ይሖዋ ለደከሙት ኃይል ይሰጣል
“እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ።”—ኢሳይያስ 40:31
1, 2. ይሖዋ በእርሱ ለሚተማመኑ ሰዎች ምን ይሰጣቸዋል? ከዚህ ቀጥሎስ የምንመለከተው ስለ ምን ነገር ነው?
ንስር በሰማይ ከሚበሩ በጣም ጠንካራ አእዋፍ መካከል አንዱ ነው። ንስሮች ክንፋቸውን ሳያርገበግቡ ረጅም ርቀት መንሳፈፍ ይችላሉ። “የአእዋፍ ንጉሥ” እየተባለ የሚጠራውና ከሁለት ሜትር በላይ ርዝማኔ ያላቸው ክንፎች ያሉት ወርቃማው ንስር “በጣም ማራኪ ከሆኑት ንስሮች መካከል የሚጠቀስ ነው፤ ከኮሮብቶችና ሜዳማ ከሆኑ ቦታዎች ላይ ከፍ ብሎ በመብረር በተራሮች ሰንሰለት ዙሪያ ለሰዓታት ሲያንዣብብ ይቆይና በሰማይ ላይ ያለች አንዲት ጥቁር ነጥብ መስሎ እስኪታይ ድረስ ወደላይ ይወነጨፋል።”—ዘ ኦውድበን ሶሳይቲ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ኖርዝ አሜሪካን በርድስ
2 ኢሳይያስ ንስር ያለውን ድንቅ የመብረር ችሎታ በአእምሮው በመያዝ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “[ይሖዋ] ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፣ ጎበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፣ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፣ አይደክሙም።” (ኢሳይያስ 40:29–31) አንድ ንስር በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሰማይ ከመጠቀ በኋላ ለረጅም ሰዓታት ሳይዝል መብረር የሚያስችሉትን ጠንካራ ክንፎች ያህል ወደፊት መግፋት የሚያስችል ኃይል በመስጠት ይሖዋ በእርሱ የሚተማመኑትን ሁሉ የሚያበረታቸው መሆኑን ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው! ለደከሙት ኃይልን ለመስጠት ያደረጋቸውን አንዳንድ ዝግጅቶች እስቲ እንመልከት።
ጸሎት ያለው ኃይል
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል? (ለ) ይሖዋ በጸሎት ለጠየቅነው ነገር ይሰጠናል ብለን የምንጠብቀው ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?
3 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ሳይታክቱ ዘወትር እንዲጸልዩ’ አሳስቧቸዋል። (ሉቃስ 18:1) የኑሮ ውጣ ውረዶች ከአቅማችን በላይ ሆነው ሲታዩን ልባችንን ለይሖዋ ማፍሰሳችን በእርግጥ ኃይላችን እንዲታደስና እንዳንታክት ሊረዳን ይችላልን? አዎን ይረዳናል፤ ይሁን እንጂ ልናስብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ።
4 ይሖዋን በጸሎት ለጠየቅነው ነገር የምንጠብቀው ምላሽ ምክንያታዊ መሆን አለበት። በአንድ ወቅት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት የነበረባት አንዲት ክርስቲያን እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “እንደ ሌሎቹ ሕመሞች ሁሉ በዚህም ጊዜ ቢሆን ይሖዋ ተዓምር አይሠራም። ይሁን እንጂ ይህ ያለንበት ሥርዓት እስከሚፈቅደው ደረጃ ድረስ እንድንቋቋመውና ብሎም እንድንድን ይረዳናል።” ጸሎቷ ለውጥ ሊያመጣ የቻለው ለምን እንደሆነ ስታስረዳም “ከይሖዋ መንፈስ ጋር በቀን የ24 ሰዓት ግንኙነት ነበረኝ” በማለት አክላ ተናግራለች። እንግዲያውስ ይሖዋ በሐዘን እንድንዋጥ ሊያደርጉን የሚችሉት የኑሮ ውጣ ውረዶች እንዳይደርሱብን ከለላ አይሆንልንም፤ ይሁን እንጂ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል!’ (ሉቃስ 11:13፤ መዝሙር 88:1–3) ይህም መንፈስ የሚገጥሙን ፈተናዎችና ተጽዕኖዎችን ሁሉ ለመቋቋም ያስችለናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ካስፈለገም በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ጭንቀት የሚያስከትሉት ችግሮች ሁሉ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ከምድረ ገጽ ተጠራርገው እስከሚጠፉበት ጊዜ ድረስ ጸንተን እንድንኖር “ከወትሮው የተለየ ኃይል” ሊሰጠን ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት
5. (ሀ) ጸሎታችን ውጤታማ እንዲሆን ምን ሁለት ነገሮች የግድ አስፈላጊ ናቸው? (ለ) ከሥጋ ድክመቶቻችን ጋር እየታገልን ከሆነ እንዴት ልንጸልይ እንችላለን? (ሐ) በጸሎት መጽናታችንና በቀጥታ ችግራችንን ጠቅሰን መናገራችን ይሖዋ ስለ እኛ ምን እንዲገነዘብ ይረዳዋል?
5 ይሁንና ጸሎታችን ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በጸሎት መጽናትና ችግሮቻችንንም ለይተን መጥቀስ ይኖርብናል። (ሮሜ 12:12) ለምሳሌ ያህል ከአንድ ዓይነት የሥጋ ድክመት ጋር በምታደርጉት ትግል የተነሳ አልፎ አልፎ የምትዝሉ ከሆነ በእያንዳንዱ ቀን መጀመሪያ ችግራችሁን ጠቅሳችሁ በዚያ ዕለት በተመሳሳይ ድክመት እንዳትሸነፉ ይረዳችሁ ዘንድ ይሖዋን ተማጸኑት። በቀኑ ክፍለ ጊዜና ማታ ከመተኛታችሁ በፊት በተመሳሳይ መንገድ ጸልዩ። በአንድ ዓይነት ድክመት ዳግም ከተሸነፋችሁ የይሖዋን ምሕረት ጠይቁ፤ ከዚህም በላይ ግን ስህተቱን በድጋሚ ለመፈጸም ያበቃችሁ ነገር ምን እንደሆነና ወደፊት እነዚህን ሁኔታዎች ለማስቀረት ምን ልታደርጉ እንደምትችሉም ንገሩት። በዚህ መንገድ በጸሎት መጽናታችሁና በጸሎታችሁ ውስጥም ችግራችሁን ለይታችሁ በመጥቀስ መናገራችሁ የምታደርጉትን ትግል በድል አድራጊነት ለመወጣት ያላችሁን ልባዊ ምኞት “ጸሎት ሰሚ” ለሆነው አምላክ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።—መዝሙር 65:2፤ ሉቃስ 11:5–13
6. ለመጸለይ እንደማንበቃ ሆኖ በሚሰማን ጊዜም እንኳ ቢሆን ይሖዋ ጸሎታችንን ይሰማናል ብለን በትክክል ልንጠብቅ የምንችለው ለምንድን ነው?
6 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የዛሉ አንዳንዶች ለመጸለይ እንኳን እንደማይበቁ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ስሜት አድሮባት የነበረች አንዲት ክርስቲያን ሴት ከጊዜ በኋላ እንደሚከተለው ስትል ተናግራለች፦ “ይህ በጣም አደገኛ የሆነ አስተሳሰብ ነው፤ ምክንያቱም ራሳችን ለራሳችን ፍርድ ሰጥተናል ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ የእኛ ሥራ አይደለም።” ‘ፈራጁ አምላክ ራሱ ነው።’ (መዝሙር 50:6) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ልባችን ሊነቅፈን ቢችልም አምላክ ከልባችን ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል’ በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 3:20) ለመጸለይ እንኳ የማንበቃ እንደሆንን አድርገን በራሳችን ላይ ልንፈርድ ብንችልም እንኳ ይሖዋ ግን ስለ እኛ እንደዛ ላይሰማው እንደሚችል ማወቁ እንዴት የሚያጽናና ነው! ይህን ያህል ዋጋ እንደሌለን እንዲሰማን ምክንያት የሆኑትን በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙንን ነገሮች ጨምሮ ስለ እኛ “ሁሉን” ያውቃል። (መዝሙር 103:10–14) ምሕረቱ እንዲሁም ነገሮችን ጥልቀት ባለው መንገድ መረዳት መቻሉ ‘ከተሰበረና ከተዋረደ’ ልብ የሚቀርብን ጸሎት እንዲሰማ ይገፋፋዋል። (መዝሙር 51:17) ይሖዋ “የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም” በማለት እያወገዘ ለእርዳታ የምናሰማውን ጩኸት እንዴት አልሰማም ሊል ይችላል?—ምሳሌ 21:13
በወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያለው ሞቅ ያለ ፍቅር
7. (ሀ) ይሖዋ ኃይላችንን እንድናድስ ለመርዳት ሲል ያደረገልን ሌላው ዝግጅት ምንድን ነው? (ለ) ስለ ወንድማማች ማኅበራችን ምን ነገር ማወቃችን ሊያበረታን ይችላል?
7 ኃይላችንን ለማደስ እንድንችል ይሖዋ ያደረገልን ሌላው ዝግጅት ደግሞ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችን ነው። የዓለም አቀፍ ወንድማማችና እህትማማች ቤተሰብ አባል መሆን እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! (1 ጴጥሮስ 2:17 አዓት) የኑሮ ተጽዕኖዎች ሲደርሱብን በወንድማማች ማኅበራችን ውስጥ የሚንጸባረቀው ሞቅ ያለ ፍቅር ኃይላችንን ለማደስ ሊረዳን ይችላል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ጭንቀት የሚፈጥሩ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን የምንጋፈጠው እኛ ብቻ እንዳልሆንን ማወቁ ብቻ ሊያበረታን ይችላል። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን መካከል ተመሳሳይ ተጽዕኖ ወይም ፈተና የደረሰባቸውና እኛ የተሰማንን ዓይነት ስሜት የተሰማቸው መኖራቸው ጥርጥር የለውም። (1 ጴጥሮስ 5:9) እየደረሰብን ያለው ነገር በእኛ እንዳልተጀመረና የሚሰማን ስሜት እንግዳ እንዳልሆነ ማወቃችን የሚያጽናና ነው።
8. (ሀ) ከወንድማማች ማኅበራችን ይህ ነው የማይባል ማበረታቻ ልናገኝ እንደምንችል የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው? (ለ) አንተ በግልህ ‘ከእውነተኛ ወዳጅ’ ድጋፍ ወይም ማጽናኛ ያገኘኸው በምን መንገድ ነው?
8 የሞቀ ፍቅር በሚንጸባረቅበት በዚህ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ በጭንቀታችን ጊዜ ይህ ነው የማይባል ድጋፍና ማጽናኛ ሊሰጡን የሚችሉ ‘እውነተኛ ወዳጆች’ ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 17:17 አዓት) ብዙውን ጊዜ ጥቂት የደግነት ቃሎችን መናገር ወይም አሳቢነታችንን የሚያሳዩ ድርጊቶችን ማድረግ ብቻ በቂ ሆኖ ይገኛል። ካደረባት የከንቱነት ስሜት ጋር ትታገል የነበረች አንዲት ክርስቲያን ወደኋላ መለስ ብላ ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “ስለራሴ የነበረኝን አፍራሽ አስተሳሰብ እንዳሸንፍ ለመርዳት ሲሉ መልካም ጎኖቼን የሚነግሩኝ ወዳጆች ነበሩኝ።” (ምሳሌ 15:23) አንዲት እህት ወጣት ሴት ልጅዋ በሞት ከተለየቻት በኋላ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚዘመሩትን የመንግሥቱን መዝሙሮች በተለይ ደግሞ ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚጠቅሱትን መዝሙሮች መዘመር አስቸጋሪ ሆኖባት ነበር። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “አንድ ቀን ከመተላለፊያው ባሻገር በነበረው መደዳ በእኔ አቅጣጫ ተቀምጣ የነበረች እህት ሳለቅስ አየችኝ። አጠገቤ መጥታ እቅፍ አድርጋኝ የቀሩትን የመዝሙሩን ስንኞች አብራኝ ዘመረች። ልቤ ለወንድሞችና ለእህቶች ባለኝ ፍቅር ተሞላ፤ እርዳታ የምናገኘው ሌላ የትም ሳይሆን በመንግሥት አዳራሽ በመገኘት መሆኑን ስለተገነዘብኩ ወደ ስብሰባዎቹ በመምጣታችን የደስታ ስሜት ተሰማኝ።”
9, 10. (ሀ) የወንድማማች መዋደዳችን ይበልጥ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በተለይ መልካም ጓደኝነት የሚያሻቸው እነማን ናቸው? (ሐ) ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት ምን ልናደርግ እንችላለን?
9 እርግጥ ነው እያንዳንዳችን የክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችን የሞቀ ፍቅር ይበልጥ እንዲጎለብት የማድረግ ኃላፊነት አለብን። በመሆኑም ልባችን ሁሉንም ወንድሞችና እህቶች የሚያቅፍ ይሆን ዘንድ ‘ሊሰፋ’ ይገባል። (2 ቆሮንቶስ 6:13) የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረባቸው ክርስቲያኖች ወንድሞችና እህቶች ለእነርሱ ያላቸው ፍቅር እንደቀዘቀዘ ቢሰማቸው እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል! ሆኖም አንዳንድ ክርስቲያኖች ብቸኛ እንደሆኑና ችላ እንደተባሉ ሆኖ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ። እውነትን የሚቃወም ባል ያላት አንዲት እህት “ገንቢ ወዳጅነትና ማበረታቻ ማግኘት እንዲሁም አፍቃሪ ከሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረብ የማይፈልግ ማን ነው? እባካችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለእኛ በጣም እንደሚያስፈልጉን አስታውሷቸው!” ስትል ተማጽናለች። አዎን በተለይ ያሉበት የኑሮ ሁኔታ ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸው ማለትም የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው፣ ነጠላ የሆኑ ወላጆች፣ ከባድ የጤና ችግሮች ያሉባቸው፣ አረጋውያንና ሌሎችም መልካም ጓደኞች ያስፈልጓቸዋል። አንዳንዶቻችን ስለዚህ ነገር ማሳሰቢያ ያስፈልገን ይሆን?
10 እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? ለሌሎች የምናሳየውን ፍቅር እናስፋው። ሰዎችን በምንጋብዝበት ጊዜ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን አንዘንጋ። (ሉቃስ 14:12–14፤ ዕብራውያን 13:2) ግብዣውን ለመቀበል ሁኔታቸው አይፈቅድላቸውም ብላችሁ ከማሰብ ይልቅ ቢቀበሉም ባይቀበሉም ለምን አትጋብዟቸውም? ከዚያ በኋላ ራሳቸው ይወስኑ። ግብዣውን መቀበል ባይችሉ እንኳ ሌሎች ስለ እነርሱ እንደሚያስቡላቸው በማወቃቸው ብቻ እንደሚበረታቱ አያጠራጥርም። ኃይላቸውን ለማደስ የሚያስፈልጋቸው ይህ ብቻ ሊሆን ይችላል።
11. የተለያዩ ችግሮች የተጫኗቸው ሰዎች በምን በምን መንገዶች ድጋፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል?
11 የተለያዩ ችግሮች የተጫኗቸው ሰዎች በሌላ መንገድም እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዲት ብቻዋን ልጅ የምታሳድግ እናት ያለ አባት የቀረውን ልጅዋን አንድ የጎለመሰ ወንድም እንዲረዳላት ያስፈልጋት ይሆናል። (ያዕቆብ 1:27) ከባድ የጤና ችግር ያለበት አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ከገበያ ዕቃዎችን በመገዛዛት ወይም የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት በኩል ጥቂት እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆናል። አንድ አረጋዊ ወንድም (እህት) ጓደኛ የሚሆናቸው ሰው ወይም ደግሞ ወደ መስክ አገልግሎት ለመሄድ አንዳንድ እርዳታዎችን ይፈልጉ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን ‘የፍቅራችን እውነተኛነት’ ይፈተናል። (2 ቆሮንቶስ 8:8) ገና ለገና የተቸገሩትን መርዳት ጊዜና ጥረት ይጠይቅብናል ብለን ከሩቁ ከመሸሽ ይልቅ የሌሎች ችግር በቀላሉ የሚገባንና አፋጣኝ ምላሽ የምንሰጥ በመሆን የክርስቲያናዊ ፍቅርን ጣዕም እንዲቀምሱ እናድርግ።
የአምላክ ቃል ያለው ኃይል
12. የአምላክ ቃል ኃይላችንን ለማደስ የሚረዳን እንዴት ነው?
12 አንድ ሰው ምግብ መመገብ ካቆመ ብዙም ሳይቆይ የነበረውን ብርታትና ኃይል እያጣ ይሄዳል። በተመሳሳይም ይሖዋ ወደፊት ለመግፋት የሚስችለንን ኃይል ለእኛ የሚሰጥበት ሌላው መንገድ በመንፈሳዊ በሚገባ መመገባችንን በመከታተል ነው። (ኢሳይያስ 65:13, 14) ምን ዓይነት መንፈሳዊ ምግብ አዘጋጅቶልናል? ከሁሉ በላይ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ነው። (ማቴዎስ 4:4፤ ከዕብራውያን 4:12 ጋር አወዳድር።) ይህ መጽሐፍ ኃይላችንን ለማደስ የሚረዳን እንዴት ነው? የሚያጋጥሙን ተጽዕኖዎችና ችግሮች የነበረንን ጥንካሬ ማሟጠጥ ሲጀምሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ስለነበሯቸው ስሜቶችና በሕይወታቸው ውስጥ ስለገጠሟቸው ትግልን የሚጠይቁ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በማንበብ ብርታት ልናገኝ እንችላለን። ግሩም የንጹሕ አቋም ጠባቂነት ምሳሌ ሆነው ቢጠቀሱም እንኳ ‘እንደኛው ዓይነት ስሜት የነበራቸው ሰዎች’ ነበሩ። (ያዕቆብ 5:17፤ ሥራ 14:15) እንደኛው ዓይነት ፈተናዎችና የኑሮ ተጽዕኖዎች ደርሰውባቸዋል። እስቲ አንዳንዶቹን ምሳሌዎች ተመልከቱ።
13. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች እንደኛው ዓይነት ስሜት እንደነበራቸውና ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዳሳለፉ የሚያሳዩት የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ናቸው?
13 የዕብራውያን አባት የነበረው አብርሃም በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት የነበረው ቢሆንም እንኳ በሚስቱ መሞት መሪር ሐዘን ተሰምቶት ነበር። (ዘፍጥረት 23:2፤ ከዕብራውያን 11:8–10, 17–19 ጋር አወዳድር።) ንስሐ የገባው ዳዊት የፈጸማቸው ኃጢአቶች ከዚህ በኋላ ይሖዋን ለማገልገል አልበቃም የሚል ስሜት እንዲያድርበት አድርገውታል። (መዝሙር 51:11) ሙሴ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት አድሮበት ነበር። (ዘጸአት 4:10) አፍሮዲጡ የገጠመው ከባድ ሕመም ‘በጌታ ሥራ’ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደገታበት ሌሎች በማወቃቸው ተጨንቆ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:25–30) ጳውሎስ ከውዳቂ ሥጋው ጋር መታገል ግድ ሆኖበት ነበር። (ሮሜ 7:21–25) ኤዎድያንና ሲንጤኪ በሚባሉ በፊልጵስዩስ ጉባኤ ይገኙ በነበሩ ሁለት ቅቡዓን እህቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ይመስላል። (ፊልጵስዩስ 1:1፤ 4:2, 3) እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እንደኛው ዓይነት ስሜቶች የነበራቸውና ተመሳሳይ ተሞክሮ ያሳለፉ ቢሆኑም እንኳ እንዳልታከቱ ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሖዋም ቢሆን ከእንግዲህ ወዲህ የእነርሱ ነገር በቃኝ አላለም።
14. (ሀ) ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ብርታት እንድናገኝ እኛን ለመርዳት የሚጠቀመው በማን ነው? (ለ) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ ቤተሰብንና ውስጣዊ ስሜትን የሚመለከቱ ርዕሶችን ይዘው የሚወጡት ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ ከቃሉ ብርታት እንድናገኝ ለመርዳት በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የማያቋርጥ መንፈሳዊ ምግብ “በጊዜው” ያቀርብልናል። (ማቴ 24:45) ታማኙ ባሪያ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለማስረዳትና የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኗን ለማወጅ ለረጅም ጊዜ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በመሣሪያነት ሲጠቀም ቆይቷል። በተለይ ደግሞ ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ እነዚህ መጽሔቶች ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ ቤተሰብን እንዲሁም አንዳዶቹን የአምላክ ሕዝቦች ሳይቀር የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ የሆኑ የስሜት ችግሮች የሚዳስሱ ወቅታዊ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሶችን ይዘው ወጥተዋል። ይህ ዓይነቱ ትምህርት የወጣበት ዓላማ ምንድን ነው? እነዚህ ተፈታታኝ ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች ከአምላክ ቃል ጥንካሬና ማበረታቻ እንዲያገኙ ለመርዳት ሲባል መሆኑ እሙን ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ርዕሶች ሁላችንም አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያሉበትን ሁኔታ እንድንገነዘብም ይረዱናል። በዚህ መንገድ የሚከተሉትን የጳውሎስ ቃላት ለመጠበቅ ይበልጥ የታጠቅን እንሆናለን፦ “የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ተናገሯቸው፣ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ”—1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት
“ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ” የሆኑት ሽማግሌዎች
15. ሽማግሌ ሆነው ስለሚያገለግሉት ኢሳይያስ ምን ትንቢት ተናግሯል? ይህስ ምን ኃላፊነት ያስከትልባቸዋል?
15 ይሖዋ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ስንዝል እኛን ለመርዳት ያደረገው ሌላም ዝግጅት አለ፣ ይኸውም የጉባኤ ሽማግሌዎችን ነው። እነርሱን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ከእነዚህም እያንዳንዱ ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከአውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል።” (ኢሳይያስ 32:1, 2 አዓት) በመሆኑም ሽማግሌዎች ይሖዋ አስቀድሞ ስለ እነሱ ከተናገረው ብቃት ጋር ተስማምተው የመገኘት ኃላፊነት አለባቸው። የመጽናኛና የብርታት ምንጭ “ሆነው መገኘትና” የሌላውን “ሸክም [ወይም “አስቸጋሪ ነገሮች” ቃል በቃል “የከበዷቸውን ነገሮች”] ለመሸከም” ፈቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል። (ገላትያ 6:2 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
16. ሽማግሌዎች ለመጸለይ እንደማይበቃ ሆኖ የሚሰማውን ሰው ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
16 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አንድ በችግሮች የዛለ ሰው ለመጸለይ እንደማይበቃ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። ሽማግሌዎች ምን ሊያደርጉለት ይችላሉ? ከዚያ ሰው ጋር ሆነውም ሆነ በሌላ ጊዜ ስለ እርሱ ሊጸልዩ ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:14) ግለሰቡ እየሰማ ወደ ይሖዋ ስለ እርሱ መጸለይ ብቻውን በይሖዋና በሌሎች ዘንድ ምን ያህል እንደሚወደድ እንዲገነዘብ ስለሚረዳው እንደሚያጽናናው የተረጋገጠ ነው። አንድ ሽማግሌ የሚያቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት መስማት የተጨነቀውን ሰው እምነት ለማጠናከር ሊረዳ ይችላል። ሽማግሌዎቹ ስለ እነርሱ ለሚያቀርቡት ጸሎት ይሖዋ መልስ እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ሆነው ሲጸልዩ መስማታቸው እርሱ ወይም እርሷም ተመሳሳይ ትምክህት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል።
17. ሽማግሌዎች ጥሩ አዳማጮች መሆን የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
17 ያዕቆብ 1:19 “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ . . . ይሁን” ይላል። የተለያዩ ችግሮች ያዛሏቸው ሰዎች ኃይላቸውን እንዲያድሱ ለመርዳት ሽማግሌዎችም ጥሩ አዳማጮች መሆን ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ምናልባት የጉባኤው አባላት በዚህ ሥርዓት ውስጥ መፍትሔ ከማይገኝላቸው ችግሮች ወይም የኑሮ ተጽዕኖዎች ጋር ይታገሉ ይሆናል። በዚህ ወቅት የሚያስፈልጋቸው ለችግራቸው መፍትሔ ይሆናል ብሎ ያሰበውን ነገር የሚነግራቸው ሳይሆን ሲናገሩ በጥሞና የሚሰማቸው ጥሩ አድማጭ ብቻ ሊሆን ይችላል። ጥሩ አድማጭ የሚባለው ምን ዓይነት ስሜት ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚነግራቸው ሳይሆን ስለ ሁኔታው ፍርድ ሳይሰጥ በጥሞና የሚያዳምጣቸው ሰው ነው።—ሉቃስ 6:37፤ ሮሜ 14:13
18, 19. (ሀ) አንድ ሽማግሌ ለማዳመጥ የፈጠነ መሆኑ በተለያዩ ችግሮች የዛለውን ሰው ሸክም ይበልጥ እንዳያከብድበት ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ‘ወንድማዊ የመውደድ ስሜት’ ሲያሳዩ ምን ውጤት ይገኛል?
18 ሽማግሌዎች፣ ለማዳመጥ የፈጠናችሁ መሆናችሁ በተለያዩ ችግሮች የዛሉትን ሰዎች ሸክም ጥበብ በጎደለው መንገድ ይበልጥ እንዳታከብዱባቸው ሊረዳችሁ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ከአንዳንድ የጉባኤ ስብሰባዎች ቀርተው ቢሆን ወይም ደግሞ የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያቸው ትንሽ ቀንሶ ከሆነ እርሱ ወይም እርሷ በአገልግሎት ይበልጥ እንዲሠሩ ወይም በስብሰባዎች ይበልጥ አዘውታሪዎች እንዲሆኑ ምክር ያስፈልጋቸዋልን? ምናልባት ያስፈልግ ይሆናል። ነገር ግን ከጉዳዩ በስተጀርባ ያለውን ነገር ሁሉ ጠንቅቀህ ታውቃለህን? ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የሚሄድ የጤንነት ችግር አለባቸውን? በቅርቡ የቤተሰብ ኃላፊነታቸው ሌላ መልክ ይዟልን? እርሱን ወይም እርሷን የተጫኗቸው ሌሎች ሁኔታዎች ወይም የኑሮ ተጽዕኖዎች ይኖሩ ይሆንን? ምናልባትም ግለሰቡ የበለጠ መሥራት ባለመቻሉ ምክንያት ቀድሞውኑ የጥፋተኛነት ስሜት አድሮበት ሊሆን እንደሚችል አትዘንጋ።
19 እንግዲያውስ ይህን ወንድም ወይም ይህችን እህት ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው? እንዲህ ነው ብለህ ከመደምደምህና ምክር ከመስጠትህ በፊት አዳምጥ! (ምሳሌ 18:13) ማስተዋል የተሞላባቸው ጥያቄዎች በማንሣት በግለሰቡ ልብ ውስጥ ያለውን ስሜት ለማግኘት ሞክር። (ምሳሌ 20:5) እነዚህን ስሜቶች ችላ ብለህ ከማለፍ ይልቅ ምን እንደሆኑ ለመረዳት ሞክር። ይሖዋ እንደሚያስብልንና አንዳንድ ጊዜ ያለንበት ሁኔታ አቅማችንን ውስን ሊያደርገው የሚችል መሆኑን እንደሚረዳልን በመግለጽ ማጽናናት ሊያስፈልግ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 5:7) ሽማግሌዎች ይህን የመሰለውን ‘ወንድማዊ የመውደድ ስሜት’ ሲያሳዩ የዛሉት ሰዎች ‘ለነፍሳቸው ዕረፍትን’ ያገኛሉ። (1 ጴጥሮስ 3:8፤ ማቴዎስ 11:28–30) እንዲህ ያለውን ማጽናኛ ካገኙ በኋላ የበለጠ እንዲሠሩ መነገር አያስፈልጋቸውም፤ ይሖዋን ለማገልገል አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ልባቸው ግድ ይላቸዋል።—ከ2 ቆሮንቶስ 8:12፤ 9:7 ጋር አወዳድር።
20. የዚህ ክፉ ትውልድ ፍጻሜ በጣም በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ለማድረግ መሆን ይኖርበታል?
20 የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከታዩት ጊዜያት ሁሉ ይበልጥ አስቸጋሪ በሆነው ጊዜ ላይ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ወደ ፍጻሜው ዘመን ይበልጥ እየገባን በሄድን መጠን በሰይጣን ዓለም ውስጥ መኖር የሚያስከትላቸው ጫናዎች እየጨመሩ ይሄዳሉ። ዲያብሎስ የሚበላውን እንደሚያድን አንበሳ ያለንበትን ሁኔታ ተጠቅሞ በቀላሉ ሊያጠምደን ስለሚፈልግ እስክንዝልና እስክንታክት ድረስ እንደሚጠብቀን ፈጽሞ አትዘንጉ። ይሖዋ ለደከሙት ኃይልን የሚሰጥ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን! አንድ ንስር በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሰማይ እንዲመጥቅ የሚያደርጉትን ጠንካራ ክንፎች ያህል ከፍተኛ ብርታት የሚያስገኝ ኃይል ለእኛ ለመስጠት ሲል ይሖዋ ባደረጋቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ እንጠቀም። የዚህ ክፉ ትውልድ ፍጻሜ በጣም የተቃረበበት ይህ ጊዜ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት የምናደርገውን ሩጫ የምናቋርጥበት ጊዜ አይደለም።—ዕብራውያን 12:1
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ ለጸሎታችን ምን ዓይነት መልስ እንዲሰጠን ልንጠብቅ እንችላለን?
◻ ከክርስቲያን የወንድማማች ማኅበራችን ብርታት ልናገኝ የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
◻ የአምላክ ቃል ኃይላችንን እንድናድስ የሚረዳን እንዴት ነው?
◻ ችግሮች ያዛሏቸው ሰዎች ኃይላቸውን እንዲያድሱ ለመርዳት ሽማግሌዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎችን ስንጋብዝ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን አንዘንጋ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች የተለያዩ ችግሮች ያዛሏቸው ሰዎች ምን ያህል እንደሚፈቀሩ ያስተውሉ ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳቸው በጸሎት ሊጠይቁ ይችላሉ