ሰዎች የምትሰጠውን ምክር ይቀበሉታል?
በተገቢው መንገድ የተሰጠ ተስማሚ ምክር ሁልጊዜ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል። ይህ አባባል ትክክል ነው? አይደለም! ሌላው ቀርቶ በጣም ጥሩ ችሎታ ባላቸው መካሪዎች የሚሰጥ ግሩም የሆነ ምክር እንኳን በተደጋጋሚ ጊዜ ችላ ይባላል ወይም ተቀባይነት ሳያገኝ ይቀራል።—ምሳሌ 29:19
በወንድሙ በአቤል ላይ ከፍተኛ ጥላቻ አድሮበት የነበረውን ቃየንን ይሖዋ በመከረው ጊዜ ይህ ሁኔታ ታይቷል። (ዘፍጥረት 4:3-5) በቃየን ላይ ሊከተል የሚችለውን አደጋ በማወቅ አምላክ እንዲህ አለው:- “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት።”—ዘፍጥረት 4:6, 7
ቃየን በወንድሙ ላይ ቂም ይዞ ከቀጠለ አድብቶ እንደሚያጠቃ እንስሳ ኃጢአት በድንገት ሊይዘው እንደሚችል ይሖዋ ነግሮት ነበር። (ከያዕቆብ 1:14, 15 ጋር አወዳድር።) ቃየን የጥፋት ጎዳና ከመከተል ይልቅ አመለካከቱን አስተካክሎ ‘መልካም ለማድረግ’ የሚያስችለው በቂ ጊዜ ነበረው። የሚያሳዝነው ግን ቃየን የተሰጠውን ምክር አልተቀበለም። ይሖዋ የሰጠውን ምክር አልቀበልም ማለቱ ከፍተኛ ኪሣራ አስከትሎበታል።
አንዳንድ ሰዎች ምንም ዓይነት ምክር ሲሰጣቸው ቅር በመሰኘት ምክሩን አንቀበልም ይላሉ። (ምሳሌ 1:22-30) ምክሩ ተቀባይነት ያጣው በምክር ሰጪው ስህተት ምክንያት ሊሆን ይችላልን? (ኢዮብ 38:2) ምክር የምትሰጠው አንተ ከሆንክ ሌሎች ምክሩን ለመቀበል እስኪቸገሩ ድረስ ከባድ ታደርገዋለህ? ሰብዓዊ አለፍጽምና ጉዳት ላይ ሊጥል ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቃቄ በመከተል ይህ ሁኔታ ሊከሰት የሚችልባቸውን አጋጣሚዎች መቀነስ ትችላለህ። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት።
“በየውሃት መንፈስ አቅኑት”
“ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።” (ገላትያ 6:1) ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ ግልጽ አድርጎ እንዳስቀመጠው ‘መንፈሳውያን የሆኑት’ ‘በማናቸውም በደል የሚገኝን’ አንድን ክርስቲያን ለማቅናት ሙከራ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ምክር ለመስጠት ሲጣደፉ የሚታዩት ምክር በመስጠት ረገድ ብዙም ብቃት የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ብቃቱ ሳይኖርህ ምክር ለመስጠት አትቸኩል። (ምሳሌ 10:19፤ ያዕቆብ 1:19፤ 3:1) ይህን የማድረግ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች ናቸው። እርግጥ ነው አንድ ወንድም ወደ አንድ ዓይነት አደጋ እያመራ እንዳለ የተመለከተ ማንኛውም የጎለመሰ ክርስቲያን ማስጠንቀቂያ መስጠት ይኖርበታል።
ምክር ወይም ተግሣጽ የምትሰጥ ከሆነ በሰብዓዊ አመለካከትና ፍልስፍና ላይ ሳይሆን በአምላካዊ ጥበብ ላይ ተመሥርተህ መሆን ይኖርበታል። (ቆላስይስ 2:8) በምታዘጋጀው ምግብ ውስጥ የምትጨምራቸው ነገሮች ሁሉ ለጤና የሚስማሙና ምንም ጉዳት የማያስከትሉ መሆናቸውን በጥንቃቄ እንደምትመረምር ባለሙያ ሴት ለመሆን ጥረት አድርግ። የምትሰጠው ምክር በግል አመለካከት ላይ ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተ መሆኑን አረጋግጥ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በዚህ መንገድ የምትሰጠው ምክር በማንም ላይ ጉዳት እንደማያስከትል እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።
ምክር የሚሰጥበት ዋነኛ ዓላማ ስህተት የፈጸመውን ግለሰብ ‘ለማቅናት’ እንጂ ሳይወድ በግድ ለውጥ እንዲያደርግ ለማስገደድ አይደለም። ‘ማቅናት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ቃል ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ሲባል የተናጋን አጥንት መልሶ ወደ ቦታው መመለስን ከሚያመለክት አነጋገር ጋር የሚዛመድ ነው። የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ደብልዩ ኢ ቫይን እንደሚሉት ከሆነ ይህ ቃል “ድርጊቱ በሚከናወንበት ጊዜ ምን ያህል ትዕግሥትና መንፈሰ ጠንካራነት እንደሚያስፈልግ” ያመለክታል። በሽተኛን አለአግባብ ላለማሳመም ምን ያህል ጥንቃቄና ብልሃት እንደሚጠይቅ አስብ። በተመሳሳይም አንድ መካሪ የሚመክረውን ግለሰብ እንዳይያስከፋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። አንድ ሰው ምክር ለማግኘት በሚጠይቅበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር እንዲህ ማድረጉ ቀላል አይደለም። ምክር የምትሰጠው ተጠይቀህ ካልሆነ ደግሞ ይበልጥ ከፍተኛ ችሎታና ብልሃት ይጠይቅብሃል።
እርግጥ ነው አንድን ሰው ከአንተ እንዲርቅ የምታደርገው ከሆነ ‘ልታቃናው’ አትችልም። ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት ለመከላከል “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን” የማሳየትን አስፈላጊነት ሁልጊዜ አስታውስ። (ቆላስይስ 3:12) አንድ ሐኪም ትዕግሥት የለሽና የሚያመናጭቅ ከሆነ በሽተኛው ምክሩን ችላ ሊልና ሕክምና በሚፈልግበት ጊዜ ዳግመኛ ወደ እሱ ላይሄድ ይችላል።
ይህ ሲባል ግን ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ፈጽሞ ጥብቅ መሆን አያስፈልግም ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በእስያ አውራጃ ለነበሩት ጉባኤዎች ምክር በሰጠበት ጊዜ ጥብቅ ነበር። (ራእይ 1:4፤ 3:1-22) ሰምተው በተግባር ላይ ሊያውሏቸው የሚገቡ አንዳንድ ምክሮችን ፈርጠም ባለ ሁኔታ ነግሯቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ ያሳየው ጥብቅነት የሰማዩ አባቱን የፍቅር መንፈስ በሚያንጸባርቁት እንደ ርኅራኄና ደግነት ባሉት ባሕርያት ሁልጊዜ የሚለዝብ ነበር።—ምሳሌ 23:1-6፤ ዮሐንስ 10:7-15
በጸጋ የሚሰጥ ምክር
“ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን።” (ቆላስይስ 4:6) ጨው የአንድን ምግብ ጣዕም በመጨመር ይበልጥ ጣፋጭ ያደርገዋል። የምትሰጠውም ምክር ጣዕም ያለው እንዲሆን “በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ” መቅረብ ይኖርበታል። ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ቅመማ ቅመሞች የተጨመሩበት ምግብም እንኳ ከአዘገጃጀት ጉድለት ሊበላሽ ወይም አቀራረቡ የማይማርክ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ የምግብ ፍላጎትን ይዘጋል። እንዲያውም አንድ ጉርሻ እንኳ ለመጉረስ ሊከብድ ይችላል።
ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ትክክለኛ ቃላትን መምረጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 25:11) ምናልባት ይህን የተናገረው ከወርቅ ተቀርጾ የተሠራ ፖም የተቀመጠበትን ውብ የብር ሳህን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። ይህ ለዓይን ምንኛ ማራኪ ነው! በስጦታ መልክ ቢሰጥህ እንዴት ባለ አድናቆት ትቀበል ነበር! በተመሳሳይም በጥንቃቄ የተመረጡና በጸጋ የተሞሉ ቃላት ልትረዳው የምትሞክረውን ግለሰብ በጥሩ ሁኔታ ሊማርኩ ይችላሉ።—መክብብ 12:9, 10
በተቃራኒው ደግሞ “ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች።” (ምሳሌ 15:1) በጥንቃቄ ያልተመረጡ ቃላት ምስጋና ከማስገኘት ይልቅ ጉዳትና ብስጭትን ያስከትላሉ። በጥንቃቄ ያልተመረጡ ቃላት ብቻ ሳይሆኑ የተሳሳተ የድምፅ ቃናም ቢሆን አንድ ግለሰብ ጠቃሚ የተባለውን ምክር እንኳ እንዳይቀበል ሊያደናቅፈው ይችላል። ብልሃትና ርኅራኄ በጎደለው መንገድ ምክር መስጠት አንድን ሰው በጦር መሣሪያ የማጥቃትን ያክል ጎጂ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 12:18 “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው” በማለት ይናገራል። አሳቢነት በጎደለው መንገድ በመናገር አንድ ሰው የሚሰጠውን ምክር መስማት እንዲቸገር ለምን እናደርጋለን?—ምሳሌ 12:15
ሰሎሞን እንደተናገረው የምክር ቃል ‘በተገቢው ጊዜ መነገር’ ይኖርበታል። ምክር የታለመለትን ዓላማ እንዲያከናውን ከተፈለገ ምክር የሚሰጥበትን ጊዜ በጥንቃቄ መምረጡ በጣም አስፈላጊ ነው! የመብላት ፍላጎት ለሌለው ሰው ምግብ ማቅረብ ምንም ጥቅም እንደ ሌለው የታወቀ ነው። ምናልባት በቅርቡ ጥግብ ብሎ በልቶ አሊያም አሞት ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው መብላት ሳይፈልግ አስገድዶ እንዲመገብ ማድረግ ጥበብ አይደለም፤ ተቀባይነትም የለውም።
በትሕትና ምክር መስጠት
“ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ . . . ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።” (ፊልጵስዩስ 2:2-4) ጥሩ መካሪ ከሆንክ ለመምከር የምትነሳሳው ለሌሎች ደህንነት ካለህ አሳቢነት የተነሳ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ከአንተ እንደሚሻሉ በመቁጠር መንፈሳዊ ወንድሞችህንና እህቶችህን “ትሕትና” በማሳየት ትይዛቸዋለህ። ይህ ምን ማለት ነው?
ትሕትና ከሌሎች የተሻልኩ ነኝ ከሚል ዝንባሌ ወይም አነጋገር ይጠብቅሃል። ማናችንም ብንሆን ከመሰል የእምነት ባልደረቦቻችን የተሻልን እንደሆንን እንዲሰማን የሚያደርግ ምንም ነገር የለም። ሁላችንም በተደጋጋሚ ስህተቶችን እንሠራለን። ልብን ማንበብ ስለማትችል ምክር የምትለግሰው ሰው የውስጥ ዝንባሌ እንዲህ ነው ብለህ ከመፍረድ መቆጠብህ በጣም አስፈላጊ ነው። ምንም ዓይነት መጥፎ የሆነ ውስጣዊ ዝንባሌ የለው ይሆናል፤ ወይም ደግሞ የተሳሳተ ዝንባሌ እንደነበረው ወይም መጥፎ ድርጊት እንደፈጸመ ላያውቅ ይችላል። ምንም እንኳ አምላክ ያወጣቸውን ብቃቶች የተላለፈ መሆኑን የሚያውቅ ቢሆንም ምክሩ ለመንፈሳዊ ደህንነቱ ከልብ በማሰብ በትሕትና የተሰጠው ከሆነ ምክሩን ለመቀበል ይበልጥ ቀላል እንደሚሆንለት ምንም ጥርጥር የለውም።
አንድ ሰው ምግብ ቢጋብዝህና ፊቱን ኮሶ አስመስሎ ቢያስተናግድህ ምን ሊሰማህ እንደሚችል እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ! ደስ ብሎህ እንደማትመገብ የታወቀ ነው። በእርግጥም “የጎመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።” (ምሳሌ 15:17) በተመሳሳይም አንድ ምክር የሚሰጥ ግለሰብ የሚመክረውን ሰው እንደማይወደው በሚያሳይ ወይም በሚያንኳስስ ወይም በሚያሳፍር መንገድ ምክር ለመስጠት ቢሞክር ሌላው ቀርቶ በጣም የተዋጣ የሚባለው ምክሩ እንኳ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል። ይሁን እንጂ ፍቅር፣ እርስ በርስ መከባበርና መተማመን ምክርን ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ቀላል ያደርገዋል።—ቆላስይስ 3:14
ተቀባይነት ያገኘ ምክር
ነቢዩ ናታን ንጉሥ ዳዊትን በሚመክርበት ጊዜ ትሕትናን አሳይቷል። ናታን ለዳዊት ፍቅርና አክብሮት እንደነበረው በተናገረውና ባደረገው ነገር ግልጽ ሆኖ ታይቷል። ናታን ምናልባት ዳዊት ምክሩን ለመስማት አስቸጋሪ እንዳይሆንበት ሲል አንድ ምሳሌ በመናገር ጀመረ። (2 ሳሙኤል 12:1-4) ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ መንገድ የፈጸመው ድርጊት ፍትሐዊ ያልሆነና ከጽድቅ የራቀ ቢሆንም እንኳን ዳዊት ለፍትሕና ለጽድቅ የነበረውን ፍቅር ነቢዩ በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞበታል። (2 ሳሙኤል 11:2-27) ምሳሌው እንዲያስተላልፍ የተፈለገው ነጥብ በገባው ጊዜ ዳዊት “እግዚአብሔርን በድያለሁ” በማለት ስሜቱን ከልቡ ገለጸ። (2 ሳሙኤል 12:7-13) ይሖዋን ለመስማት አሻፈረኝ ካለው ከቃየን በተለየ መንገድ ዳዊት ራሱን ዝቅ አድርጎ የተሰጠውን እርማት ተቀብሏል።
ይሖዋ ናታንን የላከው የዳዊትን አለፍጽምናና ምናልባትም ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን የሚችልባቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ናታን ከፍተኛ ብልሃት በመጠቀምና ዳዊት በይሖዋ የተሾመ ንጉሥ ስለሆነ ከእርሱ የሚሻል መሆኑን በመገንዘብ ወደ እርሱ አመራ። አንተም ባለህ አንድ ዓይነት ኃላፊነት የተነሳ ምክር ትሰጥ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ትሕትና የሚጎድልህ ከሆነ የምትሰጠውን ምክር ለመቀበል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
ናታን በየዋህነት መንፈስ ዳዊትን አቅንቶታል። የነቢዩ ቃላት በጸጋ የተሞሉና በጥንቃቄ የተመረጡ በመሆናቸው ዳዊት ለራሱ ጥቅም በሚያስገኝለት መንገድ ጥሩ ምላሽ ሰጥቷል። ናታን የራሱን ጥቅም በመፈለግ አልተነሳሳም ወይም ከዳዊት የተሻለ ሥነ ምግባራዊ ወይም መንፈሳዊ አቋም አለኝ ብሎም አላሰበም። ትክክለኛ ቃላትን በተገቢው መንገድ በመናገር ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! አንተም ተመሳሳይ የሆነ መንፈስ የምታሳይ ከሆነ ሌሎች የምትሰጠውን ምክር የመቀበላቸው አጋጣሚ በጣም ሰፊ ይሆናል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምትሰጠው ምክር ልክ እንደ አንድ ተመጣጣኝ ምግብ ጥሩ መሆን ይኖርበታል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምትሰጠው ምክር በብር ፃሕል ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ያክል ማራኪ ነውን?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነቢዩ ናታን ዳዊት ለፍትሕና ለጽድቅ የነበረውን ፍቅር በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞበታል