መከታተላችሁን ቀጥሉ
17. በዘኁልቁ ምዕራፍ 25 መሠረት እስራኤላውያን ምን አደጋ ደርሶባቸዋል? ይህስ ለእኛ ምን ትምህርት ይሰጠናል?
17 እስራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው ጥቂት ቀደም ብሎ በሺህዎች የሚቆጠሩት ብልግናን ለመከተል በመምረጣቸው መከራን ተቀብለዋል። (ዘኁልቁ ምዕራፍ 25) ዛሬም የይሖዋ ሕዝቦች ወደ አዲሱ ዓለም ሊገቡ የቀራቸው ጥቂት ጊዜ ብቻ ነው። ወደዚህ አዲስ ዓለም የመግባት ልዩ መብት የሚያገኙት የዓለምን የብልግና አኗኗር አሻፈረኝ ብለው የተመላለሱ ሰዎች ናቸው። ፍጽምና የሌለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የኃጢአት ዝንባሌ ይኖረን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አምላክ የቅዱስ መንፈሱን የጽድቅ አመራር እንድንከተል ሊረዳን ይችላል። (ገላትያ 5:16፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3, 4) እንግዲያውስ ኢያሱ ለእስራኤላውያን የሰጠውን ጥብቅ ማሳሰቢያ እንጠብቅ:- “እግዚአብሔርን ፍሩ፣ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት።” (ኢያሱ 24:14) ይሖዋን ላለማሳዘን አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳደራችን የበጎነትን ጎዳና ለመከታተል ይረዳናል።
18. ብልግናን እና በጎነትን በተመለከተ ሁሉም ክርስቲያኖች ምን ቁርጥ ውሳኔ ሊያደርጉ ይገባል?
18 የልብህ ምኞት አምላክን ማስደሰት ከሆነ ጳውሎስ የሰጠውን ጥብቅ ምክር ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ:- “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።” ይህን ብታደርግ ምን ታገኛለህ? ጳውሎስ “እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:8, 9) አዎን፣ በይሖዋ እርዳታ ከብልግና ርቀህ በጎነትን ልትከታተል ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሚያዝያ 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 19-24ን እንዲሁም በየካቲት 8፣ የካቲት 22ና መጋቢት 22, 1993 እና በኅዳር 22, 1996 ንቁ! መጽሔት (በእንግሊዝኛ) ላይ የወጡትን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች” . . . የሚሉትን ዓምዶች ተመልከት።
ለክለሳ የቀረቡ ጥያቄዎች
◻ በጎነትን ለመከታተል ምን ያስፈልጋል?
◻ ሕዝቅያስ፣ ዳንኤል እና ሦስቱ ዕብራውያን በጎ ሆነው የተመላለሱት በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሥር እያሉ ነው?
◻ የሰይጣንን ዘዴዎች በመቋቋም ረገድ ዳንኤልን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ክርስቲያኖች መዝናኛን በሚመለከት ራሳቸውን መጠበቅ የሚገባቸው ለምንድን ነው?
◻ በጎነትን በመከታተል ረገድ፣ ጥናት ማሰላሰልና ከሌሎች ጋር የሚኖረን ባልንጀርነት ምን ድርሻ አላቸው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቱ ሕዝቅያስ ዙሪያውን በሞሎክ አምላኪዎች ቢከበብም በጎነትን ተከታትሏል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ክርስቲያኖች መዝናኛን በተመለከተ ራሳቸውን መጠበቅ ይገባቸዋል