ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ የመመልከት መንፈስ አዳብሩ
“ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው።”—ሉቃስ 9:48
1, 2. ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ምን ምክር ሰጣቸው? እንዲህ ያለ ምክር የሰጣቸውስ ለምንድን ነው?
ጊዜው 32 ዓ.ም. ነው። ኢየሱስ በገሊላ አውራጃ በነበረበት ወቅት አለመግባባት ተከሰተ። አንዳንዶቹ ሐዋርያት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ይከራከሩ ነበር። የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስ የልባቸውን ሐሳብ ስላወቀ አንድ ትንሽ ልጅ አምጥቶ አጠገቡ አቆመ፤ ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ ‘ይህን ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ የላከኝንም ይቀበላል። ምክንያቱም ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው።’” (ሉቃስ 9:46-48) ኢየሱስ በትዕግሥት ሆኖም ጠንከር ባለ መንገድ፣ የትሕትናን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ሐዋርያቱን ረድቷቸዋል።
2 ኢየሱስ ከሌሎች እንደሚያንሱ አድርገው እንዲያስቡ የሰጠው ምክር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዶች ከነበራቸው አመለካከት ጋር ይጣጣማል? ወይስ በወቅቱ ሰፍኖ ከነበረው መንፈስ ጋር ይጣረሳል? በዚያን ጊዜ በማኅበረሰቡ መካከል የነበረውን አመለካከት በተመለከተ ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንዲህ የሚል ሐሳብ ይሰጣል፦ “እርስ በርስ ባላቸው በማንኛውም ግንኙነት ‘ከሁሉ የሚበልጠው ማነው?’ የሚለው ጥያቄ ሁልጊዜ ይነሳል፤ ደግሞም እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ክብር ማግኘቱ ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ይህ ነገር ዘወትር ያሳስባቸው ነበር።” ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ ከማኅበረሰቡ የተለየ አመለካከት እንዲኖራቸው መክሯቸዋል።
3. (ሀ) ራስን ከሁሉም እንደሚያንስ አድርጎ መቁጠር ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆንብን የሚችለውስ ለምንድን ነው? (ለ) ራስን ዝቅ አድርጎ የመመልከት መንፈስ ማዳበርን በተመለከተ የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?
3 ‘የሚያንስ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ልከኛ፣ ትሑትና ምስኪን የሆነን ሰው፣ እዚህ ግባ የማይባልን ወይም ያን ያህል ግምት የማይሰጠውንና ተደማጭነት የሌለውን ሰው ያመለክታል። ኢየሱስ አንድን ትንሽ ልጅ ተጠቅሞ ሐዋርያቱ ትሑትና ቦታቸውን የሚያውቁ መሆን እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። ይህ ምክር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጠቃሚ እንደነበረ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖችም አስፈላጊ ነው። ራሳችንን በሆነ መንገድ ከሌሎች እንደምናንስ አድርገን መመልከት ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ሁላችንም የኩራት ዝንባሌ ያለን መሆኑ ለራሳችን ላቅ ያለ ቦታ የማግኘት ምኞት እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል። በምንኖርበት አካባቢ የሚታየው የፉክክር ዝንባሌና የዓለም መንፈስ ራስ ወዳድ ወይም ኃይለኛ እንድንሆን አሊያም በሌሎች ላይ እንድንሠለጥን ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ። ታዲያ ራስን ዝቅ አድርጎ የመመልከትን መንፈስ ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል? ‘ከሁላችን የሚያንሰው ታላቅ ነው’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? የትሕትናን መንፈስ ለማሳየት ጥረት ማድረግ ያለብን በየትኞቹ የሕይወታችን ዘርፎች ነው?
“የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው!”
4, 5. ትሕትናን ለማዳበር ምን ሊያነሳሳን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።
4 ትሕትናን ለማዳበር ከሚረዱን ነገሮች አንዱ ይሖዋ ከእኛ አንጻር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ማሰላሰል ነው። ደግሞም የይሖዋ ‘ማስተዋል በማንም አይመረመርም።’ (ኢሳ. 40:28) ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋን ግርማ አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!” (ሮም 11:33) ጳውሎስ ይህን ሐሳብ ከጻፈ 2,000 የሚያህሉ ዓመታት ያለፉ በመሆኑ የሰው ልጆች ስለተለያዩ ነገሮች ያላቸው እውቀት በእጅጉ ጨምሯል፤ ይሁንና ይህ ሐቅ አሁንም ቢሆን አልተለወጠም። ምንም ያህል እውቀት ብናካብት ስለ ይሖዋ፣ ስለ ሥራዎቹና ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድ ገና ማወቅ የሚኖርብን በርካታ ነገሮች እንዳሉ መገንዘባችን ትሑቶች እንድንሆን ሊያደርገን ይገባል።
5 ሌኦa አምላክ ስላከናወናቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ ማወቅ እንደማንችል መገንዘቡ ራሱን ዝቅ አድርጎ እንዲመለከት ረድቶታል። ሌኦ ወጣት እያለ ለሳይንስ ልዩ ፍቅር ነበረው። ስለ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ብዙ ነገር የማወቅ ጉጉት ስላደረበት ስለ ጠፈር አካላት ማጥናት ጀመረ፤ ከዚያም አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሰ። እንዲህ ብሏል፦ “በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ያላቸው የሳይንስ ጽንሰ ሐሳቦች በራሳቸው የሰው ልጅ ስለ ጽንፈ ዓለም የተሟላ እውቀት እንዲኖረው እንደማያስችሉ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ይህን ትቼ ሕግ ማጥናት ጀመርኩ።” ከጊዜ በኋላ ሌኦ የአንድ አውራጃ አቃቤ ሕግ ሆኖ የሠራ ሲሆን ከዚያም ዳኛ ሆኖ አገልግሏል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እሱና ባለቤቱ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመሩ፤ በመሆኑም እውነትን ተቀብለው ራሳቸውን በመወሰን የአምላክ አገልጋዮች ሆኑ። ሌኦ በጣም የተማረ ሰው ቢሆንም ራሱን ከሌሎች እንደሚያንስ አድርጎ እንዲቆጥር የረዳው ምንድን ነው? “ስለ ይሖዋም ሆነ ስለ ጽንፈ ዓለም የፈለገውን ያህል ብንማር እንኳ ልናውቀው የሚገባ ገና በጣም ብዙ ነገር እንዳለ መገንዘቤ ነው” ሲል ተናግሯል።
6, 7. (ሀ) ይሖዋ በትሕትና ረገድ ምን አስደናቂ ምሳሌ ትቷል? (ለ) የአምላክ ትሕትና አንድን ሰው “ታላቅ” የሚያደርገው እንዴት ነው?
6 ትሕትና እንድናሳይ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ይሖዋ ራሱ ትሑት መሆኑ ነው። “እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” የሚለውን ጥቅስ እስቲ ቆም ብለህ ለማሰብ ሞክር። (1 ቆሮ. 3:9) ይሄ በጣም የሚያስገርም ጉዳይ ነው! ይሖዋ በታላቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ሆኖ ሳለ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን አገልግሎታችንን መፈጸም የምንችልበትን አጋጣሚ በመስጠት አክብሮናል። እኛ የተከልነውና ያጠጣነው ዘር እንዲያድግ የሚያደርገው ይሖዋ ቢሆንም ከእሱ ጋር አብሮ የመሥራት መብት በመስጠት የተከበረ ቦታ እንዲኖረን አድርጓል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ታዲያ ይህ የአምላክን ትሕትና የሚያሳይ አስደናቂ ምሳሌ አይደለም? በእርግጥም፣ ይሖዋ በትሕትና ረገድ የተወው ምሳሌ ሁላችንም ራሳችንን ከሌሎች እንደምናንስ አድርገን እንድንመለከት ሊያነሳሳን ይገባል።
7 አምላክ በትሕትና ረገድ የተወው ምሳሌ በመዝሙራዊው ዳዊት ላይ ይህ ነው የማይባል በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ዳዊት “የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ድጋፍህ [“ትሕትናህ፣” NW] ታላቅ አድርጎኛል” ሲል ለይሖዋ ዘምሯል። (2 ሳሙ. 22:36) ዳዊት በእስራኤል ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን የቻለው ይሖዋ ራሱን ዝቅ አድርጎ ወይም ትሑት ሆኖ ለእሱ ትኩረት ስለሰጠው እንደሆነ ተገንዝቧል። (መዝ. 113:5-7) የእኛስ ሁኔታ ከዚህ ይለያል? የባሕርይን፣ የችሎታንና የመብትን ነገር ካነሳን ማናችንስ ብንሆን ከይሖዋ ‘ያልተቀበልነው ምን ነገር አለ?’ (1 ቆሮ. 4:7) ከሁሉ እንደሚያንስ አድርጎ የሚያስብ ሰው “ታላቅ” ነው ሊባል የሚችለው የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን ይበልጥ ተፈላጊ በመሆኑ ነው። (ሉቃስ 9:48) እስቲ ይህን ጉዳይ እንመልከት።
‘ታላቅ የሚባለው ከሁላችሁ የሚያንሰው ነው’
8. ትሕትና ለይሖዋ ድርጅት ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
8 ትሕትና በአምላክ ቲኦክራሲያዊ ድርጅት ረክተን እንድንኖርና በጉባኤ የሚደረገውን ዝግጅት እንድንደግፍ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ለምሳሌ ያህል፣ በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ያደገችውን ፔትራ የተባለችን ወጣት ሁኔታ እንመልከት። ፔትራ ነገሮችን በራሷ መንገድ ለማድረግ ስለፈለገች ከጉባኤው ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች። ከዓመታት በኋላ በጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረች። በአሁኑ ሰዓት ፔትራ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በመሆኗ ደስተኛ ነች፤ በተጨማሪም የጉባኤውን ዝግጅት በቅንዓት ትደግፋለች። አመለካከቷን የለወጠው ነገር ምንድን ነው? ፔትራ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “የአምላክ ድርጅት እንደ ቤቴ ሆኖ እንዲታየኝ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ባሕርያትን በሚገባ መረዳትና ማዳበር ጠይቆብኛል፤ እነሱም ትሕትናና ልክን ማወቅ ናቸው።”
9. ትሑት የሆነ ሰው ለምናገኛቸው መንፈሳዊ ምግቦች ምን አመለካከት አለው? ይህስ ይበልጥ ጠቃሚ ሰው እንዲሆን ያደርገዋል የምንለው ለምንድን ነው?
9 ትሑት የሆነ ሰው መንፈሳዊ ምግብን ጨምሮ ይሖዋ ላደረጋቸው ዝግጅቶች በሙሉ ልባዊ አድናቆት አለው። በመሆኑም እንዲህ ያለው ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠናል፤ በተጨማሪም መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን በጉጉት ያነባል። እንደ ሌሎቹ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ እያንዳንዱን አዳዲስ ጽሑፍ በመደርደሪያው ላይ ከማስቀመጡ በፊት የማንበብ ልማድ ይኖረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን በማንበብና በማጥናት፣ ትሑት መሆናችንንና አድናቆት እንዳለን የምናሳይ ከሆነ መንፈሳዊ እድገት እናደርጋለን፤ ይህ ደግሞ ይሖዋ በአገልግሎቱ ይበልጥ እንዲጠቀምብን በር ይከፍታል።—ዕብ. 5:13, 14
10. በጉባኤ ውስጥ ራሳችንን ዝቅ የማድረግ መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
10 ከሌሎች እንደሚያንስ የሚያስብ ሰው “ታላቅ” የሚሆንበት ሌላም መንገድ አለ። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆነው እንዲያገለግሉ በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ መሪነት የተሾሙ ብቃት ያላቸው ወንዶች አሉ። እነዚህ ወንድሞች ከጉባኤ ስብሰባዎችና ከመስክ አገልግሎት ጋር የተያያዙ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ያደራጃሉ እንዲሁም ለመንጋው እረኝነት ያደርጋሉ። ራሳችንን ዝቅ አድርገን እነዚህን ዝግጅቶች በፈቃደኝነት ስንደግፍ ለጉባኤው ደስታ፣ ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ዕብራውያን 13:7, 17ን አንብብ።) ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነህ እያገለገልክ ከሆነ ይሖዋ እንዲህ ዓይነት የአገልግሎት መብት ስለሰጠህ አመስጋኝ በመሆን ትሕትና ማሳየት አይገባህም?
11, 12. በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጥሩ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችለን የትኛው ባሕርይ ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?
11 ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሰው “ታላቅ” ይሆናል፤ በሌላ አባባል ለይሖዋ ድርጅት ይበልጥ ጠቃሚ ሰው ይሆናል፤ ምክንያቱም ትሑት መሆኑ በአምላክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጥሩ አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችለዋል። ኢየሱስ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ በዘመኑ ተስፋፍቶ የነበረው መንፈስ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ስለነበር ራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ ምክር መስጠት አስፈልጎታል። በሉቃስ 9:46 ላይ “ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር” የሚል ዘገባ እናገኛለን። እኛስ ከእምነት ባልንጀሮቻችን እንደምንልቅ ወይም ከሰው ሁሉ እንደምንበልጥ ማሰብ ጀምረን ይሆን? በዙሪያችን ያሉ በርካታ ሰዎች በኩራት የተወጠሩና ራስ ወዳዶች ናቸው። እኛ ግን በትሕትና በመመላለስ እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ እንዳይጋባብን መከላከል ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግና የይሖዋን ፈቃድ ስናስቀድም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የብርታት ምንጭ እንሆናለን።
12 ኢየሱስ ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ የሰጠው ምክር በእርግጥም ትሑት እንድንሆን ያነሳሳናል። ታዲያ በሁሉም የሕይወታችን ዘርፍ ራሳችንን ዝቅ የማድረግ መንፈስ ለማሳየት ጥረት ማድረግ አይኖርብንም? እስቲ ይህን ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እንመልከት።
ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ ለማየት ጥረት አድርጉ
13, 14. አንድ ባል ወይም ሚስት ራሳቸውን ዝቅ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህስ በትዳራቸው ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
13 በትዳር ውስጥ። በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሰዎች የግል መብቶቻቸውን ለማስከበር ሲሉ የሌሎችን መብት መጋፋት ቢኖርባቸውም እንኳ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። በአንጻሩ ግን ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩት ጳውሎስ እንድናዳብረው ባበረታታን መንፈስ ነው። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ” ብሏል። (ሮም 14:19) ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሰው ከሁሉም ጋር በተለይ ከትዳር ጓደኛው ጋር በሰላም ለመኖር የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል።
14 በመዝናኛ ረገድ ይህ ባሕርይ ምን ሚና እንደሚጫወት እስቲ እንመልከት። አንድ ባልና ሚስት መዝናኛን በተመለከተ የተለያየ ምርጫ ይኖራቸው ይሆናል። ባልየው ትርፍ ጊዜውን ቤቱ ቁጭ ብሎ መጽሐፍ በማንበብ ማሳለፍ ያስደስተው ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሚስትየዋ የምትፈልገው ወጣ ብሎ ምግብ መመገብ ወይም ጓደኞቻቸውን መጠየቅ ይሆናል። ባልየው ትሕትና ማሳየቱና ለራሱ ምርጫ ብቻ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ እሷ ምን እንደምትወድና ምን እንደምትጠላ ለማወቅ ልባዊ ጥረት ማድረጉ ሚስቱ እሱን ማክበር ይበልጥ ቀላል እንዲሆንላት አያደርግም? ባልየውስ ቢሆን ሚስቱ በዚያም ሆነ በዚህ የፈለገችውን ነገር ለማሳካት ከመጣር ይልቅ ለእሱ ፍላጎት ቦታ እንደምትሰጥ ሲመለከት ለሚስቱ ያለው ፍቅርና አድናቆት አይጨምርም? ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ ከሆነ ትዳራቸው ይጠናከራል።—ፊልጵስዩስ 2:1-4ን አንብብ።
15, 16. በመዝሙር 131 ላይ ዳዊት ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዲኖረን አበረታቷል? ይህስ ጉባኤ ውስጥ በምናሳየው መንፈስ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
15 በጉባኤ ውስጥ። በዓለም ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች የፈለጉትን ነገር ወዲያውኑ ማግኘት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ትዕግሥት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ አንድን ነገር በትዕግሥት መጠበቅ ፈተና ይሆንባቸዋል። ራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስ ማዳበራችን ይሖዋን በትዕግሥት እንድንጠባበቅ ወይም ተስፋ እንድናደርግ ይረዳናል። (መዝሙር 131:1-3ን አንብብ።) ትሑት መሆንና ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ የደኅንነት ስሜትና በረከት እንዲሁም እረፍትና እርካታ ያስገኛል። ዳዊት ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን አምላካቸውን በትዕግሥት ወይም በተስፋ እንዲጠባበቁ ያበረታታው ለዚህ ነው!
16 አንተም ትሑት በመሆን ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅህ እንዲህ ያለ እረፍት ያስገኝልሃል። (መዝ. 42:5) ለምሳሌ ‘መልካም ሥራን በመመኘት የበላይ ተመልካች ለመሆን እየተጣጣርክ’ ነው እንበል። (1 ጢሞ. 3:1-7) እርግጥ ነው፣ አንድ የበላይ ተመልካች ሊያዳብራቸው የሚገቡ ባሕርያትን መንፈስ ቅዱስ በውስጥህ እንዲያፈራ አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሃል። ይሁንና አንተ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከሌሎች ይልቅ ረዘም ያለ ጊዜ እንደፈጀብህ ቢሰማህስ? ራሱን ዝቅ አድርጎ አንድ የአገልግሎት መብት ላይ ለመድረስ በትዕግሥት የሚጠባበቅ ሰው ይሖዋን በደስታ ማገልገሉን ይቀጥላል፤ እንዲሁም የተሰጠውን ማንኛውንም ኃላፊነት በደስታ ያከናውናል።
17, 18. (ሀ) ሌሎችን ይቅርታ መጠየቃችንና ለሌሎች ይቅርታ ማድረጋችን ምን ጥቅሞች አሉት? (ለ) በምሳሌ 6:1-5 ላይ ምን ዓይነት ባሕርይ እንድናሳይ ተበረታተናል?
17 ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት። ብዙ ሰዎች ይቅርታ መጠየቅ ይተናነቃቸዋል። ይሁንና የአምላክ አገልጋዮች ስህተታቸውን በማመንና ይቅርታ በመጠየቅ ራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስ እንዳላቸው ያሳያሉ። በተጨማሪም ሌሎች ሲበድሏቸው ይቅር ለማለት ዝግጁ ናቸው። የኩራት መንፈስ መከፋፈልና ጠብ እንዲስፋፋ የሚያደርግ ሲሆን ይቅር ባይነት ግን በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።
18 ከአቅማችን በላይ የሆነ ሁኔታ አጋጥሞን የገባነውን ቃል ማክበር ሳንችል በምንቀርበት ጊዜ ልባዊ ይቅርታ በመጠየቅ ‘ራሳችንን ማዋረዳችንን’ ወይም ትሑት መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። ትሑት የሆነ ክርስቲያን ሌላው ወገን በተወሰነ መጠን ተጠያቂ እንደሆነ ቢሰማውም ትኩረት የሚያደርገው በራሱ ጉድለቶች ላይ ነው፤ እንዲሁም ስህተቱን አምኖ ለመቀበል ፈቃደኛ ነው።—ምሳሌ 6:1-5ን አንብብ።
19. ሁላችንም ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንድንመለከት ለተሰጠን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር አመስጋኝ እንድንሆን የሚያደርጉን የትኞቹ ምክንያቶች ናቸው?
19 ራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስ እንድናዳብር ለተሰጠን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ ምንኛ አመስጋኞች ነን! እንዲህ ያለውን መንፈስ ማሳየት አንዳንድ ጊዜ ተፈታታኝ ሊሆን ቢችልም ከፈጣሪያችን አንጻር ስላለን ቦታ ትክክለኛ አመለካከት መያዛችንና አምላክ ራሱ ትሑት እንደሆነ መገንዘባችን ይህን ግሩም ባሕርይ ለማዳበር ያነሳሳናል። እንዲህ በማድረግ ይበልጥ ተፈላጊ የሆንን የይሖዋ አገልጋዮች መሆን እንችላለን። እንግዲያው እያንዳንዳችን ራስን ዝቅ የማድረግ መንፈስ ለማዳበር የተቻለንን ጥረት እናድርግ።
a ስሞቹ ተቀይረዋል።