ምንም እንኳ ከአፈር የተሠራችሁ ብትሆኑም በቆራጥነት ወደፊት ግፉ!
“ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ።”—መዝሙር 103:14
1. መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ከአፈር የተሠራ ነው ይላል። ይህ ከሳይንስ አንፃር ሲታይ ትክክል ነውን? አብራራ።
አካላችን ከአፈር የተሠራ ነው። “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት። ሰውም [ሕያው ነፍስ አዓት] ሆነ።” (ዘፍጥረት 2:7) ስለ ሰው አፈጣጠር የቀረበው ይህ ያልተወሳሰበ መግለጫ ከሳይንሳዊ እውነት ጋር የሚስማማ ነው። የሰው አካል የተሠራባቸው ከ90 የሚበልጡ ንጥረ ነገሮች “ከምድር አፈር” የተገኙ ናቸው። አንድ ኬሚስት በአንድ ወቅት የአንድ ጎልማሳ ሰው አካል 65 ከመቶ ኦክስጅን፣ 18 ከመቶ ካርቦን፣ 10 ከመቶ ሃይድሮጅን፣ 3 ከመቶ ናይትሮጅን፣ 1.5 ከመቶ ካልሲየም እንዲሁም 1 ከመቶ ፎስፈረስ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች የተሠራ ነው ብለው ነበር። እነዚህ ግምታዊ አኃዞች ሙሉ በሙሉ ትክክል ቢሆኑም ባይሆኑም ‘እኛ አፈር መሆናችን’ የማይታበል ሐቅ ነው።
2. አምላክ ሰዎችን የፈጠረበት መንገድ በውስጥህ የሚያሳድረው ስሜት ምንድን ነው? ለምንስ?
2 ከአፈር እንዲህ ያለ ውስብስብ ፍጡር ከይሖዋ በቀር ሌላ ማን ሊሠራ ይችላል? የአምላክ ሥራዎች ፍጹምና ምንም እንከን የሌላቸው ስለሆኑ አምላክ ሰውን በዚህ መንገድ ለመሥራት መምረጡ በእሱ ላይ ለማማረር የሚያበቃ ምክንያት አይሆንም። እንዲያውም ታላቁ ፈጣሪ በሚያስገርምና በሚያስደንቅ መንገድ ሰውን ከምድር አፈር ለማበጀት በመቻሉ ይሖዋ ላለው ከፍተኛ ኃይል፣ ችሎታና ተግባራዊ ጥበብ ያለንን አድናቆት ይጨምርልናል።—ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 139:14
የሁኔታዎች መለወጥ
3, 4. (ሀ) አምላክ ሰውን ከአፈር ሲፈጥር ምን ዓላማ አልነበረውም? (ለ) ዳዊት በመዝሙር 103:14 ላይ የጠቀሰው ምን ነበር? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብስ ወደዚህ መደምደሚያ እንድንደርስ የሚረዳን እንዴት ነው?
3 ከአፈር የተሠሩ ፍጥረታት አቅማቸው የተገደበ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ እነዚህ የአቅም ገደቦች ከባድ ሸክም ወይም ከመጠን በላይ ጥብቅ እንዲሆኑ ዓላማው አልነበረም። እነዚህ የአቅም ገደቦች ተስፋ የሚያስቆርጡ ወይም የሚያሳዝኑ እንዲሆኑ የአምላክ አሳብ አልነበረም። ሆኖም በመዝሙር 103:14 ላይ ባሉት የዳዊት ቃላት ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያመለክተው ሰዎች ያሉባቸው የአቅም ገደቦች ተስፋ መቁረጥና ሐዘን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው። ለምን? ምክንያቱም አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ባመፁ ጊዜ ከእነሱ በኋላ በሚመጡት ዘሮቻቸው ላይ አንድ የተለወጠ ሁኔታ አስከትለዋል። ከዚያ በኋላ ከአፈር የመሠራቱ ጉዳይ አዲስ ትርጉም ያዘ።a
4 ስለዚህ ዳዊት ከአፈር የተሠሩ ፍጹም የሆኑ ሰዎችም እንኳን ቢሆኑ ስለሚኖሯቸው ተፈጥሮአዊ የአቅም ገደቦች መናገሩ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የተወረሰው አለፍጽምና ስላስከተለው የሰዎች ድክመት መናገሩ ነበር። እንዲህ ባይሆን ኖሮ ይሖዋን በተመለከተ እንደሚከተለው አይልም ነበር፦ “ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፣ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፣ ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፣ እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።” (መዝሙር 103:2–4, 10) ምንም እንኳን ከአፈር የተሠሩ ቢሆኑም ፍጹም የሆኑ ሰዎች ስህተት ወይም ኃጢአት ሳይሠሩ በታማኝነት ቢቀጥሉ ኖሮ ይቅር መባል አያስፈልጋቸውም ነበር፤ ወይም ፈውስ የሚያስፈልጋቸው ሕመሞች አይኖሯቸውም ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ በትንሣኤ አማካኝነት ብቻ ካልሆነ በቀር በሌላ መንገድ ሊወጡ ወደማይችሉበት የሞት ጉድጓድ አይወርዱም ነበር።
5. የዳዊትን አነጋገር መረዳት አስቸጋሪ የማይሆንብን ለምንድን ነው?
5 ፍጹማን ካለመሆናችን የተነሣ ዳዊት የተናገራቸው ነገሮች በሁላችንም ላይ ደርሰዋል። ከአለፍጽምና የተነሣ ያሉብንን የአቅም ገደቦች ምንጊዜም እናውቃቸዋለን። አንዳንድ ጊዜ ያሉብን የአቅም ገደቦች ከይሖዋ ወይም ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት የማበላሸት አዝማሚያ ሲያሳዩ እናዝናለን። አለፍጽምናችንና የሰይጣን ዓለም ግፊቶች አልፎ አልፎ ተስፋ እንድንቆርጥ ሲያደርጉን ይከፋናል። የሰይጣን አገዛዝ ማክተሚያ በፍጥነት እየቀረበ ስለሆነ የሰይጣን ዓለም በአጠቃላይ በሰው ልጆች ላይ በተለይ ደግሞ በክርስቲያኖች ላይ ከምን ጊዜውም የበለጠ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።—ራእይ 12:12
6. አንዳንድ ክርስቲያኖች የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሰማቸው የሚችለው ለምንድን ነው? ሰይጣንስ በዚህ ዓይነቱ ስሜት ሊጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?
6 ክርስቲያን ሆኖ መኖር ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ ይሰማሃልን? አንዳንድ ክርስቲያኖች በእውነት ውስጥ ይበልጥ ረጅም ጊዜ በቆዩ መጠን ከፍጽምና ይበልጥ እየራቁ የሚሄዱ ሆኖ እንደሚሰማቸው ሲናገሩ ይሰማል። ይሁን እንጂ እንደዚህ የሚሰማቸው የራሳቸው አለፍጽምናና ፍጹም ከሆኑት የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር እነሱ እንደሚፈልጉት ያህል ተስማምተው ለመሄድ አለመቻላቸው ይበልጥ ስለሚታወቃቸው ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች በእውቀትና ስለ ይሖዋ የጽድቅ ብቃቶች ባላቸው ግንዛቤ ማደጋቸውን ሲቀጥሉ ይህ ስሜት ይመጣል። በሰይጣን እጅ ላይ ለመውደቅ እስክንመቻች ድረስ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ተስፋ እንዲያስቆርጠን በፍጹም መፍቀድ የለብንም። ሰይጣን የይሖዋ አገልጋዮች ንጹሑን አምልኮ እንዲተዉ ለማድረግ ለብዙ መቶ ዘመናት ተስፋ መቁረጥን መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም በተደጋጋሚ ሲሞክር ቆይቷል። ይሁን እንጂ ለአምላክ ያላቸው እውነተኛ ፍቅርና ለዲያብሎስ ያላቸው ‘ፍጹም የሆነ ጥላቻ’ አብዛኞቹን እጁ ላይ ከመውደቅ ጠብቋቸዋል።—መዝሙር 139:21, 22፤ ምሳሌ 27:11
7. አንዳንድ ጊዜ እንደ ኢዮብ ልንሆን የምንችለው በምን ረገድ ነው?
7 ያም ሆኖ ግን የይሖዋ አገልጋዮች አልፎ አልፎ ተስፋ መቁረጥ ሊሰማቸው ይችላል። ለዚህም አንዱ ምክንያት በምናከናውናቸው ሥራዎች አለመርካት ጭምር ሊሆን ይችላል። የጤና እክል ወይም ከቤተሰብ አባላት፣ ከጓደኞች ወይም ከሥራ ባልደረቦች ጋር ያለ ግንኙነት መሻከሩ ተስፋ መቁረጥን ሊያስከትል ይችላል። ታማኙ ኢዮብ በጣም ተስፋ ቆርጦ ስለነበረ “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!” ሲል አምላክን ተማጽኗል። ኢዮብ “ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው” ሆኖ እያለ የደረሱበት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጊዜያዊ ተስፋ መቁረጥ እንዲሰማው ካደረጉ ይህ ሁኔታ ዛሬም በእኛ ላይ መድረሱ ምንም አያስደንቅም።—ኢዮብ 1:8, 13–19፤ 2:7–9, 11–13፤ 14:13
8. አልፎ አልፎ የሚመጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ጥሩ ምልክት ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
8 ይሖዋ ልብን እንደሚያይና በጥሩ ዓላማ የሚደረጉትን ነገሮች እንደማይንቅ ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው! ይሖዋ እሱን ለማስደሰት ከልባቸው የሚጥሩትን በፍጹም አይተዋቸውም። እንዲያውም አልፎ አልፎ የሚከሰት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎታችንን በግዴለሽነት እንደማንመለከተው የሚያሳይ ጥሩ ምልክት ሊሆን ይችላል። እንግዲያው ከተስፋ መቁረጥ ጋር ምንም ትግል የማያደርግ ሰው እንደ ሌሎቹ መንፈሳዊ ድክመቱ ላይታወቀው ይችል ይሆናል። “ስለዚህ እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” የሚለውን ማሳሰቢያ አስታውሱ።— 1 ቆሮንቶስ 10:12፤ 1 ሳሙኤል 16:7፤ 1 ነገሥት 8:39፤ 1 ዜና መዋዕል 28:9
እነሱም ከአፈር የተሠሩ ነበሩ
9, 10. (ሀ) ክርስቲያኖች በእምነታቸው እነማንን መምሰል ይኖርባቸዋል? (ለ) ሙሴ ስለተሰጠው ሥራ እንዴት ተሰማው?
9 ዕብራውያን ምዕራፍ 11 ጠንካራ እምነት ያሳዩ ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን ይዘረዝራል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖችም ሆኑ አሁን በዘመናችን ያሉት ክርስቲያኖች ተመሳሳይ እምነት አሳይተዋል። ከእነሱ የሚገኘው ትምህርት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። (ከዕብራውያን 13:7 ጋር አወዳድር) ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች በእምነቱ ሊመስሉት የሚገባ ከሙሴ የተሻለ ሰው ማን ሊኖር ይችላል? በዘመኑ ኃያል የዓለም ገዢ በነበረው በግብፁ ፈርዖን ፊት ቀርቦ የፍርድ መልዕክት እንዲናገር ተሹሞ ነበር። ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ለሐሰት ሃይማኖቶችና የተቋቋመችውን የክርስቶስ መንግሥት ለሚቃወሙት ለሌሎች ድርጅቶች ተመሳሳይ የፍርድ መልዕክት እንዲያውጁ ታዘዋል።—ራእይ 16:1–15
10 በሙሴ ሁኔታ እንደታየው ይህን ተልእኮ ማከናወን ቀላል አይደለም። ሙሴ “ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” ሲል ጠይቋል። ለዚህ ሥራ ብቁ እንዳልሆነ ለምን እንደተሰማው ልንረዳለት እንችላለን። በተጨማሪም ሙሴ “እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም” በማለት ስለተናገረ ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያን ምን ይሉኝ ይሆን የሚለው ጥያቄ እንዳሳሰበው ገልጿል። ከዚያም ሙሴ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ለእስራኤላውያን እንዴት ሊያረጋግጥላቸው እንደሚችል ይሖዋ ገለጸለት። ያም ሆኖ ግን ሙሴ ሌላም ችግር ነበረው። “ጌታ ሆይ፣ እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም” አለ።—ዘጸአት 3:11፤ 4:1, 10
11. ቲኦክራሲያዊ ግዴታዎችን በተመለከተ እኛም እንደ ሙሴ ሊሰማን የሚችለው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ እምነት ብናሳይ ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
11 እኛም አልፎ አልፎ እንደ ሙሴ ሊሰማን ይችላል። ምንም እንኳን ቲኦክራሲያዊ ግዴታዎቻችንን ብናውቅም እንዴት ልናከናውናቸው እንደምንችል ግራ ሊገባን ይችላል። ‘ከፍተኛ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ ወይም የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ሰዎች ቀርቤ የማነጋግረው እንዲሁም የአምላክን መንገዶች የማስተምረው እኔ ማን ነኝ? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስሰጥ ወይም በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ስብሰባ ወቅት መድረክ ላይ ወጥቼ ክፍል በማቀርብበት ጊዜ መንፈሳዊ ወንድሞቼ እንዴት ይሰማቸው ይሆን? ብቁ አለመሆኔን አይመለከቱምን?’ ይሁን እንጂ ሙሴ እምነት ስለነበረው ይሖዋ ከእሱ ጋር ነበር፤ እንዲሁም የተሰጠውን ሥራ እንዲያከናውን ይሖዋ አስታጥቆታል። (ዘጸአት 3:12፤ 4:2–5, 11, 12) ሙሴን በእምነቱ ከመሰልነው ይሖዋ ከእኛ ጋር ይሆናል፤ እንዲሁም ለተሰጠን ሥራ ያስታጥቀናል።
12. ኃጢአትን ወይም ጉድለትን በተመለከተ ተስፋ ስንቆርጥ የዳዊት እምነት ሊያበረታታን የሚችለው እንዴት ነው?
12 በኃጢአቱ ወይም በጉድለቱ ምክንያት የሚበሳጭ ወይም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት የሚሰማው ማንኛውም ሰው “እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ” ሲል ከተናገረው ከዳዊት ጋር ሊስማማ ይችላል። በተጨማሪም ዳዊት “ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፣ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ” ሲል ይሖዋን ተማጽኗል። ሆኖም ተስፋ መቁረጥ ይሖዋን ለማገልገል ያለውን ምኞት እንዲሰርቅበት በፍጹም አልፈቀደም። “ከፊትህ አትጣለኝ፣ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።” ዳዊት “ከአፈር” የተሠራ እንደነበረ ግልጽ ነው፤ ይሁን እንጂ ዳዊት ይሖዋ “የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ” እንደማይንቅ በገባው ቃል ላይ እምነት ነበረው።—መዝሙር 38:1–9፤ 51:3, 9, 11, 17
13, 14. (ሀ) የሰዎች ተከታዮች መሆን የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) የጳውሎስና የጴጥሮስ ምሳሌ እነሱም እንኳን ከአፈር የተሠሩ እንደነበሩ የሚያሳየው እንዴት ነው?
13 ሆኖም ምንም እንኳ “በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት” ለመሮጥ እንድንበረታታ ‘እነዚህን እንደ ደመና የሚያክሉ በዙሪያችን ያሉ’ ምሥክሮች መመልከት ቢኖርብንም የእነሱ ተከታዮች ሁኑ እንዳልተባልን ልብ በሉ። ተከተሉ የተባልነው ፍጽምና የሌላቸውን ሰዎች፣ ሌላው ቀርቶ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ታማኝ ሐዋርያት እንኳን ሳይሆን “የእምነታችን ዋነኛ መገኛና የእምነታችን ፍጹም አድራጊ የሆነውን የኢየሱስን” ፈለግ ነው።—ዕብራውያን 12:1, 2 አዓት፤ 1 ጴጥሮስ 2:21
14 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ አምድ ይታዩ የነበሩት ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስ አልፎ አልፎ ይሰናከሉ ነበር። ጳውሎስ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። . . . እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 7:19, 24) ጴጥሮስም አንድ ጊዜ ከመጠን በላይ በራሱ በመተማመን “ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም” ሲል ለኢየሱስ ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ብሎ ባስጠነቀቀው ጊዜ ጴጥሮስ “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፣ ከቶ አልክድህም” ብሎ በትምክህት በመናገር ከመጠን በላይ በራሱ በመተማመን ጌታውን ተቃወመው። ይሁን እንጂ ኢየሱስን መካዱ አልቀረም፤ ምርር ብሎ እንዲያለቅስ ያደረገውን ስሕተት ፈጸመ። አዎን፣ ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ ከአፈር የተሠሩ ሰዎች ነበሩ።—ማቴዎስ 26:33–35
15. ምንም እንኳን ከአፈር የተሠራን ብንሆንም ወደፊት ለመግፋት ምን የሚያበረታታን ነገር አለ?
15 ይሁን እንጂ ሙሴ፣ ዳዊት፣ ጳውሎስ፣ ጴጥሮስና እንደ እነሱ ያሉ ሌሎች ሰዎች ምንም እንኳን ድክመቶች ቢኖሩባቸውም ድል አድርገዋል። ለምን? ምክንያቱም በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ነበራቸው፤ በእሱም ላይ ሙሉ በሙሉ ተማምነዋል። እንዲሁም ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ቢሰናከሉም ከይሖዋ ጋር የሙጢኝ ብለው ተጣብቀዋል። “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” እንዲሰጣቸው በእርሱ ላይ በትምክህት ተደግፈዋል። ይሖዋም መነሣት እንደማይችሉ ሆነው እንዲወድቁ አልፈቀደም። እኛም እምነት ማሳየታችንን ከቀጠልን የእኛን ጉዳይ በሚመለከት የሚሰጠው ፍርድ ‘እግዚአብሔር ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም’ ከሚሉት ቃላት ጋር የሚስማማ እንደሚሆን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ምንም እንኳን ከአፈር የተሠራን ብንሆንም በቆራጥነት ወደፊት እንድንገፋ ይህ ከፍተኛ ማበረታቻ ይሰጠናል።—2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት፤ ዕብራውያን 6:10
ከአፈር የተሠሩ መሆን ለእኛ በግላችን ምን ማለት ነው?
16, 17. መፍረድን በተመለከተ ይሖዋ በገላትያ 6:4 ላይ የተገለጸውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ የሚያውለው እንዴት ነው?
16 ወላጆችና አስተማሪዎች የቀሰሙት የሕይወት ተሞክሮ ልጆችን ወይም የክፍል ተማሪዎችን እርስ በርስ በማወዳደር ሳይሆን በእያንዳንዱ ልጅ ወይም ተማሪ ችሎታ መሠረት ሁኔታዎቹን ማመዛዘን ጥበብ መሆኑን አስተምሯቸዋል። ይህም ክርስቲያኖች እንዲከተሉት ከተነገራቸው ከሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ነው፦ “ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል።”—ገላትያ 6:4
17 ምንም እንኳን ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት የሚያደርገው በተደራጀ መልክ ቢሆንም ከዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በመስማማት በግለሰብ ደረጃ ፍርድ ይሰጣቸዋል። ሮሜ 14:12 “እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ይላል። ይሖዋ የአገልጋዮቹን የእያንዳንዳቸውን አፈጣጠር በሚገባ ያውቃል። ይሖዋ የአገልጋዮቹን አካላዊም ሆነ አእምሮአዊ አሠራር፣ ችሎታ፣ የወረሱትን ጠንካራም ሆነ ደካማ ጎን፣ ያሏቸውን አማራጮች፣ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ፍሬዎችን ለማፍራት በእነዚህ አማራጮች እስከምን ድረስ እንደተጠቀሙባቸው ያውቃል። ኢየሱስ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞችን በቤተ መቅደሱ መዝገብ ውስጥ ስለጣለች አንዲት መበለት የሰጠው አስተያየትና በመልካሙ መሬት ላይ ስለተዘራው ዘር የሰጠው ምሳሌ ያላግባብ ራሳቸውን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ጭንቀት ለሚሰማቸው ክርስቲያኖች የሚያበረታቱ ምሳሌዎች ናቸው።—ማርቆስ 4:20፤ 12:42–44
18. (ሀ) ከአፈር መሠራት ማለት ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ምን ማለት እንደሆነ አመዛዝነን ማወቅ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ከልብ ራስን መመርመር ተስፋ ሊያስቆርጠን የማይገባው ለምንድን ነው?
18 በሙሉ አቅማችን ለማገልገል እንድንችል በራሳችን የግል ሁኔታ ከአፈር መሠራት ምን ማለት እንደሆነ አመዛዝነን ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 10:4፤ 12:24፤ 18:9፤ ሮሜ 12:1) ለግል ጉድለቶቻችንና ድክመቶቻችን ንቁዎች ከሆንን ብቻ ነው የት ላይ ማሻሻል እንደሚያስፈልገንና እንዴት ማሻሻል እንደምንችል የምናውቀው። ራሳችንን በምንመረምርበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንድናሻሽል እኛን በመርዳት ረገድ ያለውን ኃይል በፍጹም አቅልለን አንመልከተው። አጽናፈ ዓለም የተፈጠረው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንዲሁም እየሞተ ባለው ዓለም ውስጥ ሰላማዊ የአዲስ ዓለም ኅብረተሰብ የተቋቋመው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ስለዚህ አምላክ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣቸው ለሚጠይቁ ሰዎች ይህ መንፈስ ፍጹም አቋም ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን ጥበብና ኃይል ለመስጠት የሚያስችል በቂ ኃይል አለው።—ሚክያስ 3:8፤ ሮሜ 15:13፤ ኤፌሶን 3:16
19. ከአፈር የተሠራን መሆናችን ለምን ነገር ሰበብ አይሆነንም?
19 ይሖዋ አፈር እንደሆንን የሚያስታውስ መሆኑን ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው! ይሁን እንጂ ይህንን ሐቅ ለስንፍና አልፎ ተርፎም ስህተት ለመሥራት ማሳበቢያ አድርገን መመልከት በፍጹም አይገባንም። በጭራሽ አይገባንም! ይሖዋ እኛ አፈር እንደሆንን ማሰቡ ይገባናል የማንለው ደግነቱ መግለጫ ነው። ይሁን እንጂ ‘ይገባናል የማንለውን የአምላካችንን ደግነት በሴሰኝነት እንደሚለውጡትና ብቸኛው ባለቤታችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚክዱት ለአምላክ አክብሮት የሌላቸው ሰዎች’ መሆን አንፈልግም። (ይሁዳ 4 አዓት) ከአፈር የተሠራን መሆናችን ለአምላክ አክብሮት የሌለን ለመሆን በፍጹም ሰበብ ሊሆነን አይገባም። አንድ ክርስቲያን “ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ” ከማሳዘን ለመራቅ ሰውነቱን በመጎሰምና እንደ ባሪያ አድርጎ በማስገዛት የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን ለማሸነፍ ይጥራል።—ኤፌሶን 4:30፤ 1 ቆሮንቶስ 9:27
20. (ሀ) ‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ የሆነው በምን ሁለት ዘርፎች ነው? (ለ) ብሩህ አመለካከት ለመያዝ ምክንያት የሚኖረን ለምንድን ነው?
20 አሁን በእነዚህ የሰይጣን ዓለም ሥርዓት ማክተሚያ በሆኑት ዓመታት ወቅት የመንግሥቱን ስብከት በተመለከተም ሆነ ይበልጥ የአምላክን መንፈስ ፍሬ ማፍራትን በተመለከተ ዳተኞች የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። በሁለቱም ረገድ ‘ብዙ የምንሠራው’ ሥራ አለን። ‘ድካማችን ከንቱ’ እንደማይሆን ስለምናውቅ በቆራጥነት ወደፊት ለመግፋት ጊዜው አሁን ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ይሖዋ ደግፎ ያቆመናል። ዳዊት “ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል። (መዝሙር 55:22) ምንም እንኳን ከአፈር የተሠራን ብንሆንም ፍጽምና የሌላቸው ሰብአዊ ፍጥረታት እንዲሠሩት በተሰጣቸው እጅግ ታላቅ በሆነ ሥራ ውስጥ በግላችን ድርሻ እንዲኖረን ይሖዋ እንደፈቀደልን ማወቅ እንዴት የሚያስደስት ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሄርደርስ ቢብልኮሜንታር የተባለው መጽሐፍ ቅዱስን ተንትኖ ለማስረዳት የተዘጋጀው መጽሐፍ መዝሙር 103:14ን አስመልክቶ አስተያየቱን ሲሰጥ እንደሚከተለው ይላል፦ “ሰዎችን ከምድር አፈር እንደሠራቸው በሚገባ ያውቃል፤ እንዲሁም የሕይወታቸውን ደካማ ጎኖችና አጭርነት ያውቃል። ይህ ሁኔታ ከመጀመሪያው ኃጢአት ጀምሮ ከባድ ሸክም ሆኖባቸዋል።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ ዘፍጥረት 2:7 እና መዝሙር 103:14 ሰዎች ከአፈር የተሠሩ መሆናቸውን በሚጠቅሱበት ጊዜ የሚለያዩት እንዴት ነው?
◻ ዕብራውያን ምዕራፍ 11 ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ማበረታቻ የሚያገኙበት ምንጭ የሚሆንላቸው ለምንድን ነው?
◻ በገላትያ 6:4 ላይ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ብናውል ጥበበኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?
◻ ዕብራውያን 6:10 እና 1 ቆሮንቶስ 15:58 ከተስፋ መቁረጥ ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች መሰል አምላኪዎችን በእምነታቸው ይመስሏቸዋል፤ ሆኖም የእምነታቸውን ፍጹም አድራጊ ኢየሱስን ይከተላሉ