ጸሎት ያለው ኃይል
በመካከለኛው ምሥራቅ በምትገኘው በናኮር ከተማ ጀምበሯ ልትጠልቅ አዘቅዝቃለች። ኤሊዔዘር የሚባል አንድ ሶርያዊ አሥር ግመሎች ይዞ ከከተማው ውጪ ወደሚገኝ አንድ የውኃ ጉድጓድ ደረሰ። ኤሊዔዘር ደክሞትና ውኃ ጠምቶት እንደሚሆን የታወቀ ቢሆንም ይበልጥ ያሳሰበው ሌላ ነገር ነበር። ለጌታው ልጅ ሚስት ፍለጋ ከሩቅ አገር ተጉዞ መጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ ይቺን ሴት ማግኘት ያለበት ከጌታው ዘመዶች መካከል ነው። ይህን ከባድ ኃላፊነት እንዴት ይወጣዋል?
ኤሊዔዘር ጸሎት ኃይል እንዳለው ያምናል። ፍጹም ቅንነት በተሞላበት አስደናቂ እምነት የሚከተለውን የትሕትና ልመና አቀረበ:- “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ እለምንሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፣ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ፣ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፣ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርስዋም:- አንተ ጠጣ፣ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፣ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።”—ዘፍጥረት 24:12-14
ኤሊዔዘር ጸሎት ኃይል እንዳለው የነበረው ትምክህት መና አልቀረም። እንዲያውም ወደ ውኃ ጉድጓዱ የመጣችው የመጀመሪያዋ ሴት የአብርሃም የወንድሙ የልጅ ልጅ ሆና ተገኘች! ይህች ሴት ርብቃ የምትባል ስትሆን ያላገባች፣ በሥነ ምግባር ንጹሕና ውብ ነች። የሚያስገርመው ነገር ለኤሊዔዘር የሚጠጣው ውኃ መስጠት ብቻ ሳይሆን ግመሎቹ ሁሉ ጥማቸው እስኪረካ ለማጠጣት በደግነት ጥያቄ አቀረበች። ትንሽ ቆየት ብሎ ቤተሰቡ በጉዳዩ ላይ ከመከረ በኋላ ርብቃ የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ሚስት ለመሆን ከኤሊዔዘር ጋር ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ሳታቅማማ ተስማማች። አምላክ በአንዳንድ ክስተቶች ላይ ተአምራዊ በሆነ መንገድ አልፎ አልፎ ጣልቃ ይገባ በነበረበት ዘመን ኤሊዔዘር ያቀረበው ጸሎት ምንኛ አስደናቂና ግልጽ ምላሽ አግኝቷል!
ኤሊዔዘር ካቀረበው ጸሎት ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ያቀረበው ጸሎት ከፍተኛ እምነት፣ ትሕትና እንዲሁም ለሌሎች ፍላጎት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አሳቢነት እንዳለው የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም የኤሊዔዘር ጸሎት ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት ለሚያደርግበት መንገድ ተገዢ መሆኑን አሳይቷል። አምላክ ከአብርሃም ጋር የነበረውን ልዩ ግንኙነት እንዲሁም ወደፊት ለሰው ዘር በሙሉ የሚዘንቡት በረከቶች በአብርሃም በኩል እንደሚመጡ የሰጠውን ተስፋ ያውቅ እንደነበር አያጠራጥርም። (ዘፍጥረት 12:3) በመሆኑም ኤሊዔዘር ጸሎቱን የከፈተው “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ” በማለት ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ የሚባረኩበት የአብርሃም ዘር ነው። (ዘፍጥረት 22:18) በዛሬው ጊዜ ጸሎታችን መልስ እንዲያገኝ ከፈለግን አምላክ በልጁ በኩል ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት የሚያደርግበትን መንገድ በትሕትና መቀበላችንን ማሳየት አለብን። ኢየሱስ ክርስቶስ “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል” ብሏል።—ዮሐንስ 15:7
የክርስቶስ ተከታይ የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ የተናገራቸውን የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት አይቷል። ጸሎት ኃይል እንዳለው የነበረው እምነት እንዲያው ከንቱ አልነበረም። መሰል ክርስቲያኖች ጭንቀታቸውን ሁሉ ለአምላክ በጸሎት እንዲነግሩ ከማበረታታቱም በላይ ‘ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን እችላለሁ’ በማለት የራሱን ምሥክርነት ሰጥቷል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) ይህ ማለት ታዲያ ጳውሎስ በጸሎት የጠየቀውን ነገር ሁሉ አግኝቷል ማለት ነው? እስቲ እንመልከት።
የጠየቀውን ሁሉ አላገኘም
ጳውሎስ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ “የሥጋዬ መውጊያ” ሲል የገለጸው አንድ የሚያሰቃየው ነገር ነበር። (2 ቆሮንቶስ 12:7) ይህም ተቃዋሚዎችና “ውሸተኞች ወንድሞች” የፈጠሩበት አእምሯዊና ስሜታዊ ጭንቀት ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 11:26፤ ገላትያ 2:4) ወይም አንድ ሥር የሰደደ የዓይን ሕመም ያስከተለበት አካላዊ ሥቃይ ሊሆን ይችላል። (ገላትያ 4:15) ብቻ ምንም ይሁን ምን ይህ ‘የሥጋ መውጊያ’ የጳውሎስን አቅም የሚያዳክም ነበር። “ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ” ሲል ጽፏል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ የጠየቀው ነገር ሳይሟላለት ቀርቷል። ጳውሎስ አስቀድሞ ከአምላክ ያገኛቸው ፈተናዎችን ለመቋቋም እንደሚያስችለው ኃይል የመሳሰሉት መንፈሳዊ በረከቶች በቂ እንደሆኑ ተነግሮታል። ከዚህ በተጨማሪ አምላክ “ኃይሌ በድካም ይፈጸማል” ብሎታል።—2 ቆሮንቶስ 12:8, 9
ከኤሊዔዘርና ከጳውሎስ ምሳሌ ምን እንማራለን? እርግጥ ነው፣ ይሖዋ አምላክ በትሕትና እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። ይሁን እንጂ አምላክ ነገሮችን አርቆ ስለሚመለከት ሁልጊዜ የጠየቁትን ነገር ሁሉ ይፈጽምላቸዋል ማለት አይደለም። ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ለእኛ የሚበጀውን ነገር ያውቃል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ምንጊዜም እርምጃ የሚወስደው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ዓላማው ጋር በሚስማማ መንገድ ነው።
መንፈሳዊ ፈውስ የሚከናወንበት ጊዜ
አምላክ ልጁ ምድርን በሚገዛበት የሺህ ዓመት ዘመን ውስጥ የሰው ልጆችን ከማንኛውም ዓይነት አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ በሽታዎች ለመፈወስ ቃል ገብቷል። (ራእይ 20:1-3፤ 21:3-5) እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ ይህን የገባውን ተስፋ እውን ለማድረግ ኃይል እንዳለው ሙሉ እምነት በማሳደር በጉጉት ይጠባበቃሉ። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ያን ዓይነት ተአምራዊ ፈውስ ለማግኘት ባይጠባበቁም የሚደርሱባቸውን ፈተናዎች ችለው ለማለፍ አምላክ ማጽናኛና ብርታት እንዲሰጣቸው ይጸልያሉ። (መዝሙር 55:22) በተጨማሪም በሚታመሙበት ጊዜ አቅማቸው በሚፈቅድላቸው መጠን የተሻለ ሕክምና ለማግኘት አምላክ አመራር እንዲሰጣቸው ሊጸልዩ ይችላሉ።
አንዳንድ ሃይማኖቶች ኢየሱስና ሐዋርያቱ ተአምራዊ ፈውስ እንዳከናወኑ በመጥቀስ የታመሙ ሰዎች አሁኑኑ ተአምራዊ ፈውስ ለማግኘት እንዲጸልዩ ያበረታታሉ። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ተአምራት የተከናወኑት ለአንድ ለየት ያለ ዓላማ ነበር። እነዚህ ተአምራት ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲሁም አምላክ ሞገሱን ከአይሁድ ብሔር ላይ አንስቶ አዲስ ወደሆነው የክርስቲያን ጉባኤ ማዛወሩን ለማሳየት አገልግለዋል። በዚያን ጊዜ አዲስ የተቋቋመውን የክርስቲያን ጉባኤ እምነት ለማጠናከር ተአምራዊ ስጦታዎች አስፈልገው ነበር። ጨቅላ የነበረው ጉባኤ በምሳሌያዊ አነጋገር በሁለት እግሩ ከቆመና ከጎለመሰ በኋላ ተአምራዊ ስጦታዎች ‘ተሽረዋል።’—1 ቆሮንቶስ 13:8, 11
በዚህ ወሳኝ ወቅት ይሖዋ አምላክ አምላኪዎቹን ይበልጥ አስፈላጊ ወደሆነው መንፈሳዊ የፈውስ ሥራ እየመራቸው ነው። ጊዜው ከማክተሙ በፊት ሰዎች ለሚከተለው ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለባቸው:- “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።”—ኢሳይያስ 55:6, 7
ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች የሚያገኙት ይህ መንፈሳዊ ፈውስ በአምላክ መንግሥት ምሥራች ስብከት አማካኝነት በመከናወን ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹ ይህን ሕይወት አድን ሥራ እንዲያከናውኑ ኃይል በመስጠት የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ እንዲገቡና ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርቱ እየረዳቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱን መንፈሳዊ ፈውስ ለማግኘት ከልብ የሚጸልዩ ሁሉ እንዲሁም ይህን የፈውስ ሥራ ለማከናወን እርዳታ ለማግኘት የሚጸልዩ ሁሉ በእርግጥ ጸሎታቸው መልስ እያገኘ ነው።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ኤሊዔዘርና ርብቃ/The Dorè Bible Illustrations/ Dover Publications