ፍቅራችሁን አስፉ
1. እያንዳንዳችን ምን ኃላፊነት አለብን?
1 በክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የታቀፍነው ሁላችንም በጉባኤው ውስጥ ሞቅ ያለ ስሜት እንዲኖር የበኩላችንን አስተዋጽኦ የማበርከት ኃላፊነት አለብን። (1 ጴጥ. 1:22፤ 2:17) እንዲህ ዓይነቱ ሞቅ ያለ ስሜት የሚፈጠረው አንዳችን ለሌላው ያለንን ፍቅር ‘ስናሰፋ’ ነው። (2 ቆሮ. 6:12, 13 የ1954 ትርጉም ) ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 በመካከላችን ያለው ቅርርብ ይበልጥ ይጠናከራል:- ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ይበልጥ በተዋወቅን መጠን እምነታቸውን፣ ጽናታቸውንና ሌሎች መልካም ባሕሪዎቻቸውን ይበልጥ እያደነቅን እንሄዳለን። ላሉባቸው አንዳንድ ጉድለቶች እምብዛም ቦታ የማንሰጣቸው ሲሆን በመካከላችን ያለው ትስስርም ይጠናከራል። በሚገባ የምንተዋወቅ ከሆነ አንዳችን ሌላውን ለማነጽና ለማበረታታት ይቀለናል። (1 ተሰ. 5:11) ከሰይጣን ዓለም የሚሰነዘርብንን ጎጂ ተጽዕኖ ለማሸነፍ እንድንችል አንዳችን ሌላውን ማበረታታት ወይም ‘ማጽናናት’ እንችላለን። (ቆላ. 4:11) በተለያዩ ተጽዕኖዎች በተሞላው በዚህ የመጨረሻ ዘመን በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ጥሩ ወዳጆች ለማግኘት በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ምሳሌ 18:24
3. ለሌሎች የብርታት ምንጭ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
3 ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የቅርብ ጓደኞቻችን የመጽናናትና የብርታት ምንጭ ሊሆኑልን ይችላሉ። (ምሳሌ 17:17) የከንቱነት ስሜት ይሰማት የነበረች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “ስለራሴ የነበረኝን አፍራሽ አስተሳሰብ እንዳሸንፍ ለመርዳት ሲሉ መልካም ጎኖቼን የሚነግሩኝ ወዳጆች ነበሩኝ።” እንዲህ ያሉ ወዳጆች ከይሖዋ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው።—ምሳሌ 27:9
4. በጉባኤ ውስጥ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር ይበልጥ መተዋወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ:- ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለንን ፍቅር ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለሌሎች ሰላምታ ከመስጠትህ በተጨማሪ ከእነርሱ ጋር ጥሩ ጭውውት ለማድረግ ጥረት አድርግ። በግል ጉዳዮቻቸው ጣልቃ ሳትገባ እንደምታስብላቸው ማሳየት ትችላለህ። (ፊልጵ. 2:4፤ 1 ጴጥ. 4:15) ለሌሎች እንደምታስብ ማሳየት የምትችልበት ሌላው መንገድ እቤትህ በመጋበዝ ነው። (ሉቃስ 14:12-14) ወይም አብረሃቸው በመስክ አገልግሎት ለመሥራት ዝግጅት ልታደርግ ትችላለህ። (ሉቃስ 10:1) ከወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ቀዳሚ ሆነን ጥረት የምናደርግ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን እናደርጋለን።—ቆላ. 3:14
5. ወዳጅነታችንን ማስፋት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
5 የቅርብ ጓደኞቻችን እንዲሆኑ የምንመርጠው የእድሜ እኩዮቻችንን ወይም ከእኛ ጋር የሚመሳሰል ዝንባሌ ያላቸውን ብቻ ነው? እነዚህ ነገሮች በጉባኤው ውስጥ ሊኖረን የሚችለውን ወዳጅነት እንዲገድቡብን መፍቀድ አይኖርብንም። ዳዊትና ዮናታን እንዲሁም ሩትና ኑኃሚን በመካከላቸው በዕድሜም ሆነ በአስተዳደግ የጎላ ልዩነት እያለም ጠንካራ ወዳጅነት ለመመሥረት ችለዋል። (ሩት 4:15፤ 1 ሳሙ. 18:1) አንተስ ወዳጅነትህን ማስፋት ትችላለህ? እንዲህ ማድረግህ ያልተጠበቁ በረከቶች ሊያስገኝልህ ይችላል።
6. ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ማስፋት ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?
6 ለሌሎች ያለንን ፍቅር የምናሰፋ ከሆነ እርስ በርስ የምንበረታታ ከመሆኑም በላይ በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን እናደርጋለን። በተጨማሪም ለወንድሞቻችን ፍቅር ስናሳይ ይሖዋ ራሱ ይባርከናል። (መዝ. 41:1, 2፤ ዕብ. 6:10) በተቻለህ መጠን ከብዙ ወንድሞች ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ለምን ግብ አታወጣም?