ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስ” ይሰጣቸዋል
“እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”—ሉቃስ 11:13
1. የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የሚያስፈልገን በተለይ በየትኞቹ ጊዜያት ነው?
‘ይህን ችግር በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ካልሆነ በቀር ብቻዬን ልወጣው አልችልም!’ በማለት ስሜትህን የገለጽክበት ጊዜ አለ? ብዙ ክርስቲያኖች እንዲህ ብለዋል። ምናልባት እንዲህ ያልከው ከባድ በሽታ እንደያዘህ ባወቅህበት ወቅት ሊሆን ይችላል። ካልሆነም ደግሞ የዕድሜ ልክ የትዳር አጋርህ በሞት ስትለይህ አሊያም በአንድ ወቅት የነበረህ የደስተኝነት ስሜት በመንፈስ ጭንቀት ምክንያት በጨለመበት ጊዜ ይሆናል። በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠመህን አሳዛኝ ክስተት ተቋቁመህ ያለፍከው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ከወትሮው የተለየ “እጅግ ታላቅ ኀይል” ስለሰጠህ ብቻ እንደሆነ ተሰምቶህ ይሆናል።—2 ቆሮንቶስ 4:7-9፤ መዝሙር 40:1, 2
2. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን ከማይታዘዘው ዓለም የሚደርስባቸውን እያየለ የሚሄድ ግፊትና ተቃውሞ ተቋቁመው መኖር ግድ ሆኖባቸዋል። (1 ዮሐንስ 5:19) ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስ ተከታዮች ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው በያዙ’ ሰዎች ላይ አረመኔያዊ ጦርነት በሚያካሂደው በሰይጣን ዲያብሎስ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል። (ራእይ 12:12, 17) በመሆኑም ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የአምላክ መንፈስ እርዳታ ቢያስፈልገን አያስገርምም። የአምላክን መንፈስ አብዝተን ማግኘታችንን እንድንቀጥል ምን ማድረግ ይኖርብናል? ይሖዋ፣ መከራ ሲያጋጥመን የሚያስፈልገንን ጥንካሬ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? ኢየሱስ የተናገራቸው ሁለት ምሳሌዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጡናል።
ሳታቋርጡ ጸልዩ
3, 4. ኢየሱስ ምን ምሳሌ ተናገረ? ምሳሌውን ከጸሎት ጋር ያያያዘውስ እንዴት ነው?
3 በአንድ ወቅት ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ኢየሱስን ‘ጌታ ሆይ መጸለይ አስተምረን’ ብሎት ነበር። (ሉቃስ 11:1) ኢየሱስ የዚህን ጥያቄ ምላሽ ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው ጊዜ ሁለት ምሳሌዎችን ጠቀሰላቸው። የመጀመሪያው ምሳሌ እንግዳ ስለመጣበት አንድ ሰው የሚገልጽ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ልጁን ስለሚያዳምጥ አንድ አባት የሚናገር ነው። እስቲ እነዚህን ሁለት ምሳሌዎች በየተራ እንመርምር።
4 ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ቢኖረውና በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ፣ ‘ወዳጄ ሆይ፤ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ አንድ ባልንጀራዬ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር የለኝምና’ ብሎ ለመነው እንበል። በቤት ውስጥ ያለውም፣ ‘አታስቸግረኝ፤ በሩ ተቈልፎአል፤ ልጆቼም አብረውኝ ተኝተዋል፤ ከእንግዲህ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋልን? እላችኋለሁ፤ ወዳጁ በመሆኑ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፣ ስለ ንዝነዛው ብቻ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።” ከዚያም ኢየሱስ ምሳሌው ከጸሎት ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ለማሳየት እንደሚከተለው ሲል አብራራላቸው:- “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ [“ሳታቋርጡ፣” NW] ለምኑ ይሰጣችኋል፤ [“ሳታቋርጡ፣” NW] ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ [“ሳታቋርጡ፣” NW] በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ምክንያቱም የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።”—ሉቃስ 11:5-10
5. ወዳጁን ስለነዘነዘው ሰው የሚገልጸው ምሳሌ ስንጸልይ ሊኖረን የሚገባውን አመለካከት አስመልክቶ ምን ያስተምረናል?
5 የሚፈልገውን ነገር ሳይታክት ስለጠየቀው ሰው የሚናገረው ይህ ሕያው ምሳሌ፣ በምንጸልይበት ጊዜ ምን አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ በግልጽ ያሳያል። ኢየሱስ ሰውየው የሚፈልገውን ነገር ያገኘው “ስለ ንዝነዛው” መሆኑን ተናግሯል። (ሉቃስ 11:8) ‘መነዝነዝ’ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። መነዝነዝ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “እፍረተቢስ” የሚል ነው። እፍረተቢስ የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ መጥፎ ባሕርይን ያመለክታል። ይሁንና አንድ ሰው እፍረተቢስ የሚሆነው ወይም የሚነዘንዘው መልካም ነገሮችን ለማግኘት ብሎ ከሆነ ይህ የሚያስመሰግነው ባሕርይ ነው ሊባል ይችላል። ይህ ሁኔታ እንግዳ በመጣበት ሰውዬ ላይ ታይቷል። ሰውየው አፍሮ የሚፈልገውን ነገር ከመጠየቅ ወደኋላ አላለም። ኢየሱስ ይህን ሰው ምሳሌ አድርጎ ስላቀረበልን እኛም ሳንታክት መጸለይ ይኖርብናል። ይሖዋ ‘ሳናቋርጥ እንድንለምን፣ ሳናቋርጥ እንድንፈልግና ሳናቋርጥ እንድናንኳኳ’ ይሻል። በምላሹም ይሖዋ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን አብልጦ ይሰጣቸዋል።’
6. በኢየሱስ ዘመን ሰዎች ሌሎችን በእንግድነት ስለመቀበል ምን አመለካከት ነበራቸው?
6 ኢየሱስ ሳንታክት መጸለይ እንዳለብን ብቻ ሳይሆን ለምን እንዲህ ማድረግ እንደሚኖርብን ጭምር ገልጿል። ይህን ትምህርት በሚገባ ለመረዳት እንግዳ ስለመጣበት ሰው የሚናገረውን የኢየሱስን ምሳሌ ሲሰሙ የነበሩ ሰዎች ስለ እንግዳ ተቀባይነት የነበራቸውን አመለካከት እንመርምር። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች በተለይ ደግሞ የአምላክ አገልጋዮች የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል እጅግ ከፍ አድርገው ይመለከቱት እንደነበረ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ያሳያሉ። (ዘፍጥረት 18:2-5፤ ዕብራውያን 13:2) ለአንድ እንግዳ ተገቢውን አቀባበል አለማድረግ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነበር። (ሉቃስ 7:36-38, 44-46) ይህን በአእምሯችን በመያዝ ኢየሱስ የተናገረውን ታሪክ በድጋሚ እንመልከት።
7. ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው እንግዳ ተቀባይ ወዳጁን ከእንቅልፉ ለመቀስቀስ እፍረት ያልተሰማው ለምንድን ነው?
7 በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው እንግዳ የመጣበት በእኩለ ሌሊት ነው። ይህ ሰው ለእንግዳው ምግብ ማቅረብ እንዳለበት ቢሰማውም ‘የሚያቀርብለት ነገር አልነበረውም።’ በእርሱ አመለካከት ይህ አጣዳፊ ጉዳይ ነው! ምንም ይሁን ምን ለእንግዳው ትንሽም ቢሆን እንጀራ ማግኘት እንዳለበት ተሰምቶታል። ስለዚህ ወደ ባልንጀራው ሄዶ ያለ አንዳች እፍረት ከእንቅልፉ በመቀስቀስ “ወዳጄ ሆይ፤ ሦስት እንጀራ አበድረኝ” በማለት ጠየቀው። የፈለገውን እስኪያገኝ ድረስም መጠየቁን አላቆመም። ምክንያቱም እንግዳውን በተገቢው ሁኔታ አስተናግዷል ሊባል የሚችለው እንጀራውን ካገኘ ብቻ ነው።
በጣም የምትፈልጉትን ነገር ለማግኘት ደጋግማችሁ ትለምናላችሁ
8. መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ሳናቋርጥ እንድንጸልይ የሚገፋፋን ምንድን ነው?
8 ይህ ምሳሌ ሳናቋርጥ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው? ይህ ሰው ሳያቋርጥ የጠየቀው፣ እንጀራውን ማግኘቱ እንግዳ ተቀባይ መሆኑ ያስከተለበትን ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚያስችለው ስለተሰማው ነው። (ኢሳይያስ 58:5-7) ለእንግዳው የሚያቀርብለት ነገር ካላገኘ ግዴታውን መወጣት አይችልም። በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አገልግሎታችንን ለመፈጸም የአምላክን መንፈስ ማግኘታችን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ስለምንገነዘብ ወደ አምላክ መጸለያችንንና መንፈሱን እንዲሰጠን መለመናችንን አናቋርጥም። (ዘካርያስ 4:6) የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ካላገኘን ያሰብነው ሊሳካልን አይችልም። (ማቴዎስ 26:41) ከዚህ ምሳሌ በመነሳት ልንደርስበት የሚገባው እጅግ አስፈላጊ የሆነ መደምደሚያ ምንድን ነው? የአምላክን መንፈስ ማግኘታችን ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ ከተሰማን መንፈሱን ለማግኘት ሳናቋርጥ እንጸልያለን።
9, 10. (ሀ) አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን በተደጋጋሚ መለመናችን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ?
9 በዛሬው ጊዜ ይህን ትምህርት በሥራ ላይ ለማዋል እንድንችል እንዲረዳን አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከቤተሰብህ አባላት ውስጥ አንዱ በእኩለ ሌሊት ታመመ እንበል። እርዳታ ለማግኘት አንድን ሐኪም ከእንቅልፉ ትቀሰቅሰዋለህ? ቀላል ሕመም ከሆነ እንዲህ ላታደርግ ትችላለህ። ይሁንና በሽታው ልብ ድካም ቢሆን ሐኪሙን ለመጥራት ይሉኝታ አይዝህም። ለምን? አጣዳፊ ሁኔታ ስለገጠመህ ነው። የባለሙያ እርዳታ የግድ እንደሚያስፈልግህ ተገንዝበሃል። እርዳታ አለመጠየቅህ በሽተኛውን ለሞት ሊዳርገው ይችላል። በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች ቀጣይ የሆነ አንድ ዓይነት አጣዳፊ ጉዳይ አጋጥሟቸዋል ለማለት ይቻላል። ደግሞም ሰይጣን እኛን ለመዋጥ ልክ “እንደሚያገሣ አንበሳ” በመዞር ላይ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:8) በመንፈሳዊ ሕያው ሆነን ለመቀጠል የአምላክ መንፈስን እርዳታ ማግኘታችን የግድ አስፈላጊ ነው። የአምላክን እርዳታ አለመጠየቅ አስከፊ ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል። በመሆኑም አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ሳንታክት እንለምናለን። (ኤፌሶን 3:14-16) ‘እስከ መጨረሻው ለመጽናት’ የሚረዳንን ጥንካሬ ማግኘት የምንችለው እንዲህ ስናደርግ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 10:22፤ 24:13
10 ይህም በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ቆም ብለን ‘ምን ያህል ያለመታከት እጸልያለሁ?’ እያልን ራሳችንን መጠየቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን በሚገባ ከተገነዘብን መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት በተደጋጋሚ እንደምንጸልይ አትዘንጋ።
ተማምነን እንድንጸልይ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
11. ኢየሱስ ስለ አባትና ልጅ የሚናገረውን ምሳሌ ከጸሎት ጋር ያያዘው እንዴት ነው?
11 ኢየሱስ እንግዳ ስለመጣበት ሰው የተናገረው ምሳሌ አንድ አማኝ ጸሎት ሲያቀርብ ሊኖረው የሚገባውን ዝንባሌ አጉልቶ ይገልጻል። ቀጣዩ ምሳሌ ደግሞ የጸሎት ሰሚውን ማለትም የይሖዋ አምላክን ስሜት የሚያጎላ ነው። ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን? ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል። ከዚያም ኢየሱስ ምሳሌው ከጸሎት ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ሲገልጽ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!” ብሏል።—ሉቃስ 11:11-13
12. ልጁ የሚለምነውን ነገር ስለሚሰጥ አባት የሚናገረው ምሳሌ ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን የሚያጎላው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ፣ ለልጁ ምላሽ ስለሚሰጥ አባት በተናገረው ምሳሌ ላይ ይሖዋ በጸሎት ወደ እርሱ ስለሚቀርቡ ሰዎች ያለውን ስሜት ገልጿል። (ሉቃስ 10:22) በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቀረቡት ሁለት ምሳሌዎች መካከል ያለውን ልዩነት ልብ በል። ይሖዋ፣ በመጀመሪያው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ሰው እርዳታ ሲጠየቅ ምላሽ ለመስጠት የሚያቅማማ አምላክ ሳይሆን ለልጁ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ አፍቃሪ ሰብዓዊ ወላጅ ነው። (መዝሙር 50:15) ከዚህም በተጨማሪ በሰማይ የሚኖረውን አባት ከአንድ ሰብዓዊ አባት ጋር በማወዳደር ይሖዋ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ መሆኑን ጠቅሷል። ኢየሱስ አንድ ሰብዓዊ አባት በወረሰው ኃጢአት ምክንያት “ክፉ” ቢሆንም እንኳ ለልጁ መልካም ስጦታ የሚሰጥ ከሆነ ለጋስ የሆነው የሰማዩ አባታችን እንደ ቤተሰቡ ለሚያያቸው አምላኪዎቹ መንፈስ ቅዱስን አብልጦ እንደሚሰጥ መጠበቃችን ምንኛ ተገቢ ነው!—ያዕቆብ 1:17
13. ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
13 ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን፣ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን ስንለምን ከጠየቅነው በላይ ሊሰጠን ፈቃደኛ እንደሆነ መተማመን እንችላለን። (1 ዮሐንስ 5:14) ይሖዋ ደግመን ደጋግመን ወደ እርሱ በጸሎት ስንቀርብ በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው ‘አታስቸግሩኝ፤ በሩ ተቈልፎአል’ አይልም። (ሉቃስ 11:7) እንዲያውም ኢየሱስ “[“ሳታቋርጡ፣” NW] ለምኑ ይሰጣችኋል፤ [“ሳታቋርጡ፣” NW] ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ [“ሳታቋርጡ፣” NW] በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል” ብሏል። (ሉቃስ 11:9, 10) አዎን፣ ይሖዋ ‘በጠራነው ቀን ይሰማናል።’—መዝሙር 20:9፤ 145:18
14. (ሀ) መከራ የደረሰባቸው አንዳንድ ሰዎች የትኛው የተሳሳተ ሐሳብ ያጠቃቸዋል? (ለ) መከራዎች ሲደርሱብን ተማምነን ወደ ይሖዋ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
14 ከዚህ ባሻገር ኢየሱስ ስለ አፍቃሪ አባት የተናገረው ምሳሌ የይሖዋ ጥሩነት ማንኛውም ሰብዓዊ ወላጅ ከሚያሳየው ቸርነት እጅግ የላቀ መሆኑን አጉልቶ ያሳያል። ከዚህም የተነሳ ማናችንም ብንሆን ችግሮች ሲገጥሙን ይህ የሆነው አምላክ ስላዘነብን ነው ብለን ፈጽሞ ማሰብ አይገባንም። እንዲህ እንድናስብ የሚፈልገው ቀንደኛው ጠላታችን ሰይጣን ነው። (ኢዮብ 4:1, 7, 8፤ ዮሐንስ 8:44) አንድ ሰው ራሱን እንዲኮንን የሚያበረታታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ የለም። ይሖዋ “በክፉ” አይፈትነንም። (ያዕቆብ 1:13) እንዲሁም እባብ መሰል መከራ ወይም ጊንጥ የሚመስል ፈተና አያደርስብንም። የሰማዩ አባታችን “ለሚለምኑት መልካም ስጦታን” ይሰጣቸዋል። (ማቴዎስ 7:11፤ ሉቃስ 11:13) ስለ ይሖዋ ጥሩነትና እኛን ለመርዳት ስላለው የፈቃደኝነት መንፈስ በተገነዘብን መጠን ተማምነን ወደ እርሱ ለመጸለይ ይበልጥ እንገፋፋለን። እንዲህ ባደረግን ቁጥር እኛም “እግዚአብሔር በእርግጥ ሰምቶኛል፤ ጸሎቴንም አድምጦአል” ሲል እንደጻፈው መዝሙራዊ ለማለት እንነሳሳለን።—መዝሙር 10:17፤ 66:19
መንፈስ ቅዱስ ረዳታችን የሚሆነው እንዴት ነው?
15. (ሀ) ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ ምን ቃል ገብቷል? (ለ) መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚረዳበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
15 ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ በምሳሌዎቹ ላይ የሰጠውን ማረጋገጫ በድጋሚ ጠቅሶታል። መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ ለሐዋርያቱ “እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:16) በመሆኑም ኢየሱስ ወደፊት አጽናኝ ወይም ረዳት የሆነው መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸው ነበር፤ ይህ ደግሞ የእኛንም ዘመን ይጨምራል። በአሁኑ ጊዜ ይህን ዓይነቱን ድጋፍ የምናገኝበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስ የተለያዩ መከራዎችን እንድንቋቋም ይረዳናል። እንዴት? ፈተናዎች ደርሰውበት የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ መንፈስ ቅዱስ እርሱን እንዴት እንደረዳው ገልጿል። እስቲ ምን ብሎ እንደጻፈ በአጭሩ እንመልከት።
16. ያለንበት ሁኔታ ከጳውሎስ ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው?
16 በመጀመሪያ ጳውሎስ ለእምነት አጋሮቹ ‘የሥጋ መውጊያ’ ከሆነበት አንድ ዓይነት ችግር ጋር እየታገለ መሆኑን ሳይሸሽግ ነገራቸው። ከዚያም “ይህ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ፣ ጌታን [ይሖዋን] ሦስት ጊዜ ለመንሁት” በማለት ገለጸ። (2 ቆሮንቶስ 12:7, 8) ምንም እንኳ ጳውሎስ ያለበት ችግር እንዲወገድለት አምላክን የለመነ ቢሆንም ሁኔታው ሊወገድለት አልቻለም። ምናልባት አንተም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ትገኝ ይሆናል። ልክ እንደ ጳውሎስ ይሖዋ ያለብህን ሥቃይ እንዲያስወግድልህ ያለምንም መታከት በሙሉ ልብ ጸልየህ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ችግሩ አልተወገደልህም። ይህ ማለት ይሖዋ ላቀረብካቸው ጸሎቶች ምላሽ አልሰጠህም እንዲሁም መንፈሱ እየረዳህ አይደለም ማለት ነው? በጭራሽ! (መዝሙር 10:1, 17) ሐዋርያው ጳውሎስ ቀጥሎ ምን እንዳለ ተመልከት።
17. ይሖዋ ጳውሎስ ላቀረበው ጸሎት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?
17 አምላክ ለጳውሎስ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” የሚል ምላሽ ሰጥቶታል። ጳውሎስም “ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ [“እንደ ድንኳን በእኔ ላይ ያድር ዘንድ፣” NW]፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ” ሊል ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 12:9፤ መዝሙር 147:5) በዚህ የተነሳ ከለላ የሚሆነው የአምላክ ብርቱ ኃይል በክርስቶስ በኩል ልክ እንደ ድንኳን በእርሱ ላይ አድሮ ነበር። በዛሬው ጊዜ፣ ይሖዋ በተመሳሳይ መንገድ ለጸሎታችን መልስ ይሰጠናል። ጥበቃውን ልክ እንደ ድንኳን በአገልጋዮቹ ላይ ይዘረጋል።
18. ያሉብንን ችግሮች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
18 እውነት ነው፣ አንድ ድንኳን ዝናብ እንዳይዘንብ ወይም ነፋስ እንዳይነፍስ ማድረግ አይችልም፤ ይሁንና ከእነዚህ ነገሮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ይጠብቀናል። በተመሳሳይም እንደ መጠለያ የሚሆንልን “የክርስቶስ ኀይል” መከራ እንዳያጋጥመን ወይም ችግር እንዳይደርስብን አይከላከልልንም። ሆኖም ይህ ዓለም ከሚያመጣቸው ጎጂ ነገሮችና ገዥው ሰይጣን ከሚሰነዝርብን ጥቃት መንፈሳዊ ጥበቃ እንድናገኝ ይረዳናል። (ራእይ 7:9, 15, 16) በመሆኑም ‘ከአንተ እንዲወገድልህ’ ከጠየቅኸው መከራ ጋር እየታገልህ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ የምታደርገውን ትግል እንደሚረዳልህና ‘ለጩኸትህ’ መልስ እንደሚሰጥ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ኢሳይያስ 30:19፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
19. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው? ለምንስ?
19 ከአምላክ የራቀው የዚህ ዓለም ‘የመጨረሻ ዘመን’ በአስጨናቂነቱ ተለይቶ ይታወቃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ያም ሆኖ ለአምላክ አገልጋዮች ይህ ጊዜ ጨርሶ ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ሳይታክቱና ተማምነው ለሚለምኑት ሁሉ ቅዱስ መንፈሱን አብዝቶ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው፤ ይህ መንፈስ ድጋፍና ጥበቃ ያደርግላቸዋል። እንግዲያው እኛም የአምላክን መንፈስ ለማግኘት በየዕለቱ መጸለያችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—መዝሙር 34:6፤ 1 ዮሐንስ 5:14, 15
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
• ይሖዋ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን ያቀረብነውን ልመና እንደሚሰማን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
• መንፈስ ቅዱስ መከራዎችን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ወዳጁን ስለነዘነዘው ሰው ከተናገረው ምሳሌ ምን እንማራለን?
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት ሳትታክት ትጸልያለህ?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሳቢ ስለሆነው አባት የሚናገረው ምሳሌ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?