የሚያሳድግ አምላክ ነው፤ ግን አንተ የበኩልህን ታደርጋለህን?
የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ህሊናህ ተመልከት። በትላልቅ ዛፎች፣ በሚያማምሩ ቁጥቋጦዎችና በተዋቡ አበቦች በተከበበ ውብ የአትክልት ሥፍራ ውስጥ ነህ። እንደ ብርጭቆ የጠራ ውኃ በሚፈስበት ወንዝ ዳርና ዳር በጥንቃቄ የተከረከመ መስክ ተንጣልሎአል። የአካባቢውን ውበት የሚያበላሽ አንድም ነገር አይታይም። በአካባቢው ውበት ተደንቀህ ይህን ቆንጆ ቦታ የሠራው ማን እንደሆነ ትጠይቃለህ። አትክልተኛውም በትህትና ማንኛውንም ነገር የሚያሳድገው አምላክ ነው በማለት ይመልስልሃል።
ይህን እንዳላጣኸው የታወቀ ነው። ወደ ቤትህ ተመልሰህ በሚገባ ያልተያዘውን፣ አንዳችም የሚያምር ተክል ያልበቀለበትን፣ ቆሻሻ የተጠራቀምበትንና ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ በየጉድጓዱ ውኃ የሚጠራቀምበትን የራስህን ጓሮ ስትመለከት አትክልተኛው የተናገራቸው ቃላት ትዝ ይሉሃል። የጎበኘኸውን የመሰለ የአትክልት ቦታ እንዲኖርህ ከልብህ ትፈልጋለህ። ስለዚህም አትክልተኛው የተናገረውን ቃል አምነህ በጉልበትህ በርከክ ትልና አምላክ በጓሮህ የሚያማምሩ አበቦች እንዲያበቅልልህ ከልብህ ትጸልያለህ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ምንም ዓይነት ውጤት እንደማይገኝ የታወቀ ነው።
ስለ መንፈሳዊ ዕድገትስ ምን ሊባል ይቻላል? አዳዲስ ደቀ መዛሙርት የአምላክን ቃል እውነት እንዲያውቁ በማድረግ ወይም የግል መንፈሳዊ መሻሻል በማድረግ በኩል ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ለማየት ልባዊ ፍላጎት ሊኖርህ ይችላል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ይህን የመሰለውን መንፈሳዊ እድገት ለማስገኘት ኃይል እንዳለው በማመን ይሖዋ እድገት እንዲያስገኝ ከልብህ ትጸልይ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልባዊ ፍላጎትህ፣ ከልብ የቀረበው ጸሎትህና በአምላክ ኃይል መታመንህ ብቻውን ዕድገት ያስገኛልን?
አምላክ ያሳድጋል
መንፈሳዊ ዕድገት በማስገኘት ረገድ አንተ የምታበረክተው ድርሻ ከቁጥር የማይገባ፣ እንዲያውም ምንም ትርጉም የሌለው ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 3:5–7 ላይ የገለጸው ይህን አይደለምን? እንዲህ ሲል ጽፎአል:- “አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው። ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። እኔ ተከልሁ፣ አጵሎስም አጠጣ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር።”
ጳውሎስ እድገት ሲገኝ ስለተገኘው እድገት መመስገን የሚገባው አምላክ እንደሆነ መግለጹ ተገቢ ነው። አንድ አትክልተኛ መሬቱን ሊያዘጋጅ፣ ዘሩን ሊዘራና አትክልቱን በጥንቃቄ ሊንከባከብ ይችል ይሆናል። አትክልቶቹ የሚያድጉት ግን አምላክ ሕያዋን ነገሮችን ለመፍጠር ባለው አስደናቂ ኃይል ምክንያት ነው። (ዘፍጥረት 1:11, 12, 29) ታዲያ ጳውሎስ “የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም” ሲል ምን ማለቱ ነው? (“ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የሚተክሉትና የሚያጠጡት አትክልተኞች አይደሉም” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ) አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ረገድ ግለሰብ አገልጋይ የሚኖረውን የሥራ ድርሻ ማቃለሉና አገልግሎታችንን በምንም ዓይነት መንገድ ብናከናውን ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይኖረው መግለጹ ነበርን?
“የሚተክል ቢሆን . . . አንዳች አይደለም”
ጳውሎስ በዚህኛው የደብዳቤው ክፍል እያብራራ ያለው ስለ ክርስትና አገልግሎት ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ይልቅ ሰዎችን መከተል ሞኝነት መሆኑን ነው። በቆሮንቶስ ይኖሩ ከነበሩት አንዳንዶቹ እንደ ጳውሎስና አጵሎስ ለመሳሰሉት እውቅ የይሖዋ አገልጋዮች የማይገባ ክብር ይሰጡ ነበር። ሌሎች ደግሞ ከሌሎች ክርስቲያን ወንድሞች የሚበልጡ ናቸው ብለው የሚያስቡአቸውን ሰዎች ከፍ አድርገው ይመለከቱና ኑፋቄዎችን ያስፋፉ ነበር። — 1 ቆሮንቶስ 4:6–8፤ 2 ቆሮንቶስ 11:4, 5,13
በዚህ መንገድ ለሰዎች ከፍተኛ ክብር መስጠት ጤናማ ድርጊት አይደለም። ሥጋዊ አስተሳሰብ ስለሆነ ቅንዓትና ግጭት ይፈጥራል። (1 ቆሮንቶስ 3:3, 4) ጳውሎስ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የሚያስከትለውን ውጤት ገልጾአል። እንዲህ ይላል:- “በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ . . . እያንዳንዳችሁ እኔ የጳውሎስ ነኝ፣ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፣ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፣ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ።” — 1 ቆሮንቶስ 1:11, 12
ስለዚህ ሐዋርያው “የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም” ብሎ የጻፈው እንዲህ ያለውን ሥጋዊ አስተሳሰብ ለመዋጋትና የኢየሱስ ክርስቶስን መሪነት የመቀበልና በጉባዔ ውስጥ ለሚገኘው ለማንኛውም ዕድገት መከበር የሚኖርበት አምላክ መሆኑን አጥብቆ ለማስገንዘብ ፈልጎ ነው። ሐዋርያትና ሌሎቹ ሽማግሌዎች ተራ የጉባዔው አገልጋዮች ናቸው። አንዳቸውም ቢሆኑ ከሌሎቹ የሚበልጡ ሆነው መታየት አይገባቸውም። ራሳቸውም ቢሆኑ ልዩ መብትና ከበሬታ ለማግኘት መፈለግ አይገባቸውም። (1 ቆሮንቶስ 3:18–23) ስለዚህ “ለዘሩ ሕይወት ከሚሰጠው አምላክ ጋር ሲወዳደሩ” ተካዩም ሆነ ውኃ አጠጪው ከምንም የማይቆጠሩ እንደሆኑ ጳውሎስ ተናግሮአል። — 1 ቆሮንቶስ 3:7 ፊልፕስ ትርጉም
የአምላክ የሥራ ባልደረቦች
ስለዚህ ጳውሎስ ይህን ሲናገር በመትከልና በማጠጣት ረገድ የምንፈጽመውን የሥራ ድርሻ አስፈላጊነት አሳንሶ መመልከቱ አልነበረም። “አምላክ በጊዜው ያሳድገዋል” ብለን ዝም ብለን ተቀምጠን እርሱ እስኪያሳድግ እንድንጠብቅ መናገሩ አልነበረም። አሠራራችንም ሆነ የምንሠራው ሥራ በነገሮች አስተዳደግ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ያውቅ ነበር።
ጳውሎስ ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው ጠንክረው እንዲሠሩና የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ አዘውትሮ ያበረታታ የነበረው በዚህ ምክንያት ነው። ለወጣቱ ጢሞቴዎስ “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፣ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና” በማለት የሰጠውን ምክር ልብ በል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) “ከልብ አደራ እልሃለሁ። . . . በማስተማር ጥበብና በትዕግሥት ቃሉን በጥድፊያ ስበክ። . . . አገልግሎትህን አጠናቅቀህ ፈጽም።” (2 ጢሞቴዎስ 4:1, 2, 5 አዓት) ጢሞቴዎስ የሚፈጽመው የመትከልና የማጠጣት ሥራ በነገሮች አስተዳደግ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ የማያመጣ ቢሆን ኖሮ ችሎታውን ለማሻሻል መትጋቱ ምንም ዓይነት አስፈላጊነት አይኖረውም ነበር።
አንተም እንደ ጳውሎስና እንደ አጵሎስ የአምላክ የሥራ ባልደረባ ሆኖ የማገልገል ታላቅ መብት ልታገኝ ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 3:9፤ 2 ቆሮንቶስ 4:1፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:12) በዚህ ደረጃ የምትፈጽመው ሥራ ትልቅ ቦታ አለው። አንድ አትክልተኛ ምንም ዓይነት ጥረት ሳያደርግ አምላክ በተአምር የተዋበ የአትክልት ሥፍራ ያስገኝልኛል ብሎ አይጠብቅም። ታዲያ መንፈሳዊ ዕድገትስ ከዚህ የተለየ መሆን ይኖርበታልን? አይኖርበትም። ውድ የሆነውን የምድር ፍሬ በትዕግሥት እንደሚጠብቀው ገበሬ እኛም አምላክ የሚያሳድግበትን ጊዜ እየጠበቅን በትጋት መትከልና ማጠጣት ይኖርብናል። — ያዕቆብ 1:22፤ 2:26፤ 5:7
የራስህን ድርሻ ፈጽም
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው “እያንዳንዱ እንደራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል።” ስለዚህ የየራሳችንን ሥራ በምን ሁኔታ በማከናወን ላይ እንደምንገኝ ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል። — 1 ቆሮንቶስ 3:8
የአትክልተኝነት ሥራ ምሑር የሆኑት ጂዮፍሪ ስሚዝ “አትክልተኛ ለመሆን የተለየ ብቃት አያስፈልግም። የሚያስፈልገው የእፀዋት ፍቅር ብቻ ነው” ብለዋል። (ቁጥቋጦዎችና ትንንሽ ዛፎች ) የአምላክ የሥራ ባልደረባ ለመሆንም ልዩ የሆነ የተፈጥሮ ችሎታ ወይም ብቃት አያስፈልግም። የሚያስፈልገው ስለ ሰዎች የምናስብና የአምላክ መሣሪያ ሆነን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን ነው። — 2 ቆሮንቶስ 2:16, 17፤ 3:4–6፤ ፊልጵስዩስ 2:13
ጥሩ ችሎታ ያላቸው አንዳንድ አትክልተኞች የሚሰጡትን ምክር ተመልከት። አንድ የአትክልተኝነት ምሑር እንደተናገሩት አንድ ጀማሪ አትክልተኛ ከእርሱ የበለጠ ልምድ ያላቸው አትክልተኞች የሚነግሩትን ለመስማት ፈቃደኛ ከሆነ “ብዙ ሳይቆይ የተራቀቀ አትክልተኛ ይሆናል።” እኚሁ ሰው “የተራቀቀ አትክልተኛ ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ይማራል” ብለዋል። (ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦፍ ጋርደኒንግ ) በጥሩ ሁኔታ ለመትከልና ውኃ ለማጠጣት እንድትችል ይሖዋ የሚሰጠውን እርዳታና ማሠልጠኛ በፈቃደኝነት ትቀበላለህን? ከተቀበልህ በሥራው ጀማሪም ሆንክ ብዙ ልምድ ያለህ፣ ተጨማሪ ችሎታዎችን ለማዳበርና ሌሎችን ለማስተማር የበቃህ ትሆናለህ። — 2 ጢሞቴዎስ 2:2
ጂዮፍሪ ስሚዝ “ጀማሪው ለመስማትና ለመማር ፈቃደኛ ከሆነ በጣም ከባድ ከሆኑ ስህተቶች ሊጠበቅ ይችላል” ብለዋል። እኛም ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ ብንሰማ ነገሮችን እርሱ በሚፈልገው መንገድ ለመሥራት እንችላለን። ሁኔታችን እንደዚያ ከሆነ በቃላት ለመጣላት ከሚፈልጉ ጋር በሞኝነት ከመጨቃጨቅ እንርቃለን። — ምሳሌ 17:14፤ ቆላስይስ 4:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:23–26
ሌላው ጥሩ አትክልተኛ ለመሆን የሚያስችል ጥሩ ምክር ተጣድፎ መሬት መቆፈር ከመጀመር በፊት በጥንቃቄ ማሰብ ነው። ዘ አንሳይክሎፔድያ ኦፍ ጋርደኒንግ “ዶማህን መሬት ላይ ከማሳረፍህ በፊት የምትሰራውን ሥራ ቅጭ ብለህ አመዛዝን” ይላል። አንተስ ምን ለማከናወን እንደምትፈልግና እንዴት እንደምታከናውን በጥንቃቄና በጸሎት ሳታሰላስል ወደ ክርስቲያናዊ አገልግሎትህ ትሮጣለህን? ከመጀመርህ በፊት ዓላማህ ምን እንደሆነ በግልጽ ተረዳ። ለምሳሌ ያህል የምታገኛቸው ሰዎች ምን ዓይነት እንደሚሆኑና ምን ዓይነት ችግር ሊያጋጥምህ እንደሚችል አስበህ እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችልህን ዝግጅት አድርግ። ይህም ‘አንዳንዶችን ታድን ዘንድ . . . ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ትሆናለህ።’ — 1 ቆሮንቶስ 9:19–23
“እጅህን አትተው”
የአምላክ የሥራ ባልደረቦች የመሆን መብታችንን የምናደንቅ ከሆነ የበኩላችንን ድርሻ ከመፈጸም ወደኋላ አንልም። “ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም እንዲሆን አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም እጅህን አትተው።” (መክብብ 11:6) የመጨረሻው ውጤት በይሖዋ እጅ ያለ ቢሆንም ፍሬ ልናገኝ የምንችለው በትጋት ከዘራን ብቻ ነው። — መክብብ 11:4
ጥሩ የአትክልት ቦታ ለይስሙላ ብቻ በሚደረግ ቁፋሮና ዘር በዘፈቀደ በመበተን ሊገኝ አይችልም። በተመሳሳይም በክርስቲያን አገልግሎት ለታይታ ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከማሰራጨት የበለጠ ነገር ያስፈልጋል። የአምላክ የሥራ ባልደረቦች እንደመሆናችን መጠን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን መፈለግና የአምላክን መንግሥት ምሥራች በትጋት መስበክ ይኖርብናል። (ሥራ 13:48) ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 9:6 ላይ የሰጠውን መሠረታዊ ሥርዓት ልብ እንበል። “በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፣ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።”
ማንኛውም ጥሩ አትክልተኛ እንደሚያደርገው ሁሉ እኛም ዘራችንን ለመትከል የምንሞክረው በጥሩ አፈር ላይ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ዘር በጣም ጥሩ በሆነ አፈር ላይ ከተዘራ ከዚያ በኋላ ምንም ነገር አያስፈልግም ማለት አይደለም። ጂዮፍሪ ስሚዝ እንዲህ ብለዋል:- “ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል አንድ ሰው ተክሉን ከተከለ በኋላ ምንም ነገር ስለማያስፈልግ እጁን አጣጥፎ ሊቀመጥ ይችላል ማለት አይደለም።” ተክሉ እንዲያድግ ከተፈለገ ውኃ ማጠጣትና ተክሉን ከጥቃት መጠበቅ ያስፈልጋል። — ከምሳሌ 6:10, 11 ጋር አወዳድር።
በክርስቲያን አገልግሎትም በተለይ ምንም ውጤት የማይገኝ መስሎ በሚታይበት ጊዜ ረዘም ላለ ጊዜ በርትቶ መሥራትን ይጠይቃል። ሆኖም በድንገትና አንዳንድ ጊዜ ባልተጠበቀ ሁኔታ አስደናቂ ውጤት ሊገኝ ይችላል። ጂዮፍሪ ስሚዝ እንዲህ ብለዋል:- “በአትክልተኝነት ሥራ ረዘም ያለ የድካም ጊዜ ካለፈ በኋላ ያን ሁሉ ቁፋሮ፣ አረምና ጭንቀት የሚያስረሳ ውበት ይመጣል።” አንተም የመጀመሪያውን ቁፋሮ፣ ተከላ፣ የማረምና የማጠጣት ሥራ ለመስራት ፈቃደኛ ከሆንክ ጥሩ ልብ ያለው ሰው የእውነትን መልእክት ሲቀበል የሚገኘውን እርካታ ለማግኘት ትችላለህ። — ምሳሌ 20:4
ጳውሎስና አጵሎስ ያከናወኑት የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ በክርስቲያን ጉባዔ ውስጥ ልዩ የሆነ ከበሬታ እንደማያስገኝላቸው ያውቁ ነበር። የሚያሳድግ አምላክ እንደሆነ ተረድተው ነበር። ቢሆንም በትጋት ይተክሉና ያጠጡ ነበር። እኛም የእነርሱን አርዓያ ተከትለን ሰዎች እንዲያምኑ የምናደርግ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን ራሳችንን እናቅርብ። — 1 ቆሮንቶስ 3:5, 6
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁሉንም ነገሮች የሚያሳድግ አምላክ ነው። ቢሆንም አትክልተኛውም የሚያበረክተው ድርሻ አለው