ይሖዋን የሚያስደስቱ የምሥጋና መሥዋዕቶች
“ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።”—ሮሜ 12:1
1. መጽሐፍ ቅዱስ በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች ስለሚሰጡት አንጻራዊ ጥቅም ምን ይላል?
“ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፣ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።” (ዕብራውያን 10:1) ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ጥቅስ ላይ በሙሴ ሕግ ውስጥ ይቀርቡ የነበሩት ሁሉም መሥዋዕቶች ለሰው ልጅ መዳን የሚሰጡት ዘላቂ የሆነ ጥቅም እንደሌለ ግልጽ የሆነ ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ቆላስይስ 2:16, 17
2. በሕጉ ውስጥ የተካተቱትን መባዎችና መሥዋዕቶች በሚመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ዝርዝር ዘገባዎች ለመረዳት ጥረት ማድረጉ ከንቱ የማይሆነው ለምንድን ነው?
2 ታዲያ ይህ ማለት መባንና መሥዋዕትን በሚመለከት በመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩት መረጃዎች ዛሬ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚሰጡት ምንም ጥቅም የለም ማለት ነው? በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በሚካሄደው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተመዘገቡ ተማሪዎች በቅርቡ ከአንድ ዓመት ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንብበዋል። አንዳንዶች ሁሉንም ዝርዝር ጉዳዮች ለማንበብና ለመረዳት ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርገዋል። ያ ሁሉ ጥረት ምንም ዋጋ የለውም ማለት ነው? “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን” የተጻፈ በመሆኑ እንደዚያ ሊሆን እንደማይችል የተረጋገጠ ነው። (ሮሜ 15:4) ጥያቄው መባንና መሥዋዕቶችን በሚመለከት በሕጉ ውስጥ ተካትተው ከሚገኙት ዘገባዎች ምን ዓይነት ‘ትምህርት’ እና ‘መጽናኛ’ ልናገኝ እንችላለን የሚለው ነው።
ትምህርትና መጽናኛ እንድናገኝ
3. ምን መሠረታዊ ነገር ማግኘት ያስፈልገናል?
3 ሕጉ በሚያዘው መሠረት ቃል በቃል መሥዋዕቶችን እንድናቀርብ ባይጠበቅብንም እንኳ እስራኤላውያን በጊዜው ይቀርቡ ከነበሩት መሥዋዕቶች በተወሰነ ደረጃ ያገኙት የነበረው ዓይነት ጥቅም ማለትም የአምላክን ሞገስና የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገናል። በአሁኑ ጊዜ እኛ መሥዋዕቶችን ቃል በቃል የማናቀርብ በመሆኑ እነዚህን ጥቅሞች ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ የእንስሳት መሥዋዕቶች የሚያስገኙት ጥቅም ውስን መሆኑን ከገለጸ በኋላ እንዲህ በማለት ተናገረ:- “ስለዚህ [ኢየሱስ] ወደ ዓለም ሲገባ:- መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም። በዚያን ጊዜ:- እነሆ፣ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፣ አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ይላል።”—ዕብራውያን 10:5-7
4. ጳውሎስ መዝሙር 40:6-8ን በመጥቀስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሚሠራ የገለጸው እንዴት ነው?
4 ጳውሎስ መዝሙር 40:6-8ን በመጥቀስ ኢየሱስ “መሥዋዕትንና መባን፣” ‘በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ስለ ኃጢአት የሚሠዋ መሥዋዕትን’ ለዘለቄታው ጠብቆ ለማቆየት እንዳልመጣ አመልክቷል። ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት እነዚህ ሁሉ በአምላክ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት አጥተዋል። ከዚያ ይልቅ ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱ ያዘጋጀለትን ማለትም አምላክ አዳምን በፈጠረበት ጊዜ ካዘጋጀው ሥጋ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመሳሰል ሥጋ ይዞ ነው የመጣው። (ዘፍጥረት 2:7፤ ሉቃስ 1:35፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22, 45) ኢየሱስ የአምላክ ፍጹም ልጅ እንደመሆኑ መጠን በዘፍጥረት 3:15 ላይ እንደተተነበየው የሴቲቱን ‘ዘር’ ሚና ተጫውቷል። ኢየሱስ ራሱ ‘ሰኮናው የሚቀጠቀጥ’ ቢሆንም እንኳ ‘የሰይጣንን ጭንቅላት ለመቀጥቀጥ’ እርምጃ ይወስዳል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ከአቤል ጊዜ ጀምሮ የኖሩት የእምነት ሰዎች ሲጠባበቁት የነበረው ይሖዋ የሰው ዘሮችን ለማዳን የሚጠቀምበት መሣሪያ ሆነ።
5, 6. ክርስቲያኖች ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችላቸው ምን አቻ የማይገኝለት መንገድ ተዘጋጅቶላቸዋል?
5 ኢየሱስ የተጫወተውን ይህን ልዩ ሚና በማስመልከት ጳውሎስ “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን [አምላክ] ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 5:21) “ኃጢአት አደረገው” የሚለው መግለጫ ‘እንደ ኃጢአት መሥዋዕት አደረገው’ ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ” በማለት ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 2:2) በመሆኑም እስራኤላውያን በሚያቀርቧቸው መሥዋዕቶች አማካኝነት አምላክን ለመቅረብ የሚያስችል ጊዜያዊ መንገድ የነበራቸው ሲሆን ክርስቲያኖች ግን ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችል ከሁሉ የላቀ መሠረት ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት አላቸው። (ዮሐንስ 14:6፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) አምላክ ባቀረበው ቤዛዊ መሥዋዕት ካመንንና እርሱን ከታዘዝን የእኛም ኃጢአት ይቅር ይባልልናል እንዲሁም የአምላክን ሞገስና በረከት እናገኛለን። (ዮሐንስ 3:17, 18) ይህ የሚያጽናና አይደለም? ታዲያ በቤዛው መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳለን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
6 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች አምላክን ለመቅረብ የሚያስችል ከሁሉ የላቀ መሠረት እንዳላቸው ካብራራ በኋላ በዕብራውያን 10:22-25 ላይ እንደምናነበው አምላክ ባደረገልን ፍቅራዊ ዝግጅት እንደምናምንና ለዚህም አድናቆት እንዳለን ልናሳይ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች ዘረዘረ። ጳውሎስ ምክሩን በዋነኛነት የሰጠው ‘ወደ ቅድስት የሚገቡበት መንገድ’ ላላቸው ማለትም ሰማያዊ ጥሪ ላላቸው ለተቀቡ ክርስቲያኖች ቢሆንም እንኳ ኃጢአትን ከሚያስተሰርየው የኢየሱስ መሥዋዕት ጥቅም ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ጳውሎስ በመንፈስ ተገፋፍቶ ለጻፋቸው ቃላት ትኩረት መስጠት ይኖርበታል።—ዕብራውያን 10:19
ንጹሕና ያልረከሰ መሥዋዕት አቅርቡ
7. (ሀ) ዕብራውያን 10:22 መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ ስለሚከናወነው ነገር የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) አንድ መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ምን መደረግ ነበረበት?
7 በመጀመሪያ ጳውሎስ “ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ” በማለት ክርስቲያኖችን መከረ። (ዕብራውያን 10:22) እዚህ ላይ የሠፈሩት ቃላት ሕጉ በሚያዘው መሠረት መሥዋዕት ይቀርብ በነበረበት ጊዜ የሚከናወነውን ሁኔታ ቁልጭ አድርገው የሚገልጹ ናቸው። አንድ መሥዋዕት ተቀባይነት እንዲያገኝ ከተፈለገ ከጥሩ የልብ ግፊት መቅረብና ንጹሕና ያልረከሰ መሆን ስለነበረበት ይህ መግለጫ ተስማሚ ነው። ለመሥዋዕት የሚቀርበው እንስሳ ከመንጋ መካከል ማለትም ንጹሕ ከሆኑ እንስሳት መካከል የሚመረጥ “ነውር” እና እንከን የሌለበት መሆን ነበረበት። መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው ከአዕዋፍ ወገን ከሆነ ከዋኖስ ወይም ከርግብ መሆን ነበረበት። እነዚህ ሁኔታዎች ከተሟሉ “ያስተሰርይለትም ዘንድ የሠመረ ይሆንለታል።” (ዘሌዋውያን 1:2-4, 10, 14፤ 22:19-25) የእህል ቁርባኑ ብክለትን የሚያመለክተው እርሾም ሆነ እንዲቦካ ሊያደርገው የሚችለው ማር የተቀላቀለበት መሆን የለበትም። እዚህ ላይ የተጠቀሰው ማር የፍራፍሬ ሹሮፕ ሳይሆን አይቀርም። እንስሳም ሆነ እህል መሥዋዕት ሆኖ በመሠዊያ ላይ በሚቀርብበት ጊዜ ከብልሽት የሚጠብቀው ጨው ይጨመርበት ነበር።—ዘሌዋውያን 2:11-13
8. (ሀ) መሥዋዕት ከሚያቀርብ ሰው ምን ይጠበቅ ነበር? (ለ) አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
8 መሥዋዕት ከሚያቀርበው ሰውስ ምን ይጠበቅ ነበር? በይሖዋ ፊት ለመቆም የሚመጣ ማንኛውም ሰው ንጹሕና ያልረከሰ መሆን እንዳለበት ሕጉ ይናገራል። በሆነ ምክንያት የረከሰ ሰው የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የኅብረት መሥዋዕት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይችል ዘንድ አስቀድሞ የኃጢአት ወይም የበደል መሥዋዕት በማቅረብ በይሖዋ ፊት ያለውን ንጹሕ አቋም ማደስ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 5:1-6, 15, 17) ታዲያ እኛስ በይሖዋ ፊት ሁልጊዜ ንጹሕ አቋም የመያዝን አስፈላጊነት እንገነዘባለን? አምልኮታችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን የአምላክን ሕግ በመጣስ የፈጸምነውን ስህተት ፈጥነን ማስተካከል ይገባናል። አምላክ እርዳታ ለመስጠት በሚጠቀምባቸው ‘የጉባኤ ሽማግሌዎች’ እና ‘ለኃጢአታችን ማስተሰርያ’ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠቀም ፈጣኖች መሆን አለብን።—ያዕቆብ 5:14፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2
9. ለይሖዋ በሚቀርቡት መሥዋዕቶችና ለሐሰት አማልክት በሚቀርቡት መሥዋዕቶች መካከል ምን ቁልፍ የሆነ ልዩነት አለ?
9 እንዲያውም የሚቀርበው መሥዋዕት ከማንኛውም ርኩስ ነገር የጠራ መሆን እንዳለበት የተሰጠው ጥብቅ መመሪያ ለይሖዋ በሚቀርቡት መሥዋዕቶችና በእስራኤል አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ብሔራት ለሐሰት አማልክት በሚያቀርቡት መሥዋዕቶች መካከል የነበረ አንዱ ቁልፍ ልዩነት ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ በሙሴ ሕግ ውስጥ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶችን ልዩ ስለሚያደርጋቸው ስለዚህ ገጽታ ሐሳብ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “በሙሴ ሕግ ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት ከጥንቆላ ወይም ከምዋርት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አልነበረውም፤ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ስሜት የሚንጸባረቅበት ሃይማኖታዊ ሥርዓት አይካሄድም ነበር፤ ሰውነትን የመተልተል ልማድም ሆነ ቅዱስ ግልሙትና የሚባል ነገር አልነበረም፤ ከመዋለድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚፈጸም ልቅ የጾታ ግንኙነት ፈጽሞ የተከለከለ ነበር፤ ሰዎችን መሥዋዕት አድርጎ የማቅረብም ሆነ ለሙታን የመሠዋት ልማድ አልነበረም።” ይህ ሁሉ ወደ አንድ ሐቅ ይመራናል:- ይሖዋ ቅዱስ ነው፤ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት ኃጢአት ወይም ርኩሰት ችላ ብሎ አያልፍም እንዲሁም አይደግፍም። (ዕንባቆም 1:13) ለእርሱ የሚቀርበው አምልኮና መሥዋዕት በአካል፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕና ያልረከሰ መሆን አለበት።—ዘሌዋውያን 19:2፤ 1 ጴጥሮስ 1:14-16
10. ጳውሎስ በሮሜ 12:1, 2 ላይ ካሰፈረው ምክር ጋር በመስማማት በራሳችን ምን ዓይነት ምርመራ ማካሄድ አለብን?
10 ከዚህ አንጻር ስናየው ለይሖዋ የምናቀርበው አገልግሎት በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው እርግጠኞች መሆን እንችል ዘንድ በሁሉም የኑሮ ዘርፎች ራሳችንን መመርመር ይገባናል። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በአገልግሎት በተወሰነ ደረጃ እስከተካፈልን ድረስ በግል ሕይወታችን የፈለግነውን ብናደርግ ምንም ችግር እንደሌለው አድርገን ፈጽሞ ማሰብ አይኖርብንም። በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ እስካደረግን ድረስ በሌሎቹ የሕይወታችን መስኮች የግድ በአምላክ ሕግ መመራት እንደማያስፈልገን አድርገን ማሰብም አይኖርብንም። (ሮሜ 2:21, 22) በእርሱ ዓይን ቆሻሻ ወይም ርኩስ የሆኑ ነገሮች አስተሳሰባችንን ወይም ድርጊታችንን እንዲበክሉብን ከፈቀድን የአምላክን በረከትና ሞገስ እናገኛለን ብለን መጠበቅ አንችልም። የሚከተሉትን የጳውሎስ ቃላት ሁልጊዜ ማስታወስ አለብን:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።”—ሮሜ 12:1, 2
በሙሉ ልባችሁ የምስጋና መሥዋዕት አቅርቡ
11. በዕብራውያን 10:23 ላይ በተጠቀሰው “በሕዝብ ፊት የምንሰጠው ምሥክርነት” በሚለው መግለጫ ውስጥ ምን ነገር ተካትቷል?
11 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የእውነተኛ አምልኮ ወሳኝ ገጽታ በሆነ አንድ ጉዳይ ላይ እንድናተኩር ያደርገናል:- “የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት [“ስለ ተስፋችን በሕዝብ ፊት የምንሰጠውን ምሥክርነት፣” NW ] እንጠብቅ።” (ዕብራውያን 10:23) “በሕዝብ ፊት የምንሰጠው ምሥክርነት” የሚለው መግለጫ ቃል በቃል ሲተረጎም “መናዘዝ” ማለት ነው። በተጨማሪም ጳውሎስ ስለ ‘ምስጋና መሥዋዕት’ ተናግሯል። (ዕብራውያን 13:15) ይህ እንደ አቤል፣ ኖኅ እና አብርሃም ያሉ ሰዎች ያቀረቡትን መሥዋዕት ያስታውሰናል።
12, 13. አንድ እስራኤላዊ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ምን ነገር መቀበሉን ያሳያል? እኛም ተመሳሳይ መንፈስ ለማንጸባረቅ ምን ልናደርግ እንችላለን?
12 አንድ እስራኤላዊ “በይሖዋ ፊት” የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበው “በራሱ ነፃ ፈቃድ” ነበር። (ዘሌዋውያን 1:3 NW ) ይህን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን አትረፍርፎ እንደባረከና ለሕዝቡ ፍቅራዊ ደግነት እንዳሳየ አምኖ መቀበሉን በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ በሕዝብ ፊት ይመሰክራል ወይም ያረጋግጣል። የሚቃጠል መሥዋዕትን ከሌሎች መሥዋዕቶች ልዩ የሚያደርገው በመሠዊያ ላይ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መሆኑ እንደሆነ አስታውስ። ይህም ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ማደርንና ራስን ለአምላክ መወሰንን ለማመልከት የሚያገለግል ተስማሚ ተምሳሌት ነው። በተመሳሳይ እኛም በራሳችን ፈቃድና በሙሉ ልብ “የምሥጋና መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” ለይሖዋ ስናቀርብ በቤዛው መሥዋዕት ማመናችንንና ለዚህ ዝግጅት አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየታችን ነው።
13 ክርስቲያኖች የእንስሳም ሆነ የእህል መሥዋዕት ቃል በቃል የሚያቀርቡ ባይሆኑም የመንግሥቱን ምሥራች የመመሥከርና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የማፍራት ኃላፊነት አለባቸው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች ያዘጋጃቸውን አስደናቂ ነገሮች ብዙ ሰዎች ማወቅ ይችሉ ዘንድ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሕዝብ ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ትጠቀማለህ? ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለማስተማርና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ጊዜህንና ጉልበትህን ለማዋል ፈቃደኛ ነህ? በአገልግሎቱ በቅንዓት የምናደርገው ተሳትፎ ከሚቃጠል መሥዋዕት እንደሚወጣ ጣፋጭ ሽታ አምላክን ያስደስተዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:58
ከአምላክና ከሰዎች ጋር መደሰት
14. የኅብረት መሥዋዕትን የሚያስታውሱን በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ የሠፈሩት ትኞቹ የጳውሎስ ቃላት ናቸው?
14 በመጨረሻም ጳውሎስ አምላክን ስናመልክ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ስለሚኖረን ዝምድናም ጠቅሷል። “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:24, 25) “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ፣” “መሰብሰባችንን” እና “እርስ በርሳችን እንመካከር” የሚሉት መግለጫዎች በእስራኤል ይቀርብ የነበረው የኅብረት መሥዋዕት ለአምላክ ሕዝቦች ያስገኝላቸው የነበረውን ጥቅም ያስታውሰናል።
15. የኅብረት መሥዋዕትንና የክርስቲያን ስብሰባዎችን የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው?
15 “የኅብረት መሥዋዕት” የሚለው አባባል አንዳንድ ጊዜ “የሰላም መባ” ተብሎም ይተረጎማል። እዚህ ላይ “ሰላም” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል ብዙ ቁጥር ያለው ሲሆን እንዲህ ባለው መሥዋዕት መካፈል ከአምላክና ከአምልኮ ባልንጀራ ጋር ሰላም እንደሚያስገኝ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። የኅብረት መሥዋዕትን በተመለከተ አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “በእርግጥም ይህ ከቃል ኪዳኑ አምላክ ጋር አስደሳች የሆነ ግንኙነት የሚያደርጉበት ጊዜ ሲሆን ሁልጊዜ እነርሱን በእንግድነት የሚቀበለው እርሱ ቢሆንም ይህ መሥዋዕት ሲቀርብ ግን ራሱን ዝቅ በማድረግ የእስራኤላውያን እንግዳ ይሆናል።” ይህ ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ” በማለት የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 18:20) በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ በተገኘን ቁጥር ከሌሎች ጋር ገንቢ የሆነ ግንኙነት በማድረግ፣ አበረታች የሆነ ትምህርት በመቅሰም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን እንደሚገኝ በማሰብ ልንጠቀም እንችላለን። ይህም ክርስቲያናዊ ስብሰባ አስደሳችና እምነት የሚያጠነክር እንዲሆን ያደርገዋል።
16. ከኅብረት መሥዋዕት ጋር በተያያዘ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ይበልጥ አስደሳች የሚያደርጋቸው ምንድን ነው ማለት ይቻላል?
16 የኅብረት መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ በሆድ ዕቃውና በኩላሊቶቹ ዙሪያ ያለው ስብ፣ በጉበቱ ላይ ያለው መረብና በጎድኑ አጠገብ ያለው ስብ እንዲሁም የበጉ ላት በጠቅላላ በመሠዊያው ላይ ተቃጥሎ ለይሖዋ ይቀርባል። (ዘሌዋውያን 3:3-16) ስብ በንጥረ ነገሮች እጅግ የዳበረና ከሁሉ የበለጠ የእንስሳ ክፍል እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በመሠዊያው ላይ መቅረቡ ለይሖዋ ምርጥ የሆነውን መስጠትን ያመለክታል። ክርስቲያን ስብሰባዎችን ይበልጥ አስደሳች የሚያደርጋቸው ትምህርት የምናገኝባቸው ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ ምስጋና የምናቀርብባቸው መሆናቸውም ነው። ትህትና በተሞላበት ሁኔታ ከልብ ለመዘመር፣ በትኩረት ለማዳመጥና የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ሐሳብ ለመስጠት የተቻለንን ጥረት በማድረግ ይህን እንፈጽማለን። “ሃሌ ሉያ። ለእግዚአብሔር አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፤ ምስጋናው በቅዱሳኑ ጉባኤ ነው” በማለት መዝሙራዊው ዘምሯል።—መዝሙር 149:1
የይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት ይጠብቀናል
17, 18. (ሀ) ሰሎሞን በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ በተመረቀበት ጊዜ ምን ታላቅ መሥዋዕት አቀረበ? (ለ) ሕዝቡስ ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ጊዜ ከተከበረው በዓል ምን በረከት አግኝተዋል?
17 በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ በ1026 ከዘአበ በሰባተኛው ወር በተመረቀበት ጊዜ ንጉሥ ሰሎሞን “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቁርባን የደኅንነቱንም መሥዋዕት ስብ” ጨምሮ “በእግዚአብሔር ፊት [“ታላቅ፣” NW ] መሥዋዕት” አቅርቧል። ከእህል ቁርባኑ በተጨማሪም በበዓሉ ላይ በድምሩ 22, 000 ከብቶችና 120, 000 በጎች ተሠውተዋል።—1 ነገሥት 8:62-65
18 ለዚህ ከፍተኛ ክብረ በዓል ምን ያህል ወጪ እንደወጣና ምን ያህል የሰው ጉልበት እንደፈሰሰ ልትገምት ትችላለህ? ሆኖም ይህ ሁሉ እስራኤላውያን ካገኙት በረከት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዓሉ ሲደመደም ሰሎሞን “ሕዝቡን አሰናበተ፤ እነርሱም ንጉሡን መረቁ፣ እግዚአብሔርም ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ በልባቸው ተደስተው ሐሤትም አድርገው ወደ ስፍራቸው ሄዱ።” (1 ነገሥት 8:66) በእርግጥም ሰሎሞን እንዳስቀመጠው “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።”—ምሳሌ 10:22
19. አሁንም ሆነ ለዘላለም የይሖዋን ታላላቅ በረከቶች ለማግኘት ምን ልናደርግ እንችላለን?
19 እኛ የምንኖረው “ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር . . . ጥላ” አልፎ “እውነተኛ አምሳል” በተተካበት ዘመን ውስጥ ነው። (ዕብራውያን 10:1) ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ሊቀ ካህናት ሆኖ ወደ ሰማይ የገባ ሲሆን በእርሱ መሥዋዕት የሚያምኑት ሰዎች ሁሉ ስርየት ማግኘት ይችሉ ዘንድ የደሙን ዋጋ አቅርቧል። (ዕብራውያን 9:10, 11, 24-26) እኛም ይህን ታላቅ መሥዋዕት መሠረት በማድረግና በሙሉ ልባችን ለአምላክ ንጹሕና ያልረከሰ የምስጋና መሥዋዕት በማቅረብ ‘በልባችን እየተደሰትንና ሐሤትም እያደረግን’ ይሖዋ የሚሰጠንን የተትረፈረፉ በረከቶች አሻግረን በመመልከት ወደፊት መግፋት እንችላለን።—ሚልክያስ 3:10
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• መሥዋዕቶችንና መባዎችን በሚመለከት በሕጉ ውስጥ ከሰፈረው ዘገባ ምን ትምህርትና ማጽናኛ ልናገኝ እንችላለን?
• አንድ መሥዋዕት ተቀባይነት እንዲያገኝ በመጀመሪያ ምን ነገር መሟላት ይኖርበታል? ይህስ ለእኛ ምን ትርጉም አለው?
• በፈቃደኝነት ከሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር የሚነጻጸር ምን ነገር ልናቀርብ እንችላለን?
• ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችንና የኅብረት መሥዋዕትን የሚያመሳስላቸው ምን ነገር አለ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የሰው ዘሮችን ለማዳን ኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አገልግሎታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ራሳችንን መጠበቅ አለብን
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአገልግሎት በምንካፈልበት ጊዜ የይሖዋን ጥሩነት በሕዝብ ፊት እናሳውቃለን