‘አንተ ታናሽ መንጋ፣ አትፍራ’
“አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።”—ሉቃስ 12:32
1. ኢየሱስ ‘አንተ ታናሽ መንጋ፣ አትፍራ’ ብሎ እንዲናገር ያደረገው ነገር ምን ነበር?
“ሳታቋርጡ [የአምላክን] መንግሥት ፈልጉ።” (ሉቃስ 12:31 አዓት) ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ለደቀ መዛሙርቱ በተናገረ ጊዜ በእሱ ዘመን ከነበሩት አንስቶ እስከ አሁን ያሉትን ክርስቲያኖች አስተሳሰብ የመራ አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ገልጿል። የአምላክ መንግሥት በኑሮአችን ውስጥ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። (ማቴዎስ 6:33) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በሉቃስ ዘገባ ውስጥ ለአንድ ልዩ የክርስቲያኖች ቡድን የፍቅርና የማረጋጊያ ቃላትን ተናግሯል። እንዲህ አለ፦ “አንተ ታናሽ መንጋ፣ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።” (ሉቃስ 12:32) መልካሙ እረኛ ኢየሱስ የቅርብ ደቀ መዛሙርቱ ከፊታቸው በጣም አስቸጋሪ የሆነ ጊዜ እንደሚጠብቃቸው ያውቅ ነበር። ቢሆንም የአምላክን መንግሥት መፈለጋቸውን ከቀጠሉ ምንም የሚፈሩበት ምክንያት አልነበረም። በመሆኑም ኢየሱስ የሰጣቸው ማሳሰቢያ ኃይለኛ ትእዛዝ የሚያስተላልፍ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ትምክህትና ድፍረት እንዲያገኙ የሚያደርግ በፍቅር የተነገረ የተስፋ ቃል ነበር።
2. የታናሹ መንጋ አባሎች እነማን ናቸው? ልዩ መብት ያገኙትስ ለምንድን ነው?
2 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እየተናገረ ነበር፤ “አንተ ታናሽ መንጋ” በማለትም ጠርቷቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋ ‘መንግሥትን ለሚሰጣቸው’ ሰዎች እየተናገረ ነበር። በኋለኞቹ ዘመናት ኢየሱስን ከሚቀበሉት ብዙ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ በእርግጥም በጣም አነስተኛ ነበሩ። በተጨማሪም አስደናቂ በሆነው ንጉሣዊ አገልግሎት ለመካፈል መብት የተመረጡ ስለሆኑ በጣም የተወደዱ ናቸው። አባታቸው፣ ታላቁ እረኛ ይሖዋ፣ የታናሹ መንጋ አባሎችን በክርስቶስ መሲሐዊት መንግሥት ሰማያዊ ውርሻ እንዲያገኙ ጠርቷቸዋል።
ታናሹ መንጋ
3. ዮሐንስ ስለ ታናሹ መንጋ ምን ታላቅ ራእይ ተመል ክቷል?
3 ታዲያ እንዲህ ያለ አስደሳች ተስፋ የተሰጠው ታናሽ መንጋ አባሎች የሚሆኑት እነማን ናቸው? በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ናቸው። (ሥራ 2:1–4) ሐዋርያው ዮሐንስ እነዚህን ሰዎች በገና በእጆቻቸው የያዙ ሰማያዊ መዘምራን ሆነው ሲያያቸው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አየሁም፣ እነሆም፣ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግንባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፣ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።”—ራእይ 14:1, 4, 5
4. ታናሹ መንጋ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ምን ቦታ አለው?
4 እነዚህ የተቀቡ በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ጀምረው በምድር ላይ የክርስቶስ አምባሳደሮች ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:20) በአሁኑ ጊዜ ታማኝና ልባም ባሪያ ሆነው በአንድነት በማገልገል ጥቂት ቀሪዎች ብቻ ቀርተዋል። (ማቴዎስ 24:45፤ ራእይ 12:17) በተለይ ከ1935 ጀምሮ “ሌሎች በጎች” ማለትም በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ከእነርሱ ጋር ተቀላቅለዋል። እነዚህ ሰዎች በምድር በሙሉ ምሥራቹን በማወጁ ሥራ ይረዷቸዋል።—ዮሐንስ 10:16
5. የታናሹ መንጋ ቀሪ አባሎች ዝንባሌያቸው ምንድን ነው? መፍራት የማያስፈልጋቸውስ ለምንድን ነው?
5 በአሁኑ ጊዜም በምድር ላይ የሚገኙት የዚህ ታናሽ መንጋ ቀሪ አባሎች ምን ዓይነት ዝንባሌ አላቸው? ‘የማይናወጥ መንግሥት’ እንደሚቀበሉ ስለሚያውቁ ቅዱስ አገልግሎታቸውን በአምላካዊ ፍርሃትና በቅድስና ይፈጽማሉ። (ዕብራውያን 12:28) ወሰን የሌለው ደስታ የሚያስገኝ፣ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ መብት እንደተሰጣቸው በትሕትና ይገነዘባሉ። ኢየሱስ ስለ መንግሥቲቱ ሲናገር የጠቀሳትን “ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ” አግኝተዋል። (ማቴዎስ 13:46) ታላቁ መከራ እየቀረበ ሲሄድ የአምላክ ቅቡዓን በድፍረት ቆመዋል። ‘በታላቁ የይሖዋ ቀን’ በሰው ልጆች ዓለም ላይ የሚመጣው ነገር በጣም የሚያስፈራ ቢሆንም ቅቡዓን ቀሪዎች የወደፊቱ ጊዜ የሚያመጣውን በመፍራት አይርበተበቱም። (ሥራ 2:19–21) የሚፈሩበትስ ምን ምክንያት አለ?
ቁጥሩ ቀንሷል
6, 7. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉት የታናሹ መንጋ አባሎች ቁጥር አነስተኛ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) እያንዳንዱ ግለሰብ ተስፋውን እንዴት መመልከት ይኖርበታል?
6 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉት የታናሹ መንጋ አባሎች ቁጥር ተመናምኗል። ይህ በ1994 የመታሰቢያው በዓል ሪፖርት ላይ በግልጽ ታይቷል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 75,000 በሚሆኑ የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ በመካፈል የቀሪዎቹ አባላት መሆናቸውን ያሳዩት 8,617 ብቻ ናቸው። (ማቴዎስ 26:26–30) በአንጻሩ የጠቅላላው ተሰብሳቢ ቁጥር 12,288,917 ነበር። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህ የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ ያውቃሉ። ይሖዋ ታናሹን መንጋ ለማቋቋም 144,000 ቁጥር ወስኗል፤ በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮም ሲሰበስብ ቆይቷል። ቁጥሩ ሲሞላ የታናሹ መንጋ አባሎች ጥሪ እንደሚያበቃ የታወቀ ነው፤ እነዚህን ልዩ በረከት ያገኙ ሰዎች ጠቅላላ የመሰብሰቡ ሥራ በ1935 ማብቃቱ ለዚህ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ ሌሎች በጎች በፍጻሜው ዘመን “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሚሆኑ ተተንብዮአል። ይሖዋ ከ1935 ወዲህ በአጠቃላይ ሲሰበስብ የቆየው በምድራዊ ገነት የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያላቸውን እነዚህን እጅግ ብዙ ሰዎች ነው።—ራእይ 7:9፤ 14:15, 16፤ መዝሙር 37:29
7 ከእነዚህ በምድር ላይ ከሚገኙት የታናሹ መንጋ አባሎች መካከል አብዛኞቹ በአሁኑ ጊዜ በ70፣ በ80 እና በ90 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ጥቂቶቹ መቶኛ ዓመት ዕድሜያቸውን አልፈዋል። እነዚህ በሙሉ ዕድሜያቸው ምንም ያህል ቢሆን በሚያገኙት ሰማያዊ ትንሣኤ አማካኝነት በመጨረሻ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንደሚሆኑና በክብራማው መንግሥቱ አብረውት እንደሚነግሡ ያውቃሉ። እጅግ ብዙ ሰዎች የንጉሡ የክርስቶስ ምድራዊ ተገዥዎች ይሆናሉ። እያንዳንዱ ይሖዋ ለሚወዱት ባዘጋጀው ተስፋ ደስ ይበለው። ተስፋችንን የምንመርጠው እኛ አይደለንም። ይህን የሚወስነው ይሖዋ ነው። የወደፊት ተስፋቸው በሰማያዊ መንግሥትም ይሁን በመንግሥቲቱ በምትተዳደረው ገነት በምትሆነው ምድር ሁለቱም ክፍሎች አስደሳች የወደፊት ጊዜ ስለሚጠብቃቸው እጅግ ሊደሰቱ ይችላሉ።—ዮሐንስ 6:44, 65፤ ኤፌሶን 1:17, 18
8. 144,000ዎችን የማተሙ ሥራ ምን ያህል ተከናውኗል? ይህ ሥራ ሲያበቃ ምን ነገር ይከናወናል?
8 ሥጋዊ እስራኤል በአምላክ ዓላማ ውስጥ ለነበረው ቦታ ምትክ የሆነው 144,000 ሰዎችን ያቀፈው ታናሽ መንጋ፣ “የእግዚአብሔር እስራኤል” ነው። (ገላትያ 6:16) ስለዚህ ቀሪዎቹ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያለው የዚያ መንፈሳዊ ሕዝብ ቀሪ አባላት ሆነዋል። እነዚህ ቀሪዎች ይሖዋ እንደተቀበላቸው የሚያረጋግጠውን የመጨረሻ ውሳኔ እንዳገኙ የሚያመለክት ማኅተም እየተደረገባቸው ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በአንድ ራእይ ላይ ይህ ሲከናወን በመመልከት የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል፦ “የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፣ ምድርንና ባሕርንም ሊጎዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ፦ የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ አላቸው። የታተሙትንም ቁጥር ሰማሁ፤ ከ[መንፈሳዊ] እስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።” (ራእይ 7:2–4) ይህ መንፈሳዊ እስራኤላውያንን የማተም ሥራ እየተጠናቀቀ ስለሆነ በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ያመለክታል። በተጨማሪም አራቱ መላእክት በምድር ላይ ጥፋት የሚያመጡትን አራት ነፋሳት የሚለቁበት ‘ታላቅ መከራ’ በጣም ቀርቦ መሆን አለበት።—ራእይ 7:14
9. ታናሹ መንጋ የእጅግ ብዙ ሰዎችን ቁጥር መጨመር እንዴት ይመለከተዋል?
9 እስከ አሁን ድረስ የተሰበሰቡት እጅግ ብዙ ሰዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሆነዋል። ይህም የቅቡዓንን ልብ በእጅጉ ደስ ያሰኛል። በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉት የታናሹ መንጋ አባሎች ቁጥራቸው እየቀነሰ የሄደ ቢሆንም እየሰፋ በሄደው የአምላክ ምድራዊ ድርጅት ውስጥ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት ለመሸከም የሚችሉና ብቃት ያላቸው የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላትን አሠልጥነው አዘጋጅተዋል። (ኢሳይያስ 61:5) ኢየሱስ እንዳመለከተው ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ።—ማቴዎስ 24:22
“አትፍሩ”
10. (ሀ) በአምላክ ሕዝቦች ላይ ምን ጥቃት ይሰነዘራል? ይህስ ወደ ምን ይመራል? (ለ) እያንዳንዳችንን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ቀርበዋል?
10 ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ምድር አካባቢ ተጥለዋል። ሰይጣንና ጭፍሮቹ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የመጨረሻውን አጠቃላይ ጥቃት ለመሰንዘር በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀድሞ የተነገረው ይህ ጥቃት የማጎጉ ጎግ ጥቃት ተብሎ ተገልጿል። ዲያብሎስ ጥቃቱን በተለይ የሚያነጣጥረው በማን ላይ ነው? “በምድርም መካከል” ተዘልለው በሰላም በሚኖሩት የአምላክ መንፈሳዊ እስራኤል በሆኑት የታናሹ መንጋ የመጨረሻ ቀሪዎች ላይ አይደለምን? (ሕዝቅኤል 38:1–12) አዎን፣ ሆኖም የታማኞቹ ቅቡዓን ክፍልና ታማኝ ባልንጀሮቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች የሰይጣን ጥቃት ይሖዋ አምላክ ቅጽበታዊ ምላሽ እንዲሰጥ እንደሚያነሳሳው ይመለከታሉ። ሕዝቡን ከጥቃት ለመከላከል ጣልቃ ይገባል፤ ይህም “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” እንዲፈነዳ ያደርጋል። (ኢዩኤል 2:31) በዛሬው ጊዜ ታማኝና ልባም ባሪያ ይሖዋ በቅርቡ ጣልቃ ገብቶ ስለሚያከናውነው ነገር ማስጠንቀቂያ በማወጅ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ሕይወት አድን አገልግሎት እያከናወነ ነው። (ሚልክያስ 4:5፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16) እናንተስ፣ የይሖዋን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ በመካፈል ለዚህ አገልግሎት በትጋት ድጋፍ በመስጠት ላይ ናችሁን? ወደፊትስ ደፋር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን ትቀጥላላችሁን?
11. በዛሬው ጊዜ የድፍረት ዝንባሌ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 የአሁኑን ዓለም ሁኔታ ስንመለከት የታናሹ መንጋ አባላት ኢየሱስ “አትፍሩ” ሲል የነገራቸውን ቃል መከተላቸው ምንኛ ወቅታዊ ነው! በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚከናወኑትን ነገሮች ስንመለከት እንዲህ ያለው የድፍረት አቋም በጣም አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ የታናሹ መንጋ አባል፣ በግለሰብ ደረጃ እስከ መጨረሻው መጽናት እንደሚያስፈልገው ይገነዘባል። (ሉቃስ 21:19) የታናሹ መንጋ ጌታና አለቃ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወቱ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት እንደጸና ሁሉ እያንዳንዱ ቀሪም እስከ መጨረሻ መጽናትና ታማኝነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል።—ዕብራውያን 12:1, 2
12. ልክ እንደ ኢየሱስ ጳውሎስም ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዳይፈሩ ያሳሰባቸው እንዴት ነው?
12 ሁሉም ቅቡዓን ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል። የተቀባ የትንሣኤ ሰባኪ እንደመሆኑ መጠን የተናገራቸው ቃላት ኢየሱስ አትፍሩ ሲል ከሰጠው ምክር ጋር እንዴት እንደሚስማማ ልብ በሉ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በወንጌል እንደምሰብከው፣ ከሙታን የተነሣውን፣ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤ ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፣ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ። ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው፦ ከእርሱ ጋር ከሞትን፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ ብንጸና፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፣ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ ባናምነው፣ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።”—2 ጢሞቴዎስ 2:8–13
13. የታናሹ መንጋ አባሎች ምን ጠንካራ እምነቶች አሏቸው? ይህስ ምን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል?
13 የቅቡዓን ታናሽ መንጋ ቀሪ አባሎች እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ኃይለኛ መልእክት በሚያውጁበት ጊዜ የሚደርስባቸውን መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ናቸው። ስለተሰጣቸው መለኮታዊ የመዳን ተስፋና እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ቢሆኑ ‘የሕይወትን አክሊል’ ስለማግኘታቸው እርግጠኛ ስለሆኑ እምነታቸው ጥልቅ መሠረት ያለው ነው። (ራእይ 2:10) ቅጽበታዊ ትንሣኤና ለውጥ አግኝተው ነገሥታት ሆነው ለመግዛት ከክርስቶስ ጋር አንድ ይሆናሉ። ዓለምን ድል አድርገው ለተመላለሱበት የፍጹም አቋም ጠባቂነት መንገድ እንዴት ያለ ታላቅ ድል ይሆናል!—1 ዮሐንስ 5:3, 4
በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ ተስፋ
14, 15. የታናሹ መንጋ የትንሣኤ ተስፋ በዓይነቱ ብቸኛና ልዩ የሆነው እንዴት ነው?
14 ታናሹ መንጋ ያለው የትንሣኤ ተስፋ በዓይነቱ ብቸኛ ነው። በዓይነቱ ብቸኛ የሆነው በምን መንገድ ነው? አንደኛ ነገር ‘ጻድቃንና ዓመፀኞች’ ከሚያገኙት አጠቃላይ ትንሣኤ በፊት የሚከናወን ትንሣኤ ነው። (ሥራ 24:15) በ1 ቆሮንቶስ 15:20, 23 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የቅቡዓን ትንሣኤ የተወሰነ ቅደም ተከተል ጠብቆ የሚከናወን ነው። “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፣ በኋላም በመምጣቱ [“በመገኘቱ ጊዜ” አዓት] ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው።” የታናሹ መንጋ አባሎች ኢየሱስ ያሳየውን ዓይነት ጽናትና እምነት ካሳዩ፣ በተለይ እውነተኛው ጌታ በ1918 ለፍርድ ወደ ቤተ መቅደሱ ከመጣ ወዲህ ምድራዊ ሕይወታቸውን በሚጨርሱበት ጊዜ ምን ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቃቸው ያውቃሉ።—ሚልክያስ 3:1
15 ጳውሎስ ይህን ትንሣኤ በዓይነቱ ብቸኛ እንደሆነ አድርገን የምንመለከትበትን ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሰጥቶናል። 1 ቆሮንቶስ 15:51–53 ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነሆ፣ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን፤ . . . ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።” እነዚህ ቃላት የሚሠሩት በክርስቶስ መገኘት ዘመን ለሚሞቱት የታናሹ መንጋ አባሎች ነው። በሞት አንቀላፍተው ለረጅም ጊዜ መተኛት ሳያስፈልጋቸው “በድንገት በቅጽበተ ዓይን” ያለመሞትን ባሕርይ ይለብሳሉ።
16, 17. በተለይ በዛሬው ጊዜ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትንሣኤ ተስፋቸውን በተመለከተ የተባረኩት እንዴት ነው?
16 ይህን ግንዛቤ በመያዝ በራእይ 14:12, 13 ላይ የሚገኙትን የሐዋርያው ዮሐንስ ቃላት ትርጉም ለመረዳት እንችላለን። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው። ከሰማይም፦ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው። መንፈስ፦ አዎን፣ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፣ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።”
17 ለታናሹ መንጋ ቀሪዎች እንዴት ያለ በዓይነቱ ብቸኛና ልዩ የሆነ ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል! ወዲያው በሞት እንዳንቀላፉ ትንሣኤ ያገኛሉ። በመንፈሳዊው ዓለም የሚሰጣቸውን የሥራ ምድብ ሲቀበሉ እንዴት ያለ አስደናቂ ለውጥ ይሆንላቸዋል! ይህ የታናሹ መንጋ አባሎች ልዩ ክብር መጎናጸፍ እየቀጠለ በሄደበትና ዋና ዋናዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሊያልቁ በተቃረቡበት ሁኔታ በእውነትም የታናሹ መንጋ የመጨረሻ ቀሪዎች ‘መፍራት’ የለባቸውም። የእነርሱ አለመፍራት ደግሞ በዚህች ምድር ላይ ከታየው መከራ ሁሉ እጅግ ታላቅ የሆነው መከራ በሚመጣበት ጊዜ የሚያገኙትን መዳን ሲጠባበቁ ተመሳሳይ ዝንባሌ መኮትኮት ያለባቸውን እጅግ ብዙ ሰዎች ያበረታታል።
18, 19. (ሀ) የምንኖርበት ጊዜ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ቅቡዓንም ሆኑ ሌሎች በጎች መፍራት የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
18 ታናሹ መንጋ ያከናወናቸውን ሥራዎች ደጋግሞ ማሰብና መተረክ የታናሹ መንጋ አባሎችም ሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ በመፍራት እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል። አምላክ ፍርዱን የሚሰጥበት ሰዓት በጣም ቀርቧል። የቀረን የመዳን ቀን በጣም ውድ ነው። ሰዎች እርምጃ ለመውሰድ የቀራቸው ጊዜ በጣም የተወሰነ ነው። እኛ ግን የአምላክ ዓላማ ሳይፈጸም ይቀር ይሆናል ብለን አንፈራም። አለ አንዳች ጥርጥር ይፈጸማል!
19 ታላላቅ የሰማይ ድምፆች “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል” ሲሉ ተሰምቷል። (ራእይ 11:15) በእርግጥም ታላቁ እረኛ ይሖዋ፣ በጎቹን ‘ለስሙ ሲል በጽድቅ መንገድ በመምራት’ ላይ ነው። (መዝሙር 23:3) የታናሹ መንጋ አባላት አለ አንዳች ስህተት ወደ ሰማያዊ ሽልማታቸው በመወሰድ ላይ ናቸው። ሌሎች በጎችም ከታላቁ መከራ በሕይወት አልፈው በክርስቶስ ኢየሱስ በሚተዳደረው ክብራማ የአምላክ መንግሥት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ስለዚህ ምንም እንኳ የኢየሱስ ቃል የተነገረው ለታናሹ መንጋ ቢሆንም በምድር ላይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ “አትፍሩ” የሚለውን የኢየሱስ ቃል የሚሰሙበት ምክንያት አላቸው።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የታናሹ መንጋ ቀሪ አባሎች ቁጥር ይቀንሳል ብለን መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
◻ በዛሬው ጊዜ ያሉት ቅቡዓን ቀሪዎች ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
◻ ምንም እንኳ የማጎጉ ጎግ ጥቃት እየቀረበ ቢሆንም ክርስቲያኖች መፍራት የሌለባቸው ለምንድን ነው?
◻ የ144,000ዎቹ የትንሣኤ ተስፋ በተለይ በዛሬው ጊዜ በዓይነቱ ብቸኛና ልዩ የሆነው ለምንድን ነው?