የሚጤሰውን ክር ታጠፋለህን?
ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሁሉም ዓይነት ሰዎች አውጆአል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የተጨቆኑና ተስፋ የቆረጡ ነበሩ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚያበረታታ መልእክት ነገራቸው። በመከራ ላይ ላሉ ሰዎች ርኅራኄ ነበረው።
የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ በማተኮር የኢየሱስን ርኅራኄ አጉልቷል። ማቴዎስ በክርስቶስ ላይ የተፈጸሙትን ቃላት ጠቅሶ ሲጽፍ “ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፣ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ [“የኩራዝ” አዓት] ክርም አያጠፋም” ብሏል። (ማቴዎስ 12:20፤ ኢሳይያስ 42:3) እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው? ይህ ትንቢት በኢየሱስ ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?
ትንቢቱን መመርመር
አብዛኛውን ጊዜ ሸምበቆ የሚበቅለው በረግረግ ቦታ ሲሆን ጥንካሬ የሌለውና በቀላሉ የሚታጠፍ ተክል ነው። “የተቀጠቀጠ ሸምበቆ” ደግሞ ይበልጥ ደካማ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ ይህ ሐረግ ኢየሱስ በሰንበት እንደፈወሰው እጁ የሰለለችበት ሰው ያሉትን የተጨቆኑና መከራ የደረሰባቸውን ሰዎች የሚያመለክት ይመስላል። (ማቴዎስ 12:10–14) ይሁን እንጂ በትንቢቱ ላይ ስለ ተጠቀሰው የኩራዝ ክር ምን ለማለት ይቻላል?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ቤት ውስጥ ይጠቀሙበት የነበረው ኩራዝ ከሸክላ የተሠራ ጆሮ ያለው አነስተኛ ዕቃ ነበር። ብዙውን ጊዜ ኩራዙ በወይራ ዘይት ይሞላል። ክሩ ዘይቱን መጥጦ ወደላይ ስለሚስበው መብራቱ ብርሃን መስጠቱን ይቀጥላል። እርግጥ ‘የሚጤስ የኩራዝ ክር’ ሊጠፋ የተቃረበ ነገር ነው።
ኢየሱስ በምሳሌያዊ አባባል እንደ ተቀጠቀጠ ሸምበቆ ለሆኑት የተዋረዱና የተንገላቱ ሰዎች የሚያጽናና መልእክቱን አውጅዋል። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች የመኖር ተስፋቸው ሊጨልም ጭል ጭል እያለ ስለ ነበር እንደሚጤስ የኩራዝ ክር ሆነው ነበር ለማለት ይቻላል። በእርግጥም የተጨነቁና ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ነበሩ። ሆኖም ኢየሱስ ምሳሌያዊውን የተቀጠቀጠ ሸምበቆ አልሰበረም ወይም ደግሞ በምሳሌያዊ አነጋገር ይጤስ የነበረውን የኩራዝ ክር አላጠፋም። ፍቅር፣ ደግነትና ርኅራኄ የተሞላባቸው ቃሎቹ በመከራ ላይ የሚገኙት ሰዎች የበለጠ ተስፋ እንዲቆርጡና እንዲጨነቁ አላደረጉም። ከዚህ ይልቅ የሰጣቸው ሐሳቦችና ለእነሱ የነበረው አያያዝ ሕይወታቸውን የሚያበለጽግላቸው ነበር።—ማቴዎስ 11:28–30
ዛሬም ብዙዎች ተስፋ አስቆራጭ ችግሮች ስለሚያጋጥሟቸው ርኅራኄና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ሌላው ቀርቶ የይሖዋ አገልጋዮችን እንኳ ምን ጊዜም ችግር አይበግራቸውም ለማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ አንዳንዶች ልክ እንደሚጤስ የኩራዝ ክር ይሆናሉ። ስለዚህ ክርስቲያኖች በምሳሌያዊ አነጋገር እሳቱን በማራገብ ማለትም እርስ በርሳቸው በመበረታታት ሌሎችን የሚያበረታቱ መሆን ይኖርባቸዋል።—ሉቃስ 22:32፤ ሥራ 11:23
ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን ሌሎችን ለማነጽ እንፈልጋለን። መንፈሳዊ እርዳታ የሚያስፈልገውን ማንኛውም ሰው ሆን ብለን ለማዳከም አንጥርም። ሌሎችን በማበረታታት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል እንደምንፈልግ አያጠራጥርም። (ዕብራውያን 12:1–3፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) ማበረታቻ ለማግኘት ወደ እኛ የሚመጡ ሰዎችን ሳናውቀው ልንጎዳቸው መቻላችን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በቁም ነገር እንድናስብበት በቂ ምክንያት ይሆነናል። በእርግጥም ‘የሚጤሰውን የኩራዝ ክር’ ለማጥፋት አንፈልግም። በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
የትችት ውጤቶች
አንድ ክርስቲያን ‘የተሳሳተ እርምጃ ቢወስድ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሰዎች እንደዚህ ያለውን ሰው በየዋህነት መንፈስ ለማስተካከል መጣር’ ይኖርባቸዋል። (ገላትያ 6:1 አዓት) ሆኖም በሌሎች ላይ ያሉትን ጉድለቶች እየለቃቀሙ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እነሱን ማረም ተገቢ ነውን? ወይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የሚያደርጓቸው ጥረቶች በቂ እንዳልሆኑ በመጥቀስ፣ ምናልባትም የጥፋተኝነት ስሜት እንዲያድርባቸው በማድረግ የተሻለ ነገር እንዲያከናውኑ ለመገፋፋት መሞከር ይገባልን? ኢየሱስ እንደዚህ እንዳደረገ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። ምንም እንኳ ዓላማችን ሌሎች ሰዎች እንዲያሻሽሉ ለመርዳት ቢሆንም ደግነት የጎደለው ነቀፋ የተሰነዘረባቸው ሰዎች ከመበረታታት ይልቅ ሊዳከሙ ይችላሉ። ገንቢ ትችትም እንኳ ከመጠን በላይ ሲሆን ፈጽሞ ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። አንድ ትጉ ክርስቲያን የሚችለውን ሁሉ አድርጎ ጥረቱ ምንም ተቀባይነት ካላገኘ ተስፋ ሊቆርጥና ‘ምን አለፋኝ?’ ሊል ይችላል። እንዲያውም ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ ሊተወው ይችላል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መስጠት በጣም አስፈላጊ ቢሆንም የተሾሙ ሽማግሌዎች ወይም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ግለሰቦች ተለይተው የሚታወቁበት ነገር መሆን የለበትም። ክርስቲያን ስብሰባዎች የሚካሄዱበት ዋነኛ ምክንያት ምክር ለመስጠትና ለመቀበል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘወትር የምንሰበሰበው እርስ በርሳችን ለመተናነጽና ለመበረታታት ነው። ይህም ሁላችንም እርስ በርስ ባለን ቅርርብና ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት እንድንደሰት ያስችለናል። (ሮሜ 1:11, 12፤ ዕብራውያን 10:24, 25) በከባድ ጉድለትና በአለፍጽምና መካከል ያለውን ልዩነት ተመልክተን ማለፉ ጥበብና ፍቅር እንደ ሆነ ማስተዋላችን እንዴት ጥሩ ነው!—መክብብ 3:1, 7፤ ቆላስይስ 3:13
ሰዎች ከትችት ይልቅ ለማበረታቻ ወዲያውኑ ምላሽ ይሰጣሉ። እንዲያውም ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነቀፋ እንደ ተሰነዘረባቸው ሲሰማቸው ያንኑ የተተቹበትን ነገር ይበልጥ አጥብቀው ሊይዙት ይችላሉ። ይሁን እንጂ ትክክለኛ ምስጋና ከተሰጣቸው ይበረታቱና ለማሻሻል ይገፋፋሉ። (ምሳሌ 12:18) እንደ ኢየሱስ የምናበረታታ እንሁን። ‘የሚጤሰውን ክር ፈጽሞ አናጥፋ።’
አንዱን ከሌላው ጋር ስለ ማወዳደር ምን ለማለት ይቻላል?
የሌሎች ክርስቲያኖችን ግሩም ተሞክሮዎች መስማት በጣም የሚያበረታታ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ራሱ ደቀ መዛሙርቱ በመንግሥቱ ስብከት ሥራቸው እንደ ተሳካላቸው ሲሰማ በጣም ተደስቷል። (ሉቃስ 10:17–21) በተመሳሳይም በእምነት ውስጥ ስላሉ ሌሎች ሰዎች መልካም ውጤቶች፣ ጥሩ ምሳሌነት ወይም ንጹሕ አቋም ስንሰማ እንበረታታለን፤ በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ጎዳናችን ለመቀጠል የበለጠ የቁርጠኝነት ስሜት ያድርብናል።
ሆኖም ተሞክሮው የቀረበው ‘እንደነዚህ ክርስቲያኖች ጥሩ አቋም የላችሁም፤ ከዚህ የተሻሉ ሰዎች መሆን ነበረባችሁ’ በሚል መንፈስ ቢሆንስ? አድማጩ ከፍተኛ የሆነ ማሻሻያ ለማድረግ የሚነሳሳ ይመስላችኋልን? በተለይ ሰውዬውን በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሌላ ሰው ጋር ካወዳደራችሁት ወይም ጉዳዩ ተደጋግሞ ከተጠቀሰ ተስፋ ቆርጦ ሊተወው ይችላል። ይህ በአብዛኛው አንድ ወላጅ ልጁን ‘እንደ ወንድምህ ለምን አትሆንም?’ በማለት ከመጠየቁ ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ ዓይነቱ አስተያየት ጥላቻ ሊያሳድርና ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል እንጂ ልጁ የተሻለ ባሕርይ እንዲኖረው አያደርግም። ማወዳደር በጎለመሱ ሰዎችም ላይ ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። እንዲያውም ከእነሱ ጋር ለተወዳደሩት ሰዎች አንድ ዓይነት ጥላቻ ያሳድርባቸዋል።
አምላክን በማገልገል ረገድ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት መጠን ያለው ሥራ እንዲያከናውን መጠበቅ አንችልም። ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ አንድ ጌታ ለባሪያዎቹ ለአንደኛው አንድ፣ ለሁለተኛው ሁለት ለሌላው ደግሞ አምስት የብር መክሊቶችን እንደሰጣቸው ይናገራል። መክሊቶቹ ለእያንዳንዳቸው የተሰጣቸው ‘እንደየዓቅማቸው’ ነበር። ሥራቸው የተለያዩ ውጤቶችን ቢያስገኝም በጥበብ የነገዱትና ሌሎች መክሊቶችን ያተረፉት ሁለት ባሪያዎች በታማኝነታቸው ምክንያት ተመስግነዋል።—ማቴዎስ 25:14–30
ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል” ብሎ መጻፉ ተገቢ ነው። (ገላትያ 6:4) ስለዚህ ሌሎችን በተገቢው መንገድ ለማበረታታት አፍራሽ በሆነ መልኩ ከማወዳደር መቆጠብ ይኖርብናል።
ሌሎችን ማነጽ የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች
ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን ለማነጽና ‘የሚጤሰውን ክር ከማጥፋት’ ለመቆጠብ ምን ልናደርግ እንችላለን? ማበረታቻ ለመስጠት አንድ የተወሰነ ደንብ መከተል ያስፈልጋል ማለት አይቻልም። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ካዋልናቸው የምንናገራቸው ቃላት ሌሎችን የሚያንጹ መሆናቸው አይቀርም። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
ትሑቶች ሁኑ። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2:3 [የ1980 ትርጉም] ላይ “ወገን በመለየትና በራስ ወዳድነት ወይም “ያለ እኔ ማን አለ” በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ” በማለት አጥብቆ መክሯል። ከዚህ ይልቅ የምንናገረውና የምናደርገው ነገር ትሕትና የተሞላበት መሆን ይኖርበታል። ‘በትሕትና ሌሎች ሰዎች ከእኛ እንደሚሻሉ አድርገን መቁጠር’ ይኖርብናል። ጳውሎስ ስለ ራሳችን ምንም ማሰብ የለብንም አላለም። ሆኖም እያንዳንዱ ሰው ከእኛ በአንድ መንገድ እንደሚበልጥ መገንዘብ ይኖርብናል። እዚህ ላይ “እንደሚሻሉ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “የራሱን መብቶች ከመመልከት ይልቅ ሌላ ሰው ከእሱ የተሻለ የሆነባቸውን ተሰጥኦዎች የሚያጠና” ሰው የሚል ትርጉም አለው። (ኒው ቴስታመንት ወርድ ስተዲስ ፣ በጆሃን አልበርት ቤንጂል ጥራዝ 2 ገጽ 432) ይህን ካደረግንና ሌሎች ከእኛ እንደሚሻሉ ካሰብን ከእነሱ ጋር ባለን ግንኙነት ትሑቶች እንሆናለን።
አክብሮት አሳዩ። ከልብ የመነጩ ቃላትን በመናገር ታማኝ የሆኑ የእምነት ጓደኞቻቸንን እንደምንተማመንባቸውና አምላክን ለማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ግለሰቦች አድርገን እንደምንመለከታቸው እንዲገነዘቡ ልናደርግ እንችላለን። ሆኖም መንፈሳዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል እንበል። እንዲህ ከሆነ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ እርዳታ እናድርግላቸው። ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ” በማለት ሁኔታውን አስቀምጦታል።—ሮሜ 12:10 የ1980 ትርጉም
ጥሩ አዳማጮች ሁኑ። አዎን፣ ተስፋ አስቆራጭ ችግሮች ያጋጠሟቸውን ሰዎች ለማበረታታት ብዙ መናገር ሳይሆን ጥሩ አዳማጮች መሆን ያስፈልገናል። በችኮላ ብስለት ያልታከለበት አስተያየት ከመሰንዘር ይልቅ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ለመስጠት የሚያስፈልገውን ጊዜ እንውሰድ። የችግሩን መፍትሔ የማናውቅ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምር ማድረጋችን ሌሎችን በሚያንጽና እና በሚያበረታታ መንገድ እንድንናገር ያስችለናል።
አፍቃሪዎች ሁኑ። ልናበረታታቸው ለምንፈልጋቸው ሰዎች ፍቅር ሊኖረን ይገባል። ለመሰል የይሖዋ አገልጋዮች የምናሳየው ፍቅር ለእነሱ የሚጠቅማቸውን ነገር ከማድረግ የበለጠ እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል። ፍቅራችን ሞቅ ያለ ስሜት የታከለበት መሆን ይኖርበታል። ለሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ዓይነት ፍቅር ካለን የምንናገራቸው ቃላት ለእነሱ እውነተኛ ማበረታቻ ይሆንላቸዋል። አንድ ነገር እንዲያሻሽሉ ሐሳብ ስናቀርብላቸው እንኳ ዝንባሌያችን አመለካከታችንን ለመግለጽ ሳይሆን ፍቅራዊ እርዳታ ለመስጠት ከሆነ የምንነግራቸውን ነገር ሳይረዱ ሊቀሩ ወይም ጉዳዩ ሊጎዳቸው አይችልም። ጳውሎስ ግሩም በሆነ መንገድ እንደ ገለጸው “ፍቅር ያንጻል።”—1 ቆሮንቶስ 8:1፤ ፊልጵስዩስ 2:4፤ 1 ጴጥሮስ 1:22
ዘወትር የምታንጹ ሁኑ
በዚህ በጣም አስቸጋሪ በሆነ “የመጨረሻ ቀን” የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) አንዳንድ ጊዜ እስከ ጽናታቸው መጨረሻ ድረስ መከራ የሚደርስባቸው መሆኑ ምንም አያስደንቅም። የይሖዋ አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን መሰል አምላኪዎች ሊጠፋ የተቃረበ የሚጤስ የኩራዝ ክር እንደሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ነገሮችን ለመናገር ወይም ለማድረግ እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው።
ስለዚህ እርስ በርስ መበረታታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ተስፋ የቆረጡ መሰል አምላኪዎችን ለማነጽ ትሑቶችና ሰው አክባሪዎች ለመሆን ማናቸውንም ጥረት እናድርግ። አንድ ነገር ሲያማክሩን በጥንቃቄ በማዳመጥና ዘወትር የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ እንርዳቸው። ከሁሉም በላይ እርስ በርስ ለመበረታታት ስለሚያስችለን የይሖዋ የመንፈስ የመጀመሪያው ፍሬ የሆነውን ፍቅርን እናሳይ። የምንናገረው ወይም የምናደርገው ነገር በምንም ዓይነት መንገድ ‘የሚጤሰውን ክር የሚያጠፋ’ አይሁን።