አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .
የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖትን መቀላቀልን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው?
▪ ወርልድ ክሪስቺያን ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚናገረው “በዓለም ዙሪያ 10,000 የሚያህሉ ሃይማኖቶች” አሉ። በእነዚህ ሃይማኖቶች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት ስላስከተለ ሃይማኖትን መቀላቀል የሚለው ሐሳብ ለብዙ ሰዎች ተስፋ ይፈነጥቅላቸዋል። በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ሰላምና አንድነት ሊያስገኝ እንደሚችል ያምናሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ አንድነትን ያበረታታል። ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን ‘እርስ በርሱ ተስማምቶና ተደጋግፎ’ ከሚሠራው የሰው አካል ጋር አመሳስሎታል። (ኤፌሶን 4:16) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ ለእምነት ባልንጀሮቹ “ሁላችሁም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑራችሁ” በማለት መክሯቸዋል።—1 ጴጥሮስ 3:8
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የኖሩት ብዙ ባሕሎችና በርካታ ሃይማኖቶች በነበሩበት ጊዜ ነው። ይሁንና ጳውሎስ የተለያዩ ሃይማኖቶችን ስለመቀላቀል ሲጽፍ “የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ ክርስቲያኖችን “ከመካከላቸው ውጡ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:15, 17) ጳውሎስ እዚህ ላይ ሃይማኖትን መቀላቀልን እያወገዘ እንደነበር ግልጽ ነው። ይሁንና ይህን ድርጊት ያወገዘው ለምንድን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እውነተኛ ክርስቲያን በሆነና ባልሆነ ሰው መካከል የሚደረገውን መንፈሳዊ ጥምረት አስመልክቶ ሲናገር ክርስቲያኖች አቻ ባልሆነ መንገድ እንዳይጠመዱ አስጠንቅቋል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) እንዲህ ማድረግ የአንድን ክርስቲያን እምነት ከመጉዳት ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም። የጳውሎስ ሁኔታ ከአንድ አባት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ይህ አባት በሰፈራቸው ውስጥ መጥፎ ባሕርይ ያላቸው ልጆች እንዳሉ ያውቃል። ይህ ሁኔታ ስለሚያሳስበው ልጁ ከማን ጋር መጫወት እንዳለበት ጥበብ የተሞላበት ገደብ ያወጣል። ይህ ገደብ ሌሎችን ላያስደስት ይችላል። አባትየው በዚህ መንገድ ልጁ ከሌሎች ልጆች ጋር እንዳይገጥም ማድረጉ ልጁን ከመጥፎ ተጽዕኖ ይጠብቀዋል። በተመሳሳይም ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ጥምረት አለመፍጠራቸው የሌሎች ሃይማኖቶችን መጥፎ ልማድ እንዳይከተሉ እንደሚረዳቸው ያውቅ ነበር።
ይህ የጳውሎስ አቋም ከኢየሱስ ጋር ይመሳሰላል። ኢየሱስ፣ ሰዎች እርስ በርሳቸው በሰላም እንዲኖሩ በማበረታታት ረገድ ግሩም ምሳሌ የተወ ቢሆንም ሃይማኖትን ከመቀላቀል ተቆጥቧል። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ዓመታት እንደ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ያሉ በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ነበሩ። እንዲያውም እነዚህ የሃይማኖት ቡድኖች ኢየሱስን ለማጥመድ አልፎ ተርፎም ለመግደል በአንድነት ተባብረው ነበር። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንዲጠነቀቁ’ ነግሯቸዋል።—ማቴዎስ 16:12
በዛሬው ጊዜ ስላለው ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ ሃይማኖትን ስለመቀላቀል የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ በአሁኑ ጊዜም ይሠራል? አዎን ይሠራል። ዘይትና ውኃ በአንድ ጠርሙስ ውስጥ ቢደረግም እንኳ እንደማይቀላቀል ሁሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነቶችም ተቀላቅለው ውህደት ሊፈጥሩ አይችሉም። ለምሳሌ ያህል፣ የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ተሰባስበው ለሰላም ሲጸልዩ ልመናቸውን የሚያቀርቡት ለየትኛው አምላክ ነው? ለሕዝበ ክርስትና ሥላሴ? ወይስ ለሂንዱዎች አምላክ ለብራህማ? ለቡድሃ? ወይስ ለሌላ አምላክ?
ነቢዩ ሚክያስ “በመጨረሻው ዘመን” ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ምን እንደሚሉ በትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤ በመንገዱ እንድንሄድ፣ መንገዱን ያስተምረናል።” (ሚክያስ 4:1-4) በውጤቱም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ሰላምና አንድነት ይኖራል፤ ይህ የሚሆነው ግን ሁሉም ሃይማኖቶች ስለሚቀላቀሉ ሳይሆን ሰዎች ሁሉ እውነተኛውን አንድ ሃይማኖት ስለሚከተሉ ነው።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለም ላይ ያሉ የዋና ዋና ሃይማኖቶች መሪዎች ሃይማኖትን ለመቀላቀል በ2008 ያደረጉት ስብሰባ
[ምንጭ]
REUTERS/Andreas Manolis