ቃላችሁ “አዎ ሆኖ እያለ አይደለም” ነው?
እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እንመልከት፦ በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እሁድ ዕለት ጠዋት ከአንድ ወጣት ወንድም ጋር አብሮ ለማገልገል ቀጠሮ ይዟል። የዚያን ዕለት ጠዋት ለዚህ ሽማግሌ አንድ ሌላ ወንድም ስልክ ይደውልለታል፤ ስልኩን የደወለው ወንድም ባለቤቱ የመኪና አደጋ አጋጥሟት በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል እንደተወሰደች ለሽማግሌው ነገረው። ከዚያም ያለ ደም ሕክምና በመስጠት ሊተባበራቸው የሚችል ሐኪም በማፈላለግ ረገድ እንዲረዳው ጠየቀው። በመሆኑም ሽማግሌው፣ አፋጣኝ እርዳታ የሚያስፈልገውን ይህን ቤተሰብ ለማገዝ ሲል ከወጣቱ ወንድም ጋር ለማገልገል የያዘውን ቀጠሮ ሰረዘ።
ሌላ ሁኔታ ደግሞ እንመልከት፦ አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት፣ በጉባኤያቸው የምትገኝን ነጠላ እህት ከሁለት ልጆቿ ጋር አንድ ምሽት ቤታቸው መጥታ እንድትጫወት ጋበዟት። እህት ይህንን ለልጆቿ ስትነግራቸው ፊታቸው በደስታ ፈካ። ልጆቹ ያንን ምሽት በጉጉት ይጠብቁ ጀመር። ይሁንና ግብዣው አንድ ቀን ሲቀረው ባልና ሚስቱ አንድ ያልተጠበቀ ነገር እንዳጋጠማቸውና ግብዣውን ለመሰረዝ እንደተገደዱ ለእናትየው ነገሯት። ይህች እህት፣ ባልና ሚስቱ ግብዣውን የሰረዙት ለምን እንደሆነ በኋላ ላይ አወቀች። ባልና ሚስቱ እሷን ከጋበዙ በኋላ እነሱ ራሳቸው ጓደኞቻቸው ቤት በዚያው ቀን ተጋበዙ፤ ከእህት ጋር የነበራቸውን ፕሮግራም የሰረዙት የጓደኞቻቸውን ግብዣ ስለተቀበሉ ነው።
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ቃላችንን መጠበቅ እንዳለብን የታወቀ ነው። ቃላችን “አዎ” ሆኖ እያለ “አይ” ሊሆን አይገባም። (2 ቆሮ. 1:18) ይሁን እንጂ ከላይ የተመለከትናቸው ሁለት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት የሚያጋጥሙን ሁኔታዎች ሁሉ ተመሳሳይ አይደሉም። አንዳንድ ጊዜ የያዝነውን ፕሮግራም እንድንሰርዝ የሚያስገድድ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ነበር።
ጳውሎስ ቃሉን እንደማይጠብቅ ስሞታ ቀረበበት
ጳውሎስ በ55 ዓ.ም. በሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ከኤፌሶን ተነስቶ የኤጅያንን ባሕር በማቋረጥ ወደ ቆሮንቶስ ለመሄድና ከዚያም ወደ መቄዶንያ ለመጓዝ አስቦ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ የቆሮንቶስን ጉባኤ ለሁለተኛ ጊዜ ሊጎበኝ አቅዶ ነበር፤ ይህን ለማድረግ ያሰበው የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ወንድሞች የሚልኩትን የልግስና ስጦታ ለማሰባሰብ ሳይሆን አይቀርም። (1 ቆሮ. 16:3) እንዲህ ዓይነት እቅድ እንደነበረው በ2 ቆሮንቶስ 1:15, 16 ላይ ከተገለጸው ከሚከተለው ሐሳብ መረዳት ይቻላል፦ “በዚህ በመተማመን ዳግመኛ እንድትደሰቱ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እናንተ ለመምጣት ቀደም ሲል አቅጄ ነበር፤ ከእናንተ ጋር ለአጭር ጊዜ ከቆየሁ በኋላ ወደ መቄዶንያ ለመሄድና ከመቄዶንያ ወደ እናንተ ለመመለስ ከዚያም የተወሰነ መንገድ ከሸኛችሁኝ በኋላ ወደ ይሁዳ ለመሄድ አስቤ ነበር።”
ጳውሎስ ቀደም ሲል በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ እቅዱ ለቆሮንቶስ ወንድሞች ሳይገልጽላቸው አልቀረም። (1 ቆሮ. 5:9) ይሁን እንጂ ይህን ደብዳቤ ከላከ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በጉባኤው ውስጥ ሥር የሰደደ አለመግባባት እንዳለ ከቀሎኤ ቤተሰብ እና ከሌሎች ሰዎች ሰማ። (1 ቆሮ. 1:10, 11) በመሆኑም ጳውሎስ የመጀመሪያ እቅዱን ለመለወጥ ወሰነ፤ ከዚያም በአሁኑ ጊዜ 1 ቆሮንቶስ በመባል የሚታወቀውን ደብዳቤ ጻፈላቸው። በዚህ ደብዳቤው ላይ ጳውሎስ ፍቅር ያዘለ ምክርና እርማት ሰጥቷቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከጉዞው ጋር በተያያዘ የነበረውን እቅድ እንደቀየረና መጀመሪያ ወደ መቄዶንያ ሄዶ ከዚያ በኋላ ወደ ቆሮንቶስ እንደሚመጣ ነገራቸው።—1 ቆሮ. 16:5, 6a
በቆሮንቶስ ያሉ ወንድሞች የጳውሎስ ደብዳቤ ሲደርሳቸው በዚያ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ “ምርጥ ሐዋርያት” ተብዬዎች ጳውሎስ ቃሉን የማይጠብቅና ወላዋይ እንደሆነ አድርገው አስወሩበት። ጳውሎስም ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ዓይነት እቅድ አውጥቼ የነበረው እንዲሁ ሳላስብበት ይመስላችኋል? ወይስ ማንኛውንም ነገር ሳቅድ በሥጋዊ ስሜት ተነድቼ በማቀድ አንዴ ‘አዎ፣ አዎ’ መልሼ ደግሞ ‘አይ፣ አይ’ የምል ይመስላችኋል?”—2 ቆሮ. 1:17፤ 11:5
ከዚህ ታሪክ አንጻር፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እንዲህ ዓይነት እቅድ ያወጣው እንዲሁ ሳያስብበት ይሆን?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ይህ እንዳልሆነ ግልጽ ነው! “ሳላስብበት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አንድ ሰው ወላዋይ እንደሆነ በሌላ አባባል እምነት እንደማይጣልበትና ቃሉን እንደማይጠብቅ የሚያመለክት ነው። ጳውሎስ “ማንኛውንም ነገር ሳቅድ በሥጋዊ ስሜት ተነድቼ [የማቅድ ይመስላችኋል]?” የሚል ጥያቄ አንስቷል፤ ይህም እቅዱን የለወጠው እምነት የማይጣልበት ሰው በመሆኑ ምክንያት እንዳልሆነ በቆሮንቶስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ግልጽ አድርጎላቸው መሆን አለበት።
ጳውሎስ የቀረበበት ስሞታ ትክክል አለመሆኑን ሲያስረዳ “አምላክ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ሁሉ እኛ ለእናንተ የምንናገረው ቃልም አዎ ከሆነ አይ ማለት ሊሆን አይችልም” በማለት በአጽንኦት ተናግሯል። (2 ቆሮ. 1:18) ሐዋርያው እቅዱን የለወጠው በቆሮንቶስ ጉባኤ ለሚገኙት ወንድሞቹና እህቶቹ ስለሚያስብ ነው። በ2 ቆሮንቶስ 1:23 ላይ እንደገለጸው ወደ ቆሮንቶስ ለመሄድ የነበረውን እቅድ የለወጠው ‘ለባሰ ሐዘን እንዳይዳርጋቸው’ ብሎ ነው። በእርግጥም በአካል ከእነሱ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ነገሮችን እንዲያስተካክሉ ጊዜ ሰጥቷቸዋል። ጳውሎስ እንዳሰበውም የጻፈላቸው ደብዳቤ እንዲያዝኑና ንስሐ እንዲገቡ አነሳስቷቸዋል፤ ሐዋርያው በመቄዶንያ እያለ ከቲቶ ይህን ሲሰማ በጣም ተደሰተ።—2 ቆሮ. 6:11፤ 7:5-7
ለአምላክ “አሜን” እንላለን
ጳውሎስ ወላዋይ እንደሆነ የቀረበበት ስሞታ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ቃሉን የማይጠብቅ ከሆነ በስብከቱ ሥራም ሊታመን እንደማይችል የሚጠቁም መልእክት ሊያስተላልፍ ይችላል። ሆኖም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሰበከላቸው ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሆነ አስታውሷቸዋል። “እኛ ማለትም እኔ፣ ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ የሰበክንላችሁ የአምላክ ልጅ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ አዎ ሆኖ እያለ አይደለም ሊሆን አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር በተያያዘ አዎ፣ አዎ ሆኗል።” (2 ቆሮ. 1:19) ታዲያ ለጳውሎስ ምሳሌ የሆነለት ኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የማይጣልበት ሰው ነው? በፍጹም! ኢየሱስ በዕለት ተዕለት ሕይወቱም ሆነ በአገልግሎቱ ምንጊዜም የሚናገረው እውነት ነበር። (ዮሐ. 14:6፤ 18:37) እንግዲያው ኢየሱስ የሰበከው ነገር በሙሉ እውነተኛ ብሎም እምነት የሚጣልበት ከሆነና ጳውሎስም ይህንኑ መልእክት ከሰበከ፣ ጳውሎስ የሰበከው መልእክትም እምነት ሊጣልበት ይችላል ማለት ነው።
ይሖዋ “የእውነት አምላክ” እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። (መዝ. 31:5) ጳውሎስ ቀጥሎ የጻፈው ነገር ይህንን ያረጋግጣል፦ “አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑም በእሱ [ማለትም በክርስቶስ] አማካኝነት አዎ ሆነዋል።” ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ ይሖዋ ቃል የገባቸው ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ ጨርሶ እንዳንጠራጠር ያደርገናል። ጳውሎስ አክሎም “ስለዚህ እኛ ለአምላክ ክብር እንድንሰጥ በእሱ አማካኝነት ለአምላክ ‘አሜን’ እንላለን” ብሏል። (2 ቆሮ. 1:20) ይሖዋ የገባው ቃል በሙሉ እንደሚፈጸም ኢየሱስ ማረጋገጫ ወይም “አሜን” ይሆናል!
ይሖዋ እና ኢየሱስ ምንጊዜም እውነትን እንደሚናገሩ ሁሉ ጳውሎስም ምንጊዜም የሚናገረው ነገር እውነት ነበር። (2 ቆሮ. 1:19) ጳውሎስ ‘በሥጋዊ ስሜት ተነድቶ የሚያቅድ’ ወላዋይ ሰው አይደለም። (2 ቆሮ. 1:17) ከዚህ ይልቅ ‘የሚመላለሰው በመንፈስ’ ነው። (ገላ. 5:16) ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነትም ለእነሱ እንደሚያስብ አሳይቷል። አዎ ሲል አዎ ማለቱ ነበር!
ቃልህ አዎ ከሆነ አዎ ነው?
በዛሬው ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት የማይመሩ ሰዎች አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ከገቡ በኋላ ትንሽ ችግር ሲያጋጥማቸው ወይም የተሻለ ነገር ሲያገኙ ቃላቸውን ማጠፋቸው የተለመደ ነው። ከንግድ ጋር በተያያዘ ሰዎች በጽሑፍ የሰፈረ ስምምነት ቢኖራቸውም እንኳ “አዎ” ሲሉ ሁልጊዜ “አዎ” ማለታቸው ላይሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች ጋብቻን፣ ሁለት ሰዎች እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ አብረው ለመኖር እንዳደረጉት ስምምነት አድርገው አያዩትም። ከዚህ ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የሚሄደው የፍቺ ቁጥር እንደሚያሳየው ብዙዎች ጋብቻን የሚመለከቱት በቀላሉ ሊፈርስ እንደሚችል ተራ ስምምነት አድርገው ነው።—2 ጢሞ. 3:1, 2
አንተስ? ቃልህ አዎ ከሆነ አዎ ነው? እርግጥ ነው፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው አንዳንድ ጊዜ፣ ወላዋይ ስለሆንክ ሳይሆን ከአቅምህ በላይ የሆነ ሁኔታ ስላጋጠመህ አንድን ፕሮግራም ለመሰረዝ ትገደድ ይሆናል። ይሁንና ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን አንድ ነገር እንደምትፈጽም ቃል ከገባህ ቃልህን ለመጠበቅ የምትችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሃል። (መዝ. 15:4፤ ማቴ. 5:37) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ፣ እምነት የሚጣልበትና በቃሉ የሚገኝ እንዲሁም ምንጊዜም እውነትን የሚናገር ሰው የሚል ስም ታተርፋለህ። (ኤፌ. 4:15, 25፤ ያዕ. 5:12) ሰዎች፣ በዕለታዊ ሕይወትህ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ሲመለከቱ ደግሞ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን እውነት ስትነግራቸው ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እንግዲያው ሁላችንም ቃላችን አዎ ከሆነ አዎ እንዲሆን ጥረት እናድርግ!
a ጳውሎስ 1 ቆሮንቶስን ከጻፈ ብዙም ሳይቆይ በጥሮአስ በኩል አድርጎ ወደ መቄዶንያ አቀና፤ እዚያ ሳለም 2 ቆሮንቶስን ጻፈ። (2 ቆሮ. 2:12፤ 7:5) ውሎ አድሮ ቆሮንቶስን ጎብኝቷል።