የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
ለገላትያ፣ ለኤፌሶን፣ ለፊልጵስዩስና ለቈላስይስ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች የአይሁድን እምነት የሚያስፋፉ ሰዎች ባሳደሩባቸው ተጽዕኖ ምክንያት ከንጹሕ አምልኮ ዘወር እያሉ መሆናቸውን ሲሰማ “በገላትያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት” ጠንካራ መልእክት ያዘለ ደብዳቤ ጻፈ። (ገላ. 1:2) ከ50-52 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ ቀጥተኛ ምክርና ኃይለኛ ማሳሰቢያ ይዟል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ደብዳቤ ከጻፈ ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ በሮም “የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ” በነበረበት ወቅት፣ በኤፌሶንና በፊልጵስዩስ እንዲሁም በቈላስይስ ለሚገኙ ጉባኤዎች ጠቃሚ ምክርና ፍቅር የተንጸባረቀበት ማበረታቻ የያዘ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። (ኤፌ. 3:1) እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በገላትያ፣ በኤፌሶን፣ በፊልጵስዩስ እንዲሁም በቈላስይስ መጻሕፍት ውስጥ ለሚገኘው መልእክት ትኩረት በመስጠት ጥቅም ማግኘት እንችላለን።—ዕብ. 4:12
‘ጻድቅ ተብሎ መጠራት’ የሚቻለው እንዴት ነው?
የአይሁድን እምነት የሚያስፋፉ ሰዎች የተንኮል ዘዴዎችን ተጠቅመው ጳውሎስ በሌሎች ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዲያጣ ለማድረግ በሞከሩበት ወቅት ጳውሎስ፣ ሐዋርያ መሆኑን ለማረጋገጥ በሕይወቱ ውስጥ የተፈጸሙ አንዳንድ ክንውኖችን መናገር አስፈልጎት ነበር። (ገላ. 1:11 እስከ 2:14) ጳውሎስ፣ እነዚህ ሰዎች ላነሱት የሐሰት ትምህርት የመከላከያ መልስ ሲሰጥ “አንድ ሰው ጻድቅ ተብሎ የሚጠራው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ብቻ እንደሆነ” ተናግሯል።—ገላ. 2:16 NW
ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ‘ከሕግ በታች ያሉትን በመዋጀት’ ነፃ ያወጣቸው ክርስቲያናዊ ነፃነት እንዲያገኙ እንደሆነ ተናግሯል። ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን “ጸንታችሁ ቁሙ፤ ዳግመኛም በባርነት ቀንበር አትጠመዱ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል።—ገላ. 4:4, 5፤ 5:1
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
3:16-18, 28, 29—አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን አሁንም እንደጸና ነው? አዎን። የሕጉ ቃል ኪዳን፣ አምላክ ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚተካ ሳይሆን በዚህ ቃል ኪዳን ላይ የተጨመረ ነበር። በመሆኑም ሕጉ ‘ከተሻረ’ በኋላም የአብርሃም ቃል ኪዳን የጸና ነው። (ኤፌ. 2:15) በዚህ ቃል ኪዳን አማካኝነት አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች፣ የአብርሃም እውነተኛና ዋነኛ ‘ዘር’ ለሆነው ለክርስቶስ ኢየሱስ እንዲሁም ‘የክርስቶስ ለሆኑት’ ተላልፈዋል።
6:2—‘የክርስቶስ ሕግ’ ምንድን ነው? ይህ ሕግ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የሰጣቸውን ትእዛዛት በሙሉ ያካትታል። በተለይ ደግሞ “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚለውን ትእዛዝ ይጨምራል።—ዮሐ. 13:34
6:8—‘መንፈስን ለማስደሰት ብለን የምንዘራው’ እንዴት ነው? ይህንን የምናደርገው የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ በነፃነት እንዲሠራ በሚያስችል መንገድ በመኖር ነው። መንፈስን ለማስደሰት ብሎ መዝራት፣ መንፈስ በእኛ ላይ እንዲሠራ በሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ልብ መካፈልን ይጨምራል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:6-9:- ክርስቲያን ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ችግሮች ሲነሱ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው አሳማኝ ማስረጃዎችን በማቅረብ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማጋለጥ ፈጣን መሆን አለባቸው።
2:20:- ቤዛው አምላክ በግለሰብ ደረጃ የሰጠን ስጦታ ነው። ለቤዛው እንዲህ ያለ አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል።—ዮሐ. 3:16
5:7-9:- ክፉ ባልንጀሮች ‘ለእውነት እንዳንታዘዝ ሊያሰናክሉን’ ይችላሉ። ከእንደዚህ ዓይነት ባልንጀሮች መራቃችን የጥበብ አካሄድ ነው።
6:1, 2, 5:- ‘መንፈሳዊ የሆኑ’ ወንድሞች ከባድ ሸክሞችን፣ ለምሳሌ ሳናውቅ የተሳሳተ እርምጃ በመውሰዳችን ምክንያት ያጋጠሙንን አስቸጋሪ ወይም ከባድ ሁኔታዎች በመሸከም ረገድ ሊረዱን ይችላሉ። ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻችንን መሸከም ያለብን ግን ራሳችን ነን።
‘ሁሉንም ነገሮች በክርስቶስ ሥር መጠቅለል’
ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያናዊ አንድነትን ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።” ክርስቶስ፣ ሁሉም ሰዎች “በማመን . . . ወደሚገኘው አንድነት” እንዲደርሱ ለመርዳት ወንዶችን እንደ “ስጦታ” አድርጎ ሰጥቷል።—ኤፌ. 1:10፤ 4:8, 13
ክርስቲያኖች አምላክን እንዲያከብሩና በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር ‘አዲሱን ሰው መልበስ’ እንዲሁም ‘ለክርስቶስ ካላቸው አክብሮታዊ ፍርሃት የተነሣ አንዳቸው ለአንዳቸው መገዛት’ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም መንፈሳዊውን ሙሉ የጦር ዕቃ በመልበስ “የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም” ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 4:24፤ 5:21፤ 6:11
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:4-7—ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከመወለዳቸው አስቀድሞ የተወሰኑት ወይም የተመረጡት እንዴት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተመረጡት በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በቡድን ደረጃ ነው። ይህም የሆነው ኃጢአተኛ የሆነው የሰው ዘር ዓለም ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት ማለትም የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአትን ለልጆቻቸው ከማስተላለፋቸው በፊት ነበር። በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት የተነገረው ማንኛውም ኃጢአተኛ ሰው ከመጸነሱ በፊት ሲሆን ትንቢቱ የተወሰኑ የክርስቶስ ተከታዮች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ አምላክ ያለውን ዓላማ ያካተተ ነው።—ገላ. 3:16, 29
2:1, 2 የ1954 ትርጉም—የዓለም መንፈስ እንደ አየር የሆነው እንዴት ነው? በዓለም ላይ ሥልጣን ያለውስ በምን መንገድ ነው? ‘የዓለም መንፈስ’ የሚባለው በራስ የመመራትና ያለመታዘዝ መንፈስ ሲሆን ይህ መንፈስ ልክ እንደምንተነፍሰው አየር በሁሉም ቦታ ይገኛል። (1 ቆሮ. 2:12) በዓለም ላይ ሥልጣን እንዳለው ተደርጎ የተገለጸው ኃይለኛና የማያቋርጥ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ነው።
2:6—ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገና በምድር ላይ እያሉ “በሰማያዊ ስፍራ” እንዳሉ ተደርገው የተገለጹት ለምንድን ነው? እዚህ ላይ “በሰማያዊ ስፍራ” የሚለው አገላለጽ ቃል የተገባላቸውን ሰማያዊ ውርሻ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ‘ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም በመታተማቸው’ በአምላክ ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ ማግኘታቸውን የሚያመለክት ነው።—ኤፌ. 1:13, 14
ምን ትምህርት እናገኛለን?
4:8, 11-15:- ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ምርኮ በመማረክ’ ማለትም ወንዶችን ከሰይጣን ቁጥጥር ነጻ በማውጣት የክርስቲያን ጉባኤን ለመገንባት እንደ ስጦታ ተጠቅሞባቸዋል። በመካከላችን ሆነው አመራር ለሚሰጡን በመታዘዝና በመገዛት እንዲሁም ለጉባኤው ከሚያደርጓቸው ዝግጅቶች ጋር በመተባበር ‘በፍቅር በነገር ሁሉ ወደ ክርስቶስ ማደግ’ እንችላለን።—ዕብ. 13:7, 17
5:22-24, 33:- አንዲት ሚስት ለባሏ ከመገዛት በተጨማሪ ልታከብረው ይገባል። ይህንንም የምታደርገው “ገርና ጭምት መንፈስ” በማሳየት ነው። በተጨማሪም ስለ እሱ መልካም በመናገርና የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች እንዲሳኩ ከእሱ ጋር በመተባበር ታከብረዋለች።—1 ጴጥ. 3:3, 4፤ ቲቶ 2:3-5
5:25, 28, 29:- አንድ ባል ራሱን ‘እንደሚመግብ’ ሁሉ የሚስቱን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶችም ለማሟላት መጣር አለበት። በተጨማሪም ከእሷ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ በማሳለፍ እንዲሁም በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ርኅራኄ በማሳየት ሊንከባከባት ይገባል።
6:10-13:- የአጋንንትን ተጽዕኖ ለመቋቋም እንድንችል ከአምላክ ያገኘነውን መንፈሳዊ የጦር ዕቃ ለመልበስ ልባዊ ጥረት ማድረግ ይገባናል።
“በዚያ እንመላለስ”
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ፍቅርን ጎላ አድርጎ ገልጿል። “ፍቅራችሁ በጥልቅ እውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ” በማለት ተናግሯል። ሐዋርያው፣ እነዚህ ክርስቲያኖች ከመጠን በላይ በራስ የመተማመን ዝንባሌ ወጥመድ እንዳይሆንባቸው ለመርዳት ሲል “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” በማለት መክሯቸዋል።—ፊልጵ. 1:9፤ 2:12
ጳውሎስ በመንፈሳዊ ጎልማሳ የሆኑ ክርስቲያኖችን ‘እግዚአብሔር ወደ ላይ ስለ ጠራቸው፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እንዲፈጥኑ’ አበረታቷቸዋል። “በደረስንበት በዚያ እንመላለስ” በማለትም ተናግሯል።—ፊልጵ. 3:14-16
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:23—ጳውሎስ የተጨነቀባቸው ‘ሁለት’ ነገሮች ምንድን ናቸው? ‘ለመሄድ’ ወይም ነፃ ለመለቀቅ የተመኘውስ ከምንድን ነው? ጳውሎስ ከነበረበት ሁኔታ አንጻር በፊቱ ከተቀመጡት ሁለት አማራጮች ይኸውም ከሞት ወይም ከሕይወት አንዱን የመምረጥ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ነበር። (ፊልጵ. 1:21) ከሁለቱ የትኛውን እንደሚመርጥ ባይገልጽም ‘መሄድንና [“ነፃ መለቀቅንና፣” NW] ከክርስቶስ ጋር መሆንን’ እንደሚመኝ ተናግሯል። (ፊልጵ. 3:20, 21፤ 1 ተሰ. 4:16) ክርስቶስ በሚገኝበት ወቅት የሚከናወነው ይህ “ነፃ መለቀቅ” ጳውሎስ፣ ይሖዋ ያዘጋጀለትን ሽልማት እንዲቀበል ያደርገዋል።—ማቴ. 24:3
2:12, 13—አምላክ “መፈለግንና ማድረግን” በእኛ ውስጥ የሚሠራው በምን መንገድ ነው? የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በልባችንና በአእምሯችን በመሥራት በእሱ አገልግሎት የተቻለንን ያህል የማድረግ ፍላጎታችን እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም ‘የራሳችንን መዳን ለመፈጸም’ በምናደርገው ጥረት ያለ እርዳታ አልተተውንም።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
2:5-11:- ኢየሱስ የተወው ምሳሌ እንደሚያሳየው ትሕትና የደካማነት ምልክት ሳይሆን የሥነ ምግባር ጥንካሬን የሚያመለክት ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ ትሑታንን ከፍ ከፍ ያደርጋል።—ምሳሌ 22:4
3:13:- ‘ከኋላ ያሉ’ የተባሉት ነገሮች ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራን፣ ሀብታም ቤተሰብ ስላለን ይሰማን የነበረውን ከስጋት ነፃ የመሆን ስሜት አሊያም ንስሐ የገባንባቸውንና ‘ታጥበን’ የነጻንባቸውን ከዚህ በፊት የሠራናቸውን ከባድ ኃጢአቶችም ጭምር ሊያመለክቱ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 6:11) እነዚህን ነገሮች በመርሳት ማለትም ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰባችንን በማቆም ‘ከፊታችን ያሉትን’ ነገሮች ለማግኘት መዘርጋት ይኖርብናል።
4:14-16:- በፊልጵስዩስ የሚገኙ ክርስቲያኖች በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ደሃ ቢሆኑም ለጋስነት በማሳየት ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል።—2 ቆሮ. 8:1-6
‘በእምነት ጸንቶ መኖር’
ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሐሰተኛ አስተማሪዎችን የተሳሳተ አመለካከት አጋልጧል። መዳናችን የተመካው ሕጉን በመጠበቃችን ሳይሆን ‘በእምነት ጸንተን በመኖራችን’ ላይ ነው። ጳውሎስ የቈላስይስ ክርስቲያኖችን “[በክርስቶስ] ኑሩ፤ በእርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ፣ . . . በእምነት ጸንታችሁ . . . [ኑሩ]” በማለት አበረታቷቸዋል። በዚህ መንገድ መጽናታቸው ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል?—ቈላ. 1:23፤ 2:6, 7
ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት። . . . የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይንገሥ።” አክሎም “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት” ብሏቸዋል። ከጉባኤ ውጭ ካሉት ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክቶ ደግሞ “በጥበብ ተመላለሱ” በማለት ተናግሯል።—ቈላ. 3:14, 15, 23፤ 4:5
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
2:8—ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዲርቋቸው ያስጠነቀቃቸው ‘የዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት’ ምንድን ናቸው? እነዚህ ሕግጋት የሰይጣንን ዓለም ያዋቀሩትና የሚመሩት ወይም የሚያንቀሳቅሱት መሠረታዊ ነገሮች ወይም ደንቦች ናቸው። (1 ዮሐ. 2:16) ከእነዚህም መካከል የዚህ ዓለም ፍልስፍና፣ ፍቅረ ንዋይ እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖቶች ይገኙበታል።
4:16—ለሎዶቅያ ሰዎች የተጻፈው ደብዳቤ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆነው ለምንድን ነው? ይህ ደብዳቤ ለዘመናችን አስፈላጊ የሆኑ ሐሳቦችን ስላልያዘ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆኑት ሌሎች ደብዳቤዎች ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ስለያዘ ሊሆን ይችላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2, 20:- አምላክ በጸጋው ያዘጋጀው ቤዛ፣ ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረን እንዲሁም ውስጣዊ ሰላም እንድናገኝ ያደርገናል።
2:18, 23:- “ዐጕል ትሕትና” የሚያሳይ ማለትም የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ሲል ምናልባትም ቁሳዊ ነገሮችን በመተው ወይም ራሱን በመጨቆን ትሑት የሆነ ለማስመሰል የሚሞክር ሰው “ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል።”